[the_ad_group id=”107″]

“እስሮችን ዐስቡ”

በግንብ፣ በብረት፣ በአደገኛ እሾሃማ አጥር፣ ጠብ መንጃ በታጠቁ ወታደሮች የሚጠበቅ ቅጥር ግቢ፣ ወደ ጎን ግድግዳ፣ ወደ ላይ ሰማይ ብቻ የሚታይበት የጽልመት ዓለም፣ የቁጭት ማእበል የሚንጠው አእምሮ፣ ‘ምነው ባላረኩት ኖሮ’ የሚል የጸጸት ወላፈን የሚለበልበው ልብ፣ ፍትሕን ሳታገኝ በግፍ የተከረቸመች ነፍስ፣ ከሚወዱት ቤተ ሰብ፣ ጓደኛና ከማኅበረ ሰብ ተገልሎ በሚገኝ ጠባብ ዓለም ውስጥ የተስፋን ቀን እየጠበቁ መኖር፣ ወዘተ. የወህኒ ሕይወት አንዱ አካል ነው።

“ታስሬ አልጠየቃችሁኝም”

አምልኮ በሕይወት የሚገለጥ፣ ለእግዚእበሔር የሚቀርብ የሁለንተና ምላሽ ነው። ንጹሕ የሆነ፣ ነውርም የሌለበት አምልኮ በዓለም ከሚገኝ እድፈት ሰውነትን መጠበቅ እና ችግረኞችን በችግራቸው መረዳት እንደ ሆነ ቅዱስ ቃሉ ይናገራል (ያዕ. 1፥ 27)። ከዚህ ጋር ተያይዞ የሕግ ታራሚዎችን ማገልገል ከሕይወት የሚቆረስ የክርስቲያኖች ኀላፊነት እንደ ሆነ በኢትዮጵያ ነገረ መለኮት ድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት (EGST) መምህርና የተማሪዎች ዲን የሆኑት ዶ/ር ቴዎድሮስ አሰፋ ይናራሉ። ዶ/ር ቴዎድሮስ “እስረኞችን (ታራሚዎችን) ማገልገል የጌታ ትእዛዝ” እንደ ሆነ ነው የሚያስረዱት። “ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ መጨረሻው ዘመን ባስተማረበት በማቴ. 25፥43-46 ‘…ታስሬ አልጠየቃችሁኝም’ በማለት የወቀሳቸው ‘እርጉማን’ የተወቀሱበትን ወንጀል ሲያስተባብሉ ‘ታስረህ ዐይተን መቼ አልጠየቅንህም?’ ቢሉም፣ ‘ከእነዚህ ለአንዱ ስላላደረጋችሁት ለእኔ ደግሞ አላደረጋችሁትም’ በማለት ለደረደሩት ምክንያታቸው የማያፈናፍን ምለሽ” እንደሰጣቸው ያብራራሉ።

“‘ከእነርሱ ጋር እንደ ታሰራችሁ ሆናችሁ እስሮችን አስቡ’ የሚለው የዕብራውያን መልእክት (13፥፡3) ትእዛአዝ አንጂ ‘ብታደርጉት መልካም ነው’ የሚል ምክር አዘል ቃል አይደለም” የሚሉት ደግሞ በመሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ዋና ጽ/ቤት፣ የሕግ ታራሚዎች አገልግሎት መምሪያ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ንጉሤ በቀለ ናቸው። “ታራሚዎች ከዕይታ የራቁ በመሆናቸው፣ ሰዎች የማያስቧቸው ናቸው፤ ክርስቲያኖች ግን በእነርሱ ጫማ ውስጥ ገብተው ስሜታቸውን በመጋራት ሊያጽናኗቸው እና ሊደግፏቸው ይገባል” ይላሉ አቶ ንጉሤ።
በርግጥ በማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ 25 ላይ የሚገኘው “ታስሬ አልጠየቃችሁኝም” የሚለው ቃል አተረጓጎም አሻሚ ሊመስል እንደሚችል የሚናገሩት የነገረ መለኮት መምህሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ፣ “ሁሉንም ምሳሌያዊ አነጋገር (Metaphor) በቀጥታ መተርጎም ባይቻልም፣ በዚህ ክፍል ግን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲናገር ‘ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው’ የሚለው ለሌላው የምናደርገው በጎ ምግባር ለጌታ ለራሱ እንዳደረግነው እንደሚቆጥረው ያስረዳናል” በማለት አክለው ያስረዳሉ።

“የቄሳሩ ድንጋጌ”

በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ሰብዓዊ መብቶች ደንጋጌ፣ አንቀጽ 21 “በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች መብት”በሚለውአዋጅሥር፣በተራቁጥር1እና2 “በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰብአዊ ክብራቸውን በሚጠብቁ ሁኔታዎች የመያዝ መብት አላቸው። ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከሃይማኖት አማካሪዎቻቸው፣ ከሐኪሞቻቻው እና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ለመገናኘተና እንዲጎበኟቸውም ዕድል የማግኘት መብት አላቸው።” ይላል። በዚህ ድንጋጌ መሠረት በሕግ ጥበቃ ሥር በእርምት ላይ የሚገኙ ወገኖች ሰብዓዊ ክብራቸው ተጠብቆ መያዝ አለባቸው። የእርምት ሂደቱ የተሟላ እንዲሆን ደግሞ የኅብረተ ሰቡ ድጋፍ እጅግ አስፈላጊ እንደ ሆነ ያስማማል።

በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ረዳት ኀላፊ ሆኑት አቶ አዲሱ ጴጥሮስ የታራሚዎች ሰብዓዊ ጥበቃ አያያዝ የመንግሥት ኀላፊነት እንደ ሆነ ቢገልጹም፣ ታራሚዎችን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ለማገልገል ግን ኅብረተ ሰቡና የአጋዥ ተቋማት ድጋፍ ወሳኝ እንደ ሆነ ነው ለሕንጸት የተናገሩት። “ከኅብረተ ሰቡ የሚመጡ ድጋፎችን ማረሚያ ቤቶች በደስታ” እንደሚቀበሉ አቶ አዲሱ አክለው ጠቁመዋል።

በማረም ሂደቱ ላይ ከመንግሥት ውጪ ያሉ የኅብረተ ሰቡ ተቋማት ተሳትፎን በሚመለከት ክልከላ የሚያደርግ ሕግ እንደሌለ የሚናገሩት ደግሞ የሕግ ባለሙያው አቶ መስፍን አዲሴ ናቸው። እንደ አቶ መስፍን ከሆነ፣ “ቤተ ክርስቲያንም ሆነች ሌሎች መንፈሳዊ ድርጅቶች የሪስቶሬቲቭ ጀስቲስ [ወደ ቀድሞ የመመለስ] ሂደቱን መደገፍ ይኖርባቸዋል” ባይ ናቸው። ነባራዊው “የወንጀለኛ መቅጫ አተገባበር ሂደት ተጎጂውን እና ጎጂውን የሚያራርቅ እንጂ ተቀራርበው ይቅርታ የሚጠያየቁበትን ሁኔታ የሚያመቻች አይደለም። ይህ ደግሞ ተጎጂውን የሚክስ ባለመሆኑ ታሳሪው የእስር ጊዜውን ጨርሶ ከወጣም በኋላ ቢሆን የጠላትነት ስሜቱ ሊቀጥል የሚችልበት” አጋጣሚ እንዳለ ያስረዳሉ። በመሆኑም ይህንን ክፍተት ቤተ ክርስቲያን እና ሌሎች መንፈሳዊ ተቋማት ሊሞሉት የሚችሉት እንደ ሆነ ነው የሕግ ባለሙያው የሚያስረዱት። “ሁለቱን ወገኖች በማቀራረብ የእርቅና ሰላም ሥራ ቢሠራ ተጎጂዎች የኅሊና ጠባሳቸው እንዲሽር፣ ወንጀለኞችም ቢሆኑ ይህንን የበደለኝነት ስሜት ተሸክመው እንዳይኖሩ” እንደሚያደርግ ይገልጻሉ።

እኛ ከወዴት አለን?

በአገራችን በርካታ አገልግሎቶች የቤተ ክርስቲያን አጋዥ በመሆን በወንጌል ስርጭት፣ በወጣቶች፣ በሴቶች፣ በሕፃናት፣ በጎዳና ተዳዳሪዎች፣ በአረጋውያን፣ በሴተኛ አዳሪዎች፣ በሥራ ፈጠራ፣ በትምህርትና ሥልጠና፣ በስፖርት፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ የንጹሕ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የግል እና አካባቢ ንጽሕና ወዘተ. ላይ ተሰማርተው ማኅበረ ሰቡን እያገለገሉ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ ከእነዚህ በብዙ መቶዎች ከሚቆጠሩ አገልግሎቶች መካከል በሕግ ታራሚዎች ላይ ትኩረት አድርገው የሚሠሩት በጣት የሚቆጠሩ መሆናቸው አግራሞትን የሚጭር ነው።
የነገረ መለኮት መምህሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ ቤተ ክርስቲያን እንደ ተቋምነቷ፣ አማኞችም በግለ ሰብ ደረጃ ለአገልግሎቱ ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ ሲያሳስቡ፣ “በሰንበት ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ፣ መዘመር፣ ቃሉን ማንበብና መስማት፣ መባና ዐሥራት መስጠት የአምልኳችን ክፍል እንደሆነው ሁሉ፣ ታራሚዎችን መጠየቅና ማገልገልም የአገልግሎታችን ክፍል እንደ ሆነ ማሰብ ይገባናል” ካሉ በኋላ፣ “ይህ የአገልግሎት መስክ ሰዎች ክርስቶስን እንዲያገኙ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር” እንደ ሆነ ጭምር ጠቁመዋል። የሕግ አማካሪው አቶ መስፍንም ቤተ ክርስቲያን ለታራሚዎች የምትሰጠው አገልግሎት በትክክል ክርስቶስን የምትወክልበት እንደ ሆነ አድርገው እንደሚያምኑ ነው ለሕንጸት የተናገሩት። “አገልግሎቱን በአግባቡ ከተጠቀምን እንደ ዘኬዎች ተግባራዊ ንሰሓን በማምጣት ረገድ ወንጀለኞች በራሳቸው ፈቃድ ተጎጂዎችንም ሆነ ኅብረተ ሰቡን ይቅርታ የሚጠይቁበትም ሆነ የሚክሱበትን ሁኔታ ሊያመቻች ይችላል” ባይ ናቸው።

ቤተ ክርስቲያን በውስጥ ጉዳዮቿ ብቻ ተጠምዳ ሥራ የበዛባት ትመስላለች። በውሰጥ ካሉት የአገልግሎት ዘርፎች ባልተናነሰ ግን የሕግ ታራሚዎችን ለማገልገል መነሣሣት ይገባል። አገልግሎቱ “… ሂዱ …” የሚለውን የጌታን ትእዛዝ የምንተገብርበት አንዱ መስክ ሆኖ የሚታይ ነው። በዚህ መስክ አብያተ ክርስቲያናት የሠሩት ሥራ በጣም አነስተኛ ቢሆንም የመሠረተ ክርሰቶስ ቤተ ክርስቲያን ግን በቢሮ ደረጃ በተዋቀረ አሠራር ላለፊት 18 ዓመታት ታራሚዎችን ለማገልገል ያደረገችው ጥረት ለበርካቶች ምሳሌ ሊሆን የሚችል ነው። በ18 የአገልግሎት ዓመታትም አያሌ ፍሬዎችን እንዳየች የአገልግሎቱ መሪ አቶ ንጉሤ ይናገራሉ። ከዚህም የተነሣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከኀምሣ ባላነሱ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ፈቃድ በማግኘት እያገለገለች ሲሆን፣ በ21 ማረሚያ ቤቶች አገልጋዮችን በቋሚነት በመመደብ ጭምር በማገልገል ላይ እንደሆነች ጠቁመዋል።
ይህም ሆኖ ግን የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ከዚህ የአገልግሎት መስከ የጠፉት ለምን ይሆን? በዚህ አገልግሎት ውስጥ ለብዙ ዓመታት የሠራቸው ወ/ሪት ሳባ ጴጥሮስ እንዳለችው “ታራሚዎችን ለማገልገል በርካቶች ፍላጎት የሌላቸው አገልግሎቱ እጅግ አድካሚና ዋጋ የሚያስከፍል በመሆኑ” ይሆን? ወይስ ከግንዛቤ ዕጥረት? ወይስ ሌላ?

ድጋፍ ሲባል

ከቤተ ሰብና ከአካባቢያቸው ተገልለው መብታቸው በሕግ ለተገደበ ታራሚዎች ዋናውና እጅግ አስፈላጊው ድጋፍ የሥነ ልቦና እንደ ሆነ በመስኩ ላይ የሠሩ ወገኖች ይናራሉ። ለአገልግሎት በሄደችባቸው በልዩ ልዩ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ‘ከምንም በላይ ረኻባችን እናንተ ናችሁ፤ ሰው ይርበናል፤ ፍቅር ይርበናል’ የሚለው የበርካታ ታራሚዎች ድምፅ እንደ ሆነ ነው ሳባ ጴጥሮስ የምትናገረው። “በአንድ ወቅት ታዋቂ መጋቢያንንና ዘማሪያንን በማስተባበር ወደ መርሃ ቤቴ ማረሚያ ቤት በሄድን ወቅት የታራሚያን ደስታ ወደር” እንዳልነበረው የምታስታውሰው ሳባ፣ በጊዜው “‘እኛን ወንጀለኞችን ለመጠየቅ ይህንን ሁሉ አገር አቋርጣችሁ መምጣታችሁ ከምንም በላይ ነው’ በማለት በመደነቅና በደስታ ይናገሩ ነበር” ብላለች። የመሠረተ ክርስቶሱ አቶ ንጉሤም፣ “አንዳንድ ታራሚዎች ቤተ ሰቦቻቸው በጣም ሩቅ አካባቢ የሚኖሩ ከመሆናቸው በተጨማሪ በአቅም ውስንት ምክንያት ለረጅም ዓመታት ያለ ጠያቂ ሊኖሩ” የሚችሉ ከመሆኑ የተነሣ ሰው የመፈለግ ወይም ፍቅርን የማግኘት ፍላጎታቸው እጅግ ከፍ ያለ እንደ ሆነ ያስረዳሉ።

በሥነ ልቦና አገልግሎት ማዕቀፍ ውስጥ ሊካተት የሚችለው ሌላው ጉዳይ የዕርቅ ሂደት ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ ታራሚውንና ተጠያቂውን በማቀራረብ አጥፊው ጥፋቱን እንዲሠራ ምክንያት ከሆኑ ማኅበራዊ ችግር በዘላቂነት እንዲላቀቅ የማድረግ ጥረት ነው። ታራሚዎች ከኅብረተ ሰቡ ተገልለው በአንድ ስፍራ እንዲቀመጡ የሚደረግበት ዋና ዓላማ በሠሩት ወንጀል ምክንያት ተጸጽተው ለወደፊቱ መልካም ዜጋ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። ስለዚህ ከሚቀበሉት ቅጣት በላይ የሚሰጣቸው የእርምት ትምህርት ይልቃል። ታራሚያን በማረሚያ ቤቶች ውስጥ ውስብስብ የሆኑ ወንጀሎችን ይበልጥ የሚማሩበት (ልምድ የሚለዋወጡበት) እንዳይሆን የሥነ ልቦና ትምህርት እጅግ አስፈላጊ ነው። ከሚሰጣቸው የምክር አገልግሎት በተጨማሪ በአእምሮ የታነጹ ዜጎችን ለማፍራት የትምህርት ዕድሎችን ማመቻቸት እና የንባብ ባህላቸውን ለማዳበር የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ማመቻቸት፣ መጻሕፍትና መጽሔቶችን መለገስ፣ ከመሠረታዊ ትምህርት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የሚዘልቅ ትምህርታቸውን በመደበኛና በርቀት እንዲከታተሉ ማድረግ ይቻላል።

አልባሳት (የሕፃናትን ጨምሮ)፣ የንጽሕና መስጫና መጠበቂያ ቁሳቁሶች፣ መጻሕፍትና የተለያዩ የኅትመት ውጤቶች፣ የትምህርት ቁሳቁሶች፣ የቤተ መጻሕፍት ግንባታ፣ መሰብሰቢያ አዳራሽና ወንበሮች፣ ቴሌቪዥኖች፣ የሳተላይት መቀበያ ሳህኖች እና የቴክኒክ ቁሶች፣ የሕክምና ቁሳቁስ እና መድኃኒት፣ የሥራ ፈጠራ ሥልጠና የሙያ ትምህርት እና የመሳሰሉትን ለእስረኞች ከሚደረጉ ድጋፎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

ክርስቲያኖች እነዚህንና የመሳሰሉትን ድጋፎች ለሕግ ታራሚዎች ሊያደርጉ እንደሚችሉ በአገልግሎት ውስጥ ያሉት ይናገራሉ። “አማኞች በቤታቸው በርካታ ልብሶች ሊኖሯቸው ይችላል፤ ቴሌቪዥን ቀይረው ትርፍ ያላቸው ይኖራሉ፤ መጻሕፍትና የመሳሰሉት መረጃ መሣሪያዎች ያላቸው ለእነዚህ ወገኖቻችን ሊለግሱት” እንሚችሉ የምትጠቁመው ሳባ ጴጥሮስ ነች። አቶ ንጉሤም በበኩላቸው የመጻዳጃ ቤት እጥረት ላለባቸው ማረሚያ ቤቶች መገንባት፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ መሥራት፣ ልዩ ልዩ የመጻሕፍትና የአልባሳት ድጋፍ ቤተ ክርስቲያትና አማኞች ለታራሚዎች ሊያደርጓቸው ከሚችሏቸው ድጋፎች መካከል ጥቂቶቹ እንደ ሆኑ ይናገራሉ። የራሳቸውን ቤተ ክርስቲያን ተሞክሮም ሲያካፍሉ፣ “በየዓመቱ የጥር ወር የመጨረሻው ሳምንት በመላው አገሪቱ በሚገኙ የመሠረተ ክርስቶስ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ‘እስረኞችን እናስብ’ በሚል ዝግጅት ይደረጋል። በዕለቱም የገንዘብ መዋጮን ጨምሮ አልባሳትና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች የሚለገሱ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ በእሐድ የአምልኮ ጊዜ የሚሰጠው ትምህርት ስለ እስረኞች” እንደሚሆን ነው የተናገሩት። አያይዘውም ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር በቅንጅት ለመሥራት ፍላጎቱ እንዳለ ጨምረው ገልጸዋል።

ከፍሬዎቹ መካከል

ከጥቂት ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን አባላት ‘ለምን እስረኞችን አንጠይቅም?’ የሚል ሐሳብ ላይ ተወያዩ፤ ሐሳቡ ሁሉንም ስላስማማ ከሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት በአንዱ የሚመቻቸውን ሰዓት ወስነው ምግብ፣ መጻሕፍት እና አልባሳት በመያዝ ወደ ማረሚያ ቤት በመሄድ ከዚያ አስቀድሞ የማያውቋቸውን ታራሚዎችን መጠየቅ ቻሉ፤ ይህም ልማድ ሆነ ዘለቀ። በሂደትም ቤተ ሰብነትን እና ጓደኝነትን በማጎልበት ሁለቱም ወገኖች የሚናፍቁት ኅብረት ተመሠረተ። ከታራሚዎች መካከል አንዱ ወንድም ጌታን አዳኙ አድርጎ በማመን በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ፍጹም የተለወጠ የንሰሓ ሕይወትን አገኘ። የእስር ጊዜውን ጨርሶ ከተፈታ በኋላም ጌታን ከመሰከሩለት ወገኖች መካከል ከሆነች እኅት ጋር ትዳር መሥርተው በአንድ ጣራ ሥር ለመኖር በቁ።

ምስክርነቶቻችን ቢፈተሹሳ?

“ሀገሩን ሁሉ በትምህርቱ የሚያስደምም ሰው ራስ ሆቴል አከባቢ ተነስቷል!” የሚል የወዳጆቼ ጉትጎቷ ቀን ከሌት ቢከታተለኝ፣ በአንድ በኩል በርካቶችን ያስደመመውን ትምህርት ለመቋደስ ብሎም ከዚሁ ከአመለጠህ የወዳጆቼ ጉትጎታ ለማምለጥ በሚል ሁለት ልብ ነበር እግሮቼን ያቀናሁት። በእርግጥም በዛች ቀን ብቻ ወዳጆቼን ምን ነካብኝ ያሰኙ አስተምሮቶችን በአይኔ በብረቱ ተመልክቼ ተመልሻለው፤ ዳግም አልተመለስኩም፤ ደግሞም አልመለስም።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.