ይህ ዐምድ በተቻለ መጠን ሆሄያትን (ፊደላትን) እንደ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላትና የግእዝ ቍጥሮችን ይጠቀማል።
መፀው (ወርኀ ጽጌ ወይም የአበባ ወር) የሚባለው ከመስከረም ፳፷ – ታኅሣሥ ፳፶ ቀን ድረስ ያለው ወቅት ሲኾን ዘጠና ቀናትን ይሸፍናል። በውስጡ ዐምስት ንኡሳን ክፍሎች አሉት። ከእነዚህም የመጀመሪያው ከመስከረም ፳፮ – ኅዳር ፭ ድረስ ያለው ወቅት ዘመነ ጽጌ ይባላል (ጥዑመ ልሳን /ሊቀ ካህናት/፣ ያሬድና ዜማው፣ ፲፱፻፹፩፥ ገጽ ፵፰፡፵፱)።
በቅዱስ ያሬድ የተቀመሩትና ወርኀ ጽጌ በሚባሉት ዕለታትና ሳምንታት ውስጥ የሚዘመሩት መዝሙሮች አበባን፥ ፍሬን፥ የክረምትን ማለፍ፥ የአበቦችን ማበብ የሚያወሱ ናቸው (ዝኒ ከማሁ ገጽ ፵፱)። ፍጥረትና ወቅት እግዚአብሔርን ለመወደስ መነሻ ይኾናሉ። መዘምር ዳዊት ለእግዚአብሔር ውዳሴን ለማቅረብ በአምልኮ ሰረገላ ላይ ተጭኖ በመንፈስ ፍጥረቱን ሲጐበኝ፥ ሥርዐተ ተፈጥሮኣቸውን ሲመረምርና በአኗኗራቸው ሲደመም፥ ይህን ኹሉ በጥበብ የሠራውን እግዚአብሔርንም ከፍ ከፍ ሲያደርገው እናነባለን (መዝ. ፻፬፥፩-፴፪)። በጋና ክረምትን በማፈራረቅና ለሰው ልጆች የሚያስፈልጋቸውን በማዘጋጀት እግዚአብሔር የሚያደርገው ቸርነት፥ ስለ ራሱ የተወው ምስክርነት ሲኾን፥ ለአምልኮ አነሣሽ ምክንያት ይኾናል (መዝ. ፸፬፥፲፯፤ ፻፵፯፥፰፤ ሐ.ሥ. ፲፬፥፲፯)።
ከወቅቱ በተጨማሪ ይህ ክፍለ ዘመን (ዘመነ ጽጌ) ሕፃኑ ኢየሱስ ከእናቱ ከማርያምና ከዮሴፍ ጋር መሰደዱ የሚዘከርበት ጊዜ ነው። ለዚህ ነው በርእሱ ላይ ኹለቱን ጕዳዮች ያጫፈርነው (ወርኀ ጽጌ ወስደት ያልነው)። የዚህ ጽሑፍ ቀጣይ ትኵረትም ይኸው የስደት ታሪክ ይኾናል።
የሕፃኑ ኢየሱስ ስደት ታሪክ በቅዱስ ወንጌል ተመዝግቦ ይገኛል (ማቴ. ፪፥፲፫-፳፫)። በወንጌላውያን አማኞች ዘንድ ይህ የወንጌል ክፍል እንደ ሌላው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከመታወቅ ባለፈ የተለየ ትኵረት የሚሰጠው አይመስልም። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ግን ማርያም ሕፃኑን ኢየሱስን ይዛ ወደ ግብጽ መሰደዷ ይታሰባል፤ ከመስከረም ፳፮ – ኅዳር ፮ ድረስ ባሉት እሑዶችም ታሪኩ በማሕሌት ይዘከራል።
በአንዳንዶች ዘንድ ይህ ወቅት “የጽጌ ጾም” እየተባለ ሲጠራና ሲጾምበት እንሰማለን፤ እናያለን። ይኹን እንጂ በቤተ ክርስቲያኒቱ የታወቁ ሰባት አጽዋማት (የጾም ወቅቶች) ናቸው ያሉት። ይህ ወርኀ ጽጌ ወይም አንዳንዶች “የጽጌ ጾም” የሚሉት በአጽዋማቱ ቊጥር ውስጥ አልተካተተም፤ ስለዚህ የፈቃድ ጾም ነው ተብሎ ነው የሚወሰደው። በዚህ ወቅት ከረቡዕና ከአርብ በቀር የፍስክ ምግብ መበላቱና ቅዳሴ የሚቀደሰውም በጥዋት መኾኑ “የጽጌ ጾም” የፈቃድ እንጂ በቀኖና የተወሰነ ጾም አለመኾኑን ያመለክታሉ።
ማኅበረ ቅዱሳን ግን ሐመር በተባለው መጽሔቱ የ፲፱፻፹፯ ዓ.ም. ነሐሴ ዕትም ውስጥ፥ የ፲፱፻፹፰ ዓ.ም. አጽዋማትን ይዞ በወጣው ፖስት ካርድ ላይ በተራ ቍጥር ፰ ጾመ ጽጌ መስከረም ፳፮ ይጀመራል ብሎ ጠቅሶ እንደ ነበረና፥ በጊዜው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በቍጥር 6738/8513/87 በቀን 2/13/87 በጻፈው ደብዳቤ፥ ማኅበረ ቅዱሳን ስሕተት ፈጽሟል በማለት የጽጌ ጾም በሚል ፰ኛ ጾም አድርጎ በቈጠረው ላይ አስቸኳይ ዕርምት እንዲሰጥበትና ለወደ ፊቱ እንዲህ ያለ ስሕተት እንዳይደገም፥ የኅትመት ውጤቶቹን በጊዜው ለስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ እያሳየ እንዲያወጣ ትእዛዝ አስተላልፎለት ነበር። ማኅበሩም በተሰጠው ዕርምት መሠረት ስሕተቶቹን እንደሚያስተካከል በቀን 3/1/88 ዓ.ም. በቍጥር 002/ማቅ/038 ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በጻፈው ደብዳቤ ገልጾ ነበር፤ ይኹን እንጂ ዐርማለኹ ያለውን ስሕተት አለማረሙን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የተጻጻፏቸውን ደብዳቤዎቻቸው ዐባሪ በማድረግ በድረ ገጹ ላይ አስነብቧል (http://eotcssd.org/the-news/128-2011-06-11-13-05-43.html)።
መነሻው መጽሐፍ ቅዱስ የኾነው ይህ የስደት ታሪክ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሲዘከር፥ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ በኾኑ ትውፊታውያን ታሪኮችና ድርሰቶችም ጭምር ታጅቦ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? (ማቴ. ፪፥፩-፳፫)
ሕፃኑ ኢየሱስ ከእናቱ ጋር እንዲሰደድ ምክንያት የኾነው በዘመኑ የነበረው ንጉሥ ሄሮድስ ነው። እርሱ “የአይሁድ ንጉሥ” የተባለ ሕፃን መወለዱን ዐውቀውና በኮከብ ተመርተው፥ እጅ መንሻም ይዘው ሊሰግዱለት ከመጡት ሰብአ ሰገል (የጥበብ ሰዎች) ዜናውን በመስማቱ ደነገጠ። ከዚያ የካህናት አለቆችንና የሕዝብ ጻፎችን ሰብስቦ ክርስቶስ የት እንደሚወለድ ጠየቃቸው። እነርሱም በነቢዩ ሚክያስ የተነገረውን ትንቢት ጠቅሰው በይሁዳ ቤተ ልሔም መኾኑን አስረዱት። ሄሮድስም ሰብአ ሰገልን በስዉር ጠርቶ ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከእነርሱ በጥንቃቄ ከተረዳ በኋላ፥ ወደ ቤተ ልሔም ላካቸውና ስለ ተወለደው ሕፃን በጥንቃቄ እንዲመረምሩና ካገኙት በእርሱ በኩል ተመልሰው መጥተው እንዲነግሩት፥ እርሱም ኼዶ እንደሚሰግድለት ነግሮ አሰናበታቸው።
ያ በምሥራቅ ያዩት ኮከብ እየመራቸው ሕፃኑ በሚገኝበት ስፍራ ላይ ሲደርስ ቆመ። “ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት፥ ሳጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት።” (ልብ እንበል ወድቀው የሰገዱት፥ እጅ መንሻም ያቀረቡት ለሕፃኑ ኢየሱስ ነው)። ከዚያ በሄሮድስ በኩል እንዳይመለሱ በሕልም ተረድተው በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ገቡ።
“እነርሱም ከኼዱ በኋላ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ፥ ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘኽ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስክነግርኽም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው።” ይህም ከጌታ ዘንድ በነቢይ፥ ልጄን ከግብጽ ጠራኹት የተባለው እንዲፈጸም ነው። ሄሮድስም ሰብአ ሰገል እንዳታለሉት ባወቀ ጊዜ ኮከቡ መታየት የጀመረበትን ዘመን ከእነርሱ በተረዳው መሠረት ኹለት ዓመትና ከዚያ በላይ የኾናቸውን ሕፃናት ኹሉ አስገደለ።
ሄሮድስ ከሞተ በኋላ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ፥ የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ስለ ሞቱ ተነሣና ሕፃኑንና እናቱን ይዘኽ ወደ እስራኤል አገር ኺድ አለው፤ እርሱም እንደ ታዘዘው አደረገ። ነገር ግን በሄሮድስ ፈንታ ልጁ አርኬላዎስ በይሁዳ እንደ ነገሠ በሰማ ጊዜ ወደዚያ መኼድን ፈራ፤ በሕልምም ተረድቶ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ።
ይህ የስደት ታሪክ አስቀድሞ ከጌታ ዘንድ በነቢይ ‘ልጄን ከግብጽ ጠራኹት’ የሚለው ቃለ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ የተከናወነ መኾኑ ግልጥ ነው (ሆሴ. ፲፩፥፩፤ ማቴ. ፪፥፲፬-፲፭)። ከዚህ ውጪ በስደት ታሪክ ዙሪያ ሌሎች ዝርዝር ነገሮችን፥ ለምሳሌ፦ በግብጽ ውስጥ በየትኛው ስፍራ እንደ ተቀመጡ ወይም ከስፍራ ስፍራ ይዘዋወሩ እንደ ነበር፥ ለስንት ጊዜ ያኽል በግብጽ እንደ ተቀመጡ፥ ወዘተ. ከእነማን ጋር እንደ ተገናኙና እነማን እንዳጋጠሟቸው መጽሐፍ ቅዱስ በዝርዝር አይናገርም ።
ትውፊታዊው ትረካ ምን ይላል?
ስለ ስደት የሚተረከው ትውፊታዊ ትረካ ግን በእነዚህና በመሳሰሉት ዙሪያ ብዙ ነገሮችን ያትታል። አንዳንድ በወንጌላት ውስጥ ለተመዘገቡ ኹነቶች የስደትን ታሪክ መነሻ በማድረግ ያቀርባል። ለምሳሌ፦ በጌታ ቀኝና ግራ የተሰቀሉት ኹለቱ ሽፍቶች ከጌታ ስደት ጀምሮ በሽፍትነት የኖሩና ሕፃኑንና እናቱን አግኝተዋቸው እንደ ደበደቧቸውና ልብሳቸውን ገፈው እንደ ኼዱ፥ በኋላም በአንደኛው ሽፍታ ሐዘኔታና አግባቢነት የቀሟቸውን እንደ መለሱላቸው፥ ሕፃኑ ኢየሱስም ኹለቱም ከእርሱ ጋር እንደሚሰቀሉ፥ ጥጦስ (በቀኙ የተሰቀለው) የእግዚአብሔር ፈንታ እንደኾነና ወደ ገነት በመግባት አዳምን እንደሚቀድመው፥ ኹለተኛው (ዳክርስ የተባለው) ደግሞ የዲያብሎስ ፈንታ መኾኑን መተንበዩ ይተረካል (አንድምታ ወንጌል ዘሉቃስ ፳፫፥፵፭)።
የዘብዴዎስ ልጆች እናት ወደ ጌታ ቀርባ ልጇቿ አንዱ በቀኙ አንዱ ደግሞ በግራው ይቀመጡ ዘንድ ጌታን በለመነችው ጊዜ፥ “በቀኝና በግራ መቀመጥ … ከአባቴ ዘንድ ለተዘጋጀላቸው ነው እንጂ እኔ የምሰጥ አይደለኹም” ሲል የመለሰው በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከኹለቱ ሽፍቶች ጋር ተገናዝቦ የሚተረጐም ነው (ማቴ. ፳፥፳-፳፫)።
በራእየ ዮሐንስ ምዕራፍ ፲፪ ላይ የተጠቀሰችው ሴት በአንድምታ ትርጓሜ መሠረት፣ አንድም መምህራን ናቸው፤ አንድም ምእመናን ናቸው፤ አንድም እመቤታችን ናት ተብላ ተተርጕማለች። ለቅድስት ማርያም ተሰጥታ ስትተረጐም፥ ክፍሉ ከስደት ታሪክ ጋር እንዲያያዝ ተደርጓል።
ጌታና እናቱ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነበር?
ጌታና እናቱ በስደት ጊዜ ወደ ግብጽ መጥተው ሳለ ወደ ኢትዮጵያ ጎራ ብለው እንደ ነበር የሚተረክ ትውፊታዊ ትረካ አለ። ሊቀ ጠበብት አያሌው ታምሩ እንደ ጻፉት፥ “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ … ወደ ግብጽ በተሰደደበት በሕፃንነቱ ወራት የግብጽን በረሓ ዘልቆ በኢትዮጵያ ጠረፍ ላይ በሚገኘው ኢትዮጵያዊ ምድር ሦስት ዓመት ከመንፈቅ” ማሳለፉን ጠቅሰዋል (የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕግጋት፥ ፲፱፻፶፫፥ ገጽ ፷፰)። በአንዳንድ የሰሜን ኢትዮጵያ ገዳማት፥ ጌታና እናቱ በስደት ወደ ኢትዮጵያ በመጡ ጊዜ የጐበኟቸው ስፍራዎች መኾናቸው ይነገራል። አንዳንድ አሻራዎችንም እንደ ተዉ የሚያምኑ አሉ። ይኹን እንጂ ገዳማቱ የተገደሙት በኋላ ዘመን በመኾኑ፥ ገዳማቱ የተገደሙት በዚያው ስፍራ ላይ ነው እስካልተባለ ድረስ ትረካው ከጥያቄ አያመልጥም።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ስደት ታሪክ ሲናገር፥ ለማርያም ዕጮኛ ለዮሴፍ የጌታ መልአክ በሕልም የነገረው ሕፃኑንና እናቱን ወደ ግብጽ ይዞ እንዲኼድና ተመለስ እስኪለው ድረስም በዚያ እንዲቀመጥ ነው (ማቴ. ፪፥፲፫)። በነቢይ የተነገረው ትንቢትም ልጄን ከግብጽ ጠራኹት የሚል ነውና፥ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነበር የሚለው ትረካ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው አይመስልም።
ማሕሌተ ጽጌ ወሰቈቃወ ድንግል
ማሕሌተ ጽጌ እና ሰቈቃወ ድንግል ስለ ሕፃኑ ኢየሱስና እናቱ ማርያም ስደት የተደረሱና በወርኀ ጽጌ በማሕሌት ላይ የሚዘመሩ ዐምስት ቤት (ስንኞች) የያዙ የግእዝ ግጥሞች ናቸው። ማሕሌተ ጽጌ ቃል በቃል ሲተረጐም “ያበባ ዘፈን” ማለት ሲሆን፥ ባለ ፭ ቤት (አንዳንዱ ፮ ቤት ነው) የግእዝ ግጥሞችን የያዘ ፻፶ ድርሰት ነው። የድርሰቱ መሠረትም ተኣምረ ማርያም ነው (ደስታ ተክለ ወልድ፣ ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት፣ ፲፱፻፷፪፥ ገጽ ፭፻፳፬)። ድርሰቶቹ በአብዛኛው ድንግል ማርያምን የሚያወድሱና ስለ እርሷ የሚናገሩ ናቸው። የድርሰቱ መሠረት ተኣምረ ማርያም እንደ መኾኑ፥ በተኣምረ ማርያም የተመዘገቡ ትረካዎች በማሕሌተ ጽጌ ውስጥ ተካትተዋል። ለምሳሌ፥ ስለ ዮሐንስ አፈ ወርቅ የተነገረው ይገኝበታል። ዮሐንስ አፈ ወርቅ የተባለው የቤተ ክርስቲያን አባት “አፈ ወርቅ” የሚል ስም ያገኘው፥ ጥሩና ማራኪ ንግግር በማድረግ ስለ ታወቀ መኾኑ ከሥያሜው ይታወቃል። የተኣምረ ማርያምን ትረካ መሠረት ያደረገውና በማሕሌተ ጽጌ ውስጥ ዮሐንስ አፈ ወርቅ የተጠቀሰበት አንደኛው ግጥም ግን፥ “አፈ ወርቅ” የተባለበትን ምክንያት የገለጸው በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ባልተሰማና ባልታወቀ ጽዩፍ ድርጊት ላይ ተመሥርቶ ነው፤ “… ስለ ክብርት እመቤታችን ክብርና ገናንነት የሴት ኀፍረትን በሳመ ጊዜ ሊቀ ጳጳስነት ሳይሾም አስቀድሞ አፈ ወርቅ እንዳለችው ዕወቁ” ይላል (ተኣምረ ማርያም ፲፱፻፹፭፥ ገጽ ፪፻፯)።
አንዳንድ ሊቃውንት ግን ይህ ሊስተካከል እንደሚገባ ጠቍመዋል። ቀ/ዶ/ር ምክረ ሥላሴ፥ “አንዳንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በአንድምታ ትርጉም ላይ ዮሐንስ፥ አፈ ወርቅ የተባለበትን ምክንያት የሚያትቱት ሐተታና በማሕሌተ ጽጌ ‘ሶበ ሰዐመ ኀፍረተ ትክት ቅድመ መዋዕለ ንጽሕ ሱባኤ … ወደሰቶ ወአእኰተቶ ቅድመ ገጸ ኵሉ ጉባኤ፤ አፈ ወርቅ እንዘ ትብል ጊዜያተ ክልኤ’ ተብሎ የተጻፈው ትክክል አይደለም። ይህ በማናቸውም ቤተ ክርስቲያን ስለሌለና ዮሐንስ ደግሞ ‘አፈ ወርቅ’ የተባለው ጥሩና ማራኪ ንግግር ማድረግ በመቻሉ ስለ ኾነ፥ ይህ ሐተታ መቅረት አለበት፤ ማሕሌተ ጽጌውም መታረም አለበት ብዬ በታላቅ ትሕትና አሳስባለሁ።” ብለዋል (የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ በምድር ላይ (ጠቅላላ የቤተክርስቲያን ታሪክ) አንደኛ መጽሐፍ፣ ፳፻፥ ገጽ ፬፻፩)።
ሰቈቃወ ድንግል፥ ማርያም “በስደቷ ጊዜ የተናገረችውን ሙሾ፥ ያለቀሰችውን ለቅሶ [ምናባዊ በኾነ መንገድ] አምልቶ አስፍቶ በግእዝ ቋንቋ የሚናገር መሠረቱ ነገረ ማርያም” የኾነ ድርሰት ነው (ደስታ ተክለ ወልድ፣ ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት፣ ፲፱፻፷፪፥ ገጽ ፲፪፻፫)። በሰቈቃወ ድንግል፥ የኢየሱስ እናት ማርያም በስደቷ ወቅት የገጠማትን መከራና ችግር ሊያንጸባርቅ የሚችል ይዘት ያላቸው ግጥሞች ተካትተዋል። ከጌታ ጋር ተያይዘው የተደረሱት ግጥሞች መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጣቅሱ ኾነው እናገኛቸዋለን። ጥቂቶቹን ለአብነት ቀጥሎ እናቀርባለን፤
ያዕቆብ ነገደ በፍሥሓ ለረኪበ ኵሉ መፍቅዱ
ሶበ ሰምዐ በብሔረ ግብጽ ከመ ነግሠ ወልዱ
ለአጕይዮ ወልዳ በአንብዕ አመ ሕፃናት ተኃርዱ
ነገደት ውስተ ምድረ ግብጽ ማርያም ዘመዱ
ኀበ አልባቲ ዘየአምራ ወኢ፩ዱ
ትርጉም “በግብጽ አገር ልጁ [ዮሴፍ] እንደ ነገሠ በሰማ ጊዜ፥ ያዕቆብ የወደደውን ኹሉ በደስታ ለማግኘት [ወደ ግብጽ] ኼደ። የእርሱ ወገን የምትኾን ማርያም [ግን] ሕፃናት በታረዱ ጊዜ ልጇን ለማሸሽ እያለቀሰች አንድ ስንኳ የሚያውቃት ወደሌለበት ወደ ግብጽ ምድር ኼደች።” በዚህ ግጥም ደራሲው የይሥሐቅ ልጅ ያዕቆብ ልጁ ዮሴፍ በግብጽ ትልቅ ባለሥልጣን መኾኑን በሰማ ጊዜ ወደ ግብጽ በደስታ የኼደበትን ኹኔታ፥ ማርያም ሕፃኑ ኢየሱስን ይዛ ወደ ግብጽ ከተሰደደችበት ኹኔታ ጋር በማነጻጸር፥ ኹለቱ የተለያዩ ወይም በተቃራኒ ኹነቶች (በደስታና በሐዘን) የተሞሉ መኾናቸውን አነጻጽሯል።
በስደቱ ኢየሱስ ስለ እኛ የከፈለውን ውድ ዋጋና ያሳየውን ፍጹም ትሕትና በተመለከተም የሚከተለውን ብሏል፤
ኢየሱስ ስዱድ ተስፋሆሙ ለስዱዳን
ኢየሱስ ግፉዕ ምስካየ ግፉዓን
እግዚአብሔር ማኅደር ዘአልቦ ከመ ነዳያን
ኢየሱስ ነግድ ወፈላሴ እንዘ ውእቱ ሕፃን
ወልደ አብ ፍቁር ዘበኀበ ሰብእ ምኑን
ማሕልየ ብካይ ኮነኒ ዘእሙ ሐዘን
ትርጉም፥ “ስደተኛው ኢየሱስ ለሚሰደዱት ተስፋቸው ነው፤ የተገፋው ኢየሱስ ለሚገፉት መጠጊያቸው ነው። እግዚአብሔር [ወልድ] እንደ ድኾች መጠጊያ የሌለው ኾነ። ኢየሱስ ሕፃን ሳለ እንግዳና መጻተኛ፥ የተወደደ የአብ ልጅ በሰው ዘንድ ግን የተናቀ ነበረ። የእናቱ ሐዘንም የልቅሶ መዝሙር ኾነኝ።” የዚህ የግእዝ ግጥም አብዛኛው ስንኝ ከሚከተሉት ቅዱሳት መጻሕፍት ኀይለ ቃላትን ያዘለ ነው (ማቴ. ፰፥፳፤ ሉቃ. ፱፥፶፰፤ ፪ቆሮ. ፰፥፱)።
ሰቈቃወ ድንግል የተባለው ድርሰት ነገረ ስደቱን ብቻ ሳይኾን የሚጠቱንም (የመመለሱን) ዜና ብሥራት ይናገራል። ሄሮድስ እንደ ሞተ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም የሕፃኑን ነፍስ የሚሹት ሞተዋልና ተነሣ ሕፃኑንና እናቱን ይዘኽ ወደ እስራኤል አገር ኺድ ባለው መሠረት እንደ ታዘዘው አድርጓል። ደራሲው ይህን ኹኔታ ከገለጠባቸው ግጥሞች አንዱ ማርያም የእግዚአብሔርን ማዳን እንድትናገር ያደረገበት ግጥም ይገኝበታል፤ ይህን ጽሑፍ በዚህ ግጥም ልደምድም፤
ወለተ ዳዊት በሊ እንዘ ትነገሪ ዘእግዚአብሔር አድኅኖ
ወታየድዒ ሥልጣኖ
ርኢክዎ ለኃጥእ ዐብየ ወተለዓለ ከመ አርዘ ሊባኖስ ከዊኖ
ኀሠሥክዎ በግብአትየ ወኢረከብኩ መካኖ
እስመ ሰበረ ወልድየ ለሄሮድስ ቀርኖ
ትርጉም፥ “የዳዊት ልጅ [ማርያም] ሆይ የእግዚአብሔርን ማዳን ስትናገሪና ሥልጣኑን ስታሳውቂ እንዲህ በዪ፥ ‘ኃጥእን ከፍ ከፍ ብሎ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ለምልሞ አየኹት። ብመለስ ግን ዐጣኹት። ፈለግኹት፤ ቦታውንም አላገኘኹም።’ ልጄ የሄሮድስን ቀንድ ሰብሯልና”
1 comment
👏👏👏