[the_ad_group id=”107″]

‘ምን ላስብ? ምንስ ላድርግ?’ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ

የወንጌል አማኝ ነኝ። የወንጌል አማኝ በመሆኔ ከክፉ ዳንኩ እንጂ ከዓለም አልወጣሁም። ከዓለም ወጥቼም ከሆነ፣ የወጣሁት ዓለማዊነት ከውስጤ ወጥቶ የወንጌል መልእክተኛ ሆኜ ወደ ዓለም እንድላክ እንጂ፣ የራሴን እና የብጤዎቼን ደሴት ሠርቼ፣ ተነጥዬ እንድኖር አይደለም። ጥበብ እንደ ጎደላት ሰጎን ጭንቅላቴን አሸዋ ውስጥ ቀብሬ ‘የለሁም’ ካላልኩ በስተቀር የአገሬ፣ የምድሬ ነገር ያገባኛል። ጥሪዬ ለምድር ጨውነት፣ ለዓለም ብርሃንነት እስከ ሆነ ድረስ ምድሩና ዓለሙ የሥራ መስኬ፣ የተግባር መከወኛዬ እንጂ ጥዬ የምሸሸው ጣጣ አይደለም። ያመንኩት የዓለምን መድኃኒት ነው፤ መድኃኒቱን ተቀብዬ መዳን ብቻ ሳይሆን መድኃኒት እንድሆን ተጠርቻለሁ። ስለዚህ ጥል ባለበት ፍቅርን፣ መለያየት ባለበት አንድነትን፣ ጥፋት ባለበት ልማትን፣ ኹከት ባለበት ሰላምን ለማወጅ ተጠርቻለሁ።

ሁላችንም እንደምናውቀው አገራችን ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ላይ ትገኛለች። ይህ ለውጥ ትልቅ ተስፋ አንግቦ፣ በሥጋቶች ታጅቦ እየተመመ ነው። ትናንት አሸባሪ ተብለው በባዕድ ምድር ይንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ኀይሎች ዛሬ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ አገር ቤት ገብተዋል። ተዘግተው የነበሩ መገናኛ ብዙኀን ተከፋፍተዋል። ፌስ ቡክ፣ ዩቲዩብ እና የተለያዩ ማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች እያንዳንዱን ግለ ሰብ ጋዜጠኛ፣ እያንዳንዱን ገጽ ጋዜጣ አድርገውታል። ላለፉት 44 ዓመታት የተቀነቀነው የሶሻሊዝም አስተሳሰብና ላለፉት 27 ዓመታት የናኘው ዘር ተኮር አስተሳሰብ ገና ከአገራችን ጫንቃ ላይ አልተራገፈም። ከዚህም የተነሣ እዚህም እዚያም የሕይወት፣ የአካልና የንብረት ጥፋቶች ይሰማሉ። ታዲያ እንደ ወንጌል አማኝ በእንዲህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ‘ምን ላስብ? ምንስ ላድርግ?’ የሚል ጥያቄ መነሣቱ አይቀርም። ሐሳቤን የምሰነዝረው የትኛውንም ቡድን በመደገፍ ወይም በመንቀፍ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ አንድነቷ ተጠብቆ፣ ሰላሟ ደምቆ፣ ልማቷ አሸብርቆ ለማየት ካለኝ ናፍቅቶ በመነሣት ብቻ ነው። ለጊዜው ሦስት ምክሮችን ልለግሥ።

በረከታችንን እንቁጠር

“ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ፥ ምስጋናውንም ሁሉ አትርሺ” መዝ. 103፥2

ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡበት መጋቢት 24፣ 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ያሳለፍናቸው 136 ቀናት (ይህ ጽሑፍ እስከተጻፈበት) በአገራችን ታሪክ የተለዩ ጊዜያት ናቸው ቢባል ማጋነነ አይሆንም። በእነዚህ ጊዜያት እግዚአብሔር ከአእምሮ በላይ የሆኑ ታላላቅ ነገሮችን አድርጎልናል። ስለዚህ በዕለት ተዕለት ዜና ከመወሰዳችን በፊት፣ ቆም ብለን ወደ ኋላ ተመልክተን፣ ባርኮታችንን እየቆጠርን እግዚአብሔርን ልናመሰግን ይገባናል።

 • ሕዝብ በመንግሥት ላይ፣ ሕዝብ በሕዝብ ላይ ተነሥቶ የመበታተንና የመጠፋፋት አደጋ ባንዣበበብን ማግሥት እግዚአብሔር የክፋትን ጉም በትኖ የሰላምን አየር እንድንተነፍስ አድርጎናል። ከዚህ በላይ ምን የምስጋና ርእስ ሊመጣ ይችላል?!
 • በኅሊና እስረኞች ተሞልተው የከረሙት የእስር ቤቶቻችን መዝጊያ ተቆርጦ አዕላፋት የነጻነትን አየር ተንፍሰዋል። ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ይፈጸምባቸው የነበሩ ማሰቃያ ስፍራዎች ተዘግተዋል። በእስረኞቹ ጫማ ውስጥ ሆነን ካሰብነው ይህ ትልቅ የምስጋና ምክንያት ነው።
 • የመጣው ለውጥ ከዚህ ቀደም እንደምናውቃቸው ለውጦች አንድ ሥርዐት ወድቆ፣ የሥርዐቱ አቀንቃኞችና አራማጆች ከሥር ተነቅለው በሌላ የሚተኩበት ሂደት ሳይሆን፣ ሁሉ በሥፍራው እያለ የመጣ የአስተሳሰብና የተግባር ለውጥ መሆኑ ቢያንስ በዕድሜ ዘመናችን ሁለት ጊዜ ያየናቸውን እያፈረሱ የመገንባት አዙሪት ሽሮልናልና በማስተዋል እግዚአብሔርን ልናመሰግን ይገባል።
 • በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የኢትዮጵያን መንግሥት በኀይል ለመታገል የሚንቀሳቀስ ቡድን በባዕድ ምድር የማይኖርበት ብቸኛ ጊዜ ቢኖር አሁን ይመስለኛል። ነፍጥ ያነሡ ተቃዋሚ ኀይላት ሳይቀሩ ጠቅልለው ወደ አገር ቤት የገቡበትና እየገቡ ያሉበት ጊዜ ነው። ይህ ያለ እግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት ሊታሰብ አይችልምና ባርኮታችንን እየቆጠርን እግዚአብሔርን ልናመሰግን ይገባናል።
 • ከኤርትራ ጋር የወረደው ዕርቅና የፈሰሰው ፍቅር፣ ከሌሎችም ጎረቤት አገሮች ጋር የተፈጠረው መረጋጋት ቆም ብለን ባርኮታችንን እየቆጠርን እግዚአብሔርን እንድናመሰግን ይጣራል።
 • ለበርካታ ዓመታት ተለያይተው በኖሩ ሃይማኖቶች መካከል ዕርቅ ወርዶ፣ አንድነት ሰምሮ፣ ቤተ እምነቶች ተከባብረው የሚኖሩበት መደላድል መገንባቱ ራሱን የቻለ የምስጋና ሰበብ ነው። ስለዚህ ቆም ብለን በማስተዋል እግዚአብሔርን እናመስግን።

እንረጋጋ

“ዐውሎንም ጸጥ አደረገ፥ ሞገዱም ዝም አለ። ዝም ብሏልና ደስ አላቸው፤ ወደ ፈለጉትም ወደብ መራቸው። ለሰው ልጆች ስላደረገው ተአምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን አመስግኑ።” መዝ. 107፥29-31

 • ለውጡ ከረዥም ጊዜ በኋላ የመጣና ሁሉ ነገር ባለበት የተከሰተ በመሆኑ፣ በተለያዩ ስፍራዎች ሽኩቻዎችና መቆራቆሶች እንደሚኖሩ መገመት ተገቢ ይሆናል። ታፍኖ የከረመ ሕዝብ ስሜቱን በነጻነት እንዲገልጽ ሲለቀቅ መፋነኑ አይቀርም። ‘እከሌ ጠላትህ ነው፤ እከሌ እንዲህ አድርጎሃል’ የሚለውን ስብከት ሲጋት የከረመ ሕዝብ፣ ዙሪያ ገባውን አይቶ እስኪሰክን መበጥበጡና መበጥበጡ የማይቀር ነው። ከዚህ የተነሣ ደስ የማያሰኙንን ነገሮች ማየትና የማይመቹንን ወሬዎች መስማት ይኖራል። መፍትሔው በምንሰማው ስሜታችን እንዲናወጥ ባለመፍቀድ መረጋጋት ነው።
 • ቋሚውን ከጊዜያዊው መለየት እጅግ ጠቃሚ ነው። የምንሰማው ዜና ዕለታዊና ወቅታዊ ነው። ለአገራችን የሚያስፈልጋት ለውጥ ግን ዘላቂና አስተማማኝ መሆን አለበት። መንግሥት ሰብአዊነትን ባከበረ መንገድ ፍትሕን ማስፈን ይጠበቅበታል። ሆኖም ይህ በአሁኑ የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ትዕግስትን የሚጠይቅና የሚፈትን ጉዳይ ይመስላል። ሕዝብ ከፖለቲካ ልሂቃኑ ይልቅ ሃይማኖታዊ መርሖውንና ባህላዊ ዕሴቱን በመከተል ተረጋግቶ ሌላውንም ሊያረጋጋ ይገባዋል። ያኔ ሕግና ሥርዐት የሚሰፍንበት፥ ሕዝብ ተከባብሮና ተባብሮ የሚኖርበት ሥርዐት እየተደላደለ ይመጣል። የፖለቲካው፣ የኢኮኖሚውና የማኅበራዊው ወንዝ የሚፈስስበት ቦይ እየተመሠረተ፣ በሕግ አውጪው፣ በሕግ አስፈጻሚውና በሕግ ተርጓሚው መኻል ያለው የልዩነትና የአንድነት ሚዛን እየተጠበቀ፣ ከመንግሥት ባሻገር በአገር ሰላምና በዜጎች ደኅንነት ላይ ጉልሕ ሚና ያላቸው የፍትሕ ተቋማትና የሕዝብ ማኀበራት እየተደራጁ ይሄዳሉ። ይሄ እንዲከወን ግን ሕዝብ መረጋጋት ይኖርበታል። ስለዚህ እንረጋጋ!
 • መንግሥት የሕዝብን ጥያቄ መመለስ ሲያቅተውና አገርን በሥርዓት መምራት ሲሳነው ሕዝብ ይደናገጣል፤ ይህ የተደናገጠ ሕዝብ ከእለት ተእለት ተግባሩ ወጥቶ በአስተዳደር ጉዳይ ውስጥ ይገባና ይጠቅማል ያለውን ሐሳብ ሁሉ ይሰነዝራል። በአጭር ቃል ዜጋው ሁሉ ፖለቲካውን በእጁ ይወስዳል። ሆኖም ጥያቄዎች በተወሰነ መጠን መልስ ሲያገኙና የሕዝብ ልብ የሚያርፍበት አመራር በስፍራው ሲቀመጥ ሕዝብ እየሰከነና የአገር አስተዳደሩን ጉዳይ ለባለሙያዎቹ እየተወ ወደ ተግባሩ ይመለሳል። ይህ ፈጥኖ የማይሆን ከሆነ ግን ለአመራር አስቸጋሪ ይሆናል። ትናንት መንግሥት ሲያስርና ሲገድል ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ ሲማጸን ነበር፤ ዛሬ ደግሞ የሚገድለውና የሚያሳድደው ሕዝብ (ሕዝብ ውስጥ የተሸሸጉ ጥቂቶች) ሆኖ መንግሥት ሲማጸን ይታያል። ቁም ነገሩ መሪን ማድነቅና ማሞገስ ሳይሆን፣ ለአመራሩ እንዲመች መስከንና መረጋጋት ነው።
 • መልካሙ ለውጥ ይቀጥል ይሆን? ሰላሙስ ይዘልቅ ይሆን? የሚለው ሥጋት እዚህም እዚያም ከሚስተዋለው የእኩዮች ተግባርና የውሸት ዜናዎች ጋር ተደምሮ አገርን ይንጣልና እንደ ወንጌል አማኝ ትናንት ከክፉ የጠበቀን፣ ፍቅርንና ምሕረትን፣ አንድነትንና መከባበርን የሚሰብኩ፣ ለዚህም የሚሠሩ መሪዎች የቸረን እግዚአብሔር በዙፋኑ እንዳለ በማመን ልንረጋጋ ይገባል።

እንተባበር

 • “ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን። ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ” ሮሜ 12፥9
 • ለምድራችን የሆነው ትድግናና የመጣው ሰላም፣ የእውነተኛ አማኞች ምልጃ ውጤት እንደ ሆነ አሌ የማይባል ሐቅ ነው። ሆኖም፣ “ቅዱስ ሁሉ በምቹ ጊዜ ወደ አንተ ይለምናል፤ ብዙ የጥፋት ውኃም ወደ እርሱ አይቀርብም።” ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ጸሎት በኹከትና በግርግር ጊዜ ብቻ ሳይሆን፣ ሰላም በሚመስልም ጊዜ ሊከወን ይገባዋልና ዛሬም ስለ አገራችን መጻዒ ሁኔታ በመጾምና በመጸለይ ልንተባበር ይገባል።
 • ማኅበራዊ ሚዲያዎች ባመዛኙ ጥላቻን በመስበክ፣ ዘረኝነትን በማቀንቀን፣ አሉባልታን በመንዛት ተወጥረዋል። የሐሰት ዜናዎች (fake news) ዕለታዊ ትዕዛዝ ሆነዋል። ስለዚህ እንደ ወንጌል አማኝ እነዚህን ከመፍጠርም ሆነ ከማሰራጨት መጠበቅ ይኖርብናል። የወሬና የመረጃ ምንጮቻችን የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ከተላበሱና ተጠያቂነት ካለባቸው ተዓማኒ ምንጮች ሲሆኑ፣ ጥሩ ውሃ እንደ መጠጣት ያህል ነውና ከተባራሪ ዜናዎች ራሳችንን እንጠብቅ። ቅዱስ ቃሉ፥ “እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ” (ፊሊ. 4፥8) እንዲል።
 • ልግሥና የገንዘብ ብቻ አይደለም። ከተፈወሰ አእምሮ የሚመነጭ የበጎ ሐሳብ ልግሥና ውድ ሥጦታ ነው። ስለዚህ ለአገርና ለወገን የሚጠቅሙ፣ አንድነትን የሚያጎለብቱ፣ ይቅርታንና ሰላምን የሚያበረታቱ፣ ፍትሕን የሚያሠርጹ በጎ አሳቦችን በመለገሥ እንተባበር።
 • አገር የሚያድገው በሥራ ነው፤ የሚሠራውም ዜጋ ነው። መሪዎች ይመራሉ እንጂ አያመርቱም። የጥሩ አመራር መገለጫው ሕዝብ ጊዜውን፣ ዕውቀቱን፣ ጉልበትን፣ ወዘተ. እንዲሰጥ ማድረጉ ነው። “በእስራኤል ውስጥ መሪዎች ስለ መሩ፥ ሕዝቡም ነፍሳቸውን በፈቃዳቸው ስለ ሰጡ፥ እግዚአብሔርን አመስግኑ” (መሳ. 5፥2) እንደሚል እኛም በተሰማራንበት መስክ ሁሉ በትጋትና በመሰጠት እንሥራ፣ እንፍጠር፣ እናምርት . . .።

Share this article:

መሪነትም እንደ ውበት

ለመሆኑ፣ የየቤተ ክርስቲያኑ መሪዎች አንድን የአመራር ዘይቤ በሚመሯት ቤተ ክርስቲያን በሥራ ላይ እንዲውል ካደረጉ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች እንዳሰቡት የአመራር ዘይቤውን ውጤታማነት ማየት ቢቸግራቸው ምን ማድረግ ይችላሉ?

ተጨማሪ ያንብቡ

የፍትሕ ጩኸት እና የዝምታ ኀጢአት

በቤተ ክርስቲያንና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት በሚመለከት በታሪክ ሁለት ጽንፎች መንጸባረቃቸውን የሚያስታውሰው ዶ/ር ግርማ በቀለ፣ ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ በአገራችን የሚታየውን እኩይ ምግባር በአደባባይ ለመኮነን አቅም ሊያንሳት አይገባም ይላል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.