[the_ad_group id=”107″]

የቤተ ክርስቲያን የማንነትና የወንጌል ተልእኮ ተሐድሶ

የእግዚአብሔር ተልእኮ

የወንጌል መልእክት የሚመነጨው ከእግዚአብሔር ተልእኮ ነው። “የእግዚአብሔር ተልእኮ” ስንል የሚታየውና የማይታየው ፍጥረት ሁሉ መገኛ የሆነው የልዑል እግዚአብሔር የፈጣሪነት፣ የአዳኝነትና የፍጥረት አዳሽነት የራስ ግላጫ (self-disclosure) ማለታችን ነው። እርሱ ለህልውናው ሰበብ የለሽና ዘላለማዊ ነው። ልዑል እግዚአብሔር ከፍጥረት፣ ከሕዝብና ከታሪክ በላይ ሆኖ ሁሉን ይገዛል። በሉዓላዊ አደራረጉ በጊዜና በቦታ ራሱን ገልጧል። በዚህ መለኰታዊ ራስን የመግለጥ ሂደት ውስጥ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምትክ ወይም እኩያ በሌለው ፍጹም ወሳኝነት ራስና መደምደሚያ ነው። ሕግ በሙሴ በኩል ተሰጥቶ ነበር፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መጣ። ከቶውንም እግዚአብሔርን ያየ ማንም የለም፤ ነገር ግን በአብ እቅፍ ያለው አንድያ ልጁ የሆነው አምላክ እርሱ ገለጠው። (ዮሐ. 1፥17-18)[1]

“የቤተ ክርስቲያን ጥሪ፣ ማንነትና የወንጌል ተልእኮ[2] የሚመነጨው ከዚሁ የማይሻር፣ የማይሸራረፍ፤ የማይቀየጥ የእግዚአብሔር ተልእኮ[3] ውስጥ ነው። የተልእኮ ባለቤት እግዚአብሔር ብቻ ነው። በእግዚአብሔር የተልእኮ እንቅስቃሴ ውስጥ፣ የመጨረሻ የራስ ግላጨ የሆነው ክርስቶስ፣ ማንነቱና ሥራው ፍጹምና የታሪክ ሁሉ ማሰሪያ ነው። እርሱ ከሁሉ በፊት ነው፤ ሁሉም ነገር በአንድ ላይ ተያይዞ የጸናው በእርሱ ነው (ቈላ1፥17)። የእግዚአብሔር ተልእኮ፣ በዘመን ፍጻሜ ይሆን ዘንድ ያለው ሐሳቡ በሰማይም በምድርም ያሉትን ነገሮች ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሥር ለመጠቅለል ነው (ኤፌ. 1፥10)። ከዚህ ዘላለማዊ እውነት ውጭ ቤተ ክርቲያን የራሷ የሆነ ማንነትና ተልእኮ የላትም። በየትኛው ትውልድ መካከል ያለች ቅድስት የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የራስ ግንዛቤ፣ ዐላማ፣ መልክት፣ ተአማኒነትና ቅቡልነት የሚመዘነው በዚህ እግዚአብሔር በልጁ በክርስቶስ ውስጥ በገለጠው ተልእኮ ነው።[4]

የቤተ ክርስቲያን የተልእኮ ዐውድ እንዳለችበት ዘመን ተለዋዋጭ ነው፤ ማንነቷና የወንጌል መልእክቷ ግን አይቀየሩም። ይህ ትልቅ  እንድምታ አለው። የቤተ ክርቲስቲያን ተልእኮና በትውልድ መካከል ያላት እንቅስቃሴ በሙሉ በየጊዜው ፍተሻና ቅኝት ያስፈልገዋል ማለት ነው። የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ዐውዳዊ ነው ስንል፣ ትውልዱ ባለበት ዐውድ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝና ጌታ አድርጐ ማቅረብ ማለት ነው። የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ክፍትና ገደብ የለሽ የቤተ ክርስቲያን እንቅስቅሴ ሁሉ ማለት አይደለም። የቤተ ክርስቲያን መልእክት ዋልታና ማገር (መሠረትና ውቅር) ክርስቶስና ሥራው ነው። ይህ በዐጭሩ ወንጌል ማለት ነው። የሰው አካል ያለ ልብ እንደማይኖር ሁሉ፣ የቤተ ክርስቲያንም ማንነት ያለ ወንጌል ምውት ነው። ዴቪድ ቦሽ እንደሚለው፣ “ቤተ ክርስትያን፣ ከክርስቶስና የመጀመሪያ ደቀ መዛሙርት ወንጌልና አገልግሎት በሚገጠም ታማኝነት፣ ለራስ ዐውድ አግባብነት ባለው መልኩ ትውልዷን ልታገለግል ተጠርታለች።”[5]

ማንኛውም ክርስቲያናዊ ትውልድ ከእርሱ ቀደም ሲሉ ወይም ከተከታይ ትውልዶች ጋር የዐውድ መጋጠሚያና መለያያ ቢኖረውም፣ የወንጌል መልእክት ግን ቋሚና የማይበጠስ አያያዥ ሰንሰለት ነው። ሁሉም ትውልድ ለወንጌል ታማኝ እንዲሆን ተጠርቷል። በአብዮተኝነት መንፈስ የቀደመውን ትውልድ ተልእኳዊ የራስ ግንዛቤና እንቅስቃሴ አናፈርስም፤ በዚያኑ ልክ ለራሳችን ዐውድ አግባብነት ያለውን ለወንጌል ታማኝ የሆነ መንገድ ለመከተል ደግሞ ነጻነት ያስፈልጋል።[6] በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፈልን ወንጌል በገቢርና በቃል ይገለጣል። በዚህ አንጻር ክርስቲያናዊ ነገር መለኰት፣ አረዳድና ሥነ ዐፈታት ሥር ነቀል በሆነ መልኩ ከተልእኮ የተወለደ ነው። ቤተ ክርስቲያን ዓለምን በወንጌል ለመድረስ በምታደርገው ተልእኳዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በሚነሡ ጕዳዮች፣ ነገር መለኰትም የማይነጠል ተጓዥ ነው። የቤተ ክርስቲያን ተልእኳዊ የራስ ግንዛቤ በራሱ ነገር መለኰታዊ ነው። የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ተልእኮ እምብርት ወንጌል ነው። የወንጌል ተልእኮ በጤናማ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የነገር መለኰት ዕውቀት የተጠበቀ ሊሆን ይገባዋል። ስሑት ነገረ መለኰት፣ ስሑት ወንጌል ይወልዳል፤ ስሑት ወንጌል፣ ስሑት ተልእኮ ይወልዳል። በዚህ ረገድ ተልእኮ፣ ወንጌልና ነገር መለኰት በማይለያዩ መልኩ ተንሰላስለዋል።

የተልእኮ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት

መጽሐፍ ቅዱስ ከዘፍጥረት እስከ ዮሐንስ ራእይ ድረስ፣ በአጠቃለይ ተልእኳዊ መጽሐፍ ሆኖ ነው ያለው። በዐጭሩ የቅዱሳት መጻሕፍትን ትረጕም ከዚህ ውጭ ልንረዳ አንችልም። ከዘፍጥረት እስከ ዮሐንስ ራእይ ድረስ የምንመለከተው የሚከተሉት ሦስት አእማድ እውነቶች ነው።

 1.  የእግዚአብሔር በፈጣሪነት የራስ ግላጭ
 2.  የእግዚአብሔር አዳኝነት
 3.  የእግዚአብሔር የፍጥረት አዳሽነት

የእግዚአብሔር በፈጣሪነት የራስ ግላጭ ትልቅ ተልእኳዊ እንድምታዎች አሉት። “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ(ዘፍ. 1፥1እግዚአብሔር ዘላለማዊ ነው! ይህ ዘላለማዊ አምላክ፣ የሥነ ፍጠረት መገኛ ነው። ሰውን ጨምሮ የመንፈሳዊ፣ በዐይን የሚታየውና የማይታየው ገሃዱ ዓለም መገኛ እርሱ ራሱ እግዚአብሔር ነው። የሚልቀው፣ አቻ የሆነው ወይም የሚያንሰው አምላክ የለውም። በእርሱና በፍጥረት መካከል ትልቅ የማንነትና የባሕርይ (categorical) ልዩነት አለ። ሥነ ፍጥረት፣ ሰውን ጨምሮ፣ የእርሱ ተቀጥያ አይደለም። ሥነ ፍጥረት ሁሉ ተደግፎ የተያዘው በእርሱ ሉዓላዊነት ነው። የሥነ ፍጥረት ዋጋ፣ ትርጕምና ዐላማ ምንጩ እራሱ እግዚአብሔር ነው።

እግዚአብሔር ሰውን ፈጠረ፤ስለዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጐ ፈጠራቸው። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም)ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም፤ የባሕርን ዓሦች፣ የሰማይን ወፎች፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ግዟቸውብሎ ባረካቸው።(ዘፍ 1፥27-28)።

ከዚህ እውነት የሚመነጩ ዘጠኝ ጊዜ የማይሽራቸው ተልእኳዊ ፋይዳዎች አሉ፦         

1) የእግዚአብሔርን ፈጣሪነት፦ የፈጣሪና የተፈጣሪ ኑባሬአዊና የዐይነት ልዮነት (ontological and categorical difference)

2) ሰው በእግዚአብሔር፣ ለእግዚአብሔር ክብር የተፈጠረው ነው፤ ስለዚህ የሰው ባለቤት ራሱ ልዑል እግዚአብሔር ነው።

3) እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው በራሱ አምሳያ ነው፤ ስለዚህ የሰው ኑባሬአዊ ዋጋ (ontological value)፣ የሕይወት ክቡርነት (dignity) ወይም ንጽሐ ሕይወት (sanctity) በእግዚአብሔር አምሳያ መፈጠሩ ነው።

4) “ወንድና ሴት አድርጐ ፈጠራቸው”፦ ወንድ እና ሴት እኩል ናቸው፤ አንድ ዐይነት ግን አይደሉም። በኑባሬ እኩል፣ በተፈጥሮ ተደጋጋፊ የድርሻ ልዩነት አላቸው።

5) የማኅበረ ሰብ መሠረት ቤተ ሰብ ነው፤ የቤተ ሰብ መሠረት “የወንድ እና የሴት” እኩልነት፣ ጾታዊና የድርሻ ልዩነት ነው። በዐጭሩ፣ ወንድ ባልና አባት ሲሆን፣ ሴት ሚስትና እናት ናት።

6) ሰው ከነጻ ፈቃድ ጋር ነው የተፈጠረው፤ ከዚህ አንጻር ከእግዚአብሔር ጋር፣ እርስ በእርስ እንዲሁም ከፍጥረት ጋር ባለው መስተጋብር በእግዚአብሔር ዘንድ ተጠያቂ የሆነ ሞራላዊ ፍጡር (moral being) ነው።

7) ሰው የፍጥረት ባለቤት ሳይሆን፣ የእግዚአብሔር ፍጥረት እንደ ራሴ በመሆን ጠባቂ ነው።

8) ሰው ሁሉ የፍጥረት በረከት እኩል ተካፋይ ነው።

9) ፍጥረት ግንኙነታዊ ነው። ሰው የተፈጠረው ከእግዚአብሔር ጋር፣ እርስ በእርስ እንዲሁም ከተፈጥሮ ጋር በኅብረት፣ በስምረት፣ በፍቅርና በሰላም ለእግዚአብሔር ክብር እንዲኖር ነው።

እነዚህ ፋይዳዎች፣ በተለይም ስለ እግዚአብሔር፣ ስለ ሰውና ስለ ፍጥረት ማንነት፣ እንዲሁም በመካከላቸውም ሊኖረው የሚገባውን ግንኙነት አስመልክቶ ተልእኳዊ እንድምታ አላቸው። ሰው የእግዚአብሔር አምሳያ ነው። በዚሁ ዘመን በማይሽረው ኑባሬአዊ እውነት መሠረት፣ የሰው የክቡርነት ዋጋ በማኅበራዊ፣ ጐሣዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሥሪት በፈጠረው እሴት በፍጹም ሊለካ አይችልም። ማንንም ሰው ከትውልድ አገሩ፣ ከቈዳው ቀለም፣ ከብሔሩና ከጐሣው፣ ከቋንቋውና ከባሕሉ የተነሣ አናሳና ገሚሰ ሰው አድርጐ መቊጠር፣ ማግለል፣ መበደል፣ ፍትሕ መንፈግና ከምድር በረከት ማጕደል፣ ከእግዚአብሔር ፈጣሪነት ጋር ቀጥታ ግጭት ነው። ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ለማድረግ፣ እርሱን ለማምለክና ለማክበር መፈጠሩ፣ እንዲሁም የሰው ሁሉ የፍጥረት በረከት ባለዐደራነትና እኩል ተካፋይነት  መሠረቱ፣ የእግዚአብሔር ብቸኛ የፈጣሪነት የራስ ግላጫ ነው።

ኀጢአት ትልቁ ነውጥ፤ የሰው ልጅ ዋነኛ ግለ ሰባዊና ማኀበራዊ ችግር

በዚህ የእግዚአብሔር የፈጣሪነት የራስ ግላጭ ውስጥ፣ የሰው ልጅ በኀጢአት መውደቁ ትልቁ ነውጥ፣ ትልቁ ችግር፣ የግንኙነት ስብራትና ዐመፅ ነው። ኀጢአት፣ በትምህርትና በምክር የሚስተካከል አነስተኛ የሞራል ውድቀት አይደለም። የሰው ልጅም ኑባሬአዊ፣ ሥር ነቀልና ዋነኛ፣ ግለ ሰባዊም ሆነ የማኅበራዊ ችግር ሥሩ አለመታዘዝና ዐመፅ የወለደው ኀጢአት ነው። በኦሪት ዘፍጥረት ላይ እንደምናየው፣እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ (1÷31)። ይህን እጅግ መልካምነት፣ ሰላም፣ እረፍት እንዲሁም በሁሉ ረገድ እግዚአብሔር በመግቦቱ ለፍጥረት ሁሉ የሰጠውን ምሉዕነትና ስምረት ያበላሸው ኀጢአት ነው። አዳምና ሔዋን፣ እግዚአብሔርን ተጠራጠሩ። የእግዚአብሔር የእጁ ሥራ ሆነው ሳሉ ምሉክና “እንደ እግዚአብሔር ለመሆን” በመፈለግ ከንቱ ምኞትና ባለመታዝዝ በደሉ።

ኀጢአት በእግዚአብሔር ላይ ቀጥታ የተሰነዘረ ዐመፅ ነው። በኀጢአት ምክንያት፣ የእግዚአብሔር ክብር ጐደላቸው፤ ፍጥረት ረከሰ፤ ተርገመም። ዘፍጥረት ሦስት የዓለማችን ትልቁ ችግር ነው። በኀጢአት ምክንያት፣ በዘፍጥረት ምእራፍ አንድና ሁለት የነበረው የፍጥረት ስምረት፣ እግዚአብሔር ብቻ ካልሆነ በስተቀር ማንም ሊያስታካክለው በማይችል ሁኔታ ተናውጧል (cosmic distrurbance)። የእግዚአብሔር ተልእኮ ማለት፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ያለውን ታሪክ፣ ኀጢአት ያመጣቸውን ፍጥረት ስብራቶችን የመፈወስ ያደረገውን ተልእኳዊ እንቅስቃሴ ማለት ነው። በዐጭሩ፣ እርሱ እንዲያው በጸጋው፣ በምሕረቱና በቸርነቱ የማደሱ የትድግና ሥራ ታሪክ ነው። ለቤተ ክርስቲያንም የተሰጣት ብቸኛ ተልእኮ ይህንኑ የእግዚአብሔርን ተልእኮ በቃልና በገቢ መኖርና ማወጅ ነው።

ኀጢአት አራት የግንኙነት ስብራቶችና ቀውሶች አምጥቷል፤

 1.  በእግዚአብሔርና በሰው
 2.  ሰው ከራሱ ጋር፤ የሰው ልጅ ዋነኛ ችግር ሥሩ በኀጢአት የተለወሰ ልብ ነው!
 3.  በሰውና በሰው (አስተሳሰብን፣ ማኅበራዊ፣ ባሥላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የግንኙነት መዋቅሮችን አቃውሷል)
 4.  በሰውና በተፈጥሮ

ኀጢአት የእግዚአብሔርን ክብር ከሰው ላይ ግፍፏል። ሰው በእግዚአብሔር ቁጣና የሞት ፍርድ ሥር ነው! (ሮሜ 3፥23፤ 5፥12፤ ኤፌ. 2፥1) የሰው ልጅ ቀዳሚ ችግር ከፈጣሪው እግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት መሰበር ነው። በተሰነጣጠቀ መስታወት ውስጥ የሚታይ ምስለ ጥፉ (disfigured) እንደሚሆን ሁሉ፣ አምሳለ እግዚአብሔር (Imago Dei) የሆነው ሰውም ጥፉ ሆኗል። ኀጢአት ሰውን ከእግዚአብሔር፣ ሰውን ከራሱ ጋር፣ ሰውን ከሰው ጋር፣ ሰውን ከፍጥረት ጋር አጋጭቶ ለያይቷል፤ በእርሱ ፍርድ ሥር አስቀምጦታል (ሮሜ 6፥11፣ 23፤ ኤፌ 2፥1)። ከውደቀት በኋላ፣ እግዚአብሔር አዳምን የት ነህ?” ብሎ ሲጠይቀው “የቦታ ወይም የአድራሻ ጥያቄ አልነበረም”። ይልቁንም፣ በኀጢአት ምክንያት በእግዚአብሔር ዘንድ የነበረውን ክብር ማጣቱንና ራሱን ያገኘበትን የውርደት ቦታ እንዲያስብ ነው።

ስለዚህ የሰውን ልጅ መሠረታዊ ችግር ኀጢአት መሆኑንን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚክድ፣ የሚያሳንስ ወይም የሚሸፍን ሌላ ማንኛውም ምርመራ (diagnosis) ሐሰት ነው። ከዚህ ነባራዊ እውነት ውጭ፣ ለሰው ልጅ “በችግርነትም”፣ በመፍትሔነትም” የሚቀርብለት ማንኛውም ትንታኔና መፍትሔ የሐሰት ድነት (false redemption) ነው። ሰው ራሱን ማዳን በማይችልበት ሁኔታ “ውዱቅ (fallen)” ሆኗል። የፍጥረትም ስምረት ተቃውሷል። የእግዚአብሔር ተልእኮ፣ ራሱን በአዳኝነትና በፍጥረት አዳሽነት መግለጡ ዋናውና ብቸኛ ምክንያት ሰውን ከኀጢአትና የጦሱ እስራት ለመዋጀት ነው። ከዘፍጥረት ሦስት እስከ ራእይ የምንመለከተው ይህንኑ የእግዚአብሔር የተልእኮ እንቅስቃሴ ነው። በድነት ታሪክ ውቅር ውስጥ፣ ሰው በኀጢአት ምክንያት ለገባበት ቀውስ በመፍትሔነት እግዚአብሔር ራሱን ገልጧል። አምላክ ሥጋ ኾነ! ነገር ግን የተወሰነው ዘመን በደረሰ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን፣ ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ (ገላትያ 4፥4)። የአዳምና የሔዋን ራቁትነት የተሸፈነበት ቆዳ የተገኘው እግዚአብሔር በአዘጋጀው የንጹሕ እንስሳ መሥዋዕት ነበር። ልክ እንዲሁ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደም የሰው ነውር ለአንዴና ለዘላለም ተሽፈነ!

በቅዱሳት መጻሕፍት የድነት ታሪክ ውቅር ውስጥ የምንመለከተው፣ ኪዳናዊ በሆነ ትሥሥር ከአብርሃም መጠራት (ዘፍ. 12) ጀምሮ፣ በክርስቶስ የቤዝዎት ሥራ የተፈጸመውን ሰውን ከኀጢአትና ጦሱ የመዋጀት የእግዚአብሔር ተልእኮ ነው። ይህንኑ የድነት ታሪክ ጅማሬና ፍጻሜ በዘፍጥረትና በዮሐንስ ራእይ ንጽጽሮች እናስተውላለን።

መጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ። (ዘፍ. 1፥1)                 አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ (21፥1)

ከዘፍጥረት እስከ ራእይ በምንመለከተው የእግዚአብሔር ተልእኮ፣ ኀጢአት የፈጠረውን ስብራት ማደስ ነው። ብሉይ ኪዳን በእግዚአብሔር ተልእኮ ውስጥ ራስና መደምደሚያ የሆነውን ክርስቶስን ተስፋ በማድረግ ይጠናቀቃል። አዲስ ኪዳን ደግም ወደ ኋላ በመመልከት ለብሉይ ኪዳን የተስፋ ጥላ አካል በመሆን፣ በክርስቶስ ዳግም መገለጥ የፍጥረትን ሙሉ መታደስ ተስፋ በማድረግ ይጠናቀቃል። የዚህ የድነት ታሪክ ጀማሪና ፈጻሚ ራሱ እግዚአሔር ነው።

እስራኤል ማንነቷን፣ ከእግዚአብሔር ተልእኮ ውጭ ልትረዳ አትችልም

አዳምና ሔዋን በኀጢአት ምክንያት ሲወድቁ፣ እግዚአብሔር የሰጠው ተስፋ፣ በአንተና በሴቲቱ፣ በዘርህና በዘሯ መካከል፣ ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ” (ዘፍ. 315) በክርስቶስ ፍጻሜ አግኝቷል። በክርስቶስ ሞትና ትንሣዔ ፍጻሜ በተገኘው ቤዛዊ ሥራ ውስጥ፣ የመሲሑ ዘር ተሸካሚ የሚሆን ሕዝብ ለማዘጋጀት፣ እግዚአብሔር በመጀመሪያ የጠራው አብርሃምን ነው።ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ፤ ደግሞም እባርክሃለሁ፤ ስምህን ገናና አደርገዋለሁ፤ ለሌሎች በረከት ትሆናለህ። የሚባርኩህን እባርካለሁ፤ የሚረግሙህን እረግማለሁ፤ በምድር የሚኖሩ ሕዝቦች፣ በአንተ አማካይነት ይባረካሉ።(ዘፍ. 12፥1-3)። ሙሴን ነጻ አውጭ አድርጐ ሕዝቡን ከግብፅ የባርነት ኑሮ ዐርነት የማውጣቱ ዐቢይ ዐላማ፣ ለዚሁ የድነት የተልእኮ ሥራ እንደ ነበረ እግዚአብሔር በአጽንዖት አስገንዝቧል፦

 •  እግዚአብሔርን እንዲያመልክና እንዲያገለግል፣ ያመልከኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ (ዘጸ 9፥1)
 •  ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት እንዲያደርግ፣ በግብፃውያን ያደረግሁትን፥ በንስርም ክንፍ እንደ ተሸከምኋችሁ፥ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል።(ዘጸ 19፥4)
 •  ለእግዚአብሔር ለራሱ የተለየ ሕዝብ እንዲሆን፣ “እናንተም የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ” (ዘጸ 19፥6)
 •  ግብፃውያንን እንዲሁም ተስፋይቱን ምድር በወረሱ ጊዜ በዙሪያቸው እንዳሉት ሊሆኑ አይገባም፤ ለእግዚአብሔር ተለይተዋልና! በኖራችሁበት በግብፅ እነርሱ እንደሚያደርጉት አታድርጉ፤ እኔ በማስገባችሁ በከነዓን እንደሚያደርጉትም አታድርጉ፤ ልማዳቸውንም አትከተሉ።(ዘሌ. 18፥1-3)

እግዚአብሔርም ቅሶአቸውን ድምፅ ሰማ፥ እግዚአብሔርም ከአብርሃንምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን አሰበ(ዘጸ 2፥24)። ስለዚህ የመታሰባቸውና ከፍትሕ የለሽ፣ ጨቋኛና ጨካኝ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘረኛ አገዛዝ አርነት የማግኘታቸው ዋነኛ ምክንያት፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ በመሆን በጨለማ ላለው ሕዝብ ብርሃን ለመሆን ነው። ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው በፊት በሲና ተራራ ላይም የተሰጣቸው ዐሥርቱ ትእዛዛት፣ አርነታቸው፣ ማንነታችውና (identity) ተልእኳቸውን (mission) የማይነጣጠሉ መሆኑንን በአጽናዖት ለማሳወቅ ነበር። እንደ ዳግማዊ ዘጸአት በሚታሰበው፣ የሰባ ዓመት ግዞት አርነት የማግኘታችውም ምክንያት በተመሰሳይ መልኩ ተደግሟል። የአብረሃምን ኪዳን በማሰብ፣ ከነዓን መግባት ሉዓላዊ መንግሥት መሆን፣ በበደል ምክንያት ለሁለት መከፈል (ሰሜንና ደቡብ)፣ መሰደድ፣ እንደገና መመለስና መታደስ ዋናው ምክንያት  የመሲሑ ወንጌል ተሸካሚ በመሆን ለዓለም ብርሃን እንዲሆኑ ነበር።[7] እስራኤል ማንነቷን፣ ከእግዚአብሔር ተልእኮ ውጭ ልትረዳ አትችልም።[8]

ከዚያም ሙሴ ወደ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወጣ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ከተራራው ጠራውና እንዲህ አለው፤ለያዕቆብ ቤት የምትለው ለእስራኤልም ሕዝብ የምትናገረው ይህ ነው፤በግብፅ ላይ ያደረግሁትን፣ በንስርም ክንፍ ተሸክሜ ወደ ራሴ እንዴት እንዳመጣኋችሁ እናንተ ራሳችሁ አይታችኋል። አሁንም በፍጹም ብትታዘዙኝና ቃል ኪዳኔን ብትጠብቁ እነሆ ከአሕዛብ ሁሉ እናንተ የተወደደ ርስቴ ትሆናላችሁ፤ ምንም እንኳ ምድር ሁሉ የእኔ ብትሆንም፣ እናንተ ለእኔ የመንግሥት ካህናት የተቀደሰ ሕዝብ ትሆናላችሁ፤ለእስራኤላውያን የምትነግራቸው ቃሎች እነዚህ ናቸው። ( ዘጸ. 19፥1-6)

እኔ እግዚአብሔር በጽድቅ ጠርቼሃለሁ፤ እጅህንም እይዛለሁ፤ እጠብቅሃለሁ፤ ለሕዝቡ ቃል ኪዳን፣ ለአሕዛብም ብርሃን አደርግሃለሁ። (ኢሳ. 42፥6)

እርሱን ስሙት፤ ቤተ ክርስቲያንም ከእግዚአብሔረ ተልእኮ ውጪ ራሷን ልተረዳ አትችልም

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል መስበክ ሲጀምርም፣ ሲጨርስም፣ የድነት ታሪክ ጀማሪና ፈጻሚ እግዚአብሔር ራሱ መሆኑን በተደዳጋሚ በአጽንዖት መስክሯል (ማር. 1፥15፤ ሉቃ. 4፥43፤ ማቴ. 24፥44፤ ዮሐ. 17፥1-5)። የብሉይ ኪዳን ተስፋ፣ በእርሱ ሙሉ ለሙሉ ፍጻሜ ማግኘቱን አብስሯል። በመለወጥ ተራራ ላይም፣ ጴጥሮስንና ያዕቆብን እንዲሁም የያዕቆብን ወንድም ዮሐንስ የዐይን እማኞች በሆኑበት መልኩ፣ ብሩህ ደመና ውስጥ፣ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙትበማለት የመጣው ድምፅ፣ ሙሴ (ሕግ)፣ ኤልያስ (ነቢያት)፣ የመሰከሩለት የተስፋው ወንጌል ባለቤት፣ ጀማሪና ፈጻሚ እራሱ እግዚአብሔር መሆኑን ነው። (2 ጴጥ.1፥16-18)። ጌታ የደቀመዛሙርቱን ዐይን የከፈተበትም ምስጢር፣ የድነት ታሪክ የሰው ልጅ ሁሉ ታሪክ (ማኅበራዊ፣ ፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ) መካከለኛ መሆኑ፣ በእርሱም ፍጻሜ ማግኘቱና ቤተ ክርስቲያንም የዚህ የምሥራች – ወንጌል ተሸካሚ መሆኗን በማሳሰብ ነው።[9]

ሐዋርያው ጳውሎስም፣ በክርስቶስ ልጁ ለነበረው ወጣቱ ጢሞቴዎስ ዐደራ ሲለው (1ጢሞ. 6፥20)፣ በእጁ ያለውን ወንጌል “እግዚአብሔር ለእኔ በዐደራ ከሰጠኝ የክብር ወንጌል” (1 ጢሞ 1፥11) በማለት፣ ወንጌል ተጀምሮ እስከሚያልቅ ድረስ ለቤተ ክርስቲያን በዐደራ የተሰጠ የእግዚአብሔር መልእክት መሆኑን በጥብቅ በማሳሰብ ነበር።[10] “[ጸጋው] በወንጌል አማካይነት ሕይወትንና ኢመዋቲነትን ወደ ብርሃን ባወጣው በመድኀኒታችን በክርስቶስ ኢየሱስ መምጣት ተገልጦአል፣ ስለዚህ [ይህን] የተሰጠህን መልካሙን ዐደራ በእኛ ውስጥ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ ጠብቅ(2ጢሞ 1፥8-11)።

በተመሳሳይ መልኩ፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ የእስራኤል ጥሪ፣ በአዲሱ የክርስቶስ ማኅበር ሰብ ጥሪ፣ ማንነትና ተልእኮ ሙላት ማግኘቱን በማስታወስ የወንጌልን ተልእኮ እንዲወጡ ያሳስባቸዋል።

እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እንድታውጁ፣ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር ለራሱ የለያችሁ ሕዝብ ናችሁ። ቀድሞ የእርሱ ወገን አልነበራችሁም፤ አሁን ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆናችኋል፤ ቀድሞ ምሕረትን አላገኛችሁም ነበር፤ አሁን ግን ምሕረትን አግኝታችኋል። (1ጴጥ. 2፥8-10)

ከአብርሃም መጠራት ጀምሮ እስከ አሁን ያለችው ቤተ ክርስቲያን የድነት ታሪክ ውስጥ እግዚአብሔር ሕዝቡ እንዲያስተውል የሚፈልገው፣ ተልእኳቸው በርሱ እግዚአብሔር ተልእኮ ማዕቀፍ ውስጥ የተያዘ መሆኑንን ነው። ጌታም ከትንሣዓኤው በኋላ ሐዋርያቱን፣ አብ እኔን እንደ ላከኝ፣ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ (ዮሐ. 20፥21) በማለት ልኳቸዋል።[11] በዐጭሩ፣ ከዘፍጥረት ምእራፍ አራት እስከ ራእይ የመጨረሻ ምእራፍ የምንመለከተው፣ ዘፍጥረት ሦስትን በመታደግ፣ በመፈውስ፣ በማደስ፣ ከዘፍጥረት አንድና ሁለት ጋር ማስታረቅ ነው። የቤተ ክርስቲያንም በክርስቶስ የመመሥረትና የመኖር ብቸኛና ዐቢይ ምክንያት የእግዚአብሔር ተልእኮ ነው። ሰው በክርስቶስ ከእግዚአብሔር፣ ከራሱ፣ እርስ በእርስና ከተፈጥሮ ጋር መታረቁ!

ክርስቶስ መጨረሻ፣ ምትክ የሌለውና ዘላለማዊ የእግዚአብሔር መገለጥ በመሆን፣ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደም ሰላም ሆኗል ስንል፣ ኀጢአት የፈጠራቸው የጥል ግድግዳዎች መፍረሳቸውና ዕርቅ መደረጉን ለመናገር ነው (ሮሜ 1÷1-4)። በዚህ አግባብና በቀዳማዊነት የክርስቶስ ተልእኮ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አይደለም። ወንጌል ማኅበራዊ እንድምታዎች አሉት። ሆኖም በቀዳማዊነት እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ክርስቶስን በብቸኛና የመጨረሻ መፍትሔነት ለዓለም የሰጠው፣ የክፋት ሁሉ ጉሮኖ የሆነውን የሰው ልጅ ልብ እንዲያው በጸጋው አዲስ ለማድረግ ነው። የሰው ችግር፣ ግለ ሰባዊም ሆነ ማኅበራዊ የሚቀዳው ከዚሁ በኀጢአት ከተበላሸ ልብ ውስጥ ነውና! ጌታችን የማኅበራዊ ንቅናቄ መሪ (Social Reformer) ወይም የሞራል መምህር  (Moralist) አይደለም የምንልበት ምክንያት፣ ሰው ያጣው የእግዚአብሔርን ሙሉነትና ክብር ስለ ሆነ ነው። ወንጌል፣ ሰው ያጣውን የእግዚአብሔርን ክብር በክርስቶስ የቤዝዎት ሥራ የመመለሱ የምሥራች ነው (1ጴጥ 2፥24፤ ሮሜ 3÷23)። ስለዚህ በየትኛውም መልኩና መለኪያ “ጥሩና የተሻለ” የሚባለው ማኅበራዊ መፍትሔ፣ ሰውን ምሉዕ አያደርግም። ሕግ “ነጩና ጥቁርኑ” (በአገራችን ዐውድ ደግሞ የተለያዩ ብሔሮችን) በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ያስቀምጥ ይሆናል፤ ሆኖም አንዱን በሌላው ልብ ውስጥ አያስቀምጥም! ወንጌል ብቻ ነው የሰውን ልብ የመለወጥ ኀይል ያለው። ስብከታችንም ይኸው የክርስቶስን መስቀል መካከለኛ ያደረገ የእግዚአብሔር ተልእኮ ነው። መጽሐፍ ቅዱስንም ከዚህ ውጭ ልናነብበው አንችልም!

ወደ ዋናው እንመለስ፤ የተልእኮ ተሐድሶም ይሁንልን! አሜን!


[1] የዕብራዊ ጸሐፊ ደግሞ እንዲህ ይላል፦ እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በተለያየ ጊዜና በልዩ ልዩ መንገድ በነቢያት በኩል ለአባቶቻችን ተናግሮ፣ በዚህ መጨረሻ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገውና ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ ለእኛ ተናገረን። እርሱ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራ ቅና የባሕርዩ ትክክለኛ ምሳሌ ሆኖ፣ በኀያል ቃሉ ሁሉን ደግፎ ይዞአል፤ የኀጢአት መንጻት ካስገኘ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ።(ዕብ. 1፥1-3)

[2] በላቲን Missio Ecclesiae

[3] በላቲን Missio Dei

[4] Nelson Jennings, God the Real Superpower: Rethinking Our Role in Missions (Phillipsburg, P & R, 2007), 16.

[5] David Bosch,Transforming Mission: Paradigm Shifts in Theology of Mission (Maryknoll, N.Y., Orbis Books, 1991).181.

[6] Transforming Mission, 181.

[7] ባሪያዬም ዳዊት ለዘላለም አለቃ ይሆናቸዋል። የሰላምም ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር አደርጋለሁ፥ የዘላለምም ቃል ኪዳን ይሆንላቸዋል፤ እኔም እባርካቸዋለሁ አበዛቸውማለሁ መቅደሴንም ለዘላለም በመካከላቸው አኖራለሁ።(ሕዝ 37፥24-27)፤ ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች። (ኢሳ 7፡ 14)

[8] Bauckham, Bible and Mission Christian Witness in a Postmodern World (Grand Rapids, Mich Baker Academic, 2003), 27ff. የእስራኤል የራስ ግንዛቤ ከዚህ የመነጨ እንዲሆን እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ያሳስባቸው ነበር። በሐዋርያት ሥራ ላይ የምንመለከተው የእስጢፋኖስም ስብከተ ወንጌል ይህንኑ ያረጋግጣል።አባታችን አብርሃም ወደ ካራን ከመምጣቱ በፊት፣ ገና በመስጴጦምያ ሳለ፣ የክብር አምላክ ተገልጦለት፤ ከአገርህና ከወገንህ ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ አለው . . . የእስራኤልንም ሕዝብ፣እግዚአብሔር እንደ እኔ ያለ ነቢይ ከመካከላችሁ ያስነሣላችኋልያላቸው ይኸው ሙሴ ነበር። እርሱም በሲና ተራራ ከተናገረው መልአክና ከአባቶቻችን ጋር በምድረ በዳ በሕዝቡ ጉባኤ መካከል ነበር፤ የሕይወትንም ቃል ወደ እኛ ለማስተላለፍ ተቀበለ . . . እስጢፋኖስ ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት፣ የእግዚአብሔርን ክብር፣ እንዲሁም ኢየሱስ በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና፣እነሆ፤ ሰማያት ተከፍተው፣ የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁአለ (ሐሥ. 7)። (1) የእስራኤል የተልእኮ መረዳት በእግዚአብሔር የፈጣሪት ራስ ግላጫ ላይ ያረፈ ነው (mission starts with the creation motif)። (2) እግዚአብሔር በሉዓላዊነቱ አብራሃምን በመጥራት እስራኤልን  ለዓለም ብርሃን እንድትሆን ጠርቷታል። (3) የእስራኤል ሕዝብ በዙሪያቸው ካሉት ሌሎች ሕዝቦች ለእግዚአብሔር ተልእኮ ተለይተው ተጠርተዋ፤ ስለዚህ ለእርሱ የተቀደሱ ናቸው። (4) እግዚአብሔር የታሪክ ጌታ ነው፤ ፍሰቱን ይቆጣጠራል፤ በውስጡ ያሉትን ነገሥታት በሉዓላዊነቱ ይገዛል። Donald Senior and Carroll Stuhlmueller, The Biblical Foundations for Mission (Maryknoll,N.Y.: Orbis Books, 1983), 317ff; Transforming Mission, 19.  

[9]እርሱም፣ከእናንተ ጋር በነበርሁበት ጊዜ፣በሙሴ ሕግ፣ በነቢያትና በመዝሙር መጻሕፍት ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባልብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነውአላቸው። በዚህ ጊዜ ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዲያስተውሉ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤ እንዲህም አላቸው ‘እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤ ክርስቶስ መከራን ይቀበላል፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፤ ከኢየሩሳሌም ጀምሮ ለሕዝቦች ሁሉ ንስሓና የኀጢአት ስርየት በስሙ ይሰበካል፤እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ። እኔም አባቴ የሰጠውን ተስፋ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኀይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቈዩ። (ሉቃ. 24፥44-49)

[10]ጳውሎስ፣ የክርስቶስ ኢየሱስ ያ፣ ሐዋርያ ሊሆን የተጠራና ለእግዚአብሔር ወንጌል የተለየ፤ ስለዚህ ወንጌል በነቢያቱ በኩል በቅዱሳት መጻሕፍት አስቀድሞ ተስፋ ተሰጠ። ወንጌሉም ስለ ልጁ፣ በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ሆነ፣ በቅድስና መንፈስ ደግሞ ከሙታን በመነሣቱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ በኀይል ስለ ተገለጠው ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በእርሱ በኩል ስለ ስሙ ከአሕዛብ ሁሉ መካከል ሰዎችን በእምነት አማካይነት ወደሚገኘው መታዘዝ ለመጥራት ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን። (ሮሜ 1፥1-5)

[11] Cf. Richard Bauckham, Bible and Mission: Christian Witness in a Postmodern World (Baker Academic, 2003); Wright, The Mission of God’s People.

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በተመለከተ መንግሥትና ሕዝብ ልብ ልንል የሚገባቸው ነጥቦች

ይህ ጽሑፍ ከቀናት በፊት ለንባብ የቀረበ ሲሆን፣ ዐቢይ ትኩረቱም ማኅበራዊ ንክኪን መቀነስ ላይ ያተኩራል። ጽሑፉ አነስተኛ አርትዖት ተደርጎበት ለሕንጸት አንባቢያውን እንደሚከተለው ቀርቧል።

ተጨማሪ ያንብቡ

የአዲሱ ጅምር “አብዮት” ዕጣ ፈንታ

ምኒልክ አስፋው በዚህ ዘለግ ባለ ጽሑፉ በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ የሚፈለግበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ክርስቲያናዊ የሆነ ዕይታውን ያካፍላል። በዚህም በተለይ ብዙዎች የሚመኙት “ዴሞክራሲ” እውን እንዲሆን መሠረታውያን ያላቸውን መስፈርቶች ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ ጋር እያመሳከረ ምክረ ሐሳቡን ያካፍላል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.