[the_ad_group id=”107″]

ጤናማ ትምህርት – ጤናማ ኑሮ (ክፍል 4)

የጳውሎስ መልእክት ወደ ቲቶ: በቤተክርስቲያን ውስጥ በተለያዩ የዕድሜ ክልል ውስጥ ላሉ ሰዎች የተሰጠ መመሪያ

በተለያዩ ቤተ ክርስቲያናት ከሚሰጡት የአገልግሎት ዐይነቶች መካከል የእሑድ አምልኮ ፕሮግራም፣ የጸሎትና የፈውስ፣ የወጣቶች፣ የሴቶች፣ የልጆች ፕሮግራም፣ ወዘተ… ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ መቼም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተለያዩ የአገልግሎት ዐይነቶች መኖራቸው እጅግ የሚበረታታ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት እነዚህ ፕሮግራሞች የሚካሄዱባቸው ቀናትና ሰዓታት ከመለያየታቸው ውጪ ይዘታቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የወጣቶች ፕሮግራም በይዘቱ ከእሑድ የአምልኮ ፕሮግራም የሚለይበት ነገር የለውም፡፡ ስለ ሴቶች ፕሮግራምም ቢሆን ተመሳሳይ ነገር ማለት ይቻላል፡፡ ከሞላ ጎደል ብዙዎቹ ፕሮግራሞቻችን በመክፈቻ ጸሎት (ርዝመቱና እጥረቱ እንደ ፕሮግራሙ ዐይነትና እንደ መሪው ሊለያይ ይችላል) ጀምረው፣ የዝማሬ ጊዜን (ከብዙዎቹ አገልግሎቶች ሰፊውን ጊዜ የሚወስደው ይሄኛው ክፍል ነው) አስከትለው፣ ወደ “ስብከት” (ይህ ብዙ ጊዜ ከዝማሬ ጊዜ ያነሰ ጊዜ የሚሰጠው አገልግሎት ነው) ይሻገሩና በማጠቃለያ ጸሎት ይጠናቀቃሉ፡፡ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ያስተማረው ጸሎት የመዝጊያ ጸሎት ሆኖ ማገልገሉ እንደ ተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው፡፡ ይህን ቅርጽ አለመጠበቅ ከፍተኛ ተቃውሞ፣ አልፎም ቅጣት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ቅጣት ያስከትላል ስል፣ በአንድ የእሑድ አምልኮ ፕሮግራም የሐዋርያት ጸሎትን እንደ መዝጊያ ጸሎት ባለመጠቀሜ ለተወሰኑ ወራት የእሑድ አምልኮ ፕሮግራም እንዳልመራ መቀጣቴን አስታወስኩ ነው፡፡ ለመሆኑ የፕሮግራሞቻችን ቅርጽና ይዘት በእንዲህ ዐይነት መልኩ (በተለመደው መንገድ) ካልተቃኙ የእግዚአብሔር መንፈስ አይሠራም ያለን ማን ይሆን? የፕሮግራሞቻችን ቀናትና ሰዓታት እንደሚለያዩ ሁሉ ይዘቶቻቸውም ሆነ ቅርጾቻቸው የተለያዩ ሆነው የምናየው መቼ ይሆን? በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አማኞችን በዕድሜ፣ በጾታና በሙያቸው ከፋፍሎ የሚያስፈልጋቸውን ትምህርት የምናስተምርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? በዚህ ጽሑፍ ቲቶ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉትን ሰዎች በዕድሜና በጾታ በመከፋፈል ጤናማ ትምህርት እንዲያስተምር የታዘዘበትን ክፍል እንመለከታለን፡፡

በክፍል ሦስት (ቲቶ 1፥10-16) በቀርጤስ ያሉትን የሐሰት አስተማሪዎችና የሌሎች ሰዎች ባሕርያት ተመልክተናል፡፡ እነዚህ ባሕርያት በቀርጤስ ያለው ሁኔታ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደ ሆነ በማሳየት ቲቶ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ሲመርጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ያስገነዝባሉ፡፡ ቲቶም መሪዎችን ሲመርጥ ያለበትን ዐውድ በማገናዘብ፣ የተሰጡትን መመዘኛዎች በመጠቀም በከፍተኛ ጥንቃቄ ማከናወን ይኖርበታል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ቲቶ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉትን ሰዎች በዕድሜና በጾታ በመከፋፈል ጤናማ ትምህርት እንዲያስተምርም ታዟል፡፡

አንተ ግን ከትክክለኛ ትምህርት ጋር ተስማሚ የሆነውን አስተምር፡፡ አረጋውያን ጭምቶች፣ የተከበሩ፣ ራሳቸውን የሚገዙና በእምነት፣ በፍቅርና በትዕግሥትጤናማነት ያላቸው እንዲሆኑ ምከራቸው፡፡ እንዲሁም አሮጊቶች በአኗኗራቸው የተከበሩ እንዲሆኑ፣ በጎ የሆነውን የሚያስተምሩ እንጂ የሰው ስም የሚያጠፉወይም በወይን ጠጅ ሱስ የተጠመዱ እንዳይሆኑ አስተምራቸው፤ እንዲህ ከሆኑ፣ ወጣት ሴቶች ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን እንዲወዱ ማስተማር ይችላሉ፤የእግዚአብሔር ቃል በማንም ዘንድ እንዳይሰደብ ራሳቸውን የሚገዙና ንጹሓን፣ በቤት ውስጥ በሥራ የተጠመዱ፣ ቸሮች፣ ለባሎቻቸው የሚገዙ እንዲሆኑያስተምሯቸው፡፡ እንዲሁም ወጣት ወንዶች ራሳቸውን እንዲገዙ ምከራቸው፡፡ በማንኛውም ነገር መልካም የሆነውን ነገር በማድረግ ራስህን አርአያ አድርገህአቅርብላቸው፡፡ በምታስተምራቸውም ትምህርት ጭምተኛነትን፣ ቁም ነገረኛነትን፣ የማይነቀፍ ጤናማ አነጋገር አሳይ፤ ይኸውም ተቃዋሚ ስለ እኛ የሚናገረውንመጥፎ ነገር በማጣት እንዲያፍር ነው፡፡ ባሮች ለጌቶቻቸው በማንኛውም ነገር እንዲገዙ፣ ደስ እንዲያሰኟቸው፣ የአጸፋ ቃል እንዳይመልሱላቸው አስተምር፤አይስረቁ፤ ይኸውም በሁሉም መንገድ የአዳኛችን የእግዚአብሔር ትምህርት ይወደድ ዘንድ ፍጹም ታማኝ መሆናቸውን እንዲያስመሰክሩ ነው (ቲቶ 2፥-10)፡፡

ይህ ክፍል ከአንደኛ ጢሞቴዎስ 5፥1-2 ጋር ይመሳሰላል፤ ቁጥር አንድ ሲጀምር “አንተ ግን” ይላል፡፡ ይህም ባለፈው ትምህርት ላይ ቲቶ 2፥1-10ን ከተመለከትነው ከቲቶ 1፥10-16 ጋር ያነጻጽራል፤ በተለይም ከቲቶ 1፥16 ጋር ጠንካራ ተመሳስሎ አለው፡፡ “እግዚአብሔርን እናውቃለን ይላሉ፤ ዳሩ ግንበተግባራቸው ይክዱታል፤ አስጸያፊዎች፣ የማይታዘዙና ለበጎ ሥራ የማይበቁ ናቸው” (1፥16)፤ “አንተ ግን ከትክክለኛ ትምህርት ጋር ተስማሚ የሆነውንአስተምር” (2፥1)፡፡ ቲቶ 1፥10-16 እንደሚያመለክተው የሐሰት መምህራን /ጤናማ ያልሆነ ትምህርት ያስተምራሉ እንዲሁም ፀባያቸው የተበላሸ ነው፡፡ እግዚአብሔርን እንደሚያውቁ በግልጽ ይናገራሉ ዳሩ ግን በተግባራቸው ይክዱታል፤ አስጸያፊዎች፣ የማይታዘዙና ለበጎ ሥራ ሁሉ የማይበቁ ናቸው፡፡ ቲቶ ግን ከትክክለኛ ትምህርት ጋር ተስማሚ የሆነውን ማስተማር ይኖርበታል (2፥1-10)፡፡ ምክንያቱም ትክክለኛ ትምህርት ትክክለኛ ኑሮን ይፈጥራልና፡፡ ከትክክለኛ ትምህርት ጋር የማይስማማ ልዩ ትምህርት የሚያስተምሩ አሉ፡፡ ቲቶ እነዚህን የሚቃወምበት አንዱና ዋንኛው መንገድ ጤናማ ትምህርት በማስተማር ነው፡፡

ከላይ ከተነሣው ነጥብ የምንማረው ቁም ነገር መኖር አለበት፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሕዝባችንን ʻእዚህ ቦታ አትሂዱʼ፣ ʻየእነርሱ አስተምህሮ የተሳሳተ ነውʼ፣ወዘተ.እንላለን፤ ነገር ግን የምንከለክላቸው ቦታ እንዳይሄዱና ልዩ ትምህርትን ለይተው እንዲያውቁ የሚያስችላቸውን ትክክለኛ ትምህርት ስለማስተማራችንእርግጠኞች መሆን አይቻልም፡ በአንጻሩ ግን ከእውነተኛ ትምህርትና ከወንጌል ጋር ተስማሚ የሆነውን ትምህርት የማስተማር ኀላፊነት አለበን፡ በተለይም በዚህዘመን ጤናማ ኑሮ ከሕዝባችን የምንፈልግ ከሆነ ጤናማ ትምህርት ልናስተምራቸው ይገባል፤ ሰው የሚማረውን ይኖራልና፡፡ የምናስተምረው ካልተለወጠ፣ ጤናማካልሆነ የሕዝባችን ኑሮ ጤናማ ይሆናል፣ ይለወጣል ብለን መጠበቅ የለብንም፡፡

ቲቶ ከትክክለኛ ትምህርት ጋር ተስማሚ የሆነውን ማስተማር ያለበት እነማንን ነው? አረጋውያንን (ቁ. 2)፣ አሮጊቶችን (ቁ. 3)፣ አሮጊቶች ጤናማ ኑሮ ካላቸው በበኩላቸው ወጣት ሴቶችን ያስተምራሉ (ቁ. 4-5)፣ ወጣት ወንዶችን (ቁ. 6-8)፣ ራሱን ምሳሌ አድርጎ ማቅረብ ይኖርበታል (ቁ. 7-8) እና ባሮችን (ቁ. 9-10) ነው፡፡ ከቁጥር 9 እና 10 ውጪ ባሉት ቁጥሮች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉት ሰዎች በዕድሜና በጻታ ተከፋፍለው ተቀምጠዋል፡፡ አረጋውያን (ሽማግሌዎች፣ አባቶች)፣ አሮጊቶች (እናቶች)፣ ወጣት ሴቶች (እኅቶች) እና ወጣት ወንዶች (ወንድሞች)፡፡ ቁጥር 9 እና 10 “ባሮች” ይላል፡፡ በእነዚህ ቁጥሮች ሰዎችን በሥራቸው ዐይነት አስቀምጧል፡፡ ሌላው በዚህ ክፍል ውስጥ የምንመለከተው ነገር ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ወጣት ወንዶች ሲያነሣ ቲቶ ራሱን ምሳሌ በማድረግ እንዲያቀርብላቸው ያሳስበዋል (ቁ. 7-8)፡፡ እንዲያስተምር ብቻ ሳይሆን የሚያስተምረውን በመኖር ራሱን ዐርኣያ በማድረግ እንዲያቀርብላቸው ይነግረዋል፡፡

ይህ ክፍል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉትን ሰዎች በዕድሜና በጾታ ከፋፍሎ ጤናማ ትምህርት ማስተማር፣ እንደ ዕድሜያቸውና ጾታቸው የሚያስፈልጋቸውንትክክለኛ ትምህርት ማስተማር እንደሚኖርብን ያስገነዝባል፡፡ ʻበዚህ ቀን የአረጋውያን ፕሮግራም አለʼ ሲባል ሰምቶ የሚያውቅ ይኖር ይሆን? ሰዎች እንደዕድሜያቸው የሚያስፈልጋቸው ትምህርት እየተሰጣቸው ነው? በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉትን ሰዎች በሙያቸው በመከፋፈል የሚያስፈልጋቸውን ማስተማርጤናማ ኅብረተ ሰብን ለመፍጠር ቁልፍ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ ነጋዴዎችን ሰብስበን ለሕንፃ ግንባታ ገንዘብ እንዲሰጡ እንደምንጠይቀው ሕይወታቸውንና ሥራቸውንየሚመለከት ሥልጠና አዘጋጅተን አስተምረናቸው እናውቃለን? ሌላው የምናስተምረውን ትምህርት በመኖር ለሌሎች ዐርኣያ ልንሆን ይገባል፡፡ በማንኛውም ነገርመልካም የሆነውን ነገር በማድረግ ራሳችንን ምሳሌ አድርገን ለሌሎች ማቅረብ ይርብናል፡፡

ቲቶ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉትን ሰዎች በዕድሜና በጾታ ከፋፍሎ ማስተማር ያለበት ምንድን ነው? እነዚህ በዕድሜና በጾታ የተከፋፈሉት ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መመላለስ ያለባቸው እንዴት ነው? አረጋዊያን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዴት መኖር አለባቸው? ቁጥር 2 እንደሚያመለክተው አረጋውያን ጭምቶች፣ የተከበሩ፣ ራሳቸውን የሚገዙና በእምነት፣ በፍቅርና በትዕግሥት ጤናማነት ያላቸው እንዲሆኑ ምከራቸው ይላል፡፡ የተሰጣቸው መመሪያ ለሽማግሌዎችና ለዲያቆናት ምርጫ እንደ መሥፈርት ከተሰጡት መመዘኛዎች ጋር ይመሳሰላል (1 ጢሞ. 3፥2፡ 8)፡፡ ይህ ከአረጋውያን የሚጠበቅ የኑሮ ልክ ነው፡፡ በእምነት፣ በፍቅርና በትዕግሥት ጤናማነት ሊኖራቸው ይገባል (2፥1፤ 1፥13)፡፡ ቁጥር ሁለት በግልጽ እንደሚያሳየው ቲቶ አረጋውያንን እንዲመክራቸው እንጂ በኃይለ ቃል እንዲናገራቸው አልታዘዘም፡፡ ማገልገል መምከር ነው፡፡ ይህ አገልጋይ ለአረጋውያን ሊኖረው የሚገባውን አክብሮት፣ በምን መልኩ ሊያገለግላቸው እንደሚገባ ያመለክታል፡፡ ይህ ምክር ለጢሞቴዎስ ከተሰጠው ምክር ጋር ይመሳሰላል፡- “አረጋዊውን ሰው እንደ አባትህ ቈጥረህ ምከረው እንጂበኀይለ ቃል አትናገረው” ይላል (1 ጢሞ. 5፥1)፡፡

አሮጊቶችስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መመላለስ ያለባቸው እንዴት ነው? ቁጥር ሦስት ይህን ጥያቄ በግልጽ ይመልሳል፤ “እንዲሁም አሮጊቶች በአኗኗራቸውየተከበሩ እንዲሆኑ፣ በጎ የሆነውን የሚያስተምሩ እንጂ የሰው ስም የሚያጠፉ ወይም በወይን ጠጅ ሱስ የተጠመዱ እንዳይሆኑ አስተምራቸው” ይላል፡፡ ይህ እናቶቻችን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዴት መኖር እንዳለባቸው ያመለክታል፡፡ እንዲህ ዐይነት ኑሮ እንዲኖራቸው ደግሞ ልናስተምራቸው ይገባል፡፡ አሮጊቶች የሚጠበቅባቸውን የሕይወት ልክ መኖር ከቻሉ እነርሱ ደግሞ በተራቸው ወጣት ሴቶችን ማስተማር ይችላሉ፡፡ አሮጊቶች ወጣት ሴቶችን ማስተማር ያለባቸው ምንድን ነው? ቁጥር አራትና አምስት ይህን ይመልሳል፤ ”እንዲህ ከሆኑ፣ ወጣት ሴቶች ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን እንዲወዱ ማስተማር ይችላሉ፤ የእግዚአብሔርቃል በማንም ዘንድ እንዳይሰደብ ራሳቸውን የሚገዙና ንጹሓን፣ በቤት ውስጥ በሥራ የተጠመዱ፣ ቸሮች፣ ለባሎቻቸው የሚገዙ እንዲሆኑ ያስተምሯቸው፡፡”በመጀመሪያ፣ አሮጊቶች ይህን ለማስተማር ከእነርሱ እንደሚጠበቀው መኖር ይኖርባቸዋል፡፡ ሁለተኛው፣ አሮጊቶች ወጣት ሴቶችን እንዲያስተምሩ ታዘዋል፡፡ አንዳንዶች ʻሴቶች ማስተማር ይችላሉʼ ለሚለው ሙግታቸው ይህን ክፍል ሲጠቅሱ ሌሎች ግን ʻይህ ክፍል እንደሚያሳየው ማስተማር የሚችሉት ሴቶችን ብቻ ነውʻ ይላሉ፡፡ “ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማስተማር ይችላሉ?” የሚለውን ጥያቄ በዚህ ጽሑፍ ለመመለስ የክፍሉም ዐውድ ሆነ የተሰጠኝ ቦታ አይፈቅድም፡፡ እነዚህ ሁለቱ ቁጥሮች ወጣት ሴቶች ሊኖራቸው የሚገባውን ሕይወት በምን መልኩ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መመላለስ እንደሚገባቸው በግልጽ ያሳያሉ፡፡ ወጣት ሴቶች በእነዚህ ቁጥሮች እንደተብራራው መመላለስ ያለባቸው ለምንድን ነው? ቁጥር አምስት እንደሚናገረው ʻየእግዚአብሔር ቃል በማንም ዘንድ እንዳይሰደብʼነው፡፡ ወጣት ሴቶች እንደ ተጻፈው በመኖር ወንጌል እንዳይነቀፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

እስቲ ጥቂት ራሳችንን እንጠይቅ፤ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ላሉ አባቶችና እናቶች ሥፍራ አለን? እናከብራቸዋለን? በአግባቡስ የሚመለከታቸውንናየሚጠቅማቸውን ነገር እናስተምራቸዋለን? እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን የሰጣቸውን አባቶችና እናቶች በአክብሮት እናገልግላቸው፡፡ ሌላው በቤተ ክርስቲያንውስጥ ያላችሁ አባቶችና እናቶች ሕይወታችሁ ከእነዚህ ቁጥሮች አኳያ ምን ይመስላል? በእርግጥም በእነዚህ ቁጥሮች እንደ ተብራራው እየተመላለሳችሁ ነው? ከእግዚአብሔር ቃል አኳያ ራሳችንን ልንመረምር ይገባል፡፡ እናቶች ለወጣት ሴቶች ዐርኣያ የሚሆን ሕይወት አላችሁ? ልጆቻችሁ፣ ሌሎች ወጣት ሴቶች ከእናንተሕይወት የሚማሩት ነገር አለ? የምናስተምረውን በመኖር ለሌሎች ወጣት ሴቶች ምሳሌ እንሁን፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያላችሁ ወጣት ሴቶች ሕይወታችሁምን ይመስላል? ባሎቻችሁንና ልጆቻችሁን በመውደድ፣ በቤት ውስጥ በሥራ በመጠመድ፣ ለባሎቻችሁ በመገዛት፣ ራሳችሁን በመግዛት፣ ለሌሎች ቸሮችበመሆን፣ ወዘተ… ረገድ ሕይወታችሁ ምን ይመስላል? እግዚአብሔር ከእናንተ የሚፈልገው ኑሮ በዚህ ክፍል በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ከእነዚህ ነጥቦች አኳያራሳችንን ልንመረምር ይገባል፡፡ በኑሮ የእግዚአብሔር ቃል በማንም እንዳይነቀፍ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ወጣት ሴቶች እንደ ተጻፈው መኖር ያለባቸውየእግዚአብሔር ቃል በማንም እንዳይነቀፍ ነው፡፡ በኑሮአችን ለወንጌል እንቅፋት ልንሆን አይገባም፤ ይልቅስ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲወደድ ልናደርግ ይገባናል፡፡

ወጣት ወንዶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መመላለስ ያለባቸው እንዴት ነው? ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ወጣት ሴቶች ከተናገረ በኋላ በቁጥር ስድስት ላይ “እንዲሁምወጣት ወንዶች ራሳቸውን እንዲገዙ ምከራቸው ይላል፡፡ “እንዲሁም” የሚለውን ቃል ለሁለተኛ ጊዜ መጠቀሙ ነው (ቁ. 3 ይመልከቱ)፡፡ ስለ አረጋውያን ተናግሮ “እንዲሁም አሮጊቶች” ብሎ ነበር፤ አሁን ደግሞ ስለ ወጣት ሴቶች ተናግሮ ”እንዲሁም ወጣት ወንዶች” ይላል፡፡ ለወጣት ወንዶች የሰጠው ትእዛዝ በአጭሩ “ራሳችሁን ግዙ” የሚል ነው፡፡ ይህ አጭር ቢመስልም ሌሎቹን ትእዛዛት ሁሉ ሊጠቀልል የሚችል ወሳኝ መመሪያ ነው፡፡ ወጣት ወንዶች ራሳቸውን በመግዛት ሊኖሩ ይገባቸዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለወጣት ወንዶች ከሰጠው መመሪያ ጋር በማያያዝ ቲቶ ምን ማድረግ እንዳለበት ይናገራል (ቁ. 7-8)፡፡ ቲቶ ለሚያስተምራቸው ወጣት ወንዶች (ለሁሉም) በሁሉ መልካም የሆነውን ነገር በማድረግ፣ በሚያስተምረው ትምህርት ጭምተኝነትንና ቁም ነገረኝነትን በማሳየት፣ የማይነቀፍ ጤናማ አነጋገር በማሳየት ምሳሌ ሊሆንላቸው ይገባል፡፡ ይህ የጳውሎስ የታወቀና ቁልፍ ትምህርት ነው (1 ጢሞ. 4፥12 በተጨማሪ 1 ተሰ. 1፥7፤ 2 ተሰ. 3፥9፤ ፊሊ. 3፥17)፡፡ እናም ይህ በምዕራፍ 1፥16 ላይ ከተጠቀሰው የሐሰት አስተማሪዎች ተግባር ጋር ይቃረናል፡፡ ቲቶ ይህን ማድረግ ያለበት ለምንድን ነው? ቁጥር ስምንት እንደሚያመለክተው “ተቃዋሚ ስለ እኛ የሚናገረውን መጥፎ ነገር በማጣት እንዲያፍር ነው”፡፡ በመኖር/በሕይወት ሌሎች ስለ “እኛ” (ቅዱስ ጳውሎስንና ሌሎች አማኞችን ሁሉ የሚያካትት ነው) የሚናገሩትን ነገር አጥተው እንዲያፍሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በማስተማር ብቻ ሌሎች የሚሉትን ማሳጣትና ማሳፈር አይቻልም፡፡ የምናስተምረውን በመኖር ግን በእኛ ላይ የሚናገሩትን እንዲያጡ ማድረግ ይቻላል፡፡

ወጣት ወንዶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስንኖር ራሳችንን በመግዛት ነው? በተለይም በዚህ ዘመን ራሳችንን በመግዛት ልንኖር ይገባል፡፡ እንደ አገልጋዮችለምናስተምረው ሕዝብ ምሳሌ የሆነ ሕይወት አለን?

ከላይ በዕድሜና በፆታ ከፋፍሎ ቲቶ ምን ማስተማር እንዳለበትና ራሱን በምን መልኩ ለሌሎች ምሳሌ አድርጎ ማቅረብ እንዳለበት ካሳየ በኋላ በቁጥር ዘጠኝና ዐሥር ለየት ባለ መልኩ ስለ ባሮች ወደ መናገር ይሸጋገራል፡፡ ይህን ክፍል ስናስብ ልብ ማለት የሚገባን ነገር ቢኖር እግዚአብሔር በዘመኑ የነበረውን የኅብረተ ሰብ መዋቅር ተጠቅሞ ሓሳቡን አስተላለፈ እንጂ እርሱ የጌታና ባሪያ ሥርዐት ደጋፊ አለመሆኑን ነው፡፡ ቲቶ ባሮችን ማስተማር ያለበት ምንድን ነው? ለጌቶቻቸው በማንኛውም ነገር እንዲገዙ፣ ደስ እንዲያሰኟቸው፣ የአጸፋ ቃል እንዳይመልሱላቸው እና እንዳይሰርቋቸው ነው፡፡ ቲቶ ይህን ማስተማር ያለበት ለምንድን ነው? “ይኸውም በሁሉም መንገድ የአዳኛችን የእግዚአብሔር ትምህርት ይወደድ ዘንድ ፍጹም ታማኝ መሆናቸውን እንዲያስመሰክሩ ነው፡፡” በታማኝነታቸው የእግዚአብሔር ትምህርት/ወንጌል እንዲወደድ እንዲያደርጉ ነው፡፡ ይህ ከአንደኛ ጢሞቴዎስ 6፥1-2 ጋር ይመሳሰላል፤ አጨራረሱም ከቁጥር 4-5 እና ከአንደኛ ጢሞቴዎስ 6፥1-2 ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ በእርግጥ ጌቶቻቸው አማኞች መሆን አለመሆናቸውን በእርግጠኝነት ለመናገር ያስቸግራል፡፡ ይሁን እንጂ “በማንኛውምነገር” የሚለውን፣ ቁጥር 4-5 እና 1ጢሞቴዎስ 6፥1-2 በማስተያየት አንዳንዶች “አማኞች ጌቶች የነበራቸውን ባሮች ያሳያል” ይላሉ፡፡ በተጨማሪ ቁጥር ዐሥር ላይ “እንዲያስመሰክሩ” የሚለው አማኞች አሠሪዎች የነበራቸውን ሠራተኞች ሊያሳይ ይችላል፡፡

ቲቶ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉትን ሰዎች በዕድሜ፣ በጾታና በሥራቸው ዐይነት ከፋፍሎ ማስተማር ያለበት ለምንድን ነው? ምናልባት የሚከተሉትን ሦስት ቁጥሮች መሠረት በማድረግ አማኞች በኑሮአቸው በውጪ ያሉትን ሰዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንዲስቡ መሆኑን መናገር ይቻላል፡፡ እነዚህ ሦስቱ ቁጥሮች፣ “የእግዚአብሔር ቃል በማንም እንዳይሰደብ” (ቁ. 5)፣ 1ተቃዋሚ ስለ እኛ የሚናገረውን መጥፎ ነገር በማጣት እንዲያፍር” (ቁ. 8) እና “በሁሉምመንገድ የአዳኛችን የእግዚአብሔር ትምህርት ይወደድ ዘንድ” (ቁ. 10) ይላሉ፡፡

Endasahaw Negash

ፖሊካርፕ ያኔ፣ ፖሊካርፕ ዛሬ

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ የምሥራቅም የኦሪየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት፣ እንዲሁም የአንግሊካን እና የሉተራን አብያተ ክርስቲያናት በአንድ ድምጽ ”ቅዱስ” ሲሉ የሰየሙት ሰው ነው− ቅዱስ ፖሊካርፕ።

ተጨማሪ ያንብቡ

መሄድህን ቀጥል

ይህ የቴዎድሮስ ሲሳይ ጽሑፍ፣ “ዘወትር ሳትታክት መሄድህ፣ የምትጠብቀውን ለማግኘትህ ምስክር ላይሆን ይችላል፤ በአንጻሩ፣ የሚበልጠውን ስለ መፈለግህ እና ስለ መናፈቅህ ምኞትህን ያመለክታል። ይህም በሰማይ ዋጋ አለው።” ይላል፤ ወደ ቅዱሳን ኅብረት፣ ወደ እግዚአብሔር ጕባዔ መሄድ ለደከማቸው የምክር ቃል ባካፈለበት መልእክቱ።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.