“ሜሲን ልንሸጥላችሁ ዐስበናል”
“ምን አላችሁ እና ነው የምትሸጡልን፤ አንድ ያላችሁ እሱ”
“እናንተም ይህን አላችሁ?! ሲጀመር ዋጋውን ከቻላችሁት እኮ ነው”
የታክሲው ረዳት እና ሹፌሩ የጀመሩትን ጨዋታ አንድ ሁለት የሚሆኑት ተሳፋሪዎች ተቀላቀሉበት:: “እንሸጣለን”፣ “አንገዛም” … በውስጤ ʻከት ብለሽ ሳቂʼ የሚል ስሜት ተፈጠረብኝ:: ምን እንደሚሸጥ እና እንደሚለወጥ ለእርሶ መንገር ተገቢም አይመስለኝ:: ስለ ስፔን እና እንግሊዝ ክለቦች እያወሩ ነው ብዬ ማለት ጋዜጦቻችንን፣ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥኖቻችንን ማስናቅ ነው:: እኔን ያሳቀኝ ግን እነሱ ሻጭ እነሱ ገዢ ሆነው መከረከራቸው ነበር:: “የእኛ” የሚለው የቡድን ስሜት የፈጠረው ነገር …፡፡
የቡድን ስሜት ወይም ደጋፊነት እጅግ እየበረታ በመጣ መጠን “እኔ” የሚለው ሐሳብ ይወጣና እኛ ውስጥ ራስን ማግኘት ይመጣል:: “እኔ”ን ረስቶ “እኛ” ብቻ ብሎ መኖር ይቻላል ግን?
ዛሬ የቡድን ስሜት እንዲህ በርትቶ መታየት የጀመረው በኳስ ደጋፊነት ብቻ አይደለም፤ እርስዎ ሌላም ቦታ ያገኙት ይሆናል፡፡ የእኔን ግን ላጨውትዎ:: ቃሉ “ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ መልካም ነው” ስለሚል ኅብረት መሥርተናል፤ በክርስቶስ ኢየሱስ አዳኝነት አምነናል የምንልም ተሰባስበናል:: ይህንን ስብስብ ግን ሲያስፈልግ እንደ ብሔራዊ ቡድን ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት፣ ሲያስፈልግ ደግሞ እንደ ክለብ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ስንደግፈው እና በቡድን ስሜት ስንጮኾለት የምንገኝበት ጊዜ ብዙ ነው::
ጥቂት ሐሳብ ይዘው ቡድን የተቀላቀሉ፣ ብዙ ሐሰብ ባለው በብልሁ ሳይሆን በብልጡ ይበለጣሉ::
በቡድን መጮኽ ከፍ ያለ ድምፅ እንዲወጣ ያግዛል:: በቡድን ማሰብ ለራስ ሐሳብ ስንፍና ይመቻል:: የቡድን ደጋፊ መሆን ደግሞ በቡድን የመመካትን ስሜት ይፈጥራል:: ይህ ደግሞ የቡድንን ሥራ ሳይሆን ቡድንን ራሱ በቡድንነቱ ብቻ ፍጹም አድርጎ ማየትን ያስከትላል:: በቡድን እና በቡድን ደጋፊነት ሳቢያ ተፈጥረው ካየኋቸው እንከኖች መካከል የቅርብ ሰሞን ገጠመኜን ከመንገሬ በፊት ለእርስዎ አንድ ጥያቄ ላቅርብልዎ:: ሰዎች በኢየሱስ አምነው ከጥፋት በተመለሱና ከሲኦል በዳኑ ጊዜ በሰማይ ደስታ እንደ ሆነ ቃሉ ነግሮናል:: እንደው ግን “በተለይ እነ እከሌ እና መሰሎቻቸው ሲድኑ የበለጠ ደስታ ይሆናል” ተብሎ ተጽፍዋል እንዴ? ልክ የእከሌ ቡድን ደጋፊ እንደሚከራከረው የተጨዋች ግዢ ዐይነት ግርግር እያየሁ ስለሆነ እኮ ነው ይህን መጠየቄ::
አሁን ወደ ሰሞኑ ገጠመኜ ልመለስ:: መገናኛ ብዙኀን እና ማኅበራዊ ድረ ገጽ ብድግ ቁጭ እያደረጉት ያለው የሰሞኑ ወሬ ነው:: ʻእከሌ የተበለው ዘፋኝ የእንትን ሃይማኖት ተከታይ ሆነ፤ እከሊትም ጭምርʼ:: ታዲያ፣ ክርክሩ ጦፎ ባየሁበት ወቅት ነበርና ይህንን የታክሲ ላይ ጨዋታ የሰማሁት፣ ለራሴ የነገርኩትን ለእርስዎም ብነግርዎ ብዬ ነው:: ምንም እንኳን በነጻ ብናገኘውም በሕይወት ዋጋ ግን ተገዝተናል:: የተገዛነው ግን በእኩል የሕይወት ዋጋ ነው፤ የአንዳችን ዋጋ ከአንዳችን ዋጋ አይበልጥም:: ስለዚህም፣ እንደ ቡድን ደጋፊዎች በመሆን “ተጨዋች የመግዛት” ጨረታ ውስጥ ባንገባስ:: አይመስልዎትም?