[the_ad_group id=”107″]

ወንድሞችና እኅቶች ተስማምተው በአንድነት ሲኖሩ እንዴት መልካም ነው!

የአንድና የብዙ ጉዳይ የዓለም አፈጣጠር ምሥጢር ነው። የአንድና የብዙ ሁኔታ የብዙ ጠቢባን፣ የብዙ ፈላስፋዎች ጥያቄ ነው። አንዳንዶቹ በአሐዳዊው ላይ ሌሎቹ ደግሞ በብዙው ላይ ያተኩራሉ። ሆኖም ብዝኃነትን ያለ ኅብረት፣ አንድነትን ያለ ብዝኃነት ማሰብ ይቻል ይሆን? ብዝኃነት ውበት የሚሆነው መቼ ይሆን? አንድነትስ አስደሳች የሚሆነው መቼ ይሆን?

የአንድና የብዙ ጉዳይ የዓለም አፈጣጠር ምሥጢር ነው።

በደስታም ሆነ በኃዘን ጊዜ፣ በሰላምም ሆነ በጭንቅ ወቅት፣ ተፈጥሮን እየቃኙ ወደ ልብ ጓዳ መግባት ሳይጠቅም አይቀርም። ለአንድና ለብዙ ምሥጢርም ሐይቁን መመለከት፣ የወፎቹን ዝማሬ ማዳመጥ፣ በዕፅዋት፣ በእንስሳትና በሰማዩ ውበት መማረክ ይረዳል። ምክንያቱም ተፈጥሮ ብዝኃነትንም፣ አንድነትንም አጣምራ ይዛላችና። ምን የመሰለ ኅብረ ቀለም! ምን የመሰለ ኅብረ ዜማ! የሷን ምሥጢር ማድነቅና ከእርሷ መማር የሚታክተው የሰው ልጅ ግን ያስተክዛል፤ ያሳዝናል። ሲተባበርና ሲስማማ ድንቅ ተአምር የሚሠራው የሰው ልጅ ለምን ይሆን የሚከፋፈለው? ብዝኃነቱ ነው የሚያጣላው ወይስ ሌላ ምሥጢር ይኖር ይሆን? የሰው ልጅ በጸጥታ ከራሱ ጋር መሟገት፣ ወደ ኅሊናውም ዞር ብሎ እራሱን መጠየቅ ይገባዋል። መፍትሔ የሚገኘው በመረጋጋት፣ በማዳመጥና በማሰላሰል፣ ከውሱኑ እውቀት በላይ ያለውን እውነት በመፈለግ ነው።

ብዝኃነት ያለ ኅብረት አታምርም፤ ብዝኃነት ተብላ መጠራትም አትችልም፣ ወይም አይገባትም። ይልቁንም “አለመተዋወቅ”፣ “መራራቅ” በሚሉ ቃላት ብትገለጽ ይሻላል። አንድነት ያለ ብዝኃነት አንድነት ተብላ ልትጠራ ያስቸግራል። ብዝኃነት የሌላት ወይም ያልነበራት አንድነት ትርጉም የላትም። ከመጀመርያው ወይም ከወዲሁ አንድና አንድ ወጥ ለሆነ ነገር አንድነት የሚባል ቃል ፍች የለውም። ወደ አንድነት ለመምጣትም ሆነ አንድ ለመሆን ቢያንስ ሁለት መሆን ያስፈልጋል። ብዙ መሆንም ያሻል።

ብዝኃነት ያለ ኅብረት አታምርም፤ ብዝኃነት ተብላ መጠራትም አትችልም፣ ወይም አይገባትም። አንድነት ያለብዝኃነት አንድነት ተብላ ልትጠራ ያስቸግራል። ብዝኃነት የሌላት ወይም ያልነበራት አንድነት ትርጉም የላትም።

ብዝኃነት ውበት ሊሆን የሚችለው ከአሐዳዊነት ሲሻገር ነው። ከቃየልና ከአቤል ታሪክ የኤሳውና የያዕቆብ ታሪክ ያስደስታል። የዮሴፍና የወንድሞቹ መጨረሻ ያጽናናል። የቃየልንና የአቤልን ታሪክ ከመድገም የኔልሰን ማንዴላን ራእይ መድገም ይሻላል።

ችቦ በደንብ ደምቆ እንዲያበራ ብዙ እንጨቶች ያስፈልጋሉ። እንጨቶች ኅብረት ሲኖራቸው እሳቱ ይደምቃል። የእሳቱ ውበት ሌሎችን ይሰበስባል፤ ይማርካል! እንጨቶቹ ሲለያዩ ግን እሳቱ ቀስ እያለ ይጠፋል። ብዝኃነት ያለ አንድነት ይበርዳል። አንድነት ያለ ብዝኃነት ያፍናል። ብዝኃነትና አንድነት ሲተቃቀፉና ሲሳሳሙ ደስ ያሰኛል። አንድነትና ተስፋ ሲነግሡ ብዝኃነት ቦታ አይጠብውም፤ ሀብትም አያንስም፤ መካፈልና መተሳሰብ ስላሉ አይርብም። አንድነትና ተስፋ ሲነግሡ ሕይወት ትርጉም ይኖራታል፤ ጊዜም ይበረክታል።

እኔ እኔን ለመሆን እሱ፣ እሷ፣ አንተና አንቺ ታስፈልጉኛላችሁ፤ ያለ አንተ፣ ያለ አንቺ እኔ፣ የውሸት ጣዖት ነው የምሆነው። ያለ አንተና ያለ አንቺ እኔ እራሴን ማወቅ አልችልም። ሰው ሰራሽ መስታወት ስለ ውጫዊ ገጽታዬ ጊዜያዊ መረጃ ሊሰጠኝ ይችላል። አንተና አንቺ ግን ወደ ውስጤ ዘልቄ እንድገባ ታደርጉኛላችሁ። አንተና አንቺ ግን የፈጣሪ ሥራ በመሆኔ የሚገኘውን ጸጋና ሞገስ ታዩልኛላችሁ፣ ታሳዩኛላችሁ። መስታወቱ ሊወደኝ አይችልም። አንተና አንቺ ማፍቀርንና መፈቀርን ታስተምሩኛላችሁ፤ ኀላፊነትን ታለብሱኛላችሁ።

የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት ክርስቶስ ስለ ሰው ልጅ ፍቅር ራሱን አሳልፎ ሰጠ። ወገን ወይም ማኅበር አልለየም። በዚህም ልዩ መልእክት አሰተላለፈ። እጅግ ልዩ መልእክት! ጠላትንም መውደድ። ብዝኃነትን እያከበረ አንድነትን አወደሰ። እንዲሁም የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ማንነትና ስለ አባልነት ድንቅ ትምህርት አስተማረ፤ ብዝኃነትንና አንድነትን ከማንነት ጋር አስተዋወቀ። ብዝኃነትን ሲያከብር አንድነትን አልተወም። አንድነትን ሲያውጅ ብዝኃነትን አልጨፈለቀም። እነኚህን ሁለት እውነቶች እንዴት ማያያዝ እንዲሚቻል ያሳየበትን መንገድ ማጤን ልብ ይሏል። የእሱ መፍትሔ ለብዙ ፈላስፋዎች፣ ለምድር ጠቢባን ምንኛ በጠቀመ። “ማንነቴ በአባልነቴ አይወሰንም፤ ማንነቴ ከአባልነቴ ይበልጣል” አለ።

አይሁዳዊነት፣ ግሪካዊነት፣ ሮማዊነት፣ ወንድነትና ሴትነት የብዝኃነት ማስረጃዎች ናቸው። አይሁዳዊው ልክ እንደ ግሪካዊው፣ ግሪካዊውም እንደ አይሁዳዊ መኖር አያስፈልገውም። እያንዳንዱ የራሱ ውበት አለው። ክርስቶሳዊ ኅብረት ግን የበለጠ ያስውባቸዋል። በግል ከነበራቸው ውበት የበለጠ ውበት ያጎናጽፋቸዋል። ምጡቁ ከወዲሁ የነበረውን አያጠፋውም፤ ይልቁንም ያሳድገዋል፤ ፍጹምም ያደርገዋል። “ማንነቴ አይሁዳዊነቴ ብቻ ነው፣ ግሪካዊነቴ ብቻ ነው” ማለት ማንነትን መወሰን ነው። ያለውን ውበት ማገድ ነው። የሰው ልጅ “እኔ” ሲል ጤነኛ “እኔ” እና ጤነኛ ያልሆነ “እኔ” እንዳለ ማወቅ ያስፈልገዋል። “እኛም” ሲል፣ ጤነኛ “እኛ” እና ወደ ጥፋት የሚወስድ “እኛ” እንዳላ ማጤን ይገባዋል። ከአባልነት የመጠቀ አንድነት ሲኖር ነው ውበትን መቃኘት፣ አንድነትን ማጣጣም፣ ሰላምን ማስፈን፣ ብልጽግናና ማምጣት የሚቻለው።

ጊዜና ቦታ፣ ታሪክና ምድር ለንጹሓን ተበዳዮች ይጮኻሉ። ቃላት ሲያጥራቸው የቅኔን እርዳታ ይጠይቃሉ። ሳይንስ ዝም ሲል፤ ፍልስፍና ቃላት ሲያጥረው፤ ነገረ መለኮት ሲንተባተብ፣ ፍቅርና ተስፋ ይናገራሉ። ፍቅር ከፍርሃት ያድናል። ተስፋ ለብዝኃነትም ለአንድነትም መድኃኒት ነች።

አንዲት አበባ ለብቻዋ፣ አንድ ዛፍ ለብቻው ገነትን አይሆኑም። የተለያዩ አበቦች፣ የተለያዩ ዛፎች በኅብረት ገነትን ያስገኛሉ። የሚያለመልማቸውን ውሃ በጋራ ይጠጣሉ። ፀሓይን አብረው ይሞቃሉ። በጨረቃና በከዋክብት ይደምቃሉ። ነገር ግን አበባ አበባ መሆኗን የምታውቅ አይመስልም፤ ውበቷን መረዳት የምትችል አይመስልም። ውበቷን ለማድነቅ ሰው ያስፈልጋታል። መዓዛዋን ለማሽተት ሰው ያሻታል። የሰው ልጅ ግን ራሱን ማወቅ ይችላል። የአበባንም ውበት ማድነቅ ይችላል። በርግጥም፣ ቆም ብሎ ያንን ውበት ማሰብ ይፈውሳል። ስለ ብዝኃነትና ስለ አንድነት ያስተምራል።

አንዲት አበባ ለብቻዋ፣
አንድ ዛፍ ለብቻው ገነትን አይሆኑም።

አበባ አበባን የመጉዳት ዘመቻ አታውጅም። ሰው ግን ሰውን ሲጎዳ የሰው ልጅን እየጎዳ መሆኑን ያውቀው ይሆን? ማንም ሰው በፍጡርነቱ፣ ከፈጣሪ በመምጣቱ የሰው ሁሉ ዘመድ መሆኑን አለማስተዋሉ ያሳዝናል። ዘመዱን ባዳ ማድረጉ ይገርማል። ተራሮች ቢናገሩ፣ ዕፅዋት ቢጠየቁ፣ ለእንስሳት ድምፅ ቦታ ቢሰጥ የሰዎችን ዝምድና በዘመሩ!

ሰላም ያድናል። ጥያቄው ሰላምን መመኘት ብቻ ሊሆን አይገባም። ሰላም እንደሚያድን መረዳት፣ የሰላም መሣሪያ መሆንና የሰላም መሣሪያዎችን ማክበርና ማዳመጥ ያስፈልጋል። ሰላም ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም፤ ያድናል እንጂ አያጠፋም። ሰላምን ከልብ ለሚያስቡ ሰዎች፣ ፍቅርን ለሚያውጁ መልእክተኞች ጆሮ መስጠት ሕይወትን ይሰጣል። ሰላምን ለማስፈን ሁሉም መተባበር ይገባዋል። ለመተባበርም ከፍትሕና ከምሕረት ጋር፣ ከእውነትና ከርኅራኄ ጋር መታረቅ ያስፈልጋል።


ሰላም ከሕጻንነት ይጀምራል። መኖር ማለት ለልጆች ሰላምንና ፍቅርን ማቅመስና መመስከር ነው። ብዝኃነትም ሆነ አንድነት ጸጋ ከሆኑ፣ ፍቅርና ተስፋ ከሁሉ የሚበልጡ የልጆች ስጦታዎች ናቸው። ከዚህ የሚበልጥ ሀብት የለምና። ሕይወትም ሌላ ትርጉም የላትምና። የምጣኔ ሀብት፣ ገንዘብና ኀይል ያለ ፍቅር ሙላትን አያገኙም። ከሁሉ የሚበልጥ መዋዕለ ንዋይ ፍቅር ነው። መዋዕለ ንዋይ ሲፈስስ ፍቅር በባጀት ቢገባ ትርፉ የትየለሌ በሆነ! አስተማማኝ ትርፍ! በስሜት የማይወሰን ፍቅር፣ ውሳኔንና ኀላፊነትን ያካተተ ፍቅር የኢኮኖሚ ዕሴት ነው።

የሕጻንን ፊት ማየት ደስ ይላል። የሕጻን ፈገግታ ሁሉን ይማርካል። የሕጻን ፈገግታ ፈገግታን ይወልዳል። አንድንም ብዙንም ያሸንፋል። የሰውን ፊት በፈጣሪ መነጽር ማየት ኀላፊነትን ያስታውሳል። ማሰብን ያስተምራል። አጠገብ እያለ እሩቅ የሚመስለውን መፍትሔ ያሳያል። ፍቅር ብዝኃነትን ያስውባል። ጥላቻ ብዝኃነትን ያበላሻል። ትሕትና ብዝኃነትን ያጸናል፤ ትዕቢት ግን ብዝኃነትን ወደ ስሕተት ዓለም ያወርደዋል። ማድነቅና ብዝኃነት ይፈላለጋሉ። ከራስ ወዳድነት ይልቅ ልግስና ጅግነነት ነው፤ ይቅርታ ይፈውሳልና ከበቀል ይልቅ ይቅርታ ይጀግናል።

እነሆ ወገኖች በሙሉ ዛፍ ቢተክሉ እንዴት ያምራል! አንድ ሳይሆን ብዙ ዛፎች፣ አንድ ዐይነት ሳይሆን ብዙ ዐይነት ዛፎች፤ አንድ ዛፍ ወይም አንድ ዐይነት ዛፍ አይበቃምና። በትንሽ መዛባት ሥነ ምኅዳር ሊቃወስ እንደሚችል፣ በትንሽ በጎ ፈቃድ ብዙ ሥራ መሥራት፣ ምድርን መታደግ ይቻላል። ከሰው ባሻገር፣ ሐይቁም፣ እፅዋቱና እንስሳቱ፣ ተራሮቹና ሸለቆዎቹ፣ ምድሪቱና ሰማዩም አብረው ብዝኃነትንና አንድነትን ይመሰክራሉ። ጀንበርም ከመጥለቋ በፊት መስማማቷን በልዩ ውብቷ ትገልጣለች። “ነገ ጠዋት እንገናኝ” እያለች ለተስፋ ማለዳ ቀጠሮ ትሰጣለች!

ብዝኃነት ያለ ኅብረት አታምርም፤ አንድነትም ያለብዝኃነት አትጸናም። ልዑል ፈጣሪ ሁለቱንም ይስጠን!

Abba Daniel Assefa (Dr.)

ከሐሰተኛ ነቢያት ተጠበቁ!

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን በመሠረታዊ አቋሞቿ ላይ የአመለካከት ለውጥ እያመጣች እንደ ሆነ ይስተዋላል፡፡ ለውጡም ከእምነት ወደ ስሜታዊነት፣ ከተጨባጭ እውነት ወደ ሕልመኝነት እንዲሁም ከምክንያታዊነት ወደ ምሥጢር ናፋቂነት ዞራለች፡፡ ግን ለምን? ለምን በመጣው የትምህርት ንፋስ ሁሉ እንወሰዳለን? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልሱ ዘርፈ ብዙ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከእነዚህም ጥቂቶቹን ለማንሣት ያህል፡- እግዚአብሔርን ወደ መምሰል የሚያመራውን ንጹሕ የእግዚአብሔር ቃል ከማስተማር ይልቅ የራሳችንን ገድል በየምስባኩ ማውራታችን፣ ሕዝባችንን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሳይሆን የግለ ሰቦች ተከታይ ማድረጋችን እንዲሁም አማኙ ማኀበረ ሰብ ከምንም ነገር በላይ የተኣምራት ናፋቂዎች እንዲሆን ማድረጋችንና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

እውን ክርስቲያኖች ሳይሞቱ ለዘላለም ሊኖሩ ይችላሉ?

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቴሌቪዥን መስኮት ብቻ እናውቃቸው የነበሩ አንዳንድ አፍሪካውያን “አገልጋዮች” በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መድረክ ላይ መታየት ጀምረዋል። በቅርቡ የተከሰቱ ሁለት ኩነቶችን እንኳ ብንመለከት “ሜጀር ሼፐርድ ፕሮፌት” ቡሽር ከማላዊ፣ “ነቢይ” ኮቦስ ቫን ሬንስበርግ ከደቡብ አፍርካ ወደ ኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት ልብ ይሏል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.