[the_ad_group id=”107″]

ዘመነ አስተርእዮ

እንደ መነሻ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዓመቱን በወቅቶች ከፋፍላ፥ በዚያ ላይ የተመሠረቱ መዝሙሮችን በግእዝ ለእግዚአብሔር በማቅረብና ድንቅ ሥራውን በመዘከር ትታወቃለች። ለዚህም በስድስተኛው ምእት ዓመት የተነሣው የዜማ ደራሲ ቅዱስ ያሬድ ከብሉያትና ከሐዲሳት (ከመጽሐፍ ቅዱስ)፣ ከሊቃውንትና ከመሳሰሉት መጻሕፍት ለምስጋናና ለጸሎት የሚስማሙ ንባባትን በመውሰድና ለዜማ ተስማሚ በማድረግ፥ በአራቱ ክፍላተ ዘመን እንዲነገሩ ማዘጋጀቱን የዜማ ሊቃውንት ያስረዳሉ (ጥዑመ ልሳን /ሊቀ ካህናት/ 1981፣ 28)። አራቱ ክፍላተ ዘመን የተባሉትም በዓመት ውስጥ የሚገኙት አራቱ ወቅቶች ናቸው፤ እነርሱም መፀው (ወርኀ ጽጌ ዘመነ ጽጌ/አበባ)፣ ሐጋይ (በጋ)፣ ጸደይ (በልግ) እና ክረምት ሲኾኑ፣ አኹን የምንገኘው ከአራቱ ክፍላተ ዘመን ኹለተኛው ክፍል በኾነው በበጋ (ሐጋይ) ላይ ነው።

ሐጋይ የተባለው ክፍለ ዘመን ከታኅሣሥ 26 – መጋቢት 25 ድረስ ያሉትን ዘጠና ቀናት ወይም ሦስት ወራትን ይሸፍናል። በውስጡም አራት ንኡሳን አዝማናት (ክፍሎች) አሉ። ከእነርሱም ሦስተኛው ክፍልና ከጥር 11 – ጥር 30 ድረስ ያሉትን ዕለታትና ሳምንታት የያዘው ዘመነ ጥምቀት ወአስተርእዮ ይባላል። ይኹን እንጂ ይህ ክፍለ ዘመን እስከ ጥር 30 ድረስ የሚኾነው፥ የዐቢይ ጾም መግቢያ ወደ ታች (የካቲት 1) ሲኾን ነው፤ የጾሙ መግቢያ ወደ ላይ ከፍ ሲል ግን እስከ መጋቢት 3 ድረስ ይኾናል። በሌላ አገላለጽ ዘመነ አስተርእዮ ከጥር 11 እስከ ጾመ ነነዌ ድረስ ያለውን ጊዜ ይሸፍናል (ዐሥራት 1994፤ 244)።

ይህ ወቅት ዘመነ አስተርእዮ ወይም በግሪኩ ኤጲፋንያ የተባለው፥ “መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ በእስራኤል አውራጃ እየዞረ በመምህርነት ስለ ተገለጸ” ነው (ጥዑመ ልሳን /ሊቀ ካህናት/ 1981፣ 50፡51)። ከዚህ ይልቅ በተለይም የግሪኩ ስያሜ “ኤጲፋንያ”፦ “አስተርእዮ፤ መታየት መገለጽ ዕለተ ጥምቀት” ተብሎ ስለ ተፈታና፥ “በዓለ ኤጲፋንያ በዘቦቱ አርኣየ እግዚአብሔር ስብሐተ መለኮቱ በውስተ ጥምቀት በቅድመ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ – የኤጲፋንያ በዓል እግዚአብሔር በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ ፊት በጥምቀት ውስጥ የመለኮቱን ክብር ያሳየበት [በዓል ነው]” የሚል አብነት ስለ ተጠቀሰለት (ኪዳነ ወልድ 1948፣ 250) ይህ ወቅት የኢየሱስ መሲሕነትና የእግዚአብሔር ልጅነት የተገለጠበትን የጥምቀቱን ጊዜ ያሳያል። “በዚህ ጊዜ ውስጥ አምላክ ሰው ኾኖ በሥጋ በመገለጡ፣ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ የአንድነትና የሦስትነት ምስጢር መታወቁ፣ በቃና ዘገሊላ በተደረገው ሰርግ ላይ የመጀመሪያውን ተኣምር በማድረጉ አምላካዊ ኀይሉ መገለጡ እየታሰበ ምስጋና ይቀርባል።” (ዐሥራት 1994፣ 244)።

በዚህ ዘመን እንዲዘመሩ ከተደረሱት የያሬድ ዝማሬዎች መካከል የሚከተለው ዕዝል[1] ይገኝበታል፤ “አስተርአየ ዘኢያስተርኢ ኮነ እሙነ አስተርእዮቱ ለመድኀኒነ ክርስቶስ እንዘ ይገብር ተኣምረ ወመንክረ በውስተ አሕዛብ ወለማይኒ ረሰዮ ወይነ። – የማይታየው ታየ፤ ውሃውን ወደ ወይን በመለወጥ፥ በአሕዛብ መካከልም ተኣምርን በማድረግ የመድኀኒታችን የክርስቶስ መገለጡም እውነት ኾነ” (ዝክረ ቃል ዘውእቱ መጽሐፈ ዚቅ ወመዝሙር 1995፣ 129)።

ኢየሱስ በፈለገ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ሲጠመቅ፥ ወልደ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር ልጅ) መኾኑ በአብና በመንፈስ ቅዱስ ተመስክሮለታል። አስቀድሞ ግን ቃል ሥጋ ኾኖ በመሲሕነትና በእግዚአብሔር ልጅነት ከመገለጡ በፊት በሥጋ ተገልጧል፤ ቅዱሳት መጻሕፍት እግዚአብሔር ወልድ በሥጋ መገለጡን ይመሰክራሉ (ሮሜ 9፥5፤ 1ጢሞ. 3፥16፤ 1ዮሐ. 4፥2-3፤ 2ዮሐ. 7)። በአምላክነቱ ዘመን የማይቈጠርለት እርሱ ሥጋ ኾኖ፥ ዘመን ተቈጥሮለት እስከ ሠላሳ ዓመት ዕድሜው ድረስ በመሲሕነትና በእግዚአብሔር ልጅነት ሳይገለጥ ቈይቷል። በሠላሳ ዓመት ዕድሜው ሲጠመቅ፥ ሰማያት ተከፍተው የእግዚአብሔር መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድና በእርሱ ላይም ሲመጣ ታይቷል። ከሰማያት የተሰማው ድምፅም፥ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ።” (ማቴ. 3፥16-17)። ይህ አስተርእዮት ነው ዘመኑን ዘመነ አስተርእዮ ያሰኘው ማለት ይቻላል።

ኢየሱስ ማነው?

ጥንት ብቻ ሳይኾን ዛሬም ድረስ የኢየሱስ ማንነት ጥያቄ የኾነባቸው ብዙዎች ናቸው። ኢየሱስም ስለ ራሱ፥ ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል? ሲል ጠይቋል (ማቴ. 16፥13)። ኢየሱስ ለአይሁድ ሰው ብቻ (ዕሩቅ ብእሲ) ነው (ማቴ. 13፥55-56)። እንዲህ ያስቡ የነበረው ኢየሱስ ሲጠመቅ እርሱ መሲሑና የእግዚአብሔር ልጅ መኾኑ ከተገለጠ በኋላም ነበር። የእግዚአብሔር ሐሳብ ግን፥ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ቅድስት ማርያም የወለደችው ኢየሱስ፥ ክርስቶስ (ይመጣል የተባለው መሲሕ) እና የእግዚአብሔር ልጅ መኾኑ እንዲታወቅና እንዲታመን፥ ያመነበትም እንዲድን ነው። ነገር ግን ሰማያዊው አባት እግዚአብሔር ካልገለጠ በቀር ኢየሱስን በመሲሕነቱ እና በወልደ እግዚአብሔርነቱ ማስተዋል ለሥጋና ደም አይቻልም።

የአስተርእዮው ምስክር መጥምቁ ዮሐንስ ምን አለ? “እነሆ፥ የዓለምን ኀጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ። አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፥ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ኾኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልኹት ይህ ነው። እኔም አላውቀውም ነበር፤ ዳሩ ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውሃ እያጠመቅኹ እኔ መጣኹ። ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መሰከረ። መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሆኖ ሲወርድ አየኹ፤ በእርሱ ላይም ኖረ። እኔም አላውቀውም ነበር፤ ዳሩ ግን በውሃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ፥ መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ። እኔም አይቻለኹ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ኾነ መስክሬአለኹ” (ዮሐ. 1፥29-34)።

ጌታ ኢየሱስ እርሱን ሰዎች ማን እንደሚሉት ለደቀ መዛሙርቱ ያቀረበው ጥያቄና በደቀ መዛሙርቱ በኩል የተነገረው የሰዎች ምላሽ፥ ስለ ኢየሱስ ማንነት ዛሬ ልናምንና ልንመሰክር የሚገባንን እንድናስተውል በጕልሕ ያሳየናል። ለዚያ ዘመን ሰዎች ኢየሱስ ዕሩቅ ብእሲ እና ከነቢያት አንዱ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ እናንተስ ማን ትሉኛላችኹ? ተብለው በተጠየቁ ጊዜ ሰማያዊው አባት በጴጥሮስ ውስጥ የሰጠው መልስ፥ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነኽ” የሚል ነበር። ለዚህ ምላሽ ጌታ ኢየሱስ፥ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልኽምና ብፁዕ ነኽ” አለው። አያይዞም ቤተ ክርስቲያን በዚህ ሰማያዊ መገለጥ (አስተርእዮ) ላይ እንደምትሠራ ገለጠ (ማቴ. 16፥13-18)። ኢየሱስ፥ ክርስቶስ እና የእግዚአብሔር ልጅ ነው ማለት የቤተ ክርስቲያን መሠረት ነው። ከዚህ መሠረት ውጪ ቤተ ክርስቲያንን ማሰብ ፈጽሞ አይቻልም።

እግዚአብሔር ያልገለጠላቸው ግን ኢየሱስን መሲሑ እና ወልደ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር ልጅ) ከማለት ይልቅ፥ ወልደ ማርያም (የማርያም ልጅ) ወደ ማለት ያዘነብላሉ። ኢየሱስን በመሲሕነቱና በወልደ እግዚአብሔርነቱ ከማወቅ ይልቅ በወልደ ማርያምነቱ ማወቅን የሚያስቀድሙና እዚያው ላይ የሚቀሩም አሉ። እነዚህ ክፍሎች ኢየሱስን ወልደ እግዚአብሔር ከማለት ይልቅ ወልደ ማርያም ቢሉ ይቀናቸዋል። ምናልባትም ይህ ጕዳይ በሃይማኖት ለመለያየት እንደ አንድ ነጥብ እንዲታይላቸውም ሳይፈልጉ አይቀርም። እንዲህ የሚያስቡቱ ስለ ኢየሱስ ከሥጋና ከደም የተማሩና ሰማያዊው አባት ያልገለጠላቸው ናቸው ብንል መጽሐፍ ቅዱስ ይደግፈናል። ስለዚህ እርሱን በሌላ ገጽ አምላክ ነው ቢሉ እንኳ፥ በዚህ አስተርእዮ ላይ ያልተመሠረተ ምስክርነት ይኾናልና ትክክለኛ አይኾንም፤ አያድንምም። ይህ አስተርእዮውን ካለማስተዋል የሚመጣ የሥጋና ደም ትምህርት ነው።

ኢየሱስ በሥጋ ልደት ወልደ ማርያም መኾኑንማ እንኳ ክርስቲያኖች መሲሕነቱንና ወልደ እግዚአብሔር መኾኑን ያልተቀበሉት አይሁድም ያምናሉ። ከአስተርእዮው በኋላ ግን የሚያድነው በሥጋ ልደት ወልደ ማርያም የኾነውን ኢየሱስን፥ ክርስቶስ እና ወልደ እግዚአብሔር መኾኑን ማመን ነው። ይህን ወደ ማወቅ የሚደረሰው ግን ከላይ እንዳየነው ሰማያዊው አባት ሲገልጥ ብቻ ነው። ኢየሱስን ወልደ ማርያም ለማለት ግን ምንም መገለጥ አያስፈልግም። አይሁድም ያለምንም መገለጥ በዐጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ያዩትን ኢየሱስን በትስብእቱ ዐውቀዉታል። ትንቢት የተነገረለትን፥ ሱባኤ የተቈጠረለትን፥ በተስፋ የሚጠብቁትንና በአእምሯቸው የነበረውን መሲሕ እና የእግዚአብሔር ልጅ (ማቴ. 26፥63፤ ማር. 14፥61) በሥጋ ከተገለጠው ኢየሱስ ጋር ማገናኘት ግን አልቻሉም። የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን ዋና ትግል የነበረው በአይሁድ ዘንድ የነበረውን ይህን ክፍተት ለመሙላት ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እና የእግዚአብሔር ልጅ መኾኑን መመስከር ነበር።

ሐዋርያት ባፍም በመጣፍም ስለ ኢየሱስ ይሰጡ የነበረው ምስክርነት፥ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እና የእግዚአብሔር ልጅ መኾኑን የሚገልጥ ነበር (ማቴ. 1፥16፤ 27፥17፡22፤ ሐ.ሥ. 5፥42፤ 9፥20፤ 17፥3፤ 18፥5፡28፤ ዮሐ. 20፥31)። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነታቸውን የገለጡት አንዳንድ ሰዎች፥ ኢየሱስን “ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነኽ” በማለት አምነዉበታል (ዮሐ. 1፥50፤ 6፥69፤ 11፥27፤ ሐ.ሥ. 8፥37)። በእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ እንደምናስተውለው የሐዋርያት ትልቁ ትኵረት፥ አይሁድ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እና የእግዚአብሔር ልጅ መኾኑን እንዲያምኑ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ ወንጌሉን የጻፈበት ዋና ዐላማም ሌላ ሳይኾን ወንጌሉን የሚያነቡ ኹሉ፥ “ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ” እና “የእግዚአብሔር ልጅ” እንደ ሆነ ያምኑና አምነውም በስሙ ሕይወት ይሆንላቸው ዘንድ ነው፤ የአስተርእዮው ግብ ይኸው ነውና።

ከላይ የተጠቀሱት ምስክሮች ኢየሱስን “ክርስቶስ” እና “የእግዚአብሔር ልጅ” (ወልደ እግዚአብሔር) ከማለት በቀር የማርያም ልጅ (ወልደ ማርያም) ነው ሳይሉ ያለፉት፥ በስሕተት ወይም ሰው መኾኑንና ከእርሷ በሥጋ መወለዱን በመካድ አይደለም፤ አስተርእዮው ኢየሱስን ወልደ ማርያም ከማለት ክርስቶስ እና ወልደ እግዚአብሔር ወደ ማለት ስላደረሳቸው ነው እንጂ።

የሊቃውንቱ ሐተታ

የተዋሕዶ ሊቃውንት ስለ ኢየሱስ ማንነት መጽሐፍ ቅዱስ ከሚሰጠው ምስክርነት በመነሣት ጥልቅ የኾነ ነገረ መለኮታዊ ሐተታ ያቀርባሉ። ቃል ሥጋ ከመኾኑ አስቀድሞ ከዘላለም ወልደ አብ (የአብ ልጅ) መኾኑን፥ “የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ” ቃል ሥጋ ኾኖ ከቅድስት ማርያም በመወለድ ወልደ ማርያም መኾኑንና፥ በሰውነቱም መንፈስ ቅዱስን ከአብ በመቀባት መሲሕና የእግዚአብሔር የበኵር ልጅ መባሉን ያብራራሉ። በዚህም፥ ልደት በኹለት ወገን፥ ማለትም የባሕርይ ልደትና የግብር ልደት እንደ ኾነ ይገልጣሉ። የባሕርይ ልደት፥ የባሕርይ አባትን የባሕርይ እናትን መስሎ ተካክሎ የሚወለዱት ልደት ሲኾን፥ በዚህ ልደት ከአባት ከእናት መብለጥም ኾነ ማነስ የለም።

እግዚአብሔር ወልድ በአምላክነቱ የአብ የባሕርይ ልጅ ሲኾን፥ በሰውነቱ ደግሞ የማርያም የባሕርይ ልጅ፥ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው፥ ወልድ ዋሕድ ነው። “ተወላዲው (ወልድ) አንድ አካል ቢሆንም፥ መወለጃው ባሕርይ ኹለት ነው። ያባቱ ከናቱ ልዩ ስለ ኾነ፥ ለአብ ወልድ ዘበአማን (አማናዊ) በሚባልበት በአባቱ ባሕርይ ለማርያም ወልድ ዘበአማን አይባልም፤ ጌታዋ ፈጣሪዋ ነው እንጂ። እንደዚሁ ደግሞ ለማርያም ወልድ ዘበአማን በሚባልበት በናቱ ባሕርይ ለአብ ወልድ ዘበአማን አይባልም፤ ዘበጸጋ (በጸጋ የሆነ) እንጂ። ለዚህም ትስብእት በመንፈስ ቅዱስ በመቀባት ያገኘውን የጸጋ ልጅነት በሚያመለክቱ ስሞች መጠራቱን አብነት አድርገው ያቀርባሉ፤ በኵሩ ዘላዕለ ኵሉ ተግባሩ (በሥራው ኹሉ ላይ በኵሩ)፥ መሲሑ፥ ሊቀ ካህናቲሁ (ሊቀ ካህናቱ)፥ ገብሩ (አገልጋዩ)፥ ቍልዔሁ (ብላቴናው)፥ ሐዋርያው ማለት ነው።

ይህም የሚያሳየው የግብር ልደት ለባሕርይ ልደት ምሳሌ እንጂ ዘበአማንነት (አማናዊነት) እንደሌለው ነው። ምሳሌ ከአማናዊ እንደሚያንስ፥ እንደማይተካከል የግብር ልደትም ከባሕርይ ልደት በስም (ልደት በመባል) ብቻ ይተካከዋል። በግብር ልደት መወለድ የሚቻለው፥ “ትንሹም በታላቁ እንዲባረክ ክርክር የሌለበት ነገር ነው” (ዕብ. 7፥7) እንደ ተባለው፥ “በወግ፥ በማዕርግ፥ በብዕል (በሀብት) በሥልጣን፥ በዕድሜ፥ በዘመን ከሚበልጠውና ከሚቀድመው ተባርኮ ተሹሞ፥ ሀብተ ወልድና (የልጅነት ሀብት) ስመ ወልድና (የልጅነት ስም) ተቀብሎ መውለዱና መወለዱ ሳይኖር በዚሁ በውሂቡና በነሢኡ (በመስጠቱና በመቀበሉ) ብቻ አባትና ልጅ መባባል ነው” ሲሉ ያክላሉ። ሐተታውን በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ ሲያስደግፉትም፥

  • እግዚአብሔር በነቢዩ በናታን በኩል ስለ ሰሎሞን የተናገረውንና፥ “እኔም አባት እኾነዋለሁ፥ እርሱም ልጅ ይኾነኛል” ያለውን (2ሳሙ. 7፥14)
  • ዳዊትም፥ “እርሱ፥ አባቴ አንተ ነኽ፥ … ይላል። እኔም ደግሞ በኵሬ አደርገዋለኹ” ያለውን (መዝ. 89፥26፡27)
  • መልአኩ ገብርኤል ድንግል ማርያምን ሲያበሥራት፥ “… ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል” ያላትን ይጠቅሳሉ (ሉቃ. 1፥35)።

በእነዚህ ምስክርነቶች ውስጥ እንደምናነበው አባትነትና ልጅነት (አባት መኾንና ልጅ መኾን) የተገኙት በመስጠትና በመቀበል ነው እንጂ ባሕርያዊ በኾነ መንገድ በመውለድና በመወለድ አይደለም።

የተዋሕዶ ሊቃውንት እነዚህን የቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነቶች መሠረት አድርገው፥ ሊቃውንት የመሰከሩትንም አንድ ላይ ሰብስበው እንደሚከተለው ይጠቅሳሉ፤ “ወንሰምዮ ወልደ፤ ናሁ ኮነ ለነ ወልደ በሀብት። ወተሠርዐ ወልደ እግዚአብሔር በኀይል ቅብዐ መንፈስ ቅዱስ። ወተወልደ ውእቱ ቀዳማየ እመንፈስ ቅዱስ ከመ ጸጋሁ ትዕዱ ላዕሌነ። እመሰ ኰሰይነ ልደቶ እንተ ከማነ በመኑ ተመሲለነ ንከውን ውሉደ እግዚአብሔር – ልጅ እንለዋለን፤ እነሆ ለእኛ በጸጋ ልጅ ኾኖልናል። በቅብዐ መንፈስ ቅዱስ በኀይል የእግዚአብሔር ልጅ ተባለ። ጸጋው ወደ እኛ ትሸጋገር ዘንድ እርሱ ከመንፈስ ቅዱስ የመጀመሪያ ልጅ ኾኖ ተወለደ፤ [ይህን] እንደኛ የኾነበትን ልደቱን ከካድነው በየትኛው ልደት መስለነው የእግዚአብሔር ልጆች እንባላለን?” ብለዋል። እውነት ነው፤ ኢየሱስንና እኛን ወንድማማቾች ያደረገን ልደት፥ ወልድ እም ቅድመ ዓለም ከአብ የተወለደበት ልደት አይደለም፤ ድኅረ ዓለም ከቅድስት ማርያም የተወለደበት የሥጋ ልደትም አይደለም፤ እርሱ በኵር እኛ ደግሞ ተከታዮች ወንድሞች የኾንበት በመንፈስ ቅዱስ በመቀባት የተከናወነው የግብር ልደት ነው እንጂ (ሮሜ 8፥29፤ ዕብ. 2፥13)።

ይህ ሐተታ ባዶ ፍልስፍና ሳይኾን መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ያደረገ ነው። ሊቃውንቱ ይህን የግብር ልደት ይበልጥ ለማስረዳትም፥ ስለ ወልድ በብሉይ ኪዳን የተነገሩትን ትንቢቶች በሐዲስ ኪዳን መፈጸማቸው ከተጻፉባቸው ክፍሎች ጋር በማዛመድ ያትታሉ። በተለይም ከዘላለም የአብ የባሕርይ ልጅ የኾነው ወልድ፥ ሰው ከኾነ በኋላ መንፈስ ቅዱስን በአብ ተቀብቶ የእግዚአብሔር ልጅ መባሉን ለማስረዳት የሚጠቅሱት፥ “እግዚአብሔር ይቤለኒ ወልድየ አንተ ወአነ ዮም ወለድኩከ – እግዚአብሔር አለኝ፤ አንተ ልጄ ነኽ፤ እኔም ዛሬ ወለድኹኽ” የሚለውን ትንቢታዊ መዝሙር ነው (መዝ. 2፥7)። በዚህ መዝሙር ውስጥ፥ “አንተ ልጄ ነኽ” የሚለው ከዘላለም የአብ ልጅ መኾኑን ሲያመለክት፥ “እኔ ዛሬ ወለድኹኽ” የሚለው ደግሞ ሰው ከኾነ በኋላ፥ በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ መባሉን ያስረዳል ይላሉ። በእነዚህ ኹለት ዐረፍታተ ነገር ውስጥ “አንተ ልጄ ነኽ” ያለውም፥ “እኔ ዛሬ ወለድኹኽ” ያለውም ባለቤት (Subject) እግዚአብሔር ብቻ ነው።

ይኹን እንጂ ይህን ባለማስተዋል አንዳንዶች በብሉይ ኪዳን የተነገረውን ይህን ቃል፥ የመጀመሪያው (“አንተ ልጄ ነኽ” የሚለው) ቀዳማዊ ልደቱን፥ ኹለተኛው (“እኔ ዛሬ ወለድኹኽ” የሚለው) ደግሞ ደኃራዊ ልደቱን ያሳያል ይላሉ፤ አክለውም በሐዲስ ኪዳን “ልጁን ላከ (ፈነወ ወልዶ)” ተብሎ የተነገረው ስለ ቀዳማዊ ልደቱ፥ “ከሴት ተወለደ (ወተወልደ እም ብእሲት)” ተብሎ ደግሞ ስለ ደኃራዊ ልደቱ ተነግሯል ብለው ኹለቱን ለማነጻጸር ይሞክራሉ (አባ ጎርጎርዮስ 1974፣ 70)። እነዚህን በብሉይና በሐዲስ ኪዳን የተነገሩ ኹለት መልእክቶች ተነጻጻሪ ማድረግ ግን ትልቅ ችግር አለበት። በተለይ “አንተ ልጄ ነኽ፤ እኔ ዛሬ ወለድኹኽ” በሚሉት በኹለቱም ዐረፍታተ ነገር ውስጥ፥ “ልጄ ነኽ” እና “ወለድኹኽ” ያለው እግዚአብሔር ብቻ ስለ ኾነ፥ የኹለተኛውን ዐረፍተ ነገር ባለቤት ቅድስት ማርያምን ማድረግ ይመስላልና እንዲህ ከታሰበ ትልቅ ነገረ መለኮታዊ ችግር ውስጥ ይከታል። የዐረፍተ ነገሩ ባለቤት እግዚአብሔር መኾኑን አለማወቅም ይኾናል። ከዚህ ይልቅ ከቅድስት ማርያም በሥጋ የተወለደውን ኢየሱስን እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስና በኀይል በመቀባቱ መሲሕና ወልደ እግዚአብሔር መባሉን የሚያመለከት ከመኾን አያልፍም።

ሊቃውንቱ የግብር ልደትን ትንቢቱን ከተናገረው ከዳዊት ጋር በማነጻጸር ያትታሉ። “እግዚአብሔር አለኝ፤ አንተ ልጄ ነኽ፤ እኔም ዛሬ ወለድኹኽ” የሚለው በዳዊት ሲተረጐም፥ “አንተ ልጄ ነኽ” የሚለው በእስራኤላዊነቱ ዳዊት ለእግዚአብሔር የበኵር ልጅ መኾኑን ያሳያል (ዘፀ. 4፥23)፤ “እኔ ዛሬ ወለድኹኽ” የሚለው ደግሞ በሳሙኤል እጅ ለንግሥና የተቀባበትን ቀን (1ነገ. 17፥13) ያመለክታል። አክለውም ወልድን በተመለከተ፥ “እኔ ዛሬ ወለድኹኽ” የሚለው የሚያሳየው ዕለተ ፅንስን ነው፤ ሥግው ቃል በዳዊት ባሕርይ የተቀባው ሰው በኾነ ጊዜ ነውና ይላሉ።

ከቤተ ክርስቲያን አበው አንዱ ቄርሎስም በእስትጉቡእ፥ “ይህም ወንጌል በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ተወለደ እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኀይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ ነው፤ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።’ (ሮሜ 1፥3፡4) የሚለውን ቃል ሲተረጕም፥ ‘ጳውሎስም ክርስቶስ አንድ መኾኑን ሊያሳየን ሲፈልግ፥ ስለ ልጁ ከዳዊት ዘር በሥጋ ተወለደ፤ በኀይል በቅብዐ መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ተባለ’ ብሎ ካነበበ በኋላ፥ ትርጓሜውን ‘ከዳዊት ዘር የተወለደው እንዴት አምላክ እንደ ኾነ ንገረኝ? እም ቅድመ ዓለም ያለውና ከእግዚአብሔር አብ ጋር ለዘላለም የሚኖረው ወልድ በምን መንገድ የእግዚአብሔር ልጅ ተባለ? ስለ ራሱ አንተ ልጄ ነኽ፤ እኔ ዛሬ ወለድኹኽ ይላልና። ‘ዛሬ’ ማለት ያለፈ ዘመን አይደለም፤ ያለ ዘመን ነው ብሎታል።’ የትርጓሜውም ስልት፥ ምክንያቱና አፈታቱ ይህ ነው። ንስጥሮስ ቃል ሥጋ ኾነ የሚለውን ነቅፎ ቃል በሰው ዐደረ እንጂ ሰው አልኾነም፤ ሰው ኹኖ አልተቀባም ስላለ፥ ሥጋ በሥጋ መጣ አይባልምና ቃል ሥጋ ካልኾነ ከዳዊት ዘር የተወለደው እንደ ምን ‘ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው’ (ሮሜ 9፥5) ተባለ? ዓለም ሳይፈጠር ከአብ ጋራ የነበረውና ለዘላለም የሚኖረውስ ወልድ በሰውነቱ ካልተቀባ በምን ምክንያት ዳግመኛ የግዜር ልጅ ተባለ? ምላሽ እንዳለኽ ንገረኝ፤ እንደሌለኽ ግን ርሱ ባለቤቱ ስለ ራሱ በዳዊት ዐድሮ እግዜር ልጄ አንተ ነኽ፤ ዛሬም ወለድኹኽ አለኝ ብሏልና፤ ስለዚህ ነው። ‘ከግዜር ወዲያ ፈጣሪ ከባለቤቱ ወዲያ መስካሪ’” እንዲሉ ከእርሱ በላይ ስለ እርሱ ማን ሊመሰከር ይችላል?

ይህ የመዝሙር ክፍል በሐዲስ ኪዳን በክርስቶስ ተፈጽሞ እናነባለን (ሐ.ሥ. 13፥33፤ ዕብ. 1፥5፤ 5፥5)። በሐዋርያት ሥራ የተጠቀሰው ከትንሣኤ ክርስቶስ ጋር ታያይዞ ነው የቀረበው፤ “ይህን ተስፋ እግዚአብሔር በኹለተኛው መዝሙር ደግሞ፥ አንተ ልጄ ነኽ፤ እኔ ዛሬ ወለድኹኽ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ኢየሱስን አስነሥቶ ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞአልና።” (13፥33)። እንደ ሊቃውንተ ተዋሕዶ ሐተታ፥ “የግብር ልደት የሚፈጸመው ኋላ በትንሣኤ ነው። እስከዚያ የልደት መያዣ ወይም ዐረቦን ይባላል፤ ውጥን፥ ጅምር፥ ወይም ፅንስ ሽል እንደ ማለት ነው (ሮሜ 6፥3-9፤ 2ቆሮ. 1፥22፤ 5፥5)።” የሐዋርያት ሥራን መሠረት በማድረግ በሃይማኖተ አበው መጽሐፍ ላይ፥ “ወውእቱ ቅድመ ዘተወልደ እሙታን – እርሱ ከሙታን አስቀድሞ የተወለደ ነው” ተብሎ ተጽፏል። ይኹን እንጂ የዐረቦኑና የትንሣኤው ልደት፥ “እኔ ዛሬ ወለድኹኽ” በሚለው የታሰረ አንድ ነው እንጂ ኹለት አይደለም፤ ዐረቦን እንደ ፅንስ፥ ትንሣኤ ደግሞ እንደ ልደት ነውና ይላሉ።

በዕብራውያን ክፍል የተጠቀሱት ደግሞ ከንጉሥነቱና ከሊቀ ካህናትነቱ ጋር ተያይዘዋል። በምዕራፍ አንድ ውስጥ የተጠቀሰው ስለ ንጉሥነቱ እንደ ተነገረ በዐውዱ ውስጥ ይታያል (ዕብ. 1፥5፡6፡8)። “እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ ሊቀ ካህናት ሊሆን ራሱን አላከበረም፤ ነገር ግን፥ አንተ ልጄ ነኽ፤ እኔ ዛሬ ወልጄኻለኹ ያለው እርሱ ነው፤” የሚለውም ከሊቀ ካህናትነቱ ጋር ተያይዟል (ዕብ. 5፥5)።

ኢየሱስ፥ የሳሌም ንጉሥና የልዑል እግዚአብሔር ካህን በኾነው በመልከ ጼዴቅ አምሳል (ዕብ. 7፥1) ንጉሥም ሊቀ ካህናትም ኾኗል። ነገር ግን ክህነታቸውና መንግሥታቸው ኀላፊና ሥጋዊ እንደ ነበረው የብሉይ ኪዳን ካህናትና ነገሥት የሚያልፍ ግዙፍ ቅባት አልተቀባም። “ክህነቱም መንግሥቱም መንፈሳዊና ዘለዓለማዊ ስለ ኾነ በማያልፍና በማይጠፋ በረቂቁ ዘይት በመንፈስ ቅዱስ ቅብነት ተሹሟል (ኢሳ. 11፥1-2፤ 42፥1፤ 61፥1፤ ሐ.ሥ. 10፥38)። ሲሾምም ካባቱ ጋራ አንድ የሚኾንበት ሥልጣንና ችሎት እያለው፥ ይቻለኛልና በገዛ እጄ ልሾም አላለም፤ አባቱ ቀብቶ ሾመው እንጂ” (ሐ.ሥ. 4፥27፤ ዕብ. 5፥4-6፤ ሉቃ. 1፥32)። ከዚህ የተነሣ መሲሕ፥ በኵር፥ ኹለተኛው አዳም፥ ክርስቶስ፥ ቀዳሜ ጸጋ (ጸጋን በመቀበል የመጀመሪያ) ወዘተ. በሚሉ ስሞች ተጠርቷል። እኛንም በመሲሕነቱ መሲሓውያን፥ በቅቡዕነቱ ቅቡዓን፥ በወልደ እግዚአብሔርነቱ ውሉደ እግዚአብሔር፥ በክርስቶስነቱ ክርስቲያን አሰኝቶናል።

በዚህ የግብር ልደት ክርስቶስ በኵር በእርሱ ሥራ ያመንን እኛ ደግሞ ተከታይ ወንድሞቹ ኾነናል። “አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችኹ እንጂ እንደ ገና ለፍርሀት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችኹምና። የእግዚአብሔር ልጆች መኾናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ልጆች ከኾንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፤ ዐብረንም ደግሞ እንድንከበር ዐብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር ዐብረን ወራሾች ነን። … ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይኾን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤” (ሮሜ 8፥15-17፡29)።

ቄርሎስም፥ “ወረሰየነ ዕሩያነ ምስሌሁ በመንፈስ ቅዱስ። – በመንፈስ ቅዱስ ከእርሱ ጋር የተካከልን አደረገን።” ሲል፥ ዮሐንስ አፈወርቅ ደግሞ፥ “ስምኽን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለኹ አለ፤ ይህም እርሱን ይተካከሉት ዘንድ ለእነርሱ የሰጣቸውን ክብርና ታላቅነት ይገልጥ ዘንድ ነው፤ እርሱ ራስ፥ እኛ ብልቶች፥ በመውረስም ከእርሱ ጋር አንድ ነን።” ብሏል (ዕብ. 2፥13) (ይህም በግእዝ “መዋርስት” ይባላል፤ ተወራራሾች ዐብረው የሚወርሱ ማለት ነው)።

ከዚህ በመነሣት ሊቃውንቱ ክርስቶስ በሰውነቱ በአብ መንፈስ ቅዱስን ተቀብቶ መሲሕና የእግዚአብሔር ልጅ የተባለበት ልደት፥ ከግብርና ከጸጋ ወንድሞቹ ከምእመናን ጋር ነው የሚያስተካክለው እንጂ ከወላጁ፥ ከሿሚውና ከአውራሹ ጋር አያስተካክለውም ይላሉ (ሮሜ 8፥17)። ስለዚህ ነው፥ “እኔ እኼዳለኹ፤ ወደ እናንተም እመጣለኹ እንዳልኋችኹ ሰማችኹ። የምትወዱኝስ ብትኾኑ ከእኔ አብ ይበልጣልና ወደ አብ በመኼዴ ደስ ባላችኹ ነበር።” (ዮሐ. 14፥28) ያለው ሲሉ ሊቃውንቱ ያብራራሉ። በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት አንዳንድ ክፍሎች ውስጥ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ አንሶ የሚታይባቸው የአንዳንድ ምንባባት ፍቺ በግብር ልደቱ አንጻር የሚፈታ ይኾናል። እርሱ በግብር ልደት ከምእመናን ጋር የሚተካከል አንጋፋ ወንድም (በኵር) ነው የተባለው፥ ምንም የእርሱ ልደት በምርት፥ የእኛ ደግሞ በቅንጣት ቢመሰልም መቀበል ስለሚያስተካክለን ነው፤ “ʻዝኆንም ለሆዱ፥ ድንቢጥም ለሆዱ ኹሉም ወንዝ ወረዱʼ እንዲሉ” ይላሉ ሊቃውንቱ።

መድረሻ

የወልድ መገለጥ በሚዘከርበት በዘመነ አስተርእዮ ልናስተውለው የሚገባ ትልቁ ነገር፥ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስና የእግዚአብሔር ልጅ መኾኑን ነው። ኢየሱስን በዚህ ማንነቱ ካላስተዋልነው፥ እርሱን መገለጥ በማያስፈልገው በሰውነቱ ብቻ ዐወቅነው እንጂ እግዚአብሔር በገለጠው መንገድ አላስተዋልነውም ማለት ነው። የዚህ ጽሑፍ ዋና መልእክትም ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መኾኑን ማሳወቅና ሰዎች ኹሉ በእርሱ አምነው እንዲድኑበት ማስረዳት ነው። የተዋሕዶ ሊቃውንት ምስጢረ ሥጋዌን ያብራሩበት የሐተታቸው ዋና ዐላማም በሥጋ የተገለጠው ወልድ፥ ክርስቶስ እና የእግዚአብሔር ልጅ የኾነበትን መንገድ ማብራራትና በእርሱ መገለጥ ለእኛ የተሰጠውን የልጅነት ክብርና በኵራችን ከኾነው ከእርሱ ጋር ዐብረን የምንወርስ ወራሾች መኾናችንን ማስገንዘብ ነው። በሚከተሉት ጥቅሶች የጽሑፉን መልእክት እናጠቃል፤

  • “ክርስቶስ አይደለም ብሎ ኢየሱስን ከሚክድ በቀር ውሸተኛው ማን ነው? አብንና ወልድን የሚክድ ይህ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው።” (1ዮሐ. 2፥22)
  • “ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በሚታመን ሁሉ እግዚአብሔር በእርሱ ይኖራል፤ እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል።” (1ዮሐ. 4፥15)።
  • “ክርስቶስ ነው ብሎ በኢየሱስ የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዶአል፥ ወላጁንም የሚወድ ሁሉ ከእርሱ የተወለደውን ደግሞ ይወዳል።” (1ዮሐ. 5፥1)።

ዋቢ መጻሕፍት

ሔኖክ ወልደ ሚካኤል (መጋቤ አእላፍ) (2001) ዝክረ ቃል ዘውእቱ መጽሐፈ ዚቅ ወመዝሙር። ዐዲስ አበባ፣ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት።

ኪዳነ ወልድ ክፍሌ (1948) መጽሐፈ ሰዋስው ወግሥ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ። ዐዲስ አበባ፣ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት።

(1986) “ሃይማኖተ አበው ቀደምት ወፍልጠተ ውሉድ ደኀርት”። ስቱትጋርት።

ዐሥራት ገብረ ማርያም (1994) ትምህርተ መለኮት። ዐዲስ አበባ፣ ማተሚያ ቤቱ ያልተጠቀሰ።

ጥዑመ ልሳን ካሳ (ሊቀ ካህናት) (1981) ያሬድና ዜማው። ዐዲስ አበባ፣ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት።

[1] ዕዝል ከግእዝና አራራይ ጋር የሚቈጠር የዜማ ስም ሲኾን፥ እዚህ ላይ የተጠቀሰው “ዕዝል” ግን በዕዝል ዜማ የሚያዜሙት መዝሙር ነው (ኪዳነ ወልድ 1948፣ 290)።

[2] በዚህ ንኡስ ርእስ ሥር የቀረበው ጽሑፍ የተመሠረተው “ሃይማኖተ አበው ቀደምት” የተሰኘው መጽሐፍ ስለ ምስጢረ ሥጋዌ በሰጠው ትንታኔ ላይ ነው። በዚህ ጕዳይ ላይ “ተዋሕዶ” እኔ ነኝ የሚሉት ሌሎቹም ቡድኖች ልዩ ልዩ አገላለጥና ሐተታ እንዳላቸው ይታወቃል።

Yimrhane Kirstos

“ታሪካዊ” የተባለው የኅብረቱ ውሳኔ እና የተሰጠው ምላሽ

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ጠቅላላ ጉባኤ፣ ከመጋቢት 21-22፣ 2009 ዓ.ም. ድረስ ባካሄደው 32ኛ መደበኛ ስብሰባው፣ በአስተምህሮ ዝንፈት፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባልሆኑ ልምምዶች እና በሞራል ውድቀት ላይ እጅግ ጠንካራ ነው የተባለለት የአቋም መግለጫ አወጣ፡፡ መግለጫው የወጣው በተጠቀሱት ጕዳዮች ላይ ኅብረቱ ያዘጋጀው ጥናት ለጠቅላላ ጉባኤው ከቀረበና ውይይት ከተካሄደበት በኋላ እንደ ሆነም ተነግሯል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

ለምን ተወለደ?

የጌታችንን ልደት በምናስብበት በዚህ ሰሞን፣ “ተወለደ” የሚለው ቃል የተሸከመው ነገረ መለኮታዊ ጭብጥ እጅግ የገዘፈና ፋይዳው ያየለ መሆኑን ሳምሶን ጥላሁን እንደሚከተለው ያብራራል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.