በዕለቱ ከደብረ ዘይት ከአንድ አገልግሎት እየተመለስኩ እንደ ነበር አስታውሳለሁ። ነገር ግን አቃቂ አካባቢ በሚገኝ አንድ የሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ በአምልኮ ርእሰ ጕዳይ ላይ ውይይት እንደሚካሄድ ስለ ሰማሁ ወደዚያው አመራሁ። ዝግጅቱ 11፡00 ሰዓት ላይ እንደሚጀመር ቢነገርም፣ ከታዳሚው ለሚሰነዘሩ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጡ ከሌላ ስፍራ ከተጋበዙት ሁለት አገልጋዮች እና ከአዘጋጆቹ በቀር አዳራሹ ባዶ ነበር። ሰዓቱ 11፡30 ሆነ፤ አንድ አምስት ሰዎች ብቻ ብቅ ብለዋል። ተጋባዦቹ ሰዓታቸውን ጠብቀው ሲገኙ፣ የታዳሚዎቹ መዘግየት አዘጋጆቹን አስጨንቋቸዋል። 12፡00 ሰዓት ሆነ። አሁንም ግን የተገኙት ሰዎች ከዐሥር አይበልጡም። አዘጋጆቹ ወጣ ገባ ማለት አብዝተዋል። 12፡15 ደረሰ። የረባ ለውጥ የለም። ምናልባት ዝግጅቱ ከዚህም በላይ ከተራዘመ፣ አቋርጬ ለመሄድ ስለምገደድ ሁኔታውን ለማጣራት እና ከሁለቱም ተጋባዦች ጋር ስለምንተዋወቅ ሰላም ለማለት ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ የአገልጋዮች ቢሮ አቀናሁ። ሰላም ተባብለን ከመጨረሳችን፣ አዘጋጆቹ ጕባኤውን አስጀምረው ተጨማሪ ሰዎች ይገኙ እንደ ሆነ በዝማሬና በጸሎት ጥቂት ጥበቃ ለማካሄድ ተስማምተው ወጡ። ከተጋባዥ አገልጋዮቹ ጋር አጠገብ ለአጠገብ ተቀምጠን ስለ ሰዓት ግንዛቤአችን ጨዋታ ጀመርን። ከዚያ የዕለቱ ርእሰ ጕዳይ ወደ ሆነው የአምልኮ ጥያቄ ሳይታሰብ አመራንና አንደኛው አገልጋይ ሐሳቡን በረጅሙ አጫወተኝ …
* * *
ወቅቱ ለሰርጌ የምሯሯጥበት ነበር፤ “አልሞላልህ” ያሉኝን ነገሮች የማሳደድ እና ከማግባቴ በፊት ማተሚያ ቤት ለመስደድ የወሰንኩትን መጽሐፍ የማጠናቀቅ ትግል ይዣለሁ። ሰርግ የምጠራቸው አንዳንድ የቅርቤ ሰዎች ጋብቻዬን የት እንደምፈጽም ከተረዱ በኋላ ይጠይቁኝ የነበረው ግን የድምፅ ማጉያ መሣሪያዎችን (sound systems) ማግኘቴን ነበር። ለስብከትና ለቃለ መሓላው የጸሎት ቤቱ አዳራሽ ውስጥ ያለውን የድምፅ ማጉያ መጠቀም እንደሚቻል፣ ከዚያ ውጭ ግን ምንም እንደማያስፈልገኝ ብናገርም፣ “እንዴ ጌታማ ሳይመለክ እንዴት!” የሚል የተቃውሞ ምላሽ ይቀርብልኝ እንደ ነበር አስታውሳለሁ። ንግግራቸው ከቃል ኪዳን ሥርዐቱ በኋላ ወይም በኬክ ቈረሳው ሰዓት ላይ ከአዳራሹ ውጭ በሚካሄደው ፈንጠዝያ ላይ ማነጣጠሩ ገብቶኛል። በሰርጌ ዕለት ያንን በጩኸት የመዘመርና የመዝለል (“Evangelical jump” ብሎታል አንድ ሰው) ክፍለ ጊዜ እንደማልፈልገውና ሰዎች ለስላሳ መጠጣቸውን እየተጎነጩ በርጋታና በመደማመጥ የሚጨዋወቱበትን መርሓ ግብር እንደምመርጥ ብናገርም ሰሚ አልነበረኝም። ግና ትኵረቴ በምመሠርተው ቤተ ሰብ የዕለት ተዕለት ኑሮ ጌታን የማክበር እንጂ፣ የአንድ ቀን ዳንኪራ ስላልነበር ስክነት የሞላበትን ክብረ በዓል መርጫለሁ። ሆኖም እግዚአብሔር በሰርጌ እንዳልተመለከ የገመቱ ሰዎች ይህን አልተረዱምና፣ “ጌታ ሳይመለክማ ምኑን ሰርግ ሆነው?” የሚል የቍጣ ንግግርም ገጥሞኛል፤ የአምልኮ ነገር ብዙዎችን ይቈረቍራቸዋል ማለት ነው።
እነዚህ ንግግሮች ግን እኔኑ መልሰው ሲያስቈጡኝ ነበር። እንዴት ነው ጌታን ሳላመልክ ጋብቻዬን እንደምመሠርት አድርገው ሰዎች የሚያስቡት? እኔና እጮኛዬ የአንዳንዶችን “የምትጋቡ ከሆነ ምናለበት?” የሚል የኀጢአት ስብከት ንቀን በንጽሕና የሰርጋችንን ቀን ጠብቀናል፤ አብረን ጊዜ ማሳለፍ ስንፈልግም በጊዜ ተገናኝተን ከመምሸቱ በፊት ስንሰነባበት የነበረውም ራሳችንን ከኀጢአት ፈተና ለመጠበቅና ለወጣቶች ምሳሌ ለመሆን ብቻ ሳይሆን፣ ለሚመለከቱን ሰዎች አእምሮም ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ሆኖ ስላገኘነው ነበር። ታዲያ ያንን ሁሉ የሰቀቀን ሰዓት በእግዚአብሔር ጸጋ ተቋቁመን፣ ሥጋችንን ሳናሳድፍ እስከ ጋብቻችን ቀን ማግስት መቈየታችን አምልኮ አይደለምን? እኔና እርሷ ለፍቅር ስንመራረጥም ሆነ ለሰርጋችን ሚዜዎችን ስንመርጥ ዘርን እና ጎሳን ሰዎችን የማቅረቢያ ወይም የማግለያ መስፈርት በማድረግ ፋንታ በክርስቶስ ደም መዛመዳችንን በማስበለጣችን የጌታን ክቡር ደም አላከበርንምን? እናም ይህ አምልኮ ካልሆነ ምንድን ነው?
ለአንድ ቀን ታይታ ሲባል ዕዳ ሳንገባ ሰርጋችንን በአቅማችን ልክ በመወጠናችን፣ በመጠን እንድንኖር የተሰጠውን አምላካዊ ቃል አልታዘዝንምን? የሰርጋችንን ዕለት ቤተ ክርስቲያን ታዳሚውን ከቀጠርንበት ሰዓት ሠላሳ ደቂቃ ቀድመን መገኘታችንስ ታዳሚዎቻችንንም ሆነ የጊዜውን ባለቤት በማክበር ባለአእምሮ ክርስቲያንነታችንን አላሳየንምን? የሰርጋችን ዕለት ላብ በላብ እና አቧራ በአቧራ እስክንሆን ካልዘመርን ጌታን እንዳላመለክን የሚቈጠረው ለምንድን ነው?
ከሰርጋችን በኋላም ቢሆን በመካከላችን ግጭት ሲፈጠር ሳንወያይና ዕርቅ ሳናወርድ ባለመተኛት “በቍጣችሁ ላይ ፀሓይ አይግባ” የሚለውን ቅዱስ ቃል (ኤፌ. 4፥26) ለመታዘዝ ጥረናል። በተለይ እኔ ይቅርታ ከመጠየቅ የዘገየሁ ብሆንም፣ ከውይይታችን በኋላ ችግራችንን በይቅርታ ፈትተን ነው ወደ አልጋችን የምንሄደው። እናሳ ይህ እግዚአብሔርን ማምለክ ካልሆነ ምን ሊባል ነው? ሚስቴ ደግሞ የራሷ ፍላጎትና ሕልም ሳይኖራት እኔን ብቻ እየተከለተች እንዳትኖር እንቅፋት አልሆንኩባትም። ለራሴ ሕልም ዋጋ እንደምሰጥ ሁሉ፣ የእርሷም ሕልም በእኔ ዘንድ የከበረ ነው፤ ሩጫዋ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ዋጋ እንዳለው ተረድቼ ላግዛት መጣሬም የእግዚአብሔር ቃል እንደሚያስተምረው ሚስቴን የማክበሬ አካል ነው (1ጴጥ. 3፥7)። በዚህም እግዚአብሔርን በመታዘዝ እርሱን አመልካለሁ። ታዲያ ሰዎች አምልኮን ጮኾ ከማዜም ጋር ብቻ የሚያጋምዱት ከምን የተነሣ ነው?
በዝማሬ ብቻ ሳይሆን በመስጠትም ጌታ ይመለካል። ስለዚህም በላባቸው ከሚያገኙት ገቢ ዐቅም በፈቀደ መጠን ወገኖቻቸውን የሚደግፉ አማኞች በዙሪያችን አሉ። ይህም ድርጊት አምልኮ በመሆኑ፣ “ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ” በማለት ተጽፎልናል (ያዕ. 1፥27)። በርካታ ክርስቲያኖችም ለእግዚአብሔር ሥራ እንዲውል ገንዘባቸውን ለቤተ ክርስቲያን እንደሚሰጡ ግልጽ ነው። እኔ በበኩሌ ይህን ሳደርግ፣ “ይቺን ስሰጠው፣ ይህን ያህል አብዝቶ ይሰጠኛል” በሚል ትርፍ የማካበት ጥማት አይደለም። “አካሄዳችሁ ገንዘብን ያለ መውደድ ይሁን” የሚለው መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ እዚህም ውስጥ ቦታ አለው (ዕብ. 13፥5)። አሁን አሁን “እግዚአብሔርን በመስጠት አስደንግጡት” ሲባል እንደምሰማው፣ እግዚአብሔርን በስጦታዬ ለማስደንገጥም አልሻም፤ ድንጉጥ አምላክ የለኝምና! ለቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ስሰጥ ለእግዚአብሔር ሥራ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ስለማውቅ፣ እንዲሁም ከዘላለም ሞት ላዳነኝ አምላክ ፍቅሬንና ምስጋናዬን የምገልጥበት አንዱ መንገድ በመሆኑ ነው። ከእግዚአብሔር ጋር በገንዘብ የመደራደር ፍላጎት የለኝም። አስቀድሜ የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን ስከተል፣ የሚያስፈልገኝ ሁሉ እንደሚጨመርልኝ እገነዘባለሁና (ማቴ. 6፥33)። መስጠት አምልኮ ነው!
የጤና ችግር ሲገጥመኝ ደግሞ እጸልያለሁ፤ ሌሎችም እንዲጸልዩልኝ አደርጋለሁ። በዚህ ሁሉ መኻል ግን ካልተፈወስኩ የሐኪም ርዳታ እጠይቃለሁ እንጂ፣ “ተፈውሻለሁ፤ ተፈውሻለሁ” እያልኩ አላውጅም። እምነትና ድርቅና ዝምድና እንደሌላቸው ዐውቃለሁ፤ “ቅዱስ ውሸት”ም አይደለም። እግዚአብሔር የሚከብረው በእውነት ብቻ በመሆኑ፣ ሳልፈወስ እንደ ተፈወስኩ አድርጌ አልመሰክርም፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ፈውሶችም እንደዚህ አልነበሩም።
እውነት መገለጫው ግን ይህ ብቻ አይደለም። እውነት ሁሉ የእግዚአብሔር ነው፤ የእግዚአብሔር ያልሆነ እውነት የለም፤ ኖሮም አያውቅም። መንፈሳዊ ሆነም አልሆነም፣ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ይኑርም አይኑርም፣ በመገለጥ የተረዳነውም ይሁን በሳይንስ፣ ከታሪክም እንማረው ከፍልስፍና እውነት ሁሉ የእግዚአብሔር ነው። ግኝቱ የአማንያንም ይሁን የኢአማንያን፣ እውነት ከሆነ ባለቤቱ እግዚአብሔር ነው። ስለዚህ ከቤተ ክርስቲያንም ይሁን ከመሥሪያ ቤቴ፣ ከሰፈር ጓደኞቼም ሆነ ከፖለቲካው ዓለም የተረዳሁትን እውነት ለመቀበልና በእግዚአብሔር ጸጋ ለዚያ እውነት ለመቆም እታትራለሁ። ይህም እግዚአብሔርን በመንፈስ ብቻ ሳይሆን በእውነት የማምለክ አካል እንደ ሆነ አስባለሁ። ታዲያ ለተረዳሁት እውነት መቆሜን እያየ፣ “ጮክ ብለህ ስላልዘመርክ፣ ወይም ወደ ላይ ስላልተፈናጠርክ አምላክህን አላመለክህም” የሚለኝ ማነው?
የድነት መንገድም እግዚአብሔር ዓለምን ከራሱ ባስታረቀበት (2ቆሮ. 5፥19)፣ በሰማይ እና በምድር መካከል ዕርቃኑን በተንጠለጠለው በክርስቶስ ኢየሱስ የመስቀል ሥራ በማመን እንጂ በየትኛውም የሃይማኖት ቡድን አባልነት እንደማይገኝ ገብቶኛል። ስለዚህ ከሌሎች ሥላሴያውያን አማኞች ጋር በጋራ ጕዳዮቻችን ላይ አብሬ ለመሥራትም ሆነ ከእነርሱ ለመማር ዝግጁ ነኝ፤ እውነትን ፈላጊ ነኝና። ነገር ግን ሰፈሬ በነጻ የማገኘውን ጀሪካን ሙሉ የገብርኤል ጠበል እንደማልፈልግ ሁሉ፣ ታሽጎና “anointed water” በሚል ፈረንጅኛ ታጅቦ የመጣውን “የጴንጤ ጠበል”ም የመቀበል እንጥፍጣፊ ፍላጎት የለኝም። ሌላው ሲያደርገው ስሕተት፣ እኛ ስናደርገው ደግሞ ትክክል የሚሆንበት ምክንያት አይታየኝምና። ስጠየቅ በምመልሰውም ሆነ በምይዘው አቋም ለሰው ፊት ወይም ለወገኔ እንዳላደላ ደግሞ መጽሐፉ ይከለክለኛል (ፊልጵ. 2፥3)። እግዚአብሔርን በእውነት ከማምለክ ጋር ይጣረሳልና!
አንዳንድ ጊዜ በአውቶቡስ ወይም በሃይገር ተሳፍሬ ስጓዝ ስለ ገጠሙኝ ነገሮች በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀን እና በሌሎች ዓለማዊ (secular) መጽሔቶች ስጠቅስ “ሼም የለም እንዴ? እንዴት በሃይገር መጓዙን ያወራል? ያሳፍራል እኮ” የሚሉ ሰዎች ገጥመውኛል። በየወቅቱ ኪሴና ሁኔታው እንደሚፈቅደው በጋሪ፣ በባጃጅ፣ በታክሲ፣ በሎንቺን፣ በአውሮፕላን ልጠቀም እችላለሁ። የትኛው ያሳፍራል? የትኛውስ ያኰራል? የሌለኝን ገንዘብ፣ “አለኝ፤ ግን አልያዝኩም” እያልኩ ውሸትን በእምነት ስም ላውጅ? ወይስ በወቅቱ ዐቅሜ የሚፈቅድልኝን ልኑር? የሰዎችን ጥሩ መኪና ባየሁ ቍጥር በአምሮት እየቃበዝኩ፣ “በኢየሱስ ስም የእኔ ነው” እያልኩ በምኞት ቅዱስ ስሙን እንዳላረክስ ደግሞ፣ “የባልንጀራህን ንብረት አትመኝ” የሚለው መለኮታዊ ትእዛዝ ያግደኛል (ዘፀ. 20፥17፤ ሮሜ 7፥7)። ይህን አክብሬ የምኖረው እግዚአብሔርን በመፍራት ነው። ታዲያ ይህ አምልኮ አይደለምን?
እግዚአብሔር ስዘምር የምሟሟቅበትን ስሜት ብቻ ሳይሆን፣ የማስብበትን አእምሮ እንደ ፈጠረልኝም አምናለሁ። ስለዚህ በአእምሮዬ እግዚአብሔርን ለመውደድ እሻለሁ (ሉቃ. 10፥27)፤ በአማኝ ባለአእምሮነት እግዚአብሔር እንደሚከብር ተምሬአለሁና። አእምሮዬን የማልጠቀም ከሆነ፣ እግዚአብሔር አላስፈላጊ ነገር መፍጠሩን ማተት ስለሚሆንብኝ በዕለት ኑሮዬ ብቻ ሳይሆን በአምልኮ ሕይወቴም አእምሮዬን መጠቀሙን መርጫለሁ። ስጸልይ በአእምሮዬ እጸልያለሁ (1ቆሮ. 14፥15)። ትንቢትም ሲነገረኝ አልንቅም፤ ነገር ግን በመንፈስም፣ በአእምሮም እመረምረዋለሁ (1ተሰ. 5፥20-21)። ልከኛ ሆኖ ካላገኘሁት እጥለዋለሁ። ስብከት ስሰማም ይህንኑ ነው የማደርገው። እኔም ለመስበክ ወደ ምስባኩ ስወጣ አእምሮውን እንደ ሳተ ሰው፣ “የምናገረውን ለምን እንደምናገር አላውቅም” አልልም፤ የምናገረውንም ሆነ ለምን እንደምናገር ዐውቃለሁ። መንፈሳዊነት ሚዛናዊነትም ነውና በማስተላለፈው መልእክትም ሚዛናዊ ለመሆን እታገላለሁ! ምትሐተኛም አይደለሁም፤ ስለዚህ የሰዎች ችግር በእኔ አገልግሎት በዚያን ቀን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚንከባለል አጉል ተስፋ አላዘንብም። ይህ ደግሞ ለራሴ የተለጠጠ ግምት እንዳይኖረኝ ያግዘኛል።
አገልግሎቴን የታዋቂነት ምኞቴን እና የዝና ጥማቴን መወጫ እንዳላደርገውም እፈራለሁ። ስለዚህ ቢሆንልኝ፣ መጽሐፍ እንደሚል ባልንጀሮቼ ከእኔ እንደሚሻሉ መቍጠር እፈልጋለሁ (ፊልጵ. 2፥3)፤ ከማንም እንደማልበልጥ ሁሌም ማስታወስ ግዴታዬ ነው። ስለዚህ ዛሬ አንዳንድ ቦታ እንደ ተጀመረው ሰዎች የድምፅ ማጉያውን መሣሪያ ተንበርክከው እንዲያቀብሉኝ አልፈልግም። እኔም ብሆን ትንፋሼንና መንገዴን በእጁ ለያዘው እና በመስቀል ጣር ለወለደኝ አምላክ እንጂ ለማንም አልንበረከክም። ከሌላው ልዩ አድርጌ ራሴን ለመቆለልም “የእግዚአብሔር ሰው” የሚል መጠሪያ አልመዝዝም፤ እግዚአብሔርን በእውነት እና በጽድቅ የሚያመልኩ አማኞች ሁሉ የእግዚአብሔር ሰዎች እንደ ሆኑ ጠንቅቄ ዐውቃለሁና። ከአገልግሎት በኋላም እንዳልታበይ፣ “የማልጠቅም ባሪያ ነኝ፤ ማድረግ የሚገባኝን ነው ያደረግሁት” በማለት ነፍሴን እሰብካታለሁ (ሉቃ. 17፥10)። ይህ ደግሞ ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ በትእቢት እንዳልወድቅ ሥጋዬን የምጎስምበት አንዱ መንገድ ነው (1ቆሮ. 9፥27)። የዚህ ሁሉ ዋነኛው ሰበብ ለእግዚአብሔር ብቻ መንበርከክ እና ክርስቶስን ብቻ ማጉላት እውነተኛ አምልኮ በመሆኑ ነው።
ዛሬ ዛሬ ሰዎች ስለ አምልኮ ያላቸው ግንዛቤ እየተጣመመ መምጣቱን ማስተዋል ከባድ አይደለም። ሳምንቱን ሙሉ እንዳሻቸው ኖረው፣ ሰንበት ሲመጣ መዘመርን ብቻ እንደ ማምለክ የሚተረጕሙ ሰዎች ሞልተውናል። አምልኮ ለማቅረብ የአምልኮን ትክክለኛ ትርጓሜ መረዳት አስፈላጊ ነው። የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የግዕዝ መዝገበ ቃላት እንደሚነግረን፣ “አምላክ” ወይም “መለኮት” የሚለው ቃል የተገኘው “መለከ” ከሚለው የግዕዝ ሥርወ ቃል ሲሆን፣ ትርጓሜውም “ማሸነፍ፣ መግዛት፣ መንገሥ፣ ጌታ መሆን” ማለት ነው። “አምልኮ” ደግሞ እግዚአብሔርን አምላክ ማድረግን፣ ማለትም ለእርሱ መገዛትን እና መሸነፍን ያሳያል፤ ይህም በነገር ሁሉ ይገለጻል። ስለዚህ በሰርጋቸውም ሆነ በሌላ የአምልኮ መርሓ ግብር ላይ በጩኸት እና በዝላይ የሚዘምሩ ሰዎች በእውነት ጤናማ ሕይወት ኖሯቸው በየዕለቱ ለእግዚአብሔር እየተገዙና ለፈቃዱ እየተሸነፉ የሚኖሩ ከሆነ ትክክለኛ አምልኮ ያቀርባሉ። አምልኮ የማይዳስሰው የሕይወት ክፍል የለምና!
* * *
ረጅሙን ሐሳብ ያለ ወትሮዬ በዝምታ አደመጥኩት። ለጥቆ ግን በርካታ ሰዎች ባይገኙም፣ ጥያቄና መልሱ እንዲካሄድ ስለ ተወሰነ ውይይታችን መቋረጥ ነበረበት። ሆኖም በዕለቱ ማግኘት የነበረብኝን መልእክት እንዳገኘሁ ስለ ገመትኩና ከአቃቂ ተነሥቼ አያት አካባቢ ወደሚገኘው ሰፈሬ ለመድረስ ትራንስፖርት ማግኘቴን ስለ ተጠራጠርኩ ከዚያ በላይ ለማምሸት አልደፈርኩም። ከመውጣቴ በፊት ግን ሐሳቡን ለሕንጸት አንባቢዎች ማቅረብ እችል እንደ ሆነ የባለታሪኩን መልካም ፈቃድ ጠየቅሁ፤ እርሱም፣ “እዚህ የተገኘሁትስ ይህንኑ ለማስተማር አይደለምን?” በማለት ሳያቅማማ ይሁንታውን ቸረኝ። ስለ ቅንነቱና ግልጽነቱ ምስጋናዬን ካቀረብኩ በኋላ ጥሩ ጊዜ እንዲኖራቸው መልካም ምኞቴን ገልጬ የቤተ ክርስቲያኒቱን ቅጥር ግቢ ለቅቄ ወጣሁ።
ለመሆኑ የእኛስ አምልኮ ምን ይመስላል?
Add comment