[the_ad_group id=”107″]

እውነተኛ አምልኮተ ሕይወት

አምልኮን በአንድ ቃል ለመግልጽ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ከራስ ለሚበልጥ አንድ አካል የሚሰጥ ታላቅ አክብሮትና ስግደት፣ ወይም በፍርሀትና መንቀጥቀጥ ራስን ለሌላው ማስገዛት ወይም መስጠት የሚለውን ሐሳብ ይገልጻል፡፡ አምልኮ በዕለተ ሰንበት በጋራ ተከማችተን የምናሰማው የዝማሬ ድምፅ ወይም የምናከናውነው ሃይማኖታዊ ሥርዐትና ልማድ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን መላው ሕይወታችንን በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ ለጌታ ማስገዛትና መኖርን ያካተተ ልምምድ ነው፡፡ 

ሰው የተፈጠረበት ተቀዳሚ ዓላማ እግዚአብሔርን እንዲያመልክና ከእርሱ ጋር ሕያው ኅብረት እንዲኖረው ነው፡፡ እግዚአብሔር ፍጹም ጻድቅና ቅዱስ፣ ከክፋትም የራቀ ሕያው አምላክ ነው፡፡ ሰው ደግሞ ከኀጢአት ውድቀት የተነሣ ከጽድቅ ይልቅ ዐመፃን የሚሻ፣ ራስ ወዳድና ስግብግብ ፍጥረት ነው፡፡ ታዲያ ይህ ዐይነቱ ሰው እንዴት ሆኖ ለአምላኩ ፈቃድ የሚመች አምልኮ ሊያቀርብ ይችላል? በእውነቱ ይሄ ወሳኝ የሆነ ጥያቄ ነው፡፡ ምንም እንኳን በልጁ የቤዛነት ሥራ አምነንና ድነትን አግኝተን የምንመላለስ ብንሆንም፣ የምንኖረው ግን ከኀጢአት ጋር እየታገልን ነው፡፡ በፍጹም ልባችን ጨክነን ለአምላካችን ፈቃድ ብቻ ለመኖር ስንውተረተር በድንገት በሥጋችን ምኞት ተስበንና በኀጢአት ማጥ ውስጥ ተዘፍቀን ራሳችንን እናገኘዋለን፡፡ የሚገርም ነው!

በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረው ሰው አምላኩን ለማምለክ ሲቀርብ፣ ለአምላኩ የሚመቸው ነገር ምን እንደ ሆነ አስቀድሞ ማወቅ ይኖርበታል፡፡ በዛሬው አጭር መልእክቴ እውነተኛ የሆነ አምልኮተ ሕይወት ምን ዐይነት እንደ ሆነ ማሳየት ይሆናል፡፡ ይህንንም ከመዝሙር መጽሐፍ 131፥1-3 ሁለት ሐሳቦችን በመመልከት እንጀምራለን፡፡

አቤቱ ልቤ አይታበይብኝ፥

                        ዐይኖቼም ክፍ ከፍ አይበሉብኝ፤

                        ከትልልቆች ጋር ከእኔም ይበልጥ ከሚከበሩ ጋር አልሄድሁም፡፡

                        ነፍሴን አሳረፍኋት፥

                        የእናቱንም ጡት እንዳስተዉት ዝም አሰኘኋት

                        ነፍሴ የእናቱን ጡት እንዳስተዉት በእኔ ውስጥ ናት

                        ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም እስራኤል በእግዚአብሔር ይታመን፡፡

1. ባለው ነገር ረክቶ እና ደስተኛ ሆኖ መኖር

በእጃችን ያለውና የእኛ ነው የምንለው ነገር በሙሉ በራሳችን ብርታት ያገኘነው ሳይሆን፣ በአምላክ ቸርነት የተጎናጸፍነው መሆኑ ከገባን ባለን ነገር መርካትና መደሰት አይሳነንም፡፡ ያለኝ ይበቃኛል ብሎ የሚኖር ሰው ርካታው በጌታው ብቻ እንጂ ዙሪያውን በሰበሰበው ቁሳቁስ እንዳልሆነ ጠንቅቆ የተገነዘበ ሰው ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ተጨማሪ ነገሮችን ለማግኘት ሲደክም ከጌታው ጋር ያለውን መለኮታዊ ቁርኝት በቁሳቁስና ጠፊና አላፊ በሆኑ ነገሮች ይለውጠዋል፡፡ ይህንን የዘመረው ዳዊት በእስራኤል ላይ ንጉሥ የነበረ፣ በጊዜው ትልቅ ስምና ዝና የነበረው፤ ሀብትና ባለጠግነት ያላነሰው፣ ሚስቶችና ልጆች ያሉት፣ በሀገሪቱ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ መወሰን የሚችል ገናና ሰው ነበር፡፡ ይህ ሰው ከየት እንደተነሣና ማን እዚህ እንዳዳደረሰው በደንብ የገባው ስለ ነበር ከጌታው ጋር ያለውን ኅብረት በምንም ነገር ሊተካው አይፈልግም፡፡ ስለዚህ “ልቤ አልታበየም፤ ሐሳቤም ለአጉል ትልቅነት አልተነሳሳም፤ እንዲሁም አሁን ካለኝ የበለጠ ነገር ለመያዝ ከአቅሜ በላይ አልተንጠራራሁም” (ከአ.መ.ት. የተወሰደ) በማለት ባለው ነገር መርካቱን በግልጽ ተናገረ፡፡

ንጉሥ ዳዊት ይህንን ሲል ነፍሱ ተጨማሪ ነገር ሳትፈልግ ቀርታ አልነበረም፤ ነገር ግን የነፍሱን የውስጥ ጩኸት ዝም ማሰኘት ስለቻለ ነው እንጂ፡፡ በቁጥር 2 ላይ “ነፍሴን አሳረፍኳት” በማለት ይናገራል፡፡ እንደው ቆም ብለን ብንጠይቅ፡- ዳዊት ነፍሱን ያሳረፋት ከምን ነበር? ከብልጥግናና ክብር፣ በአጠቃላይም እግዚአብሔር ከሌለበት የተጨማሪ ነገሮች ፍለጋ … ወዘተ ነበር፡፡ ነፍሱ እነዚህን ነገሮች አጥብቃ ትፈልግ እንጂ እርሱ ግን በጭራሽ አልፈቀደላትም፤ እንደውም የነፍሱን ፍቃድ ዝም ማሰኘትን ነበር የመረጠው፡፡

ዘማሪው ነፍሱን እንዴት አድርጎ ዝም እንዳሰኛት በምሳሌ ሲያስረዳ፣ ለእናቱ ጡት ጽኑ የሆነ ፍቅር ያለው ሕፃን የሚወደውን ጡት ትቶ በእናቱ ጭን ላይ ዐርፎ እንደሚቀመጥ ሁሉ፣ ነፍሱ በውስጡ ጸጥ ብላ የተቀመጠች መሆኑን ይገልጻል፡፡ ዳዊት በምንም ዐይነት ሁኔታ ለነፍሱ ፈቃዷን እንድታደርግ ዕድል እንደማይሰጣት ይናገራል፡፡

2. ጌታን በመታመን መኖር

ዛሬ ባለን ነገር ረክተን ብንኖርና ልባችንን ከቁሳቁስ ይልቅ እግዚአብሔር ላይ ብናሳርፍ፣ ምን ያህል እርሱን ደስ ማሰኘት በቻልን ነበር?! ነገር ግን ዛሬ ከጌታ ይልቅ ልባችን ምንጥቅ የሚልለት ነገር ከልክ በላይ መብዛቱ እጅግ የሚያስገርም ነው፡፡ አንዳንዴማ ጌታ ትዝ የሚለን በዕለተ ሰንበት ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመሄድ ስንነሣ ብቻ ነው፡፡ በሌላው ቀን በጌታ አልረካ ያለው ልባችን በቀንና በሌሊት ሲንቀዋለል የሚከርመው አላፊና ጠፊ የሆነውን ቁሳቁስ በመፈለግ ላይ ነው፡፡ በጌታ ላይ ልባችን ይረፍ፤ ሌላውን ሁሉ ትተን ባለን ነገር እንደሰትና እንርካ፡፡ ዘማሪው እንዳለው ዛሬም እኛ ነፍሳችንን እናሳርፋት፡፡ የጌታን እንጂ የነፍሳችንን ፍቃድ ለመፈጸም አንድከም፡፡ አሜን ይሁንልን!

እውነተኛ የአምልኮ ሕይወት ያለው ሰው ሁልጊዜ ኑሮው በእምነት ነው፡፡ ሕይወቱ  ሰልፍና ውጣ ውረድ የበዛበት ቢሆንም እንኳን፣ በጌታው ላይ ያለው እምነቱ ፈጽሞ አይላላም፡፡ ከጌታው ጋር መልካም የአምልኮ ሕይወት ያለው ዘማሪው በዚህ ክፍል ላይ የሚናገረው፣ “ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም እስራኤል ሁሉ በእግዚአብሔር ይታመን” በማለት ነው፡፡ በጌታው የሚታመን ሰው ጌታውን ከሁሉ አብልጦ የሚወድድ ነው፡፡ በጌታው በመታመኑም ነፍሱ ከክስረት ይልቅ ወደ መንፈሳዊ ብልጽግና ትገባለች፡፡ ስለዚህም የተለማመደውን ይህንን መለኮታዊ በረከት ሌሎችም ይካፈሉት ዘንድ መግቢያ በሩ በጌታ ላይ መታመን እንደ ሆነ እየተናገረ ይጋብዛቸዋል፡፡

ጻድቅ ሕይወቱ ብርቱ ውጊያ የበዛበት ቢሆንም፣ ዘወትር በጌታው እየታመነ ወደ ፊት መገስገሱን አያቆምም፡፡ በእምነት የጌታውን ፊት እየተመለከተ በየዕለቱ ማለቂያ ከማይገኝለት የአምላኩ የበረከት ሙላት እየጨለፈ ይጎነጫል፡፡ በዚህ ስፍራ ላይ ዘማሪው መላው እስራኤልን ወደዚህ የመታመን ሕይወት ይጋብዛቸዋል፡፡ “ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ” የሚለው አባባሉ አማኝ ምንጊዜም ቢሆን መኖር ያለበት በእምነት መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ሰው ከአምላኩ ሌላ የሚታመንበትና የሚመካበት ነገር ካለው ፈጽሞ ጤነኛ የሆነ የአምልኮ ሕይወት ሊኖረው አይችልም፡፡ ዘማሪው በዚህ ክፍል ላይ ዘመኑን ሁሉ በእምነት ለመኖር መወሰኑን ያውጃል፡፡ ውሳኔውም ሆነ ጽኑ አቋሙ ጠንካራና የማይበገር ነው፡፡ ይሄ ሰው በጭራሽ እምነት አልባ ኑሮ ለመኖር የማይሻ ነው፡፡

ዛሬ በአምልኮ ሕይወታችን ውስጥ በጌታ መታመን ዋነኛ ተግባር እንጂ ዐልፎ ዐልፎ እየከረምን እንደ መረቅ የምናጣቅሰው ልምምዳችን ሊሆን አይገባም፡፡ የእግዚአብሔር እጅም በኀይል ለሥራ የሚንቀሳቀሰው በስሙ ለሚታመኑ ቅዱሳን ነው፡፡ ዛሬ ከጌታ ሌላ የተመረኮዝነውንና የተንጠለጠልንበትን ነገራችንን ትተን ራሳችንን ሙሉ በሙሉ በጌታ ላይ እንጣል፡፡ በፍጹም ልባችንም በእርሱ እንታመን፡፡ የዚያን ጊዜ በእውነትም ጌታን በሕይወታችን ማየትና ተኣምራቱንም ማጣጣም እንጀምራለን፡፡ የሰማነውን በልቦናችን ያክርምልን፡፡ ቸሩ አምላክ በቸር ያገናኘን፡፡

Share this article:

“ቤቴ” ወይስ “ቤታችሁ”?

የጌታ ኢየሱስን ምድራዊ ሕይወት ለማሳየት የተሠሩ በርካታ ፊልሞች እና የተለያዩ ምስሎች አሉ። ከሞላ ጎደል በሁሉም ውስጥ ተሥሎ የሚቀርብልን ገጽታው ግን በሆነ መልኩ ተመሳሳይ ነው፤ ርጋታ እና ልስላሴ ጎልቶ የሚነበብበት ገጽታ። በርግጥም ይህ በአብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባቦች በቀረቡ ታሪኮች ላይ ሳይመሠረት አልቀረም። ሆኖም አንድ ቦታ ላይ ይህ ይቀየራል፤ ጌታ ኢየሱስ የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛ እየገለባበጠ እና ለሽያጭ የቀረቡ እርግቦችን እያባረረበ በቤተ መቅደሱ ግቢ ሲዘዋወር።

ተጨማሪ ያንብቡ

Why Are There So Many Angry Theologians?

“Instead of bending our intellectual life toward the pursuit of others, we bend others toward the observation of our intellectual capabilities in hopes of praise that ought to be rendered unto the Lord.” Writes Ronni Kurtz on Christianity Today.

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.