[the_ad_group id=”107″]

የነገረ መለኮት ነገር

ነገረ መለኮት ማጥናት አስፈላጊ ነውን?

የትምህርት ቤቶቹ አቋም ምን ይመስላል?

የምሩቃኑስ ተስፋ?

መግቢያ

ክርስትና በአፍሪካ ውስጥ በስፋት በመስፋፋት ላይ እንደ ሆነ የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ሆኖም ግን ʻእየተስፋፋ ያለው ክርስትና ምን ዐይነት ገጽታ አለው?ʼ የሚለው ትኩረት የሚያሻው ጥያቄ ነው። የቁጥር ዕድገት ቤተ ክርስቲያን በማኅበረ ሰቡ ውስጥ ያላትን መገኘት በማግዘፍ የሚኖራትን ሚና ያጎላዋል። በተመሳሳይ መልኩ ደግሞ ዕድገቱ የተለያዩ ተግዳሮቶችን ይዞ ይመጣል። ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ዕድሎች የማትጠቀም ወይም ለተግዳሮቶች ምላሸን የማትሰጥ ከሆነ በምትኖርበት ማኅበረ ሰብ ውስጥ ያላት ፋይዳ እጅግ አናሳ ይሆናል።

ቤተ ክርስቲያን ሂሳዊ የሆነ ሚና እና ኀላፊነትን እንድትወጣ የምትኖርበትን ዐውድ ጠንቅቃ ማወቅ አለባት። አፍሪካ ውስጥ ከክርስትና ጋር በተያያዘ በበጎ የምናነሣቸው ብዙ ጎኖች ቢኖሩም፣ ምሁራዊ የሆኑ ኀላፊነቶችን (intellectual responsibility) በመወጣት ግን ገና ብዙ ይቀረናል። በአእምሮአቸው የበሰሉ፣ በቤተ ክርስቲያን እና በማኅበረ ሰብ ላይ ተጽእኖ መፍጠር የሚችሉ አገልጋዮች በብዛት ያስፈልጉናል። በተለይ በዚህ ዘመን ይህ እጅግ አስፈላጊ ሆኖ መታየት ጀምሯል። እምነታችን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተና ነገረ መለኮታዊ (theologically engaged) መሆን አለበት። ይህንንም ለማድረግ የነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች የሚጫወቱት የራሳቸው የሆነ ትልቅ ሚና አላቸው።

በዚህ ጽሑፍ የነገረ መለኮት ትምህርት በኢትዮጵያ ውስጥ ምን ዐይነት ገጽታ እንዳለው በወፍ በረር ለመቃኘት ይሞከራል።

የነገረ መለኮት ታሪካዊ አመጣጥ 

ጠቅለል ባለ መልኩ የነገረ መለኮት ትምህርት ስለ እግዚአብሔር እና እግዚአብሔር ከዓለም ጋር ስላለው ግንኙነት የሚያጠና የትምህርት ዘርፍ ነው። ይህ የትምህርት ዐይነት በሥሩ የተለያዩ ዘርፎች አሉት ፡- ታሪካዊ ነገረ መለኮት፣ ሥልታዊ ነገረ መለኮት፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነገረ መለኮት፣ ሐቲት/ሥነ አፈታት፣ ተግባራዊ ነገረ መለኮት፣ ወዘተ… በመባል ይከፋፈላል። የነገረ መለኮት ተማሪዎች በትምህርት ቤት ቆይታቸው መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት መፍታት እንደሚገባቸው፣ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እና ትውፊት በታሪክ ውስጥ ምን እንደሚመስል፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ምን እንደሚያስተምሩ እና ከቤተ ክርስቲያን ሕይወት ጋር ስላላቸው ተዛምዶ እንዲሁም ለተግባራዊ አገልግሎት የሚሆኑ ክኅሎቶችን ይማራሉ።

የክርስትና ሥረ መሠረት የአይሁድ ሃይማኖት ነው፤ ስለዚህም ገና ከመነሻው ክርስትና ልክ እንደ አይሁድ ሃይማኖት ለትምህርት ትልቅ ትኩረት ይሰጥ ነበር። ክርስትና ከጅምሩ የመማርና የማስተማር ሃይማኖት ነበር እንጂ በስሜትና በሰዎች ልምምድ ላይ የተመሠረተ አልነበረም። ነገር ግን የክርስትና አስተምህሮዎች ከሥነ ጽሑፍ ውጪ በትረካዎች/በተረኮች፣ በመዝሙር፣ በቀኖናዎች፣ ወዘተ … በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይተላለፉ ነበር። ሉቃስ ቀደምት ክርስቲያኖች “የሐዋርያትን ትምህርት” ለማስተላለፍ ይተጉ እንደ ነበር ይጠቁመናል (የሐዋ. 1፥1-22፤ 2፥42)።

ቤተ ክርስቲያን እያደገች ስትመጣም የተለያዩ ቤተ እምነቶችም ለነገረ መለኮት ትምህርት የተለያዩ ትኩረቶችን ሰጥተዋል። በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትምህርት ትልቅ የሆነ ሥፍራ ይሰጠዋል፤ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥም ተመሳሳይ ነው። የ17ኛውን ክፍለ ዘመን የተሃድሶ እንቅስቃሴንም ስናጠና መነሻው ከትምህርት እና ከመጠየቅ ጋር የተያያዘ ነው። ʻእያንዳንዱ አማኝ የመንግሥቱ ካህን ስለሆነ እምነቱን ማወቅ አለበትʼ የሚለው አመለካከት የሉተር መርሕ ነበር። ትምህርት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አዲስ ክስተት ሳይሆን በተለያየ መንገድ ራሱን ይገልጽ ነበረ። በሌላ አባባል፣ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች በተለያየ መልኩ ራሳቸውን በማሠልጠን እውቀትን ይገበዩ ነበር።

የነገረ መለኮት ትምህርት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ነው፤ በተለየም ባህላዊ በሆኑ ትምህርት ቤቶች ውስጥ። በኋላ ላይ ከዘመናዊ ትምህርት መምጣት ጋር ተያይዞ የነገረ መለኮት ትምህርት በኮሌጅ ደረጃ መሰጠት ጀምሯል። በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ድቁናንም ሆነ ቅስናን ለማግኘት በባህላዊ የነገረ መለኮት ትምህርት ማለፍ የግድ ነው። የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያናም በተመሳሳይ በየገዳማቷ ባሉ የሥነ መለኮት ትምህርት ቤቶች ሰፊና ጥልቀት ያለውን መደበኛ ሥልጠና ትሰጣለች።

በወንጌላውያን አማኞች ዘንድ የነገረ መለኮት ትምህርት በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ጊዜያትን አላስቆጠረም። ሆኖም ግን ባለፉት ሃያ ዓመታት እየተስፋፋ መጥቷል። በቀደምትነት የነገረ መለኮት ትምህርትን መስጠት የጀመረችው የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ስትሆን፣ ይህም የሆነው (እ.ኤ.አ. በ1960 ዓ.ም.) ነበር። የኢቫንጀሊካል ቲዮሎጂካል ኮሌጅ (ETC) ደግሞ ከ30 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። በተለያዩ ቤተ እምነቶች ሥር ያሉ ሌሎች ትምህርት ቤቶችም እየተበራከቱ መጥተዋል። በድኅረ ምረቃ ትምህርትም የሚሰጡ እንደ የኢትዮጵያ የነገረ መለኮት ድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ሥልጠናዎችን እየሰጡ ነው። ከዚህ በፊት ተማሪዎች የነገረ መለኮት ትምህርትን ለመማር ወደ ውጪ መሄድ ያስፈልጋቸው ነበር። አሁን ግን እዚሁ ትምህርቱን የሚሰጡ በርካታ ተቋማት ስለተከፈቱ መማር ለሚፈልጉ ሰፊ ዕድሎች አሉ።

90 ሚሊዮን ሕዝብ ባለበት አገር ውስጥ የነገረ መለኮት ትምህረት ቤቶች እየተስፋፉ መምጣታቸው አስፈላጊ ነው። ሆኖም ግን የቁጥሩ ማደግ በነገረ መለኮት ትምህርት ጥራት ላይ ችግር እየፈጠረ መጥቷል። ሊቀለበሱ የማይቻሉ ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት መፍትሔ የሚያሻቸው አንዳንድ ችግሮች እየተስተዋሉ ነው። የነገረ መለኮት ትምህርት ተገቢ በሆነ ሁኔታ ከተስፋፋ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተልእኮዋን በአግባቡ እንድትወጣ ትልቅ አስተዋጽኦን የሚያበረክተውን ያህል ጥራት የሌለው ትምህርት ደግሞ ብዙ ችግሮችን ያስከትላል።

የነገረ መለኮት ጥናት አስፈላጊነት

የነገረ መለኮት ጥናት መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ለመረዳት፣ ሌሎችንም በዚህ መረዳት ለማገልገል፣ ትክክለኛ አስተምህሮን ይዞ ለመጓዝ፣ ትውፊትን ለማስቀጠል፣ ለወቅታዊ ችግሮች/ጥያቄዎች ወቅታዊ መልስ ለመስጠት፣ ወዘተ… ጉልሕ ስፍራን ይይዛል። የነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች ለአገልግሎት የሚረዱ ክኅሎቶች የሚገኙበት ሥፍራዎች ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ የሰዎች መንፈሳዊነት የሚቀረፅባቸው ከባቢ ጭምር ናቸው። በሌላ አባባል የነገረ መለኮት ትምህርት አማኞች እግዚአብሔርን በታደሰ አእምሮ መውደድንና መታዘዝን የሚለማመዱበት መድረክ ነው።

ʻየነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች ያሉን ለምንድን ነው? ለምንስ ያስፈልጉናል?ʼ ለዚህ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ሊኖረን ያስፈልጋል። በርግጥ ለጥያቄዎቹ የሚሰጡ ምላሾች ከዐውድ ዐውድ ሊለያዩ ይችላሉ። ሆኖም ግን የነገረ መለኮት ትምህርት በዓላማ የሚሰጥ ሊሆን ይገባዋል። በመሠረቱ የነገረ መለኮት ተቋማት አካዳሚያዊ/ሙህራዊ እና ሙያዊ ዓላማዎች አላቸው። አካዳሚያዊ ትኩረቱ አእምሮን ማበልጸግና ምርምር ማድረግ ሲሆን፣ ሙያዊ ደግሞ ትልቁ ትኩረቱ ተማሪዎች የአገልግሎት ሙያዎችን በመቅሰም በተለየዩ የአገልግሎት መስኮች እንዲሰማሩ ማድረግ ነው። ሆኖም ግን በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ እነዚህን ሁለት ትኩረቶች እንዴት ነው አጣጥመን የምንሄደው በሚለው ጉዳይ ላይ የተለያዩ ክርክሮች አሉ።

የአብዛኛዎቹ የነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች ዓላማ ቤተ ክርስቲያንን እና ከዚያም አልፎ ኅብረተ ሰብን ማገልገል ሲሆን፣ ይህም ባሕርያቸው እንደ ቤተ ክርስቲያን አጋዥ ተቋማት እንዲታዩ ያደርጋቸዋል። በመሆኑም፣ ቤተ ክርስቲያን የመጋቢነትንና የተልእኮ ጥሪዋን እንድትወጣ አገልጋዮችን በማሠልጠን ያግዟታል። የነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች ቤተ ክርስቲያንን በማስታጠቅ በፍጥነት እየተለዋወጠ ባለው ዓለም ውስጥ ምስክር የምትሆንበትም መርጃዎች በማቀበል ብቁ እንድትሆን ያደረጋሉ። ለዚህ ነው የነገረ መለኮት ትምህርት ዋና ዓላማው ተማሪውን መለወጥ ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንን/አማኝ ማኅበረ ሰቡን መለወጥ ነው የሚባለው። ይህ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እና ኅብረተ ሰቡን ማድመጥ ይጠይቃል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ግንኙነት እጅግ ወሳኝ ነው፤ በነገረ መለኮት ተቋማቱ መካከል፣ ከቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ከኅብረተ ሰቡ ጋር። ይህ ካልሆነ በነገረ መለኮት ትምህረት ቤቶች የሚሰጡ ትምህርቶች ከነባራዊው ሁኔታ በእጅጉ የራቁ ሊሆኑ ይችላሉ። የዚህ ውጤቱ ደግሞ ተማሪዎች የተማሩትን ትምህርት በተማሩበት ማኅበረ ሰብ ውስጥ እንዳይተገብሩት ትልቅ እንቅፋት ይሆንባቸዋል፤ በትምህርት ቤት ያገኙትን እውቀትም ከተጨባጭ የቤተ ክርስቲያን ችግሮች ጋር ማስታረቅ እንዲሳናቸው ያደርጋል።

የጥሩ ነገረ መለኮት ተቋም መለኪያዎች

ስቲቭ ሃርዲ (Excellence in Theological Education effective Training for Church leaders) በተባለው መጽሐፉ ልዕቀት ያላቸው የነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች የሚከተሉትን ያሟሉ ናቸው ይላሉ፡- ጥሩ አመራር፣ ጥሩ ዕቅድ፣ መልካም አስተዳደር፣ ጥሩ ሥርዐተ ትምህርት፣ ጥሩ መምህራን፣ ጥሩ አገልግሎት መስጫ፣ ጥሩ የቤተ መጽሐፍት አገልግሎት፣ አስተማማኝ ገንዘብ የማግኛ ዘዴ፣ ሥልጠናን ማስፋፋት እንዲሁም ግምገማና ለውጥ። እንደ ሃርዲ አስተሳሰብ አንድ ደረጃውን የጠበቀ የሥነ መለኮት ተቋም ለመገንባት ከላይ የተዘረዘሩትን መሥፈርቶች ማሟላት ወሳኝ ይሆናል። በአገራችን ከሚገኙ የነገረ መለኮት ተቋማት መካከል ምን ያህሎቹ እነዚህን መሥፈርቶች ያሟላሉ የሚለው ለአጥኚዎች የሚተው ቢሆንም፣ በተጨባጭ እንደሚታየው ግን አንዳንድ ትምህርት ቤቶች መሥፈርቱን ስለማሟላታቸው ጥያቄ ማንሣት ይችላል።

ዐውዳዊነት፣ ሥርዐተ ትምህርትና አበርክቶ

“የብልጽግና ወንጌል”፣ የስሕተት አስተምህሮና ልምምድ፣ ድኽነት፣ የአመራር ቀውስ፣ “ኪራይ ሰብሳቢነት”፣ ወዘተ… በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች ዘንድ የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው። ʻበነገረ መለኮት ትምህርት ቤት ውስጥ ያለው ሥርዐተ ትምህርት ለእንደዚህ ዐይነት ችግሮች ትኩረት እየሰጠ ነውን?ʼ የሚለው ጥያቄ ሊታሰብበት የተገባ ነው። የትምህርት ሥርዐታችን የምዕራቡ ዓለም ግልባጭ ብቻ ከሆነ ውጤታማ ለመሆን አስቸጋሪ ነው፤ የምዕራቡ ዓለም የትምህርት ሥርዐት ለአገራችን ችግር መፍትሔ ላይሰጥ ይችላልና። ስለዚህም የነገረ መለኮት ትምህርት ዐውዳዊ ሊሆን ግድ ይለዋል፤ ነገረ መለኮት ዓለም አቀፋዊ ገጽታ ያለው ቢሆንም፣ ለዐውዳዊ እውነታዎች ግን ጆሮውን የደፈነ መሆን የለበትም።

ሁሉም ነገር የምዕራቡን ዓለም የሚመስል መሆን የለበትም፤ ለባህሎቻችን ስሜታዊ ቅርበት ሊኖረን ይገባል። ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸው ተመልሰው የሚያገለግሉበትን ስፍራና ማኅበረ ሰብ ያገናዘበ ትምህርት መስጠት አለባቸው። የነገረ መለኮት ትምህርት ፋይዳ የሚኖረው በቀጣይነት በአካባቢ ካሉ ችግሮች ጋር እየተወያየ ሲሄድ ነው። የዘመኑን ምልክቶች በማንበብ መፍትሔ እየሰጠ መሄድ አለበት እንጂ ኀልዮታዊ (theoretical) ብቻ መሆን የለበትም። የነገረ መለኮት ትምህርት ዐውድን ባገናዘበ መልኩ ከተሰጠ ቤተ ክርስቲያንን እና አገርን በመለወጥ ረገድ ትልቅ ሚና ሊጫወት ይችላል። ይህን እንዲሆን ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን የምንፈታበት ዕይታ ዐውደ ገብ የሆነና ለአሁኑ ጥያቄ ምላሽን የሚሰጥ መሆን አለበት።

ከሚስዮናዊያን የወረስነውን ሥርዐተ ትምህርት እንደገና የአገራችንን ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ መቅረጽ አለብን። አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ይህን ማድረግ እንዳይችሉ የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙት ከውጪ ተቋማት ነው። የምዕራቡን ዓለም የትምህርት ሥርዐት እንዳለ መገልበጥ የነገረ መለኮት ትምህርት በአገራችን ውስጥ ለሚነሡ ችግሮች መፍትሔ እንዳይሰጥ ያደርገዋል። የነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸው የመጡበትን ቤተ ክርስቲያን እና ማኅበረ-ባህላዊ ዐውድ ማወቅ አለባቸው። ለዚህ ደግሞ ሥርዐተ ትምህርቱ ይህን ታሳቢ አድርጎ የተቀረጸ ሊሆን ይገባዋል። አንዳንድ ጊዜ የትምህርት ሥርዐቱ የተገደበ ከሆነ የትምህርት አሰጣጡ ከላይ ወደ ታች ይሆናል (top-down model)፤ አስተማሪው ሰጪ፣ ተማሪዎች ደግሞ ተቀባይ ብቻ። ይህ ሂደት የተማሪዎችን አፍላቂነት የሚገድብ ሲሆን፣ ተማሪዎች ከዐውዳቸው ጋር ጥሩ መስተጋብር እንዳይኖራቸው ዕንቅፋት ይሆናል። ከዚህ ይልቅ ተማሪዎች ልምምዳቸውን፣ ሃይማኖታዊ ትውፊታቸውን፣ የእምነት ማኅበረ ሰባቸውን የሚወያዩበት ዕድል በትምህርት አሰጣጡ ሂደት ውስጥ ሊፈጠርላቸው ይገባል።

የነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶቻችን በኢትዮጵያ ዐውድ ውስጥ ምላሽ መስጠት የሚያስችል ሥርዐተ ትምህርትን መዘርጋት አለባቸው። ʻየወንጌላውያን አማኞች በማኅበረ ሰቡ ውስጥ የነቃ ተሳትፎ አያደርጉምʼ የሚል ሂስ ይቀርብባቸዋል። የሥነ መለኮት ምሩቃን በቤተ ክርስቲያን ከሚያደርጉት አስተዋጽኦ በተጨማሪ በጽሑፍ የሚያበረክቱት በጎ ነገር በእጅጉ የተገደበ ነው። ምሁራዊና ችግር ፈቺ የሆኑ ጥናቶችንና ምርምሮችን የማድረግ ባህል በነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶቻችን ውስጥ እምብዛም የተለመደ አይደለም። ለዚህም ነው አንዳንድ ጊዜ ተመራቂዎች ችግር ፈቺ ሲሆኑ የማንመለከተው። ችግሮቻችንን ከምንፈታባቸው መንገዶች መካከል አንዱ ሐሳብን በተለያዩ መንገዶች ማንሸራሸር ነው። ሆኖም ግን ይህ እንዳይሆን የነገረ መለኮት ተማሪዎች ድምፃቸውን የሚያሰሙባቸው በቂ መንገዶች የሉም።

በኢትዮጵያ ውስጥ የነገረ መለኮት ተማሪዎችና ምሁራን የምርምር ውጤቶቻቸውን የሚያሳትሙበት ይሄ ነው የሚባል የምርምር መጽሔት የላቸውም። ይህ በሌለበት ሁኔታ ደግሞ ተጽእኖን መፍጠር እጅግ አስቸጋሪ ነው። ሰዎች እንዲጽፉ ካልተበረታቱ ደግሞ አፍላቂ እና ችግር ፈቺ መሆን አይችሉም።

ኢትዮጵያ ብዝኀ ሃይማኖት ያለባት አገር እንደ መሆኗ ትምህርታችን ይህን ያገናዘበ ሊሆን ይገባዋል። አንዳንድ ጊዜ በነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተማሪዎች የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሳይማሩ የምዕራቡን ዓለም ታሪክ ብቻ ሊማሩ ይችላሉ። አካባቢያችንን ካላወቅን የነገረ መለኮት ትምህርት ሽባ እና ውጤት አልባ መሆኑ አይቀሬ ነው። ለዚህ ነው ʻየክርስቲያን አገልጋይ በአንድ እጁ መጽሐፍ ቅዱስ በሌላ እጁ ጋዜጣ መያዝ አለበትʼ የሚባለው። ለሥነ አፈታት፣ ለብሉይ እና ለአዲስ ኪዳን፣ ለአስተምህሮ (ዶክትሪን) የምንሰጠውን ትኩረት ያህል ለማኅበረ ሰባዊ ሳይንስ ጥናት፣ ለፖለቲካ እና ለሌሎች ዘርፎች ትኩረትም መስጠት አለብን። ይህ የአገልግሎት ብቃትን የሚሳድግ ነው። ሁለትዮሽ (dualistic) አመለካከትን ካላስወገድን በቀር ያወቅነውን በተግባር መተርጎም እጅግ አስቸጋሪ መሆኑ አይቀርም።

የነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸው ምን እየሠሩ እንደ ሆነ ማጥናት አለባቸው።  ይህ የሥርዐተ ትምህርታቸውን እንዲገመግሙ ከማድረጉም በተጨማሪ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ተባብረው የሚሠሩበትን ዕድል በመፍጠር በቤተ ክርስቲያን እና በማኅበረ ሰቡ ውስጥ የሚኖራቸውን ፋይዳ ቀጣይነት ያረጋግጥላቸዋል።

ትምህርት እና አገርኛ ቋንቋ

የነገረ መለኮት ትምህርትን በአገርኛ ቋንቋ ማስተማር ፋዳው ብዙ ነው። ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ቢማሩ ያወቁትን እውነት በከባቢያቸው ካለው እውነታ ጋር በቀላሉ ማዛመድ ይችላሉ። ይህንንም በመገንዘብ ሊሆን ይችላል አንዳንድ ትምህርት ቤቶች የነገረ መለኮት ትምህረትን በአማርኛ እና በኦሮምኛ ቋንቋ መስጠት ጀምረዋል። ሆኖም ግን በኢትዮጵያ ውስጥ እየተስተዋለ ያለው ችግር ለተማሪዎች ማጣቀሻ የሚሆኑ በቂ መጻሕፍት አለመኖራቸው ነው። ይህ በሆነበት ሁኔታ ደግሞ የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ አይቻልም። ስለዚህም የሚመለከታቸው ትምህርት ቤቶችም ሆኑ ሌሎች ተቋማት ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረትን በመስጠት የተለያዩ መጻሕፍት የሚተረጎሙበትን እንዲሁም የተለያዩ ሞዲዩሎች የሚጻፉባቸውን መንገዶች ቢያፈላልጉ መልካም ነው። በአገርኛ ቋንቋ ማስተማር የትምህርት ተደራሽነትን የሚያሰፋ ቢሆንም፣ ተማሪዎች በትምህርት ላይ እያሉም ሆነ ከትምህርት በኋላ የሚያጣቅሱት በአገርኛ ቋንቋ የተጻፉ መጻሕፍትና የምርምር ውጤቶች ስለሌሏቸው የእውቀት አድማሳቸው በእጅጉ የተገደበ ይሆናል። ከዚሁ ጋር በተያያዥነት የሚነሣው በእነዚህ ትምህርት ቤቶች የሚያልፉ ተማሪዎች ትልቁ ችግር የተማሪዎች የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታ በእጅጉ አነስተኛ መሆኑ ነው፤ ስለዚህም ትምህርትን በአገሪኛ ቋንቋ ከመስጠት በተጨማሪ ተማሪዎች በእንግሊዝኛ የተጻፉ መጻሕፍትን ማጣቀስ እንዲችሉ ለቋንቋው ትልቅ የሆነ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

የኢትዮጵያ ሥነ መለኮት ተቋማት ችግሮች

ተቋማዊነት

ተቋማዊነት የማስተማሪያ ሕንፃና ቁሳቁስ (facilities)፣ ከመምህራን፣ ከገንዘብ፣ ወዘተ… ጋር ተያያዘ ነው። አንድ የነገረ መለኮት ትምህርት ቤት ጥሩ ተቋም ነው የሚባለው ተገቢው የአደረጃጀት መዋቅር፣ የሰው ኀይልና አሠራር ሲኖረው ነው። ከዚህ አንጻር የነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶቻችን ሲፈተሹ ጥሩ ተቋማዊነትን የሚያሳዩ ትምህርት ቤቶች ቢኖሩም፣ በዛው ልክ ደግሞ የተቋምነት ገጽታ የሌላቸው፣ ነገር ግን እንዲሁ “በጨበጣ” ትምህርት የሚሰጡ ይገኛሉ። አንድ ተቋም እንደ ጥሩ ተቋም ካልተዋቀረ ጥሩ የትምህርትና የምርምር ማዕከል ሊሆን አይችልም። የነገረ መለኮት ተቋማትን እንደ መንፈሳዊ ድርጅት አድርጎ በመቁጠር ተቀባይነት ያለውን የተቋም አመራር ይዞ ከመከተል ይልቅ፣ ሕግና ደንብን ባልተከተለ መልኩ መምራት በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚስተዋል ችግር ነው። ይህ ደግሞ ጥራት ያለው ትምህርት እንዳይኖር ከማድረጉ በተጨማሪ በተማሪዎች ውጤታማነት ላይ ትልቅ የሆነን ተጽዕኖ ይፈጥራል።

የጥራት ችግር

ጥራት ያለው የነገረ መለኮት ትምህርት መስጠት ብዙ ገንዘብን የሚጠይቅ ነው። ይህ ግድ የማይላቸው ግለ ሰቦችም ሆኑ ተቋማት ግን እዚህም እዚያም መታየታቸው አልቀረም። ቀላል ግምት የማይሰጠው ቁጥር ያላቸው ት/ቤቶች በቂ አስተማሪዎችና መርጃ መሣሪያዎች ሳይኖራቸው በዲግሪና ከዚያም በላይ ባሉ የትምህርት ደረጃዎች ተማሪዎች ያስመርቃሉ። ይህ አካሄድ በጊዜ ሂደት የነገረ መለኮት ምሩቃን ሊጫወቱት የሚችሉትን ሚና የሚያኮስስ መሆኑ ለማንም የተሰወረ አይሆንም። ተማሪዎች በቂ እውቀትን ሳይገበዩ ከተመረቁ የሚኖራቸው ፋይዳን መገመት የሚያስቸግር አይሆንም። አንዳንድ ተቋማት በአነስተኛ ደረጃ ላይ ያለ ቤተ መጻሕፍት ሳያዘጋጁ እንኳን ትምህርት ይሰጣሉ።

በብዙ የነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለአስተማሪ ጥራት ትልቅ የሆነ ትኩረት አይሰጠውም። የተመረቀ ሁሉ ማስተማር የሚችል የሚመስላቸው ብዙ ትምህርት ቤቶች አሉ። እንደውም አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ቋሚ አስተማሪ ሳይኖራቸው በትርፍ ሰዓት መምህራን ብቻ ትምህርት ይሰጣሉ። እነዚህና ተዛማጅ ችግሮች በትምህርት ጥራት ላይ ትልቅ የሆነ ተጽእኖ እያሳደሩ ነው። ይህ ደግሞ የነገረ መለኮት ምሩቃን ቤተ ክርስቲያን እና ማኅበረ ሰብ ላይ አዎንታዊ ተጽእኖን ማሳደር እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል።

የትምህርት ቤቶች መበራከት

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች በቁጥር እየተበራከቱ መጥተዋል። ሥነ መለኮት “የተቆላ ገብስ ነው፤ ሲበሉት ይጥማል ሲዘሩት አይበቅልም” የተባለበት ጊዜ እንዳልነበረ ሁሉ፣ አሁን ብዙዎች ፊታቸውን ወደ ነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች እያዞሩ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ ገበያው እያደገ ሲመጣ ብዙ ቤተ እምነቶች እና አንዳንድ ግለ ሰቦች ትምህርት ቤቶችን እየከፈቱ ይገኛሉ።

በቅርበት ከታየ አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች ተመሳሳይ የትምህርት ሥርዐትን ነው የሚከተሉት፤ ለየት ያለ አካሄድ የሚከተሉ ትምህርት ቤቶችን ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ከዚያም ሲብስ አንዳንዶቹ ትምህርት ቤቶች የግለ ሰብ ንብረት ናቸው። ይህ ደግሞ ከገንዘብ፣ ከአመራር፣ ከትምህርት አቀባበል መለኪያ ከጥራት፣ ወዘተ… ጋር የተያያዙ ችግሮችን እየፈጠረ ነው። አንዳንድ ትምህርት ቤቶች 12ኛ ክፍልን ላላጠናቀቀ ተማሪ ዲግሪ እንደሚያድሉ ይታወቃል።

የነገረ መለኮት ትምህርት ቤት መበራከት ፋይዳው የጎላ ቢሆንም፣ በአግባቡ ያልሠለጠኑ ተማሪዎችን ማፍራት (ill-trained theologian) ተገቢ ካለመሆኑ በተጨማሪ የሞራል ጥያቄ ያስነሣል። ትምህርት ቤቶች እየተበራከቱ ሲሄዱ አገር በቀል የሆነ እና እውቅና የሚሰጥ ተቋም አስፈላጊነትን ያጎላዋል። በዚህ ረገድ “የኢትዮጵያ ሥነ መለኮት ተቋማት ማኅበር” የጀመረው ጅምር የሚያስመሰግነው ነው። የነገረ መለኮት ትምህርት ጥራት እንዲጠበቅ፣ የመምህራንን አቅም ማሳደግ (Faculty development) እና ቤተ መጻሕፍትን ለማጠናከር በጋራ መሥራት ያስፈልጋል።

“የውሸት ዲግሪ”

“የውሸት ዲግሪ” የሚሰጡ አንዳንድ ትምህርት ቤቶችም ብቅ እያሉ ነው። በትምህርት ዓለም ውስጥ የተለያዩ የዲግሪ ጀረጃዎች መኖራቸው እሙን ነው። ሰርተፍኬት፣ ዲፕሎማ፣ ማስተርስ እያለ ከፍተኛ እና የመጨረሻ ወደ ሆነው የዶክትሬት ድግሪ ይዘልቃል። ትምህርቱ እንደሚሰጥበት አገር እነዚህ የትምህርት ዘርፎች የሚፈጁት የትምህርት ጊዜ ይለያያል። ለምሳሌ በአሜሪካን አገር በተለምዶ የመጀመሪያ ዲግሪ ለማግኘት አራት ዓመት፣ የማስተርስ ዲግሪ ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት፣ የዶክትሬት ዲግሪ በትንሹ አራት ዓመታት የሚፈጅ ሲሆን፣ የእንግሊዝን የትምህርት ሥርዐት በሚከተሉ አገራት ደግሞ የመጀመሪያ ዲግሪ ሦስት ዓመት (የሆነርስ ዲግሪ ደግሞ አራት ዓመታት)፣ የማስተርስ ዲግሪ ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት፣ የዶክትሬት ዲግሪ ደግሞ በትንሹ ሦስት ዓመት ይፈጃል።

አሁን ግን በተልእኮ ከማይታወቁ ትምህርት ቤቶች በአንድ ዓመት ውስጥ የዶክትሬት ዲግሪ ተምረን አጠናቀቀን የሚሉ አገልጋዮች እየተበራከቱ መጥተዋል። አንዳንድ ትምህርት ቤቶች በዝቅተኛ ክፍያ ዲፕሎማን ያድላሉ። በአንዳንድ የነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች ደግሞ ትምህርትን ላልተከታተሉ ተማሪዎችም ዲግሪ በትውውቅ እንደሚሰጥ የአደባባይ ምስጢር ሆኗል። እነዚህ ትምህርት ቤቶች በደንብ የተቀረጸ ሥርዐተ ትምህርት እና ብቁ የሆኑ መምህራን የሏቸውም። አንዳንድ ተማሪዎችም በትምህርት ውጣ ውረድ ውስጥ ሳያልፉ በአጭሩ የዲግሪ ባለቤት የመሆን ፍላጎት ስላላቸው ይህን ከመሰሉት ተቋማት በገንዘባቸው ዲግሪውን ይገዛሉ።

አንዳንድ ቤተ እምነቶች አገልጋዮች ሥነ መለኮት የተማሩ መሆን አለባቸው የሚል ፖሊሲ አላቸው። ከዚህም የተነሣ የደሞዝ እርከኑንም ሆነ ተቀባይነቱን ለማግኘት ትምህርቱ የግድ አስፈላጊ የሚሆንባቸው ግለ ሰቦች አሉ። ከዚህም በተጨማሪ ትምህርት በኅብረተ ሰቡ ውስጥ ሊያስገኝ የሚችለውን ክብር በመገንዘብ አንዳንዶች ለዝና እና ለክብር አቋራጭ መንገዱን መፈለጋቸው አይቀርም። ይህንን ክፍተት ለመሙላት የተዘጋጁ የሚመስሉ ት/ቤቶች ደግሞ “እኛ አለንላችሁ!” በማለት ብቅ ይላሉ። ገንዘቡን ተቀብለው “ዲግሪውን” ያድላሉ።

የተማሪዎች ትልቁ ጥያቄ

ሌላው ከነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች ጋር በተያያዘ የሚነሣው አንዱ እና ትልቁ ችግር ተማሪዎች ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ ወደ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናቸው የመመለስ ፍላጎታቸው በእጅጉ የቀነሰ ሆኖ መገኘቱ ነው። አንዳንድ ቤተ እምነቶች በነገረ መለኮት የተመረቁ ተማሪዎችን ለመቀበል ፈቃደኞች አይደሉም፤ ወይም የተመቻቸ ሁኔታ የላቸውም፤ ከዚህም የተነሣ ተማሪዎች ከተማሩ በኋላ ሌሎች አማራጮችን ሲፈልጉ ይስተዋላሉ። ይህም ሂደት አጥቢያዎች ለነገረ መለኮት ተቋማት በጎ አመለካከት እንዳይኖራቸው አድርጓል፤ በማድረግም ላይ ነው። ይህን ችግር ለመቅረፍ የነረገ መለኮት ትምህርት ቤቶች ከአጥቢያዎች ጋር በመቀራረብ በስፋት በመሥራት ችግሩን ለመቅረፍ መንቀሳቀስ አለባቸው። ተማሪው ʻስጨርስ የት እሆናለሁ?ʼ ለሚለው አግባብ ያለው ጥያቄ አግባብ ያለው መልስ ይሻል።

ማጠቃለያ

የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቶች የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የሚሠለጥኑበት ቦታ እንደ መሆኑ ተገቢ ግብና ትክክለኛ የትኩረት አቅጣጫ ሊኖራቸው ያስፈልጋል። ይህም ብቻ ሳይሆን የሚሰጠው ትምህርት ፋይዳ እንዲኖረው እንዲሁም ተግባራዊ እንዲሆን ዐውዱን ያገናዘበ ሊሆን ይገባዋል። ተግባራዊ ትምህርትም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

የነገረ መለኮት ምሩቃን በኢትዮጵያ ክርስትና ውስጥ ሊጫወቱት የሚገባው ሚና ዘርፈ ብዙ ነው። ይህ ሚና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብቻ የተገደበ ሳይሆን በኅብረተ ሰቡም ዘንድ የሚገለጥ መሆን አለበት። ይህን ለማድረግ ደግሞ የነገረ መለኮት ትምህርት ወሳኝ ነው። በርግጥ ጥራት ያለው የነገረ መለኮት ትምህርት መስጠት ብዙ ወጪን የሚጠይቅ ነው። ስለሆነም የተለያዩ የነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች በተቀናጀ መንገድ ቢሠሩ የሚስተዋሉትን የጥራት ችግሮችን ተባብረው መፍታት ይችላሉ። በዚህ ረገድ “የኢትዮጵያ ሥነ መለኮት ተቋማት ማኅበር” እየሠራው ያለው ʻይበልʼ የሚያሰኝ ነው።

የነገረ መለኮት ተቋማት ከማኅበረ ሰቡ ከተገነጠሉ ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች በአእምሮ እውቀት ብቻ የታጨቁ፣ ልባቸው ግን ባዶ የሆነ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ በነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች የሚሰጠው ሥልጠና ፍላጎትን ያገናዘበ ሊሆን ይገባዋል። ለዚህ ነው አንዳንድ ተቺዎች ʻየነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች ከእውነታው ብዙ የራቁ ምሩቃንን ነው የሚያፈሩትʼ እያሉ የሚከሱት። ይህ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ነገረ መለኮትን እና የነገረ መለኮት ተማሪዎችን በተመለከተ ተጠራጣሪ እንድትሆን ያደርጋታል።

የነገረ መለኮት ተቋማት በቤተ ክርስቲያን ኅልውና ላይ የተመሠረቱ ስለሆነ ከአማኝ ማኅበረ ሰቡ የተገነጠሉ ሊሆኑ አይገባም። ነገረ መለኮት የእውቀት ጉዳይ ብቻ ከሆነ ሕይወት አልባ ይሆናል። ለቤተ ክርስቲያን የሚኖረውም አበርክቶ ይኮስሳል። በኢትዮጵያ ውስጥ የነገረ መለኮት ትምህርት ቤተ አስፈላጊነትን በመገንዘብ ብዙ ቤተ እምነቶች የተለያየ ጀረጃ ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቶችን ከፍተዋል። ይህ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ቢሆንም፣ ብዙ ችግሮችም በተያያዥነት ይነሣሉ። በቂ በጀት፣ የሰው ኀይልና መርጃ መሣሪዎች ሳይኖሩ ትምህርት ቤቶችን መክፈት በምናፈራቸው ተማሪዎች ላይ አሉታዊ ተጽእኖን ይፈጥራል። ያለ ምንም በቂ ዝግጅት ትምህርት ቤቶችን መክፈትም ደግሞ ተገቢ አይደለም።

ከላይ እንደተመለከተው የነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች ቤተ ክርስቲያንን ለማገዝ የተቋቋሙ ናቸው። በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እና ከዚያ ባሻገር የሚያገለግሉ አገልጋዮችን ያሠለጥናሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቶች ዋና ተልእኮ ቤተ ክርስቲያንን ብሎም ኅብረተ ሰብን መለወጥ ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ መጠየቅ ያለበት ትልቁ ጥያቄ ʻበርግጥ፤ ጥሩ የሆኑ የነገረ መለኮት ምሩቃንን እያፈራን ነው?ʼ የሚለው ነው።

Share this article:

የማንነት ስምምነት ካልቀደመ እየሠሩ ማፍረስ ይቀጥላል

አገራችንን በዚህ ጊዜ እየተፈታተናት ያለው ጉልሕ ችግር፣ በማንነት ላይ ያሉ ጥያቄዎቻችን ምላሽ ስላላገኙ ነው፤ ይህንንም በተገቢው መንገድ እስካልፈታን ድረስ ውጥረቶች መቀጠላቸው አይቀርም ይላል በሰላም ግንባትና በእርቅ ላይ ተመራማሪ የሆነው ሰሎሞን ጥላሁን።

ተጨማሪ ያንብቡ

መስቀሉ፦ ሲሞን ቬይ

የክርስቶስ ስቃይ ያለ ጥርጥር ልዕለ ተፍጥሯዊ ፍትሕ ነው። ያሉትን የርኅራኄ ርዳታ ሁሉ ፍጹም የከለከል ፍትሕ ነው፤ የእግዚአብሔር አብ ፍቅር እንኳ እንዳይራራለት ያደረገ ፍትሕ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.