[the_ad_group id=”107″]

ምስክርነቶቻችን ቢፈተሹሳ?

1. መግቢያ

“ሀገሩን ሁሉ በትምህርቱ የሚያስደምም ሰው ራስ ሆቴል አከባቢ ተነስቷል!” የሚል የወዳጆቼ ጉትጎቷ ቀን ከሌት ቢከታተለኝ፣ በአንድ በኩል በርካቶችን ያስደመመውን ትምህርት ለመቋደስ ብሎም ከዚሁ ከአመለጠህ የወዳጆቼ ጉትጎታ ለማምለጥ በሚል ሁለት ልብ ነበር እግሮቼን ያቀናሁት። በእርግጥም በዛች ቀን ብቻ ወዳጆቼን ምን ነካብኝ ያሰኙ አስተምሮቶችን በአይኔ በብረቱ ተመልክቼ ተመልሻለው፤ ዳግም አልተመለስኩም፤ ደግሞም አልመለስም። በዛች የሁለት ሰአታት ቆይታዬ በብዙ ተደምሜያለሁኝ። አደብ ገዝቶ ልብ እያለ የሚያደምጥ ሰው ጥቂት ሳይሆን አይቀርም የሚሉ ነገሮችንም መታዘቤም አልቀረልኝም። ዋና ነገሬ ጉባኤው አይደለምና፣ ተነግረው ጉባኤውን ጮቤ ካስረገጡ ንግግሮች መካከል አንዱን ብቻ አነሳለሁ። ስብከቱ ስለ “እምነት” ነበረ። ሰባኪው ኢንጊሊዘኛ እየቀላቀለ እምነት አዎንታዊ ቃልን ከማወጅ ጋር ስላለው ብርቱ ቁርኝት መጽሐፉን እንደምንም ጠምዝዞ የሚፈልገውን “አስባለው”። እኔም የውስጤን ጩኽትና ምጥ ታግሼ እንደ “ጨዋ ተጋባዥ እንግዳ” መስመር የሳተውን አስተምሮት ሰማሁለት። በትምህርቱ መሀል፣ ተግባራዊ ምሳሌ ለመስጠት በሚል ዋቢ ጠራ። አጀማመሩ ጆሮዎቼን አሰላቸው! “ታውቃላችሁ” አለ። ከዛም ቀጠለና፣ “ የሆነ ጊዜዬ ጣቴ መቁሰል ጀመረች ። እኔም ለጥቂት ቀናት ችላ አልኳት። መቁሰሏን ስትቀጥል ግን ተመለከትኳትና፣ “አንተ ቁስል ሂድ!” ብየ አዘዝኩት። ቁስሉ ወዲያው አልጠፋም። እኔም ተውኩት። ከጥቂት ቀን በኋላ ስፈልገው በቦታው አልነበረም። እንዳዘዝኩት ሄዷል።” ብሎ አረፈው። ከጉባኤው ውስጥ፣ ጥቂቶች ወይም “አስጀማሪዎቹ” በእግሮቻቸው ቆመው አጨበጨቡ። ጭብጨባን ሲሰማ መመረቅ የለመደውም፣ እልልታውና ጭብጨባውን አቀለጠው። እርግጥ ነው፤ ጭብጨባ ጭብጨባን ይወልዳልና መበራከቱ አልደነቀኝም! የእኔ አእምሮ ግን ጥያቄ መጠየቁን ቀጠለ።

2. ጥያቄዎቼ

ራሴን፣ “ በእርግጥ ጣቱ መቁሰሉና ከትእዛዙ ለጥቆ መጥፋቱ ተአምር ነበረን?” ስልም ጠየኩት። “ከሰባኪው በመተማመን ከተነገረው አዋጅ ባሻገርስ ነገሩ ተአምር መሆኑን ምን ማረጋገጫ አለኝስ?” ስልም ቀጠልኩ። ዙሪያዬን መልሼ ቃኘሁት፣ ከእኔ ባሻገር ይህንን ጥያቄ የጠየቀ ያለ አይመስልም። እኔ ብቻ መጠየቄ ስህተት ወይም አለማመን ይሆንንስ በሚል ራሴንም ፈተሸኩት። ምንም ለማመን ተግቼ ብጥርም ነገሩ ወደ ልቤ ጠብ አላለኝም። ልቤ፣ ስለ እውነት ሸፈተ። እኔም፣ እንደ ሰባኪው ሁሉ ቁስል ነገር እጄ ላይ ወጥቶ፣ ያለምንም እርዳታ ድኜ አውቃለሁ! እርግጥ ነው ፤ እንደ እርሱ መድረክ ላይ ፈውስ ነው በሚል ግን አልፎከርኩበትም። የሱን ቁስል መዳን፣ ከእኔ ምን ይለየዋል? በጊዜ ሂደት የማይድን ስለመሆኑ በህክምና ባለ ሙያ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ፣ “ለምንስ በማላውቀው ጉዳይ ተአምር ነው በሚል ነገር ማዳመቂያ ሆናለሁኝ?” አልኩ።እዛ መንፈሳዊ ስብሰባ ላይ የሆነው ክስተት በእኛው ዘመን ተንሰራፍቶ እየገዛ ወዳለ ሀሳብ ወሰደኝ። አዎን! እያመመኝ በየቤተክርስቲያናችን የእግዚአብሄር መገኘት ዋነኛ ምልክቱ በመካከላች ተሰሩ ተብለው የሚነገሩት ተአምራዊ ነገሮች መሆናቸው ውስጤን ቆጠቆጠው። ይኽን ስል ተአምራት በመካከላችን አልሆኑም ማለቴ ግን አይደለም። አሳሳቢው ነገር ተአምር አለ የተባለበትን ቦታ እያሳደደ የሚከትመው ቁጥር መጨመሩና ተአምረኞቹም በተጋባዥነት ሳይፈተሹ የእኛውኑ ኮንፍራንስ አድማቂ ተጋባዥ መሆናቸውም ነው። በሁለተኛነት ያሳሰበኝ ተአምሩ ተአምር መሆኑ ሳይረጋገጥ ለማወጅ መፍጠናችንም ነው። መቼም መመኘትን የሚከለክል የለምና ተአምራትን እንደ ካቶሊካውያን መርምረን ብናረጋግጥና ከእውነተኞቹ ጋር አብረን ብንደሰት፣ ከአውነት የራቁትንም ባናራግብ ፤ብሎም ደግሞ መሳቂያና መሳለቂያ ከመሆንም ብንተርፍስ ማለቴም አልቀረም።

ካቶሊክ ወንድሞቻችን፣ ተአምር ሆነ ሲባል አብረው ለማጨብጨብ አይፈጥኑም። ስላልተጨበጨበም ተአምሩ ፈጥኖ ከመካከላችን እንደማይነጠቅም ተገንዝበዋል! አለማጨብጨባቸው ግን ተአምር የለም ብለው ስለሚያምኑ አይደለም፤ እንደ እኛው ሁሉ ተአምር አሁንም ድረስ እንዳለ ያምናሉ። የሚለያቸው ነገረ ጉዳዩን ሰከን ባለ ሁኔታ ያጠኑታል። ሚዛናቸውም ታዲያ ቀላል እንዳይመስላችሁ፤ እጅጉን ጠበቅ ያለ ነው። “ተአምር ነው!” የሚል አዋጅ ከማስነገራቸው በፊት፣ ፈውስ የተባለው ክስተት በህክምና ባለሙያዎች አማካኝነት የተፈጥሮዋዊ መሻል የተነሳ ወይም የህክምና ክትትል ውጤት አለመሆኑ በብርቱ እንዲጣራ ይደረጋል። ከዚያም በበቂ መረጃ ፈውሱ ሲረጋገጥ፣ ለእግዚአብሔር ክብር ይሰጥበታል። እንዲህ አይነቱ የፈውስ ጥንቃቄም፣ በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት ነው። እኛ ወንጌላውያኑ መካከል፣ ፈውስን አስመልክቶ እግዚአብሔርን መጠባበቁ የሚያስመሰግን ሆኖ ሳለ፣ ፈውስ በሚል የሚነገሩት አንዳንድ ምስክርነቶች ግን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡና ለብዙ አይነት የልብ ስብራት ጭምር የሚያጋልጡ ሆነዋል። “ተፈወሱ” ብለን መድረክ ያስወጣናቸውን እና መድሃኒት ያስጣልናቸውንም ከቀናት በኋላ አልቅሰን ቀብረናል። ነገሩ በርካቶችን ለሞት መዳረጉ እንዲያበቃ፣ በነገሩም መሳቂያና መሳለቂያ የሚያደርሰን ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት አንዳንድ ምስክርነቶቻችን በብርቱ መፈተሸ እና ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። ይኽን ማድረግ እንዲያስችለን በሚል ጥቂት ነገር ላካፍላችሁ።I

3. ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው ምስክርነቶች

ከምንም አስቀድሞ፣ “ከበሽታ ተፈወሰ ወይም ተፈወስኩ” የሚሉ ምስክርነቶችን ስንሰማ የሰማነውን ሁሉ ሳንፈትሽ ለሌሎች ማወጅ እንዳለብን ማሰብ አያስፈልገንም። እንደዚህ ካመንን ደግሞ፣ ምስክር ልንሆን የወሰኛቸውን ፈውሶች አስመልክቶ በቂ በሆነ መረጃ ማጣራትና መመርመር ያስችለናል። ጌታችን ፣ “ ሂድ፣ ራስህን ለካህን አሳይ” (ማቴ. 8፡4) በማለት ምስክርነት አስመልክቶ ፈር ቀዶልንስ የለ? ይህን ለማደረግ ከሚረዱ ጉዳዮች መካከል፣ በዛሬው ጽሑፌ ውስጥ አራት ሀሳቦችን አነሳለሁኝ።

3.1 በጊዜ ሂደት የሚድኑ በሽታዎች

አንዳንድ በሽታዎች በባህሪያቸው፣ በጊዜ ሂደት ውስጥ ራሳቸውን የሚወስኑ ናቸው። ከዚህ የተነሳ የህክምና ባለሙያዎቹ፣ “ ሰልፍ ሊሚቲንግ” በሚል የሚጠሩዋቸው። የነዚህ በሽታዎች መለያ በቂ ጊዜ ከሰጠናቸው ሰውነታችን በራሱ የመከላከልን አቅም በማጎልበት ይቋቋማቸዋል። ይኽ ሲባል ግን የህክምና እርዳታ፣ መዳናችን ለማፋጠን ፋይዳ የለውም ማለት አይደለም። ህክምና እርዳታን አገኘንም ሆነ አላገኘንም፣ ጊዜ ከሰጠነው ግን መዳናችን አይቀርም። ለመረዳት እንዲቀል የምናውቀውን በጉንፋን መጠቃትን እንደ ቀላል ምሳሌ መመልከት ይቻላል። አንደ ህክምና ባለሙያዎች ገለጻ፣ ወደ ሀኪም ቤት ከሚጎርፉት 50 ፐርሰንት ወይም ግማሹ ታማሚዎች በዚሁ በሽታ የተጠቁና፣ ተፈጥሮ ራሱ በቆይታ ደህንነታቸውን የሚያረጋግጥ መሆኑ ነው። የዚህ ነገር አውነተኛነት የገባኝም፣ በባዕድ ምድር ታመው ሀኪም ጋር የሄዱ ወዳጆቼን በመመልከትም ነው። እነዚህ ወዳጆቼ፣ “ ውሃ በደንብ ጠጡ፤ እረፉም” ሲል ነበር ሀኪሙ የሸኛቸው። ወዳጆቼም ውሃቸውን በመጠጣትና በማረፍም ከበሽታቸው ድነዋል። በዚህ መልክ የሚድኑ በሽታዎችን፣ ለየት ባለ መልኩ የመለኮት ጣልቃ ገብነት እንደ ነበረበት አድርጎ ማቅረብ እንዲሁም ውዳሴን መቀበል የሚያስታዝበን እንጂ የሚያስመሰግነን አለመሆኑን ልንገነዘብ ያስፈልጋል።

3.2 የአስተሳሰብ ለውጥን ከአካላዊ መሻል ጋር መደባለቅ

ከመታመም ጋር ተያይዞ ሌላ ልብ መባል ያለበት ጉዳይ፣ የሚሰማንን ስሜት ከታማሚው አካላች ነጥሎ መመልከት አለመቻል የሚፈጥረውን ችግር ነው። አንዳንድ ጊዜ ፣ ከዚህ በፊት ከበሽታው ጋር ተያያዥነት ያላቸውና ሲሰሙን የነበሩ ህመሞችን ቦታ አናገኝላቸው ይሆናል። የሚሰማን ህመም በዛ ጊዜ ቀነሰ ወይም ጠፋ ማለት ግን በበሽታው ተጠቅቶ የነበረው የሰውነታችን ክፍል ጤናማ ሆነ ማለት ግን አይደለም። የለውጡ ምክንያት አንዳንዴ መለኮታዊ ሀይል የታመመውን የሰውነት ክፍላችንን አድኖት ሳይሆን፣ ነገረ ጉዳዩን የምንመለከትበት የአመለካከት ለውጥ ህይወታችን ውስጥ ከመከሰቱ የተነሳ ይሆናል። ስለዚህም፣ ከጸሎት መልስ የተሰማንን የመዳን ስሜት ተካልበን በመከተል፣ ከወዳጅ ዘመድ ተበድረን የገዛናቸውን ውድ መድሃኒቶችን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለው መጸዳጃ ቤት ከመጨመራችን በፊት ሰከን ብለን ማስብ ይኖርብናል።

ለምሳሌ ያህልም፣ በወንጌል ጀማ ስብከቶች አከባቢ ሁሌ ባይሆንም አንዳንዴ የሚከሰተውን ነገር በምሳሌነት ላንሳ። እጅግ የሚያነሳሱና ከፈውስ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ስብከቶች ስንሰማ፣ ወደ ተመስጦ የሚወስዱ ሙዚቃና መዝሙሮችን ስንዘምር፣ ፈውስን በተከፈተ ልብ እንድንጠብቅ የሚያደርጉ አዋጆችን ከመድረግ ሲከታተሉብን ለየት ያለ ስሜት ድንገት ሊሰማን ይጀምር ይሆናል። ከበሽታችን ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የህመም ስሜቶችንም በእርግጥ ልንረሳ እንችላለን። በእንዲህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ስንሆን አእምሮዋችን፣ ወደ ነርቭ ስረአታችን ውስጥ ኢንዶርፊኖችን ይለቃል። እነዚህ ኢንዶርፊኖች ደግሞ ሀኪሞቹ ህመማችን ለመቀነስ በሚል በሀኪሞች ከሚሰጡ ሞርፊኖች የበለጠ ህመማችን አንዳይሰማ የማደርግ አቅም አላቸው። ባለሙያዎቹ የኢንዶርፊኖች ህመም እንዳይሰማን የማድረግ አቅማቸው ከሞርፊኖች ጋር ሲነጻጸር ሁለት መቶ እጥፍ ያክል መሆኑን ይነግሩናል። ህመማችን በዚህ መጠን ሲቀንስ፣ እንደ ዳንን ቢሰማን በእርግጥም አይገርምም። በዚህ ሁኔታ፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ህመማችን ተወግዷል በሚል የአቻኩሎ ጉተታ ወደ መድረክ ልንወጣና ለጉባኤው መዳመቂያ ልንሆን እንችላለን። ማይክ አስጠግተው፣ “አሁን ህመሙ አለ” ላሉንም “የለም” ልንል ብሎም ደግሞ ህመማችን ስለ ጠፋ በደስታ እንባ ፊታችን ታጥቦም ምስክርነት እንሰጣለን። በእንዲህ አይነት ሁኔታ፣ የሚደገፉትን ክራንቻቸውን ጥለው መድረክ ላይ የሮጡ ሰዎችን እናውቃለን። ነገር ሁሉ አልፎ ቤታችን ስንደርስ ግን ያ ስሜታችን አንዳንዴ ማታውን ሌላ ጊዜ ደግሞ ቀናትን ወይም ሳምንታትን አሰልሶ የሚመጣበት ሁኔታ ይገኛል። መዳናችንን ሰከን ባለ ሁኔታ በህክምና ተከታትለነው ቢሆን ግን የሚሰማንን ስሜት ከታማሚው አካላችን ጋር አነጻጽሮ መመልከት ስለሚያስችል፣ ከእንዲህ አይነቱ ስህተት በቀላሉ ልንድን እንችላለን። ለነገሩ፣ ፈውሱን የራሳቸውን ስም ማዳበሪያ አድርገው ለመጠቀም የጓጉ አንዳንድ ሰባኪዎቻቸንስ መች እንድንሰክን ይፈቅዱልና! አሁን አሁን ደግሞ ያጣደፉን ሳይበቃ ፣ ድሮውኑንም ያልዳነውን በሽታ፣ “ ሰይጣን ሊበቀላት” በሚል መንፈሳዊ ቃል ቀባብተን የድሮው ስህተታችን እናስቀጥለዋለን።

3.3 የስነ ልቦናዊ ተጽእኖዎችን ሚና በቅጡ አለመገንዘብ

ሌላው ሰዎች ሊገነዘቡት የሚገባ ነገር ከበሽታ ማገገም ሆነ መዳን ጋር ተያይዞ ስነ ልቦናዊ ተጽእኖዎች የሚኖራቸው አዎንታዊ ሚናን ነው። ስነ ልቦናዊ ተጽእኖዎች በአካለዊ በሽታችን ላይ የሚያደርሱትን ተጽእኖ ባላወቅን ቁጥር፣ ሁሉንም ነገር መለኮታዊ ፈውስ አድርገን እንድንቆጥር የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች አሉ። ስነ ልቦናዊ ለውጦች የፈጠሩትን መሻልም የልዕለ ተፈጥሮዋዊ ሀይል ጣልቃ ገብነት አድርገን እንወስደዋለን። ሰዎች ህመማችንን አስመልክቶ የሚያቀብሉን ሀሳብ፣ የሚሰጡን ትኩረት፣ የሚነኩን መንካቶች በእኛ ላይ የሚፈጥሩት አዎንታዊ ስሜት እንዲሁ ተንቆ የሚተው አለመሆኑን በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የሚሰማን ህመም መጠኑ መቀነሱ እና መጨመሩ ካለንበት ውጥረት ጋር ቁርኝት የሚኖርበት አጋጣሚ ትንሽ አይደለም። ሰዎች ውጥረትን በሚቀንስ መልኩ ሲነኩን እና እንክብካቤ ሲያደርጉልን አብሮም ህመማችን ይቀንሳል። አንዳንድ ጊዜ አካላዊ በሚል የያዝናቸው እንደ መስማት እና መመልከትን ጨምሮ ከደረሰብን ስነ ልቦናዊ ተጽእኖና ጥቃት የተነሳ የተከሰተ በሚሆንበት ጊዜ፣ ያለ መለኮት ጣልቃ ገብነት እንደ መስማትና ማየትን ጨምሮ ያሉ ችግሮቻችን ሊፈቱ የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉ ልብ ማለት ያስፈልገናል። 3.4 በመከላችን ማስመሰል እና ማጭበርበር ሊኖር እንደሚችል አለመገንዘብ

ባለንበት ዘመን፣ በመካከላችን በማስመሰል እና ማጭበርበር መለኮታዊ ሀይል እንደ ተገለጠ አድርገው የሚያቀርቡ ሰዎች መኖራቸውን መካድ መንፈሳዊነት አይመስለኝም። ቅዱሱ መጽሐፋችን እኮ ፣ “… ሰይጣን ራሱ የብረሃንን መልአክ አስኪመስል ራሱን ይለውጣልና። እንግዲህ ደግሞ አገልጋዬቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳችን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤”(2ኛ ቆሮ፣ 11፡14- 15) ሲል መክሮናል። በሀገረ አሜሪካ ሬቨረንድ ጂም ጆንስ የተባለና ፒፕልስ ቴምፕል የተሰኘ መጨረሻው ያላማረ የከልት መንፈሳዊ ድርጅት መስራችን ብንማርበት በሚል ላውጋችሁ። በጉባኤው የነበረውን ልምምድ ሲገልጹት፣ “ የሰውን ስም ሲጠራ፣ ተጠሪው ይቆማል፤ አስተናጋጁም ማይክ ይዞ ይጠጋዋል። ጂም ደግሞ፣ “ከዚህ በፊት አይተኽኝ ታውቃለህ?” ሲል ይጠይቃል። ሰውየውም አላውቅም ሲል ይመልሳል። “ከዚህ በፊትስ ቤትህ መጥቼ አውቃሉኝ?” አታውቅም። “ እንግዲህ፣ የምትኖረው እንዲህ አይነት ቦታ ነው፣ የስልክ ቁጥርህም ይህ ነው፣ ሳሎን ውስጥ ይኽ አለህ። ሶፋህ ላይ ያለውም ትራስ እንዲህ አይነት ነው።… ቤትህ መጥቼ ከዚህ በፊት ነበርን?” ሲል ይጠይቃል።” ይህ መለኮታዊ የሚመስለው ልምምድ ሲጣራ ግን ለዚሁ ስራ በተመደቡ ስድስት ሴቶች አማካኝነት የተሰበሰበ መረጃ መሆኑ ነገሩ ሲጋለጥ ተደርሶበታል።II ዛሬም ድረስ በርካቶች፣ መረጃዎች ባሰማሩዋቸው ጀሌዎቻቸው አስጠንተው የሚናገሩ መኖራቸውን መካድ አያስፈልገንም። ሲያስፈልግም፣ በገንዘብ ሰዎችን ቀጥረው ሁሉ ድራማ የሚተውኑም ጭምር በመካከላችን መኖራቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል። ለእነዚህ ሰዎች፣ ቤተክርስቲያን የንግድ ስፍራ ናትና! እኛን የሚቀፈን ነገር አይቀፋቸውም። በቅርብ ጊዜ ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ መፈጸሙን የሰማውትን ታሪክ በመረጃነት ላንሳ። “ተነሳ” የሚባልለት ወጣት አለ፤ በርካታ ድንቃ ድንቆች ይሆናሉ በሚልም ክርስቲያኑ ማህበረሰብ ይተማል። ይኽ ወጣት ታዲያ ልዩነቱ፣ “ ሰው ሲፈልግ “ገድሎ መልሶ ማስነሳቱ” ነው። መንፈሳዊ ስልጣን ተብየው እንግዲህ ከፈውስ አልፎ ሞትንና ህይወትን ማደል ላይ ደርሷል! ይኽንንም የሚፈጽመው ደግሞ ወጣት ልጆችን በመጠቀም ነው። አንድ ጊዜም እጁን በመዘርጋት አንዲቷን “ ገደላት” ደግሞም በሳምንት እንደምትነሳ ተናገረ፤ በሳምንቱም “ ከሞት አስነሳት”። ነገረ ጉዳዩ ያላማረው አባት ግን ልጅቱን በአርጩሜ እውነቱን ተናገሪ በሚል ሲዠልጣት፣ ድራማውን እንድትሰራ ገንዘብ ከፍሏት እንደ ነበረና ቤት ዘግቶ ለአንድ ሳምንት ያህል ይመግባት እንደ ነበረ አጋለጠጭ። እኚህና መሰል ታሪኮችን በመካከላችን፣ ሰነባብተዋል።

4. ምን እናድርግ

“ ምስክርነቶቻችን አስመልክቶ ምን እናድርግ?” ብለን መጠየቅ ግድ የሆነብን ጊዜ ላይ የደረስን ይመስለኛል። እውነተኛዎቹን ከሀሰተኞቹ ለመለየት ካልሰራን ፣ እግዚአብሔር መስራት አቁሟል ወደ ሚል ሌላ ጥግ ልንገፋም እንደምንችል መገንዘብ ይኖርብናል። አሁን ያለውን ሁኔታ ቸል ካልነው፣ ነገሩ አደጋ ነው። መመርመር መዳፈር አይደለም (1ኛ ዬሐ. 4፡1) በሚል የአዲስ ኪዳናዊ የአስተሳሰብ ቅኝት ምስክርነቶችን መመርመር መጀመር ይኖርብናል። ይኽን ለማድረግ ግን፣ ከሁሉ በፊት ማድረግ ያለብን ማስተካከያ አለ። ጸጋ ስጦታዎችን ለቤተ ክርስቲያን መታነጽ በብርቱ መፈለጋችን እየቀጠልን (1ኛ ቆሮ. 14፤12)፣ ስጦታዎችን ከመናፈቃችን የተነሳ ምስክርነት በሚል የቀረቡትን ሁሉ ግን አግበስብሰን ቤተ ክርስቲያንን ለማፈራረስ መቀበል የለብንም። በሰከነ መንፈስ እና በመረጃ ነገሮችን ማድረግም ከክህደት ጋር ግንኙት እንደሌለው ማመን እንዲሁም ለተፈጻሚነቱም ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። እግዚአብሔር ከምንም በፊት እሱን እንድንፈልግ ይርዳን፤ መንፈስን መለየትን ጨምሮ እውነተኛ የጸጋ ስጦታዎችን በመካከላችን ያትረፍርፍልን፤ ትክክል ያለሆኑ ልምምዶቻችን መለየት እንድንችል፣ የሁሉ ጊዜ መገኘቱንም እንድንገነዘብ ጥበብ ይስጠን!


ማጣቀሻ

  1. Andrew Neher, Paranormal and Transcendental Experience: A psychological Examination, (Dover Publications, 2013), 173.
  2. Flo Conway & Jim Siegehman, Snapping: America’s epidemic of sudden personality change, (New York: Delta Books, 1979), 234

Tekalign Nega (Ph.D.)

ተካልኝ ነጋ (ፒኤችዲ) ከባለቤቱ ከትኅትና መስፍን ጋር በአዲስ አበባ ይኖራል። በአሁኑ ጊዜ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት መዕረግ የሚያስተምር ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የድኅረ ምረቃ የሥነ መለኮት ትምህርት ቤት (ኤገስት) ተጋባዥ መምህር ነው። ዶ/ር ተካልኝ “የጸሎት-የንግድ ቤት?!” መጽሐፍ ደራሲ ከመሆኑ ባሻገር፣ የተለያዩ መጣጥፎችን በክርስቲያናዊ ሚዲያ በማቅረብ፣ በተለያዩ ርእሰ ጉዮች ላይ ጥናታዊ ጽሑፎችን በማዘጋጀት፣ ለመሪዎች ሥልጠና በማቅረብ፣ በተለያዩ አገር አቀፋዊ ኮሚቴዎች ውስጥ በመሳተፍ እንዲሁም በስብከተ ወንጌል አገልግሎቱ በወንጌላውያን አማኞች መካከል ይታወቃል። የፒኤችዲ ትምህርቱንም ያጠናቀቀው ኔዘርላንድ አገር ከሚገኘው ቲልበርግ ዩኒቨርስቲ በካልቸራል ስተዲስ (Islamic studies) ነው። ከዚህ ቀደምም በአካውንቲንግ እና ፋይናንስ፣ እንዲሁም በሥነ ልቦና ጥናት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አጠናቅቋል። ከኤገስትም እንዲሁ የማስተርስ ዲግሪ በሥነ መለኮት እና የሪሰርች ማስተርስ በክርስቲያን ሙስሊም ግንኙነት ላይ ሠርቷል። የጋራ ትውስታ (Collective memory)፣ በኢስላማዊ ቅስቀሳዎች (Islamic activism)፣ በብልጽግና ወንጌል፣ በጋራ ጥቅሞች (Common good)፣ በሜንቶሪንግና በማማከር ላይ ምርምር የማድረግ ፍላጎት አለው።

Share this article:

ቅዱስ መንፈስም ይለያል!

በደግም ቀን ሆነ በክፉዉም ዘመናት ክርስቶስን እና እውነተኛ ትምህርቱን የሚገልጠው መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ሊሆን ይገባል ስንል በብዙ ምክንያቶች ነው። አንድም ዙሪያችን በብዙ እንቅስቃሴዎች የተሞላ በመሆኑ በተፈጥሮውም ሆነ በመንፈሳዊው ዓለም ብቻችንን አይደለንምንና ነው። አንድም በአንዱ መንፈስ ቅዱስ የማይገዛ ሕይወት፣ ትምህርት እና አገልግሎት ለሌሎች ብዙ መንፈሶች ጥቃት ስለሚጋለጥ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ

መንፈስ ቅዱስ በታሪክ ውስጥ

በዘመናችን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ምስባኮች ላይ መንፈስ ቅዱስ የሚለው ስም መጥራት የተለመደ ቢሆንም፣ ሕዝበ ክርስትያኑ ስለ መንፈስ ቅዱስ ማንነት ጠንቅቆ ያውቃል ለማለት አስቸጋሪ ይመስላል። መንፈስ ቅዱስን አስመልክቶ ግልጽ አስተምህሮ ያለም አይመስልም። ለአንዳንዶች መንፈስ ቅዱስ ተአምራት ማድረጊያ ኀይል፣ እንዲሁም በጨርቅ ተደርጎ እና በጠርሙስ ታሽጎ የሚወሰድ ትንግርት መፍጠሪያ ሲሆን፣ ለሌሎች ደግሞ ማነቃቂያ እና ተሃድሶ የሚያመጣ እሳት ወዘተ. ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ

ትጥቅ አስፈቺው ኢየሱስ!

ናኦል በፈቃዱ፣ የሰሞኑ መነጋገሪያ ከሆነው ትጥቅ የመፍታትና አለመፍታት ፖለቲካዊ ውዝግብ ባሻገር፣ ሌላ ትጥቅ አስፈቺ እንዳለ ያስታውሰናል። ክርስቲያኖችም የትጥቅ ትግል እንዴት ሊያዩት እንደሚገባም ሐሳብ ያቀብላል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.