“ልወቅስህ መጣሁ” ከሚለኝ ሰው ይልቅ፣ “ላመሰግንህ ደወልሁ” የሚለኝ ቶሎ የጆሮዬን ንቃት ያገኛል፤ የዐይኔን ፈገግታ፣ የግንባሬን ፍካት ይቀበላል። ድምፆችን ግን መርጠናቸው አይመጡም። አሁን መስማት የሚያሻን ድምፅ ምን ዐይነት ነው? የንስሓ ወይስ የፍስሓ? ወዳጆቼ፤ እውነተኛ ፍስሓ ከእውነተኛ ንስሓ ይፈልቃል። በደል ባልተስተካከለበት ቦታ የደስታ ፈንጠዝያ የእብድ ጩኸት ይሆናል። ንስሓ የጤና ድምፅ ነው፤ እና እባካችን አሁን ስለ ንስሓ እንነጋገር።
አስቀድሞ የጥያቄ እሩምታ፦
- አንድ ሰው እውነተኛ ንስሓ መግባቱን በምን እናውቃለን?
- ሌሎች ባጠፉት እኔ ንስሓ እገባለሁን?
- ንስሓ አስገቢ አናዛዥ፣ ንስሓ ገቢ ተናዛዥ የሚባል አመዳደብ አለ እንዴ?
- ንስሐ መግባት የሚባለውን ጣጣ ትቼ ደግ ደጉን ብቻ ብሠራስ?
- ደጋግሜ በበደል መዘፈቄን እያወቅሁት አሁን ንስሓ ብገባ ምን ፋይዳ አለው?
- ንስሓ እንግባስ ቢባል እውነት አሁን እግዚአብሔር እኛን ይምረናል?
ንስሓ የመጽሐፍ ቅዱስ ቋንቋ ነው። መሠረታዊ የክርስትና አስተሳሰብ ነው። ሁሉን ነገር ውብ አድርጎ የሠራው ጥበበኛ አምላክ ፍጥረቱ ተበላሽቶበታል። ኀጢአት የሚባል የንጽሕና ጉድለት ዐመፅና መሳሳት ወደ ሰው ልጅ ልብ ዘልቆ ሰውንም ፍጥረትንም በክሏል። ቅዱሱንና እውነተኛውን አምላክ አሳዝኗል። ስለዚህ ለበደል ይቅርታ መለመን፣ የኀጢአት ኑዛዜ ማቅረብ፣ ከተሳሳቱበትም መመለስ የመጽሐፍ ቅዱሱ ንስሓ ዐይነተኛ ባሕርያት ናቸው። ለንስሓ ባይተዋር የሚሆነው ሰው ለመጽሐፍ ቅዱስም ባይተዋር የሆነ ነው። ከዘፍጥረት እስከ ራእየ ዮሐንስ የተዘረጋው የንስሓ ጎዳና ነው። እኛ ግን አሁን ላለብን አንገብጋቢ አበሳ፣ መጽሐፈ ዕዝራንና መጽሐፈ ነህምያን እንደ መነሻ በማድረግ የእውነተኛ ንስሓ ገጽታዎችን ወይም አንኳሮችን እንነጋገር።
1. እውነተኛ ንስሓ ራስን ይጨምራል
“እኔና የአባቴ ቤት በድለናል” ብሎ የጮኸው ያ ጥንቁቅ መሪ ነህምያ፣ የእስራኤልን ጉስቁልና በአንዳንድ ወስላቶች ላይ እያላከከ ንስሓ ለማስገባት የቆመ ባላባት አልነበረም። “አምላኬ ሆይ፤ ፊቴን ወደ አንተ ቀና ለማድረግ ፈራሁ። ከአባቶቻችን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በደላችን ታላቅ ነው።” ያለውም ትሑቱ ካህን ዕዝራ ነበር። (ነህ 1፥6፤ ዕዝ 9፥6) ወዳጆቼ እነዚህ ሰዎች በተለይ የሠሩት ኀጢአት ኖሮ፣ ቀንደኞቹ በደለኞች እነሱ ሆነው ወይም በዐመፃ ተከስሰው የቀረቡ አልነበሩም። ይልቁን የሕዝቡን በደል በላያቸው ተሸክመው የሚቃትቱ ማላጆች ነበሩ። በእግዚአብሔር ማኅበር ውድቀት ውስጥ እጁን ታጥቦ እኔ የለሁበትም” የሚል መሪ የንስሓን ምስጢር ገና አልተረዳም። እነሱ እኛ ነን፤ እኛ እነሱ ናቸው። ደግሞስ ልብንና ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ የእያንዳንዳችንን ጥፋት እያወጣ ቢዘረዝረው፣ ማን ነው ከወቀሳ የሚያመልጥ? በእኛ አገር ቤተ ክርስቲያን፣ በተለይም በጌታ ቤት አገልጋዮች በሆንነው ሰዎች መካከል በእነዚህ ዓመታት የተፈጸሙት በደሎች ራስ አስይዘው የሚያስጮኹ ናቸው። ‘እኔ በድያለሁ’ ማለት ከተሳነን፣ ጣቶቻችንን በተወሰኑ ሰዎችና ቡድኖች ላይ አነጣጥረን የምንሟገት ከሆነ “ንስሓ” የሚባለውን ፈዋሽ መድኃኒት ገና አላገኘነውም።
2. በቃሉ መለኪያ ራሱን ይፈትሻል
ንስሓ የሚያስገባን ነገር ምንድን ነው? ሰው ስለተቀየመን ነው? እኛ በውስጣችን ቆሻሻነት ስለተሰማን ነው? ‘ንስሓ ግቡ’ ተብለን ስለተወተወትን ነው? ወይስ እንዲያው “ከነገሩ ጦም ዕደሩ” በሚል የሰላም አየር ለመፍጠር ብለን ነው? እውነተኛ የኀጢአት ወቀሳ ከእውነተኛው መለኪያ መንሸራተታችን ሲገባን የሚመጣ ነገር ነው። በቅዱስ ቃሉ ውስጥ ባሉት መለኪያዎች ራሳችንን ስንፈትሽና ከደረጃው የወደቅን መሆናችን ሲገባን ዋይታችን እውነተኛ መሠረት ያገኛል። “ባሉበትም ቦታ ቆመው ከአምላካቸው ከእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ሩብ ቀን አነበቡ። የቀረውን ሩብ ቀን ደግሞ ንስሓ በመግባትና ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር በመስገድ አሳለፉ።” (ነህ 9፥3)።
አሁን በእኛ መካከል ሰዎች ‘ንስሓ ገብተዋል፣ አልገቡም’ እያልን ግራ እስኪገባን የሚያደርሰን ምን ይሆን? የኀጢአት ወቀሳው በእግዚአብሔር ቃልና በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ወደየሰዉ ልብ ስላልገባ ይሆን? ንስሓችን እውነተኛ የሚሆነው ያደረግሁት፣ የኖርኩት በፍጹሙ የእግዚአብሔር ቃል ፊት ሊቆም የሚችል ነውን? ብዬ የምሬን የጠየቅሁ እንደሆን ነው። ‘የወቀሰኝ የሰማይና የምድር ጌታ ልዑል እግዚአብሔር ነው’ ያልሁ ጊዜ ነው። ከዚያ ውጪ ግን ሥነ ልቡናዊ ወይም ፖለቲካዊ ጨዋታ ብቻ ሊሆን ይችላል። ልመናዬ የሰማይ ብርሃን በልባችን ቷ ብሎ እንዲበራ፣ ፈሪሃ እግዚአብሔርም እንዲቆጣጠረን ነው።
3. ጥፋትን ግልጽ ያደርጋል
“ቆመውም ኀጢታቸውንና የአባቶቻቸውን በደል ተናዘዙ” (ነህ 9፥2)፤ “የኢየሩሳሌም ሰዎች ጠቅላላ ወደ እርሱ በመሄድ ኀጢታቸውን እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ተጠመቁ” (ማር 1፥5) (ነህ 1፥7-9)።
በአዲስ አበባ ሆቴሎች ውስጥ “ሽፍንፍን” የሚባል ምግብ ነበር። ዘንፋላ እንጀራ በላዩ ጣል ተደርጎበት እስክትገልጡት ድረስ ምንነቱ የማይታይ። መጽሐፍ ቅዱሳዊው ንስሓ ግን በደልን በስሙ ጠርቶ “አጥፍቻለሁ” ይላል። በገንዘብ ጉዳይ ቢሆን፣ በአውስቦ ጣጣ ቢሆን፣ በጥቅምና ከበሬታ ፍላጎት ሩጫ ቢሆን፣ በማታለል ቢሆን፣ በሐሰት ትምህርት ጉዳይ ቢሆን፣ ርግጥ ፍርጥ አድርጎ ‘ያጠፋሁት ይህ፣ ይህ ነው’ እንዲል ይጠበቃል። አሁን በእኛ መካከል የተሠሩ ኀጢአቶችና ክፉ ድፍረቶች ይህን ያህል ስውር ናቸውን? ንስሓ ከገባን የጥፋቶቹን ስም እንጥራ። በሐሰት ትምህርት ምክንያት ስንት ወጣት ከመሥመር ተፈናቀለ? በስግብግብነት ወንጌል የስንቱ ልብ ያለ አግባብ ተንጠለጠለ? በአልጠግብ ባይነት የስንቱን ቤት ዘረፍን? በተሳሳተ ትንቢት ስንቱን ሰው ከአምላኩ ጋር አጣላን? ባልተገራ የሥጋ ፍትወት ስንት ጊዜ የከበረውን ጌታ ስም አሰደብን? ኡኡታ ሲያንሰን ነው።
ኑዛዜ በጣም መሠረታዊ የንስሓ ክፍል ነው። “እርስ በርሳችሁ በኀጢአታችሁ ተናዘዙ” እኮ ተብሏል (ያዕ 5፥16)። ኑዛዜ በእግዚአብሔር ፊት መደረጉ ቀዳሚ ሲሆን፣ እንደ አግባብነቱ ደግሞ በእግዚአብሔር ማኅበር ፊት፣ በእግዚአብሔር ቤት አገልጋዮች ፊትም ሊደረግ ያስፈልጋል። ኀጢአት ሲጠሩት ቢያሳፍርም፣ በስሙ መጠራት ይገባዋል። በአገራችን የሚነገር ተረት አለ። ጓደኛው የሁለት ዓመት እስራት ተፈርዶበት ወደ ወህኒ ሲወሰድ ያገኘው ሰው ደንግጦ፣ “ምን አድርገህ ነው የሚያስሩህ?” ሲለው፣ “አንድ ገመድ ሰርቄ” ብሎ መለሰለት፤ “ለአንድ ገመድ ይህ ሁሉ ቅጣት!” ብሎ ሲገረም፣ “አይ ገመዱን ከታሰረበት ፈረስ ጋር ነበር የወሰድሁት” አለው ይባላል። እውነተኛ ንስሓ ቅን ኑዛዜ ይፈልጋል። “ኑና እንዋቀስ… ኀጢአታችሁ እንደ አለላ ብትቀላ እንደ አመዳይ ትነጻለች…” (ኢሳ 1፥18)።
4. እውነተኛ ጸጸትን ይገልጻል
ያለ ጸጸት የሚረግ ንስሓ በእግዚአብሔር ክብር ላይ ማላገጥ ነው። በደል አምላክን የሚያሳዝንና የሚያስቆጣ ብርቱ ጉዳይ ነው። ከበደልን በኋላ የአፍ ማሟሻ ይቅርታ መጠየቅ የእውነተኛ ንስሓ ባሕርይ አይደለም። ድንጋጤና ሀፍረት፣ ጸጸትና ትካዜ የሌለበት ንስሓ የእግዚአብሔርን ቅዱስነት ያላስተዋለ፣ የፍትሐዊነቱን ጥልቀት ያላገናዘበ ተራ ልምምድ ነው። የአምላክን ረቂቅ ሥራና ዘላለማዊ ፍትሐዊነት የተገነዘበ ኢዮብ በተናገረው ንግግር አፍሮና ደንግጦ፣ “ራሴን እንቃለሁ፤ በአፈርና በአመድ ላይ ተቀምጬ እጸጸታለሁ” ይላል (ኢዮ 42፥6)።
የንጉሥ ዳዊት ኑዛዜ የሚያስተምረን ብርቱ ትምህርት ደግሞ በቅዱስ አምላክ ፊት በሞራል ራቁትነት ስንቆም የሚሰማን ጸጸትና እሮሮ የእውነተኛ ንስሓ መግቢያ በር መሆኑን ነው። “አንተን ብቻ በደልሁ፤ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ።… አቤቱ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ” (መዝ 51፥4-10)።
ያ ትሑት ካህን ዕዝራ እንዲህ ይላል፣ “…አምላኬ ሆይ ፊቴን ወደ አንተ አነሣ ዘንድ አፍራለሁ፣ እፈራማለሁ…”። ይህን ልብ የሚነካ ጸሎት የጸለየው የእግዚአብሔር አገልጋዮች ርኩሰት ያደርጋሉ የሚል ሪፖርት እንደሰማ፣ ልብሱን ቀድዶ በድንጋጤ ከተቀመጠ በኋላ ነው (ዕዝ 9፥6)። የጸጸት እጦት ራሱን የቻለ ፍርድ ነው ልበል? እግዚአብሔር ሲራራልን ነው ጸጸት ልባችን ውስጥ የሚፈጠረው። ከበደል ይቅርታ ልመና ጋር የጸጸት ልቡና እንድናገኝ መማጠን ሳይሻለን አይቀርም።
5. የእግዚአብሔርን ጻድቅነት ይቀበላል/ያውጃል
በደልን ማላከክ፣ ሰበብ መደርደር፣ ‘እነ አገሌም አድርገዋል’ እያሉ እኩያ መፈለግ፣ ሲከፋም ስለ በደላችን እግዚአብሔርን መውቀስ ወይም በስውር ልብ ማማት ከንስሓ መንገድ መራቅ ነው። “እኔ በድያለሁ” የሚል ትሑት ሰው፣ ጨምሮ “አንተ ግን ንጹህ ነህ” ሊል ይጠበቅበታል። ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ሲተያይ ሌላ ቋንቋ ሊኖረው አይችልም።
“በደረሰብንም ነገር ሁሉ አንተ ጻድቅ ነህ፤ አንተ እውነት አድርገሃልና፤ እኛም ኀጢአት አርገናል።” (ነህ 9፥33)
የእግዚአብሔር ፍጹም ጻድቅነት ባይኖር ኖሮ መናዘዣ ቦታም፣ ይቅርታ የሚለመንም አይኖርም ነበር። የእኛ ኀጢአት ከእርሱ ጽድቅ ጋር ሲፋጠጥ የሚጠብቀን ቅጣት እንዲነሣልን መማጠኛም ነው ንስሓ። እንኳን እርሱ ጻድቅ ሆነ! የዓለሙ ሁሉ እንቅስቃሴ በምን ይመዘን ነበር? የሚምረን እኮ ጽድቁን አዛንፎ ሳይሆን ፍቅሩን አብዝቶ ነው። እግዚአብሔርን “አንተ ጻድቅ ነህ” ማለት ክብሩን መግለጽ፣ ልባዊ ትሕትናም ማሳየት ነው።
6. በጌታ የምሕረት ኪዳን ይመካል
“…ቃል ኪዳን አደረግህ፣ አንተም ጻድቅ ነህና ቃልህን ፈጸምህ።” (ነህ 9፥8)
ያለንበትን ውድቀት፣ የሰመጥንበትን የኀጢአት ረግረግ ስናስተውል፣ ‘እንዴት ከዚህ እንወጣለን? አምላክስ በምን መንገድ ይታረቀናል?’ የሚል ፍርሀትና ተስፋ መቁረጥ ይመጣብን ይሆናል። ከእኛ ዘንድ እግዚአብሔርን ሊያባብል ወይም በቃል ይሁን በሥራው ሊያስገርም፣ ምሕረትም ከእጁ ፈልቅቆ ሊያመጣልን የሚችል ማንም የለም። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ንጹሕ ደሙን አፍስሶ የምሕረት ደጅ አስከፈተልን። “…ይህ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው” ያለው ከአባቱ ዘንድ በደሙ በኩል ለእኛ የሚሰጠውን ስርየት ዋስትና ሲያረጋጥልን ነው። ተስፋ ቢስ ኀጢአተኛ በዚህ የኪዳን ደም ተመክቶ “ስለ ልጅህ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስትል ማረኝ” ብሎ ሊማጠን ይችላል። የልዑል አምላክን ምሕረትም በነጻ ይቀበላል። ትምክህታችን ይኸው ብቻ ነው። በዚህ የደም አምባ ውስጥ ተገን እናገኛለን፤ ከመዐትም እናመልጣለን።
7. እውነተኛ ንስሓ የመመለስ ርምጃ ይወስዳል
እውነተኛ ንስሓ በቃላት ቀለም ያሸበረቀ ቅጠል ብቻ ሳይሆን፣ በድርጊት ለውጥ የተንዠረገገ ፍሬ ነው። በዋይታ፣ በልቅሶ፣ በጸጸት፣ በመሀላ (ቁርጥ ውሳኔ) መንገድ ሄዶ ከነበሩበት የጥፋት ጎዳና መመለስ ነው። “…በላያቸው ትቢያ ነስንሰው ተከማቹ፤ የእስራኤልም ዘር ከእንግዶች ሁሉ ራሳቸውን ለዩ” (ነህ 9፥2)። “ከአምላካችን ጋር ቃል ኪዳን እናድርግ፤ እንደ ሕጉም ይደረግ” (ዕዝ 10፥3)። መጥመቁ ዮሐንስ ሰዎች እንዲናዘዙና ለምልክትም በውሃው ውስጥ እንዲጠመቁ ብቻ እየነገረ አልኖረም። ይልቁን በጣም ተግባራዊ ዝርዝር ይሰጣቸው ነበር። “ሁለት ልብስ ያለው ለሌለው ያካፍል፤ …ከታዘዘላችሁ አብልጣችሁ አትውሰዱ፣ በማንም ግፍ አትሥሩ… ደመወዛችሁ ይብቃችሁ…” (ሉቃ 3፥10-14)።
በእኛ አገር ቤተ ክርስቲያን ሁኔታ እውነተኛ ንስሓ ገብተን ከሆነ በባሕርይና በተግባር ለውጣችን ምስክር ልናቆም ይገባናል። ከየልባችን በፈለቀ የሐሰት ትንቢት ሰው ስናደናግር ኖረን ከሆነ፣ አፋችንን መዝጋትና ንጹሑን ቃለ እግዚአብሔር ብቻ መናገር፤ በአገልግሎት ስም የየሰዉን ኪስ በጮሌ ቋንቋ አራቁተን ለራሳችን ገንዘብ አከማችተን ከሆነ፣ ልባችንንም እጃችንንም መሰብሰብ ይገባናል። ሰው በመተቸት ብቻ ሠልጥነን ውሏችን የስድብ ሠፈር ሆኖብን ከሆነ፣ ቆም ብለን ራሳችንን በመንፈሱና በቃሉ መፈተሽ ይገባናል። ከራሳችን ድምፅ ሌላ የማንንም ምክር አልሰማም ብለን እብሪት አፍኖን ከሆነ፣ ‘እባካችሁ ምከሩኝ’ ልንል ይገባናል። የእግዚአብሔር ያልሆነ “እንግዳ ዘር” ክፉ ባሕርይ አብቅለን ከሆነ፣ በምትኩ የመንፈስን ፍሬ ልናሳድግ ይገባል። እግዚአብሔር አምላክ በልባችን ያለውን ሁሉ ያያል፤ ሰዎች ግን የተገለጠውን የንስሓችንን ፍሬ ሊያዩ ያስፈልጋል።
እና ወዳጆቼ ቀን ሳይረፍድ ወደ ዕረፍትና ወደ መንፈሳዊ ልማት የሚያመጣንን የንስሓን ጎዳና እንጀምረው። ‘ተስፋ የለኝም፣ ብዙ ነገር ተበላሽቷል፤ መቃናት አይችልም’ አንበል። ሰማያዊው ጌታ የምሕረት እጁን ዘርግቶ ሲጠብቀን ያንን ሩኅሩኅ እጅ አንግፋ። ለቁጣ አልመረጠንምና ቶሎ ብለን እግሩ ሥር እንደፋ።
Add comment