[the_ad_group id=”107″]

ባህላዊ እምነቶች ያጠሉበት የአፍሪካ ክርስትና

ቤተ ክርስቲያን ከ2000 ዓመታት በላይ ባስቈጠረው ዕድሜ ዘመኗ፣ በተለያዩ ባህሎች እና ወጎች ውስጥ አልፋም እንኳ ቢሆን ታላቁን የክርስቶስን የማዳን መልእክት ይዛ ስለ መቀጠሏ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ ይህ ሲባል ግን በዘመናቱ መካከል ከዚህ መሠረታዊ መልእክት የተለየ ያስተላለፈችባቸው ጊዜያት የሉም ማለት አይደለም፡፡ ዛሬም እንኳ ስሑት የሆነ መልእክት የምታስተላልፍበት አጋጣሚ እንዳለ እናስተውላለን፡፡ (“ስሑት” የምንልበት ሚዛናችን መጽሐፍ ቅዱሳዊው ክርስትና መሆኑን እዚህ ላይ ጠቊሞ ማለፉ ተገቢ ይሆናል፡፡) ይህ ታላቁ መልእክት በንጽሕናው እንዳይተላለፍ እንቅፋት እየገጠማቸው ካሉ ሕዝቦች መካከል ደግሞ አፍሪካውያኑ ይገኙበታል፡፡

በአፍሪካ ምድር ላይ ያለቸው ቤተ ክርስቲያን ምን መልክ አላት? ቤተ ክርስቲያን አፍሪካዊ የሆኑ ባህሎችን፣ ወጐችን እና ዕሴቶችን እንዴት አቻችላ ይዛ ነው የቀጠለችው? “ትክክለኛ አይደሉም” የሚባሉትን እንከኖች ነቅሳ የምታወጣበት ጥበቡንስ አግኝታው ይሆን? ለእነዚህንና ለመሳሰሉት ሁሉ ጥያቄዎች በዚህ መጣጥፍ ሙሉ ምላሽ መስጠት ባይቻልም፣ ለውይይት መነሻ የሚሆን ዐሳብ ለመፈንጠቅ ተሞክሯል፡፡

“ባህላዊው እምነት” ስንል

የአፍሪካ አገራት የየራሳቸው የሆነ ባህል፣ ወግ፣ ሥርዐት እና አመለካከት ቢኖራቸውም በተመሳሳይ መልኩ የሚያመሳስላቸው መልክ ደግሞ አላቸው፡፡ ከሚያመሳስላቸው ነገሮች (factors) አንዱ ሃይማኖት ነው፡፡ በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ በርካታ ሃይማኖቶች ነበሩ፤ ዛሬም አሉ፡፡ ታሪክም ሆነ የአፍሪካ ሥነ መለኮት አዋቂዎች እንደሚስማሙበት፣ በዓለም ላይ ታላላቅ ከሚባሉት ሃይማኖች መካከል ክርስትና እና እስልምና “መጤ” ሃይማኖቶች ሲባሉ፣ የባህል ሃይማኖት (African Traditional Religion) ከአህጉሪቱ መነሻ ጋር አብሮ የኖረ እንደ ሆነ ይነገራል፡፡ ይህ “የባህል እምነት” ተብሎ የሚታወቀው የአፍሪካን ሕዝብ ባህልና አኗኗር በጥልቀት የያዘ ከመሆኑም ባሻገር፣ በክርስትና እና በእስልምና እምነት ላይ በአሉታዊ መልኩም ሆነ በአዎንታዊ ጎኑ ተጽእኖ አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል፡፡

የባህል እምነት በክርስትና ላይ እያደረገ ያለውን ተጽእኖ ከመመልከት በፊት፣ “የአፍሪካ ባህላዊ እምነት” ሲባል ምን ማለት እንደ ሆነ፣ መገለጫዎቹም ምን እንደሚመስሉ በወፍ በረር መቃኘቱ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ የአፍሪካ የባህል እምነት በራሱ የቆመ ሃይማኖት ይሁን እንጂ፣ ወጥ የሆነ አሠራር እና ሥርዐት ያለው እምነት አይደለም፡፡ ብዙ የአፍሪካ ተመራማሪዎች እንደሚስማሙት፣ የአፍሪካ የባህል እምነት እንደ አንድ ሃይማኖት አንድን አምላክ (deity) የሚከተል ሳይሆን፣ የሕይወት ወይም የአኗኗር ዘይቤ ንጽረተ ዓለም ነው፡፡ ቦላጀ ኢደው “የአፍሪካ ባህላዊ ሃይማኖት” በሚለው መጽሐፋቸው በዚህ ጕዳይ ላይ ሰፊ ትንታኔ ይሰጣሉ፡፡

በአፍሪካ የባህል እምነት ውስጥ አራት መሠረታዊ ጕዳዮች አሉ፡፡ እነዚህም፡- አምላክ፣ መናፍስት፣ ሕያዋን እና ግዑዛን አካላት የሚባሉ ናቸው፡፡ በአፍሪካዊው ባህላዊ እምነት “አምላክ” የፍጥረት ሁሉ ጀማሪና አጽኝ (Sustenance) ነው፡፡ ለአምላክ የሚሰጡ ስያሜዎችም ባሕርያቱን የሚገልጹ ናቸው፤ “ጠቢቡ” (The wise one)፣ “ሁሉን ዐዋቂ” (who knows or sees all)፣ “ፈራጅ”፣ ወዘተ.፡፡ መናፍስት” (Animism) በምድር ላይ ካሉ ሰዎች በላይ የሆኑ አካላት ሲሆኑ፣ ከብዙ ዓመታት በፊት የሞቱ ሰዎች መንፈስን (Ancestral spirit) ያጠቃልላል፡፡ “ሕያዋን የሆኑ” (ሕይወት ያላቸው) የሚባሉት ሰዎችን፣ እንስሳትን እና ዕፅዋትን የሚጨምር ነው፡፡ እነዚህም የመኖርን ትርጕምና የሕይወትን ምሳሌ ያመለክታሉ፡፡ በአፍሪካ የባህል ሃይማኖት ውስጥ ስፍራ ከሚሰጣቸው ዕሳቤዎች መካከል አራተኛው “ግዑዛን” አካላት ሲሆኑ፣ እነዚህም በእምነቱ ውስጥ ዋጋ ያላቸው ቁሳቁሶችን ጨምሮ፣ ተፈጥሯዊ ክስተቶችን ሁሉ ያካትታሉ፡፡

በባህላዊ እምነት ውስጥ ቅዱስ (sacred) የሚባሉ መጻሕፍት ወይም በጽሑፍ የተደራጁ መመሪያዎች የሉም፡፡ ይሁን እንጂ በቃል ሲተላለፉ የኖሩ አባባሎች፣ ታሪኮች እና የተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዐቶች እምነቱን ያስቀጥላሉ፡፡ በአፍሪካ የባህል እምነት ውስጥ አምላክ የማይደረስበት ሩቅ (transcendent) ሲሆን፣ ወዲሁ ደግሞ ለፍጥረቱ ቅርብ (immanent) እንደ ሆነ ግንዛቤ አለ፡፡

ሥርዐተ አ ምልኮው

በባህላዊው እምነት አምላክን ለማምለክ የሚደረጉ የተለያዩ ክንዋኔዎች ወይም ሥርዐቶች አሉ፡፡ እነዚህ ክንዋኔዎች መልከ ብዙ ቢሆኑም፣ በሁሉም ዘንድ የሚያመሳስላቸው የአምልኮ ሥርዐቾች ደግሞ አሏቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል የመጀመሪያው፣ መሥዋዕት እና ምጽዋት የማቅረብ የአምልኮ ሥርዐት ነው፡፡ ይህ ሥርዐት በተለያዩ ጎሣዎች አቀራረቡና ዐይነቱ ይለያያል፡፡ ለምሳሌ፣ በቀድሞ ዘመን በናይጄሪያ ባለው የዩርባ ጎሣ አምላኪዎች ዘንድ የተለየ በረከት ለማግኘት ሲሉ የሰው ልጅን መሥዋዕት አድርጎ የማቅርብ ልማድ ነበር፡፡ በዚህ ዘመን ይህ ልማድ እጅግ እየቀነሰ የመጣ ቢሆንም፣ መሉ ለሙሉ ስለ መጥፋቱ ርግጠኛ መሆን እንደማይቻል ይነገራል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያለው ሌላኛው የአምልኮ ሥርዐት የስጦታ ምጽዋት (Gift Offerings) የሚባለው ሲሆን፣ ይህም በአብዛኛው ምግብ እና መጠጥ በማቅረብ የሚከናወን ነው፡፡ የስጦታ ምጽዋት ሰዎች ስኬት ሲገጥማቸው ወይም አካላዊ ጤንነት ሲያገኙ ወይም ልጆች ሲወልዱ፣ ወዘተ. የሚያቀርቡት ነው፡፡ በሌላ መልኩ ክፉ ነገር ሲያጋጥም፣ ዕድል ሲጠምና ክፋት ሲበዛ “አምላክ ተቆጥቶ ነው” በሚል የሚቀርቡ ስጦታዎች ደግም አሉ፡፡

ጸሎት ወይም ልመና የአፍሪካ ባህላዊ እምነቶች የሚመሳሰሉበት ሌላኛው አምልኳዊ ሥርዐት ነው፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ሰዎች በጠዋት፣ ማንንም ከማናገራቸው በፊት “የተቀደሰ” ወደ ተባለው ሥፍራ ሂደው ይጸልያሉ፡፡ ይህ ጸሎት ለቁሳዊ በረከት፣ በጠላት ላይ ድልን ለማግኘት ወይም ረዠም ዕድሜ ለመኖር የሚደረግ ነው፡፡ ይህ ዐይነቱ ጸሎት በሁሉም የአፍሪካ የባህል እምነት አራማጆች ዘንድ የሚደረግ ሥርዐት እንደ ሆነ ይታመናል፡፡

በአፍሪካ ኅብረተ ሰብ የባህል እምነት ተከታዮች ዘንድ ሌላኛው የአምልኮ መገለጫ ተደርጎ የሚወሰደው አምላካዊ ስምን ከልጆች ስም ጋር አብሮ የማካተት አምልኳዊ ልማድ ነው፡፡ የተወለደው/ችው ሕፃን የጸሎት መልስ እንደ ሆነ ብቻ ሳይሆን፣ የተለየ መሆኑን ለማሳየት ጭምር የሕፃኑ/ኗ ስም ከአምላክ ስም ጋር እንዲያያዝ ይደረጋል፡፡ ይህም ምስጋና የማቅረቢያ መንገድ ተደርጎ ነው የሚወሰደው፡፡ እዚህ ላይ ሳይነሣ የማይታለፈው ሌላኛው የባህል አምልኮ መገለጫ፣ ሙዚቃ እና ዳንስ በአምልኮ ጊዜ ያለው ሥፍራ ነው፡፡ ይህ የሙዚቃ እና የዳንስ ሥርዐት በአብዛኞቹ የባህል እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚተገበር መሆኑ ይታመናል፡፡

በአፍሪካ የባህል እምነት መለወጥ (conversion) የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ያን ያህል የሚሰተዋል አይደለም፡፡ አንድ ሰው በተወለደበት ጎሣ የሚያደርገውንና የሚታመነውን መከተል የተለመደ ብቻ ሳይሆን ከጎሣው ተወላጅ የሚጠበቅ ነው፡፡ በመሆኑም፣ ሃይማኖት የግል ሳይሆን የጋራ ሆኖ በሁሉ ዘንድ ይታመናል፤ ሥርዐቱም በደቦ ይፈጸማል፡፡

በአፍሪካ የባህል እምነት መሠረት ማንም ሰው “አምላክን” በቀጥታ ቀርቦ ሊያናግረው አይችልም፡፡ ሥርዐቱን ለማድረግ የግድ መካከለኛ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ለማስፈጸም ደግሞ “ነቢይ”፣ “ጠቢብ ሰው”፣ “አዋቂ”፣ “ፈዋሽ” (medicine man)፣ “ዝናብ አዝናቢ”፣ ወዘተ. የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ሰዎች የግድ ያስፈልጋሉ፡፡ የእነዚህ ሰዎች ዋና ተግባር የመንፈሳዊም ሆነ ማኅበራዊ ምሪትን የሚሰጡ፣ የሚያማክሩ፣ ከመለኮት የሚቀበሉትን መልእክት ለአማኒያን የሚያስተላልፉ ናቸው፡፡ “አምላክ” እነዚህን ሰዎች በሕልም፣ በራእይም ሆነ በሌላ መንገድ ይገናኛቸዋል፡፡ እነዚህ “መካከለኛ” ናቸው የሚባሉ ሰዎች የመናፍስቱን ዓለም ማናገር የሚችሉና በአብዛኛው በመንፈሱ ቁጥጥር ሥር የሆኑ ናቸው፡፡ በአጭሩ የአማልክቱና የመናፍስቱ አፍ ሆነው ያገለግላሉ ማለት ነው፡፡

ከላይ እንደ ተጠቀሰው፣ በአፍሪካ ባህላዊ እምነት ውስጥ ግዑዛን አካላት ጉልሕ ሥፍራ አላቸው፡፡ እነዚህ ግዑዛን አካላት ሥርዐተ አምልኮው የሚፈጸምባቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ “አምላክ” ላደረገው ሥራ እንደ ምልክት የሚቈጠሩ ናቸው፡፡ በዚህም “አምላክ” ከአማኞች ጋር አብሮ እንዳለ አስረጅ ሆነው ይታያሉ፡፡ በርግጥ “የአምላክ” አብሮነት የሚገለጠው እንዲሁ በማመን ብቻ ሳይሆን ምልክቶችን በማድረግ ነው፡፡ ለዚህም ነው በአማኒያን ዘንድ ምልክቶች እና ድንቆች እጅግ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጣቸው፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለአምልኮ ሥርዐቱ ተብለው የሚለዩ ቦታዎች አሉ፡፡ በአብዛኛው ተራራና ኮረብታማ ሥፍራዎች በአፍሪካ የባህል እምነት “የተቀደሱ” (scared places) ተብለው የሚለዩ ናቸው፡፡ ዛፎች፣ ወንዞችና ፋፋቴዎች በተመሳሳይ ልዩ ቦታ የሚሰጣቸው ግዑዛን አካላት ናቸው፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ፣ የተለያዩ ቅርፃ ቅርፆች እና የእጅ ሥራ ውጤቶች አማኞች አብረዋቸው እንዲኖሩ የሚያደርጓቸው ቁሶች ናቸው፡፡ በአንገት ላይ በማሰር፣ በቤት ወይም በሥራ ቦታ የመሚቀመጡት ቁሶች ለገድ፣ ለስኬት፣ ለጤና፣ ክፉ መናፍስትን ለማራቅ፣ ወዘተ. በሚል አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው፡፡        

የባህል እምነቱ በክርስትናው ላይ ያሳደረው ተጽእኖ

በደምሳሳው ያየነው እንደ ሆነ የአፍሪካ የባህል እምነት በአፍሪካ ማኅበረ ሰብ ላይ ያሳረፈው ከፍተኛ ተጽእኖ መኖሩ እሙን ነው፡፡ በማኅበረ ሰቡ ውስጥ ሥር ሰድዶ ያለው ይህን መሰሉ ሃይማኖታዊ መስተጋብር፣ አፍሪካውያን ስለ እምነት በሚኖራቸው ንጽረት ላይ የሚያሳርፈው አሻራ በጉልሕ እንዲታይ ያደርገዋል፡፡ ቀደም ሲል እንደ ተጠቀሰው፣ መለወጥ (conversion) የሚለው ዕሳቤ እጅጉን ደብዛዛ መሆኑ (ምናልባትም ጭራሹኑ አለመኖሩ) ለአህጉሪቱ “መጤ ነው” ለሚባለው ክርስትና ብርቱ ፈተና እንደሚሆንበት መገመት አይከብድም፡፡ ምንም እንኳን አፍሪካውያን ወደ ኦርቶዶክስ ወይም ካቶሊክ ወይም ፕሮቴስታንት ክርስትና ቢመጡም፣ የመለወጥ ሂደቱ ግን ቀላል አይሆንም፡፡

በተለይ የፕሮቴስታንት ክርስትና ወደ አፍሪካ ከመጣበት ጊዜ አንሥቶ በተለያዩ ሂደቶች ውስጥ አልፎአል፡፡ ሚሲዮናውያን የክርስትናን እምነት ወደ አፍሪካ ይዘው የመጡበት መንገድ በራሱ አነጋጋሪ እንደ ሆነ ታሪክ ይዘክራል፡፡ ይልቁንም ደግሞ የአውሮጳ “የወንጌል ሰባኪዎች” የቅኝ ገዦች መሣሪያ የሆኑባቸው የታሪክ አጋጣሚዎች በአፍሪካውያኑ ላይ የማይሻር ጠባሳ ጥሎ አልፏል፡፡ ይህንን ተከትሎም በርካታ አፍሪካውያን የነገረ መለኮት ልኂቃን፣ በተለይ ከቅኝ ግዛት ነጻ መውጣት በኋላ፣ “አጸፋዊ ክርስትና” ማበጀት ጀመሩ፡፡ “ምእራባዊ ነው” ላሉት ክርስትናም አቻ እኩያ የሆነ፣ ባህል ተኮር ወይም አገር በቀል ክርስትና ሊያዳብሩም ቻሉ፡፡ ዛሬ ይህንን አመለካከት የሚደግፉ “የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያናት” ተከታዮች ቁጥር ከመቶ ሚሊዮን በላይ እንደ ሆነ የሚታመን ሲሆን፣ Independent church የሚል የወል መጠሪያ ይዘዋል፡፡ “ራስ አገዝ” ተብለው የሚጠሩት እነዚሁ አፍሪካዊ ቤተ እምነቶች የባህል ዐውዳዊነትን ለመጠበቅ በሚል ትልቅ ውሳኔን የጠየቀ፣ ነገር ግን ቅይጣዊነትን (syncretism) ያስከተለ ርምጃ ተራምደዋል፡፡

ይህ በመሆኑም ልክ በባህላዊው እምነት ውስጥ እንዳለው ሁሉ፣ “አዋቂ” ማለትም የመናፍስቱን ዓለም የሚያውቅ፣ “ፈዋሽ”፣ እና የመሳሰሉ ስያሜ የተሰጣቸው ሰዎች በአንዳንድ ቤተ እምነቶች መታየት ጀመሩ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ የእግዚአብሔርን አብሮነት ለማወቅ፣ ለነገሮች ስኬት፣ ልጅ ለመውለድ እንዲሁም ለተለያዩ ጉዳዮች የሚሆኑ ቁሶች፣ ለምሳሌ “የተጸለየበት ውሃ”፣ “ቁራጨ ጨርቅ”፣ “ሳሙና”፣ “ዘይት”፣ ወዘተ. በቤተ ክርስቲያን ትልቅ ትኩረት የሚሰጣቸው ማስፈጸሚያዎች ሆኑ፡፡

ከላይ እንደ ተገለጸው የአፍሪካ የባህል እምነት የሥርዐተ አምልኮ ማጠንጠኛ ዕሳቤ፣ ሕይወት በዚህ ምድር አሁንና ዛሬ ነው፡፡ ከሞት በኋላ ሕይወት እንዳለ ቢታመንም፣ እሱም ቢሆን የሚታየው በቁሳዊና በአካላዊ ጉዳዮች በኩል ነው፡፡ የነፍስ መዳን፣ ከአምላክ ጋር ኅብረት ማድረግ፣ የባሕርይ ለውጥና የጽድቅ ሕይወት የመሳሰሉት ክርስቲያናዊ ዕሴቶች እንግዳ የሚሆኑባቸው “ቤተ ክርስቲያናት” አሉ፡፡ ስለዚህም ቀላሉ መፍትሔ መካከለኛ የተባሉትን ሰዎች አብዝቶ መከተል፣ “የመንፈሳዊ ዓለም አፍ ናቸው” በማለት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገለጹት የጸጋ ሥጦታዎች ጋር በማደባለቅ እነርሱን መስማትና መከተል “የክርስትናው ማእከል” ይሆናል፡፡

መውጫ

የክርስትና እምነት ወደ አፍሪካ ይዘው ከመጡት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ብቃት ያላቸው ሰባኪያንና አስተማሪዎች ሳይሆኑ ለወንጌል መስፋፋት ቀናዒ ልብ የነበራቸውና በተለያየ የሙያ መስክ የተሰማሩ ሚሲዮናውያን ነበሩ፡፡ ይህ በመሆኑ፣ ክርስትናው ሲገባም ሆነ ከገባ በኋላ የማኅበረ ሰቡን ዐውድ መጠበቅና ማክበር አልቻለም። እምነቱን ያመጡት ሰዎች፣ የራሳቸውን ባህል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ከሆነው መርሕ ነጥሎ መለየት የተሳናቸው በመሆኑ ቆይቶም ቢሆን የባህል ጦርነት እንዲፈጠር ማድረጉ አልቀረም፡፡ “እኔ ያልኳችሁን ብቻ ተቀበሉ፤ እኔ አውቅላችኋለሁ” ዐይነት አስተሳሰብ በሚሲዮናውያኑ ዘንድ ይቀነቀን የነበረ መሆኑ፣ በኋላ በአሉታዊ መልኩ ለተነሣው “አጸፋዊ ክርስትና” መነሻ ሰበብ መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ ይሁን እንጂ፣ ኢትዮጵያዊቷ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነውን መርሕ ለክርስትና ርምጃዋ የሙጥኝ ብትል ለዐውዳዊነት ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት አይከልካትም፡፡

ይህን ማንነቴን ምን ልበለው?

ባንቱ ገብረ ማርያም በዚህ ዐጭር ጽሑፋቸው፣ የሕይወታቸውን ዙሪያ ገባ ይቃኛሉ፤ ቃኝተውም አንድ መለያ ብቻ የሌለው ማንነት የተጎናጸፉ መሆኑን ይገነዘባሉ። አንድ ጥያቄ ግን ማንሣታቸው አልቀረም፤ “ይህን ማንነቴን ምን ልበለው?” የሚል።

ተጨማሪ ያንብቡ

እኛ ከእግዚአብሔር ጋር የንግድ ስምምነት የለንም

መጋቢ ጻድቁ አብዶ፣ በኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን ግንባር ቀደም ከሚባሉት አገልጋዮች መካከል የሚጠቀሱና ቤተ ክርስቲያኒቱን ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ ናቸው፡፡ ለስምንት ዓመታትም የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን ዋና ጸሐፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በትምህርት ዝግጅታቸውም፣ ከኢስት አፍሪካ ስኩል ኦፍ ቲዮሎጂ (East Africa School of Theology) በነገረ መለኮት ጥናት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን፣ በድኅረ ምረቃ መርሓ ግብር በሥልታዊ ነገረ መለኮት ጥናት (MTh in Systmatic Theology) በኢትዮጵያ የሥነ መለኮት ድኅረ ምረቃ ት/ቤት (EGST) ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል ሥነ መለኮት ሴሚናሪየም ፕሪንሲፓል ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ሚክያስ በላይ ከጴንጤቆስጤ አስተምህሮና ልምምድ ጋር በተያያዘ ከሚነሡ የስሕተት ትምህርቶች አኳያ እንዲሁም በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ለብዙዎች መነጋገሪያ ስለሆኑት “ሜጀር ሼፐርድ ፕሮፌት” ቡሽሪ አነጋግሯቸዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

“ስለ ዘፈን” የሚለው የዘሪቱ ጽሑፍ

“ስለ ዘፈን” የተሰኘው የዘሪቱ ከበደ ጽሑፍ በሕንጸት ድረ ገጽ ላይ መነበቡን ተከትሎ፣ የተለያዩ ዐሳቦች ሲንሸራሸሩ ሰንብተዋል። ዘሪቱ ያነሣቻቸውን ሙግቶች በመደገፍም ሆነ በመቃወም ዐሳባቸውን በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ላይ ካቀረቡት መካከል፣ ተስፋዬ ሮበሌ (ዶ/ር) አንዱ ናቸው። ዶ/ር ተስፋዬ በአራት ክፍል አዘጋጅተው በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ያስነበቡትን ጽሑፍ፣ በሕንጸት ድረ ገጽ ላይ እንዲነበብ በጠየቁት መሠረት የላኩልንን ጽሑፍ እንደሚከተለው አቀርበነዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.