[the_ad_group id=”107″]

የትንሣኤው ዐዋጅ

ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ መነሣቱ የሚታሰብበት የትንሣኤ በዓል በክርስቲያኖች ኹሉ ዘንድ በምስጋናና በዝማሬ በታላቅ ድምቀት ይከበራል። በኢኦተቤ ትውፊት መሠረት ከዘጠኙ የጌታ ዐበይት በዓላት መካከል አንዱና ታላቁ በዓል የትንሣኤ በዓል ነው። በቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመናን ዘንድ በዓሉ አስቀድሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመውን ጾም በማሰብና በመጾም፥ በመጨረሻም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለድኅነተ ዓለም በአይሁድ እጅ የተቀበለውን መከራና ሥቃይ የሚያስታውሰውን ሰሙነ ሕማማት (የሕማማት ሳምንት) በማስቀደም፥ በመጨረሻም ሞትን ድል አድርጎ የተነሣውን ጌታ በዝማሬዎች በመወደስና ትንሣኤ ክርስቶስን በማወጅ ይከበራል። ልዩ ልዩ ሃይማኖታውያንና ባህላውያን ሥነ ሥርዐቶችም የበዓሉ አካላት ናቸው።

ምንም እንኳ በዓለ ትንሣኤ አንድ ቀን የሚከበር በዓል ቢኾንም፥ በዓሉ እስከ ኀምሳኛው ቀን (በዓለ ጰራቅሊጦስ) ድረስ በዓለ ፋሲካ ኾኖ ነው የሚሰነብተው። ኀምሳኛው ዕለትም እንደ መጀመሪያው ዕለተ ትንሣኤ በትንሣኤ ቀለም (ሥርዐተ አምልኮት) ይከበራል። ሰውኛ ዘይቤን በመጠቀም ቅዱስ ያሬድ ምድር በክርስቶስ ደም ታጥባ ፋሲካን የምታደርግ መኾኑን በዝማሬው እንዲህ ሲል ገልጧል፤ “ … ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሐጺባ በደመ ክርስቶስ – ምድርም በክርስቶስ ደም ታጥባ ፋሲካን ታደርጋለች” (መጽሐፈ ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ ገጽ ፪፹፱)።  “ፋሲካ” ሲባል ፋሲካችን ክርስቶስ መታረዱን መሠረት ያደረገ (፩ቆሮ. ፭፥፯) የመድኀኒታችን የትንሣኤው መታሰቢያ መኾኑን ነው የሚያመለክተው፤ “. . . ፋሲካ ተዝካረ ትንሣኤሁ ለመድኀኒነ – . . . ፋሲካ የመድኀኒታችን የትንሣኤው መታሰቢያ ነው” እንዲል ቅዱስ ያሬድ (ዝኒ ከማሁ ገጽ ፪፻፺)።

ዘወትር እሑድን ሳይለቅ በየዓመቱ በሚከበረው በዓለ ትንሣኤ ከሚታዩት ልዩ ልዩ ትእምርታዊነት ካላቸው ነገሮች ባሻገር፥ አንድ ጊዜ የተከናወነውና የምሥራቹን ላልሰማና በእምነት ላልተቀበለው ኀጢአተኛ ሰው በቄሱ አማካይነት ለሕዝቡ የሚታወጀው የትንሣኤ ዐዋጅ (ትንሣኤ፤ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሥር የሚካሄድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሐዋርያዊ ድርጅት ፲፱፻፷፫፣ ገጽ ፳፩) ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው። ዐዋጁ በበዓለ ፋሲካ ለኀምሳ ቀናት የሚታወጅ ነው።

ዐዋጁ እንዲህ የሚል ነው፦ ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን

በዐቢይ ኀይል ወሥልጣን

አሰሮ ለሰይጣን አግዐዞ ለአዳም

ሰላም እም ይእዜሰ ይኩን ሰላም

ትርጕም፦ “ክርስቶስ በታላቅ ኀይልና ሥልጣን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ።

ሰይጣንን አሰረው፤ አዳምን ነጻ አወጣው፡፡

ሰላም ከእንግዲህ ወዲህ ሰላም ይኹን” (መጽሐፈ ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ ፲፱፻፹፰፣ ገጽ ፪፻፹፱)

ይህ ዐዋጅ በቅዱስ ያሬድ ድጓ ላይ የሚገኝ ሲኾን፣ ከበዓለ ትንሣኤ እስከ በዓለ ኀምሳ ድረስ በቅዳሴ ላይ ቄሱ ከሕዝቡ ጋር በመቀባበል በግእዝ በንባብ ያውጀዋል። ዐዋጁን በሥርዐተ ቅዳሴ ውስጥ የሚፈጸም ሥርዐት ብቻ አድርጎ ከመመልከት ዐልፎ፣ ምን ያኽሉ ሰው አስተውሎት ይኾን? ምን ያኽሉስ የክርስቶስ ትንሣኤ ያስገኘለትን ጽድቅ ተቀብሎ ይኾን? ስንቱስ ሰው በዐዋጁ ምክንያት የነፍሱን ነጻነት ተጐናጽፎ ይኾን? የሚሉት ዐዋጁን በሚሰሙ ኹሉ ዘንድ ሊመለሱ የሚገባቸው ጥያቄዎች ናቸው። የዐዋጁ መልእክት እነሆ!

፩. “ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን በዐቢይ ኀይል ወሥልጣን”

“ክርስቶስ በታላቅ ኀይልና ሥልጣን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ።” ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ የተነሣው ʻመቃብር ክፈቱልኝ፤ መግነዝ ፍቱልኝʼ ሳይል በታላቅ ኀይልና ሥልጣን ነው፡፡ ይህ የዐዋጁ የመጀመሪያ ነጥብ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ መነሣቱን ብቻ ሳይኾን፣ የተነሣበትን ኹኔታ ጭምር ነው የሚገልጠው። ትንሣኤው በታላቅ ኀይል እና ሥልጣን የተከናወነ ነው። ከእርሱ በፊትም ኾነ በኋላ በሞት ላይ ኀይሉንም ኾነ ሥልጣኑን ማሳየት የቻለ ኀይለኛም ኾነ ባለሥልጣን አልተነሣም፤ አይነሣምም። በዚህ ዓለም ኀያላን የተባሉ ብዙዎች፥ ባለሥልጣን የነበሩ ብዙዎች፥ በዘመናቸው ኀይላቸውንና ሥልጣናቸውን በሌላው ላይ ሲያሳዩ የነበረ ቢኾንም፥ በሞት ላይ ግን ማሳየት አልቻሉም። ኹሉንም ሞት ገዛቸው፤ ሠለጠነባቸውም። እርሱን ግን ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለም (ሐ.ሥ. ፪፥፳፬)። ቅዱስ ያሬድም፥ “አርአየ ሥልጣኖ ላዕለ ሞት ገባሬ ሕይወት ክርስቶስ። – ሕይወትን የሠራ ክርስቶስ ሥልጣኑን በሞት ላይ አሳየ” ሲል ጌታ በሞት ላይ ያሳየውን የሥልጣኑን ታላቅነት መስክሯል (መጽሐፈ ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ ፲፱፻፹፰፣ ገጽ ፪፻፺፭)። 

በሐዲስ ኪዳን ዘመን እግዚአብሔር ታላቅ ኀይሉንና ሥልጣኑን ያሳየው በክርስቶስ ትንሣኤ መኾኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሌሎች ሰማያውያንና መንፈሳውያን ነገሮችን ጨምሮ ይህን የኀይሉን ታላቅነት ያውቁ ዘንድ እንደሚጸልይላቸው ለኤፌሶን ሰዎች በተናገረበት ክፍል፥ “ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው፥ ከአለቅነትና ከሥልጣንም፥ ከኀይልም፥ ከጌትነትም ኹሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይኾን፥ ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ኹሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው፥ በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጕልበት ይታያል፤” ብሏል (ኤፌ. ፩፥፳-፳፩)። የትንሣኤውን ኀይል ታላቅነት የመሰከረው ይኸው ብፁዕ ጳውሎስ መልሶ፥ “እርሱንና የትንሣኤውን ኀይል እንዳውቅ … እመኛለሁ” (ፊል. ፫፥፲፡፲፩) ሲል፥ ኀይለ ትንሣኤው ከመታወቅ የሚያልፍ እጅግ ታላቅ መኾኑንና ገና እንዳላወቀውም ግልጽ አድርጓል። ኀይለ ትንሣኤው እግዚአብሔር የብርታቱን ጕልበት ያሳየበት ታላቅ ክሥተት በመኾኑ፥ እኛም ዘወትር እንደ ጳውሎስ እርሱንና የትንሣኤውን ኀይል ለማወቅ መፈለግና መመኘት አለብን። 

ቤዛችን ኢየሱስን ከሙታን በመነሣቱ፥ የእግዚአብሔር ታላቅ ኀይልና ሥልጣን መታየት ብቻ ሳይኾን፥ ለእኛ ያስገኘልን ብዙ ሰማያዊና መንፈሳዊ በረከት አለ። “ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ” ተወልደናል (፩ጴጥ. ፩፥፫-፭)።    በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብረን፥ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችን፥ ከእርሱ ጋር ተነሥተናል (ቈላ. ፪፥፲፪)። አበውም፥ “ወበትንሣኤሁሰ አንሥአነ ለነ ለእለ ተረፍነ ወነበርነ ውስተ ጽልመት ወጽላሎተ ሞት። – በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ የነበርነውንና በዚያ የቀረነውን እኛን በትንሣኤው አስነሥቶናል።” ሲሉ መስክረዋል (ሃይማኖተ አበው ዘዮሐንስ ምዕራፍ ፻፫ ቍ. ፲፯፤ ገጽ ፬፻፵፱)።   

፪. አሰሮ ለሰይጣን አግዐዞ ለአዳም

“ሰይጣንን አሰረው፤ አዳምን ነጻ አወጣው።” እግዚአብሔር ታላቅ ኀይሉንና ሥልጣኑን ባሳየበት በክርስቶስ ትንሣኤ በሞት ላይ ሥልጣን የነበረውን ሰይጣንን እንዳሰረውና ለሞት ተገዝቶ የነበረውን አዳምን ደግሞ ነጻ እንዳወጣው ይህ የዐዋጁ ነጥብ ይመሰክራል። እርሱ መድኀኒታችን ሰው ኾኖ የመጣው በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን ዲያብሎስን በሞቱ ለመሻርና፥ “በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ” ለማውጣት መኾኑ ተጽፎአል (ዕብ. ፪፥፲፬-፲፭)። ይህም የተረጋገጠው በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነው። ስለዚህ ትንሣኤ ሰይጣን ድል የተነሣበትና ሥልጣኑን የተገፈፈበት፥ በእርሱ ሥልጣን ሥር ለነበሩ ሰዎች ደግሞ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻ የወጡ መሆናቸው የታወጀበት ድል ነው። 

ክርስቶስ በሞቱና ሞትን ድል አድርጎ በመነሣቱ ሰይጣንን ድል ነሥቶታል፤ ለሰው ልጆችም ዐርነትን ዐውጇል። ይኹን እንጂ ሰው ከሰይጣን አገዛዝ ነጻ ሊወጣ የሚችለው፥ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ (በክርስቶስ ሞት የኀጢአቱ ዕዳ እንደ ተከፈለለት እና በክርስቶስ ትንሣኤም መጽደቁ እንደ ተረጋገጠለት ሮሜ ፬፥፳፫-፳፭) ሲያምን ነው። ዛሬ ማንም በሕይወቱ ይህ የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ካልታወጀለትና ካላመነው ከሰይጣን አገዛዝ ነጻ ሊወጣ አይችልም። በቅዱስ ወንጌልም ይህ ድል አድራጊ የትንሣኤው ጌታ “ዘየአምን በወልድ ቦ ሕይወት ዘለዓለም፤ ወዘሰ ኢየአምን በወልድ ኢይሬእያ ለሕይወት ዘለዓለም አላ መቅሠፍተ መዓቱ ለእግዚአብሔር ይነብር ላዕሌሁ። – በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።” ሲል ከዚህ ውጪ ነጻ መውጣት እንደሌለ ግልጽ አድርጓል (ዮሐ. ፫፥፴፮)።

ምናልባት በጊዜው እንደ ነበሩት አይሁድ እኛም “የአብርሃም ዘር ነን ለአንድም ስንኳ ከቶ ባሪያዎች አልኾንም” በሚለው መንፈስ ተይዘን ይኾናል። በምድር የተከበረ ማንነት፥ ወይም ስመ ሃይማኖት ሊኖረን ቢችልም እንኳ፥ በኀጢአት ምክንያት በባርነት ውስጥ እንደምንኖርና ነጻ መውጣት እንደሚያስፈልገን መዘንጋት የለበትም። ከዚህ ነጻ የሚያወጣን ደግሞ እርሱ ብቻ መኾኑን በሚከተለው ቃሉ አረጋግጦልናል፤ “ልጁ ዐርነት ቢያወጣችሁ በእውነት ዐርነት ትወጣላችሁ።” (ዮሐ. ፰፥፴፫-፴፮)። በክርስቶስ ነጻ የወጣንም፤ ጸንተን መቆምና ዳግም በባርነት ቀንበር እንዳንያዝ መጠንቀቅ ይገባናል (ገላ. ፭፥፩)።        

፫. ሰላም እም ይእዜሰ ይኩን ሰላም

“ሰላም ከእንግዲህ ወዲህ ሰላም ይኹን” በክርስቶስ ትንሣኤ ሰላም ኾኗል፤ ይህ የዐዋጁ የመጨረሻው ነጥብ ነው። ጌታ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ በዝግ ቤት ተሰብስበው ወደ ነበሩት ደቀ መዛሙርት ገብቶ የተናገረው ቃል “ሰላም ለእናንተ ይኹን” የሚል የምሥራች ነው (ዮሐ. ፳፥፲፱)። ይህ ተራ ሰላምታ ብቻ ሳይኾን፥ በሞቱና በትንሣኤው አማካይነት በእግዚአብሔርና በእነርሱ መካከል ሰላምን ማውረዱን የሚያመለክትም ነው። ከሙታን ተለይቶ የተነሣው ቤዛ ኵሉ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ይዞት የመጣው ታላቅ የምሥራች ሰላም ነው። ኀጢአት ባለያያቸው በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ገብቶ በፈጸመው የቤዝዎት ሥራ ሰላም ወርዷል። እግዚአብሔርና ሰው ታርቀዋል፤ በመካከላቸው ሰላም ኾኗል። የትንሣኤው ዐዋጅም ይህ ሰላም ያልደረሳቸውና ይህን ሰላም ያልተቀበሉት ይህ ሰላም እንዲደርሳቸው የሚታወጅ ነው።

በዚህ ዓለም ሰውን ሰላም የሚነሡ ብዙ ነገሮች ቢኖሩም፥ የእነዚህ ኹሉ ነገሮች መሠረቱ ግን ሰው ከእግዚአብሔር አለመታረቁ ነው። ሰው የኀጢአቱ ዕዳ በክርስቶስ ሞት እንደ ተከፈለለትና ጽድቁም በትንሣኤው እንደ ታወጀለት ካልተረዳና የራሱ አድርጎ ካላመነው፥ የቱንም ያኽል ሃይማኖተኛ ቢኾን፥ የቱንም ያኽል በጎ ምግባር ቢኖረው ውስጣዊ ሰላም አይኖረውም። ኹልጊዜ እኔን እግዚአብሔር ተቀብሎኛል ወይ? ወደ መንግሥቱስ እገባለሁ ወይ? የሚለውን ጥያቄ ራሱን በራሱ ሲጠይቅ፥ ወይም ጥያቄው በሌሎች ሲቀርብለት እርግጠኛነት አይሰማውም፤ ይህ ከሌሎቹ ሰላም ከነሡት ነገሮች ጋር ተደምሮ የውስጥ ሁከቱ እንዲጨምር ያደርጋል። ስለዚህ የእግዚአብሔር ሰላም ለእርሱ ያልደረሰለት ኀጢአተኛ ሰው በእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ሞት ከእግዚአብሔር ጋር መታረቁን ማመንና መቀበል አለበት። ያን ጊዜ ለእርሱ ሰላም ይኾናል። 

የሰላም ንጉሥ የሆነው ሰላማችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ “ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም።” የሚል ተስፋን ሰጥቷል (ዮሐ. ፲፬፥፳፯)። በወንጌል በኩል የሚሰበከውን ይህን ሰላም መቀበልና ወደ እግዚአብሔር ዕረፍት መግባት በክርስቶስ ትንሣኤ ተረጋግጧል። “ይእዜኒ ለሰላም ንትልዋ መድኀኒነ ተንሥአ ነዋ፤ – እነሆ መድኀኒታችን ተነሥቷልና አኹን ሰላምን እንከተላት።” (መጽሐፈ ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ ፲፱፻፹፰፣ ገጽ ፪፻፺)።

ማጠቃለያ

የትንሣኤ በዓል ታላቅ ደስታ የሚደረግበት በዓል ነው። ነገር ግን የደስታው ምክንያት ምንድነው? ክርስቶስ ከሙታን መነሣቱ እና በመነሣቱ የሚያምኑበት ሰዎች ከሞት ወደ ሕይወት፥ ከሰይጣን ባርነት ወደ እግዚአብሔር ልጅነት መሸጋገራቸው ነው። ለሰው ከዚህ የሚበልጥ ትልቅ ነገር ከቶ የለም። በትንሣኤ በዓል የመደሰታችን ምክንያቱ ይህ ሊኾን ይገባል። ይህን ማእከል ያላደረገ “ደስታ” ግን በትንሣኤው የተገኘ ሳይኾን ምክንያቱ ሌላ ነው።

በኢኦተቤ ትንሣኤ የደስታና የሐሤት በዓል መኾኑ ተደጋግሞ ተመልክቷል። ቅዱስ ያሬድ በድጓው ላይ፥ “ዛቲ ዕለት ዐባይ ፋሲካ ተዝካረ ትንሣኤሁ ለመድኀኒነ ንፌኑ ስብሐተ ንጹሐ ጸሎተ በትፍሥሕት ወበሐሤት ንግበር በዓለ ፋሲካ እንተ ባቲ አብ አንሥኦ ለወልዱ እሙታን። – ይህች ዕለት የመድኀኒታችን የትንሣኤው መታሰቢያ የሚደረግባት ታላቅ ፋሲካ ናት። ንጹሕ ምስጋናን፥ ጸሎትንም እናቅርብ፤ አብ ልጁን ከሙታን ያነሣባትን የፋሲካ በዓል በደስታና በሐሤት እናድርግ” ይላል። (መጽሐፈ ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ ፲፱፻፹፰፣ ገጽ ፪፻፺)። በዚህም የበዓሉ ምክንያት ምን እንደ ኾነ፥ በዓሉ በምን መንገድ መታሰብና መከበር እንዳለበት ግልጽ አድርጓል።

ይኹን እንጂ ብዙ ጊዜ ከመንፈሳዊው ጉዳይ ይልቅ ባህላዊው ስለሚያመዝን፥ ብዙዎች በዓሉን በሥጋዊ ፈንጠዝያ እንጂ መንፈሳዊ ይዘቱን ጠብቀው በትንሣኤ ክርስቶስ ያገኙትን ሰላምና ዕረፍት እያሰቡ የትንሣኤውን ጌታ በምስጋናና በአምልኮት አያከብሩትም። ይህም ትልቅ ኪሳራ ከመኾኑም በላይ፥ ሰማያዊውን በምድራዊ መንፈሳዊውን በሥጋዊ ነገር መለወጥ ይኾናል። ስለዚህ የትንሣኤውን በረከት በመረዳት በዓለ ትንሣኤውን በተገቢው መንገድ ማወቅና የትንሣኤውን ጌታ ማክበር ይገባል። በዓሉ ሲከበር ዐዋጁ ከቶም ሊዘነጋ አይገባም። ወይም ደግሞ ዐዋጁ እንደ ዐዋጅ መታየቱ ቀርቶ ወግና ልማድ ወደ መኾን ደረጃ ዝቅ ማለት የለበትም። እንዲያ ከኾነ የትንሣኤው መልእክት ከሰዎች ሳይደርስና ሰዎችም ሳይጠቀሙበት ይቀራሉ።

Yimrhane Kirstos

ዘመነ አስተርእዮ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዓመቱን በወቅቶች ከፋፍላ፥ በዚያ ላይ የተመሠረቱ መዝሙሮችን በግእዝ ለእግዚአብሔር በማቅረብና ድንቅ ሥራውን በመዘከር ትታወቃለች። ለዚህም በስድስተኛው ምእት ዓመት የተነሣው የዜማ ደራሲ ቅዱስ ያሬድ ከብሉያትና ከሐዲሳት (ከመጽሐፍ ቅዱስ)፣ ከሊቃውንትና ከመሳሰሉት መጻሕፍት ለምስጋናና ለጸሎት የሚስማሙ ንባባትን በመውሰድና ለዜማ ተስማሚ በማድረግ፥ በአራቱ ክፍላተ ዘመን እንዲነገሩ ማዘጋጀቱን የዜማ ሊቃውንት ያስረዳሉ (ጥዑመ ልሳን /ሊቀ ካህናት/ 1981፣ 28)። አራቱ ክፍላተ ዘመን የተባሉትም በዓመት ውስጥ የሚገኙት አራቱ ወቅቶች ናቸው፤ እነርሱም መፀው (ወርኀ ጽጌ ዘመነ ጽጌ/አበባ)፣ ሐጋይ (በጋ)፣ ጸደይ (በልግ) እና ክረምት ሲኾኑ፣ አኹን የምንገኘው ከአራቱ ክፍላተ ዘመን ኹለተኛው ክፍል በኾነው በበጋ (ሐጋይ) ላይ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ

ፍቅርን የመግለጫ መንገዶች

በፍቅር የተጋመዱ ጥንዶች ትሥሥራቸውን አስመልክቶ ጥያቄዎችን ማንሣታቸው አይቀርም። አንዳንዱ ጥያቄ የሚሰነዘረው ለአፍቃሪው ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ መልስ ከተፈቃሪው ይሻል። ከሚነሡት ጥያቄዎች መካከል አንደኛው “የፍቅር ጥያቄ” ነው። ራሳችንን፣ “በርግጥ አፈቅራታለሁኝ?”፣ “እሷስ ከልቧ ታፈቅረኛለች?” እንላለን። መነሾው ቢለያይም፣ በደስታ መኻል ስንቅር የሚል ጥያቄ እንደ መሆኑ ያስጠላል፤ ያስፈራልም። ሲ. ኤስ. ሊዊስም፣ “ፍቅር በሕይወታችን ካለ ጽኑና ቀጣይ ደስታ ከዐሥሩ የዘጠኙን እጅ ድርሻ ይወስዳል” እንደ ማለቱ ጥያቄው አይናቅም።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.