[the_ad_group id=”107″]

ጕራማይሌው የቴሌቪዥን አገልግሎት

ይህ ያለንበት የ21ኛው ክፍለ ዘመን የአስተሳሰብና የባህል ሽግግር/ለውጥ እጅግ በጣም ፈጣን የሚባል ነው፡፡ እንደ ከዚህ ቀደሙ በአንድ አካባቢ ያሉ አስተሳሰቦች፣ ፍልስፍናዎች፣ ሃይማኖታዊ ተዋስኦዎች፣ ወዘተ. ወደ ሌላው አካባቢ ለመድረስ ዓመታትን፣ ምናልባትም ዘመናትን የሚያስቆጥሩበት ረጅሙ ጊዜ አሁን አጥሯል፡፡ ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶች ቢሰጡም፣ የብዙኀን መገናኛ ሚና ግን ጉልሕ ሥፍራ የሚይዝ እንደ ሆነ ከብዙዎች የተሰወረ አይደለም፡፡

የቴክኖሎጂው መስፋፋትና ማደግ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተለት ያለው የሚዲያው ኢንዱስትሪ፣ ዓለምን ዘዋሪ፣ ሐሳብ አፍላቂ/አስተላላፊ ከመሆኑም በላይ ሊናቅ የማይችል ብርቱ ጉልበት አዳብሯል፡፡ በአጠቃላይ፣ የብዙኀን መገናኛ የፈረጠመ ጡንቻና አቅም አግኝቷል ወደሚባልበት ደረጃ ደርሷል፡፡ አሁን ባለንበት ዘመን ሚዲያውን የያዘ የትኛውም አካል ተጽእኖው እጅግ የበዛ የመሆኑ እውነት በግልጽ እየታየ ነው፡፡ በርግጥ ይህ ጉልበቱ ከባሕርዩ የሚመነጭ ነው፤ ስያሜው ራሱ እንደሚገልጸው ብዙኀን መገናኛ አንድን መልእክት፣ ለብዙ ሰዎች (ሕዝብ)፣ በተመሳሳይ ጊዜ፣ በተመሳሳይ ወይም/እና በተለያየ መንገድ ማስተላለፍ መቻሉ ነው የአቅሙ ምንጭ፡፡

የቴሌቪዥኑ ትሩፋቶች

ባለፉት ረጅም ዓመታት የብዙኀን መገናኛ ለወንጌል መስፋፋት የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በተለይም፣ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ይጠቀሙ የነበሩ ክርስቲያናዊ ተቋማት ያሳደሩት ተጽእኖ በዚህ ባለንበት ዘመን የክርስትና እምነት እንዲስፋፋ ምክንያቶች ከሆኑ መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በቀደመው ዘመን፣ በእኛም አገር የወንጌል መልእክትን ሲያሰራጩ የነበሩና የብዙ ቅዱሳንን ሕይወት የለወጡ የሬዲዮ ጣቢያዎች ነበሩ፤ ዛሬም አሉ፡፡ የኀትመት ሚዲያውን የተመለከትን እንደ ሆነ፣ መጽሔቶችና ጋዜጦች ባለፉት ጥቂት ዐሥርት ዓመታት የበኩላቸውን የወንጌል ኀላፊነት ሲወጡ ቆይተዋል፡፡ ከቴክኖሎጂው መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሳተላይት ቴሌቪዥን እና የድረ ገጽ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በወንጌል መስፋፋት ላይ የራሳቸውን አሻራ በማሳረፍ ላይ ናቸው፡፡

አንድ ሊካድ የማይቻለው ሃቅ የክርስቲያን መገናኛ ብዙኀን በኢትዮጵያ መሰራጨት ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ የወንጌል መልእክት ተደራሽነት መጨመሩ ነው፡፡ በሬዲዮ ይተላለፉ የነበሩ ትምህርቶችና መልእክቶች በሺህዎች (ምናልባትም በሚሊዮኖች) የሚቆጠሩ አድማጮችን አገልግሏል፡፡ የሬዲዮ አገልግሎቶች በዋና ዋና ከተሞች ካለው አድማጭ ባልተናነሰ በገጠር አካባቢ ላሉ አማኞች መተኪያ ያልተገኘላቸው “አገልጋዮች” ነበሩ (ምናልባት እስከ አሁንም ናቸው)፡፡ በአንዳንድ የአገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች የሬዲዮ አገልግሎቶች በቤተ ክርስቲያን አዳራሽ ውስጥ ወይም ሰዎች በሚሰበሰቡባቸው አካባቢዎች ይደመጡ እንደ ነበር ምስክርነቶች አሉ፡፡

በተለይም የሳተላይት ቴሌቪዥን ሥርጭት ከጀመረ በኋላ ሰዎች አማራጭ የመገልገያ መንገድ አግኝተዋል፡፡ አማኞች የሆኑም ያልሆኑም ቤታቸው ውስጥ ሆነው በቴሌቪዥን መስኮታቸው የሚተላለፉትን መልእክቶች ይከታተላሉ፡፡ ይህ የቴሌቪዥን አገልግሎት በምእራባውያን አገራት ውስጥ በስፋት ሥራ ላይ የዋለ ሲሆን፣ “ክርስቲያናዊ” ዕሴት (ባሕል) እንዲስፋፋ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱ ይነገርለታል፡፡ ኤድ ስቴትዘር በክርሰቲያኒቲ ቱዴይ ድረ ገጽ ላይ “The Christian and his Television” በተሰኘ ርእስ ባሰፈረው ጽሑፉ፣ በአሜሪካ አገር ይሰራጩ የነበሩት የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ክርስቲያናዊ ባሕልን ማስረፅ እንደ ቻሉ ጠቅሷል፡፡ በተለይም በ1970ዎቹ እና 80ዎቹ (እ.አ.አ) እንደ ቢሊ ግርሃም ያሉ ሰባኪያን ያሳደሩት ተጽእኖ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው እንደ ሆነ ነው የሚያምነው፤ ያንንም ጊዜ በአሜሪካን የቴሌቪዥን አገልግሎት “ወርቃው ዘመን” ብሎ ይጠራዋል፡፡

ይኸው የቴሌቪዥን አገልግሎት ተጽእኖ ወደ አገራችን በመምጣት ላይ እንዳለ ይታመናል፡፡ በተለይም በቴሌቪዥን አገልግሎት በሚቀርቡ ሥራዎች ብዙዎች እየተጠቀሙ እንደ ሆነ የፕሮግራም አዘጋጆች ከሆኑት መካከል የሚናገሩ አሉ፡፡ የጎልደን ኦይል ሚኒስትሪ መሥራችና ፕሬዚደንት የሆኑት እንዲሁም ዞይ የተሰኘ የቴሌቪዥን ፕሮግራም በሳምንት ሁለት ጊዜ በኤልሻዳይ ቴሌቪዥን ኔትዎርክ ላይ የሚያቀርቡት ያሬድ ጥላሁን (ወ/ዊ) የቴሌቪዥን አገልግሎት ጠቀሜታን ሲመሰክሩ፣ “ባለፉት 20 ዓመታት በየመድረኩ ካገለገልኩት ሰው ይልቅ ባለፉት 5 ዓመታት በቴሌቪዥን መስኮት ያገለገልኩት የሰው ቁጥር በጣም ከፍተኛ ነው” ሲሉ ለሕንጸት ተናግዋል፡፡ በተለይ እርሳቸው መልእክታቸውን ለሚያስተላልፉበት የኤልሻዳይ ቴሌቪዥን ኔትዎርክ ባለቤቶች በአገልግሎት ዘርፉ በኢትዮጵያ ቀዳሚ በመሆን ለብዙዎች ዕድል በመፍጠራቸው ያላቸውን አድናቆት ሳይሰስቱ የሚናገሩት ወንጌላዊው፣ የቴሌቪዥን አገልግሎት ጠቀሜታ ለክርክር የሚቀርብ እንዳልሆነም አያይዘው ይገልጻሉ፡፡

ሳሌም ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ የአዲስ አበባ ተወካይ የሆኑት አቶ መስፍን ኀይለ ኢየሱስ ስለ ቴሌቪዥን አገልግሎት ጠቀሜታ ሲያብራሩ ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት ነው፡፡ “እኛ ስንጀምር ሁለት ትልልቅ ነገሮችን አግኝተናል ብለን እናስባለን” የሚሉት አቶ መስፍን፣ “አንደኛው በቀላሉ መደረስ የማይቻሉ ሰዎች በቲቪ ፕሮግራሞች መደረሳቸውን አይተናል፡፡ አንዳንድ ሰዎች በተለያየ ምክንያት ከቤተ ክርስቲያን የሚቀሩበት አጋጣሚ ይኖራል፤ ሆኖም ግን በቴሌቪዥን በኩል በሚተላለፉ መልእክቶች ካሉበት መንፈሳዊ ድካም እንዲወጡ ሆነዋል፡፡ ሁለተኛ ወንጌል ያልደረሳቸው ሰዎች በቴሌቪዥን አማካይነት ወንጌልን ሰምተዋል” ሲሉ ቢያንስ በእነዚህ ሁለት ተጨባጭ ምክንያቶች የቴሌቪዥን አገልግሎት አስፈላጊነትና በጎ ተጽእኖ ትልቅ መሆኑን ለሕንጸት አስረድተዋል፡፡

የሚዲያው አገልግሎት ሌላኛው ትሩፋት፣ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች ወደ እርሷ እንዲመጡ ከምታደርገው ጥሪ ባንጻሩ እርሷ ወደየቤቱ እንድትገባ ማድረግ መቻሉ ነው፡፡ በመሠረቱ፣ ቤተ ክርስቲያን “ወደ እኔ ኑ!” በሚለው ጥሪዋ ትክክለኝነት ላይ ሰፊ ውይይት አለ፡፡ “እንግዲህ ሂዱና…” (ማቴ. 28፥19) የሚለው የጌታ ትእዛዝ ቤተ ክርስቲያን ወደ ኅብረተ ሰቡ ሁሉ ዘልቃ የመግባት ተልእኮ እንዳለባት የሚያሳይ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የብዙኀን መገናኛዎች ተልእኮውን እጅግ ቀላልና ውጤታማ አድርገውታል ማለት ይቻላል፡፡ ከታላቁ ተልእኮ አንጻር፣ ይህም ማለት ወንጌልን ላልሰሙ ለማድረስ እና የወንጌል ትምህርትን በሰከነ መንገድ ለማስተላለፍ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ወደር የማይገኝላቸው አገልጋዮች ሲሆኑ መክረማቸውን የዘርፉ ባለሙያዎች ያምኑበታል፡፡

ዶ/ር ንጉሤ ተፈራ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ባዘጋቸው ዐውደ ጥናት ላይ “የመገናኛ ብዙኀን ተግባርና ሊኖራቸው የሚገባ የሙያ ሥነ ምግባር ከመጽሐፍ ቅዱስ አኳያ” በሚል ርእስ ባቀረቡት ወረቀት ላይ “መገናኛ ብዙኀን ለማኅበራዊ ለውጥና ዕድገት ለግንዛቤ ማስፋትና የባሕርይ ለውጥ ለማምጣት ከመጠቀም ባሻገር የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማስፋት ጠቃሚነት ያላቸው ዐይነተኛ መሣሪያ መሆናቸው ከታወቀ ወይም ግንዛቤ ካገኘ ውሎ አድሮአል፡፡ ይህንንም ቀደም ብለው የተረዱ ግለ ሰቦችና አብያተ ክርስቲያናት ለረዥም ጊዜ ሲጠቀሙባቸው ቆይተዋል፡፡ መገናኛ ብዙኀን የምስራቹን ቃል በሚሊዮን ለሚቆጠር ሕዝብ ለማድረስ የሚያስችሉና እስከ አሁን ምትክ ያልተገኘላቸው መሣሪያ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡” ሲሉ ጽፈዋል፡፡

የቴሌቪዥን አገልግሎት በኢትዮጵያ

በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያውያንን ቀዳሚ ትኩረት አድርገው የተቋቋሙ የክርስቲያን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቁጥር አራት ደርሷል፡፡ ከአራቱ ቀደሚ ሆኖ የአገልግሎቱን ዘርፍ ለአገራችን ያስተዋወቀው ኤልሻዳይ ቴሌቪዥን ኔትዎርክ ሲሆን፣ እሱን ተከትሎም ሳሌም ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ፣ ሲጄ ቲቪ እና ሆሊ ቲቪ የተባሉ ጣቢያዎች በተከታታይ ለሥርጭት በቅተዋል፡፡ አሁን በሥርጭት ላይ ያሉትን ጣቢያዎች ካላቸው ተመሳስሎ በመነሣት በሁለት ጎራ ከፍሎ መመልከት ይቻላል፤ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ጣቢያዎች (ኤልሻዳይ ቴሌቪዥን ኔትዎርክ እና ሳሌም ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ) በአንድ ጎራ፣ ቀጣይ ሁለቱን ደግሞ (ሲጄ ቲቪ እና ሆሊ ቲቪ) በሌላ ጎራ፡፡

ኤልሻዳይ ቴሌቪዥን ኔትዎርክ ካስቆጠረው የአገልግሎት ዕድሜ ባሻገር በርካታ ፕሮግራሞችን በማስተላለፍና ብዙ ተመልካች በማፍራት ረገድ ቀደማውን ሥፍራ እንደሚይዝ ይታመናል፡፡ ጣቢያው በግለ ሰቦች ባለቤትነት ይዞታ ሥር የሚተዳደር ሲሆን፣ የተለያዩ ቤተ እምነቶች እና አጋር ቤተ ክርስቲያናት (Ministries) እንዲሁም በግለ ሰቦች ደረጃ የሚዘጋጁ ፈርጀ ብዙ የሆኑ ፕሮግራሞችን ወደ ተመልካቾች ያደርሳል፡፡ ከጉባኤ የተቀዱ ትምህርቶች፣ ስብከቶች፣ ነጻ የማውጣት አገልግሎቶች፣ ትንቢታዊ መልእክቶች፣ ወዘተ. እንዲሁም ከስቱዲዮ የተቀረፁና በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የተዘጋጁ ትምህርቶች፣ ስብከቶች፣ ጸሎቶች፣ የውይይት/የቃለ መጠይቅ መሰናዶዎች (ቶክ ሾው)፣ ሳምንታዊ የዜና ሽፋን፣ ልዩ የበዓል ዝግጅቶች፣ የቀጥታ ሥርጭቶች፣ የመዝሙር ክሊፖች፣ በሌላ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የተዘጋጁ የውጪ አገር ፕሮግራሞች፣ ወዘተ. በተለያዩ ቋንቋዎች በዚሁ ጣቢያ የሚተላለፉ ናቸው፡፡ (ሕንጸት መጽሔት የኤልሻዳይ ቴሌቪዥን ኔትዎርክለማነጋገር ያደረገው ጥረት ባለመሳካቱ ተጨማሪ መረጃዎችን ማካተት አልተቻለም፡፡)

በሁለተኝነት የአገልግሎት ዘርፉን የተቀላቀለው ሳሌም ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ ለበርካታ ወራት ያህል ሥርጭት ሲያደርግ ቢቆይም፣ አሁን ግን አገልግሎቱ “ለጊዜውም” ቢሆን መቋረጡ ይታወቃል፡፡ የጣቢያው የኢትዮጵያ ተወካይ የሆኑት አቶ መስፍን ኀይለ ኢየሱስ ይህንኑ በተመለከተ ተጠይቀው ሲመልሱ፣ “አዎ፤ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ተቋርጧል፤ አንዳንድ ነገሮችን እያስተካከልን ነው ያለነው፡፡ በቅርብ ጊዜ ግን ይጀምራል፤ ግፋ ቢል በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የሚጀመር ይመስለናል፡፡” ብለው ነበር፡፡ የሳሌም ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ በፕሮግራሞቹ ይዘት በብዙ መልኩ ከኤልሻዳይ ቴሌቪዥን ኔትዎርክ ጋ ተመሳሳይነት አለው፡፡ በጣቢያው ፕሮግራሞቻቸውን ያቀርቡ የነበሩትም የተለያዩ ቤተ እምነቶች፣ አጋር ቤተ ክርስቲያናት እና ግለ ሰቦች ናቸው፡፡ ከጉባኤ የተቀዱና በስቱዲዮ የተሰናዱ ዝግጅቶች እንዲሁም የመዝሙር ክሊፖች ጣቢያው በአየር ላይ በቆየባቸው ጊዜያት ያስተላልፋቸው የነበሩ ፕሮግራሞች ናቸው፡፡ ሳሌም ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክየአየር ሰዓቶችን ለተለያዩ ተቋማትና ግለ ሰቦች እያደላደለ በመስጠት ዕለታዊ ሥርጭቱን ለመሸፈን ይሠራ የነበረ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ፣ ከዕለታዊ ሥርጭቱ ሰፊውን ሰዓት የሚሸፍነው በራሱ በተሠሩ ፕሮግራሞች ሳይሆን በሌሎች አካላት ተዘጋጅተው በሚቀርቡ መሰናድዎች ነው፡፡ ይህም ሳሌም እና ኤልሻዳይእንዲመሳሰሉ ከሚያደርጓቸው ባሕርያት መካከል አንዱ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ፣ ሳሌም ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ እንደ ኤልሻዳይ ሁሉ በግለ ሰቦች የባለቤትነት ይዞታ ሥር ያለ ነው፡፡

የክርስቶስ ኢየሱስ ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን ባለቤትነት የሚተዳደረውና በሦስተኛነት ወደ ሥርጭት የገባው ሲጄ ቲቪ (CJ TV) ነው፡፡ ይህ የቴሌቪዥን አገልግሎት ከላይ ከተጠቀሱት ከኤልሻዳይ እና ከሳሌም የተለየ የዝግጅት ይዘት ያለው ነው፡፡ ጣቢያው በዋናነት የሚያስተላልፈው በየክርስቶስ ኢየሱስ ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ላይ የሚደረጉ ማናቸውንም ዐይነት ክንውኖች ነው፡፡ በተለይም፣ በነቢይ ታምራት ታረቀኝ የተደረጉ ትምህርቶች፣ ስብከቶች፣ ነጻ የማውጣት አገልግሎቶችና ትንቢታዊ መልእክቶች ይተላለፉበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቃለ መጠይቆችና የመዝሙር ክሊፖችን ለሥርጭት የሚቀርቡ ዝግጅቶች ናቸው፡፡

ሆሊ ቲቪ በሆሊ ኢንተርናሽናል ቤተ ክርስቲያን ባለቤትነት በቅርቡ ለሥርጭት የበቃ የቴሌቪዥን ጣቢያ ነው፡፡ ይህ ጣቢያ በይዘት አቀራረቡ ከሲጄ ቲቪ ጋ ተመሳሳይ ሲሆን፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን የጉባኤ አገልግሎት ትኩረት ያደረገ ሥርጭት ያለው ጣቢያ ነው፡፡ በተለይም ነቢይ በላይ ሽፈራው በመድረክ ላይ የሚያደርጓቸውን አገልግሎቶች ሰፊ ሽፋን በመስጠት ለተመልካቾች ያቀርባል፡፡ ከዚህ ባሻገር ቃለ መጠይቆች እና የመዝሙር ክሊፖች ጣቢያው ለሥርጭት ከሚያቀርባቸው ዐይነተ ውሱን ዝግጅቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የቲቪው አገልግሎት የገጠመው ችግር

በኢትዮጵያ ያለው የክርስቲያን መገናኛ ብዙኀን፣ በተለይም የቴሌቪዥን አገልግሎቱ ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዐይነት አዎንታዊ ገጽታ ብቻ የለውም፡፡ የጠቀሜታውን ያህል እየፈጸማቸው ያሉ ስሕተቶችና ጥፋቶች እጅግ የሚያሳስባቸው ወገኖች ቁጥር ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ የእነዚህ ወገኖች ጭንቀትና ሥጋት ተራ ሥጋት ሳይሆን፣ በተጨባጭ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል እንደ ሆነ በማመን ላይ የተመሠረተ ጭምር ነው፡፡

“ʻአሁን ያሉት የክርስቲያን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መኖራቸው እየጠቀመን ነው ወይስ እየጎዳን?’ ስል ብዙ ጊዜ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡” የሚለው መርዓዊ ንጉሤ (መጋቢ) ነው፡፡ “በርግጥ ብዙ ሰዎች በዚያ እየተጠቀሙ፣ ጌታ ኢየሱስን እያገኙ፣ በተለያየ መንገድ ወደ እውነት እየመጡ እንደ ሆነ እንሰማለን፡፡ ከዚህ ተነሥቼ ታዲያ ብርታቱም ድካሙም እኩል ሥፍራ እንደሚይዝ እገምታለሁ” የሚለው መጋቢው፣ ነገር ግን የሚሰሙት መልካም ዜናዎች ብቻ ሳይሆን “የማንሰማቸው በጣም ብዙ ኪሳራና ችግሮችም አሉ፡፡” ይላል፡፡ “ሲጀመር የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የመድረክ ወይም የጉባኤ ሥርዐቷ በችግሮች የተሞላ ነው፡፡ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንኳን ʻአንዳንዶቹ ነገሮች በአደባባይ መደረግ አለባቸው ወይ?’ ተብለው ጥያቄ ላይ የሚወድቁ ናቸው፡፡ በጣም የሚያሳዝነውና የሚያስደነግጠው ነገር ለጥቂት ሰዎች የሚያሳቅቀው የመድረክ አገልግሎት በቴሌቪዥን ለሚሊዮኖች ይቀርባል፡፡” ሲል አፍራሽ ጎኑን ያሳያል፡፡ ለዚህም እንደ አስረጅ አድርጎ የሚያቀርበው በየጊዜው ወንጌላውያን ካልሆኑ ወዳጆቹ የሚመጣበትን ወቀሳና ስሞታ ነው፡፡ “ʻምንድን ነው ግን እንዲህ የሚያደርጋችሁ?’ ይሉኛል፡፡ ምን ብዬ ልመልስላቸው? ብዙ ጊዜ ዝም ነው የምለው፡፡ እናም ስቀውብኝ ተሳልቀውብኝ ይሄዳሉ፡፡” ሲል በኀዘኔታ ቁጭቱን ይገልጻል፡፡

ወ/ዊ ያሬድ በበኩሉ ይህ የቴሌቪዥን አገልግሎት በቂ ዝግጅት ሳይደረግበት እንደ መጣ የድንገቴ ዕድል አድርጎ ይመለከተዋል፡፡ “በደንብ ሳንዘጋጅባቸው እንደ ደራሽ ውሃ ከመጡብን ነገሮች አንዱ ይህ የቴሌቪዥን አገልግሎት ነው፡፡” የሚለው ወ/ዊ ያሬድ፣ “በመሠረቱ የቴሌቪዥን አገልግሎት ትልቅ የሙያ ዘርፍ እንደ መሆኑ ከፍተኛ የሆነ ዝግጅትን ይጠይቃል፤ በቴክኒክም ሆነ በመልእክት አኳያ፡፡ ይሁን እንጂ ለዚህ ተገቢው ትኩረት ባለመደረጉ ቅይጥ የሆነ ነገር ነው የሆነው፡፡ መልእክት ያላቸው ድፍረት ግን የሌላቸው፤ ድፍረት ያላቸው በአንጻሩ መልእክት የሌላቸው” ሰዎች መታያ መድረክ እየሆነ መምጣቱን አበክሮ ይገልጻል፡፡

የሚዲያ አገልግሎቱ በሚፈለገው ደረጃና ጥራት እንዳይሄድ ዕንቅፋት ከሚፈጥሩ መሠረታዊ ችግሮች መካከል የሙያ ሥነ ምግባር ጉድለት ትልቁን ሥፍራ የሚወስድ ነው፡፡ በመሠረቱ የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ጉድለቶች ሊከሰቱ ከሚችሉባቸው ምክንያቶች መካከል የተቋማዊ አደረጃጀት ዕጦትና ሙያው የሚጠይቀውን ክኅሎት አለማዳበር ቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዙ ናቸው፡፡

የተቋማዊ አደረጃጀት ዕጦት

የተቋማዊ አደረጃጀት ዕጦት በክርስቲያን የሚዲያ ተቋማት ላይ ብቻ የሚታይ ችግር አይደለም፤ በአገር አቀፍ ደረጃም እንኳ ብዙ ሥራዎች ተቋማዊነትን ተላብሰው አይተገበሩም፡፡ አንድ የመገናኛ ብዙኀን ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዲችል እና ዘለቄታ ያለው በጎ ተጽእኖ እንዲያሳድር የተቋማዊ አደረጃጀት አስፈላጊነት የግድ ይሆናል፡፡ በተቋማዊ አደረጃጀት ውስጥ ጉልሕ ሥፍራን ከሚያዙት መካከል ኤዲቶሪያል ቀዳሚው ነው፡፡ ሌሎቹን የተቋማዊነት መለኪያዎች ለጊዜው ትተን በኤዲቶሪያል ላይ ብቻ በማተኮር ʻዋና ተደራሽነታቸውን የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞችን ያደረጉ የሚዲያ ተቋማት ተገቢ የሆነ ድርጅታዊ ቁመና አላቸው ወይ?’ ብለን ብንጠይቅ መልሱ በአብዛኛው አጥጋቢ አይሆንም፡፡ ሌላው ይቅርና ምን ያህሎቹ የሚዲያ ተቋማት ክርስቲያናዊ መሠረቱን ያልለቀቀና ሙያው የሚጠይቀውን ጭብጥ የተጎናጸፈ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ እንዳላቸው በርግጠኝነት መናገር ያስቸግራል፡፡

አንድ የክርስቲያን ሚዲያ ኤዲቶሪያል፣ በታላቁ ተልእኮ ላይ የተመሠረተ፣ ማለትም የታላቁ ተልእኮ ጭብጦችን ያስተነተነ እና ለወንጌል እውነት ተቆርቋሪ የሆነ እንዲሁም ለሙያው ሥነ ምግባር ከበሬታን የሚሰጥ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ይኸው አቋሙም በሚሠራቸው በእያንዳንዱ ተግባራት ላይ ሊንጸባረቅ የሚችል ነው፡፡ ተጠያቂ እና ግልጽ የሆነ አሠራር (በግለ ሰቦች ይዞታ ሥር ቢሆንም እንኳ) እንዲኖረው መደረጉ፣ ለሚያስተላልፈው መልእክት ይዘት እጅግ መጨነቁና መጠንቀቁ፣ ሙያው ለሚጠይቀው ቅርፅ/አቀራረብ መጠበቡና ሌሎችም የጥሩ ኤዲቶሪያል ገጸ በረከቶች ናቸው፡፡

ኮምፓሽን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን ስፔሻሊስት የሆነውና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን ት/ቤት በብሮድካስት ጋዜጠኝነት ትምህርቱን የተከታተለው ናትናኤል አሰፋ ለችግሮቹ አንደኛው ምክንያት ይኸው ተገቢ የሆነው የኤዲቶሪያል ፖሊሲ ዕጦት እንደ ሆነ ያሠምርበታል፡፡ “አንድ ሚዲያ ግልጽ የሆነ የኤዲቶሪያል ፖሊሲ ሊኖረው ይገባል፡፡ ሊደረጉ የሚገቡና ሊደረጉ የማይገቡ ተብለው የሚቀመጡ ነገሮች መኖር አለባቸው፡፡ እዚህ ጋ ችግር ካለ ሥራውን በተገቢው መንገድ ለመሥራት በጣም አዳጋች ነው የሚሆነው፡፡” ይላል፡፡ ወ/ዊ ያሬድ ጥላሁንም ይህንኑ ክፍተት እንደታዘቡ ይናገራሉ፤ “በአጠቃላይ የቴሌቪዥን አገልግሎቱ ጠንካራ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ የለውም፤ ከአብያተ ክርስቲያናት የተውጣጡ ግለ ሰቦች የሚመክሩበት ኤዲቶሪያል ቦርድም ያለ አይመስለኝም፡፡” ብለዋል፡፡

የሙያ ክኅሎት ዕጦት

ጋዜጠኝነት ራሱን የቻለ የሙያ መስክ (ዲሲፕሊን) ነው፡፡ ይልቁንም ደግሞ አሁን ባለንበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን የጋዜጠኝነት ሚና ጎልቶ እየወጣ እንደ ሆነ በመስኩ ላይ ምርምር የሚያደርጉ ይናገራሉ፡፡ እጅግ በሠለጠኑት አገራት ሚዲያው በአንድ አገር መንግሥት ውስጥ ቁልፍ ድርሻ ከሚጫወቱ ተቋማት መካከል የሚጠቀስ መሆን ችሏል፡፡ ይህን ግዙፍ ተቋም የሚዘውሩ ግለ ሰቦች ደግሞ ዘመኑ የሚጠይቀውን ሙያዊ ፍልስፍና፣ ክኅሎት እንዲሁም የሥነ ምግባር ደንቦች ማወቅ ወይም ለዚህ ራሳቸውን ማዘጋጀት ይጠብቅባቸዋል፡፡ ‘አንድ ሰው ጥሩ ጋዜጠኛ ለመሆን የግድ በጋዜጠኝነት ት/ቤት ውስጥ ገብቶ መማር አለበት ወይ?’ የሚለው አነጋጋሪ ቢሆንም፣ ሁሉም ባለሙያዎች እንደሚስማሙበት የጋዜጠኝነት ሙያ ራሱን የቻለ የሥራ መለኪያዎችና ሕግጋት ያሉት ነው፡፡ በመሆኑም፣ በብዙኀን መገናኛ ሙያ ላይ የተሰማራ ሰው መሠረታውያን የሚባሉትን የጋዜጠኝነት ሙያ ግዴታዎች ማወቅ ይጠበቅበታል፡፡ እነዚህ መሠረታውያን የጋዜጠኝነት መለኪያዎች ደግሞ በትምህርት/በሥልጠና እና/ወይም በተገቢው ልምድ መካበት የሚችሉ ናቸው፡፡

በተመሳሳይም፣ በኢትዮጵያ ያሉ የክርስቲያን ሚዲያ ተቋማት የዚህ ዕጦት ሰለባ ሆነው ይታያሉ፡፡ የፕሮፌሽናሊዝም  ዕጦት ከሚፈጠርባቸው ምክንያቶች መካከል፣ በሥልጠናው አስፈላጊነት ላይ ግልጽ የሆነ ግንዛቤ አለማዳበር፣ በቂ የማሠልጠኛ ተቋሟት አለመኖር እንዲሁም የሠለጠኑና ልምዱን ያካበቱ ባለሙያዎች በቅርብ መታጣት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የዚህ አገር አቀፋዊ ችግር ተጋሪ የሆነው የክርስቲያን ሚዲያው ራሱን ከፕሮፌሽናሊዝም ዕጦት የሚያስጥልበት ሌላ አማራጭ ስላልነበረው የችግሩ ሰለባ ሆኗል፡፡

አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዲችል በሙያው የሠለጠነ የሰው ኀይል የግድ ያስፈልገዋል፡፡ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ያሉ የክርስቲያን ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ይህንን የሚያሟሉ እንዳልሆኑ ይነገራል፡፡ ናትናኤል አሰፋም ይህኑን መታዘቡን ነው የሚገልጸው፤ “እኔ ከሥራዬ ጋር በተያያዘ የሚዲያ ሽፋን እንዲሰጡን የምንጋብዛቸው ጣቢያዎች አሉ፡፡ ያዘጋጀነው ዝግጅት (event) ላይ እንዲገኙ ነው የምንጠራቸው፤ ነገር ግን ሲመጡ የቪዲዮም ሆነ የፎቶ ካሜራ ሳይዙ ይመጣሉ፡፡ በአንጻሩ አንተ እንድትሰጣቸው ይጠይቁሃል፡፡” ሲል አሠራራቸውን ይተቻል፡፡ አያይዞም ምንም እንኳን አንድ ጋዜጠኛ በቦታው ራሱ ተገኝቶ መዘገቡ የሙያው ሥነ ምግባር የሚጠይቀው ቢሆንም፣ ያልተገኙበት ዝግጅት ላይ ዘገባ ተጽፎ እንዲሰጣቸው የሚጠይቁበትና የተሰጣቸውን ያለምንም አርትኦትና ተጨማሪ ግብዓት እንደ ወረደ የሚያቀርቡበት ጊዜም እንዳለ ይናገራል፡፡ “እኔ ይህንን እንደ አንድ ትልቅ ችግር ነው የማየው” የሚለው ናትናኤል፣ የዚህ ሰበብም ጣቢያዎቹ ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ ባለሙያዎች መጠቀም ስለማይፈልጉ ወይም አቅሙ ስለሌላቸው ሊሆን እንደሚችልም ይገምታል፡፡

ከዚህ ባለፈ የቴክኒክ ጉዳዮችም የሙያ ዕጦት በጉልሕ የሚታይባቸው የድክመቱ አካል ናቸው፡፡ የድምፅና የምስል ጥራት እንዲሁም የስቱዲዮ አደረጃጀት በሚፈለገው ደረጃ ላይ አለመሆኑ ከፍተኛ ወቀሳ የሚቀርብበት ጉዳይ ነው፡፡ ስብከቶች ወይም ትምህርቶች እጅግ ያነሰ ወይም የበዛ ድምፅ ይዘው ይታያሉ፤ የምስል ውሕደቱ የተምታታና ከደረጃው በታች ሆኖ ይቀርባል፤ በቂ ብርሃንና ውብ ድባብ በሌለው ስቱዲዮ ውስጥ ፕሮግራሞች ይቀረጻሉ፣ ወዘተ.፡፡ በአጠቃላይ አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሊያሟላ የሚገባው ዘመናዊ ስቱዲዮ እንዲሁም በቂ የሠለጠነ የሰው ኀይል አደረጃጀት የሌላቸው ናቸው ለማለት ያስደፍራል፡፡

ይህንን የጥራት ችግር ለመቅረፍ የራሳቸውን ርምጃ እንደወሰዱ የሚናገሩት ወ/ዊ ያሬድ ናቸው፡፡ ለዚህም የራሳቸውን ስቱዲዮ በከፍተኛ ወጪ የገነቡ ሲሆን፣ ትምህርቶቻቸውን በራሳቸው ስቱዲዮ ውስጥ እያዘጋጁ እንደሚልኩ ነው የጠቆሙት፡፡ “ይህንን የምናደርገው የጥራት ጉዳይ ስለሚያስጨንቀን ነው” ይላሉ ወ/ዊ ያሬድ፡፡

አንገት ከሚያስደፉን ነገሮች መካከል

የተቋማዊነት ዕጦትና የሙያ ክኅሎት ጉድለት በአንድ በብዙኀን መገናኛ ሥራ ላይ በተሰማራ አካል ውስጥ በሚከሰትበት ጊዜ፣ የትኛውንም መልእክት/ትምህርት ያለማጥለያ ስለሚያስተላልፍ ዝብርቅርቅ የሆነ መልእክት እንዲቀርብ ያደርጋል፡፡ አንድ ተመልካች እንዳለው፣ “የጨረባ ተዝካር” ይመስል ውል የሌላቸው ፕሮግራሞች እዚህም እዚያም፣ አሁንም በኋላም ለተመልካቾች ይቀርባል፡፡ ታዲያ፣ ‘የኢትዮጵያ የወንጌላውያን አማኞችን ትኩረት ያደረጉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በኩል እየተፈጠሩ ያሉ ተጨባጭ ችግሮች ምንድን ናቸው?’ የሚል ጥያቄ መነሣቱ አይቀርም፡፡ ለዚህ ማሳያ ሊሆኑ የሚችሉ ጥቂት አስረጆች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

የስሕተት ትምህርት እና ልምምድ ማስተላለፊያ መሆኑ

በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ፈተና ከሆኑት መካከል የስሕተት ትምህርትና እንግዳ ልምምድ መሆናቸው በብዙዎች ዘንድ የታመነ ሆኗል፡፡ ባለፉት ዓመታት የኑፋቄ ትምህርቶችና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይዘት የጎደላቸው ልምምዶች የአብያተ ክርስቲያናት ደጆችን ሲያንኳኩ ከርመዋል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ላይም ተሳክቶላቸው ደጅ አስከፍተው ወደ ውስጥ መዝለቅ ችለው ነበር፡፡ ይህም እንኳ ሆኖ ከሞላ ጎደል በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ተመሳሳይ የወንጌል መልእክት ይተላለፍ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን፣ በተለይም ከኤሌክትሮኒክ ሚዲያው መምጣት ጋር ተያይዞ የስሕተት ትምህርቶቹ የቤተ ክርስቲያንን ደጅ ከማንኳኳት ይልቅ በቴክኖሎጂው ድጋፍ በቀጥታ ወደ አማኞች ቤት መዝለቅ ችለዋል፡፡ በዚህም አማኞች የትም ሳይሄዱ፣ ቤታቸው ቁጭ ብለው ከትምህርቶቹ ጋር የመተዋወቅ “ዕድሉ” ተፈጠረላቸው፡፡

“በትምህርት ጉዳዮች ላይ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ችግር እየሆኑ ነው፡፡” የሚለው መጋቢ መርዓዊ ንጉሤ ነው፡፡ “አንዳንድ ጊዜ በጣም ጥሩ ነገር ትሰማና ጎሽ እንዳልክ ቀጥሎ የሚመጣው ነገር በጣም ችግር ያለበት ሆኖ ታገኘዋለህ፡፡ አንዳንዶቹ ትምህርቶች በጣም አስደንጋጭ ናቸው፡፡ የአብያተ ክርስቲያናትን እምነት የሚጻረሩ፣ ʻውጕዝ’ ተብለው፣ ʻከእነርሱ ጋር ኅብረት የለንም’ ተብለው የተወገዙትን ትምህርቶች እንሰማለን፡፡ አጥፊ የሆነ፣ ዐውዳሚ የሆነ፣ ከሕይወት የሚያጠፋ ትምህርቶችን እናያለን፡፡” ይላል፡፡

እንግዲህ ‘የአንድ ክርስቲያናዊ ሚዲያ ኀላፊነት የት ድረስ ነው?̕ የሚለው ጥያቄ የሚነሣው እዚህ ላይ ነው፡፡ ገንዘብ ለከፈለ ሁሉ ሽፋን የሚሰጡ የክርስቲያን ሚዲያ ተቋማት ባሉበት ሁኔታ ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ የሚሆን ጤነኛ ትምህርት በወጥነት ይተላለፋል ማለት እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ በቴሌቪዥን የሚተላለፉ ሥርጭቶች “የነጻ ገበያ መርሕን” የሚከተሉ ይመስል ራሳቸውን ያለ ገደብ ለሁሉ ክፍት አድርገው ማቅረባቸው የዚሁ የኀላፊነት ጉድለት ማሳያ አድርገው የሚወስዱ ጥቂቶች አይደሉም፡፡

እንደ መጋቢ መርዓዊ ከሆነ የቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ ካለባቸው የገንዘብ ችግር የተነሣ ተቀባይነት የሌላቸው ሰዎችን ለመቀበል ሳይገደዱ አልቀሩም፡፡ “የቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ ለሚያስተላልፉበት የአየር ሰዓት የሚከፍሉት ገንዘብ ቀላል አይደለም፤ ስለዚህ ያንን ገንዘብ ለመክፈል የሚችሉት በአብያተ ክርስቲያናት ተቀባይነት የሌላቸውን ሰዎች በመቀበል ነው፡፡ ፈጥነው የደረሱላቸው ደግሞ እነዚሁ በትምህርታቸው ተቀባይነት የሌላቸው ሰዎች ናቸው፤ በጣም በተቸገሩበት ጊዜ አብረዋቸው የነበሩት እነሱ ናቸው፡፡ ስለሆነም፣ የገንዘብ ችግራቸው ወደዛ የመራቸው ይመስለኛል፡፡” ሲል ምክንያታቸውን ለመመዘን ይሞክራል፡፡ የሳሌም የአዲስ አበባ ተወካይ የሆነው አቶ መስፍንም የጣቢያዎቹን ሕልውና የሚፈታተነው ይኸው የገንዘብ ችግር መሆኑን ይስማሙበታል፡፡

ይህም ቢሆን እንኳ፣ አንድ ʻየክርስቲያን ሚዲያ ነኝ’ የሚል አካል ሁሉን ትምህርት እንደ ቡፌ በአንድ ጠረጴዛ ላይ ዘርግቶ ‘የፈለጋችሁትን ምረጡና ብሉ’ ማለቱ የኀላፊነት ደረጃውን ከግምት ውስጥ ማስገባቱ አይቀርም፡፡ ወ/ዊ ያሬድ ጥላሁንም ኀላፊነትን በተመለከተ አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ፡፡ “ሚዲያውን የያዙ ወገኖች እጅግ ትልቅ ኀይል በእጃቸው ላይ እንዳለ ማወቅ አለባቸው፤ ዐውቀውም በብዙ ፍርሃት ሊይዙት ይገባል፡፡ ወንጌል ተጣሞ ከሚሰበክ ባይሰበክ እንደሚሻል” ማሰብ ተገቢ መሆኑንም ያሠምሩበታል፡፡

የልዕለ ሰብ ግንባታ መድረክ መሆኑ

ግለ ሰቦችን ያለቅጥ የማግነን ችግር በእኛ አገር የተጀመረ አይደለም፡፡ እንደውም ትልቅ ወቀሳ የሚቀርበው በአሜሪካ እና በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት ያሉ መንፈሳዊ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ ነው፡፡ በእኛም አገር አገልግሎት የሚሰጡ ጣቢያዎች በግለ ሰቦች ሰብእና ወይም አገልግሎት ላይ ከፍተኛ ትኩረት የሚያደርጉ ከመሆናቸው የተነሣ የግለ ሰቡ ማንነት ከሚያስተላልፈው መልእክት በላይ ገዝፎ ሊታይ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ሆኗል፡፡ ክርስቲያናዊ ትሕትና የማይታይባቸው ማለትም፣ ያለ እነርሱ እግዚአብሔር የማይሠራ የሚመስላቸው እና እነርሱ ወይም የእነርሱ አገልግሎት ከሌሎቹ የተሻለ ብቻ ሳይሆን፣ ብቸኛው እንደ ሆነ አድርገው የሚያምኑ ኢትዮጵያውያን ሰባኪዎችና አስተማሪዎች በቴሌቪዥን ጣቢያዎች እየታዩ ናቸው፡፡

ዶ/ር ንጉሤ ተፈራ እነዚህን ስለመሰሉት ሲጽፉ፣ “አንዳንዶቹ ለእግዚአብሔር ክብር የሚዘጋጁ ሳይሆን ለንግድና ለትርፍ ወይም የራስን ዝና በማስተዋወቅ ለመጠቀም ታስበው የተቋቋሙ መሆናቸውን ሥራቸው ይመሰክራል፡፡” ይላሉ፡፡ ይህን የመሰለው አካሄድ በጊዜ ሂደት ወደ ጣዖተ ሰብ (personality cult) የሚመራ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የየትኛውም የክርስቲያን ሚዲያ ትኩረት የምስራቹ ቃል ለሕዝቦች መድረስ እና የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን መታነጽ መሆን አለበት፡፡ ከዚህ ባለፈ ሰዎችን ለማግነን ወይም የጥቂቶችን ጥቅም ለማስጠበቅ አገልገሎት ላይ የሚውል መንፈሳዊ ሚዲያ ክርስቲያናዊ መሠረቱን ያጣል፡፡

ይኸው ችግር ሳሌም ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክን የገጠመው እንደ ሆነ አቶ መስፍን ሳይሸሽጉ ይናገራሉ፤ “የሰዎችን ጸጋ ስትገልጽ የሰዎች ጠባይ (character) ብዙ አይታወቅም፤ ጸጋው ነው እንጂ የሚታወቀው ጠባዩ አይታወቅም፡፡ በዚህ ምክንያት የሚመጡ አንዳንድ ነገሮች አሉ፡፡ በእነዚያ ሰዎች ጠባይ ማነስ፣ ሳሌምየግለ ሰቦቹን ጉድለት እንደ ደገፈ አድርገው የሚያስቡ ሰዎች አሉ፡፡” ይላሉ፡፡ አክለውም፣ “አንዳንድ ሰዎች ለምሳሌ በአገልግሎታቸው ተጽእኖ አምጪዎች ናቸው፣ ነገር ግን በባሕርይ በጣም የሚያስቸግር ነገር ኖሯቸው ከሳሌም ጋር ተደባልቆ ዋጋ የከፈልንባቸው ጊዜያት አሉ፡፡ … በዋናነት የምንሠራው ከአብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ጋር ነው፡፡ … ከዚህም ተነሥተን የእያንዳንዱን ሰው የእምነት አቋም እንጠይቃለን፡፡ የእምነት አቋማቸውን ሳይገልጹ ወደ አገልግሎት አይወጡም፡፡ መጀመሪያ ላይ ግን ይህንን ሁሉ አንጠይቅም ነበር፤ አሁን ግን ግማሾቹ የእምነት አቋማቸውን እያመጡ እየታየ፣ እየተመዘነ ነው ያለው፡፡” ሲሉ የተፈጠረውን ስሕተት ለማረም ጣቢያው እያደረገ ያለውን ጥረት ይገልጻሉ፡፡

አማኝ ማኅበረ ሰቡ ምንም እንኳን ከዚህ በተቃራኒው የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዕሴት ቢኖረውም፣ በብዙኀን መገናኛ ላይ የሚታዩ ሰዎች የወካይነት ሚና ሊጫወቱ የሚችሉበት አጋጣሚው መኖሩ አይቀርም፡፡ ታዲያ ከላይ የተጠቀሱ ዐይነት ግለ ሰቦች የሚያሳዩዋቸው አሉታዊ ተግባራት አማኝ ማኅበረ ሰቡ በአጠቃላይ ከኅብረተ ሰቡ ጋር በሚኖረው መስተጋብር አሉታዊ መልክ መከሰቱ አይቀሬ ይሆናል፡፡ ከዚህ የተነሣ አማኞች ለኅብረተ ሰቡ በሚያበሥሩት የወንጌል እውነት ተዓማኒነት ላይ የራሱን ጥላ ሊያጠላበት ይችላል የሚል ብርቱ ሥጋት አለ፡፡

ብዙኀን መገናኛ ሊተላለፉ የማይገባቸው ኹነቶች መቅረባቸው

ምእመናን ለአምልኮ ሲሰበሰቡ ሥርዐት በተሞላው መልኩ ሊሆን እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያዛል፡፡ አንዳንዶቹ መንፈሳዊ ልምምዶች ከተለመደው/ተፈጥሯዊ ከሆነው የተግባቦት ይዘት ወጣ ያሉ በመሆናቸው ልዩ አትኩሮት ተሰጥቶባቸው እንዴት ባለ መንገድ ተግባራዊ መደረግ እንዳለባቸው በግለጽ ተነግሯል (1ቆሮ. 14)፡፡ እነዚህ ልምምዶች በአብዛኛው “የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች” የሚባሉትን በመተግበር ላይ የሚስተዋሉ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ግልጽ ቢሆንም፣ በአገራችን ክርስትና ለልምምዶች የሚሰጠው ስፍራ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሣ መጽሐፍ ቅዱሳዊው መርሕ ብዙ ጊዜ ትኩረት ሲነፈገው ይስተዋላል፡፡

በቤተ ክርስቲያን የምንታዘበው ይህን መሰሉ መንፈሳዊ ልምምድ ሚሊዮኖች ሊመለከቱት በሚችሉበት ቴሌቪዥን ጣቢያ ያለ በቂ ጥንቃቄና እርማት ሲተላለፍ ተደጋግሞ እየታየ ነው፡፡ በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኖቻችን ስንመለከት የምንደነግጥባቸው ልምምዶች በብዙኀን መገናኛ ሲተላለፉ ማየት ምን ያህል የሚያሸማቅቅ መሆኑን መገመት አያዳግትም፡፡ ተገቢው ትርጓሜ የማይሰጥባቸው “ረጅም የልሣን ጸሎቶች”፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ “የትንቢት ንግርቶች”፣ “መንፈሳዊ ሣቅ” የሚባል የአደባባይ ረብሻ፣ አካባቢ የሚያውክ ብርቱ ጩኸት እና እዚህ ለመጥቀስ የሚያስቸግሩ ሌሎች በርካታ ልምምዶች በቴሌቪዥን መስኮቶቻችን በተደጋጋሚ የምንመለከታቸው ኹነቶች ናቸው፡፡

እንዲህ ያለው ዐልቦ ሥርዐት ቢያንስ ሁለት ጉዳቶች ያስከትላል፡፡ የመጀመሪያው፤ አማኞች የከበሩትን የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች እንዲያቃልሉና እውነተኛውንም እንዲጠራጠሩ ማድረጉ ነው፡፡ ሁለተኛው በክርስቶስ ወንጌል የማያምኑ ወይም በቂ ግንዛቤ የሌላቸው ሰዎች ከሚታዩት ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድርጊቶች የተነሣ ለምስራቹ ቃልም ሆነ ለአማኝ ማኅበረ ሰቡ የሚኖራቸው አመለካከት እጅግ አሉታዊ እንዲሆን ማድረጉ ነው፡፡ በሌለ አገላለጽ፣ ይህን መሰል ልምምዶች በብዙኀን መገናኛ መተላለፋቸው ለወንጌል እንቅፋት የመሆኑ አጋጣሚ ይሰፋል፡፡ የወንጌልን ቃል ላልሰሙ ዐይነተኛ መሣሪያ ነው የተባለለት የብዙኀን መገናኛ፣ በአግባቡ ካልተያዘ ያንኑ ያህል አጥፊነቱ ወደር የማይገኝለት መሆኑ አይቀርም፡፡

ለ ምሥጢርን አለማክበር

በተደጋጋሚ እንደምናየው ሰዎች ፈቃደኛ ባልሆኑበት መንገድ ምስላቸው በቴሌቪዥን ይተላለፋል፡፡ የአንዳንዶቹ ምስል “ከአጋንነት እስራት ነጻ ሲወጡ” ወይም “በመንፈስ ኀይል” ተነክተው ሲወድቁ (አንዳንድ ጊዜም እርቃናቸው ሳይሸፈን) ይታያል፡፡ ሰዎች ‘እግዚአብሔር አደረገልን’ ለሚሉት ተኣምር ምስክርነታቸውን በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ወይም በመለስተኛ ኅብረቶች ደረጃ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ እነዚሁ ሰዎች ግን፣ በተመሳሳይ ምስላቸው በቴሌቪዥን ቀርቦ፣ ድምፃቸው ተቀርጾ ‘ምስጢሬ’ ያሉት የግል ጉዳያቸው ለሕዝብ እንዲቀርብ ላይፈልጉ ይችላሉ፡፡ በመሠረቱ ይህ ተፈጥሯዊ እና ሕጋዊ መብታቸው ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ፣ በቴሌቪዥን መስኮት መቅረባቸው በማኅበራዊ መስተጋብራቸው ላይ ሊያሳድር የሚችለው ጫና ከግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ነው ሰዎች ለብዙኀን መገናኛ ከመቅረባቸው በፊት ፈቃደኝነታቸው መረጋገጥ የሚኖርበት፡፡

በአንጻሩ ግን፣ ይህ የሰዎች መሠረታዊ መብት ሳይጠበቅ ለሌሎች “የአገልግሎት ትክክለኝነት” ማሳያ ተደርጎ በቴሌቪዥን የሚቀርብበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ የአንድን አገልጋይ እውነተኝነት ለማሳየት የሌሎች ሰዎችን ገመና በአደባባይ ማቅረብ ከማስታወቂያ ሥራ የሚለይ አይሆንም፡፡ ይህ ደግሞ የሞራልም ሆነ የሕግ ተጠያቂነትን ያመጣል፡፡ ምስክርነታቸውን በአደባባይ የሰጡ ሰዎች ይቅርና በጉባኤ የተካፈሉ ሰዎች ምስል በቴሌቪዥን መተላለፉ ጥያቄ ሊያስነሣ የሚችል ነው፡፡ ለዚህ ነው ፕሮግራሙ በቴሌቪዥን ከመተላለፉ በፊት ጉባኤውን ቀድሞ ማሳወቅ ተገቢና ትክከለኛ አካሄድ የሚሆነው፡፡

“እነዚህ ሰዎች ሕይወት አላቸው፤ ኑሮ የሚባል ነገር እኮ አለ፤ ጎረቤቶች አሏቸው፤ ነገ ጠዋት እዛ ጎረቤት መካከል እንዴት ነው የሚመላለሱት፤ እንዴት ነው የሚያወሩት?” ይላል መጋቢ መርዓዊ ንጉሤ ነው፡፡ ናትናኤል አሰፋም በበኩሉ ለሰዎች ማኅበራዊ ሕይወትና ግላዊ መብት ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ ያስገነዝባል፤ “በመሠረቱ፣ ሰዎቹ ፎቶ ሲነሡም ሆነ፣ ቪዲዮ ሲቀረጹ ፈቃደኝነታቸው መጠየቅ ይኖርበታል፡፡” የሚለው ናትናኤል፣ “አያድርገውና ሰዎች ወደ ፍርድ ቤት ቢያመሩ ተቋሙን ትልቅ ዋጋ ነው የሚያስከፍለው፡፡” ሲል ጉዳዩ የት ድረስ ሊደርስ እንደሚችል ይጠቁማል፡፡

እንደ መፍትሔ

እንግዲህ ከላይ የተጠቀሱት ብቻ ሳይሆኑ ከዚህ የሚልቁ የብዙኅን መገናኛ የሥራ ዝንፈቶች በተለይ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው (የቴሌቪዥን አገልግሎት በዋናነት) የሚታዩ ናቸው፡፡ እስካሁን የተስተዋሉት ጉድለቶች ያመጡት ጉዳት በቀላሉ የሚታይ ባይሆንም፣ አሁንም አልረፈደም ማለት ይቻላል፡፡ በመሆኑም፣ በቀዳሚነት የሚዲያ ተቋማቱ፣ ቀጥሎም የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት፣ አጋር የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶች፣ የሥነ መለኮት ተቋማትና በአማኝ ማኅበረ ሰቡ ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ሌሎች ተቋማት እንዲያጤኑት በሚል ከዚህ ውስን የመፍትሔ ርምጃዎች ተሰንዝረዋል፡፡

ተቋማዊነትን ማጎልበት

በኢትዮጵያ ያሉ ወይም ኢትዮጵያውያንን ትኩረት ያደረጉ የክርስቲያን መገናኛ ብዙኀን ለተቋማዊነት ቅድሚያ ሊሰጡት ይገባል፤ ይህንንም ለማድረግ ሰፊ ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ ሂደትም ዘርፉ የሚጠይቀውን ተቋማዊ አደረጃጀት መገንባት፣ በሙያው ሥነ ምግባርና ክኅሎት የበለጸገ የሰው ኀይል ማዋቀር፣ ዘመኑ የሚጠይቀውን ቁሳቁስ ማሟላት፣ ድርጅታዊ አሠራሩን ግልጽ እና ተጠያቂነትን ማእከል ያደረገ እንዲሆን ማስቻል ይገባል፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን ክርስቲያናዊ ዕሴቶችን ማእከል ላደረጉ የሙያው ሥነ ምግባራት ተገዢ መሆን መቻል ያስፈልጋል፡፡

አብያተ ክርስቲያናት የራሳቸውን ጠንካራ የሚዲያ ተቋማት እንዲገነቡ ማድረግ

የኢትዮጵያ ወንጌላውያ አብያተ ክርስቲያናት የብዙኀን መገናኛ ያለውን ጠቀሜታ በተገቢው መረዳት ያለባቸው ጊዜ ቢኖር አሁን ነው፡፡ “ከእንቅልፍ በመንቃትም” ሚዲያውን በመጠቀም የወንጌል ተልእኳቸውን ለመወጣት ልዩ ትኩረት መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በመሆኑም፣ በቤተ እምነት ደረጃ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት የራሳቸው የሆነ የብዙኀን መገናኛ ተቋም መገንባት የሚኖርባቸው ሲሆን፣ አቅማቸው እንደ ፈቀደም የሚዲያ አገልግሎቶችን ለምእመናን እንዲሁም በአጠቃላይ ለኅብረተ ሰቡ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህም ተገቢውን በጀት መመደብ፣ ሙያው በሚጠይቀው ደረጃ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ማሰባሰብና ምቹ የሥራ ምኅዳር መፍጠር፣ ወዘተ. ያስፈልጋቸዋል፡፡

የክርስቲያን ሚዲያ መማክርት ማቋቋም

የሚዲያ ተቋማት ሥነ ምግባራዊ ግድፈቶችን ለመቆጣጠርና ለማረም እንዲሁም ከውጪ የሚመጣባቸውን አላስፈላጊ ግፊት ለመቋቋም የሚያስችላቸውን ሥራ የሚሠራ የሙያ ማኅበር ማቋቋማቸው የተለመደ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ የክርስቲያን ብዙኀን መገናኛ ተቋማት እና/ወይም ባለሙያዎች ተመሳሳይ ዐላማ ያነገበ የመማክርት ጉባኤ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህም ጉባኤ የሚዲያ ሥራ ሂደትን ከመገምገም አንስሥቶ የሥነ ምግባር ዝንፈት በሚከሰትበት ጊዜ አስቀድሞ የሚወቅስና እርማት እንዲወሰድ ከማድረግ ባለፈ፣ የሙያ አጋሮች የተሻለ ሥራ እንዲሠሩ የሚችሉበትን የክኅሎት ሽግግርና የልምድ ልውውጥ እንዲያገኙ ሁኔታዎችን የሚያመቻች ሊሆን ይችላል፡፡

የትምህርትና የሥልጠና ተቋማትን ማቋቋም

አማኝ ማኅበረ ሰቡ በአገር አቀፍ ደረጃ አሁን ካለው የሕዝብ ቁጥር እና ወደፊት ይኖረዋል ተብሎ ከሚጠበቀው ተጽእኖ አንጻር ያለው የሚዲያ ሽፋን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ በመሆኑም፣ የወደፊቱን ብሩኅ ዕድል (prospect) ታሳቢ ያደረጉና በሙያው የሠለጠነ የሰው ኀይል ማፍራት የሚችሉ የሥልጠና/የትምህርት ተቋማት በዐይነትና በብዛት መስፋፋት ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይም ክርስቲያናዊ ዕሴቶችን መሠረት ያደረጉ የጋዜጠኝነት እንዲሁም የተግባቦት ሥልጠናዎችን የሚሰጡ ትምህርት ቤቶች አስፈላጊነታቸው የግድ ሆኗል፡፡ በመሆኑም፣ አዳዲስ ት/ቤቶችን ለማቋቋም ጥረት ማድረግ፣ ካልሆነም አሁን ባሉት የሥነ መለኮት ተቋማት በኩል ተገቢው ሥልጠና እንዲሰጥ በዘርፉ የትምህርት ክፍል ማዋቀር ያስፈልጋል፡፡

Hintset

ወንድሞችና እኅቶች ተስማምተው በአንድነት ሲኖሩ እንዴት መልካም ነው!

የአንድና የብዙ ጉዳይ የዓለም አፈጣጠር ምሥጢር ነው። የአንድና የብዙ ሁኔታ የብዙ ጠቢባን፣ የብዙ ፈላስፋዎች ጥያቄ ነው። አንዳንዶቹ በአሐዳዊው ላይ ሌሎቹ ደግሞ በብዙው ላይ ያተኩራሉ። ሆኖም ብዝኃነትን ያለ ኅብረት፣ አንድነትን ያለብዝኃነት ማሰብ ይቻል ይሆን? ብዝኃነት ውበት የሚሆነው መቼ ይሆን? አንድነትስ አስደሳች የሚሆነው መቼ ይሆን? 

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.