[the_ad_group id=”107″]

ሐሰተኞቹ የት ነው ያሉት?

ድኅረ ክርስቶስ ልደት ሦስት መቶ ዐሥራ ሦስት ዓመተ ምሕረት ላይ “የሚላኑ አዋጅ” (The Edict of Milan) የተሰኘ አንድ አዋጅ ታወጀ። አዋጁ፣ ‘ቤተ ክርስቲያን መደበቋ ያብቃ፤ ብዙ ተጎድታችኋል፣ ብዙ ተጠቅታችኋል፤ አሁን ሕዝቡ ሁሉ የሮምን መንግሥት እንዲደግፍ ስለሚፈለግ የሮም መንግሥት ፈቅዷልና እንደ ፈለጋችሁ ማምለክ ትችላላችሁ። ቤተ ክርስቲያን ይፋ ወጥተሽ መልእክትሽን ለዓለም ሁሉ መንገር ትችያለሽ’ የሚል ነበር። ቤተ ክርስቲያንም ይህን አዋጅ ሰምታ አንድ ጊዜ ግር ብላ ወደ ዓለም ወጣች። ይህ በራሱ እሰዬው የሚያሰኝ ነበር። ይሁንና፣ ከዚህ ነጻነት ጋር ተያይዞ ብዙ ዐይነት የዓለም ልምምዶች ወደ ቤተ ክርስቲያን ገቡ። ከዚያ በኋላ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ብዙ ውጣ ውረድ የታየበት የጨለማ ዘመን ተተካ። ከዚህም የተነሣ ቦግ ብሎ በርቶ የነበረው ንጹሑ የወንጌል ችቦ፣ ወደ ኩስታሪ ሊለውጥ እስኪቃረብ ድረስ ስልምልም ብሎ ደከመ። የስሕተት ትምህርት ቤተ ክርስቲያንን ሊያስምጣት ቁልቁል እየደፈቃትና እየተናነቃት፣ ጌታ በተሐድሶ እስኪጎበኛት ድረስ ከዐሥራ ሁለት ክፍለ ዘመናት በላይ የጨለማ ጉዞን በደበሳ ለመጓዝ ዳረጋት።

በርእሱ ላይ እንደተጠየቀው ሐሰተኞቹ የት ነው የሚገኙት? ለዚህ መልስ ፍለጋ ወደ ሐዋርያው ጴጥሮስ ሁለተኛ መልእክቱ እንሂድ። “ሐሰተኞች ነቢያት ደግሞ በሕዝቡ መካከል ነበሩ፤ እንዲሁም በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ” ይላል (2ኛ ጴጥ 2፥1)። በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ዘመን ለነበሩ አማኞች፣ ስደት የየቀኑ ኑሯቸው ነበር። ጌታቸው እንደ ተሰደደ እንዲሁ ደቀ መዛሙርቱ፣ ሐዋርያቱ አሁን ደግሞ የዚህ መልእክት ተቀባዮች በጣም ይሰደዱ ነበር።

ሐዋርያው ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያንን በእንብርክክ ያስሄዳት ውጥንቅጡ ሳይመጣ በፊት ነበር፣ ‘እናንተዬ፤ ሐሰተኞች ነቢያት እና አስተማሪዎች እኮ በእናንተ መካከል ነበሩ፤ አሁንም አሉ፤ ወደፊትም ይመጣሉ’ ሲል ያሳሰበው።

አዲስ ነገር የለም

በሙሴ ዘመን እግዚአብሔር አስቀድሞ ለሕዝቡ በመጠንቀቅ ለእስራኤላውያን የተናገረውን በዘዳግም 13፥1-6 እንመልከት። ጭምቅ ሐሳቡ፣ ሕልም አላሚ፣ ራእይን የሚያይ በተሰጠህ ጊዜ፣ ሰው ተመልሶ እኔ ካመለከትኋቸው የሕይወት መንገድ ሊያወላግዳችሁ፣ ጣኦታትን ታመልኩ ዘንድ ደባ ቢሠራ፣ ሸር ቢያመጣ እርሱን አትስሙት፤ እንዲያውም ግደሉት፤ እንዲህ ያለውን ጉድፍ ከመካከላችሁ አጥፉት፣ አርቁት’ የሚል ነው። ታዲያ ያኔ እግዚአብሔር ቀድሞ የተናገረው ሁሉ በኋላ እውን እንደ ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናነባለን። ኋላ ላይ በእስራኤላውያን መካከል ሐሰተኞች ነቢያት እንደ ክረምት አግቢ ነበር የፈሉት።

ነቢዩ ኤልያስን በመቃወም የቆሙትን የበኣል ነቢያትን ብዛት ከእውነተኛው ነቢይ ከአንዱ ኤልያስ ጋር ያነጻጽሩት።

ኤርሚያስ 23፥13-14ን ብታነብቡ፣ ነቢዩ በሚያሳዝን ሁኔታ፣ “በሰማሪያ ነቢያት ላይ ስንፍናን አይቻለሁ፤ በበኣል ትንቢት ይናገሩ ነበር፤ ሕዝቤንም እስራኤልን ያስቱ ነበር። በኢየሩሳሌምም ነቢያት ላይ የሚያስደነግጥን ነገር አይቻለሁ፤ ያመነዝራሉ በሐሰትም ይሄዳሉ” እያለ የዘመኑን ክስረት ይነግረናል። ኤርምያስ ከሐሰተኞች ነቢያት ጋር ብዙ ግብ ግብ ነበረበት። ሐሰተኞች ነቢያት ያኔም በሕዝቡ መካከል ነበሩ። ምንም አዲስ ነገር የለም። እንዲያውም በኤርሚያስ 5፥31 ላይ፣ “ነቢያት በሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፤ ካህናትም በእነዚህ እጅ ይገዛሉ፤ ሕዝቤም እንዲህ ያለውን ነገር ይወድዳሉ፤ በፍጻሜውስ ምን ታደርጋላችሁ?” የሚል አስደንጋጭ ጥቅስ አለ።

ሕልም የሚያልሙት በሐሰት ያልማሉ፤ ሕዝቡም ይሄንን ይወድዳሉ። ምን ይሻላችኋል? ይላል ኤርሚያስ። እነዚህ ሐሰተኞች ነቢያት እና አስተማሪዎች የሚገኙት ደግሞ በሕዝቡ መካከል ነው። በየዋህነት ሳይመረምር የሚከተላቸውን ሕዝብ በመርበባቸው፣ እያነባበሩ መጣላቸው አይቀሬ ነው።

አንድ ጊዜ ኢሳይያስ በጣም ተቸግሮ “… ዐመፀኛ ወገንና የእግዚአብሔርን ሕግ ለመስማት የማይወድዱ የሐሰት ልጆች ናቸውና፣ ባለ ራእዮችን አትመልከቱ ይላሉ፤ ነቢያትንም ‘ጣፋጩንና አታላዩን ነገር እንጂ ቅኑን ነገር አትንገሩን፤ ከመንገድ ፈቀቅ በሉ፤ ከጎዳናውም ዘወር በሉ፤ የእስራኤልንም ቅዱስ ከእኛ ዘንድ አስወግዱ’ ይሏቸዋል” (ኢሳ 30፥9-11) ማለቱን እናነብባለን።

ኢሳይያስ እዚህ ቦታ ላይ የሚናገረው በእግዚአብሔር መንፈስ ሆኖ ስለ ሐሰተኞቹ ነቢያት ሳይሆን፣ በሐሰተኞቹ ትምህርት ተመርዞ ሙልጭ ብሎ ተጠርጎ ከእግዚአብሔር ሐሳብ እና ፈቃድ ስለ ራቀውና እንደ ሟርትም ‘ከጌታ ባይሆንም ከልባችሁ እያማጣችሁ በማፍለቅ ደግ ደጉን ብቻ ንገሩን’ ማለት ደረጃ ስለ ደረሰው ሕዝብ ነው። ሕገ እግዚአብሔርን አንጡራ ሀብቱ አድርጎ ተጠንቅቆ ያልያዘ፣ በሐሰተኞቹ ወጥመድ ውስጥ በሁለንተናው ሰተት ብሎ በመግባት ክፉኛ የተጠመደው ይህ ሕዝብ፣ “የእስራኤልን ቅዱስ ከእኛ አስወግዱ” ማለት ደረጃ እንደ ዋዛ ደረሰ። እናም እግዚአብሔር በነቢዩ ኢሳይያስ አፍ የፍርድን ቃል በሕዝቡ ላይ ተናገረበት (ኢሳ 30፥12-14)። ፍርዱም “ለእሳት መጫሪያ፣ ለውሃ መጥለቂያ ስባሪ ገል እስከማይተርፍ ድረስ፣ እንክትክት ብሎ እንደ ደቀቀ የሸክለኛ ማድጋ ትደቅቃላችሁ። የበደላችሁ ብዛትና ዳፋው ውጤቱ እዚህ ድረስ ነው” የሚል ነበር። ጌታ ከዚህ ይጠብቀን።

በመካከላችሁ አሉ

ኤርሚያስ እና ሕዝቅኤል በነበሩበት ዘመን በእስራኤል መካከል ሐሰተኞች ነቢያት ነበሩ። ሐዋርያው ጴጥሮስም ይህንኑ እየነገረን ነው። ሐሰተኞቹ በመካከላችሁ ናቸው! ብዙ ጊዜ ከቤተ ክርስቲያን ውጪ የሚመጡትን የሐሰት ትምህርቶች በተገቢው መንገድ እንመክታቸዋለን። ‘ኢየሱስ ክርስቶስ ከማርያም አልተወለደም’ የሚል ትምህርት ቢመጣ፣ ‘እርሱ ከድንግል የተወለደ አይደለም’ የሚል ትምህርት ቢከሰት፣ ነቅሰን ነው የምናወጣው። ‘ኢየሱስ ክርስቶስ አልሞተም፤ የሞተው እርሱን የሚመስል ነው’ የሚል ቢመጣ፣ ከሥሩ ነው የምንመነግለው። ምንም ችግር የለብንም፤ በደንብ ነው የምናውቀው፤ ውጪ ያሉ ናቸውና። አሁን ግን ችግሩ፣ “በመካከላችሁ አሉ” ስለተባሉት የምንሰጠው ምላሽ ነው ፈተና የሆነብን።

አዎን፤ የሰይጣን አንዱ አሠራሩ እንዲህ ያለ ነው። እናታችን ሔዋንን ያሳታት በሚያባብል፣ በሚጣፍጥ ቃል ነበር። ‘ሔዋን፤ … እንተዋወቅ። እኔ ሰይጣን እባላለሁ፤ ከዚህ በፊት አልተዋወቅንም እንጂ፣ እዚሁ ቅርብሽ ነበር የምኖረው። እናም ይኸውልሽ … ምናምን’ አላላትም። ሰይጣንነቱን፣ አሮጌ እባብነቱን ሰውሮ ለእርሷ የሚያስብ መስሎ፣ ቃል አጣምሞ፣ ጥቅስ ሰባብሮ እና ሸራርፎ፣ ክፉ ነገር በልቧ አስቀምጦ፣ ቅንነቷን አበላሽቶ ነው ለውድቀት ያበቃት።

በመጨረሻው ዘመንስ?

ሰይጣን በመጨረሻው ዘመን ሕዝብ የሚወድደውን ነገር ማቅረብ የሚችሉ መልእክተኞች አሉት። ጳውሎስ በ2ኛ ጢሞቴዎስ 4፥1-5 ላይ የጻፈውን ማስጠንቀቂያ እንመልከት፤ እንዲህ ይላል። “በእግዚአብሔር ፊት በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት፣ በመገለጡ እና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ፤ ቃሉን ስበክ፤ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፤ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ ዝለፍና ገሥጽ፤ ምከርም። ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሱበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮዎቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፣ እንደገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ። እውነትንም ከመስማት ጆሮአቸውን ይመልሳሉ፤ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ። አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፣ መከራን ተቀበል፤ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ፤ አገልግሎትህን ፈጽም።”

እውነታው ይኸው ነው፤ በመጨረሻው ዘመን ሕዝቡ ራሱ የሚፈልገው እንደ ገዛ ምኞቱ ደስ የሚያሰኘውን የሚነግረውን መምህር ነው። እውነተኛውን ነገር ለመስማት ጆሮቻቸውን ስለሚያሳክካቸው ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሱበት ዘመን ይመጣል።

‘አንተ የተቀበልከውን ይሄንን እውነተኛውን ወንጌል መስበክ ሥራህ አድርግ’ ይለዋል። በአጭር ቃል ተጠንቅቆ መኖር ይሻላል። የዚህ ዓለም ክፋት እየባሰበት እንጂ እየቀነሰ አይመጣም። ጴጥሮስን ጨምሮ ሐዋርያቱ በነበሩበት ዘመን ተቸግረው እንዲህ በጥብቅ ይናገሩ ከነበረ፣ እኛማ እንዴታ!

አሁንማ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው የተደረሰው። ደረቱን ገልብጦ፣ ኸረ እንዲያውም እርቃኑን በአደባባይ በገሃድ ያለ ነገር ሆኗል። ዛሬ ይህን ብንናገር “የአዋጁን በጆሮ!?” በሚያሰኝ መልኩ እኛ ጥግ ጥጉን፣ ጓዳ ጓዳውን እያልን ስናወራ የሐሰት ትምህርት በውጭ ፀሓይ የሞቀው፣ አገር ያወቀው ጉዳይ ሆኗል። እየባሰበት ሄዷል ለማለት ነው። ደግሞም ከዚህ በኋላ ይከፋል፣ ይብሳልም።

Pastor Bedilu Yirga

የእግዚአብሔርን ክብር ማየትና መጠማት:- የኢየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻው ግብ

አማረ ታቦር Seeing and Savoring Jesus Christ ከተሰኘው የጆን ፓይፐር መጽሐፍ በተከታታይ ከሚያቀርባቸው ጽሑፎች መካከል፣ ይህ “የእግዚአብሔርን ክብር ማየትና መጠማት፦ የኢየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻው ግብ” ሲል ወደ አማርኛ የመለሰው ይገኝበታል።

ተጨማሪ ያንብቡ

ሰባዎቹ የጆናታን ኤድዋርድስ ቁርጠኛ ውሳኔዎች:- (The 70 Resolutions of Jonathan Edwards)

በዐሥራ ስምንተኛ ክፍለ ዘመን፣ በምድረ አሜሪካ ለተነሣው መንፈሳዊ መነቃቃት ግንባር ቀደም አስተዋጽዖ እንዳደረገ የሚነገርለት ጆናታን ኤድዋርድስ፣ በግል ሕይወቱ ለመተግበር የቆረጠባቸውን ውሳኔዎቹን አማረ ታቦር፣ “ሰባዎቹ የጆናታን ኤድዋርድስ ቁርጠኛ ውሳኔዎች” በሚል ወደ አማርኛ የመለሰው እንደሚከተለው ቀርቧል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.