ስመ ጥር ካደረጉትና ዝናን ካጎናጸፉት መጻሕፍቱ መካከል፣ “ኑዛዜ” የተሰኘውን ጥራዝ ሳይጠቅስ የሚያልፍ ጸሐፊ አለ ለማለት ያስቸግራል፤ “ጌታ ሆይ፤ ለራስህ ስትል ስለ ፈጠርከን ልባችን በአንተ ላይ እስኪያርፍ ድረስ የትም ይባክናል” የተሰኘውና ተደጋግሞ የሚነሣው ኀይለ ቃልም ከዚሁ መጽሐፍ ነው ተመዞ የወጣው።
በተጸውዖ ስሙ ላይ፣ “ቅዱስ” የተሰኘው ቃል የተቀጸለለት ይህ ታዋቂ የቤተ ክርስቲያን አባት በሰሜን አፍሪካ በምትገኘው ታጋስኪ በተሰኘችው ስፍራ ተወልዶ የዚህን ዓለም አየር መማግ ጀመረ።
ወላጅ እናቱ የቤተ ክርስቲያንን ገጽ ካስጌጡ ልበ መልካም እንስቶች አንዷ ስትሆን፣ በጎውን የምትመኝለት ልጇ በክርስቶስ መንገድ ላይ ይጓዝላት ዘንድም በጽኑ ተጋድላለች። ይሁንና ራሱን ለራሱ ካስገዛበት ጊዜ አንሥቶ ከወላጅ እናቱ ፈቃድ እየራቀ፣ እየራቀ መሄድ ጀመረ። ባጭሩ የልቡን መሻት ተከትሎ ለሥጋው ፍትወት አደረ፤ የጨዋታ ስፍራዎችንም አዘወተረ።
ዕድሜው ዘለግ እንዳለ፣ የወቅቱ ደራሲያንን ሥራ ይፈትሽ፣ በእነርሱም አእምሮውን ያጎለምስ ገባ፣ አንደበቱንም አሰላ፤ አተባ። አካሄዱን ተግ ብሎ ያስተዋለው አባትም ዕድሜው ዐሥራ ሰባት ላይ ሲደርስ፣ በዘመኑ ዝነኛ ወደ ነበረው የካርታጎ ተቋም ሕግ ያጠና ዘንድ ሰደደው።
የመንግሥት ባለ ሥልጣን የነበረው አባቱ ብዙም ሳይቆይ አረፈ፤ እንዲያም ሆኖ ትምህርቱ ላይ እንከን አልተፈጠረበትም፤ የቅርብ ዘመዱ የሆነ አንድ አስተዋይ ከእውቀቱ እንዳይስተጓጎል የሚቻለውን ሁሉ አደረገ። ልጁም አደገ፤ በእውቀቱም በረታ፣ በንግግርም ትንታግ ሆነ።
በዚህ መሥመር መግፋት ግን አልተቻለውም፤ ከአጓጉል ጓደኞች ጋር ገጠመና ልቡ ወደ በደል አዘነበለ። በዐሥራ ስምንት ዓመቱም ከአንዲት ልጅ እግር ጋር ያለ ጋብቻ መኖር ጀመረ፤ ልጅም ወለደችለት።
ይሁነኝ ያለው መንገድ እንዳሰበው የልብ ደስታን አላመጣለትም። መንፈሱ ታወከ። የነፍሱን ማዕበል ለማስከንም፣ “እውነትን ፍለጋ” የተሰኘውን ሐረግ አንግቦ ወደ እውቀት ጥሻ ወረደ። ለተለያዩ ትምህርቶችም ራሱን ክፍት አደረገ፤ የዘመኑን ፍልስፍናዎች መረመረ። እንደሚባለው፣ “ሆርቴንሲዩስ” የተባለው የሲሲሮ ድርሰት ይበልጥ እውነት እንዲፈልግ መሻትን ለኮሰበት። እርሱም ቢሆን “ጥበብን የመሻት ጥልቅ ናፍቆት አሳደረብኝ” ሲል ስለዚህ መጽሐፍ መስክሯል።
በዚህ የብትለት ጉዞው እውቀቱን እያሰፋ ቢሄድም መንፈሱን ግን ሊያሰክን አልተቻለውም። እናም ፊቱን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ መልሶ በፍልስፍና መነፅር ይፈትሸው ጀመረ። እንደ እርሱ አባባል፣ የጠለቀና የረቀቀ ምስጢር አጣበት። ርግጥ በንባብ ሂደቱ የኀጢአቱን ጥልቀት በሚገባ ቢገነዘብም እምነቱን ሊያተጋ የሚችል ኀይል ግን ከውስጡ ፈንቅሎ ሊወጣ አልቻለም። በመከያው፣ “የማይጠቅም መጽሐፍ” ሲል ወደ ጎን ገፋው።
ፍለጋውን በማግዘፍ ወደ ማኒ እምነት ተሳበ። ውሳኔውም የእናቱን ልብ ክፉኛ ሰበረ። በምክርም በልመናም ልታለዝበው ሞከረች፤ በጸሎት ተጋችለት። ዐሳቡን ግን ልታስቀይረው አልተቻላትም።
ከምድረ ፋርስ የበቀለው የማኒ እምነት፣ በሌሎች ሃይማኖቶች መስረግ እንጂ ራሱን ችሎ የመሄድ ውቅር ስለሌለው ወደ መካከለኛው ምሥራቅ፣ ወደ ሰሜን አፍሪካና ወደ አውሮፓ ለመገስገስ ጊዜ አልፈጀበትም። በዚህ ሂደት ነበር ወደ ካርታጎ የመጣው።
የሥጋውን ፈተና መቋቋም ያቃተው ባለ ታሪካችን አውግስጢኖስ በዚህ ረገድ ያለውን ድካም ለመግራት ማኒን እንደተገነ ታሪክ ያወሳል። በገባበት ቅጽበትም ለአዲሱ አስተሳሰብ ሰዎች እጃቸውን እንዲሰጡ ብርቱ ጥረት አድርጓል። ይሁንና ሁሌም በሥጋው መሻት ተሸናፊ እንጂ ማኒ ወዳስቀመጠው የብጽፅና ደረጃ ሊሸጋገር ባለመቻሉ በማኒ ላይ ያለው ተስፋ ወደቀ። “ዋጋ ቢስ” ሲልም እምነቱን እንደ ተቸ ጸሓፍት ይነግሩናል።
የማኒ እምነት አቀንቃኝ የሆኑ ወዳጆቹ፣ ርእሰ መምህራቸው ፋውስተስ ጠለቅ ያለ እውቀት ሊያመላክተው እንደሚችል በመግለጥ ይታገሰው ዘንድ መከሩት፤ ፋውስተስን ባገኘው ጊዜ ግን በንግግር ችሎታውና በአቀራረቡ የተመሰጠ ቢሆንም ነፍሱን የሚያላውስ አላባ እንዳላገኘበት ግን ተናግሯል፤ “ገጽታው የተዋበ ዋንጫን ዐሳየኝ፤ በውስጡ ግን ጥም የሚቆርጥ መጠጥ አላገኘሁበትም” በማለት ነበር የፋውስተስን ትንታኔ የተቸው።
በወዳጆቹ ምክር ድምፁን አጥፍቶ ወደ ሮም አቀና። የመሄዱ ዜና እንደ ተሰማ የእናቱ ኀዘን ናረ። ሁኔታው ስላስጨነቃት ወደ ጳጳሱ በመሄድ የልቧን ሸክም አዋየችው፣ “ዐሳበ ግትር በመሆኑ ምን ማድረግ ይቻላል?” በማለት አስተዛዘናት። የተቻለውን እንዲያደርግ አልቅሳ ተማጠነችው፤ “አይዞሽ ይህን ያህል ዕምባ ያፈሰስሽለት ልጅ አይጠፋም” ሲል አጽናናት።
ሮም በቆየበት የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ኅሊናውን ሊያረጋጋ የቻለን እውነት አላገኘም። ከዚህ የተነሣ ወደ ሚላኖ ወርዶ በአንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ውስጥ የንግግር ሥልት መምህር ሁኖ ተቀጠረ። በዚያም ቢሆን የኅሊናው ትግል እያሻቀበ እንጂ እየከሰመ አልመጣም። ይበልጥ ያንገላታው ገባ።
ሚላኖ በቆየበት ጊዜ ወደ ታዋቂው ጳጳስ ሰበካ እያመራ መልእክቱን መስማት ጀመረ። የአምብሮስዩስ አንደበትና ሞገሱ ቀልቡን ገዛው፤ እያደርም ነፍሱ በወንጌል ብርሃን ትላወስ ገባች። በኋለኛ ዘመኑ ባሳተመውና ዝናን ባተረፈለት “ኑዛዜ” በተሰኘው መጽሐፉ ስለ አምብሮስዩስ ሲያወሳ፣ “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያጣሁትን እውነት ይገልጥልኛል የሚል እምነት ባይኖረኝም፣ በማንነቱና በንግግር ችሎታው ግን ደጋግሜ ጎብኝቼዋለሁ። የአነጋገሩ ጥበብ እየሳበኝ መጣ፤ ይሆነኛል ብዬ ግን ለፍሬ ዐሳቡ ትኩረት አልሰጠሁትም፤ ይሁን እንጂ ከአነጋገር ምትሃቱ ጋር አንዳንድ ቁም ነገሮች እያፈተለኩ መንፈሴን ይነኩ ጀመር፤ ከዚያም ጥበቡንና ፍሬ ዐሳቡን መነጠል አቃተኝ” ሲል ጽፏል።
የብርሃን ጮራ ልቡ ላይ ቢፈነጥቅም አጠቃላይ የሆነው የወንጌል እውነት ግን አላዛልቀው አለ። የዘመኑን ፍልስፍና አብጠርጥሮ የተረዳው ኅሊናው የወንጌልን እውነት ለመገንዘብ ዳገት ሆነበት። በዚህ ፍዘት ውስጥ እያለ ዳግመኛ መጽሐፍ ቅዱስን ለመፈተሽ ልቡን ሰጠ። በንባብ መሥመር ላይ በገባበት ሰዓት ተናጠበና በአውሮፓ ይላወስ በጀመረው በአዲሱ የአፍላጦን ፍልስፍና ተማረከ። በዚያም ቢሆን ያገኝ ዘንድ የተጋለትን የመንፈስ እረፍት አጣ። እንደገና መለስ ብሎ የአዲስ ኪዳን ምንባባትን በተለይ የጳውሎስን መልእክታት ያገላብጥ ገባ። በዚህ ፍለጋው የክርስቶስ ቤዛነት እየፈካለት፣ የኀጢአቱ ግዝፈት እየታወቀው፣ ማንነቱንም እየተረዳ መጣ። እንዲያም ሆኖ እንኳ ልቡን ለክርስቶስ ማስገዛት አልተቻለውም።
ትካዜና ቁዘማ ሰቅዞ ያዘው። በአንድ ዕለት ከወዳጁ አልፕዩስ ጋር ይህንኑ ስቃዩን እያወጋ ሳለ ፓንቲያኑስ የተሰኘው ክርስቲያን መኮንን በግብፅ ካሉ ጓደኞቹ ሁለቱ ይህን ምድር ንቀው ምናኔ መግባታቸውን አጫወተው። ወሬው ልቡንም መንፈሱንም ክፉኛ ረበሸው። ፊቱን ወደ አልፕዩስ መልሶ፣ “እኒህ ተራ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት ሲተጉ እውቀት ዘልቆናል የምንል እኛ እንዲህ ተርመጥምጠን እንቅር?” በማለት በወደቀ መንፈስ ጠየቀውና ፈጥኖ መንገድ ገባ፤ እልፍ እንዳለ ህውከቱ አየለበት፣ የእንባው ከረጢት ተነደለ። “እስከ መቼ አትታደገኝም?!” ሲል በሰቆቃ ጮኸ። የውስጡ ገሞራ ፈንቅሎ ከመሬት ደፋው፤ በዚያ ስቃይ ውስጥ እያለ፣ “አንሣና አንብብ! አንሣና አንብብ!” የሚል ድምፅ ጆሮው ገባ። ገሸሽ ያደረገውን አዲስ ኪዳን አንሥቶ ከፈተው፤ ተቅበዝባዥ ዐይኖቹ ሮሜ 13፥14 ላይ አረፉ፤ “ይልቁንም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም ይፈፅም ዘንድ ለሥጋ በሐሳባችሁ አታመቻቹለት።” እንደ ቀድሞው መሆን አልቻለም። ጥርጣሬው ተገፈፈ፤ ጭንቀቱ ተወገደ፤ የኀጢአት ይቅርታ ማግኘቱን አመነ፤ ልቡም ክርስቶስን ለማገልገል ቆረጠ። በ386 ዓ.ም. ወደ ክርስቶስ ተጠጋ፤ በ33 ዓመቱ እጁን ሰጠ። በዓመቱ በሚላኖው ጳጳስ አምብሮስዩስ እጅ ጥምቀተ ውሃ ወሰደ። የብዙ ዘመን ዕምባዋ ውጤት የሆነው የልጇ ወደ ልቡ መመለስ እናት ሞኒካን በሐሴት አጥለቀለቃት።
የሕይወት ለውጡን አስመልክቶ፣ “ዘግይቼ አፈቀርኩህ፤ በውስጤ ሳለህም አንተን በውጪ በመፈለግ ባተልኩ” እንዳለ ይነገርለታል። ታሪክ እንደሚያወሳው የእናቱ ዕምባ፣ የአምብሮስዩስ ስብከቶች ይልቁንም የቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት ለሕይወት ለውጡ ዐቢይ የሆነውን ሚና ተጫውተዋል።
ከሚላኖ ወደ አፍሪካ አመራ። ኦስትያ ወደብ እንደ ደረሰ ወላጅ እናቱን ሕመም መታት፤ ይኼኔ ወደ ደረቷ አስጠግታው፣ “እስከ ዛሬ በሕይወት ለመኖር እመኝ የነበረው ያንተን የሕይወት ለውጥ ለማየት እንደ ነበረ ታውቃለህ፤ ከእንግዲህ ወዲህ በዚህች ምድር ላይ ሌላ ለማየት የምናፍቀው ምናለ?” ስትል የውስጧን አጫውታዋለች። በአምስተኛው ቀን፣ በኀምሣ ስድስት ዓመቷ አረፈች።
ለአውግስጢኖስ መራር እውነትን መጠጣት ሆነበት፤ ብርቱ ኀዘን ዘለቀው። በዚህ ሁኔታ የማያውቁት ወዳጆቹም ለዘብ እንዲል በመከሩት ጊዜ፣ “ዘመኗን በሙሉ ስታነባልኝ ለኖረችው እናቴ ጥቂት ዕምባ ባፈስላት ኀጢአት አሰኝቶ ማንም አይሳለቅብኝ” እንዳለ ይወሳል።
ወደ አፍሪካ በተመለሰ በአምስተኛው ዓመት ማዕረገ ክህነት ተሰጠው። የአባቱን ንብረት ሸጦ ለድኾች በተነ። ከዓለማዊ ጉዳይ ራቀ። ጊዜውን መንፈሳዊ መጻሕፍትን በመመርመር ያሳልፍ ጀመረ። በጸሎትም ተጠመደ። በሂጶ በገደመው ገዳምም አያሌ አገልጋዮችን እያስተማረ ለሰሜን አፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ያበረክት ጀመር። ሕዝቡ የሂጶ ካህን ሁኖ ያገለግላቸው ዘንድ ተማጠኑት፤ ብቁ እንዳይደለ በመግለጽ ምርጫቸውን ተቃወመ። ዘግይቶ ግን ምናልባት ዐሳቡ ከእግዜር ዘንድ መጥቶ ቢሆንስ የሚል መንፈስ ስላደረበት ጥያቄውን ተቀበለ። ዐራት ዓመት በክህነት ካገለገላቸው በኋላ፣ የካርታጎው ጳጳስ የሂጶው ጳጳስ ረዳት ይሆን ዘንድ ሾመው። የሂጶው ጳጳስ እንዳረፈም የጵጵስናውን ሙሉ ሥልጣን ጠቅልሎ እንዲይዝ ተደረገ።
በዚህ መልክ የጵጵስና ተግባሩን በብቃት ማከናወኑን ተያያዘው። በየዕለቱ የወንጌል ስብከትን ያቀርባል፤ ችግረኞችን ይረዳል፤ እርቅ ያወርዳል፤ በታላላቅ ጉባዔያት ላይ በመገኘት አከራካሪ ለሆኑ ርእስት የመፍትሔ ዐሳቦችን ያቀርባል። የዐቃቤ እምነት ተግባሩንም ይወጣል።
በተለይ ፔላጊዮስን፣ ማኒንና ዶናቱስትን ክፉኛ ተፋልሟል። ተቅበዝባዥ ነፍሱ በክርስቶስ ፍቅር ከመማረኳ አስቀድሞ ሕይወቱን ያናተበውን የማኒን እምነት እየነቀሰ ጉድለቱን አመላክቷል። “ሰዎችን በትምህርትና በወዳጅነት መንፈስ እንጂ በማስፈራራትና በቅጣት ወደ አምላክ መንግሥት ማፍለስ አይቻልም” ሲልም ዶናቱስትን ተችቷል። “ኀጢአት ዐልባ ሕይወትን በመኖር ድነት ማግኘት ይቻላል” ባዩን ጰላጊዮስንም ተፋልሟል።
አብዛኛዎቹ ጸሓፍት እንደሚስማሙበት ከምዕራብ ቤተ ክርስቲያን አባል መካከል እንደ አውግስጢኖስ ዐሳቡን በጽሑፍ ያሰፈረ አባት አልታየም። እንደሚባለው ከሆነም ሁለት መቶ የሚሆኑ መጻሕፍትን ጽፏል። ይህን አስመልክቶ አንድ የታሪክ ሰው ሲናገር፣ “አውግስጢኖስ የጽሑፍ ችሎታውን ለማስመስከር ሳይሆን በልቡ ሞልቶ የተትረፈረፈውን የክርስቶስን ፍቅር ነው በወረቀት ያሰፈረልን” ሲል ዘክሮታል።
በተለይ በምድራዊና በሰማያዊ መንግሥት መካከል ያለውን ልዩነት በሰፊው የገለጠበትና ኋላም የሮም ሊቃነ ጳጳሳት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥልጣን ለማገዘፍ እንደ ፍኖተ ካርታ የተጠቀሙበት፣ “የእግዚአብሔር መዲና” የተባለው መጽሐፉ ተደጋግሞ የሚነሣ ቢሆንም “ኑዛዜ” የተሰኘው መጽሐፉ ግን እስካለንበት ዘመን በያዘው ፍሬ ዐሳብ ተወዳጅነቱን ያጣ አይደለም። ማርቲን ሉተር የተባለው የቤተ ክርስቲያን አባት ስለዚህ መጽሐፍ ሲናገር፣ “ከመጽሐፍ ቅዱስ ቀጥሎ የሚተካከለው የሌለ” በማለት መስክሮለታል።
የቅዱስ አውግስጢኖስን ሕይወት የዘገበ አንድ መጽሐፍ እንዳስተዋለው፣ ምሥራቃውያን አበው በነገረ ክርስቶስ ላይ ሲራቀቁ አውግስጢኖስ ግን የኀጢአት ባሕርይን፣ የእግዚአብሔርን ጸጋና የድነት መንገድን ብሎም በእነዚህ ርእሳት ዙሪያ የቤተ ክርስቲያን ሚና ምን ሊሆን እንዲገባ ያሰላስል እንደ ነበር ተናግሯል። ርግጥ በዘመኑ ተነሥተው የነበሩና ጸጋን ያክፋፉ አስተምህሮዎች የአውግስጢኖስን ትኩረት ወደዚህ መሥመር ሳያነቁት እንዳልቀረ በርካቶች ይስማማሉ። ከዚሁ ጋር የታሪክ ጸሓፍት እንዳሉን፣ ከቤተ ክርስቲያን አዳሾች አንዱ የሆነው ሉተር ድነትን በተመለከተ የአውግስጢኖስን ትምህርት በሚገባ ተጠቅሞበታል።
በሌላ አንጻር በተለያዩ የፍልስፍና ማዕበላት ሲናጥ የነበረው ይህ የቤተ ክርስቲያን አባት፣ ክርስትናን ከአመክንዮ ጋር በማቆራኘት ሁነኛ ተግባራትን አከናውኗል ባይ የፍልስፍና መምህራን እንዳሉ ሁሉ፣ ሁለቱን ጠባያት ለማቀናጀት የሄደባቸውን መሥመሮች ነቅሰው ለመረዳት የተቸገሩም አልጠፉም፤ ያም ሆኖ፣ እግዚአብሔር የማስተዋልን ኀይል በሰው ውስጥ አኑሯል፤ ከዚህ የተነሣ የሰው ልጅ የማገናዘብ ችሎታ በቅድመ ክርስትና ሕይወቱም ሆነ በድኅረ ክርስትና ዘመኑ ሊያበረክትለት የሚችለው ድርሻ የሚናቅ አይደለም ሲል ባወሳው አጠቃላይ መርሑ አማካይነት የፍልስፍናውን አካሄድ ማጤን እንደማይገድ ብዙዎች ይስማማሉ።
ለ38 ዓመታት ያለመታከት ሰሜን አፍሪካን የክርስትና ማዕከል በማድረግ ከምዕራባዊያን ጋር ያጋመዳት ሥሉጥ የነገረ መለኮት ማእምር፣ ታላቅ ሰባኪና ስመ ጥር ጳጳስ፣ ደግሞም በርካታ ጸሓፍት የመሰከሩለት ጥልቅ ዐሳቢና ደራሲ ቅዱስ አውግስጢኖስ አረፈ። አፍሪካም ታላቅ አባት አጣች።
ሼፈር በተለያዩ መጻሕፍቱ፣ አውግስጢን በሌጣው፣ ላውሬት በዘገባው፣ ምክረ ሥላሴ በጥራዙ፣ ግሩታየርድ በፍልስፍናው የነጠቡለትንና ስብዕናውን ከግብሩ አጋምደው የዘከሩትን ታሪክ እኛም ዝኒ ከማሁ አስፍረነዋል።
Add comment