[the_ad_group id=”107″]

የሰሞኑ የኅብረቱ ትጭጭት (ጋብቻ)

የአብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ቁጥራቸው 150 የሚደርሱ “መንፈሳዊ” ተቋማትን በአጋር አባልነት የመቀበሉን መራር እውነታ አውቀናል። በኅብረቱ መግለጫ ሚዲያ ተጠርቶላቸው የካሜራ ክብር ያገኙት ግን አራቱ ብቻ ናቸው። ሌሎቹ ነገራቸው በድብስብስ የታለፈ ሊባል የሚችል ነው። ራሳቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ብቅ ብለው እኛም ነበርንበት ባይሉ መኖራቸውን ከቶውን ባላወቅን ነበር። አራቱ ትኩረት ያገኙበት ምክንያት፣ በተክለ ሰውነት “አውራዎች” ስለሆኑ ይሆናል።የኅብረቱ በአጋርነት ተቀብለናል ውሳኔ፣ ከጥቂቶች በስተቀር፣ ለአብዛኛው ሰሚ ዱብ እዳ የሚባል ነው። የውሳኔው ሂደት አንድ ዓመት ወስዷል ሲል ያበሰረን መግለጫ፣ የማይታረቁ ስሜቶችን በወንጌላውያን አማኞች መካከል ቢፈጥር አይገርምም፤ ደግሞም ፈጥሯል። አዲሱ ውሳኔ ዱብ ያለው፣ አውግዘናል ባልን ማግስት (አንድ ዓመት) መሆኑ ለግራ መጋባቱ የበኩሉን ሚና ተጫውቷል።

ዓመትን ለምን ማግስት አልኩት? በምክንያት ነው። ዓመት የማግስትን ያክል ያነሰብኝ፣ እያወራን ያለነው ያልተቀደስ ትጭጭት (ጋብቻ) የተከናወነው በርካቶች ከሚወከሉበት ተቋም ጋር ከመሆኑ የተነሣ ነው። ግዙፍና ብዙኀን ባለቤት የሆኑበት ተቋም ባለቤቱ ግለ ሰቦች ስላልሆኑ፣ በርካታ ክርክር እና ክፍፍል ያለበት ነገርን፣ በዚህ ፍጥነት ለመቀየር መድፈር አልነበረባቸውም። እንዲህ ዐይነት ተቋማት፣ አባሎቻቸውን አማክረው፣ ሐሳብ አንሸራሽረው፣ ጥናት አስጠንተው ወደ ድምዳሜ የሚመጡ እንዲሆኑ ይጠበቃል። በዚህ ውሳኔ ግን ባለ ድርሻ የሚባሉ አካላት በትክክል የተደመጡበት ሂደት (due process) ሆኖ አላገኘሁትም። በቦርድ ውስጥ ጭምር ውክልና ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት ተቀላቀሉ ከተባሉት ጋር ገና ያልተቋጨ ውይይት ላይ መሆናቸውን መስማት የተሳትፎ ውስንነትን እና ጤናማ ያልሆነ ጥድፊያ ሂደቱ ታይቶበታል የሚለውን መላምቴን ይበልጡኑ ያጠናክረዋል። በእኔ ሚዛን በየትኛውም ምልከታ፣ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ለተካተቱበት ኅብረት ዓመት በፈጀ ሂደት ተቀላቅለዋል የሚለው ውሳኔ ጥድፊያ ነው፤ ውሳኔውም ስሕተት ነው።

እንደ እኔ ምልከታ ውሳኔው የፈጠራቸው ስሜቶቹ እና ምላሾቹ ሦስት ዐይነት ናቸው። የመጀመሪያዎቹ፤ ፈንዳቂዎች ናቸው። ጥቂት የማይባሉ ሰዎች እንኳን ደስ አለን ሲሉ ተገባብዘዋል፤ ጊዜው የፈንጠዚያ ሆኖላቸዋል። ለእነርሱ የዜማ ጊዜ መጥቷል። እነዚህ፣ ኅብረቱን ‘ብትዘገይም አበጀህ’ ብለውታል፤ ተቀላቃዮቹንም እንዲሁ ‘ልበ ሰፊ’ በሚል አወድሰዋቸዋል። ለእነርሱ አዲሱ መንገድ የኅብረት እና የመያያዝ ጉዞ ነው። እኚህ ያልተካተቱ ሌሎችም እንዳሉ ያምናሉ፤ በሩም ይበልጡኑ ለወደፊት ወለል ብሎ እንዲከፈት ይጠብቃሉ። ለእነርሱ ትጭጭቱ (ጋብቻው) ተጀመረ እንጂ ገና አልተጠናቀቀም።

ሁለተኛዎቹ፤ ያልበረዳቸው እና ያልሞቃቸው ሊባሉ ይችላሉ። ትኩስ ስሜት አለማሳየታቸው የግድ ዳተኝነታቸውን አያመለክትም። ትንታኔያቸው ስሜት አልባ (dispassionate) እና አቋማቸው ለመገመት የሚያስቸግር (ambivalent) ለሰሚዎቻቸው መምሰሉ ግን አይካድም። ምናልባትም አንዳንዶቹ በጉዳዩ ላይ ጊዜ ሰጥተው ገና በማሰብ ላይ ያሉ ስለ ሆኑ ይሆናል። ለድምዳሜ የምንፈልገው ጊዜ መለያየቱ ብቻ ሊያለያየን አያስፈልግም። ከእነዚሁ መካከል አንዳንዶቹ ስሜት አልባ የሆኑት፣ በኅብረቱ ማንነት (identity) እና ፋይዳ ላይ ገና ድሮ ተስፋ ከመቁረጣቸው የተነሣ ነው። ለእነርሱ፣ ኅብረቱ የወንጌላዊነት ሰብእናው ከተምታታበት ስለሰነበተ፣ አዲሱ ውሳኔው የሚጠበቅ እንጂ የሚያስገርም አይደለም። እይታቸው ማንነቱ ድሮውን ከጠፋበት ኅብረት፣ ከዚህ የተሻለ ውሳኔ መጠበቅ የዋህነት እንደ ሆነ ያምናል።

ሦስተኞቹ፤ ተፋላሚዎች ናቸው። በጉዳዩ እጅግ ተቆጥተዋል፣ አዝነዋል። ያዘኑበትን ምክንያት የምተረጉመው በአዎንታዊ እይታ ነው። እነኚህ በኅብረቱ በተወሰነ መልኩ ያምናሉና፣ ከትላንት ይልቅ ዛሬ እንዲበረታ ተስፋ የሚያደርጉ ነበሩ። ልባቸው የታመመው ከዚሁ ተስፋ የተነሣ ሳይሆንም አልቀረም። ኅብረቱ ለእነርሱ በሂደት ሊዋጅ የሚችል ነበረ፤ ስለዚህም ተፋላሚዎቹ፣ በኅብረቱ ውሳኔ እጅጉን ተቀይመዋል፤ አዝነዋል። አንዳንዶቹ እንደውም ግልጽ የዘመቻ ፍልሚያ ጀምረዋል፤ “ኅብረቱ አይወክለኝም” ሲሉም ተሰምተዋል። ከመካከላቸው ጥቂቶቹ ኅብረቱን ሆነ የሚወክሉትን አንዳንድ ሰብዕናዎችን (ፕሬዚዳንቱንም ሆነ ቦርዱን) በግልጥ ዘልፈዋል። ዘለፋቸውም ባለንበት የመቻቻል ዘመን፣ ‘ጽንፈኛ’ የሚል ስያሜን ቢያሰጣቸው አይገርምም። ለእነርሱ ጉዳዩ ያለ አቋም እና ያለ ስሜት የሚጻፍ ነገር አይደለም። ልመናቸው፣ ‘ስሜታዊ አትሁኑ’ አትበሉን ነው። ጥያቄያቸው አሁን ካልተቆጣን መቼ እንቆጣ ነው።

እኔም ምድቤ፣ በውሳኔው ካዘኑት ውስጥ ነው። ውሳኔው ትልቅ ታሪካዊ ስሕተት ነው ብዬም አምናለሁ። ይህንኑ ሐዘኔን ስገልጽ በምችለው መጠን ክርስቲያናዊ ጨዋነትን ለመላበስ እና ለማይመስሉኝ ምልከታዎች ቸርነት ለማድረግ ጥራለሁ። እንደ ሁሌው፣ ግራጫ ባልሆነ ጉዳይ፣ ስሕተት እና ትክክል ሊባል በሚችል ነገር መካከል መሆን ስሕተት ነው ብዬ እሟገታለሁ። እንድንወስን የሚፈለገው ምርጫ በእውነትና በሐሰት መካከል ሲሆን፣ መኻል ሰፋሪነት ሰዋዊ እንጂ አምላካዊ ጥበብ አይደለም። አንዳንዶች ትክክል ሁሌ መኻል ያለች ትመስላቸዋለች፤ ይህ አስተሳሰብ ግን ሁሌ ትክክል አይደለም። አንዳንዴ የእውነት መዳረሻ፣ በተቃራኒ አስተያየቶች መኻል ሳይሆን ጥግ መሆኑንም አስተውላለሁኝ።

‘ውሳኔው አሳዝኖኛል’ የሚለውን ምልከታዬን ሳንጸባርቅ፣ አቀራረቤ በምንም መልኩ የታይታ ልከኝነት (political correctness) ለማሳየት በማሰብ አልተቃኘም። በዚህ ዘመን ትልቁ ችግርም ቅኝታችን የታይታ ልከኝነት መሆኑ ነው። የታይታ ልከኝነት የሚፈጥረው የአሸማጋይ አስተሳሰብ፣ አውነትን ለራስ ገጽታ ግንባታ መጠቀሚያ ስለሚያደርግ እንቀዋለሁ። ስለ እግዚአብሔር እና ስለ መንግሥቱ እያወሩ ራስን እና የሚገኝ ጥቅምን ማእከል ማድረግ ደግሞ የስሕተቶች ሁሉ ስሕተት እንደ ሆነ አምናለሁ። እርሱ እኮ ልባችንን ያያል፤ ይመዝናልም። ዋጋችንን ከሰውም እግዚአብሔርም አናገኘውምና ሸላሚያችንን መምረጥ ይገባናል። እርሱን ስንከተለው የገባነው ቃል ኪዳንም ‘ደስ ላሰኝህ እጥራለሁ’ እንጂ ‘ሰዎችን ሁሉ ደስ አሰኝልሃለሁ’ የሚል አልነበረም፤ አይሆንምም። ገብቶኛል ያልኩትን የዛሬዪን እውነት ለሕሊናዬ ባለኝ ታማኝነት በግልጽ አስቀምጣለሁ። በጽሑፌ፣ ገብቶኛል ከምለው እውነት ባሻገር፣ የማንም ባለ እዳ አይደለሁም። ነገሬን ግልጽ ላድርግ። ቅልቅሉ ስሕተት ነው፤ ትጭጭቱ (ጋብቻው) ቅዱስ አይደለም። ምናባልባትም ከዚህ ቀደም ኅብረቱ ሠርቶ ከሚያውቃቸው ስሕተቶች ሁሉ የከፋ ታሪካዊ ስሕተት ነው።

ለምን መግለጫውን ታላቅ ታሪካዊ ስሕተት ስል እንደፈረጅኩት ምክንያቶቼን ልጥቀስ። ምክንያቶቼ ለአንዳንዶች ውሀ የሚቋጥር ትችት ሊሆን ይችላል፤ ለሌሎቹ ደግሞ በተቃርኖ። የደጋፊዎቼን ቁጥር ሳላሰላ፣ የማምንበት እውነትን የመናገር ግዴታዬን መወጣት እንዳለብኝ እረዳለሁ። ‘ኅብረቱ ተሳስቷል’ የሚለውን ሙግቴን የማዋቅረው ኅብረቱ ተቀበልኳቸው በሚል የዘረዘራቸውን የቅበላ መስፈርቶች ትክክል ናቸው በሚል ዕሳቤ አይደለም። ስለምን የኅብረቱን ሚዛን አልገዛውም? ምክንያቶቼ በዋነኝነት ሁለት ናቸው። አንደኛው፤ አንዳንዶቹ መስፈርቶቹ ግልጽነት የሚጎድላቸው ከመሆናቸው የተነሣ ነው። ለምሳሌ፣ “ክርስቶስን የሚሰብኩ” የሚለውን ሚዘን ላንሣ። እንዳሻው ተናግሮ፣ የሚፈልገውን አድርጎ፣ ‘ኢየሱስ ጌታ ነው’ የሚለውን የጨመረ ሁሉ ክርስቶስን ሰበከ በሚባልበት ዘመን፣ ክርስቶስን መስበክ የሚለው ሚዘን በግልጽ ካልተብራራ በስተቀር ሁላችንንም አያግባባም። በማያግባባ ሚዛን ነገርን መመዘን ሀቅ ላይ አያደርስም። ነገሩ የጣት ቀለበትን፣ በድሮው የወፍጮ ቤት ሚዛን እንደመመዘን ነው። 1 ሆነ 100 ግራም ስታስቀምጡበት፣ ሚዛኑ ልዩነታቸውን አያሳይም። የወርቅን ዋጋ የምናውቅ 1 ግራምን ከ100 ግራም ጋር አንድ አለመሆኑ አይጠፋንም። ሁለተኛ፤ አንዳንዶቹ ሚዛኖች ከተመዛኙ እጅግ ጥቂት የሚጠብቁ (minimalist) ከመሆናቸው አንጻር ነው። ለምሳሌ፣ ‘ዘይት አትሽጥ’ እና ‘ገስተ ሀውስ ዝጋ’ የሚሉትን እናንሣ። እነዚህ እኮ ልክ እንደ ራስ ምታት ናቸው። ራስ ምታት በአብዛኛው ምልክት እንጂ ዋና በሽታ አይደለም። በማስታገሻ ዝም ቢደረግ፣ ታማሚው ጥልቅ ችግር ስላለበት ከችግሩ አይድንም። እንዲህ ዐይነት መፍትሔ፣ ሕመሙን እንጂ በሽታውን መግደል አይደለም። ለነገሩ ጉዳዩ ሲጀምር መቼ እኚህ ጥቃቅን ነገሮች ሆኑና? ዝሆኑን ውጠነው፣ ስለ ትንኞቹ ማውራት ጥበብ ሊሆን የሚችል አይመስለኝም። ክሱን አሳንሰን ፍርዱን መቀነስ ጥበብ ቢመስልም፣ እንዲህ ዐይነቱ ጥበብ ማናችንንም ላመንበት እውነት ታማኝ አያደርገንም። ስለዚህም፣ ኅብረቱ ባወጣቸው ሚዛኖች በመመሥረት ቅልቅሉን መዳኘት ልክ ነው ብዬ አላስብም። ከዚህ በታች ቅድስና የጎደለውን መተጫጨት (ጋብቻ) በኅብረቱ ሚዛን ሳልቀነበብ፣ ከመሰሉኝ አቅጣቻዎች አንጻር እተቻለሁኝ። እንደ ሁሌው ላድነው የምፈልገው፣ የማሳዝነው አይደለምን?

ስሕተት አንድ፡- ታሪካዊ ስሕተቶችን ማስቀጠል

ኅብረቱ ከዓመት በፊት አቋም ይዞ፣ መግለጫን ስለ እውነት አውጥቷል። እውነት ቀን ወጥቶላት ተወድሳ ነበር። ሽንጡን ገትሮ ለእውነት ሲከራከር፣ የማስተማሪያ መድረኮችን ሳያሰልስ ኅብረቱ ሲያዘጋጅ፣ የወረቀቱ አንበሳ ጥርስ አወጣ የሚል ውዳሴ ተቀብሏል። እኔም ጎራዬ ኅብረቱን ካወደሱት መካከል ነበር። ምክንያቱም ከእውነት ጋር በመቆሙ ክብር ይገባው ነበር። የበኩሌን አስተዋጽኦ ለማበርከትም ተግቻለሁኝ። እውነት የምትነገርበትን ምኅዳርን ውሳኔው ስላሰፋ፣ ዛሬ መልሶ እስኪቀለብሰው ድረስ ተደስቻለሁኝ። ያ ያወደስነው መንገድ ራሱ ግን እንከን አልባ አንዳልነበረ እረዳለሁ። እንከኑም ይስተካከላል በሚልም ተስፋ አድርጌያለሁኝ፤ ክፍተቱንም እንደ ግለ ሰብ ለሚመለከታቸው ሰብእናዎች ጠቁሜያለሁ። በግሌ ውሳኔው ወደ ውስጥ ጭምር ተነጣጥሮ፣ በመግለጫው የተወገዙ አስተምህሮዎችን የሚቀበሉ የኅብረቱን አባላት (ለምሳሌ፣ ዊነርስ ቻፕል) የማረቅ ወይም የመቀነስ ሥራ ይሠራል በሚል ጠብቄያለሁ። ይህ ግን አልሆነም፤ የጣት ቅሰራው ወደ ውጭ ብቻ እንደ ሆነ ቀጠለ። ራስን መተቸት የእውነተኛ መንፈሳዊነት ሀ ሁ መሆኑን እንደ ኅብረት ዘነጋን። በመካከላችን ያሉ ሐሰተኞች የፈለጉትን በየመድረካቸው እየሰበኩ፣ በዝምታ የአንድነት ጊዜያችንን እስከታደሙ ደረስ ግድ አልሰጠንም። በመካከላችን ሆነው ከስሕታቸው ሳይታረሙ በዝምታ መሸበባቸው ብቻ አረካን።

ኅብረቱ ትችቱን የሚሰነዝረው ወደ ውጭ እንጂ ውስጣዊ ምልከታ ኖሮት ራሱን አለማረቁን እኛም አየን፤ ሌሎችም ከውጭ ሆነው ታዘቡን። በእንዲህ ዐይነት ሁኔታ የምንተቻቸው ሁሉ ከወቀሳ ለማምለጥ እኛኑ መቀላቀል ያስፈልጋል ብለው ቢያሰሉ ምን ይገርማል? አይገርምም። በዚህ ቅልቅል የሆነውም ይኸው ነው። ስሌቱ እንዳንተችና እንዳይጠነቋቆሉብን፣ እንቀላቀላቸው የሚል የአእምሮ ቅኝትን ፈጠረ። በሩ በቅልቅሉ መንገድ ወለል ተብሎ ተከፈተ፤ ባለን አቅም ጠብቀን መከላከል በማንችልበት መጠንም ሰፋ።

በሌላ አነጋገር ኅብረቱ ወንጌላውያን ሊባሉ የማይቹሉ ማኅበሮችን በታሪካዊ የስሕተት ውሳኔ ከዚህ ቀደምም አቅፎ ነበር። በአሁኑ የመቀላቀል ውሳኔ ኅብረቱ ያሳየው የቀደመውን መንገዱን አለመማሩን ብቻ ሳይሆን፣ የቀደመውን ታሪካዊ ስሕተት ማስቀጠል መፈለጉን ጭምር ነው። የዛሬው ስሕተት ከቀደመው አብዝቶ ይበልጣል። የዛሬው የኅብረቱ መሪዎች፣ ከዚህ ቀደሞቹ በበለጠ በውሳኔያቸው ሊወቀሱ ያስፈልጋል። ምክንያቱ ደግሞ የቀደመው ስሕተት ኅብረቱ አዳልጦት የወደቀበት ሲሆን፣ የአሁኑ የቅበላ ስሕተት ኅብረቱ በውዴታ፣ ብዙ መረጃ በእጁ እያለ፣ ያለድንግዝግዝ በብርሃን ተንደርድሮ የገባበት ውሳኔ ከመሆኑ አንጻር ነው። ይህን ለምን እንዳልኩ ግልጽ ነው። ውሳኔው ከመወሰኑ በፊት ኅብረቱ ጥናት አስጠንቶ፣ የወንጌላውያንን ማንነት አስተንትኖ፣ ለውሳኔ ማዕቀፍ የሚሆን ንድፍ አበጅቷል። ወንጌላዊነት እና ወንጌል ምን ማለት እንደ ሆነ ኅብረቱ እንደ ገባው አስባለሁ። ቅልቅላችን ድንግርግርነት የወለደው ሳይሆን፣ በዚህ እውነት ላይ ያደረግነው ዐመፅ ሊባል ሁሉ ይችላል። ከዚህ ቀደም ግን እንዲህ ዐይነት ማዕቀፍ አልነበረምና የመቀበል ውሳኔ የሚደረገውም የሌሎችን የእምት አንቀጽ ከቀደምት አባላት ጋር በማስተያየት ብቻ ነበር። ተመልከቱልኝ በሚል ይቀርብ የነበረው የእምነት አንቀጽ፣ የእኛውኑ አባላት ቅጂ ስለሆነ፣ ወረቀት እያየን ብቻ አንድ ነን በማለት የማይመስሉንን ስንቀበል ሰነበትን። አሁን ግን ልዩነታችን ፀሓይ የሞቀው ሆነ። አሁን ያደረግነው፣ ከቃላቸው በተቃርኖ የሆነውን ሥራቸውን እያወቅን፣ ቃላቸውን ብቻ አምነን የማይመስሉን በጉያችን አቀፍን። ይህ የሆነው ግን በየዋህነታችን ብዛት ወይም ስላላወቅን አይደለም።፡ ዙሪያችን የከበበን የተበዳዮች እና የተበዝባዦች ጩኽት በቅጡ ካልተሰማን መፈተሸ ያለበት የእኛው ጆሮ እንጂ ሌላ አይደለም። በወንጌል ስም የሚደረገው ውንብድና እኮ ግልጽ ከሆነ ሰነባበተ። እንዴት ይህ ሁሉ ጉድ አይሰማንም? ስለዚህም፣ ኅብረቱ ከትላንት በበለጠ እያወቀ አጥፍቷል፤ በውሳኔውም ታሪካዊ ስሕተቶችንም አስቀጥሏል እላለሁ። ከታሪክ መማር አለመቻልን የመሰለ ውድቀት የለም!

በአሁኑ የመቀላቀል ውሳኔ ኅብረቱ ያሳየው የቀደመውን መንገዱን አለመማሩን ብቻ ሳይሆን፣ የቀደመውን ታሪካዊ ስሕተት ማስቀጠል መፈለጉን ጭምር ነው።

ስሕተት ሁለት፡- ከንሰሐ የጎደለ ንሰሐ

እኔ እንደሚገባኝ ንሰሐ ከቀደመ የስሕተት መንገድ ለመመለስ፣ የቀደመ በደለኝነትን ማመን፣ አቅም በፈቀደ መጠን ጥፋትን መካስ፣ ነገም ተመሳሳይ ስሕተት ላለመሥራት ከልብ መጨከንን ይፈልጋል። እንዲህ ዐይነቱ ንሰሐ እንዲከወን ደግሞ ጊዜ ይስፈልጋል። ለዚህም ነው አገልጋይ ንሰሐ ሲገባ ከአገልግሎቱ ለተወሰነ ጊዜ በማረፍ፣ በምክር እና በጉብኝት የጥሞና ጊዜን ከአምላኩ እና ከተወሰኑ ሰዎች ጋር እንዲያሳልፍ የማድረግ ልማድ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለው። ካለህበት ቀጥል የሚባልለት የክርስቲያናዊ የአገልግሎት ውድቀት የለም። አሁን ያየነው መቀላቀል፣ ከዚህ የተለየ ነው። ተቀላቃዮቹ ነገር እንደ ነበረ ይቀጥል (business as usual) በሚል መርሕ፣ ከመድረኮቻቸውና ከቲቪ መስኮቶቻችን ለአንድ ቀን እንኳን ሳይወርዱ ተቀላቅለውናል። ከአገልግሎት የጥሞና ጊዜ አሰጥቶ የማያሳርፍ ንሰሐ ይገርማልና፣ እነዚህ ግለ ሰቦች ንሰሐ ገብተዋል ለማለት ይከብዳል። አሁን ያደረግነው ነገር ከዚህ ቀደመን እውቅና ያልሰጠነውን ነገራቸውን የአደባባይ እውቅና በመስጠት ማስቀጠል ነው። በኅብረቱ መግለጫ፣ ነቢያቶቹ የኛም ነቢያት ሆኑ፣ እኛም ሕዝባችንን በይፋ አሳልፈን ሰጠን።

ለነገሩ፣ አድበስብሰው፣ ካልሆነ ማናቸውም በጥፋታቸው ማዘናቸውን አልገለጹም። አንዳንዶቹ እንደውም ለወደፊት እናረግም ያሉዋቸውን እና የፈረሙባቸውን ነገሮች አስመልክቶ፣ ቀድሞውኑ አልተረዳችሁንም እንጂ “ሸቃጭ” አልነበርንም ሲሉ በልበ ሙሉነት ተናግረዋል። ገስት ሀውስ የከፈቱበትን ምክንያትም እንግዶች እንዲመቻቸው ነው ሲሉ አለመጸጸታቸውን የሚያመለክት ሰበብ ደርድረዋል። ሌሎቹ በዝምታ ዘለውታል። ገስት ሀውሶቹ የሚሰጡትን አገልግሎት እና የሚከፈልባቸውን ዋጋ ለምናውቅ ለእኛ ግን ምክንያቶቹ ሰበብ እንጂ እውነቶች አልነበሩም። መልእከታቸው ግልጽ ነው። ስለ ውግዘቱ ግለ ሰቦቹ የነበራቸው እይታ፣ አዲስ ነገርን ሳይገባችሁ መፈረጅ ልማዳችሁ ስለ ነበረ ተወገዝን እንጂ፣ ቀድሞውን አንዳች ጥፋት አልነበረም የሚል ነው። ነገ ደግሞ ሁላችንም የምንጠማው ነገር፣ ግን ያልደረስንበት ልምምድ ሆኖ ይቀርብልናል። የወደፊቱ የእኛው መድረኮች ጥያቄ እነርሱን አምጡ ወይም እንደ እነርሱ አድርጉ መሆኑ ግልጽ ነው። ዶማውን ዶማ ለማለት ከደፈርን፣ ንሰሐ የገባው የአብያተ ክርስቲያናት ኅብረት እንጂ ተቀላቃዮቹ አይደሉም። ነገሩ፣ ፊትን የማዳን (face-saving) እርምጃ ነው፤ ኅብረቱ ያዳነው ክብሩን እንጂ አውነትን አይደለም። የኅብረቱ ውሳኔ አንድምታ፣ ያጠፋሁት እኔ ብሆንም፣ ለክብሬ ስትል ይቅርታ የምትጠይቁኝ አናንተ ሁኑ የሚል ነው። ነገ በቅልቅሉ የሚያተርፉ ዛሬ ዝቅ ቢሉ ትርፋቸውን አስልተው ነው። በዚህ ሁሉ ግርግር ውስጥ ማንም ከአውነት ጋር ፊት ለፊት ስላልተፋጠጠ፣ ቅልቅሉ ከእውነተኛ ንሰሐ እጅጉን የጎደለ ነው።

ስሕተት ሦስት፡- የደቦ ቅልቅል

በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የተደረገው ቅልቅል፣ የአንድ ዓመት ውይይት ፍሬ እንደ ሆነ ተነግሮናል። ነገሩ ለሰሚ ረጅም፣ አካሄዱም አድካሚና በርካታ ግለ ሂስ የተደረገበት ያስመስለዋል። አንድ ዓመት ሞላው የሚለውን እንዳለ ልቀበልና ይህንን ልበል። በዚህ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 150ዎቹን ለመቀበል ተግቶ ይሠራ የነበረው ማነው? ስንት ጊዜስ ኅብረቱ ከነዚህ ግለ ሰቦች ጋር ተገናኝቷል? ርግጥ ሁለት (ከበዛ ሦስት) ጊዜ፣ የተወሰኑትን ሰብስቦ የደፈና የሚመስል ሥልጠና (ውይይት) አድርጓል። በሥልጠናው ከተሳተፉት እንደ ሰማሁት ነገሩ ሁሉ ድብስብስ ነበር። ስለ ማን እንደተወራ ሳይታወቅ፣ ስለ እንትን የተወራበት ጊዜ! ውይይት በማካሄድ ተሳታፊ የነበሩት ፕሬዚዳንቱ እና ቦርዱ ናቸው ብንል (ዝርዝራቸው በግልጽ አልተገለጸም)፣ “የእግዚአብሔር ሰዎቹም” ሆነ ጽሕፈት ቤቱን የሚወክሉት ሰዎች የሥራ ውጥረት ያለባቸው መሆናቸው እናስተውላለን። ከዚህም የተነሣ ውይይቱ ጥልቅና በግልጽነት ረጅም ጊዜ ወስዶ የተደረገ ነው ብሎ ለማመን እቸገራለሁ። የቦርድ አባላት ለቅልቅል ለፎቶው ማድመቂያ እንኳን መድረክ ላይ ባልተገኙበት፣ አንዳንዶቹ ገና ውይይት ላይ ነን ባሉበት፣ ስምምነቱ ከአውራዎች ጋር መደረጉ የቦርዱ ተሳትፎ ካለም እጅጉን ውስን መሆኑን ይጠቁማል።

የደቦ ቅልቅል፣ ጥልቅ መርማሪነት ያለበት አይደለም፤ ነገር ተድበስብሶ የሚተውበት ሥረዐት ነው። እውነተኛ ኅብረት በአንጻሩ የልብ ለልብ ትሥሥር እና የተፈተነ አንድነት ነው። ስለዚህም፣ ወሰደ የተባለው የአንድ ዓመት ጊዜ ሥራው ከሚፈልገው ኀላፊነት የተነሣ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በግልጽ ቋንቋ የተሰጠው ውሳኔ ትልቅነት፣ በአንድ ዓመት መካከል ከሚደረጉ፣ ጥቂት ስብሰባዎችና አካሄዶች አብዝቶ መብለጥ ነበረበት። ከዚህ ላነሰ ጉዳይ እንኳን ስንቴ እንሰበሰብ እና እንመካከር የለ እንዴ?! ጥድፊያውና የደቦ ቅልቅሉ፣ የይድረስ ይድረስ እንደ መሆኑ መሠረቱ ረግራጋ ሊሆን ይችላል ብዬ እንዳምን ምክንያት ሆኖኛል። በጥድፊያ እውነተኞች መቼም እንደማያተርፉ ለሁላችን ግልጽ ነው። ግር ግር ለማን እንደሚመችስ መች ይጠፋናል። እንደ እኔ ምልከታ ከሆነ፣ ሰዎች (አገልጋይ የሚባሉትን ጨምሮ) በሚናገሩትና በሚኖሩት መካከል የማይታረቅ ክፍተት ያለበት ዘመን ላይ ነን። ሳንመረምር ማንንም በንግግር ብቻ ማመንን የመሰለ ተላላነት የለም። ከዚህም የተነሣ፣ ገለልተኛ ቡድን ተቋቁሞ፣ ነገሮች በዝርዝር ተነግረው፣ ሰዎቹ ከእውነት ጋር ተጋፍጠው፣ ተጎጂዎች ከጎጂዎቻቸው ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተው እና ይቅርታ ተደራርገው፣ ያደረጉት ቅልቅል ቢሆን ሚዛን ይደፋልኝ ነበር። እኔም አንዲት ነፍስ ዳነች ስል በርግጥም በአምላኬ ፊት ሐሴት ባደረኩኝ። ሰዎችን የተጋፈጥናቸው ከእውነት ባነሰ ነገር ከሆነ፣ ንሰሐቸውም የዛኑ ያኽል ነው። ነገሩ ሁሉ የኤፍ ኤም ሬዲዮ አዘጋጆች ማናችንንም በግል ቅርበት ሳያውቁን በጅምላ ሁላችሁን እንወዳችኋላን የሚሉትን ወይም መነሳንሳችሁን ከቀኝ ወደ ግራ አዙሩ በሚል ለተመራቂዎች የሚሰጥ ትእዛዝ መስሎኛል። የትምህርት ቤቱስ ይሁን፣ እዚያች ቀን ላይ ለመድረስ፣ የተኬደበት መንገድና የፈተናው ብዛት ድርጊቱን ትርጉም ይሰጠዋል። ንሰሐችን እኮ ከስሜት ኩርኮራ ማለፍ አለበት። ጠብቀን ስናይ ነገር እንደ ነበረ መቀጠሉን መገንዘብ አንቸገርም። በቅልቅሉ እውቅና የተሰጣቸው ግለ ሰቦች ኖሩ እንጂ፣ የቆመ አንዳች ስሕተት፣ በጸጸት የተመለሰ ልብም ሆነ እጅ አይታይም። ነገር እንደ ነበረ ከቀጠለ ንሰሐው የታለ?

ስሕተት አራት፡- ከተገዛችሁልን የይበቃል ስሌት

የተቀላቃዮችን መግለጫ ልብ ብለን ከተመለከትነው የሚሸተን አንዳች ነገር አለ። ርግጥ ነው፤ ሌሎችን ኅብረቱ የሚመለከትበት አቋም በሦስት ከፍሎ መሆኑ ተነግሮናል። ልዩነቱ መደረጉ መልካም ነው። በርግጥም የተቀላቀሉት 150ዎቹ በሙሉ የስሕተት መምህራን ናቸው ብዬ አላምንም። እውነተኞች ከመካከላቸው ሊኖሩ ይችላሉ ወይም አሉ። ለምን እነ እንትና ተካትተው እነ እንትና ተዘለሉ የሚለውን ግን በተጨባጭ ለመመዘን የሦስትዮሽ አከፋፈሉ የሚጠቅመው ፋይዳ እምብዛም ነው። የትኞቹ ስንት ከስንት አምጥተው አለፉ፣ የቀሩትን ምን ያክል አጉድለው ጣልናቸው ለማንም ግልጽ አይደለም። ሚዛን አውጥተን የተመራነው ግን በልባችን ፈቃድ ከሆነ ሚዛናችንን ከንቱ አላደረግነውምን? ያልተነገረው፣ ነገር ግን የተተገበረው የሚመስው ሚዛን፣ ከተቀበልናቸው መካከል አንዱ በመግለጫው እንዳለው ነው። ‘ቢከብድም ዝቅ’ ብለን ብሏል። ሚዛኑ እኛ ጋር በመምጣት ‘ተገዢነትህን ታረጋግጣለህ ወይስ አታረጋግጥም?’ በሚል መርሕ ላይ ሳይመሠረት አልቀረም ያሰኘዋል። በአካትቱኝ ግብ፣ ብሞትም በእናንተው እጅ ልሙት ብሎ የማለና የተገዘተ ሁሉ፣ ከተካተተ በኋላ ይሰማን ከመሰለን ስተናል። ቃል በረከሰበት ዘመን፣ ድርጊትን ያልመዘነ ሚዛን ሆነ ግምገማ ጎደሎ ነው፤ ፍርዱም ልክ አይደለም። በየስድስት ወሩ እንገመግማችኋለን ቢሆንም ማስፈራሪያም ዋስትናም አይደለም።

በርግጥም የተቀላቀሉት 150ዎቹ በሙሉ የስሕተት መምህራን ናቸው ብዬ አላምንም። እውነተኞች ከመካከላቸው ሊኖሩ ይችላሉ ወይም አሉ።

ስናስገባ ያላከበድነውን ሚዝን፣ በስድስት ወር ግምገማችን፣ እናከብደዋለን ብዬ ለማመን እጅጉን እቸገራለሁኝ። ለነገሩስ በየትኛው የሰው ኀይልስ ነው ኅብረቱ እንዲህ ዐይነት ጥልቅ ግምገማ የሚያደርገው? እስከ ዛሬስ ቢሆን ማንን ገምግመን፣ ማንን ከመካከላችን ለየን? ታሪካዊ ስሕተቶችን የማረም ባህል ቢኖረንማ፣ ቀድመን የሠራናቸውን ዛሬ ላይ ባስተካከልናቸው ነበር። ስሕተቶቻችን በጉያችን እንዳቀፍን እንደ ቀጠልን ሁሉ፣ ያቀፍናቸውን እንዳቀፍን እንደምንቀጥል ለመገመት ነቢይ መሆን አያስፈልገንም። ስሌታችን ከተገዛችሁልን ይበቃል ሳይሆን አልቀረም እንድንል ያደረገን ደግሞ በተቀበልናቸው ባልተቀበልናቸው መካከል ያለው ልዩነት፣ ከእኛው ግላዊ ስሜት በበለጠ ይህ ነው የሚባል ልዩነት ስለሌለው ነው። በሦስት ክፍሎች የመቦደኛው ሚዛን፣ ዝርዝር መመሪያ እና ምርመራ ከሌላው በስተቀር፣ እጅጉን ግላዊነት የተንጸባረቀበት መደምደሚያ ላይ እንደሚያደርስ ምስክሩ ከሚመሳሰሉት መካከል አንዳንዶቹን ተቀብለን መሰሎቻቸውን መግፋታችን ነው። እንደውም በገለልተኝነት ለተመለከተው ተቋማዊ ፍትሕ በቀሩት ላይ ተጓድሎባቸዋል የሚል ጥያቄን ማስነሣቱ አይቀረም።

ስሕተት አምስት፡- መጋቢያዊ ርኅራኄ ማነስ

እንደ እኔ አመለካከት የተቀላቅለዋል ውሳኔ፣ መጋቢያዊ ርኅራኄው እጅጉን አናሳ መሆኑን እንዳምን አድርጎኛል። ኅብረቱ ከተቋማዊ አደረጃጀት ባሻገር፣ በዚህ ውሳኔ አብልጦ ሊጎዳ ላላው ወንጌላዊው ማኅበረ ሰብ በቂ ጥንቃቄ እንዳደረገለት አይሰማኝም። የውግዘት ውሳኔ ሁልጊዜ በውስጡ ርኅራኄም ጭከናም እንዳለው ሁላችንም እናውቃለን። ውግዘቱ ሁልጊዜ ከእውነት አንጻር እና በሐሰት የሚጎዱትን ከመጠበቅ አንጻር እንዲደረግ ይጠበቃል። በዚህ የቅልቅል ውሳኔ፣ ኅብረቱ ሊራራላቸው የሚገቡትን አማኞች፣ በአንጻሩ ወደ ጎን ገሸሽ አድርጓል። በዚህም በደካሞች እና እውነትን ከሐሰት ለመለየት በልቦናቸው ባልጠነከሩ አማኞች ላይ የጭካኔ በትሩ አርፏል። አሁን፣ በጎቹ ያሉበት በር ወለል ተደርጎ ተከፍቷል፤ ለሌሎች ስንራራ፣ በርኅራኄ እንድንጠብቃቸው እግዚአብሔር ባመነን ላይ በበለጠ ጨክነናል። በርካታ የልብ ስብራቶችን፣ መበዝበዞችን፣ መምታቶችን፣ ከመቼውም በበለጠ ልንሰማ በደጅ ነን።


ተያያዥ ጽሑፎች

Share this article:

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በተመለከተ መንግሥትና ሕዝብ ልብ ልንል የሚገባቸው ነጥቦች

ይህ ጽሑፍ ከቀናት በፊት ለንባብ የቀረበ ሲሆን፣ ዐቢይ ትኩረቱም ማኅበራዊ ንክኪን መቀነስ ላይ ያተኩራል። ጽሑፉ አነስተኛ አርትዖት ተደርጎበት ለሕንጸት አንባቢያውን እንደሚከተለው ቀርቧል።

ተጨማሪ ያንብቡ

“ኑ፡- ʻአምላክʼን እንፍጠር”

“ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” ያለው እግዚአብሔር ነው። የዚህ ፍጥረት ዋነኛ ተግባር ለፈጣሪው ሙሉ ዕውቅና መስጠት፣ በእርሱ እና ለእርሱ እንዲኖር፣ በዘለዓለምም መንፈስ በእግዚአብሔር ደስ እንዲለው ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ

“ማዝመር” እና “መዘመር”

በርእሱ ላይ የተጠቀሱት ሁለቱ ቃላት “ማዝመር እና መዘመር” ወይም “አዝማሪነት እና ዘማሪነት” በዓለማዊ (Secular) በተሰኘው እና መንፈሳዊ በምንለው ክልል የዜማ እና የቅኔ ኪነ ጥበብ መገለጫ ስለ መሆናቸው፣ እንደውም በጋራ ተጨፈልቀው የተሠሩና ያለ ምንም ልዩነት አደባባይ የዋሉ ያህል ሲነገሩ ማድመጥ የተለመደ ነው፡፡ ነገር ግን የዜማና የቅኔ ጥበብ በተለይም የዝማሬው ኪነ ጥበብ የአንድ ዘመን የሰዎች የፈጠራ ግኝት ወይም በ“እከሌ ፍልስፍና” የተገኘ አለመሆኑን ከመንፈሳዊው ዓለም ታሪካዊ አስተምህሮ ተገቢ ትምህርት መቅሰም ይቻላል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.