[the_ad_group id=”107″]

የልየታ መንፈስ ጥሪ!

ቁና ሙሉ ስሜት በየልባችን ጠባብ ጓዳ ታምቋል። ከጥግ ጥግ የተወጠሩት የስሜት አውታር በሲቃ አፍነው መተንፈሻ አሳጥተውናል። የዛሬይቱን የእኛን አገር ቤተ ክርስቲያን፣ አማኙንም ማኅበረ ሰብ ትክ ብሎ ያየ ሰው ʻያው እንደተለመደውʼ ብሎ ሊሄድ አይችልም። ኡኡታ ይቃጣዋል፤ ድንግርግርታ ያናውዘዋል፤ ትካዜ ያሰምጠዋል፤ ግርምት ይይዘዋል፤ የምስጋና ዜማ ከታፈነው ጉሮሮ መኻል ያፈተልክበታል፤ በጥያቄ ብዛት ልቡናው ይሽከረከራል … ምኑ ቅጡ!

በየጸሎት ቤቱ፣ በየአዳራሹ፣ በየአደባባዩ፣ በየቴሌቪዥኑ፣ በየመጻሕፍቱ፣ በሰፈር በከተማ ከሚባለው ከሚሠራው ሁሉ ነገር ስቦ ስቦ ልባችን የአያሌ ስሜቶች መፈልፈያ ቋት ሆኗል።


ለምሳሌ

“ኢየሱስ ክርስቶስ አምላኬ፣ ጌታዬ፤ እኔም የእርሱ ሎሌ” ስል የኖርኩትን ሰው፣ “በጥቂት ብትለያዩ ነው እንጂ አንተም እኩያው ነህ፤ አንተ ዳግም እንደ ተወለድህ እርሱም ሁለቴ ልጅ ሆኗል።” እያሉ በጌታዬ ላይ ሲሳለቁ በምን አንጀቴ ዝም ልበል?

የክርስቲያንነት ሀሌታም አሜኔታም፣ ቁሳዊ ብልጽግና የሆነ ይመስል፣ እርሱ የሞተልን ቱጃሮች እንድንሆን መሆኑን እየነገሩኝ በድኾች ወንድሞቼ ላይ ክፉ ሳቅ ሲስቁ በምን ሕሊና ልስማ?

የቤተ ክርስቲያን መድረክ ከዓመት እሰከ ዓመት የድንፋታ፣ የፉከራ፣ የዝላይና የረገዳ፣ አንጎል የሚያዞር ጩኸትና ቱማታ እየሆነ ጥሞና በይፋ ሲረገጥ እንዴት ዝም ብዬ ልይ?

የከበሩት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ለገበያ እንደ ቀረቡ ዕቃዎች በገንዘብ ሲሸጡ፣ ሲገዙ፣ የተቸገረው ኅብረተ ሰብም ያለ የሌለውን ጥሪት ለጥቂት ብልጦች ማክበሪያ ሲበትን ስሰማና ሳይ እንዴት አልተክዝ?

በአገልጋይነት ስም እየተጠሩ ጌታ በሞተለት ሕዝብ ላይ እንደ ነገሥታት የተቆነኑ አስገባሪዎች አይቼ፣ እንደ ጥንት ባላባቶች በአጀብ ከበባ የሚንቀሳቀሱ አይቀረቤ አምባገነኖችን ተመልክቼ እንዴት አልበሳጭ?

ደግሞ ሌላ ዐይነት ምሳሌ

የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠርቶ ሰዎች ከደዌያቸው ሲፈወሱ፣ ከእሥራታቸው ሲፈቱ በአጠገቡ የጸለዩላቸው አገልጋዮች ስም ተያይዞ ቀርቦ ሁለቱ ስሞች ያለ አግባብ እንዲሻሙ ሲደረግ፣ የተፈወሱትም ሰዎች ምስጋና ለማመጣጠን ሲታገሉ፣ አገልጋዮቹ ልብሳቸውን ቀድደው አለመጮኻቸው ግር ይለኛል።

መንግሥቱን ሊያሰፋ በድንቅና ታምራት የሚገለጠው ጌታ ኢየሱስ ታምራቱ እልፍ ጊዜ እየተነገሩ እርሱ ግን ሲረሳ፣ የታምራቱ ዐላማ በጩኸትና በጭብጨባ ሲታፈን፣ የወንጌል ቃል ሲጠፋ ሳይ ጭንቅ፣ ጥብብ ይለኛል፤ ያቁነጠንጠኛል፤ ʻምንድን ነው ነገሩ?ʼ እያለ ልቡናዬ ይጥበረበርብኛል።


ሌላም ዐይነት

አሁን በልዩ ልዩ ሥፍራ እንደሚታየው ብዙ ሕዝብ ወደ ቤተ እግዚአብሔር እየተመመ ሲሄድ፣ ብዙዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የጌታን የኢየሱስን ስምና የማዳኑን ኀይል ሲሰሙ ልቤን ደስ ይለዋል፤ ከአካላዊ ደዌ ሲፈወሱ የሚያቀርቡትን ምስጋና እየሰማሁ ከልባቸው ቅንነት የሚፈልቀውን መገረም እያየሁ እኔንም ይገርመኛል፤ የእግዚአብሔርንም ቸርነት አደንቃለሁ።

ኢየሱስ ክርስቶስና የስሙ ጉልበት በሕዝባችን መካከል መነጋገሪያ መሆኑ፣ ምስኪኖች ለጥያቄዎቻቸው መልስ ፍለጋ ዐይናቸውን ወደ እርሱ ማቅናታቸውን እያየሁ ደስ ሲለኝ፣ ወዲያው ደግሞ ከኀይሉ ጋር እንጂ ከእርሱ ጋር ስለ መተዋወቃቸው ጥርጥር ይገባኝና ደስታዬና ትካዜዬ ይደባለቃሉ።

አዝመራው ነጥቶ ሳለ፣ አጓጉል ወፈ ሰማይ ፍሬውን ሲያነካክተው፣ እኛም ሁላችን በግርግርና በፉከራ፣ በጥርጥርና በጭቅጭቅ፣ በጎራ ከለላና በቡድን ትዕቢት መነጋገርና መደማመጥ ተስኖን፣ ነዶውን መሰብሰብ ሲያቅተን ሳይ እተክዛለሁ።


እና የስሜቴ ጕራማይሌ ይቀጥላል

እየተቆጣሁ፣ እየተደናገርሁ፣ እየተገረምሁ፣ እየተከዝሁ፣ እየጠየቅሁ አለሁና ወደ ሰማይ አምላክ ጩኸቴ “ድፍርሱን አጥራልን፣ ጨለማውን ግፈፍልን፣ የከበረውን ከተዋረደው ለይልን፣ አስመሳዩን ከእውነተኛው ነጥልልን፤ እባክህ የልየታ መንፈስህን ላክልን” እያልሁ ነው።

ልየታ አንድም የሐኪም ሥራ ነው። በሰውየው ገላ ላይ የነገሠውን በሽታ እየለቀሙ ማውደም፣ የሚተርፈውን ማትረፍ፣ ጤናን ከጤና ሰላቢ ማላቀቅ። ይህ ተግባር ብርቱ ተመልካችነት፣ ቆራጥ ጭካኔ፣ የታካሚውን ደኅንነት ለማረጋገጥ የቆመ ንጹሕ ዕርዳታ ሰጪነት ይጠይቃል።

ቤተ ክርስቲያን ከታመመች ቆየች። እያንዳንዱ በሽታዋ እንደ ካንሰር እየተስፋፋ መላ አካልዋን እንዳይመርዝ ከታላቁ ሐኪም ጋር የመሥራት ጊዜው አሁን ነው። ድንገተኛ ክፍል ገብታ የተዘረረች ይመስላል። አጣዳፊ የነፍስ አድን ሥራ ያሻል። ʻየምትተርፍ አይመስለኝምʼ እያለ ባልወለደ አንጀት በአልገዋ ላይ የሚተዋት ሠራተኛ እንዴት ጨካኝ ነው!? ʻኧረ ምንም አልሆነች፤ አታሟርቱባትʼ የሚለውም ሞቷን ያፋጥናል። ይልቁን ቶሎ ዕርዳታ ይስጣት። መሠረታዊ በሽታዋ እንዲታወቅ ትመርመር። ምንድነው የሆነችው? የልየታ መንፈስ ያለህ!

ይህ መንፈስ እንደ ስሙ ቅዱስ መንፈስ ነው፤ ብርቱና ኀያል ነው። እኛ ለየፍላጎቶቻችን የምናልበው ጥገት ሳይሆን፣ የራሱ ዐላማና ሥራ፣ ዕውቀትና ፈቃድ ያለው አምላክ ነው፤ የቤተ ክርስቲያን ተስፋ እርሱ ነው።

መንፈስ ቅዱስ እውነተኛ መንፈስ ነው፤ ስለ እውነት ይናገራል። የእግዚአብሔርን ሐሳብ የሚያቀብለን የሰማይ ምስጢረኛ ነው። ድንግርግርታና ቀላማጅነትን የማይወድድ፣ የእውነት ዐርበኛ ነው። የሐሰትን ድር የሚበጣጥስ ሾተል ነው። ማን ሊያታልለው ይደፍራል? ማን በፊቱ ይቀባጥራል? ሐናንያንና ሰጲራን ያስታውሷል። ይህ መንፈስ ካደረብን ምላሳችን ጤና ያገኛል፤ የፈውስ ቃል ተፈጥሯችን ይሆናል።

መንፈስ ቅዱስ እሳት ነው፤ ገለባውን ያቃጥላል። የግል ክብር ፍለጋ፣ የተቆለለ የራስ ዝና ገለባ፣ ጥቅም ለማሳደድ በድብቅ የገባ የልብ ሌባ፣ የቂም፣ የፉክክር፣ የʼከማን አንሼʻ ገለባ በብርቱ ነበልባሉ ብን ትን ብሎ ይጠፋል።

ይህ መንፈስ ምን ብርቱ ቢሆን፣ ምን እሳት ቢሆን አካሄዱ ሥርዐት ዐልባ አይደለም። ሊደብቀው የሚሻ፣ በግርግር ሊያጨናብረው የሚፈልግ ነገር ስለሌለ በርቱዕ መንገድና በውብ ሥርዐት ይጓዛል፤ ለፍጥረተ ዓለሙ ምሕዋር ያበጀ፣ ለሰው መንፈስ አቅል የሰጠ ይህ የመላ ዓለሙ አቀናባሪ ሁሉን በጥበብ ሥርዐቱ ይመራል። እንግዲያው፣ ቤተ እግዚአብሔር የዚህ መንፈስ ማደሪያ ናትና እውነት ተናጋሪ፣ በጽድቅ ኗሪ፣ በሥርዐት ተመሪ መሆኗ የግድ ነው፤ አለበለዚያ ሌላ ቤት ትሆናለች።

ከሁሉ በላይ ደግሞ ይህ መንፈስ የፍቅረ መንፈስ ነው። “የእግዚአብሔር ፍቅር በመንፈስ ቅዱስ በልባችን ስለ ፈሰሰ” ተብሏልና መንፈሱ የወደቀበት ሁሉ በዚህ ፍቅር ይጥለቀለቃል። የሰማዩን ጌታ በፍጹም ፍቅር ይወድዳል፤ የምድር ላይ ባልንጀሮቹን በንጹሕ ፍቅር ይወድዳል፤ ቤተ እግዚአብሔርን በ“ገብጋባ ፍቅር” ይጠብቃታል።


ታድያ ምን እናድርግ?

ይሁዳ በታላቅ ፍልአምሮት (passion) የሚጽፍ ነው። ቃላቱን በፍጥነት ዝርግፍ፣ ዝርግፍ የሚያደርገው እጅግ ያስቆጣውን የዘመኑን ወልጋዳ ትምህርትና ሕይወት ለመገሠጽ ነው፤ ምእመናንንም ለማስጠንቀቅ፣ ለማሳየትም ነው፤ ለማንቃት፣ ለማበረታታትም ነው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥና አካባቢ ያያቸውን ክፉ አራዊት በሦስት ምሳሌዎች ይገልጣቸዋል፤ ቃየላዊ ጥላቻ፣ በለዓማዊ ስግብግብነት እና ቆሬያዊ ትዕቢት። የፍርድ ማስጠንቀቂያውን ከሰጠ በኋላ ግን ብርቱ ምክሮች ያቀርባል።

“የሐዋርያትን ቃል አስቡ፣ በተቀደሰ ሃይማኖት ራሳችሁን አንጹ፣ በመንፈስ ቅዱስ ጸልዩ፣ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ፣… አንዳንዶችን ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ … በፍርሀት ማሩ…”

የእኛ ሁኔታ ከይሁዳ ዘመን እጅግም አይለይም። የተሰጠው ምክር ሁሉ ለእኛም ይሠራል። በተለይ ግን ለዚህ ውይይታችን አንዱን ላተኩርበት፤ “አንዳንዶችን… አንዳንዶችን… አንዳንዶችን” የሚለውን። ይሁዳ ፍርደ ገምድል አይደለም። ምንም እንኳ ክፉ ሽታ አየሩን እንደ በከለው ቢያውቅም፣ አውዳሚው ጢስ በየስፍራው እየተጎለጎለ ቢታየውም ሊተርፍ የሚችል እንዳለ ያውቃል። አንድ ጥግ ይዘን የቀረውን ሁሉ በአንድ ጅራፍ እየገረፍን ሊተርፍ የሚችለውን ሁሉ መጥረጋችን ብልህነት አይመስለኝም። እሳቱ ቢለባለብም “ንጠቁ” ተብለናልና አንዳንዶችን ለማትረፍ ለምን አንነሣም? ʻእኔን ይፈጀኛል፣ ልብሴን ያቆሽሻልʼ እያልን ዳር ቆመን ለመመልከት አንጀታችን እንዴት ይጨክናል? አንዳንዶች በርኅራኄ እጅ ተመንድገው ሊወጡ ይችላሉ፤ በትሑት አንደበት ሊቃኑ ይችላሉ፤ በቅዱስ ፍርሀት ሊደነግጡ ይችላሉ፤ በእውነት ቃል ሊገሩ ይችላሉ፤ በፍቅር ዐይን ሊማረኩ ይችላሉ። እስኪ ስለ አንዳንዶች እናስብ። ለማዳን ስንጠጋ፣ ለማትረፍ ስነዘረጋ ርኩሱን ቅዱስ ማለት የለብንም፤ ጨለማው ብርሃን ነው እያልን ማሞካሸት አይጠበቅብንም። “በሥጋ የረከሰውን ልብስ እንኳ እየጠላችሁ” ተብሏልና ዐመፅን በስሙ ጠረቶ የታሰረውን ሰው ግን ለማዳን መዘርጋት የጥበብ ጎዳና ነው።


ሌላ ምክር

በመካከላችን በጌታ በእየሱስ ክርስቶስ ስም ድውያን ሲፈወሱ፣ ከእስራት ሲፈቱ፣ ከሁሉ ይልቅ ደግሞ ወደ ወንጌል እውነት ሲመጡ መደሰት የጤና ምልክት ነው። በፈውስ ስም፣ በነጻነት ስም ለሚቀርቡ ማጭበርበሮች፣ ግርግሮችና ላልተፈተሹ ታምራት ማጨብጨብ ተገቢ አይደለም። ነገር ግን በእውነት ተከናውነው ለምናያቸው በጎ ድንቆች ምላሻችን አዎንታዊ ቢሆን የጌታን ስም ገናናነት ለማወጅ ይመቻል። ʻሐሰቱ አገሩን ሞልቶታልʼ ብለን የእውነቱን ታምር ለምን እንሸሻለን?


ደግሞ ሌላ

መመካከር ማንን ገደለ? ለጠብ የምንቸኩል፣ ጎራ ለመያዝ የምንጣደፍ ለምንድነው? ምናልባት እኔ እዚህ የማስበውን እዚያ ያለ ሌለ ሰው ሽፋኑን ብቻ ለውጦ ያንኑ ያስብ ከሆነስ? ምናልባት እዚያም ቤት ቡናው በስኒ ይጠጣ እንደሆነስ? በስኒው ቀለም ልዩነት ከመጣላት፣ ʻየተቀዳው ነገር ቡና ነው፣ አተላ?ʼ እያሉ መጠየቅ አይሻልም? የወንድሜን ቁመና ከራስ ፀጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ በትልቅ “ኤክስ” ከምደመስስ አንዲት የጠዳች ጣት እንዳለው እንኳን ቢታየኝስ? ቢታጠብና ቢጸዳ የምድሩን መልክ እንደሚያሳምር ባስብስ? ሳንደማመጥ መጣላት ሞኝነት ነው።

ለክርስቶስ አካል አንድነት የሚከፈለውን ሁሉ ለመክፈል ብንዘጋጅስ? ቅን ምክክር እና ውይይት ግልብነታችንን ይገታልናል፤ የቡድን አጫፋሪነታችንን ይዋጋልናል፤ እውነትን ለማይት አደብ ይሰጠናል።


ደግሞ አንድ ምክር

“ልባሙች የሆናችሁ አይምሰላችሁ፤ ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ” ያለው ሐዋርያ የሥጋ ብልሃትና ጮሌነት ለሠመረ ግንኙነት ፋይዳ እንደሌለው ሲያሳስበን ነው። ትዕቢትና ʻእበልጣለሁʼ ባይነት፣ ምሬትና በቀል፣ ጉረሮዬን ደፍኖ ሲተናነቀኝ ከሞት የሚያተርፈኝ ትሕትና ብቻ ነው። የላይኛይቱ ጥበብ ጎዳና የንጽሕና፣ የገርነት የእሺ ባይነት፣ የታራቂነት መንፈስ ነው። እስኪ ቆም ብለን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሞተለት ማኅበር እናስብ፤ ስለሞተላቸው ግለ ሰቦች እናስብ። እርሱ አድናለሁ ብሎ ነፍሱን ሲሰጥ፣ እኛ በምላስ ጅራፍ የምንገራረፍ እንዴት ዐይነት ሰዎች ብንሆን ነው? የጌታ ኢየሱስ ልጅ አጥፊ አይደለም፤ አቅኚ እንጂ።


ሌላ ምክር

አንድ ወዳጄ እንዲህ አለኝ፦ “ከጩኸት የማመልጥበት ቦታ ጠፋ፤ በምውልበት ሜዳ የገበያ ጩኸት፣ በቤተ ክርስቲያን በአምልኮ ስም፣ በጸሎት ስም የሚደረግ ንግግርና ጩኸት፣ ቤት ስገባ የቴሌቪዥን ጩኸት! የት ሄጄ አደብ ልግዛ? የት ገብቼ ከአምላኬ ጋር ላውራ?” ያለ ውሉ የሚደረግ ጩኸት ሁለት የአካል ክፍሎችን ይጎዳል፤ ጆሮና ጉሮሮ። አእምሮንም ሳይደፍን አይቀርም። ለምንድን ነው ጸጥታ የምንፈራው? አምልኮ መሪው ይፈራል፤ ጸሎት መሪው ዝምታ ይፈራል፤ ዘማሪው ይፈራል፤ ሰባኪውም እንኳ ይፈራል። ዝምታ የሚገድለን ይመስላችኋል? ይልቁን ነፍሳችንን ከግልቢያ አይመልስልንምን? መንፈሳችንን እያጸዳ አያስውብልንምን? ኧረ እባካችን ዝም እንበል። በጸጥታ ከሰማያዊው አባት ጋር ስለማንተያይ ይኸው ራቁት ቀረን፤ አልባሽ፣ አጉራሽ አጣን። የቃሉ ገበታ አይፍረስ፤ የጸሎት ጥሞናው አይደፍርስ።

ተማጽኖ

ለመሆኑ የእኛ ተልእኮ ምንድን ነው? መንግሥተ እግዚአብሔር እንዲሰፋ፣ የክርስቶስ ኢየሱስ ማዳን ለሁሉም እንዲደርስ መትጋት፣ ያመኑቱ የክርስቶስ ጥኑ ተከታዮች እንዲሆኑ ማብቃት አይደለም? በፍጅት ጊዜ ካጠፋን ዋናውን ሥራ ማን ይሥራው? ለንጹሕ ወንጌል እየተጋደልን በጨለማ ያሉትን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃን ማምጣት ጥሪያችን ነው። በአጭር ታጥቀን በሰፊው መስክ ላይ መሰማራት ግድ ነው።

የተባለው ሁሉ ተብሎ በሁላችን መካከል የጠፋውን ወይም ከሌላ ጋር የተደባለቀውን የመንፈስ ቅዱስ እሳት ለይተን ለማጣራት ጉሮሯችንን እንጥረግ። ሰማያዊው መንፈስ ሆይ ና! ፍዝ ነፍሳችንን አንቃልን፤ ልፍስፍስ ጉልበታችንን አጽናልን፤ ድንጋይ ልባችንን ፈርክስልን፤ የፍቀር ነበልባል ለኩሰና በርቱዕ አንደበት ባርከን፤ የርኅርኄ ልብ አብቅልልን፤ የልየታ ጸጋ ስጠን፤ በጥበብህ አሰልጥነን፤ በሀልዎትህ ንገሥብን! … ኦ መንፈስ ቅዱስ፤ በትኩስ ጉብኝት ዳስሰን።

Nigussie Bulcha

የማይናወጥ ሐሴት

“እግዚአብሔር አምላክህከጓደኞችህ ይልቅበደስታ ዘይት ቀባህ፥”ዕብራውያን 1፥9 “መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ …ወደ ጌታህ ደስታ ግባ:”ማቴዎስ 25፥21 የማይናወጥ ሐሴትየኢየሱስ ክርስቶስ ደስታትርጕም በአማረ ታቦር ከከፋ አደጋ ያዳኖት

ተጨማሪ ያንብቡ

የበዓለ ጥምቀት አከባበር በግብጽና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት

ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላደረገው ነገር ኹሉ የመታሰቢያ በዓል አዘጋጅቶ አምላክ የኾነው እርሱ ሰው በመኾን ያሳየውን ድንቅና በትሕትና የተሞላ ሥራውን በመዘከር እርሱን በእውነተኛ ልብ ማምለክና ማክበር መቻል መልካም ነገር ነው። ትልቁ ጥያቄ ግን በዚህ ውስጥ የበዓሉን ባለቤት ስንቱ ሰው አስታውሶት ይኾን?

ተጨማሪ ያንብቡ

ይህን ማንነቴን ምን ልበለው?

ባንቱ ገብረ ማርያም በዚህ ዐጭር ጽሑፋቸው፣ የሕይወታቸውን ዙሪያ ገባ ይቃኛሉ፤ ቃኝተውም አንድ መለያ ብቻ የሌለው ማንነት የተጎናጸፉ መሆኑን ይገነዘባሉ። አንድ ጥያቄ ግን ማንሣታቸው አልቀረም፤ “ይህን ማንነቴን ምን ልበለው?” የሚል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.