
“አሁን ብትመለስ ጌታ ወደ ቤትህ”
“ስንቶች ለስምህ ቆመው ዘምረዋል
ስንቶች በስምህ ስብከትን ሰብከዋል
አሁን ብትመለስ ጌታ ወደ ቤትህ
ከሕይወት ጎድለዋል ጠፍተዋል ልጆችህ”
[the_ad_group id=”107″]
የተለያዩ ክስተቶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በማያያዝ፣ “በዚህ ጊዜ ጌታ ሊመጣ ነው፤ የዓለም መጨረሻ ሊሆን ነው” የሚሉ ግምቶች ከመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ለመኖራቸው ታሪክ እማኝ ነው። የመጀመሪያው ዘመን የኢየሩሳሌም አማኞች ከአይሁድ ከሚደርስባቸው ስደት የተነሣ፣ የሮም ክርስቲያኖች ከሮም መቃጠልና ይህንን ተከትሎ ኔሮ ባስነሣባቸው እንደ እሳት የሚፋጅ ስደት ምክንያት የመጨረሻው ዘመን መቃረቡን አስበው ነበር። ከእስልምና ሃይማኖት በጦር ኀይል መስፋፋትና ከቤተ ክርስቲያን መዳከም ጋር በተያያዘ፣ በኋለኞቹ ዘመናትም ከአንደኛው እና ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጋር፣ በኮምዩኒዝም ክህደት ምክንያት፣ በቤተ ክርስቲያንና በክርስቲያኖች ላይ በደረሰው ዘግናኝ ሥቃይና ስደት፣ ከአውሮፓ ኢኮኖሚክ ኮምሽን ምሥረታ ጋር ወዘተ. በተያያዘ የመጨረሻው ዘመን እንደ ደረሰ የገመቱ በርካቶች ነበሩ።
ዘመንን ከብሉይ ኪዳን ትንቢትና ከአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ጋር በማጣቀስ “የክርስቶስ መምጫው በዚህ ቀን ነው” እስከ ማለት በደረሰ መላ ያጣ ግምት ተከታዮቻቸውን እስካሳቱና መሳለቂያ እስከሆኑት “የይሆዋ ምስክር ነን” ባዮች እንዲሁም ክርስቶስ በ2011 ይመጣል ብለው ትንቢት እንደተናገሩት የፋሚሊ ሬድዮ መሥራች ያሉ ያሉ በርካቶች ናቸው። የይሆዋ ምስክር የተሰኘው ድርጅት አባላትም የክርስቶስ መምጫ በዚህ ቀን ይሆናል ብለው ተንብየው ሲያበቁ፣ በተባለው ቀን ትንቢቱ ባለመፈጸሙ “ካፈርኩ አይመልሰኝ” በማለት በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ጅማሬ “በ1914 ላይ ክርስቶስ በመንፈስ ወደ ዓለም መጥቶ መግዛት ጀምሯል፤ የአምላክ መንግሥትም በዚህ ጊዜ ተመሠረተ” በማለት እውነታውን ክደዋል።
የመጨረሻው ዘመንን በተመለከተ የተለያዩ አመለካከቶች ቢኖሩም፣ ሁሉም ወገኖች የሚስማሙበት ቁልፍ የክርስትና አስተምሀሮ ግን የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ተመልሶ መምጣት ርግጥ መሆኑን ነው። እንደ ነገረ ክርስቶስ፣ ነገረ ድነት፣ ምስጢረ ሥላሴ ሁሉ ነገረ ፍጻሜ መሠረታዊ የክርስትና ትምህርት መሆኑ ሊሠመርበት ይገባል። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የምንመለከታቸው የ2007 ዓለም አቀፍ ክስተቶችን አንድ በአንድ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ማያያዝ አይቻልም። ምክንያቱም ጦርነት፣ በሽታ፣ የተፈጥሮ አደጋዎች፣ ወዘተ. በዚህ ባለንበት ዘመን የጀመሩ ሳይሆን፣ ከውድቀት ጀምሮ የነበሩ የሰው ልጅ ታሪክ ክፍል መሆናቸው ነው። ይሁን እንጂ፣ እነዚሁ ክስተቶች በመጨረሻው ዘመን እጅግ በከፋ ሁኔታ እየጨመሩ እንደሚሄዱ ማስተዋል ወዲሁም ደግሞ ዘመኑን መመርመር ተገቢ ነው።
ባለፉት 12 ወራት የበርካቶችን ትኩረት የሳቡ ክስተቶች ተፈጽመዋል፤ እየተፈጸሙም ይገኛሉ። በ2007 ዓ.ም (በፈረንጆቹ 2014/15) በዓለም ላይ የተፈጸሙት ዐበይት ክስተቶች ምን ዐይነት ተጽእኖ በዓለማችን ላይ አምጥተዋል? ስለ ተፈጸሙት እና እየተፈጸሙ ስላሉት ነገሮችስ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ደቀ መዛሙርቱ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን “… የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱ ምንድር ነው?” ብለው በጠየቁት ጊዜ (ማቴ. 24፥3) የሰጣቸው መልስ፡-
6 ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ …። 7 ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፥ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤ 8 እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። 9 በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፥ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። 10 በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ፤ 11 ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ፤ 12 ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። 13 እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። 14 ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።
እነዚህን ትንቢቶች ባለፉት 12 ወራት ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች ሽፋን ከሰጧቸው ጉዳዮች ጋር አያይዘን እንመልከት።
ለአፍታ እንኳን ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮችን የከፈተ ሰው ዓለማችን በቀን ውስጥ ከሚገጥሟት ክስተቶች ውስጥ አብዛኛው ሽፋን የሚሰጠው የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋ፣ ጦርነት፣ ስደት፣ ፖለቲካዊ ውዝግብ፣ ግድያ፣ ጾታዊ ጥቃት ዋና ዋናዎቹ ሆነው ያገኛቸዋል። በ2007 ዓ.ም. በዓለማችን ከፍተኛ ትኩረት ከሳቡ ክስተቶች ውስጥ በጨካኝቱ እና በሚፈጸማቸው ዘግናኝ ግድያዎች፣ ምናልባትም በዓለም ታሪክ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት አሸባሪው ቡድን አይሲስ እስላማዊ መንግስት ለመመሥረት ነፍጥ አንሥቶ የበርካቶችን ሕይወት መቅጠፉን መቀጠሉ ይገኝበታል። አይሲስ በኢራቅ እና በሶሪያ ባደረጋቸው ወረራዎች የየአገራቱን ሰፊ አካባቢ ከተቆጣጠረ በኋላ የበርካቶችን ሕይወት እንደ ቅጠል ማርገፉን ቀጥሏል። የቡድኑን እኩይነት የሚያጎሉት ደግሞ እጅግ ዘግናኝና ኢ-ሰብአዊ በሆነ ሁኔታ ሕፃናትን ሳይቀር አሠቃይቶ መግደሉ ነው።
እስከ ሰኔ 2007 ድረስ ብቻ ለዓመታት በዘለቀው የሶርያ የእርስ በርስ ጦርነትና በአይሲስ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 210,060 ሲሆን፣ 10,664 ሕፃናትና 6,783 ሴቶች ከሟቾቹ ውስጥ ይገኛሉ ሲል የሬውተርስ የዜና ምንጭ ዘግቧል። አሶሽየትድ ፕሬስ የዜና ምንጭ በበኩሉ በሐምሌ 2007 እንደ ዘገበው በኢራቅ በአይሲስ ሽብርተኛ ቡድን ጥቃት ምክንያት 5,576 ሰዎች ሕይወት ሲጠፋ፣ 1.2 ሚሊዮን ሰዎች ከቤታው እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል ብሏል። በሶሪያ ለዓመታት በዘለቀው በመንግሥትና ተቃዋሚዎች መካከል በተከፈተው የእርስ በርስ ጦርነት ሳቢያ 11,420 ሕፃናት በፍንዳታና በጥይት ሕይወታቸው እንዳለፈ ተዘግቧል። እንደተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዘገባ በአጠቃላይ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ በኢራቅ ቁጥራቸው 7,800 የሚሆኑ ሰላማዊ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ወደ እስራኤልም ስንመጣ ሦስት እስራኤላውያን ታዳጊዎች ታግተው ከተገደሉ በኋላ በእስራኤልና በፍልስጥኤም መካከል ውጥረት ተከስቶ ከእስራኤል ወገን በጋዛ ሰርጥ የበቀል ቅጣት ሲደረግ፣ በሀማስ በኩል የሮኬት ጥቃት በእስራኤል ላይ ተሰንዝሯል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባወጣው ሪፖርት መሠረት 2,192 ሰዎች በጋዛ ሰርጥ ሲገደሉ፣ በእስራኤል በኩል ደግሞ 72 ሰዎች ጉዳት እንደ ደረሰባቸው ታውቋል።
በፈረንጆቹ 2014 የዓለምን ትኩረት በከፍተኛ ሁኔታ ከያዙ ጉዳዮች አንዱ በምሥራቅ አውሮፓዊቱ አገር ዩክሬይን ከሩሲያ ጋር ውሕደትን በሚያቀነቅኑ አፍቃሪ ሩሲያውያንና በዩክሬን መንግሥት መካከል በተፈጠረው ግጭት ከዋና ከተማዋ ኪዬቭ ጀምሮ መላ አገሪቱ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ መግባቷ ነው። በዋና ከተማዋ ኪዬቭ የሩሲያ ደጋፊዎች ባካሄዱት ሰልፍ ላይ በተነሣ ግጭት 1,100 ሰዎች ሲቆስሉ፣ 82 ሰዎች እና 13 የፖሊስ አባላት እንደ ሞቱ በወቅቱ ተዘግቧል።
በቅርቡ እንደ አገር ተመሥርታ ሕልውናዋን ያገኘችው ደቡብ ሱዳን በባለሥልጣኖቿ መካከል በተፈጠረ እሰጥ አገባ የአገሪቱ ጦር ለሁለት ተከፍሎ ከፍተኛ እልቂት ያስከተለ ጦርነት መከሰቱ ይታወሳል። በኢጋድ የሰላም አደራዳሪዎች ከፍተኛ ጥረት ጦርነቱ ጋብ ቢልም የሰላም ስምምነቱ እልባት ሳያገኝ እየተጓተተ ይገኛል። የኢኮኖሚ ጉዳዮችን በግርድፉ ስንመለከትም፣ የግሪክ መንግሥት የገጠመው የኢኮኖሚ ውድቀት ዋነኛ የዜና ሽፋን ሆኖ የከረመ ሲሆን፣ የዓለምን ምጣኔ ሀብት በከፍተኛ ሁኔታ ከሚያንቀሳቅሰው የነዳጅ ዘይት በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋጋው አሽቆልቁሎ የነዳጅ ላኪ አገራትን ኢኮኖሚ ውጥረት ውስጥ የከተተ ክስተት መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
ሌላው የዓመቱ አስከፊ ዜና አጥፍቶ ጠፊዎች በእስልምና ሃይማኖት ስም እጅግ አስከፊና ዘግናኝ አደጋ ያደረሰቡበት መሆኑ ነው። በመስከረም 07 2007 ዓ.ም. በአፍጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡል፣ በታሊባን ታጣቂዎች የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት 3 የኔቶ (NATO) ወታደሮች የተገደሉ ሲሆን፣ ከሞቱት ወታደሮች በተጨማሪ 16 ንጹሓን ዜጎች መጎዳታቸው ታውቋል። “ፍንዳታው የአካባቢው ያሉትን ሕንጻዎች አናግቷል” ሲል የዘገበው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ነው። በፈረንጆቹ ጥር 7 ቀን፣ 2007 ዓ.ም. በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ ቻርሊ ሄብዶ የተሰኘው ጋዜጣ አዘጋጆች በስብሰባ ላይ ሳሉ ሁለት አሸባሪ ወንድማማቾች በከፈቱት ተኩስ 11 ሰዎች ተገድለው ሌሎች 11 ሲቆስሉ፣ ጥቃቱን የሰነዘሩት ወንድማማቾች ከሁለት ቀናት በኋላ በፈረንሳይ ፖሊስ ተገድለዋል። ይህንን የሽብር ድርጊት በማውገዝ 3.7 ሚሊዮን ሰዎች በፈረንሳይ ድርጊቱን ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸው የወራት ትውስታ ነበር። ወደ አሜሪካ ስንሻገር፣ በነሐሴ ወር ሚካኤል ብራውን የተባለ ጥቁር የ18 ዓመት ታዳጊ፣ ፈርጉሰን በተባለች ከተማ በነጭ የፖሊስ ባልደረባ ተገድሎ ከፍተኛ የጥቁሮች ብጥብጥ የተነሣበት ዓመት ነበረ።
በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ናይጄሪያ ዓለምን እጅግ ያነጋገረ ድርጊት ተፈጽሟል። ቦኮ ሀራም የተሰኘው እስላማዊ አሸባሪ ቡድን በሽብር ድርጊቱ ዕድሜያቸው በ16 እና 18 መካከል የሚገኙ 276 ሴት ተማሪዎችን አግቶ ባልታወቀ ጫካ ውስጥ እንደ ሰወራቸው ተሰምቷል። ይህንንም በማውገዝ በበርካታ የዓለማችን ክፍሎች ሰላማዊ ሰልፎች የተከናወኑበት ዓመት ነው፤ 2014/15። እንደ ተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮ ቢሮ (UNOCHA) ገለጻ፣ የናይጄሪያው አክራሪ ቡድን ቦኮ ሀራም ባስነሣው ግጭት እስከ መጋቢት 2015 ድረስ 1.2 ሚሊየን ሰዎች ከሰሜናዊ ምሥራቅ ናይጀሪያ፣ 47,276 ደግሞ ከሰሜናዊና ሰሜናዊ ምሥራቅ ክልል የተፈናቀሉ ሲሆን፣ 168,000 ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው ወደ ጎረቤት አገራት ኒጀር፣ ቻድ እና ካሜሮን ተሰደዋል። ከአንዳንድ የመረጃ ምንጮች እንደሚሰማው ቦኮ ሀራም ከጥር 2014 ጀምሮ ለ8,700 ሰዎች ሕይወት ማለፍ ምክንያት ሲሆን፣ ሕልውናውን ካወጀና ጥቃት መሰንዘር ከጀመረ አንሥቶ በአጠቃላይ ከ13 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈ ታውቋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሰነዘሩ የሽብር ጥቃቶችን እንደሚዘግበው ድረ ገጽ (www.thereligionofpeace.com) ዘገባ ከሆነ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ጥር 1 ቀን 2015 ጀምሮ እስከሐምሌ31ቀን2015ድረስባሉት8ወራትብቻ በዓለም ላይ በተለያዩ ስፍራዎች 1,836 የሽብር ጥቃቶች ተሰንዝረው 18,948 ሰዎች ሲገደሉ፣ 16,329 ሰዎች መቁሰላቸው ታውቋል።
የዓለም የምግብና ዕርሻ ድርጅት (FAO) እንዳስታወቀው በ2003 እና 2013 መካከል በማደግ ላይ በሚገኙ አገራት የሚኖሩ 1.9 ቢሊዮን ሰዎች አደጋ ውስጥ እንደገቡና የጉዳቱ መጠንም በገንዘብ ሲሰላ 49 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚሆን ገልጿል። የጎርፍ አደጋን ስንመለከት በቦስኒያ፣ በአፍጋኒስታን እና በኔፓል ከፍተኛ ጎርፍ ተከስቶ 43 ሰዎች ሞተው 175 ሰዎች ሲቆስሉ፣ 50 ሰዎች የገቡበት እንዳልታወቀ በወቅቱ ተዘግቧል። በፈረንጆቹ 2014 ዓ.ም በአሜሪካና ደቡባዊ ካናዳ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን አደጋ ውስጥ የከተተ፣ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ያደረገ፣ በርካታ የአየር በረራዎች እንዲሰረዙ ምክንያት የሆነ አደገኛ የአየር ንብረትና የጎርፍ አደጋ ተፈጥሮ እንደ ነበር ይታወሳል። ባዳክሻን የተሰኘ አነስተኛ የአፍጋኒስታን ከተማን የመታው ጎርፍ 300 ቤቶች እንዲቀበሩ ሲያደርግ፣ ለ2,100 ሰዎች ሕይወት ማለፍ ምክንያት ሆኗል። በፓኪስታን ካሽሚር ግዛት ጃሙ በተሰኘ አካባቢ የተከሰተው የጎርፍ አደጋ 282 ሰዎችን ለሞት ዳርጓል። በቻይና ላውንዲ በተሰኘች 265,900 ሰዎች በሚኖሩባት መንደር በተከሰተ የምድር መንቀጥቀጥ የ600 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ 2,400 ቆስለዋል። በተጨማሪም 230,000 የሚሆኑ ሰዎች በአደጋው ጉዳት ሲደርስባቸው፣ 12,000 ቤቶች እንደ ፈረሱና 30,000 ቤቶች ጉዳት እንደ ደረሰባቸው ታውቋል። በጥቅምት ወር ኔፓል ውስጥ የተከሰተው ሳይክሎን የተሰኘ አደገኛ ነፋስ የቀላቀለ ዝናብ 568,000 ሰዎችን ከመኖሪያቸው ሲያፈናቅል፣ ለ61 ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል። በኅዳር ወር በፊሊፒንስ በተከሰተ አደገኛ ነፋስ 1.2 ሚሊዮን ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ሲሰፍሩ፣ ነፋሱ በትንሹ የ27 ሰዎች ሕይወት እንዲያልፍ ምክንያት ሆኗል። በሕንድ በተነሣ ከፍተኛ ሙቀት ምክንያት በርካታ ሰዎች ለህልፈተ ሕይወት መዳረጋቸው ይታወቃል።
ከማሌዥያ ዋና ከተማ ኩዋላላምፑር ወደ ቻይና ቤጂንግ 239 ሰዎች አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ የመንገደኞች አውሮፕላን የውሃ ሽታ ሆኖ የቀረው በፈረንጆቹ 2014 ማርች ላይ ነበረ። የጠፋውን አውሮፕላን ፍለጋ በርካታ አገራት አውሮፕላኖችን እና መርከቦችን አሰማርተው በፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ ሰፊ ፍለጋ ቢያደርጉም እስካገባደድነው ዓመት ድረስ ፍለጋው መና ቀርቷል። በ2014/15 በከፍተኛ ሁኔታ ዓለምን ሥጋት ውስጥ የከተተው በምዕራብ አፍሪካ አገራት የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። እንደ ዓለም የጤና ድርጅት ዘገባ በኢቦላ ምክንያት 18,000 ሰዎች ጉዳት ሲደርስባቸው፣ 7000 ሰዎች ሕይወታቸው ዐልፏል።
ከአገር አገር መሰደድ እና መፈናቀል የዓለማችን የዘወትር ክስተት መሆኑ ይታወቃል። በ2014 በጦርነትና በግጭት የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 60 ሚሊዮን መድረሱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጿል። በሶርያና በመካከለኛው ምሥራቅ የተፈጠሩ ግጭቶች ዋነኛ የመፈናቀል ምክንያት ናቸው። በርካታ ሰዎች ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ አገራት ለመግባት በሚያደርጉት አደገኛ የባሕር ላይ ጉዞ በሜዲትራኒያን ባሕር ላይ ሕይወታቸው እንደሚያልፍ በስፋት ሲዘገብ፣ ድርጊቱ የአውሮፓ አገራትን ሥጋት ውስጥ እንደ ከተተ ይታወሳል።
የዓለም ታሪክ የአክራሪዎች እና የአጥፍቶ ጠፊዎች ጥቃት የጨመረበት ይመስላል። 2007 አይሲስ በተሰኘው እስላማዊ አክራሪ ቡድን በርካታ ክርስቲያኖች በኢራቅ ለስደትና ለመከራ የተጋለጡበት፣በርካቶችም በግፍ የተገደሉበት ዓመት ነው። አገራችን ኢትዮጵያም የዚህ የግፍ ድርጊት ሰለባ የሆነች ሲሆን፣ በሊቢያ በስደት ላይ የሚገኙ 28 ኢትዮጵያውያንና 21 ግብፃውያን ክርስቲያኖች በጭካኔ የተገደሉበት ዓመትም ነው። ኦፕን ዶርስ ዶት ኦርግ የተሰኘ ድረ ገጽ በዓለም ዙሪያ በየወሩ 233 ክርስቲያኖች በእምነታቸው ምክንያት ይገደላሉ ሲል፣ 214 አብያተ ክርስቲያናትና የክርስቲያን ይዞታ የሆኑ ንብረቶች እንደሚወድሙ አትቷል። በተጨማሪም 772 ግጭቶችና ወንጀሎች በክርስቲያኖች ላይ ይከሰታሉ ብሏል። ዛሬም ክርስትና የሚጠይቀውን ዋጋ የሚከፍሉ፣ ስለ ወንጌልም የመከራን ጽዋ እየተጎነጩ የሚገኙ ክርስቲያች በርካቶች ናቸው፤ በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ይሰደዳሉና።
ክርስትና በዓለም ላይ በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ ላይ የሚገኝ እምነት ነው። በዓለም ላይ የወንጌላውያን ክርስቲያኖች ቁጥር በየዓመቱ የሚጨምር ሲሆን፣ ወንጌል ለሚሊዮኖች በመሰበክ ላይ ነው። 1.4 ቢሊዮን ሕዝብ እንዳላት የሚነገረው ኮምዩኒስት ቻይና 5 በመቶ ወይም 67 ሚሊዮን የሚሆነው ሕዝቧ ክርስቲያን ሲሆን፣ በ2015 የክርስቲያኖች ቁጥር 160 ሚሊዮን እንደሚሆንና በ2030 ቁጥሩ በከፍተኛ ሁኔታ አድጎ 247 ሚሊየን እንደሚደርስ ይገመታል። አምልኮ በሕግ የሚከለከልባት ቻይና በዓለም ክርስቲያኖች የሚሰደዱባት 37ኛ አገር እንደሆነች ወርልድ ዋች ሊስት ገልጿል።
ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረውን ቃል በ2007 ዓ.ም. ከታዩ ክስተቶች ጋር አያይዘን ስንመለከት የእያንዳንዷ ቀን ክስተት የቃሉን እውነተኝነት ያሳስበናል። “ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ … እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል” የሚለው የጌታችን ቃል ትኩረት ያሻዋል። ያለንበት ወቅት በርካታ አገልጋዮች ለወንጌል ጀርባቸውን ሰጥተው ለራሳቸው ምቾት የሚሯሯጡበት፣ በርካቶችም የቅድስናን ትምህርትና እውነተኛውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ለመታገሥ ዐቅም ያጡበት፣ ወንጌል ለራስ ብልጽግና እና ዝና ማግኛ የሆነበት፣ አምልኮ ለእግዚአብሔር መሆኑ ቀርቶ ለሰው ደስታ እና መዝናኛ የዋለበት ጊዜ ነው። የእርስ በርስ ብጥብጥ እና አለመግባባት በቤተ ክርስቲያን፣ በአገልጋዮች፣ በመሪዎችም መካከል የተስፋፋበት፣ የክርስቲያኖች የክስ ዶሴ መንግሥታዊ ቢሮዎችንና ፍርድ ቤቶችን ያጣበበበት፣ ወንጌል ዋጋ የሚከፈልለት መሆኑ ቀርቶ ዋጋ በምድር የሚገኝበት ሆኗል። ይህ ሁሉ ነገር ጌታችን ሊመጣ በደጅ እንደ ሆነ፣ ነገር ወደ ፍጻሜው እየፈጠነ እንደሆነ፣ ያለንበት ወቅት የዘመን እላቂ እንደ ሆነ ከመንገር ሌላ ምን ቋንቋ ይኖረው ይሆን!? ቃሉ አንዲህ ይላል፤ “ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ።”
ማራናታ!!!
Share this article:
“ስንቶች ለስምህ ቆመው ዘምረዋል
ስንቶች በስምህ ስብከትን ሰብከዋል
አሁን ብትመለስ ጌታ ወደ ቤትህ
ከሕይወት ጎድለዋል ጠፍተዋል ልጆችህ”
“ዘጠኙ ቅዱሳን” የተሰኘው ይህ የገናዬ ዕሸቱ ጽሑፍ፣ በወንጌልና ተልእኮ እንቅስቃሴ ላይ አተኩራ ከምታስነብባቸው ሥራዎቿ መካከል ሦስተኛው ነው።
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society
Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.
Add comment