[the_ad_group id=”107″]

ፍቅርን የመግለጫ መንገዶች

በፍቅር የተጋመዱ ጥንዶች ትሥሥራቸውን አስመልክቶ ጥያቄዎችን ማንሣታቸው አይቀርም። አንዳንዱ ጥያቄ የሚሰነዘረው ለአፍቃሪው ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ መልስ ከተፈቃሪው ይሻል። ከሚነሡት ጥያቄዎች መካከል አንደኛው “የፍቅር ጥያቄ” ነው። ራሳችንን፣ “በርግጥ አፈቅራታለሁኝ?”፣ “እሷስ ከልቧ ታፈቅረኛለች?” እንላለን። መነሾው ቢለያይም፣ በደስታ መኻል ስንቅር የሚል ጥያቄ እንደ መሆኑ ያስጠላል፤ ያስፈራልም። ሲ. ኤስ. ሊዊስም፣ “ፍቅር በሕይወታችን ካለ ጽኑና ቀጣይ ደስታ ከዐሥሩ የዘጠኙን እጅ ድርሻ ይወስዳል” እንደ ማለቱ ጥያቄው አይናቅም።

ፍቅርን መግለጥ መቻል ስጋት ይቀንሳል፣ መሰጠትን ያሳያል፣ እርካታን ያሳድጋል፣ መቃቃርን ይመክታል፤ ጤናማም ያደርጋል።[i] ስጋት የወለደው ጥያቄ ደግሞ ልባችን ተንሰራፍቶ ከመቀመጥ ይልቅ ማስረጃ ለማሰባሰብ እየኳተነ መሆኑን ያሳብቃል። በፍቅር መረጃ ያልጠገበ ልብ ደግሞ አደገኛ ነው፤ መቃቃር ይወልዳል። መጽሐፍ ቅዱሳችንም ‘ፍቅር ሙያ በልብ ነው’ በማለት የፍቅር ዝምታን አያደንቅም። እንደውም ካልተገለጠ የሚሰጠው ፋይዳ እምብዛም መሆኑን “የተገለጠ ዘለፋ ከተሰወረ ፍቅር ይሻላል” (ምሳ. 27፥5) ይለናል።

ፍቅርን የመግለጫ መንገዶች

ሁላችንም ፍቅርን የምንገልጸበት መንገድ አንድ አይደለም። ፍቅር በተግባቦት የሚለዋወጡት ስለሆነ የጋራ ቋንቋ ይፈልጋል።አሊያማ፣ የከወነው ግራ ያጋባል፤ ቅራኔ ያስከትላል። የተለያየ መረዳት ፍቅርን የመስጠትንና የመቀበልን ሂደት ያኮላሸዋል። ፍቅር በሚል የምንጠብቀው ሌላ ሆኖ እስካለ፣ ያቀረብነው ምንም ቢከብር ለ‘ተቀበል’ ተባዩ ጠብ አይልም። የተፈቃሪን የፍቅር ግንዛቤ ሳናውቅ ያሳየነው ትጋት ምንዳም የወቀሳ መዐት ይሆናል። አንዳንዴ የአልተፈቀርኩም መነሾም የፍቅር መረዳታችን መለያየት እንጂ ፍቅር መነፈጋችን አይደለም። ከዚህ በታችም የፍቅር መግለጫ ለየቅል መሆኑን በማሳየት፣ ግንዛቤያችን እንድናሰፋ እጋብዛለሁኝ።[ii] በሂደቱ ጉርሻዎችን መጠቆሜ “ያለ አላዋቂ ሳሚ…” ከሚል ወቀሳ አንዳንዶችን አድን ይሆን በሚል ነው።

አዎንታዊ የፍቅር ቃላት

ፍቅርን ስናስብ መጀመሪያ የሚመጡልን አዎንታዊ ቃላት ናቸው። በአዎንታዊና በተከሸኑ ቃላት ፍቅርን መግለጥ ግን በብቸኝነት ለኪነ ጥበብ ሰዎች፣ በተለይም ለዘፋኛች የታጠረ አስመስሎታል። በአፍቃሪያን መካከል የሚነገር ቃል ምንም ቢጎላደፍ፣ ቅርርብ እና ትሥሥር የወለዱት እንደመሆኑ ዓለማቀፋዊ ሽልማት ካገኘ የፍቅር እንጉርጉሮ የበለጠ ይከብራል። ተፈቃሪ ደግሞ ከማንም በበለጠ ጣፋጭ የፍቅር ቃላትን መስማት የሚፈልገው ከአፍቃሪ መሆኑን ማስተዋል ይኖርብናል።

በአደባባይ ፍቅር፣ ያውም “የገበያው ፍቅር” እንዲህ እየተነገረለት ባለበት ዘመን ፍቅርን በቃላት አለመግለጽ ጨዋነት አይደለም፤ ያስወቅሳል። ታዲያ አፍቃሪያን ውዱ ልብ እንጂ ዋጋው በሚንር ወረቀት የማይታተሙት ቃላት በስስት እየቆጠቡ እንካችሁ የሚሉት ለምን ይሆን? በተለይ ክርስቲያኑ ፍቅርን ከተነፈሰ ለአምላክ ካለው ፍቅር የሚገምስ ሳይመስለው አይቀርም፤ ቁጥብ ነው። አንዳንዶች እንደውም ከአምላክ ጋር የፍቅር ኪዳን ሲገቡ፣ “ሌላ ሰው ታፈቅርና ዋ!” የተባሉ ሁሉ ይመስላል። ለአምላክ ያለን ፍቅር ዕድገት የጤናማነት መለኪያ አፍቃሪነታችን አካታችነቱ ሲጨምር መሆኑንም አንዘንጋ።

ጠቢቡ ሰሎሞን ሚስትን አስመልክቶ፣ “እንደ ተወደደች ዋላ፣ እንደ ተዋበች ሚዳቆ” ማለቱም ለትምህርታችን ነው (ምሳ. 5፥18-19)። መሀልየ ሰሎሞንንም ስናነብ፣ አካላዊ ውበቷን ሲያደንቅ፣ ከሌሎች ጋር በማነጻጸርም ከእርሷ የተሻለ የሚስበው እንደሌለ መናገሩንም እናስተውል (መሀ.ሰለ 1፥15-16)። አሁን እስኪ ሀገሩ ሁሉ የሚያወራለትን ዐይን የማይታየን ይመስል ዝም ማለታችንንስ ምን ይሉታል?

አብዛኛዎቻችን “የኔ ቆንጆ በጣም ነው የምወድሽ”፣ “ታኮሪኛላሽ” ማለት ይተናነቀናል። ተሳክቶልን ከተናገርንም ከልብ ሳይሆን በሽምደዳ የተጠኑ የሚመስሉ ቃላትን እናዘንባለን፡፡ ዐይኖቻችን የፍቅራችንን ስስት፣ ድምፃችንም በአድናቆት መዋጣችንን አያሳይም። “ትውደኛለህ?” ተብለን ከተጠየቅንም፣ “ስንቴ ልንገርሽ?” ማለት ይዳዳናል። ጥያቄው መዘግየታችንን እንደማመልከቱ፣ “በቃህ ምሬሃለሁኝ!” እስክንባል ልንለጥቅ በተገባን ነበር!

ፍቅርን የምንገልጽበት መንገድ ፈጠራን ያካተተ ቢሆን ይጠቅማል። የተፈቃሪያችንን ዐይን ሳንታይ በመያዝ ወደ ጆሮ ተጠግቶ በለሆሳስ መናገርን የሚከለክል ሕግ አልሰማሁም፤ ከሩቅ ሆኖ መጣቀስን ሆነ በከናፍርታችን “እምጷ…” ማለትም ክልከላ አልወጣለትም። ከናፍርታችንን ያለ ድምፅ በማንቀሳቀስ “እወድሻለሁ” ማለት መፍነክነክን ይጨምራል።

አንድ ዐይነት ቃል ለሕይወት ዘመናችን ያከራዩን ይመስል፣ “እወድሃለሁ” ብቻ ላይ ከመፈናጠጥ ብንጠበብስ? “ለ’ኔ እኮ አንቺ …”፣ “ለ’ኔ ከምንም ትበልጪብኛለሽ”፣ “አንቺን ማግኘቴ በሕይወቴ ብዙ ደስታን ፈጥሮልኛል” እንዲሁም ውስጣዊ ውበትንም ማድነቅ ይቻላል፡፡ እነዚህ ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ሲሆኑ፣ ቃላቱን መጠቀም ከመንፈሳዊነት መጉደል አይደለም። (ምሳ. 31፥30፣ 1ኛ ጴጥ. 3፥3-5)።

ከእንቅልፍ ስትነቃ ዐይኗ የሚያርፍበትን ቦታ አጥንተን፣ “እወድሃሻለሁ” የሚል የፍቅር ጽሑፍ ብንተው፣ በሞባይል ወይም በኢ-ሜይል ጣፋጭ የፍቅር ቃላትን ብንከትብ፣ ከእግዚአብሔር የተቀበልናት ስጦታ መሆኗን የሚያመለክት ድምፅን ቀድተን ቤታችን ብንተው የሚፈጠረውን ደስታ ቃላት አይገልጸውም። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን የምናደርገውን ነገር በሙሉ በእውነተኝነት ማድረግ እንደሚያስፈልገን መረሳት የለበትም። ‘እኔ እያለሁ ተፈቃሪዬ አዎንታዊ የፍቅር ቃላትን በየትኛውም ቀን አትራብም’ በሚል ለራሳችን ቃል ልንገባ ያስፈልገናል።

አካላዊ ንክኪ

አንዳንድ ተፈቃሪያን ደግሞ ለቃላት እምብዛም ስፍራ የላቸውም። የፍቅር ቋንቋቸው፣ ከቃላት ይልቅ አካላዊ ንክኪ ይሆናል።እነኚህ ተፈቃሪያን፣ ሌሊቱን አምጠን ከወለድነውን የፍቅር ስንኝ ይልቅ ተጠግተን እንድናቅፋቸው ይመርጣሉ። በአካላዊ ንክኪ ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶችም ሌላውን ሰው መንካት በባሕርይ ላይ አዎንታዊ ተጽእኖን እንደሚያሳርፍ፣ እይታን በሚፈለገው አቅጣጫ ለመቅረጽ ሚና እንዳለው፣ ከቃላት ባሻገር የሚደረጉ ተግባቦቶችን እንደሚያቀል፣ ጥልቅ ትሥሥርን እንደሚፈጥር ያመላክታሉ።[iii] ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋው ወራት ለምጽ ያለበትን፣ ታማሚውን እንዲሁም ቅድስና የጎደላቸው የተባሉትን ፍቅሩን ለማሳየት በእጆቹ ዳስሷቸዋል (ማቴ. 8፥3፣ 15፤ 9፥29፤ 17፥7፤ 20፥34)።

እኚኽ ተፈቃያን ልባቸው የሚረሰርሰው ስንጠጋጋቸው ነው። መታቀፍ፣ መሳም፣እጃቸውን መፍተልተል፣ ትከሻቸውንም ማሳጅ መደረግ ይፈልጋሉ።ምርጫቸው ይኽ ሲሆን ተጠግተን ልናቅፋቸው፣ ትከሻቸውን ጨበጥ ጨበጥ ልናደርግ፣ እጃቸውን ልናፍተለትል፤ እንዲሁም ልንላፋቸውም ጭምር እንችላለን (ዘፍ.26፥8)።

ልብ ብሎ ለተመለከተ፣ ተፈቃሪያችን የፍቅር መግለጫዋ አካላዊ ንክኪ እንደሆነ ለማወቅ የምንችልባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉን። ወንበር ስንለይ ወንበሯን ካስጠጋች፣ እጆቿ ወገባችንን የሙጥኝ ካለ፣ ስንላቀቅ እጃችንን ከፈለገች፣ እግሯን በእግሮቻችን ማቆላለፍ ከወደደች፣ ስንገናኝ ጉንጫችንን/ ከናፍርታችንን ከመረጠች፣ ጥምጥም ማለት የምትወድ ከሆነ፣ አካላዊ ንክኪ የፍቅር መግለጫ ምርጫዋ የመሆን እድሉ ይሰፋል።

እንዲች አይነት ተፈቃሪ፣ እጃችን ውስጥ የሻጠችውን ክንዷን ቀስ ብለን የምናስለቅቀው ከሆነ፣ በተደገፈችን ቁጥር፣ “ራስሽን ችለሽ አትቀመጪም?” ካልናት፣ መፈቀሯን ብትጠይቅ አይፈረድባትም ።ይኽ ሲባል ፍቅር ሲገለጥ ተቀባይነት ባለው ቦታ መደረጉን የማረጋገጥ ሃላፊነትም እንዳለብን አንዘንጋ።ሌሎች ባሉበት የሚደረግ የፍቅር ገለጣ፣ ተፈቃሪ የእፍረት ስሜት እንዲሰማው አለማድረጉን ማረጋገጥ ያስመሰግነናል።የዚኽ መልእክት ፍቅር ማህበራዊ ጨዋነት ያስፈልገዋል ለማለት ነው እንጂ በአደባባይ ስፍራ አይኑረው የሚል ሙግት አይደለም።

  • የበጎነት አገልግሎት

አንዳንድ አፍቃሪያን ደግሞ ፍቅርን የሚገልጡበት መንገዳቸው ለሌላው ሰው በጎነት በማሳየት በማገልገል ይሆናል (1ኛ. ጴጥ. 3፥6)።ስለዚህም እንዳገለጉ ወይም እንደተገለገሉ ሲሰማቸው ፍቅርን እንደ ሰጡ ወይም እንደተቀበሉ ይቆጥራሉ።ለእኚህ ተፈቃሪያን ፣ የመፈቀራቸው ሆነ የማፍቀራቸው ምስክራቸው የሚቀበሉት በጎነትና ርህራሄ እንደመሆኑ ለሌላ አይነት ፍቅር ገለጣ ልባቸው ላይሸነፍ ይችላል።

ለምሳሌ ያህል ፍቅርን በማገልገል የሚረዳ ባል አምሽታ እንደ ተኛች ያወቀ ቀን ቀድሞ ከእንቅልፍ በመንቃት ቁርስ ቢያዘጋጅ፣ ልጆችን ልብስ አለባብሶ ትምህርት ቤት የማድረስ ሀላፊነትን ቢወጣ አፍቃሪ የመሆኑ ማስረጃ ይሆናል። ምሽት ታክሲ ሲሳፈሩ፣ አመቺውን ወንበር ቀድሞ በመቆናጠጥ እንድትሸጎጥ ከመፈለግ ይልቅ ለእርሷ ቅድሚያ ቢሰጥ፤ ሸመታ ሲወጡ የተገዙትን ነገሮች ለመያዝ ቢፈቅድ ፍቅሩን ያመለክታል።እንዲህ አይነት አፍቃሪ በዚህ መልክ ያሳየውን ፍቅር ልብ ካላልነው የስብራቱ ምክንያት ልንሆን እንደምንችል ማወቅም ያስፈልጋል።

ከቢሮ ስትመለስ ውሎዋን መጠየቅ፣ ስሜቷን መካፈል፣ ግድ ስለሆነባት ወደ ቤት ይዛ የመጣችው ስራ ካለ ከመጨቃጨቅ ይልቅ በፍጥነት መጨረስ እንድትችል ማገዝ ድካሟን ያለመልመዋል። ቤት ውስጥ የተበላሹ ነገሮች ካሉ ለመጠገን ወይም ለማስጠገን መሞከርም ፍቅርን ይበልጡኑ ያደረጃል። ምናልባትም ነገር ሲቆሽሸ እና ሲዘበራረቅ የማትወድ መሆኗን በመገንዘብ፣ ነገሮችን ማጸዳዳት፣ ልጆች ዝብርቅር ያደረጉዋቸውን እቃዎች ጊዜ ወስዶ ፈርጅ በፈርጁ ማደራጀትም የሚፈጥረው አዎንታዊ ትስስርም የሚናቅ አይደለም።

  • ስጦታ

አንዳንድ ተፈቃሪያን ደግሞ ፍቅርን የሚገልጡበት መንገድ ስጦታን በመቀባበል ይሆናል (ምሳ. 18፥16)።እኚህ አፍቃሪያን ማፍቀራቸውን የሚያሳብቅባቸው ለሚወዱት ሰው ስጦታ ለመስጠት መጠበባቸውን ነው።ስጦታን በሚሰጡበት ጊዜም፣ የመነሻ ምክንያት ይፈልጋሉ። ስለዚህም ለቀናት ያላቸው ዋጋ ከፍተኛ ነው። የተያየንበት፣ የተዋወቅንበትን ፣ የተጠያየቅንበትን የተጋባንበትን ፣ የቤተ ሰቡን አባል ልደቶች ሁሉ ታሳቢ ያደርጋሉ። በእነዚህ ቀናት፣ ሌላኛውን ለማስደነቅ ያስባሉ፣ ስጦታም ያቀርባሉ። ተፈቃሪ ፍቅርን በስጦታ የሚገልጥ ከሆነ፣ ስጦታ ለመስጠት መዘጋጀት ይኖርብናል። የተሰጠንን ስጦታን በተለይም ስጦታው የፈለቀበትን ልብ ቸል ልንለው አያስፈልግም።

ስጦታ ስናበረክት ቁም ነገሩ ምን ያህል ውድ ነው በሚለው አይመሠረትም። አንዳንዶች እንደሚያደርጉት ስጦታ ለጥፋት መካሻ ብቻ ልናደርገው አይገባም። ስጦታችን መልእክቱ እንዳሰብናትና ፍላጎቷን ለማጥናት ጊዜ እንደሰጠን ነው።በሱፐር ማርኬት ፊት ለፊት ስናልፍ የምትወደውን ቸኮሌት ማንሳት ጣእሟን ማወቃችን ከማመልከቱ ባሻገር፣ በቀን ውሎዋችን ውስጥ እንዳሰብናት ይመሰክራል።በተፈቃሪ ልብ ውስጥ ከመኖር የበለጠ ምንስ ስጦታ አለ?

ስጦታ ስንሰጥ የምርጫችን መሠረት ምርጫዋ ቢሆን ይሻላል።አበባ ለምትወድ ተፈቃሪ ውድ ልብስ ከመግዛት፣ ከበር አበባ ቀንጥሶ መስጠት የተሻለ መፍነክነክ ይፈጥራል።ስጦታችንንም ነገ የሚደርቅ አበባ ወይም ሆድ የማይሞላ ቸኮሌት ከሚል ማጀቢያ ጋር ማቅረብም አያስፈልግም። ብዙ ወንዶች ከሚስቱት ነገሮች መካከል አንዱ ስጦታቸው የቤትን ጎዶሎ እንጂ የሷን ፍላጎት አለማሰቡ ነው። ስጦታችን እሷነቷን፣ ልዩነቷን እና ትስስራችንን ዋጋ እንደምንሰጠው ቢያመለክት ይመረጣል።

  • የአብሮነት ጊዜ

አንዳንድ ተፈቃሪያን በአብሮነት ነገሮችን መከወን ደስ ያሰኛቸዋል። በአብሮነታቸውም የቀን ውሎን መተረክ እንዲሁም የሌላኛውን መስማት ይሻሉ። መስማት የተባለውን መድገም መቻል አይደለም፤ ልብንና አካልን አቀናጅቶ ባልተከፋፈለ የልብ ጉጉነት የተናጋሪን ጉዳይና ስሜት ቀዳሚ ማድረግ እንጂ! እንደ አማራጭ መንገዶች ፊልም በጋራ መመልከት፣ ቲያትር መግባት፣ ቤት ማጽዳት፣የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትና ቤተ ክርስቲያን መሄድ ፣ ማህበራዊ ክንውኖችን ላይ መሳተፍ ይቻላል።

ተፈቃሪያችን የፍቅርን መረዳቷ የአብሮነት ጊዜያት ሲሆኑ፣ እንደምንም ተጣበን በጋራ ነገሮችን ለመከወን ራሳችን ማስገኘት ይኖርብናል።በተለይ በተለያየ ስራ መስክ ተጠምደን የምንውል ከሆነ፣ አሰልሰው የሚመጡ የእረፍት ቀናትን እና በአላትን አስቀድመን ለአብሮነት ማቀድ ይኖርብናል።ከስራ መልስ በቀስታ ወክ ልናደርግ፣ አንዳንድ ቀን ወጣ እያልን ልንመገብም እንችላለን።

  1. መደምደሚያ

ፍቅር የሚገልጥበት መንገድ ለየቅል ነው።የተፈቃሪን የፍቅርን አገላለጥ መገንዘብም እንዲሰማልን የፈለግነው ፍቅራችን ጆሮ እንዲያገኝ ይረዳዋል። የተነጋገርናቸው አማራጭ የፍቅር መግለጫ መንገዶች ግን የማይመጋገቡና ንጥል አይደሉም። ምርጫቸው ይለያይ እንጂ፣ ተፈቃሪዎች የፍቅር ቃላትን ሹክ ብንላቸው፣ አካላዊ ንክኪን ብንጠቀም ፣ በበጎነት ብናገለግላቸው፣ አብሮነታችን ቢጨምር፣ ስጦታን ብናበረክት ደስ ይሰኛሉ። ፍቅራችን መግለጥ እንድንችል ፍቅሩ እግዚአብሔር ጸጋውን ያብዛልን!

[i]Marie-Joelle Estrada, “Communication in Intimate Relationships: The Romantic Construal Model,” in The psychology of love, ed. Michele Antoinette Paludi (California: Praeger, 2012).107-132

[ii] Gary D Chapman, The heart of the five love (Chicago : Northfield Publishing, 2007)

[iii] Elliot Greene & Barbara Goodrich-Dunn, The psychology of the body, (Philadelphia: Lippincott Williams & Wilkins, 2012)

Share this article:

“የክርስቲያን ሚዲያዎች ሲታዩና ተግባራቸው ሲገመገምም አብዛኛዎቹ አንባቢውንም ሆነ ተመልካቹን የማይመጥኑ…ሆነው እናገኛቸዋለን” – ቃለ መጠይቅ ከዶ/ር ንጉሤ ተፈራ ጋር

ሚክያስ በላይ ከዶ/ር ንጉሤ ተፈራ ጋር ባደረገው ቆይታ፣ አማኝ ማኅበረ ሰቡን በሚመለከት ስለ ኮሙኒኬሽንና የመገናኛ ብዙኅን አጠቃቀም፣ አብያተ ክርስቲያናት ከኅብረተ ሰቡ ጋር ስላላቸው መስተጋብር እንዲሁም በአጠቃላይ ከቤተ ክርስቲያንን አመራር ጋር ሊያያዙ በሚችሉ ጭብጦች ዙሪያ ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል።

ተጨማሪ ያንብቡ

የነገረ መለኮት ነገር

ክርስትና በአፍሪካ ውስጥ በስፋት በመስፋፋት ላይ እንደ ሆነ የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ሆኖም ግን ʻእየተስፋፋ ያለው ክርስትና ምን ዐይነት ገጽታ አለው?ʼ የሚለው ትኩረት የሚያሻው ጥያቄ ነው። የቁጥር ዕድገት ቤተ ክርስቲያን በማኅበረ ሰቡ ውስጥ ያላትን መገኘት በማግዘፍ የሚኖራትን ሚና ያጎላዋል። በተመሳሳይ መልኩ ደግሞ ዕድገቱ የተለያዩ ተግዳሮቶችን ይዞ ይመጣል። ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ዕድሎች የማትጠቀም ወይም ለተግዳሮቶች ምላሸን የማትሰጥ ከሆነ በምትኖርበት ማኅበረ ሰብ ውስጥ ያላት ፋይዳ እጅግ አናሳ ይሆናል።

ተጨማሪ ያንብቡ

የትንሣኤው ዐዋጅ

ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ መነሣቱ የሚታሰብበት የትንሣኤ በዓል በክርስቲያኖች ኹሉ ዘንድ በምስጋናና በዝማሬ በታላቅ ድምቀት ይከበራል። በኢኦተቤ ትውፊት መሠረት ከዘጠኙ የጌታ ዐበይት በዓላት መካከል አንዱና ታላቁ በዓል የትንሣኤ በዓል ነው። በቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመናን ዘንድ በዓሉ አስቀድሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመውን ጾም በማሰብና በመጾም፥ በመጨረሻም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለድኅነተ ዓለም በአይሁድ እጅ የተቀበለውን መከራና ሥቃይ የሚያስታውሰውን ሰሙነ ሕማማት (የሕማማት ሳምንት) በማስቀደም፥ በመጨረሻም ሞትን ድል አድርጎ የተነሣውን ጌታ በዝማሬዎች በመወደስና ትንሣኤ ክርስቶስን በማወጅ ይከበራል። ልዩ ልዩ ሃይማኖታውያንና ባህላውያን ሥነ ሥርዐቶችም የበዓሉ አካላት ናቸው።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.