
God Moves in a Mysterious Way: Hope for the Hard Years Ahead
We do not need to grasp all that God is doing. In the end, God will show that his ways, so high above our own, were perfect at every turn.
[the_ad_group id=”107″]
እግዚአብሔር የሰው ዘርን በሙሉ ለእርሱ ይሆን ዘንድ ዐስቦ ፈጠረ። ዐብሮት የሚሆንን፣ የሚመስለውንና የሚያመልከውን ታዛዥ ሕዝብ ፈልጎ አዳምንና ሔዋንን ፈጠረ። እነርሱም በተመቸ ቦታ በዕረፍት ነበሩ፤ ከእግዚአብሔር ጋር በሰላም ነበሩ። አዳም እግዚአብሔር ለእርሱና ለዘሩ ፈጥሮ እንዲሰይማቸው አሳልፎ በሰጠው ፍጥረታት የሞላለትን ዓለም ይጠብቅና ይገዛ፣ በዚያም ይሠራ ነበር፤ ነገር ግን፣ አይለፋም ነበር፤ በመታዘዝ ሥር ተጠብቆ የተባረከ ነበርና።
በመታዘዝ ቅጥር ውስጥ ደኅና የነበረው ሰው፣ ባለመታዘዝ ኀጢአት ወደቀ፤ ለትውልዱና ለምድርም ርግማንን አመጣ። እግዚአብሔር ለአዳምና ለዘሩ ያሰበው የበዛ ሕይወትንና በረከትን ነበር፤ አዳም ግን ባለመታዘዙ ምክንያት ሞትን የሚሞት ሆነ፤ ርግማንንም አጨደ። የነበረበትን ክፍታ ባለማስተዋሉ፣ የማይገባውን ከፍታ ከክፉው ምክር የተነሣ በተመኘ ጊዜ ከውድቀት ጋር ተገናኘ። ከእግዚአብሔር ዕውቀት የተሻለ ዕውቀት እንዳለ ባመነ ጊዜ፣ ታበየ፤ በጎመጀ ጊዜ ሳተ። ስላልታዘዘም ከእግዚአብሐር ክብር ተለየ፤ ከዕረፍት መናፈሻ ወደ መቅበዝበዝ ምድረ በዳ ወጣ (ዘፍጥረት ምዕራፍ 3)።
አዳም ከእግዚአብሔር መገኘትና ከበረከት ገነት ባለመታዘዙ ወጣ፤ ለትውልዱም ሞትን አወረሰ፤ ይህም የእግዚአብሔርና የሰው ልጆች ጠላት በሆነው በዲያብሎስ ሽንገላ ምክንያት ሆነ።
ዲያብሎስ የውሸት አባት፣ የእግዚአብሔር ዐሳብ ጠላት፣ የሰው ልጆችም ቋሚ ባለጋራ ነው። እርሱ የጨለማ አለቃ፣ የክፋት ምንጭ፣ የዚህ ዓለም ሥርዐት ገዥ ነው። የሰው ልጆችን ልብ በሚወድዳቸውና ሊያድናቸው በሚወድደው በእግዚአብሔር ላይ ክፍ ክፍ እንዲል የሚያነሣሣ፣ ውድ የሆነውን ዘላለማዊ እውነት በማራከስ የሰዎችን አእምሮ በከንቱ ዕውቀት የሚያሳውር፣ ወንድማማች የሆነውን የሰው ዘር ልዩነትን እያጎላና እያከፋፋ የሚያጥላላ ጨለማ ነው። እርሱ ለሰው ልጆች ያለው ዐላማ ጥፋት ብቻ ነው፤ ሞት። ሊጠፋ ተወስኖበታልና አጥፍቶ ሊጠፋ ተግቶ ከእግዚአብሔር መንግሥት በተቃራኒ ይሠራል፤ የሰው ልጆችንም እስከ ዛሬ በማታለል ሥራ ከሕይወት መንገድ እያከላከለና እያወጣ፣ ወደማይወጣበት ሞት ለመጣል የሚጥር ነው። “ሌባው ሊሰርቅ ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ።” (ዮሐንስ 10፥10)።
ሕይወት የሆነው ኢየሱስ ግን ሕይወትን የሚሰጥ፣ ብቸኛው የሰው ልጆች የመዳን ተስፋ ነው። በእርሱ ያመነ፣ በመንፈሱ ሕያው ይሆናል። በእርሱ ያመነ ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረትን ወደ ማድረግ፣ ወደ ዐብሮነት ይመለሳል፤ እንደውም የእግዚአብሔር ልጅነትን መብት ያገኛል። “ለተቀበሉትና በስሙ ላመኑት ግን የእግዚአብሔር ልጆች የመሆንን ሥልጣን ሰጣቸው።” (ዮሐንስ 1፥12)።
እግዚአብሔር ሰውን ፈጥሮ በጨረሰ ጊዜ ሥራውን ሲገመግም፣ መልካም እንደ ሆነ ዐይቶ ነበር። የሰው ልጅ በፍጥረቱ እንደ እግዚአብሔር ዐሳብና ፈቃድ መልካምን ሊያደርግ የተፈጠረ መልካም ፍጡር የነበረ ቢሆንም ባለመታዘዝ ጠንቅ ሙት ሆነ፤ ከእግዚአብሔር መገኘት በመውጣቱ በሥራው እጅግ ክፉ ሆነ፤ እግዚአብሔርም ሰውን በመፍጠሩ ተጸጸተ። “እግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፤ በልቡም አዘነ።” (ዘፍጥረት 6፥6)።
ሆኖም ግን እግዚአብሔር ምድርን ጨርሶ አላጠፋም። ቅሬታ የሚሆንን ትውልድ መርጦ በዚያም እርሱን የሚያመልክ፣ ለእርሱ የተለየን ሕዝብ አባት ይሆን ዘንድ አብራምን፣ “አብርሃም” ብሎ ጣዖት አምላኪ ከነበረው ከአባቱና ከዘመዶቹ ቤት ለይቶ ጠራው፤ ከእርሱም ትውልድ የሚታዘዘውን ብሩክና ለሕዝቦች ሁሉ መባረክ ምክንያት የሚሆንን ሕዝብ ሊያወጣ ተስፋን ሰጠው (ዘፍጥረት 12፥1-13)።
እግዚአብሔርም ለአብርሃም ልጆች፣ ለእስራኤል ሕዝብ ፍቃዱን በመግለጥና ለእርሱ ክብር ይሆኑ ዘንድ ሕዝቡ በማድረግ ተስፋውን ፈጸመ። ሕዝቡንም የአምላክነት ክንዱንና የማዳን ኀይሉን ያውቁ ዘንድ ለብዙ ትውልድ በባርነት ከነበሩበት ከግብፅ ምድር፣ በባርያው በሙሴ መሪነት በብዙ ድንቅና ታምራት አወጣቸው፤ በምድረ በዳም የአቅርቦት እጁን ከሰማይ መናን እያወረደና ውሃን ከዐለት እያፈለቀ አሳያቸው። እግዚአብሔር ለእርሱ ይለዩ ዘንድ ወድዶ፣ ሕዝቤ ላላቸው ለእስራአል፣ የሚጠብቁትንና ለትውልድ ሁሉ የሚያስተምሩትን ሕግንና ሥርዐትን ሰጣቸው (ዘዳግም 28፥20)።
የዚህች ዓለም ዕድሜ ዐጭር ነው፤ ደስታዋም ይሁን መከራዋ፣ ውበቷም ይሁን ጕስቍልናዋ ዐላፊ ነው።
እግዚአብሔርም የእኔ ላለው፣ ይሠዋለት ዘንድ ከብዙ ሕዝቦች መኻል በበጎ ፍቃዱ ለመረጠው ለእስራኤል ሕዝብ፣ ፍቅሩንና ኀይሉን እየገለጠ፣ በመረጣቸው ነቢያት አፍ እየተናገረና የሚገዙትን ነገሥታት እየቀባ፤ ጦርነታቸውን እየተዋጋ፣ በበዛው በደላቸው እየገሠጸና እየማራቸው፣ ይቀደሱለት ዘንድ በብዙ ደከመ። እግዚአብሔር ሕዝቤ ያለው ሕዝብ ግን እንደ እግዚአብሔር መሻት ሊሆን፣ በፍጹም ልቡም ሊገዛለት አልቻለም። ሰው የእግዚአብሔርን ሕግ በመጠበቅ ፍጹም መሆን አልቻለም፤ በእግዚአብሔር ሚዛን አንድም ጻድቅ አልተገኝምና። “ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፥ በደላችንም አንደ ንፋስ ወስዶናል።” (ኢሳይያስ 64፥6)፤ “ጻድቅ የለም እንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፣ በአንድነት የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ቸርነትን የሚደርግ የለም፣ እንድ ስንኳ የለም።” (ሮሜ 3፥11-12)።
እግዚአብሔርም ለዚህ መፍትሔ የሚሆንን መንገድ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አበጀ፤ በመልኩ ከፈጠረው የሰው ዘር መኻል፣ ለእርሱ የሚሆንና ከእርሱ ጋር የሚሆንን ሕዝብ ይፈልግ ነበርና። እርሱ አባት በሆነበት ቤት፣ ልጆቹ የሚሆኑትን ብዙኃን በአንድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን በኩል ሊቀበልና ለዘላለም ከእርሱ ጋር ሊያኖራቸው አስፈላጊውን ሁሉ ዋጋ ከፈለ፤ ከፍሎም አጸደቃቸው (ሮሜ 3፥22-24)።
በአዳም አለመታዘዝ በሰው ዘር ሁሉ ላይ የቀጠለው የኀጢአት በሽታ በኢየሱስ ክርስቶስ መታዘዝ ምክንያት መድኃኒትን አገኝ። በቀደመው አዳም ምክንያት ሙት የሆነው የሰው ዘር በሁለተኛው አዳም ድል አድራጊነት ሕያውነትን ማግኘት የሚችል ሆነ። ለሰው ልጆች የሚገባውን ቅጣት አንዱ ልጁ ተክቶ ተቀበለ፤ በእኛ ዘንድ የሌለውንና ሊገኝብንም ያልቻለውን ፍጽምና ለምናምንበት ሁሉ የእኛ ሆኖ ይቈጠርልን ዘንድ በጸጋው ሰጠን፤ ሰጥቶም የራሱ አደረግን። (ሮሜ 5፥19፤ 2 ቆሮንቶስ 5፥21)።
እግዚአብሔር የሚገዛለትን ሕዝብ በክርስቶስ የመረጠው፣ በምድር ላይ ካለ አንድ ነገድ ወይም ወገን ሳይሆን፣ ልጁን
ሊቀበሉና በስሙ ሊያምኑ ከሚወድዱ የሰው ልጆች ሁሉ፣ በመንፈሱ የዳነን አንድ አዲስን ወገን በመፍጠር ነው።
እግዚአብሔር የሚገዛለትን ሕዝብ በክርስቶስ የመረጠው በምድር ላይ ካለ አንድ ነገድ ወይም ወገን ሳይሆን፣ ልጁን ሊቀበሉና በስሙ ሊያምኑ ከሚወድዱ የሰው ልጆች ሁሉ፣ በመንፈሱ የዳነን አንድ አዲስን ወገን በመፍጠር ነው። ይህም ወገን፣ በቀደመው ኪዳን ከተወደደው የእስራኤል ሕዝብ እንዲሁም ከሕዝቦች ሁሉ ለእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም በኩል በሆነው አዲስ የምሕረት ኪዳን ተቀድሶ ለዘላለም ለእግዚአብሔር የተለየ ሕዝብ ነው። “ሁለቱን አንድ ያደረገ፣ የሚለያየውንም የጥል ግድግዳ ያፈረሰ ሰላማችን እርሱ ነውና፤ ሕግንም፣ ከትእዛዛቱና ከሥርዐቱ ጋር በሥጋው ሻረ። ዐላማውም ከሁለቱ አንድን አዲስ ሰው በራሱ ፈጥሮ ሰላምን ለማድረግ ነው።” (ኤፌሶን 2፥14-15)።
ይህ ሕዝብ የእግዚአብሔር ሕዝብ ወደ መሆን የተሻገረው እራሱ አውቆ መርጦ፣ በየወገኑ ተመራርጦ፣ ወይም ተመራጭ ለመሆን የሚያበቃው ምንም ዐይነት ብልጫ ተገኝቶበት ሳይሆን፣ በእግዚአብሔር ምሕረትና በጎ ፈቃድ ነው። የእግዚአብሔር መንግሥት ዜግነት፣ ማንም ይገባኛል ብሎ ሊጠይቀው የሚችል፣ መብቱ ስለሆነና ስለተገባው የሚያገኘው ዕድል አይደለም። በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን፣ የምሕረቱን መንገድ ለሚቀበል የሰው ዘር በሙሉ ወድዶና ፈቅዶ የከፈተው የማዳን በር ነው (ኤፌሶን 1፥5)።
በእምነት የዘላለማዊ መንግሥቱን ዜግነት ያገኘው ሕዝብ፣ ከባዱ ሸክሙ የተንከባለለለት፣ አእምሮን በሚያልፍ የጌታ ሰላም የሚጠበቅ ሕዝብ ነው። ይህ ሕዝብ ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥና ብርሃን በሚሆንባት፣ እንባና ኀዘን፣ መከራና ስደት፣ ልፋትና ጦርነት በሌለባት አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር፣ የአሁኑን ዓለም ክፉ ቀናት ዐልፎ ለመኖር ይበቃል። በኢየሱስ ክርስቶስ ያመነውም ሕዝብ ተስፋ ይህ ዘላለማዊ ርስት ነው (2 ጴጥሮስ 3፥13)።
በዚህ ዓለም ስለ ስሙ የሚደርስባቸውን ስደትና መከራ ታግሠው ድል ለሚነሱ፣ ለቃሉም ታማኝ ሆነው በመጨረሻዋ
ቀን ለሚገኙ፣ ልዩ ሽልማትና ከአምላክ አንደበት ጎሽታ ከዘላለም ዕረፍትና ሐሴት ጋር ይቈያቸዋል።
የዚህች ዓለም ዕድሜ ዐጭር ነው፤ ደስታዋም ይሁን መከራዋ፣ ውበቷም ይሁን ጕስቍልናዋ ዐላፊ ነው። የእግዚአብሔር ሊሆኑ የሚወድዱ፣ ለዓለምና ለሥጋቸው መሻት ሞተው ላዳናቸው ለኢየሱስ ክርስቶስ ሊኖሩ የሚገባ ነው።
እግዚአብሐር ፈልጎና ዋጋን ከፍሎ የራሱ ያደረጋቸው ሁሉ፣ በተሰጣቸው ወደር የሌለው ሕይወት ፈንታ ሕይወታቸውን መልሰው “ጌታ ነው!” ብለው ላወጁት ኢየሱስ የሰጡ፣ የሕይወታቸውንም መሪ ለእርሱ አሳልፈው ሰጥተው በእርሱ መንፈስ ፈቃድ የሚመላለሱ በፍጹም ልብና ዐሳባቸው ለአምላካቸው የሚገዙ ናቸው። “በሕይወት ያሉትም ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለሁሉ ሞተ።” (2 ቆሮንቶስ 5፥15)።
በዚህ ዓለም ስለ ስሙ የሚደርስባቸውን ስደትና መከራ ታግሠው ድል ለሚነሱ፣ ለቃሉም ታማኝ ሆነው በመጨረሻዋ ቀን ለሚገኙ፣ ልዩ ሽልማትና ከአምላክ አንደበት ጎሽታ ከዘላለም ዕረፍትና ሐሴት ጋር ይቈያቸዋል። በእምነትና በታማኝነት በዚህ ምድር የእርሱ ለሆኑ ልጆቹ ሁሉ፣ በመንግሥቱ ንግሥናና ክብርን፣ እርሱ በሚገኝበት መካከል ለዘላለም መሆንን አዘጋጅቷል። እርሱ የሕዝቡ ርስት፤ ዐብሮነቱም ሽልማታቸው ነው። “ልጆች ከሆን ደሞ ወራሾች ነን፤ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፤ አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን።” (ሮሜ 8፥17)።
Share this article:
We do not need to grasp all that God is doing. In the end, God will show that his ways, so high above our own, were perfect at every turn.
“ኢየሱስ ክርስቶስ የሰዎች ሁሉ ጥልቅ የነፍስ ፍለጋ ነው። ሰው ከእርሱ ጋር ኅብረት ያደርግ ዘንድ ፈጥሮታልና፣ ሰው ያንን ማድረግ በቻለ ጊዜ ብቻ ያርፋል። ሰውም ያንን እስኪያደርግ ድረስ ጥልቅ የሆነውን ክፍተቱን እየሸነገለና ያንንም ለመሙላት የተለያየ ነገርን በማሳደድ በብዙ ይደክማል።” ይህ፣ ዘሪቱ ከበደ “የእግዚአብሔር ሕዝብ” በሚል እያስነበበች ካለችው ጽሑፍ፣ ሦስተኛና የመጨረሻ ከሆነው ክፍል የተወሰደ ነው። ተጨማሪ ያንብቡ፦
” ‘ማን ኦፍ ጋድ መባል አማረኝ’ አለ … ቲቪ ላይ ማፍጠጥ፣ ኮት በሰደሪያ መልበስ፣ ጸጉሩን እንደ አክሱም ሐውልት ማቆም፣ ድምፁን ማጎርነንና መንጎራደድ አብዝቶ ነበረና፡፡” አስናቀ እንድሪያስ ይህን የምኞት ጉዞ እንዲህ ያስቃኘናል።
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society
Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.
2 comments
~ አጠር ያለ አስተያየት(ምናልባትም ጥያቄ ያዘለ አስተያየት)
ፅሑፉ የእግዚአብሔር ሕዝብ ስለተባለው ስለ እስራኤል ህዝብ ያትትና በኋላም ይሄ የእግዚአብሔር ህዝብ ህዝበ ክርስቲያኑ እንደሆነ ፍንጭ እስከነመደምደሚያው ይሰጣል። በዚህ ሃሳብ ላይ የከፋ ተቃርኖ ባይኖረኝም ፁሑፉ የተገነባበት የሃሳብ ሂደትና የታሪክ ፍሰት አለኝ ከምለው መረዳት ጋር ተፋልሶብኛል።
~ እግዚአብሔር የሰው ዘር በሙሉ የእርሱ እንዲሆን አስቦ ፈጠረ (የዚህ ሃሳብ መነሻ ግላዊ ግምታዊ ነፀብራቅ ነው? ወይስ ተፅፎ የሰፈረልን እውነት አለ እንዲህ ደፍረን እንድናገር የሚጋብዘን?!)። እግዚአብሔር በፍጥረት መጀመሪያ ህዝብ የመፍጠር እቅድ ነበረው? ወይስ “ህዝብ” የሚለው ሃሳብ የመጣው ከውድቀት መልስ ነው? ግብታዊ ላለመሆን እሞክራለሁ። በዛው ልክም ግልብ የሆኑ መንደርደሪያ ሃሳቦች መዳረሻቸው የቱጋ ሊሆኑ እንደሚችሉ ሳንርቅ እንታዘባቸዋለን ብዬ እላለሁ።
~’ዐብሮት የሚሆንን፣ የሚመስለውንና የሚያመልከውን ታዛዥ ሕዝብ ፈልጎ አዳምንና ሔዋንን ፈጠረ። እነርሱም በተመቸ ቦታ በዕረፍት ነበሩ፤ ከእግዚአብሔር ጋር በሰላም ነበሩ’ የሚል ተደራቢ ሃሳብ እናገኛለን። ያለኝም ጥያቄ በዛኑ ልክ ነው። መረጃዎቹ ከየት ነው ተሰፍረው የሚመጡት? አዳም ለምን ተፈጠረ? እንደተባለው አብሮ ከ እግዚአብሔር ጋር በአብሮነት ሊኖር!? መስሎ ከሚታይ ግምት ይልቅ በስሎ የሚቀርብልንን ፅሑፍ እኛ አንባቢያን እንሻለን! “ብዙ ተባዙ” የሚለው ቃል የቁጥር ቀመርን ለማስቀመጥ እንዳልሆነ አበዛሃለው በተባለው በአብርሃም ሕይወት ውስጥ አነፃፅረን እናነበዋለን። ምክንያቱም አብርሃም በአንድ ይስሃቅ ነበረና ነው የተሸኘው!
ሌላው አብርሃም የተጠራው እግዚአብሔርን እንዲያመልክ ታስቦ እንደሆነ ፅሁፉ ያለበቂ ማስረጃ እንዲህ ሲል ያስነብበናል።”ሆኖም ግን እግዚአብሔር ምድርን ጨርሶ አላጠፋም። ቅሬታ የሚሆንን ትውልድ መርጦ በዚያም እርሱን የሚያመልክ….” አምልኮ ምንድነው ከሚል ትንታኔ ጋር ምልከታን እና ምላሽን ይፈልጋል። ማን እግዚአብሔርን አመለከ እና ምን ሲያደርግ ነው ህዝብ እግዚአብሔርን አመለከ ብለን ልንል የምንችለው?
መነሻ መንደርደሪያ ሃሳቦቹ ልል ከመሆናቸው የተነሳ መዳረሻ ማሳረጊያ ሃሳቦቹ ሰዋዊ ግምት ላይ ያደሩ መሆናቸውን እናነብበታለን
አሜን። ጌታ አምላክ ሰውን በአምሳያው ፈጠረ። ከአዳም ከዚያም ሔዋን …
ከአብርሃም በፊት ኖህ ቢጠቀስ፤ ከአብርሃም መመረጥ ጋር ገላትያ ም-3 በተያያዥነት ቢጨመር ጥሩ ነው።
– በጣም እናመሰግናለን! ጌታ ኢየሱስ ይባርክሽ። ጸጋውንም ያብዛልሽ! አሜን።