[the_ad_group id=”107″]

ያላለቀው ጉዞ!

አገር ለማ የሚባለው መቼ ነው? ማልሚያ መንገዱስ? እንደ ዜጋ የእኔ ድርሻ ምን ሊሆን ይችላል? እነዚህ ጥያቄዎች ስለ አገሩ ግድ የሚሰኝ ሁሉ ከሚያነሣቸው ጥቂቶቹ ናቸው። የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የአገር ልማት ሚዛንን የነፍስ ወከፍ ጊቢ (per capita) ወይም አገራዊ ምርታማነት (GNP) ብቻ ከሚያደርገው ዕድገት (growth) ፊታቸውን በሂደት አዙረዋል። ትኩረታቸው ከዕድገት ወደ ልማት (development) የዞረው ያለ ምክንያት አይደለም። በሰው ልጅ ታሪከ አገር አድጎ አገር ሳይለማ ስለታየ ነው። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆኑት ተፈጥሮ የቸራቸውን ነዳጅ በመቸብቸብ፣ በኢኮኖሚያቸው ያደጉ ነገር ግን አገራቸው ያልለማ በርካታ የመካከለኛው የምስራቅ አገራት መኖራቸው ናቸው። ልማት ከዕድገት የሚለየው፣ የተገኘው ዕድገት ሁሉን ተጠቃሚ ማድረግ አለበት የሚል ንድፈ ሀሳብ በመሆኑ ነው። ጥቂቶችን ብቻ የሚጠቅም አገር ደግሞ በዘላቂነት ለማናችንም አይጠቅመንምና ከሚገኘው ዕድገት የሁላችንም ተጠቃሚነት ሊታሰብበት ይገባል። የዚህች መጣጥፍ ዐላማ ዕድገት ልማት እስኪሆን የሚሠራ ብዙ የቤት ሥራ እንዳለን ለማሳየት እና ሁላችንንም ለተሳትፎ ለመቀስቀስ ነው። ይህንን ለማሳየት እንዲረዳኝ፣ አገራዊ ልማትን በምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች መነጽር እመለከታለሁ። ጥረቴ፣ ከዕድገት ወደ ልማት የሚደረገው ጉዞ አለማለቁን በማሳየት ጉዟችንን እንድንቀጥል ለማበረታት ነው።


ፓለቲካዊ ትርፍ እና የወዳጆቻችን ዕርዳታ

ዕድገት የሆነ ዓመት ብቅ ብሎ፣ ሌላ ጊዜ የሚጠፋ መሆኑ ቀርቶ፣ በቀጣይነትና  (sustainable) ራስ ደገፍ (self-sustaining) ሲሆን አገር ለማ ይባላል።1 የአገራችን ዕድገት በዚህ ሚዛን ሲታይ ልማት ለመባል ብዙ ይቀረዋል፤ አለን የምንለው ዕድገት በብድር እና በዕርዳታ ላይ እጅጉን የተንጠለጠለ ሆኖ እናገኘዋለን። የዕድገት መሠረታችን የውጭ ዕርዳታ እና ብድር ሆኖ ከቀጠለ፣ የቁጠባ ባህል አዳብረን ቁጠባን ወደ ኢንቨስትመንት መቀየር ካልቻልን፣ ወደ ውጭ የምንልከው ምርት የሚያስገኘው ገቢ ጨምሮ ከፍጆታ ዕቃዎች (consumption goods) ባሻገር የማምረቻ መሣሪያዎችን (capital goods) ለመግዛት የማያስችል የውጭ ምንዛሬ እጥረት አንቆ ከያዘን፣ ከውጭ በምናስገባው ምርት  ላይ የተለት ተዕለት ኑሯችን መንጠልጠሉን ከቀጠለ፣ በዕርዳታም ሆነ በብድር የተቀበልናቸውን ግብአቶች በትክክል ማስተዳደር የምንችልበት እውቀት፣ ክኅሎት፣ አስተዳደራዊ ልምድ፣ ተቋማዊ ዝግጁነት፣ እንዲሁም የሥራ ባህላችንን በተሻለ መልኩ ካላዳበርን፣ ልባችንን ያሞቀው የለውጥ ተስፋ ፍንጣቂ የሸንበቆ ድጋፍ መሆኑ አይቀርም።

የተደገፍንበት ድጋፍ ሸንበቆ ነው የምልበት ምክንያት፣ የምንቀበለው ዕርዳታ እና ብድር መሠረቱ ሰዋዊ ርኅራኄ ብቻ ስላልሆነ ጭምር ነው። መንግሥታት እንካችሁ የሚሉን ብድርም ሆነ ዕርዳታ ዋንኛ መሠረቱ ከርኅራኄ በበለጠ ፓለቲካዊ ትርፍ መሆኑ ግልጽ ነው። በርካታ አገራት ለሌሎች አገራት ድጋፍ የሚሰጡበት ምክንያት፣ ያቺ አገር ባለችበት ቀጠና ውስጥ ለዓለም አቀፍ ደኅንነት (international security) ልትጫወት የምትችለው ሚና አዎንታዊ ነው ብለው ሲያምኑ ነው። አትጠቅመንም ያሉ ቀን ፊታቸውን ያዞሩባታል። የትጠቅመናለች አሳባቸው የተለወጠ ቀን ለዕርዳታ የተዘረጋው እጃቸው መልሶ ይታጠፋል። ዕርዳታም ሆነ ብድር ፓለቲካዊ መልኩ እንደሚጎላ ማሳያው፣ ዕርዳታ የሚሰጡት አገራት አምባገነን መሪዎች ከሥልጣን ቢገረሰሱ ሊመጣ የሚችለውን ውስጣዊ ቀውስ በማሰብ፣ አገራት መገለጫችን ናቸው ከሚሏቸው ዕሴቶች በተቃርኖ የቆሙ አምባገነኖችን የደገፉባቸውን ጊዜያት በመመልከት መገንዘብ እንችላለን። ስለዚህም፣ እንደ አገር ውጭ ተመልካች መሆናችን እንዲያበቃ እንትጋ። የዕድገታችን መሠረት አገራዊ እንዲሆን የቁጠባ ባህላችንን እናዳብር፤ የቆጠብናትን ተደጋግፈን እና ተባብረን ወደ ኢንቨስትመንት ለመለወጥ እንጣር፤ ወደ አገር የምናስገባቸውን የፍጆታ ዕቃዎች ወደ ማምረቻ ዕቃዎች እንዲያዘነብሉ በማድረግ ዛሬ ያስመጣነውን ነገር ነገ እኛው ልናመርተው እንጨክን፤ በአገራዊ ምርቶች ፍጆታዎቻችንን ለመቀየር እንሞክር፤ ያሉንን ውስን ንብረቶች ያለማባከን መጠቀም የምንችልባቸውን አስተዳደራዊ ጉልብትናዎች በመፍጠር ብክነት እናስወግድ።


ግብርናውን ማዘመን

ዕድገታችን ልማት ሲሆን፣ በምርት ሂደታችን ላይ የዓለም አገራትን ተጠቃሚ ካደረገ ለውጥ ጋር የምርታማነት መዋቅራዊ  ለውጥ (Structural adjustment) ይኖረናል።2 አገር ያላት ካፒታል እና የሰው ኀይል ውስን እንደ መሆኑ፣ ይበልጡኑ ውጤታማ ልንሆንበት በምንችለው መስክ ላይ መዋል ይኖርበታል። የአገራችንን የሰው ኀይል እና ካፒታል ዘመኑ ወዳመጣቸው እና ይበልጡኑ ትርፋማ ወደሚያደርጉ የኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በቃኘነው ቁጥር፣ የአገር ምርታማነትም (productivity) ሆነ ገቢው ያድጋል። በየጊዜው የሚፈጠሩት የቴክኖሎጂ ለውጦች፣ አገራዊ እና ዓለማቀፋዊ ንግዶች ፍላጎቶች (demand) መለዋወጥ፣ እኛም ከለውጡ እንድንጠቀም ከተፈለገ አብረናቸው መለወጥ ይኖርብናል። ያደጉ የሚባሉ አገራትን በምሳሌነት እናንሣ። ለአገር ኢኮኖሚ የአገልግሎት ዘርፍ የሚጫወተው ሚና እየጨመረ፣ በአንጻሩ ደግሞ የግብርናው እና የኢንዱስትሪው ድርሻ እየቀነሰ ሄዷል። የእኛው አገር ሁኔታ ግን ከቀድሞው እምብዛም አልተለወጠም፣ ዛሬም በገቢር ኢኮኖሚያችን ግብርና መር፣ በበሬ ማረስም መገለጫው ነው። ከአገራዊ ምርት ግብርናው 43% ድርሻ አለው፤ ትጋቱ ሕይወቱን ያንኑ ያህል ባይለውጥለትም፣ 80% የሚያህለው ሕዝባችን ላቡን አንጠፍጥፎ የሚሰዋው ለዚሁ ዘርፍ ነው። 85% የሚያህለው የውጭ ምንዛሬ ገቢያችን ምንጩ ግብርና ነው።3 እንዲህ ዐይነቱ ስታስቲካዊ አኀዝ የኩራት ምንጭ ሊሆን አይገባም። ውድ የሆነውን የሰው ኀይል፣ በቴክኖሎጂ ባልደረጀ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ በማያደርግ ግብርና ላይ መመሥረታችንን ከቀጠልን ውድድሩ በጦፈበት በዓለም ገበያ ከተሸናፊዎቹ ተርታ መገኘታችን ይቀጥላል። የሕዝባችንን ታሪክ ሁል ጊዜ በበሬ የሚያርስ የገበሬ እና የግብርና ታሪክ ማድረግ ሥልጡንነት ሳይሆን የኋላ ቀርነት ምልክት መሆኑን አንዘንጋ!


እውቀት ተኮር ኢኮኖሚ ግንባታ

የአገር ልማትም እንዲሁ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር አብሮ መሄድን ይጠይቃል።4 ማናችንም የግል ሕይወታችንን ብንመለከት የቴክኖሎጂ እመርታዎች ሕይወታችንን በማጎልበት ሆነ ኑሮዋችንን በማቅለል ረገድ የሚጫወቱት ሚና መገንዘብ አይቸግረንም። በአገር ደረጃም የቴክኖሎጂ ሚና ቢበዛ እንጂ አያንስም። በኢኮኖሚ ዐደገ የሚባለው ዓለም እውቀት መር በሆነ መልኩ ዓለማችንን እየመራ ባለበት ሁኔታ፣ አዲስ እውቀትን መፍጠር፣ የተፈጠረውን መጠቀም እና ማሰራጨት፣ ለኢኮኖሚ ስኬት እና ለማኅበረ ሰብ ልማት ያለውን ሚና ልንንቅ አይገባም። ከቴክኖሎጂ ጋር አብሮ መዘመን ሲባል ግን፣ በሌላ ቦታ የተፈበረኩ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ብቻ አይደለም። እንደ ማኅበረ ሰብ ፈጠራን የተሞላን እና የወደፊቱን ተመልካች መሆን አለብን። ይህ እንዲሆን ተቋማት የራሳቸውን የምርምር እና የጉልብትና ማእከል እንዲፈጥሩ ማበረታት ያስፈልጋል። በትምህርት ተቋማትና በኢንዱስትሪው መካከል ያለው ትሥሥርም መጠናከር ያስፈልገዋል። በየቦታው የከፈትናቸው የሙያ ተቋማት፣ ሁለተኛ ዙር ተግባራዊ ሥልጠና የማይፈልጉ፣ ይልቁኑ ቴክኖሎጂን በመፍጠር ገንቢ ሚናን የሚጫወቱ ምሩቃንን ማብቃት ይኖርባቸዋል። 

ኢኮኖሚያችንም ብልጠት ተኮር ሳይሆን እውቀት ተኮር መሆን አለበት። ሌላ ቦታ የደረጀ ቴክኖሎጂ መጠቀም የመቻል ክኅሎትን ማደርጀት ብቻውን እንደ ዘመንን የሚያስቆጥርበት ዘመን ካላበቃ፣ በውድድሩ መስክ ተከታይ መሆናችን ይቀጥላል። የትምህርት ሥርዐታችን ከአሁን ተኮርነት ዘልቆ፣ አስቀድሞ ተመልካቾችን በመፍጠር፣ የወደፊቱን ቴክኖሎጂ ፍላጎት የሚመለከቱ እና የሚፈጥሩ ሰብእናዎችን ወደ መፍጠር መቃኘት ይኖርበታል። የትምህርት ሥርዐቱ ከቁጥር ባሻገር ጥራት ላይ ማተኮር ካቃተው ላለንበት ችግር መፍትሔ የሚሆኑ ሰዎችን አይፈጥርም። አዳዲስ ቴክኖሎጂ ከመጠቀሙ ጎን፣ ዐውዳዊነትን ታሳቢ ያደረጉ ቴክኖሎጂዎችን መፈበረክ ካልቻልን፣ የደረስንበት ቴክኖሎጂ ሁሉ ለዘመኑ ያረጀ እና ለተወዳዳሪነት የማያበቃ መሆኑ አይቀርም። ይህ እንዲሆን ደግሞ እውቀትን ማግኘትን አስመልክቶ አስተሳሰባችን በአዲሰ መልኩ መቃኘት ያስፈልገዋል። ቴክኖሎጂ እንዲዘምን ከተፈለገ፣ ማኅበረ ሰባችን ሳይንሳዊ እና ተራማጅ (scientific and progressive) እንዲሆን ይጠበቃል። ሳይንሳዊ እምርታዎችን ማናናቃችንን ከቀጠልን እና ወደ ፊት ተመልካች ካልሆንን፣ ኋላ ቀርነታችንን የሚነጥቀን አይኖርም።


ዘመናዊ ፓለቲካ፣ ማኅበረ ሰብ እና ተቋም

የሚፈለገው አገራዊ ልማት ሲኖር፣ ፓለቲካችንን (political modernization)፣ ማኅበረ ሰባችንን (social modernization) እንዲሁም ተቋሞቻችንን (institutional modernization) ይዘምናሉ።5 ፓለቲካዊ ልማት መኖሩን የሚያመለክቱ ምልክቶች ይታወቀሉ። እንደ ፓለቲካል ሳይንቲስቱ ሳሙኤል ሀንቲግተን ገለጻ፣ ፓለቲካ የሚዘምነው የሥልጣን ምንጭ ግንዛቤ አመክንዮ ሲሆን፣ ፓለቲካዊ መዋቅሮች ልይይት (political differentiation) ሲኖራቸው እና ፓለቲካው ሁሉን አሳታፊ ሲሆን ነው።6 የመንግሥት አስተዳደር (ፓለቲካ) ልይይት ኖረው የሚባለው በአስፈጻሚ፣ በሕግ አውጪ እና በዳኝነት ሥረዐት መካከል ያለው የኀላፊነት ወሰን በትክክል ሲሠመር ነው። የዳኝነት ሥርዐቱ ፍትሕን የሚያስከብርበት መንገድ ከየትኛውም ፖለቲካዊ ተጽእኖ የጸዳ፣ መሠረታዊ መብቶችን ለፓለቲካ ጥቅም የማይሸረሽር፣ ሕግን የሚተረጉምበት ልዕልና የተከበረለት እንጂ የይስሙላ መሆኑ ሲያበቃ፣ ፓለቲካው እንደ ዘመነ ማሰብ እንችላለን። የዳኝነት ሥርዐቱም እንደ ፈለገ እንዲፋንን አይፈቀድለትም፤ በሕግ አውጪው እና በአስፈጻሚው ክትትል ይደረግበታል። አስፈጻማዊ ዳኞችን ለሹመት ያቀርባል፣ ሁኔታዎች ሲሟሉ ፍርደኞችን ይቅር ይላል። ሕግ አውጪው ደግሞ የቀረቡለትን ዳኛን ተመልከቶ ይሾማል፤ ሕግ አስፈጻሚ ነጻነትን እንዳይገፋ፣ ሕገ መንግሥትን በመተርጎም የእያንዳንዳችንን ነጻነት ይጠብቃል።

ማኅበረ ሰብ ሲዘምን፣ በማኅበረ ሰብ ውቅር ውስጥ ያለ ተዋረድ ምሥጢሩ የተመዘዝንበት ሥረወ ግንድ ወይም ጎሣ መሆኑ ይቀርና፣ በእኩል ነጻ መርጫችንን በመጠቀም የቀረቡ ዕድሎቻችንን የቱን ያህል ተጠቅመናቸዋል በሚለው ላይ የተመሠረተ ይሆናል። ያኔም በሰፈራችን እኛ ያላለማውን፣ ሌላው ግን ላቡን አንጠፍጥፎ የገነባውን ንብረት ለመቀራመት አመቺ ቀን አድብቶ የሚጠብቅ ወጣት አይኖረንም። በምጣኔ ሀብት ዕይታ፣ ተቋማት የእርስ በእርስ ግንኙቶቻችን እንዲያስተዳደሩ ብለን የፈጠርናቸው ፓሊሲዎች፣ ሕግጋት፣ መመሪያዎች፣ መሠረታዊ እሴቶች፣ የማትጊያ ሥርዐቶች፣ የተጠያቂነት ሥርዐቶች፣ ተቀባይነት ያላቸው ልምዶች ናቸው። እነዚህ ተቋሞቻችን ዘመኑ የሚባለው፣  ሕግጋቶቹ መደበኛ ሲሆኑ (formal institutions) እና በዕለት ተዕለት ኑሮ ውስጥ መተግበር ሲችሉ እና ከመንጋ ፍርድና አድሎ ከተሞላ የሀብት ድልድል መትረፍ ሲቻል ነው። ተቋማት ሲዘምኑ እነዚህን ሕግጋት በትክክል መተግበር ሲያሸልም፣ በአንጻሩ ሕግጋቱን ደግሞ መተላለፍ ያስቀጣል። ኢመደበኛ ሕግጋት (informal institutions) በሕግ ማእቀፍ ያወጣንላቸውን ሕግጋት መጣረሳቸውን ከቀጠሉ ያሉን ሕግጋት ከወረቀት አንበሳነት ባለፈ የሚጠቅሙን ነገር አይኖርም። የወረቀት አንበሳ የማስፈራቱ ወሰኑ ሩቅ አይደለም፤ ያወቅን ቀን ተጠግተን እንዳብሰዋለን።


የምንናፍቀው ነገ

ልማታችን እንዲፈለግ የዜጎቻችን የኑሮ ሁኔታ እጅጉን መቀየር ይኖርበታል።7 ከምንም በፊት የወገናችን ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ማብቃት አለበት። እስከ መቼስ ድረስ የዕለት ጉርስን ማግኘት ተአምር እንደ ሆነ ይቀጥላል? በሰፈሮቻችን በዝተው ማየት የምንፈልጋቸው በዕድሜ የጠገቡ አዛውንት ብርቅዬ መሆናቸው ማቆም አለበት። ስንቱ ያለ ዕድሜው በለጋነቱ ተቀጨ? ልጆችስ ያለ እናታቸው ዐደጉ? ስንትስ የጎዳና ልጆች አሉን? በሕክምና ሊረዱ የሚችሉ በስቃይ መማቀቃቸው መቀነስ አለበት። ልጆች ልጅነታቸውን ከዕድሜያቸው ባለፈ ኀላፊነት እንዳያጣጥሙት ከመነጠቅ (child labor) ተርፈው፣ ልጅነታቸውን ሲቦርቁበት መመልከት ሁላችንም እንፈልጋለን። ዕድገታችን ራስ ገዝ እና ቀጣይ እስኪሆን፣ የኢኮኖሚ አወቃቀራችን ይበልጡኑ አገራችን በዓለም አቀፍ ውድድር ተጠቃሚ በሚያደርገን መልኩ እስኪቃኝ፣ የቴክኖሎጂ ደረጃችንን ሌሎች በደረሱበት ልክ እስኪደርስ፣ ፓለቲካችን፣ ማኅበረ ሰባችንን እና ተቋሞቻችንን እስኪዘምኑ፣ የዜጎቻችን የኑሮ ሁኔታ መሠረታዊ በሚባል መልኩ እስካልቀየር፣ ዕድገታችን ያላለቀ ጉዞ ነውና ወገባችንን አሸንፍጠን ልንራመድ እንደ አገር እንጨክን።


  1. Grabowski, Richard, Sharmistha Self, and William Shields. Economic Development: A Regional, Institutional, and Historical Approach: A Regional, Institutional and Historical Approach (Routledge, 2014),5
  2. Ibid.
  3. Heshmati, Almas, and Haeyeon Yoon, eds. Economic Growth and Development in Ethiopia. Springer Singapore, 2018፣ 138
  4. Richard, Self, and Shields, Economic Development: A Regional,5
  5. Ibid.
  6. Bendix, Reinhard, and Coenraad M. Brand. State and society: a reader in comparative political sociology. University of California Press,1973, 1973)፣ 170.
  7. Richard, Self, and Shields, Economic Development: A Regional,5

Share this article:

ልዩ ወንጌል

በሕንጸት ቁጥር 1 ዕትም፣ በአውራ ነገር ዐምድ ሥር “የወንጌላውያኑ መንታ መንገድ” በሚል ሐተታዊ ጽሑፍ ተስተናግዶ ነበር፡፡ ጽሑፉ በዋናነት ከመቶ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው የወንጌላውያን ክርስትና በኢትዮጵያ ይዟቸው ስለመጣው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ለውጦች በማተት፣ አማኝ ማኅበረ ሰቡ ስላበረከታቸው በጎ አስተዋጽዖዎች በመጠቆም ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ይህንን በጎ ተጽእኖውን ማስቀጠል በማይችልበት ደረጃ ላይ እንደደረሰና ለዚህም ምክንያቱ ልዩ የሆነ አስተምህሯዊ አቋምና ልምምድ በቤተ ክርስቲያን መተዋወቁ እንደ ሆነ ይጠቁማል፡፡ ይህ ልዩ አስተምህሮና ልምምድ ደግሞ በ“እምነት እንቅስቃሴ” ወይም በ“ብልጽግና ወንጌል” የተጠመቀ “ክርስትና” ወደ አማኝ ማኅበረ ሰቡ መዝለቁ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

እግዚአብሔር – አለ!

“የሰላም መረበሽና የፍትሕ ቀውስ እየከረረ በመጣበት በዚህ ዘመን፣ እንደ ክርስቲያን ተስፋ የምናደርገው የታሪክን አቅጣጫ በልጓም የያዘውን ልዑል እግዚአብሔርን ነው።” መጋቢ ግርማ በቀለ (ዶ/ር) “እግዚአብሔር አለ!” በተሰኘው በዚህ ዐጭር አጽናኝ መልእክት ያስተላለፉትን ያንብቡ።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.