
[the_ad_group id=”107″]
እግዚአብሔርን ያስደነቀና ያስገረመ ነገር ካለ በርግጥም አስገራሚና አስደማሚ ጕዳይ ነው። የእግዚአብሔር ቃል በኢሳያስ 56፥19 ላይ እንዲህ ይላል፡- “ሰውም እንደሌለ አየ፥ ወደ እርሱ የሚማልድ እንደሌለ ተረዳ ተደነቀም …”፡፡ እግዚአብሔር በምንም የማይገረምና የማይደነቅ አምላክ ነው። ታድያ በሰው ልጆች አለመጸለይና አለመማለድ ስለ ምን ይሆን የተደነቀው? የምር ልብ ብለን ብናየው እርሱን ያስደነቀ ነገር እውነትም ድንቅ ነው። በጸሎት ውስጥ ያለው ኀይል ወሰን የማይገኝለት ነው፤ አምሳያም የሌለው ነው። ፀሓይንና ጨረቃን በስፍራቸው ያቆመና ባህርን ከፍሎ እንደ ግድግዳ ያቆመ ኀይል ከጸሎት ውጪ ከየት ሊያገኝ ይችላል? ሙታንን ማስነሣትና አጋንንትን ማስወጣት የሚችል ጉልበት በየትኛውም የምርምር ጣቢያና ዩኒቨርስቲ ውስጥ እንዳለ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አልተሰማም። መናን ከሰማይ የሚያወርድና ውሃን ከዐለት ለማፍለቅ የሚችል ኀይል በታሪክ ውስጥ አልተመዘገበም። ጸሎት ለደካማ ሰዎች የተሰጠ ብርቱ መለኮታዊ ክንድ ነው።
በምድር ላይ የተፈሩ እንደ ኒዩክሌር ያሉ ኀይላት እንኳን ከጸሎት ኀይል ጋር ቢነጻጸሩ በአንዲት ስንጥር ላይ ጠፍታ እንደምትጨስ ደካማ እሳትም አይሆኑም። እስኪ እንዲያው ያሳያችሁ፤ ሰው በብዙ ሺህ ሜጋ ዋት የሚቆጠር የኤሌክትሪክ ኀይል እያለለት በኩራዝ ካልተጠቀምኩ ሞቼ እገኛለሁ ቢል ወይም በደቂቋ የባትሪ ድንጋይ ቤቴንና አካባቢዬን ካላበራሁ ብሎ ቢፎክር፣ እንዴት አያስደንቅ? ሰው በጸሎት በኩል ሙሉ የእግዚአብሔር ኀይል በነጻ ቀርቦለት እያለ፣ በራሱ ደካማ ጉልበት ሲፍጨረጨርና ሲውተረተር ሲታይ እንዴት አያስገርም? በተለይ ሁሉን ለሚችለው አምላክ።
“The Kneeling Christian – By Unknown Author” የተባለው መጽሐፍ ደራሲ ሲናገር፣ “ሁላችንም ወደ ሰማይ ስንሄድ ከሁሉ ይልቅ የእግር እሳት ሆኖብን፣ እየደነቀ የሚያንገበግበን ጕዳይ ምን ያህል አለመጸለያችንና ብንጸልይ ኖሮ ደግሞ ምን ያህል ልንለወጥ እንችል እንደነበርና የለውጥም ምክንያት እንሆን እንደ ነበር ስንረዳ ነው” ይላል። ለዚህም ነው ያዕቆብ በመልእክቱ 5፥16 ላይ ”የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኀይል ታደርጋለች” ሲል፣ የጸሎትን ታላቅ ጉልበት አጥብቆ የጻፈው። የኤልያስንም ሕይወት ምሳሌ በማድረግ፣ “እሱም እንደ እኛ የሆነ ሰው ነበር” በማለት ወደ ድንቁ የጸሎት መስክ እንድንገባ አበክሮ ይጋብዘናል።
የጸሎት ጉልሕና ምትክ የሌለው ተጽዕኖ ሊታይ ከሚገባቸው የሕይወታችን ስፍራዎች አንዱ አእምሯችን ነው። በርግጥ ሰው ሁሉ ስለ አእምሮው መማሩ፣ መረዳቱና አስፈላጊውንም መርሕ ተከትሎ፣ ኮትኩቶ ማሳደጉ በጸሎት ሊተካ የሚችል ጕዳይ አይደለም። ሆኖም ይህንን የሰውን ድርሻ ለመፈጸምም ሆነ መለኮታዊውን አጀንዳ ተረድቶ ለመኖር የጸሎትን ስፍራ ሊተካ የሚችል ምንም ዐይነት የሰው ጥረት ሊኖር አይችልም፤ አይገባምም። ቀደም ብለን እንዳልነው ጌታ አእምሮውን የሰጠን ለእኛ ነው። ምንንነቱን መረዳትና እንዴት እንደሚለወጥ መንገዱን መለማመድም አማራጭ የለውም። በመረዳትም መለወጥ፣ ተለውጦም የለውጥ መሣሪያ መሆን የውስጣችን ረኻብ ሊሆን ይገባል። ይህ ረኻብ ደግሞ ጥልቅ የጸሎትን ጩኸት በውስጣችን ይቀሰቅሳል።
ሰው ምንም ያህል ጥረት ቢያደርግና ቢማስን፣ የእግዚአብሔርን ጥልቅና ድንቅ ሥራ ሊተካም ሆነ ሊበልጥ አይችልም። ከተሠሪው ይልቅ ሠሪው ሥራውን ማስዋብ ወይም መለወጥ፣ ቢያስፈልግም እንደገና መሥራት ይችላል። ለምድራችንም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን፣ ለእያንዳንዳችንም ሆነ ለትውልዱ የገባውን ቃል ለመፈጸም በሚያስፈልገው ዐይነትና መጠን የአእምሮ ለውጥንና ተሓድሶን ማድረግ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው። ሰው በብዙ ዓመትና ልክ በሌለው ድካም የሚሠራውን፣ አምላካችን ግን በግሩም ኀይሉና በአስደናቂ ጥበቡ በቅጽበትና በጥራት እንደሚፈጽመው ጥርጥር የለውም። ልብንና ኩላሊትን የሚመረምር፣ በፊቱ እንዳች የተሰወረ የሌለ ጌታ ምን ይሳነዋል? በጸሎት በፊቱ ለቀረቡት ጉብኝቱና የሚሠራው ተኣምር ልክ የለውም!
የጸሎትን ጉልበት ከአእምሮ ተሓድሶና ለውጥ አንጻር ከማየታችን በፊት ጥቂት ነገሮችን እንደ መነሻ እንመልከት። በመጽሐፍ ቅዱሳችን “አእምሮ”፣ “ልብ”፣ “አሳብ” የሚሉትን ቃላት በምናነብበት ጊዜ በአብዛኛው የሚናገረው ስለ አእምሯችን ነው። የሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ይህንን ያስረግጣሉ፡- “በልባችሁ መታደስ ተለወጡ…” (ሮሜ 12፥2)፤ “… እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን፡፡” (1ቆሮ 2፥16)፤ “በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ይሁን፡፡” (ፊል 2፥5)፤ “አእምሮንም ሁሉ ለክርስቶስ ለመታዘዝ እንማርካለን፡፡” (2ቆሮ 10፥5፤ “‘እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፣ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንአትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ።” (2ቆሮ 11፥3)
ምንም እንኳን ለአእምሮ መታደስና መለወጥ፣ ሰው ሊያደርጋቸው የተገቡ ጠቃሚ ቁልፍ ነገሮች ቢኖሩም፣ እነዚህ ሁሉ ግን ጸሎትን ሊተኩም፣ ሊተካከሉም አይችሉም፤ ምክንያቱም በጸሎት የእግዚአብሔር እጅ የሰውን ልቦናና ሰው የማይደርስበትን ረቂቅ ክፍሉን ይዳስሳልና። ሠሪው ለተሠሪው የራሱን አሳብና አስተሳሰብ ይሞላዋል፤ ልቡን ወይም አእምሮውን በራሱ ቅኝትና አቅም መጠን ይለውጥለታል። መኪናችንን ለቧንቧ ሠራተኛ፣ ቴሌቪዥናችንንም ለአናጺ እንዲያድሱልን ፈጽመን አንሰጥም። ታዲያ አእምሮን የሚያህል መተኪያም ሆነ እኩያ የሌለውን ውድ ስጦታና ሀብታችንን ከእኛ ላልተለዩ፣ እንደ እኛም ግራና ቀኛቸው ለጠፋባቸው ሰዎች አሳልፈን በመስጠት ምን መፈየድ ይቻላል?! እግዚአብሔር ደግሞ የእጁ ሥራ ነውና አእምሮአችንን ሊለውጥና ሊያበለጽግ እጁን ዘርግቶ ይጠብቃል። ከፍ ያለው ንጉሣዊ ጎዳናና የከበረ መንገዱ ደግሞ ጸሎት ነው። ከአእምሮ መለወጥ አኳያ በጸሎት ውስጥ የተሠሩ ሥራዎችን እስኪ እንይ።
በ1ኛ ሳሙኤል ምእራፍ 9 እና 10 ላይ እንደተተረከው ሳኦል ከማይታወቅና ከተናቀ ቤተ ሰብ የመጣ፣ የጠፉትን የአባቱን አህዮች ፍለጋ ሲንከራተት የነበረና እነርሱን እንኳ ማግኘት ያልቻለ እስራኤላዊ ሰው ነበር። በጊዜው ልቡ ቢበረበርና ቢፈተሽ ኖሮ አንዳችም ንጉሣዊ አስተሳሰብና የአእምሮ ደርዝ አልነበረውም። አብሮት ከነበረው ብላቴና ጋር ወደ ሳሙኤል የሄዱት የጠፉ አህዮቹን እንዲያፋልገው ነበር። ሳሙኤል ደግሞ የጠፉት አህዮች ስለ ተገኙ ልብህን አትጣልባቸው ብሎ አረጋጋው። በመቀጠልም “… ባለራእዩ እኔ ነኝ … በልብህ ያለውን እነግርሀለሁ …” (1ሳሙ 9፥19) በማለት፣ እርሱን ራሱን እግዚአብሔር ለንግሥና እንደሚፈልገውና ጊዜውም አሁን እንደ ሆነ ቢነግረው ትንሿ የሳኦል ልብ ድብልቅልቋ ወጣ።
እግዚአብሔር በሳኦል ላይ ያሰበውን ለመፈጸም ካደረጋቸው ነገሮች መካከል ሁለቱ ሳኦልን ከአህያ ፈላጊ የሰፈር ገበሬነት አንሥቶ ወደ የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥነት በመቀየር ከፍተኛ ስፍራ ነበራቸው። አንደኛው፤ “የእግዚአብሔርም መንፈስ በኀይል ወረደበት” (10፥10) የሚለው ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ “ከሳሙኤልም ዘንድ ለመሄድ ፊቱን በመለሰ ጊዜ እግዚአብሔር ሌላ ልብ ለወጠለት…” (10፥9) የሚለው ነው። ይህም በሕዝቡና ቀድሞ በሚያውቁት ላይ የፈጠረው ጥያቄ ቀላል አልነበረም። ጥያቄያቸውም የዘመኑ አባባል እስኪሆን ደርሶ ነበር፤ እንዲህ የሚለው፦ “የቂስን ልጅ ያገኘው ምንድር ነው?” 1ሳሙ 10፥11። ይህንን ጥያቄ የጠየቁት ሳኦልን በአዘቦቱ ቀን የሚያውቁትና ሳሙኤልን ከጐበኘና በቅባትና በጸሎት ሕይወት ውስጥ አእምሮው ተጠምቆ፣ በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ተትረፍረፎ ያዩት ወዳጆቹ ነበሩ።
ሳኦል የታወቀ የጸሎት ሰው ባይሆንም፣ በዘመኑ አስደናቂ የጸሎትና የምልጃ ሰው ከሆነው ካህንና ነቢይ ሳሙኤል ጋር ጊዜ አሳልፎ ነበር። ይህም በ1ሳሙ 10፥12 ላይ“ሳኦል ደግሞ ከነቢያት ወገን ነው እንዴ?” እስኪባል ድረስ ማንነቱን በለወጠ እንግዳ የጸሎት መነቃቃትና ሕይወት ውስጥ አስገብቶት ነበር። ምንም እንኳን ወዲያው ወደ ለመደው የግብርና ኑሮው ቢመለስም፣ በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ አስተሳሰቡ ብቻ ሳይሆን አኗኗሩም ተቀይሮ፣ የእስራኤል ንጉሥና የምድሪቱ መሪ እንደ ሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይነገረናል።
መጽሐፍ ቅዱሳችን ላይ እግዚአብሔር በሰው ጸሎት መደሰቱን በግልጽ ከተገለጸባቸው ጥቂት ቦታዎች አንዱ ይህ ነው። አባቱን በመተካት በቅርብ የነገሠው ወጣቱ ሰሎሞን እግዚአብሔርን ለማምለክ ወደ ገባኦን ኮረብታ በመሄድ መሥዋዕት አቅርቦ ሲመሽ እንደ ልማዱ ወደ አልጋው ሄዶ ነበር። ሌሊት ላይ ባልጠበቀው ሰዓት በተኛበት ቀኑን ሙሉ ላቀረበለት የጸሎትና የአምልኮ መሥዋዕት የመለኮት ምላሽ መጣ። ሰሎሞን በተኛበት እግዚአብሔር ተገለጦ እንዲህ ነበር ያለው፡- “እግዚአብሔርም በገባዖን ለሰሎሞን በሌሊት በሕልም ተገለጠለት እግዚአብሔርም፦ ምን እንድሰጥህ ለምን አለ።” (1ነገ 3፥5)፡፡ ሁሉን የሚችል አምላክ የፈለግኸውን ጠይቅ ሲል በርግጥ መልሱ ቀላል አይሆንም። ደግሞ አንድ ነገር ብቻ ጠይቅ አልተባለም፤ የፈልግኸውን ነገር እንጂ! አትጠይቅ የተባለውም ነገር አልነበረም። ነገሩ የብሩ መጠን እንዳልተጻፈበት፣ ፊርማ ብቻ ተቀምጦበት የተሰጠ ባዶ ቼክ ነበር። ቼኩ ደግሞ የእግዚአብሔር ነውና ስጦታው ወሰንም ልክም የሌለው ነው።
ሰሎሞን የጠየቀው ነገር እግዚአብሔርን እጅግ አስደስቶታል። የጠየቀው ብቻ ሳይሆን ያልጠየቀውም ነገር በእግዚአብሔር ፊት መልካም ሆኖ ነበር የታየው። ያልጠየቀው ነገር ደግሞ ማንም ሰው ቀን ከሌት የሚማስንላቸው ነገሮች ነበሩ፤ “ረጅም እድሜ፣ ብልጽግናና የጠላቶቹን ነፍስ”። እግዚአብሔር ግን ያልጠየቀውንም ነገር አትረፍርፎ ሰጠው። የለመነውን ደግሞ ማንም አይቶት በማያውቀው መጠን ሰጠው። ለብዙ ዘመናት ‘ጥበበኛ አእምሮ’ ይሰጠኝ ብሎ የጠየቀ ስላልነበረም ይመስል፣ ሰሎሞን ሁሉን ሰብስቦ ወሰደው ማለቱ ስሕተት ይሆን? ቃሉ እንደሚለው፣ ”እኔ እንደ ቃል አድርጌልሃለሁ እነሆ፥ ማንም የሚመስልህ ከአንተ በፊት እንደሌለ ከአንተም በኋላ እንዳይነሣ አድርጌ ጥበበኛና አስተዋይ ልቡና ሰጥቼሃለሁ።” (1ነገ 3፥12)።
ከዚህም በላይ እግዚአብሔር ለሰሎሞን የተቀበለውን ጥበብና እውቀት የሚሸከምበትን በባህር ዳር እንዳለ አሸዋ ሰፊ ልብንም አብሮ ሰጠው። “እግዚአብሔርም ለሰሎሞን እጅግ ብዙ ጥበብና ማስተዋል በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋት ሰጠው።” (1ነገ 4፥29) የልብ ስፋት ማለት የስጦታው መያዣ ነው። ዐሥር ሚሊዮን ብር የተሰጠው ሰው ብሩን በትንሽ ኪሱ ሊከትተው ቢታገል፣ ኪሱን ከመቅደድና ብሩን ከመበታተን ሊተርፍ አይችልም። ለዚህም ነው የአእምሮ ትልቅነትና ስፋት የሌለው ሰው ትንሽ እውቀትና ጥቂት ታዋቂነት ሲያገኝ፣ ያቺንው ሚጢጢ ልቡን አሳብጦ በትዕቢት ሊፈነዳ የሚደርሰው። እግዚአብሔር ይዘቱን ብቻ ሳይሆን መያዣውንም አብሮ ይሰጣል። ዛሬ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ይህች ዓለም የአዋቂዎች ብቻ ሳይሆን ሰፊ ልብ ያላቸው፣ ስጦታቸውን በትክክል የሚሸከሙ፣ የተለወጡ ባለ አእምሮዎች ይጎድሏቸዋል። ምንም እንኳ ሰሎሞን በሌላ ኀጢአት ተሸንፎ ጌታን ቢያሳዝንም፣ አስገራሚው ነገር ምን ከሰው ሁሉ የበለጠና በብዙ ጥበብ፣ ዝናና ብልጽግና ቢሞላም፣ በትዕቢት ግን ፈጽሞ አልወደቀም። ጌታ ዛሬም የሰጠንን በትሕትና መሸከም የምንችልበትን የልብ ስፋት ይስጠን።
ይህ ግራና ቀኙን የማያውቅ ወጣት ንጉሥ የጸለየው ጸሎት ምንኛ ኀይለኛ ነበር። እንዴት አንድ ሰው 3000 ምሳሌዎችን ሊያሳካ ይችላል? ደግሞ የሰሎሞን ምሳሌዎች እኮ እኛ እንደምናውቃቸው ተረትና ምሳሌዎች አይደሉም። ለዚህ “መጽሐፈ ምሳሌ” በቂ ማስረጃ ነው። እያንዳንዱ ምሳሌ የአምላክን ጥበብ የሚያንጸባርቁ የሕይወት ፈርጦች ናቸው። ደግሞስ ይሄ ስንት ሥራ የሠራ ንጉሥ በምን ጊዜው ነው 1005 መኃልዮችን/መዝሙሮችን ሊደርስ የቻለው? መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን አስገራሚና ጥልቅ የፍቅር ዜማ ናቸው። መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ 72 እና 127 የሰሎሞን መዝሙሮች እንደ ሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች ይነግሩናል። ተወዳዳሪ የሌለውንና አስገራሚውን፣ በዛሬው ተመን በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚገመተውን፣ በጭቃ ሳይሆን በወርቅና በእንቁ የተለበጠውን፣ ዓለምን ያስደመመው መቅደስ መሃንዲስና ቀያሽ ይኸው ሰሎሞን ነበር። ንግሥት ሳባማ አገር አቋርጣ መቅደሱንና የራሱን ቤት፣ ሥርዐቱንና አኗኗሩን አይታ ነፍስም አልቀረላት ይለናል መጽሐፉ።
ታዲያ ይሄው ጥበበኛ ሰው ይህንን ሁሉ እኔ ሠራሁት አላለም። ምንም እንኳ ከእግዚአብሔር ጋር ዘመኑ ሁሉ የሰላም ባይሆንም፣ ʻየወርቅ ጋሻ ያነገቡ ወታደሮቼና ከግብፅ ያስመጣኋቸው ፈረስና ሠረገሎቼ ጠበቁኝʼ አላለም። በመዝሙር 127፥1-2 እንዲህ ይላል፡- “እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፥ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ፥ ጠባቂ በከንቱ ይተጋል። በማለዳ መገሥገሣችሁም ከንቱ ነው። ለወዳጆቹ እንቅልፍን በሰጠ ጊዜ፥ እናንተ የመከራን እንጀራ የምትበሉ፥ ከተቀመጣችሁበት ተነሡ።” ይህ ልቡ የሰፋለት ሰው መዝሙር ነው።
የእውቀቱ ደርዝ ከዚህም አልፎ እንሰሳትና እጽዋት፣ ዓሦችንና አራዊትን በመጨመር የሥነ ሕይወት ተመራማሪ እንደ ነበር ስናይ ያስገርመናል። ይህ ንጉሥ በዘመኑ በእስራኤል ውስጥ ወርቅን የድንጋይ ያህል ያረከሰና ብልጽግናን የኑሮ ዕለታዊ ክስተት ያደረገ ንጉሥ ነበር። ቃሉ እንደሚለው፣“ንጉሡም ብሩንና ወርቁን በኢየሩሳሌም እንደ ድንጋይ እንዲበዛ አደረገው የዝግባም እንጨት ብዛት በቈላ እንደሚበቅል ሾላ ሆነ።” (2ዜና 1፥15)። ይህ መቼም ህልም እንጂ እውን አይመስልም፤ በተለይ ድንጋይ ወርቅ በሆነበት አገር ለምንኖር። በጸሎት አማካኝነት እግዚአብሔር የአንድ ሰውን እንኳ አእምሮ ሲባርክና ሲለውጥ፣ ድንጋይ ብቻ ሳይሆን ድንጋይ የሚሆነው ወርቁና ብሩም የድንጋይ ያህል ይረክሳል።
ሰው በጸሎቱ ስፍራ ‘ምን እንድሰጥህ ትወድዳለህ?” ለሚለው አምላካዊ ደምፅ አስተዋይ ልቦና ካለ፣ ጌታ አምላክም መንፈሱን ሳይሰፍር፣ የልብ ስፋትንም ሳይመትር በባህር ዳር እንዳለ አሸዋ ይሰጣል። ይህ ሲሆን ሌላው ሊሄድበት ያንገዳገደውን የአምላክ ሥርዐትና መንገድ እሱ/እሷ ከዘማሪው ጋር “ልቤን ባሰፋኸው ጊዜ፥ በትእዛዝህ መንገድ ሮጥሁ” (መዝ 119፥32) ማለት ይችላል። እንደ ቤርያም ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል በሙሉ ልብ ይቀበሉ ዘንድ የሚመረምሩበትን ሰፊ ልብ ይታደላሉ (ሐሥ 17፥11)።
በባዕድ ምድር በምርኮ ላሉት ራሳቸውን ለእርሱ ለለዩና ከፊቱም ለማይታጡ ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ፣ ቅድስናቸውን ጠብቀው ትምህርታቸውን በትጋት ይማሩ ነበርና በጸሎት የተማጸኑት ጌታ አላሳፈራቸውም። “ለእነዚህም ለአራቱ ብላቴኖች እግዚአብሔር በትምህርትና በጥበብ ሁሉ እውቀትንና ማስተዋልን ሰጣቸው፤ ዳንኤልም በራእይና በሕልም ሁሉ አስተዋይ ነበረ።” (ዳን 1፥17)። ይህም ዳንኤል ጾምንና ጸሎትን ቀድሶ ስለ ምድሩና ስለ ሕዝቡ፣ ስለ ራሱም ሲጸልይ ጌታ መልአኩን ልኮ ይጎበኘው ነበር። “እኔም ገና ስናገር ስጸልይ፥ በኃጢአቴና በሕዝቤም በእስራኤል ኃጢአት ስናዘዝ፥ በአምላኬም በእግዚአብሔር ፊት ስለ ተቀደሰው ስለ አምላኬ ተራራ ስለምን፥ ገናም በጸሎት ስናገር አስቀድሜ በራእይ አይቼው የነበረው ሰው ገብርኤል እነሆ እየበረረ መጣ በማታም መሥዋዕት ጊዜ ዳሰሰኝ። አስተማረኝም፥ ተናገረኝም እንዲህም አለ፦ ዳንኤል ሆይ፥ ጥበብንና ማስተዋልን እሰጥህ ዘንድ አሁን መጥቻለሁ።” (ዳን 9፥20-22)።
አሁንም ቢሆን የልዩ ጉብኝት ምሥጢሩጸሎት ነው! ዛሬም ጌታ በቀን ብቻ ሳይሆን በሌሊትም ልጆቹን ይጐበኛል፡፡ ዛሬስ ማነው እንደ ኢሳያስ እንዲህ ብሎ የሚጸልይ? “… እግዚአብሔር የተማሩትን ምላስ ሰጥቶኛል ማለዳ ማለዳ ያነቃኛል፥ እንደ ተማሪዎችም ትሰማ ዘንድ ጆሮዬን ያነቃቃል።” (ኢሳ 50፥4)። ጆሮው የተነቃቃ፣ ምላሱም የተማረ ይህንን ጸሎት ይጸልይ፡- “አሰተዋይ ልቦናን ስጠኝ።”
በሰዎች አእምሮ ላይ የጸሎትን አስገራሚ የመለወጥ ኀይል ከምናይበት ክፍል ውስጥ እስራኤላውያን ከግብፅ ወጥተው ጉዞ በጀመሩበት ጊዜ ያለው ነው። ከአራት መቶ ዓመት በላይ በባርነት ኖረው ነበርና ጡብ ከመጠፍጠፍና ከባርነት የዘለለ ይህ ነው የሚባል እውቀትና ጥበብ ነበራቸው ማለት አይቻልም። የጸሎት ሰው ሙሴ በተራራው ላይ ከተገለጠው እግዚአብሔር ጋር ቆይቶና የመገናኛውን ድንኳን አሠራርና ዕቅድ ይዞ ሲመጣ፣ ለሥራው የሚሆን እቃም ሆነ አቅም አልነበረውም። እግዚአብሔር ደግሞ “በተራራው ላይ እንዳሳየሁህ ለመሥራት ተጠንቀቅ” ብሎት ነበር፤ ድንኳኑ የሰው ሳይሆን የልዑል ነውና! ሙሴ በዚህ ጕዳይ እጅግ እንደ ጸለየ ጥርጥር የለውም፡፡ እግዚአብሔርም ከሕዝቡ መካከል ባስልኤል የተባለውን ሰው በስሙ ጠራው። “በሥራ ሁሉ ብልሃት፣ በጥበብም በማስተዋልም በእውቀትም የእግዚአብሔርን መንፈስ ሞላበት የጥበብን ሥራ ያስተውል ዘንድ፥ በወርቅና በብር በናስም ይሠራ ዘንድ፥ በፈርጥ የሚሆነውን የዕንቍ ድንጋይ ይቀርጽ ዘንድ፥ እንጨቱንም ይጠርብ ዘንድ፥ የብልሃት ሥራውንም ሁሉ ይሠራ ዘንድ።” (ዘፀ 35፥31-33)።
ይህም ብቻ ሳይሆን ለባስልኤልና ለሌላው እስራኤላዊ ኤልያብ ሕዝቡን እንዲያስተምሩና ሥራውን እንዲሠሩ ጥበብን ሞላባቸው፤ እንዲህ እንደሚል፦ “እርሱና የዳን ነገድ የሆነው የአሂሳሚክ ልጅ ኤልያብ ያስተምሩ ዘንድ በልባቸው አሳደረባቸው። በአንጥረኛ፥ በብልህ ሠራተኛም፥ በሰማያዊና በሐምራዊ በቀይም ግምጃ በጥሩ በፍታም በሚሠራ ጠላፊ፥ በሸማኔም ሥራ የሚሠራውን፥ ማናቸውንም ሥራና በብልሃት የሚሠራውን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ በእነርሱ ልብ ጥበብን ሞላ” (ዘፀ 35፥34-35) ይላል። ደግሞም ሕዝቡና አለቆቻቸው በቃችሁ እስኪባሉ ለመገናኛው ድንኳን መሥሪያ አስገራሚ የሆነን ስጦታ ይዘው ይመጡ ነበር። በጥበብ ያልተሞላ ማንም አልነበረም፤ የመሥራትና የመስጠት ጥበብ፤ በምድረ በዳ ምንም በሌለበት ስፍራ እግዚአብሔር ጥበቡንና መልካም አእምሮን ሞልቶባቸው ነበርና። በተራራው ላይ የተጸለየው ጸሎት በሜዳው ላይ ሥራውን እየሠራ ነበር።
በሕዝቡ መካከል የነበሩ ሴቶች ደግሞ ለየት ያለን ጥበብ ይዘው ተገልጠው ነበር፤ ይህም ግሩም ክኅሎትን የሚጠይቅ ነበር። “በልባቸው ጥበበኞች የሆኑ ሴቶችም በእጃቸው ፈተሉ፥ የፈተሉትንም ሰማያዊውን ሐምራዊውንም ቀዩንም ግምጃ፥ ጥሩውንም በፍታ አመጡ። ልባቸውም በጥበብ ያስነሣቸው ሴቶች ሁሉ የፍየልን ጠጕር ፈተሉ።” (ዘፀ 35፥25-26)። ሥራው ያላሳተፈው ሰው አልነበረም፤ ሥራው ያልቀየረው ሰው አልነበረም፤ እንዲህ እንደሚል፦ “ሙሴም ባስልኤልንና ኤልያብን፥ እግዚአብሔርም በልቡ ጥበብን ያደረገለትን በልብ ጥበበኛ ሰው ሁሉ፥ ሥራውንም ለመሥራት ይቀርብ ዘንድ ልቡ ያስነሣውን ሁሉ ጠራቸው።” (ዘፀ 36፥2) የእግዚአብሔርን ሐሳብ እና እንዲሠራ የፈለገውን ዕቅድ በተራራው ላይ በጸሎት ያየው ሙሴ፣ ሥራው ሲጠናቀቅ በተራራው ላይ ያየውን “መንፈሳዊ ምሳሌ” እና ሕዝቡ በሜዳው የሠሩትን አነጻጽሮ ሲያይ ውጤቱ አስገራሚ ነበር። እግዚአብሔር የለወጠውና በጥበብ የሞላው አእምሮ በሰው ሊገመት የማይችለውን ሐሳብ እንኳ ያለ እንከን ሊሠራ ይችላል። “ሙሴም ሥራውን ሁሉ አየ፥ እነሆም አድርገውት ነበር እግዚአብሔር እንዳዘዘው እንዲሁ አድርገውት ነበር ሙሴም ባረካቸው።” (ዘፀ 39፥43)።
በተመሳሳይ ሁኔታ እንደ ሙሴ ሁሉ በጸሎት ትጋቱ የማይታክተው ጳውሎስ በእስር ቤትም ሆኖ በቈላስይስ ላሉ ቅዱሳን ሲጸልይ እንዲህ ይል ነበር፡- “ስለዚሁ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምረን የፈቃዱ እውቀት መንፈሳዊ ጥበብንና አእምሮን ሁሉ እንዲሞላባችሁ እየለመንን፥ ስለ እናንተ ጸሎትን አልተውንም።” (ቈላ 1፥9)። የብሉይ ኪዳኑ ታላቅ ነቢይ ሙሴ አገልግሎቱን በመፈጸሚያው ላይ ተተኪውን ኢያሱን በሕዝቡ ፊት አቅርቦ ሲሾመው እጁን ጭኖበት ነበር፤ “ሙሴም እጆቹን ስለ ጫነበት የነዌ ልጅ ኢያሱ የጥበብን መንፈስ ተሞላ የእስራኤልም ልጆች ታዘዙለት፥ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።” በርግጥ ጸሎት የሰውን አእምሮ በጥበብና በመልካም ነገሮች ሁሉ የሚሞላ ታላቅ ኀይል አለው (ዘዳ 34፥9)።
ጌታ በምድር ላይ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በነበረው የመጨረሻዎቹ ቀናት የነገራቸውን ነገሮች ስናስብ ወደ ልቦናችን የሚመጣው አንዱ ነገር ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ እንዲሰብኩ ዐደራንና ተልእኮን መስጠቱ ነው። ሌላው በጸሎት እየጠበቁ ኀይልን እስኪቀበሉ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ ማዘዙ ሲሆን (ሉቃ 24፥49)፣ ሦስት ዓመት ሙሉ ያስተማራቸውንና ያስታጠቃቸውን ቃልና መጻሕፍት እንዲረዱ አእምሯቸውን መክፈቱ ዐቢዩ ጕዳይ ነበር። “በዚያን ጊዜም መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሯቸውን ከፈተላቸው።” (ሉቃ 24፥45)። ይህም የሚመጣው የመንፈስ ቅዱስ ኀይል በእነርሱ ላይ ሲወርድ የቃሉን የመረዳት ባለጠግነት በመገለጥና በኀይል እያጨቁ በአይሁድም ሆነ በአሕዛብ ሁሉ ልብ ወይም አእምሮ ውስጥ እንዲሞሉት ነው።
ጸሎት አእምሮን ይለውጣል፣ ያሰፋል፣ ይሞላል፤ ደግሞ በአስደናቂ ሁኔታ ይከፍታል። በጸሎት የተከፈተ አእምሮ የሰማይን ሀብትና ሐሳብ ያለመከልከልና ያለ መያዝ ወደ ምድር መድኃኒትና መፍትሔ በሚሆን መንገድ መልቀቅ ይችላል። የብዙ ሥጦታዎችና ራእዮች አለመተግበር ምክንያቱ፣ መከፈታቸውን የሚጠባበቁ ወይም ያልተከፈቱ አእምሮዎች ናቸው። አእምሯችን ሲከፈት በመንፈሳችን የሚቃጠለው፣ በውስጣችን የተከማቸው ሕልምና ረኻብ ሁሉ መውጫና መገለጫ ያገኛል። አሁንም ጸሎት ዐይነተኛው መንገድ ነው።
ዛሬ ሰዎች በአቋራጭና ጽድቅ በጎድለው አማራጭ፣ በራስም ከንቱ ጥረት ዐላማቸውን ሊያደርሱ ይቅበዘበዛሉ። መማርና ማንበብ፣ መጣርና መሥራት መልካም ነው። በጸሎት ውስጥ ግን ያለ ከንቱ አቋራጭና ፍሬ ቢስ ጊዜ ማቃጠል፣ እግዚአብሔር ያዘጋጀው የጽድቅ ጎዳናና ቀና መንገድ አለ። ይህ መንገድ ያልተለመደ ስኬትንና ልክ የሌለው መንፈሳዊና አካላዊ በረከቶችን የተሞላ ነው።
የሉቃስ ወንጌልንና የሐዋርያት ሥራን የጻፈው ሐኪም ሉቃስ በጌታም ሆነ በሐዋርያት ሕይወት የጸሎትን ድርሻና ተጽዕኖ በግልጽ ለወዳጁ ቴዎፍሎስ ይተርክለታል። ጌታ አእምሯቸውን እንዲከፍትላቸውም ሆነ ከከፈተላቸው በኋላ መንፈስ ቅዱስ በኀይል እንዲወርድባቸውም ሆነ ከወረደባቸው በኋላ፣ የጸሎትን መካከለኛ ስፍራ ደጋግሞ ያሳያል። በብሉይና አዲስ ኪዳን መካከል አራት መቶ ዓመታት መንፈሳዊ ዝምታ ነበረ። የሐዋርያት ዘመን ታላላቅ የግሪክ ፈላስፎች አስተሳሰብ የገነነበት፣ አስገራሚው የሮም ፖለቲካዊ አገዛዝ ሁሉን በመዳፉ ሥር ያስገባበትና እጅግ የከረረው የአይሁድ ሃይማኖተኝነት የጦዘበት ጊዜ ነበር። ይህም በአጭር ቃል እግዚአብሔር ዝም ባለበት 400 ዓመታት ውስጥ የሰው ድምፅ የገነነበት ዘመን እንደ ነበር ያሳያል።
በዚህ ጊዜ ነው እንግዲህ ይህንን ሁሉ ተራራ አልፈው የወንጌል ዐደራ የተሰጣቸው። ከኢየሩሳሌም ጀምሮ እስከ ምድር ዳርቻ ምስክርና የጽድቅ አምባሳደሮች እንዲሆኑ ተልእኮ የተቀበሉት። ለዚህ ደግሞ የታደሰና የተከፈተ አእምሮ በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ከተቀጣጠለ መንፈስ ጋር የግድ አስፈላጊ ነበር። የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን በርግጥም የጸሎት ማኅበር ስለ ነበረች ተግዳሮትን ሁሉ እየሰባበረች የተልእኮዋን ሰማያዊ እሳት ከመንግሥቱ ቃል ጋር እያጋመች በስፍራ ሁሉ ማድረስ ችላ ነበር። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እስከ መጨረሻው ምእራፍ ድረስ ጸሎት መካከላኛ ነው። በጸሎት የተጀመረ ሥራ በጸሎት ይቀጣላል፣ በጸሎትም ብቻ የድል ፍጻሜ ያገኛል። ለዚህም የሚቀጥሉት የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ክፍሎች ቋሚ ምስክር ናቸው፡- (1፥14፤ 2፥1፡5፤ 3፥1፤ 4፥21፡31፤ 6፥4፤ 8፥2፤)
ጌታ ጸለየ፤ ሐዋርያት ጸለዩ፤ እግዚአብሔር በዘመናት ታላላቅ ሥራን የሠራባቸው ሰዎች ሁሉ እየጸለዩ ዐልፉ። እኛም ዛሬ ለመለወጥም ሆነ በሥራችንና በምድራችን ፈጣንና ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለማምጣት ጸሎት ታላቁ ጎዳና ነው። በአእምሯችንም ሆነ በመንፈሳችን መጸለይ መልካም ነው። ግን ደግሞ ስለ አእምሯችን በጥብቅና በብዛት መጸለይ ውጤቱ በመለኮታዊ ጎዳና ላይ መሄድ መሆኑን እንወቅ። “ለምኑ”፣ “ፈልጉ”፣ “አንኳኩ” ተብለናልና እስክንቀበል፣ እስክናገኝና እስኪከፈትልን ድረስ አጥብቀን በእምነት መለመን አለብን። ጌታ እንዳለው ለሚለምን ሁሉ ይሰጠዋል፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ ለሚያንኳኳም ይከፈትለታል። እግዚአብሔር የተባረከ፣ የተከፈተ፣ የተለወጠና በሐሳቡ የተሞላ ጠቢብ ልብ ይስጠን።
Share this article:
መጋቢ በድሉ ይርጋ (ዶ/ር)፣ ‘የሐሰተኛ ነቢያት እና መምህራን አድራሻ የት ነው?’ ሲሉ ይጠይቃሉ፤ ምላሹንም ከመጽሐፍ ቅዱስ ፈልገው ያቀርባሉ፤ የሐሰተኞቹ መገኛ ምካቴውን አስቸጋሪ እንዳደረገውም ያመለክታሉ።
ከፍቺ በኋላ በተፈጠረብኝ ተስፋ ቢስ ስሜት፣ ሕይወት ዳግም ተመልሶ እንዴት መልካም ሊሆን ይችላል ብዬ ዐስብ ነበረ። ባዶ እና የደረቅሁ ነበርሁ።
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society
Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.
Add comment