[the_ad_group id=”107″]

እኵያ ወይም ደባል የሌለው ኦርቶዶክሳዊ ወንጌል

የወንጌላውያን እምነት ሚሲዮናዊ ማዕከል የነበረው የምዕራቡ ዓለም፣ አሁን የደረሰበት የድኅረ ክርስትና የአመራር፣ መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ቀውሶች ዘገምተኛ የቍልቍሎሽ መንገድ ጅማሬ፣ ክርስቶስንና ሥራውን ጠርዝ ላይ ባሰቀመጠ ጊዜ ነበር። ቢያንስ በስኮትላንድ የዛሬ መቶ ዐሥራ ሁለት ዓመት የነበረውን ወርቃማ ዓለም ዐቀፋዊ የወንጌል አጀንዳ መነሻ ካዳረግን (The 1910 World Missionary Conference, Edinburgh, 14-23 June 1910)፣ የእኛን የወቅቱን ሁሉን ዐቃፊ የአስተምህሮና አመራር ቀውስ ስመለከት በፈጣን ሩጫ የገባንበት ይመስለኛል።

የቤተ ክርስቲያን መልእክት የተሰቀለው፣ የሞተው፣ የተነሣው፣ አሁን በአብ ዘንድ የተቀመጠውና በክብር ዳግመኛ የሚመለሰው ክርስቶስ ብቻ ነው (1ቆሮ 1፥23)። እርሱ የበላይ፣ እኵያ፣ አናሳ ወይም ተፎካካሪ አምላክ የለውም። የስብከታችን ተኣማኒነትና የጽድቅ ተጽእኖ ዐቅም መሠረቱ ያረፈው፣ ለእግዚአብሔር ቃል የመጨረሻና የበላይ ባለሥልጣንነት ባለን መሠጠትና ታማኝ ባለ ዐደራነት ላይ ነው። አማኙ ማኅበረ ሰብ፣ ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የተጠራ፣ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን ከሆነ (1ጴጥ 2፥9)፣ ይህን መሠረታዊ እምነት ከሚያፋልስ የትኛውም ንጽረተ ዓለም፣ አስተምህሮ፣ ሃይማኖትና ርዕዮተ ዓለም ጋር የማይታረቅ ልይነት አለው።

ቃል ሥጋ ሆነ! በርግጥ አምላክ እንደ እኛ ሆነ። የሰውን ሁለተና፣ በሥጋ ብቻ ሳይሆን በጊዜ፣ በቦታ፣ በቋናቋና በባሕል ሰው ሆኗል። ቋንቋና ባሕል የለሽ (culture-less) ክርስትና የለም። በዐጭሩ፣ ክርስቲያናዊ መስተጋብሮች ከቋንቋና ባሕል ጋር ሊለያዩ አይችሉም። ክርስቶስም በደሙ የዋጀንና የእግዚአብሔር መንግሥትና ካህናት ያደረገን “ከነገድ ሁሉ፣ ከቋንቋ ሁሉ፣ ከወገን ሁሉ፣ ከሕዝብ ሁሉ” ነው። የእርሱ ቤዛዊ የመስቀል ሥራ በኀጢአት የተለወሰውን የሰውን ሁለንተና ዋጅቷል። ይህም ባሕላችንን ያካተተ ነው። በርግጥ በክርስቶስ ብቸኛ የማዳን ሥራ ከተዋጀን፣ ከወንጌል እውነት ጋር ከሚጣረሱ ፋይዳዎች ጋር ቀጥታ የሆነ የማይታረቅ ግጭት አለን።

ስለዚህ የክርስቶስ ብቸኛ ቤዛዊ ሥራ ዋጅቶናል ስንል፣ ከኀጢአትና ባዕድ አምልኮ ጋር ትሥሥር ካለው ከየትኛው ባሕል ጭምር ማለታችን ነው። ባሕል ስንል፣ የማኅበራዊ ስብስባችን የጋራ ፋይዳ ነው። ይህም እምነታችንን፣ ዕሴቶቻችን፣ ቋንቋችንን፣ ርእዮተ ዓለማችንን፣ ሙዚቃ፣ ምግብ፣ ጋብቻ፣ የወንድ፣ የሴት የልጆች እንዲሁም ቤተ ሰባዊ ድርሻና ኀላፊነቶች በሙሉ ያጠቃለለ ማንነት ነው። ክርስቶስ በእነዚህ ፋይዳዎች ላይ ደባል ሆኖ አይደለም ያዳነን! ይልቁንም፣ የእርሱ ሕዝብ ያደረገን እነዚህን ማንነቶች ሁሉ በመለወጥ፣ በእርሱ ውስጥ በተገኘው ማንነት ለክብሩ እንድንኖርለት ነው። በአንድ ጊዜ ለክርስቶስም ከወንጌል ጋር ተቃርኖ ላለውም ባሕል መኖር አንችልም!

በዚህ አግባብነት ኢሬቻ ባሕል ብቻ ሳይሆን ሃይማኖትም ነው። በየትኛውም መልኩ (ቢያንስ እንደ ወንጌላውያን አማኞች) ኅሊናችን ላይ ጫና ሳናደርግ፣ ሁለቱን መለያያት አንችልም። ይኸው እውነት በኢሬቻ ብቻ ላይ ሳይሆን፣ በሲዳማው ፍቼ ጨምበላላ፣ በወላይታው ጊፋታ፣ በሀዲያው ያሆዴ እንዲሁም በሌሎች ባሕላዊ በዓላት ላይ ባሉት ዕይታዎች ላይም አግባብነት አለው። ከሰብአዊ መብት አንጻር፣ ሌላውን በዐመፅ እስካላሰገደደ ድረስ፣ ማንኛውም ግለ ሰብ ወይም ሕዝብ ያሻውን እምነትና ባሕል የመከተል ነጻ ፈቃድና መብት አለው። ሆኖም ሁለት የአተያይ ተፋልሶዎች አሉ። አንደኛው ሰፋ ባለ መልኩ ሲታይ፣ ባሕላዊ በዓላት ፈጽሞውኑ ሃይማኖታዊ ገጽታ የላቸውም የሚለው ሙግት ነው። ሁለተኛው ደግሞ ጠበብ ባለ መልኩ ሲታይ፣ እነዚህ ባሕላዊ በዓላት ከወንጌል እውነት ጋር ምንም ዐይነት ተቃርኖ የላቸውም የሚለው ልዝብ ክርስቲያናዊ ፋይዳ ነው።

ሦስት ጠረዝ ላይ የቈሙና ኀላፊነት የጎደላቸው ምልከታዎች አሉ፦ አንደኛው፤ የትርክት እስረኛ በመሆንና ባሕላዊ በዓላትን ፖለቲካዊ ልብስ በማልበስ፣ አገራችን ያለችበትን የክፍፍል ውጥረት የበለጠ የሚያከርር ዕይታ ነው። ይህም፣ መውጣት ባቃተን የአግላይነትና የጥላቻ ዑደት ውስጥ የበለጠ ይዘፍቀናል። ይህን ለትውልድ ልናወርስ አይገባም!

ሁለተኛው፤ በዓላትን ከባሕል አንጻር ብቻ በማየት ክርስቲያናዊ ካባ የሚያለብስ አመለካክት ነው። ሦስተኛው፤ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የታቀፉና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌላቸው ትውፊቶችን በመንተራስ፣ ባሕላዊ በዓላት ክርስቲያናዊ ቅቡልነት እንዲያገኙ የሚደረግ ሙግት ነው። በበሰለ አመክንዮአዊ ውይይት ልዩነቶችን ያለ ጥላቻና መከፋፈል በልብ ስፋት መቀበል ሲቻል፣ አንዳንድ ጠርዝ ለቀቅ ዕይታዎች ቤተ ክርስቲያኒቷን እስከ ማንጓጠጥ መድረሳቸው አሳፋሪና አሳሳቢ ነው።

የእኔ ትኵረት ሁለተኛው ምልከታ ላይ ያለ ነው። ምክንያቱም ይህ አመለካከት፣ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን የወንጌል አደባባዮች የምዕራቡን ዓለም ክርስትና ሕይወት ለነሳው ብዝኀተ ሃይማኖተኝነት (religious pluralism) አሳልፎ ስለሚሰጥ ነው። ብዝኀተ ሃይማኖተኝነት፣ የክርስትናንን መሠረታዊ ዕሴቶች በማደብዘዝና በሃይማኖቶቸ መካከል ያለውን ልዩነት አንጻራዊ በማድረግ፣ ሁሉንም “የአንድ እውነት” የተለያዩ ገጽታዎች በማድረግ ይሟገታል።

በዚህ ዕይታ ውስጥ፣ እውነትን አንጻራዊ እንዲሁም ሰውን መካከለኛ ያደረገው ዓለማዊ (secular humanism) የድኅረ ሥልጣኔ ነጽረት ዓለም ይነጸባረቃል። እንዳስተዋልኩት፣ ይህ አመለካከት ክርስትና ከባሕልና ሌሎች ሃይማኖቶች ጋር ሊኖረው የሚገባውን ጤናማና ሚዛናዊ የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊና ነገረ መለኮታዊ ዕይታ እያደበዘዘ ይገኛል።

በኢማኑኤል ካንት የፍልስፍና ተጽዕኖ ሥር የወደቀው እና የወንጌል እምነቱን በለዘብተኛ ነገረ መለኮት አስተምህሮ (liberal theology) የተካው፣ ኬምብሪጅን ጨምሮ በተለያዩ ከፍተኛ ተቋማት በማስተማሩ በስፋት የሚታወቀው ጆን ሂክ፣ “ሁሉም ሃይማኖቶች የአንዱ መለኮታዊ እውነት ልዮ ልዩ የሆኑ አቻ መልኮች ናቸው” በማለት የዘራው ክፉ ዘር፣ የምዕራቡን ዓለም የወንጌል እምነት ለመሸርሽር ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።[2] ሂክ፣ “በሃይማኖቱ ዓለም ውስጥ፣ ክርስቶስ ወደ አንዱ አምላክ ከሚያመላክቱ የመገለጥ ከዋክብት መካከል አንዱ ኮከብ እንጂ፣ በራሱ ብቸኛና ፍጹም ብርሃን አይደለም” በማለት ከሞገተ በኋላ፣ ክርስቶስን መካከለኛና ብቸኛ አዳኝ አድርጐ መስበክ፣ “ሃይማኖታዊ ኢምፔሪያሊዝም ነው” በማለት ደምድሟል።[3]

የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል አሁን ለደረሰበት የራስ ውድቀት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገው፣ የወንጌልን ንጽሕና ያጠለሸ ልቅ ኢኪዩሚዝም (ecumenism) እንደ ሆነ ታሪክ ያስገነዝበናል። የካውንስሉ ሁሉን ዐቃፊነት (ሃይማኖት፣ ባሕልና ፓለቲካ) መርሕ መሠረት ያደረገው፣ “ዶክትሪን ይለያያል ፍቅር አንድ ያደርጋል” የሚለው ተቃርኗዊ አመለካከት ነው። የዚህ ዐይነቱ ኢኪዩሚዝም መንፈስ ምድራችን ላይ ሰንኮፉን ለመጣል እያኮበከበ መሆኑን ልብ ልንል ይገባል። በክርስትናና በሌሎች ሃይማኖች መካከል ያሉትን የማይታረቁ ልዩነቶች አንጻራዊ በማድረግ ሁሉን ያገበሰበሰው ኢ-ሥላሴያዊ ዓለም ዐቀፋዊነት (Unitarian Universalism) እምነት ተረኛ ይሆናል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግሥት የዓለም አብያተ ክርስቲያናንት ካውንስል በአምስተርዳም ሲመሠረት፣ አሁን የደረሰበት መንፈሳዊ ቀውስ ላይ እደረሳለሁ ብሎ አልነበረም።

ወንድሞችና እኅቶች፣ የወንጌል እውነት ሲቀየጥ መንፈስ ቅዱስ ይሸሸናል፤ ልብ እንበል! ይህን የምለው ከብዙ አክብሮትና ትሕትና ጋር ነው። የክርስቶስ ወንጌል ከደባል ጋር የማያኖረውና ሊፋቅ የማይችል ድንበር አለው። የክርስትና መልእክት ዋጋ ያስከፍላል! ለትውልዱ ምን ይሆን እያስተላለፍን ያለነው?

ሐዋርያው ጳውሎስም፣ በክርስቶስ ልጁ ለነበረው ወጣቱ ጢሞቲዎስ ዐደራ ሲለው (1ጢሞ 6፥20)፣ በእጁ ያለውን ወንጌል፣ እግዚአብሔር ለእኔ በዐደራ ከሰጠኝ የክብር ወንጌል (1 ጢሞ 1፥11)፣ በማለት፣ ወንጌል ተጀምሮ እስከሚያልቅ ድረስ ለቤተ ክርስቲያን በዐደራ የተሰጠ የእግዚአብሔር መልእክት መሆኑን በጥብቅ በማሳሰብ ነበር።

“ጳውሎስ፣ የክርስቶስ ኢየሱስ ባሪያ፣ ሐዋርያ ሊሆን የተጠራና ለእግዚአብሔር ወንጌል የተለየ፤ ስለዚህ ወንጌል በነቢያቱ በኩል በቅዱሳት መጻሕፍት አስቀድሞ ተስፋ ተሰጠ። ወንጌሉም ስለ ልጁ፣ በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ሆነ፣ በቅድስና መንፈስ ደግሞ ከሙታን በመነሣቱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ በኀይል ስለ ተገለጠው ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በእርሱ በኩል ስለ ስሙ ከአሕዛብ ሁሉ መካከል ሰዎችን በእምነት አማካይነት ወደሚገኘው መታዘዝ ለመጥራት ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን።” (ሮሜ 1፥1-5)

በመቀጠልም፣ በሕይወቱ ማብቂያ ዋዜማ ላይ ጳውሎስ በአራት ምስክሮች ፊት መጋቢ ጢሞቴዎስን ስለ ወንጌል ባለ ዐደራነት በጥብቅ ያሳስበዋል፦ በእግዚአብሔር ፊት እንዲሁም በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ ባለው በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት መገለጡንና መንግሥቱን በማሰብ ይህን ዐደራ እልሃለሁ፦ 1) ቃሉን ስበክ፤ 2) ጊዜው ቢመችም ባይመችም ዝግጁ ሁን፤ 3) በታላቅ ትዕግሥትና በማስተማር አቅና፤ 4) ገሥጽ፤ 5) አበረታታም።

ጌታ ሆይ፤ በደምህ ዋጋ በመክፈል፣ እንዲሁም ታሪክ ቅዱሳን በነፍሳቸው ተወራርደው ያስረከቡንን የአንተን ወንጌል ዐደራ ጠባቂ፣ ታማኝ አስተላላፊም አድርገን። አሜን!


[1] “ኦርቶዶክስ” የሚለው ቃል አግባብነት፣ የማከብራትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ለማመልከት አይደለም። ከሥርወ ቃላት ትንተና (etymology) አንጻር፣ የቃሉን መሠረታዊ ፍቺ ለማሳየት የዋለ ነው። “ኦርቶዶክስ” (ὀρθόδοξος)፣ መንታ ቃል ነው፤ አንደኛው፤ “ኦርቶስ (ὀρθός)” ቀጥተኛ፣ ትክክል፣ ያልተበረዘ የሚሉ ዐሳቦችን የያዘ ሲሆን፣ ሁለተኛው፤ “ዶክሳ (δόξα)”፣ አስተምህሮና አመለካከትን የሚገልጽ ነው። በዚህ መሠረት “ኦርቶዶክስ” ስንል፣ “ቀጥተኛ፣ ትክክል፣ ያልዘመመ” መሠረት ላይ ያረፈ እምነት ማለታችን ነው።

[2] John Hick. An Interpretation of Religion: Human Response to the Transcendent, Basingstoke: Macmillan, 1989, 301

[3] John Hick. Philosophy of Religion [Englewood: Prentice – Hall, 1983] 107ff

ለክቡር ጥሪ የሚመጥን ክቡር ሕይወት

አንዳንዶች ሰዎች በሕይወታቸው ትርጉም ላለው፣ ብሎም ዓላማቸው ላደረጉት ጉዳይ እስከ ሞት ሊደርስ በሚችል መከራ ውስጥ ያልፋሉ፡፡ ማዕበሉ የሚንጥና የሚያንገላታ ቢሆንም፣ የሕይወት ምስቅልቅሎሹ ቢበረታም ዓላማቸውን ግን የሙጥኝ ይላሉ፡፡ በእውነቱ እንደነዚህ ዐይነት ሰዎች ተፈትነው ያልተረቱና የማይናወጥ ጠንካራ ሰብዕናን የተላበሱ ናቸው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

ዘመነ አስተርእዮ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዓመቱን በወቅቶች ከፋፍላ፥ በዚያ ላይ የተመሠረቱ መዝሙሮችን በግእዝ ለእግዚአብሔር በማቅረብና ድንቅ ሥራውን በመዘከር ትታወቃለች። ለዚህም በስድስተኛው ምእት ዓመት የተነሣው የዜማ ደራሲ ቅዱስ ያሬድ ከብሉያትና ከሐዲሳት (ከመጽሐፍ ቅዱስ)፣ ከሊቃውንትና ከመሳሰሉት መጻሕፍት ለምስጋናና ለጸሎት የሚስማሙ ንባባትን በመውሰድና ለዜማ ተስማሚ በማድረግ፥ በአራቱ ክፍላተ ዘመን እንዲነገሩ ማዘጋጀቱን የዜማ ሊቃውንት ያስረዳሉ (ጥዑመ ልሳን /ሊቀ ካህናት/ 1981፣ 28)። አራቱ ክፍላተ ዘመን የተባሉትም በዓመት ውስጥ የሚገኙት አራቱ ወቅቶች ናቸው፤ እነርሱም መፀው (ወርኀ ጽጌ ዘመነ ጽጌ/አበባ)፣ ሐጋይ (በጋ)፣ ጸደይ (በልግ) እና ክረምት ሲኾኑ፣ አኹን የምንገኘው ከአራቱ ክፍላተ ዘመን ኹለተኛው ክፍል በኾነው በበጋ (ሐጋይ) ላይ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ

8 comments

Your email address will not be published. Required fields are marked *

  • ጌታ ይባርክህ ወንድማችን ዶ/ር ግርማ፡፡ ይህ ጉዳይ በጣም አሳሳብ ስለሆነ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ተገብ የሆነ አቋም በመውሰድ ካልሰራችበት የምዕራባዊያኑ አብያተ ክርስቲያናት አይነት ዕጣ ፋንታ ልገጥመን ይችላል፡፡ አማኙ በክርስቶስ ኢየሱስ ያገኘውን የእግዚአብሔርን ልጅነት ከምድራዊ ማንነት አሳንሶ ወይም አቻ አድርገው የሚመለከትበት ዘመን ላይ ነው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ያለችው፡፡

  • ይሄን ለዐይን የማይከብድ ጽሑፍ ሰፍ ብዬ ነበር ማንበብ የጀመርኩት። የተነሳው ርእሰ ጒዳይ ወቅታዊና አንገብጋቢ ከመሆኑ አንፃር ጠለቅ ያሉ ሃሳቦች ይኖሩበታል ብዬ ጠብቄ ነበር። በጽሑፉ ብዙም አልረካሁም። ጸሐፊው የወንጌልን ትምህርት በአግባቡና ቀጥተኛ በሆነ መልኩ በማንሳቱ እያመሰገንኩ፣ ጽሑፉን ሳነብ አልተነሱም ብዬ ያሰብኳቸውን እንዲሁም ጥያቄ የፈጠሩብኝን ነገሮች እንዲህ አቀርባለሁ፦
    1. ጸሐፊው ልምን የደቡቡን ብቻ አነሳ? ልምን የሰሜኑንስ አላነሳም? ለምሳሌ የቡሄ በዓል። ይሄን በዓል ወንጌላውያን ያከብሩታል (በቤተክርስትያን ውስጥ ባይሆንም በግለሰብ ደረጃ ግን ያከብሩታል)። መስቀልስ ቢሆን? በደቡብም በሰሜንም ይከበራል። ወንጌላውያን በአንድም በሌላም ያከብሩታል። የደቡቡን አጽንኦት ሰጥቶ ያነሳበት ምክንያት በተወሰነ ደረጃ ቢገባኝም ምናልባት ጸሐፊው ካደገበት ባሕል ውጭ ስለሆነ ይሆንን (ያደገበትን ባሕል ባላውቅም) ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል (fear of the unknown).
    2. ሌላው የማነሳው ጥያቄ እና ጸሐፊው በደንብ ጠልቆ ሄዶበት ቢሆን ኖሮ ያልኩት ለምንድነው እነኝህ የተጠቀሱት በኣላት (ኢሬቻ፣ ጊፋታ፣ ፊቼ ጨምበላላ፣ ወዘተ) ከወንጌል አስተምህሮ ጋር የማይሄዱት? ምናቸው ነው ከኦርቶዶክሳዊው የክርስትና ትምህርት ጋር የሚጋጨው?
    3. መዋጀት የሚለው ቃል ብዙ ነገር ውስጡ ያለብት (loaded) ቢሆንም ለምንድነው ባህሎችን የማንዋጀው? ኢሬቻ የምስጋና በኣል ከሆነ ለምንድነው ወንጌላውያን አማኞች እውነተኛውን ፈጣሪ፣ ዘመንን የሚቀይረውን ጌታን የማያመልኩበት? አንድ ክርስትያን አማኝ ባሕሉን ወድያ ማለት አለበት ወይ? ባሕል አልባ መሆን ይቻላል ወይ? ለምሳሌ እንቁጣጣሽ (የኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ) እግዚአብሔርን እያመሰገንን እናከብረዋለን። ወደኋላ ብንሄድ ምናልባት አረማዊ (pagan) የሆነ መንሻ ሊኖረው ይችላል። የገናን በኣልን ብንወስድ አንዳንዶች መነሻው አረማዊ ነበር ይላሉ፤ አንዳንዶች እንደውም ጌታ ታኅሳስ ውስጥ አልነበረም የተወለደው ይሉናል። ግን አሁን ሁላችን የምናከብረው በኣል ሆኖአል። ይሄ ወደ መጀመርያው ነጥቤ እንድሄድ ያደርገኛል። እነኝህን የደቡብ በኣላት ጸሐፊው ለይቶ የጠቀሰው ምናልባት እሱ ካደገበት ባሕል ውጭ ሆኖበት ከሆነስ?

    ተስፋዬ ጸሐፊው ጽሑፉን የተሻለ አፍታቶ ጽፎት ጽሑፉ ያለውን እምቅ ኃይል (potential) ያወጣዋል፣ ብዥታዬንም ያጠራል ነው።

    • Dear Dr, l’m have been following and blessed with your articles. But l also need explanations regarding the three points raised by bro #Teddy in the above comment. Thanks!

  • It is commendable that somebody discussed a subject that really needs to be addressed. There is no doubt the author intended to write more, but I suspect most readers won’t read a lengthy one. The reason it’s so short and concise is because of that.

    Brother Teddy raised some issues above or below in the comments that I agree with. Perhaps the author will have the chance in the future to elaborate on the points raised.

    Finally, “በመቀጠልም፣ በሕይወቱ ማብቂያ ዋዜማ ላይ ጳውሎስ በአራት ምስክሮች ፊት መጋቢ ጢሞቴዎስን ስለ ወንጌል ባለ ዐደራነት በጥብቅ ያሳስበዋል፦ በእግዚአብሔር ፊት እንዲሁም በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ ባለው በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት መገለጡንና መንግሥቱን በማሰብ ይህን ዐደራ እልሃለሁ፦ 1) ቃሉን ስበክ፤ 2) ጊዜው ቢመችም ባይመችም ዝግጁ ሁን፤ 3) በታላቅ ትዕግሥትና በማስተማር አቅና፤ 4) ገሥጽ፤ 5) አበረታታም።” , let’s try to be that.

    Thank you, Dr Girma

  • ኢሬቻ፣ ፍቼ ጨምበላላ፣ ጊፋታ፣ ያሆዴ፣ ወዘተ፣ “ከሰብአዊ መብት አንጻር፣ ሌላውን በዐመፅ እስካላስገደደ ድረስ፣ ማንኛውም ግለ ሰብ ወይም ሕዝብ ያሻውን እምነትና ባሕል የመከተል ነጻ ፈቃድና መብት አለው” ያልከው ትክክል ነው። ችግሩ፣ ባንድ እጅ መብት ብለን የሰጠነውን፣ ስላልተስማማን፣ በሌላኛው ለመውሰድ መሞከራችን ነው። እየተባባሰ የመጣው፣ ፖለቲከኞችና ወንጌል አማንያን ተቻኩለን በማውገዛችን ነው። የሚገርመው፣ በ “ባእዳን” ባህሎች ላይ የምናሰማውን ውግዘት በምሑር ኢ-አማንያን፣ በጎሣ ፌዴራሊዝም አራማጆች ላይ አለማሰማታችን ነው።

    በመቻኮል ያባባስናቸው አያሌ አገራዊ ሰብአዊ ጒዳዮች ደግሞ አሉ። ለምሳሌ፣ ፊደልን ትተን ለምን በቊቤ አልን። ያንንም ኢትዮጵያዊ ከመሆን ጋር አገናኘን። ውጤቱ? ዜግነትን ጥያቄ ውስጥ አስገባን፤ ብዙዎችን አስቆጥተን አሸሸን፤ ብዙዎች ያላሰቡትን እንዲያስቡ ገፋፋን። ፖለቲከኞች ያሰቡትን አሳካን። ኢሬቻ የሸዋ ኦሮሞ በዓል ነው፤ ዛሬ አልተጀመረም። ኢሬቻ እንደ ማንኛውም የኃይማኖት ሥርዓት ከወንጌል ጋር የማይጣጣም ገጽታ የለውም ማለት አይደለም። በክርስትናም እንኳ ከወንጌል አስተምህሮ ጋር የማይጣጣም ባህልና አመለካከት ታሪኩ ብዙ ነው። ኢሬቻ ለአብዛኛው ኦሮሞ ሕዝብ (የአካባቢውን አማራ ትግሬ ጉራጌ ወዘተ ጨምሮ)፣ ከመኸር በኋላ ከአዲሱ ዓመት ጋር የሚመጣ የደስታ የመብላት የመጠጣት የመገባበዝ የጭፈራ ሰሞን ነው። ሁሉ ቢቀር፣ መስከረምን በምድራችን ለታዘበ፣ እንደ ልምላሜዋ ውበት እና ስፋት ተስፋ ከማድረግና እግዚአብሔርን ከማመስገን ውጭ አማራጭ የለውም! ተስፋ የምናደርገው፣ እምነታችንም፣ የክርስቶስ ወንጌል ኃይል፣ ሙት ለሆነው ሁሉ ትንሣኤን ያቀዳጃል ብለን ነው!

  • ወንድሜ ቴዲ፣

    ስለ ጥያቄዎችህ አመሰግናለሁ፤ አግባብ ናቸው።

    ፩) ጸሐፊው ልምን የደቡቡን ብቻ አነሳ

    ከጹሑፍ ዐውድ እንደምትረዳው፣ ዐቢይ ዓላማዬ በሁሉን ዐቃፊነት ወይም የአንዳንድ ባህሎችን ሃይማኖታዊ ገጽታ በማሳነስ፣ ወደ ቅይጥነትን የሚወስዱን ነገር-መልኮታዊ ልዝብተኝነት ለማሳያት እና ቤተ ክርስቲያንን ለማሳሰብ እንጂ ባህል በባህል እየሂድሁ ተመሳሳይ ዳሰሳ ለማድረግ አይደለም። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥም፣ በተለይም ከድርሳናትና ከገድላት ጋር በተያያዝ ያሉ ብዙ ባዕድ ልምምዶች እንዳሉ የተወቀ ነው። ጽሁፌም፣ እዚያ ያለው ባህላዊ ቅይጥነት ቸል ተብሎ ሌላው ላይ ለምን ትኩረት ይሰጣል ወደ ሚለው ውይም በወንጌላዊው ማኅበረሰብም ውስጥ ተመሳሳይ “ነጻነት” ሊኖር ይገባል የሚለው ድምዳሜ ጠንካራ ሙግት አይደለም። በተለይም የወንጌል ብርሃን በርቶልናል የምንል ከሆን! መልዕክቴ ይኸው እሬቻን ብቻ ላይ ሳይሆን፣ የሲዳማውን ፍቼ ጨምበላላ፣ የወላይታውን ጊፋታ፣ በየሀዲያውን ያሆዴ እንዲሁም ለሌሎች ባህላዊ በዐላት ላይ ባሉት እይታዎች ላይም አግባብነት አለው።

    ፪) ምናቸው ነው ከኦርቶዶክሳዊው የክርስትና ትምህርት ጋር የሚጋጨው?

    ይህም ጥሩ ጥያቄ ነው። በአገራችን የወንጌላዊያኑ ማኅብረሰብ መካከል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዐውዳዊነትን እጅግ በመለጠጥ፣ ባህል፣ ማኅብራዊና ፓለቲካና ከክርስትና ጋር የማጋባት አባዜ ውስጥ መገባት ጀምረናል። በርግጥ፣ በክርስቶስ የመስቀል ቤዛዊ ሥራ የተገኘው ድነት፣ ሰውን ሁለንተናዊ በሆነ መልክ የሚዋጅ ነው። ኀጢአት ግለሰባዊ (Individual) ብቻ ሳይሆን ከተፈጥሮ ጋር እንዲሁም ከማኅበራዊ (social) መስተጋብሮቻችንን አቃውሷል። በዚህ መልኩ የክርስትና መልዕክት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንድምታዎች ወይም ክትለቶች (implications) አሉት። ቤተ ክርስቲያን ሰማያዊም (የክርስቶስ መንፈሳዊ አካል – Sacredness)፣ ምድራዊም (sociological) አካል አላት። የኤፌሶንን ምእመናን ሐዋርያው ጳውሎስ “በአንድ ጊዜ በኤፌሶንም በሰማያዊውም ስፍራ በክርስቶስ ጋር” መቀመጣቸውን ባሳሰበበት እሳቤ ማለት ነው (ኤፌ 1፥1-3)። በዚህ አግባብነት፣ በአገራችን ዐውድ፣ ምድራዊው ኑሯችን በብዙ ፈርጁ ከቶ ላይነጠል ከምድራዊ ዜግነታችን እንዲሁም የሕይወት ትግልና ተስፋ ጋር ተጋምዷል። ለፖለቲካዊ፣ ለኢኮኖሚያዊና ለማኅበራዊ ጉዳዮች ባይተዋር ልንሆን አንችልም። የወንጌል “የምሥራችነት” ሰውን “በግለ ሰብነት” ብቻ ሳይሆን፣ “በማኅበራዊነቱም” የሚመለከት ነው። ሆኖም፣ የወንጌላች ዐውድ ይቀያየር እንጅ መልዕክቱ ግን ህያውና የማይቀያየር ነው። አይጨመርበትም፣ አይሻሻልም አይቀነበትም። ዐውዳዊ አግባብነት ለማግኘት ስንል ሁሉን አናቅፍም። ባህሎችና ነጸረ-ዓለሞች ሁሉ በዚህ የወንጌል እውነት ሊፈተሹ ይገባል። ለምሳሌ፣ በቅርበት የማውቀው እሬቻ “ባህል ብቻ ነው” ማለት ትልቅ ተፋልሶ ነው። በእሬቻ መርሐ-ግብር ላይ የሚቀርበው ምስጋና እና አምልኮ በርግጥ ለመጸሐፍ ቅዱሱ ዋቃ – ለክርስቶስ ኢየሱሱ ዋቃ ነው? በዖዳ ዛፍ ላይ ወይም በሲዳ ድንጋይ ላይ ቅቤ እየተቀባ፣ ለዚህ አገልግሎት የሚለመነው መንፈስ (አያና) [Ayyana፣ ntermediary spirits] በመንፈስ ቅዱስ ነው? በዚያን ቀን በሚያገልግሉት ቃልቻዎች የሚያድረው መንፈስስ፣ ቅዱሱ ነው? ዘመን መለወጫን ማክበር አንድ ነገር ነው፤ “የኢሬቻውን ዋቃ” ማምለክ ግን ሌላ ነው። ሆኖም ማንም ያሻውን ማምለክ፣ ማክበር፣ መቀየጥ፣ ሰብአዊ መብቱ ነው። በአንድ ጊዜ የክርስቶስን ወንጌልና የእሬቻን ባዕል ሃማኖታዊ ገጽታ መያዝ ተፋልሶ ነው – ያማይታረቅ ተቃርኖ አላቸውና! ይህ ድምዳሜዬ ለሁሉም ሃይማኖች እንዲሁም ሃይማኖታዊ ገጽታ ላላቸው ባህሎች ሁሉ አግባብነት አለው። ለተጨማሪ ጥናዊ ጽሑፍ : https://www.diva-portal.org/…/diva2:681146/FULLTEXT01.pdf file:///C:/Users/Girma/Downloads/84373-Article%20Text-205310-1-10-20130114.pdf

    ፫) መዋጀት የሚለው ቃል ብዙ ነገር ውስጡ ያለብት (loaded) ቢሆንም ለምንድነው ባህሎችን የማንዋጀው? በአጭሩ ወንጌል ሲሰበክ፣ ስንታዘዘውና ሲንኖርው ባህላችንም ይዋጃል – ከወንጌል ጋር ተቃርኖ ያለው ይቀራል። ክርስቲያናዊ ሕይወት ምሉእ ሕይወት ነው፤ ማለት ከፊሉ ምድራዊ ከፊሉ ሰማያዊ ወይም ዓለማዊና የተቀደሰ በሚል ጐራ አይከፋፈልም። በሁለንተናዊ ይዘቱ፣ ሕይወት በምሉዕነት ለእግዚአብሔር ክብር መኖር አለበት። “አእምሮንም ሁሉ እየማረክን ለክርስቶስ እንዲታዘዝ እናደርጋለን” (2ቆሮ 10፥5)። በሁለንተናዊ የሕይወት ፈርጅ፣ በትውልድ ላይ የጽድቅ ተጽእኖ ማለት ይህ ይመስለኛል። የክርስቶስ ማኅበረሰብ የመሆናችን ተኣማኒነት የሚለካው ለጨለመውና ጣዕም ላጣው ዓለም ብርሃንና ጨው በሆንበት መጠን ነው። ከወንጌል ተልዕኮ አንጻር ሊኖርን የሚገባው ድርሻ ጳውሎስ በአቴና እንዳደረገው ነው። (1) “ጳውሎስ በአቴና ሆኖ ሲጠብቃቸው ሳለ፣ ከተማዪቱ በጣዖት የተሞላች መሆኗን በማየት ***መንፈሱ ተበሳጨበት***።” ሐዋ. 17:16 – (2) “ስለዚህ በምኵራብ ሆኖ ከአይሁድና እግዚአብሔርን ከሚፈሩ ግሪኮች ጋር፣ ደግሞም በገበያ ስፍራ ***ዕለት ዕለት ከሚያገኛቸው ሰዎች ጋር ይነጋገር ነበር****” – ሐዋ. 17:17)። – (3) “ስለዚህ ጳውሎስ በአርዮስፋጎስ በተሰበሰበው ሕዝብ መካከል ቆሞ እንዲህ አለ፤ “የአቴና ሰዎች ሆይ፤ በማናቸውም ረገድ፣ ***በጣም ሃይማኖተኞች መሆናችሁን አያለሁ****፤ እየተዘዋወርሁ ሳለሁ፣ የምታመልኳቸውን ነገሮች ስመለከት፣ ‘ለማይታወቅ አምላክ’ የሚል ጽሑፍ ያለበት አንድ መሠዊያ አይቻለሁና፤ እንግዲህ ***ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እገልጽላችኋለሁ****። – ሐዋ. 17:22-23 – (4) “ዓለምንና በውስጡ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ ***እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነው****፤” ሐዋ. 17:24 – (5) “እንግዲህ የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን፣ ***አምላክ በሰው ሙያና ጥበብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ*** ይመስላል ብለን ማሰብ አይገባንም።” (ሐዋ. 17:29) – (6) ቀደም ሲል እግዚአብሔር እንዲህ ያለውን ***አለማወቅ*** በትዕግሥት ዐልፎአል፤ አሁን ግን በየቦታው ያሉ ***ሰዎች ሁሉ ንስሓ እንዲገቡ ያዛል***፤ በመረጠው ***ሰው*** (Christ) አማካይነት በዓለም ላይ በጽድቅ የሚፈርድበትን ቀን ወስኖአልና፤ እርሱንም ከሙታን በማስነሣቱ ለሰዎች ሁሉ ይህን አረጋግጦአል።” (ሐዋ. 17:30-31 – (7) “አንዳንድ ሰዎች ግን ጳውሎስ ባለው በመስማማት ተከተሉት፤ ***አመኑም***” – (ሐዋ. 17:34)

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.