በየዕለቱ በመገናኛ ብዙኀን የምንሰማው የጦርነት እና የግጭት ወሬ የምንኖርባትን ዓለም በሰቆቃ የተሞላች አድርጓታል፡፡ ጥላቻውና በቀለኝነቱም ከቀን ወደ ቀን እያየለ የሚመጣ እንጂ የሚበርድ አይመስልም፡፡ ʻበሥልጣኔ መጠቅን፣ የዕውቀትን ጣሪያ ነካን፣ የሰው ልጅ የአስተሳሰብና የመፍጠር ልዕልና ናኘ፤ ከዚህም የተነሣ ዓለም አንድ መንደር ሆናለችʼ በሚባልበት በዚህ ዘመን፣ ደም መፋሰሱና መገዳደሉ ሊቆም ቀርቶ ሊቀንስ አለመቻሉ እንቆቅልሽ ነው፡፡ አክራሪ ሃይማኖተኝነት እና አክራሪ ብሔርተኝነት/ ዘረኝነት ይከስማሉ በሚባልበት በዚህ ጊዜ እንዴት መልሰው ሊጎመሩ ቻሉ? የመንፈሳዊነትና የሞራል ጠባቂያን ናቸው የሚባሉት የሃይማኖት ሰዎች እንዴት የጥላቻውና የበቀሉ ወጥመድ ጠልፎ ጣላቸው? የአስታራቂ ሽማግሎች መንበር ከወዴት አለ?
አገራችን ኢትዮጵያ ከዚህ የጥላቻ እና የቁርሾ ልክፍት ነጻ ነች ብንል ዕብለት ይሆንብናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ እንደ ሌሎቹ አገራት በከፋ የደም መፋሰስ አዘቅት ውስጥ አንሁን እንጂ፣ በቅራኔና በኩርፊያ የተሞላ ኅብረተ ሰብ ያለን መሆናችንን ግን መካድ ለማናችንም አያዋጣንም፡፡ የታሪክ ንባባችን ለየቅል ሆኗል፤ በአንድ ሁነት ላይ የማይታረቁ ግትር አቋሞች ይዘን እየኖርን ነው፡፡ ይቅርታ ለማድረግም ሆነ፣ ይቅር ለማለት ዝግጁ የሆንን አንመስልም፡፡ አንዳንድ የጥናትና የምርምር ተቋማት እነዚህንና ሌሎች መለኪያዎችን ይዘው አገራችን ኢትዮጵያ “የመፈረካከስ አደጋ የተጋረጠባት” እንደ ሆነች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ይህ ጨለምተኝነት አይመስለንም፤ አሁን እየታዩ ያሉ ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን ካለመቀበልም የመጣ ላይሆን ይችላል፡፡
ጥላቻና በቀለኝነት ከሁሉ በላይ በሃይማኖት ቤት ውስጥ፣ በተለይም ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሥር ሰድዶ ሲታይ አለመደንገጥ አይቻልም፡፡ በምሕረቱ ደጅ አፍ ላይ፣ በምሕረቱ ጎንበስ ቀና የሚሉ ካህናት ጠብ ጫሪ እና አቀጣጣይ ሲሆኑ ማየት እንዴት ያስደነግጣል?! አስታራቂ ሊሆኑ የተጠሩ በጥባጭ ሲሆኑ መመልከት ነገን በፍርሃት ከመጠበቅ ውጪ ሌላ አማራጭ አይሰጥም፡፡
አብያተ ክርስቲያናት በውስጣቸውም ሆነ በምድሪቱ ላይ ላለው ቁርሾ የማስታረቅ ካህናዊ ኀላፊነታቸውን መወጣት ካለባቸው ጊዜው አሁን ነው፡፡ የዕርቅን ቃል፣ የምሕረትን መልእክት፣ የሰላምን አገልግሎት ይዘናል የሚሉ አባቶች (የሃይማኖት ቤተ ሰዎች) ሁሉ አሁን መታያ ጊዜያቸው ነው፡፡ በርግጥም መሪዎች የምንፈልገው አሁን ነው፡፡ ጠበኞችና በቀለኞች፣ ቡድንተኞችና አድሎ አድራጊዎች የሆኑ መሪዎች ሳይሆን፣ አስታራቂ ሽማግሌዎች፣ አርቆ ዐሳቢና ቅን መሪዎች እንፈልጋለን፡፡ ብዙም አይደል፤ ጥቂት ካገኘን ሊበቁን ይችላሉ፡፡ ጥቅቶቹ ብዙ ሲሠሩ አይተናልና እነሱኑ እንናፍቃልን!
Add comment