
Encountering God Should Make You Afraid
“The fear of God is a form of xenophobia—a fear of the stranger, or, in this case, the One who is utterly strange and altogether different.” By Michael Horton, (the article is picked from TGL)
[the_ad_group id=”107″]
ዮሴፍ ዕድሜው ከ18 ወይም 19 የሚሆን አፍላ ወጣትና በሰላም የተቀመጠ ደኀና የኮንስትራክሽን/ የእንጨት ሥራ ባለሙያ ነው። የሚኖርበት አገር የዛፍ አገር ባለመሆኑ ብዙ ጊዜ የሚሠራው የእንጨት ሥራ አንዳንዴ እንጨት ወዳለበት እየሄደ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከሥፍራ ሥፍራ እየተዘዋወረና እንጨት እያስመጣ ነው። ምኞቱ ደኅና ሥራ ሲያጋጥመው ያቺን እየሠራ ተደላድሎ መኖርና ጨዋ ሠርቶ ዐዳሪ እስራኤላዊ መሆን ነው። በግል የስኬት ሕልማችን መኻል ጣልቃ የመግባት ሉአላዊ አቅምና መብት ያለው እግዚአብሔር ግን በዚህ ሰው ሕይወት ውስጥ እንግዳ ሆኖ መስተናገድ ፈለገ። እንዲህ ሲያደርግ ግን ከሙሉ መግቦቱ ጋር ነው። እያንዳንዳችንን ከምቾት ቀጠናችን አውጥቶ ታላላቅ አጀንዳዎች በእኛ ለመፈጸም እግዚአብሔር ሊጠቀምብን ይወድዳል።
ሔሮድስ ግን የሰይጣን አሻንጉሊት ነው፤ ሰይጣንም እግዜር ወደዚህ ዓለም እንዲህ ለጥቃት ተጋላጭ ሆኖ ይመጣል ብሎ አላሰበም ነበር። እኔ እንደሚመስለኝ ቅዱሳን ወ ርኩሳን መላእክት እግዜር ሰው ሆኖ በናዝሬት መንደር ጸራቢ ቤት ይወለዳል ብለው አያስቡም። በኋላም ተነግሯቸው ነው ለብሥራት የመጡት።
የሔሮድስና የሰይጣን ፍላጎት ግን አንድ ዐይነት ነው፤ ሁሉን በቁጥጥር ሥር ማዋል። ይህ ጥማት ደግሞ ሔሮድስን አእምሮውን ሁሉ ነው ያሳተው። ‘ዐድገው ከቁጥጥር ውጪ ይሆኑብኛል’ ብሎ የሰጋባቸውን ጨቅላ ሕጻናት ሁሉ ገና በቁጥጥሩ ሥር እያሉ መጨረስ መረጠ። የዮሴፍ እንግዳ ሕጻኑ “እግዜር-ሰው” ግን ወደ በርሃ ሄዷል። ልብ በል፤ በአንተ ቤት የሚስተናገድ ሕልም እግዜር የሰጠህ ከሆነ፣ በአንተ አቅም ሳይሆን ሕልሙን በሰጠህ አምላክ አቅም ነው የሚከለለው። ሔሮድስ ሕዝቡን የሚፈልገው ሊጠቅማቸው አይደለም፤ ሕዝቡ እንዲያውም ተወድዶ አያውቅም። መሪዎች ለፖለቲካ ጥቅማቸው ነው ሕዝብ የሚፈልጉት። በገሊላ፣ በሰማሪያና በይሁዳ ያሉ ሁሉ ይኸው ነው ታሪካቸው፤ ልክ እንደ ዛሬዎቹ።
በክርስቶስ ልደት ያ አካባቢ ወደ አፍሪካ፣ ግብፅ እንዲሁም እሲያ ለመሸጋገሪያ የመልከአ ምድር ጥቅምነት እንጂ፣ የኢኮኖሚ መስህብነት እንኳ የለውም። በአጠቃላይ እዚያ መወለድ ብዙም የሚያጓጓ አይደለም፤ ሃይማኖቱም የተፈቀደላቸው ፖለቲካውን እስካልነካ ድረስ ነው፤ ልክ እንደ አሁኑ። እጅግ ይገርማል!!! እንዲያውም ሰጥ ለጥ ብሎ ለተገዛ ሕልም ዐልባ ማኅበረ ሰብ እጹብ ድንቅ መቅደስ አሠርቶላቸዋል። ሔሮድስ ግን ከይሲ ንጉሥ ነው፤ የገዛ ሚስቱን የገደለ፣ ጣረሞቷ የሚያስጨንቀው የተጨናነቀ (stressful) ንጉሥ ነው። ሮም ያለውም ቄሳር የአይሁዳውያንን ሔሮድስ ዝም የሚለው ሕዝቡን ጭጭ እስካደረገለት ድረስ ብቻ ነው። የባሕርይ እናታቸው ግን አንድ ናት። የዓለም ሰላም ማለት ይሄ ነው። ከክፋት ጋር በመቻቻል የሚመጣ ሰላም የመጨረሻ ምንዛሪውም ክፋት ነው። ይህ ዐይነቱ መቻቻል እኛም ጋ ሲመጣ ግን መድኃኒቱን ከበሽታ የከፋ ገዳይ ያደርገዋል።
በሮም ታሪክ ዘጋቢዎች እንደተጻፈው፣ ሔሮድስ የሞት መኝታው ላይ በሕመም ወድቆ ሳለ ገና ሳይሞት አይሁድ በደስታ መፈንደቃቸውን በሰማ ጊዜ ጠቢብና ባለጠጋ አይሁዶች በሙሉ ታስረው እርሱ የሞተ ዕለት በሰይፍ እንዲገደሉና ሞቱ በልቅሶ እንዲደምቅ ፈልጎ ነበር፤ አልተሳካለትም እንጂ። ክፋት እስኪሞት ድረስ ክፋት ነው። ክፋት ቢማር የተማረ ክፋት፣ ቢበለጽግ ባለጸጋ ክፋት፣ ቢወፍር ወፍራም ክፋት፣ ቢቀጥን ቀጭን ክፋት፣ ቢጠቁር ጥቁር ክፋት ቢነጣም ነጭ ክፋት ይሆናል። ሔሮድስ ጅምላ ጨራሽ ክፋት ያለው አሸባሪ ንጉሥ ነው (የራሔል እንባ ይመስክር)፣ ቁጥራቸው ስንት እንደ ሆነ የማይታወቅ ሕጻናት ጨፍጭፏል።
ቤተ ክርስቲያን ሲገባም ክርስቲያን አይሆንም፤ ምንም ሹመት ስጡት ያው ክፋት ነው። ክፋት የሚለካው ስንት ሰው ላይ ደረሰ በሚል የምቾት ቀጠና መቆጣጠሪያ አሃዝ ሳይሆን በክፋትነቱ ነው። በአንድ ሰው የተነሣ ወደ ዓለም የገባ ኀጢአት በሰይጣን አጋፋሪነት፣ በሔሮድስ ሥራ አስፈጻሚነት በርካታ ሕጻናት አለቁ። የሕጻኑ ኢየሱስ የዝግጅት ዐላማ እስኪፈጸም ለጊዜው ከዚህ ክፋት ተሰወረ። የቤቱ እንግዳ ማንነት ገና በደንብ ያልገባው ዮሴፍ ግን በደረጃው የከለላ ሚናውን መጫወት ጀመረ፤ በዮሴፍ ለሕልም ታማኝነት የተነሣ ግን ለዚያ ሕዝብ የተስፋ ብርሃን ተጠብቆ ቆየ። ዮሴፍ በዚህ አጋጣሚ ግን የመላእክት ጓደኛ ሆነ (ማቴ 1፥20፤2፥13፡19) ሕጻኑ ተጸንሶ ሁለት ዓመት እስኪሞላው ሦስት ጊዜ መላእክት ጎበኙት። ከተመቻቸንበት ቀጠና የሚያንፏቅቀን እግዜር ከሆነ አዲስ ድምፅ መስማታችን ግድ ነው።
ወንጌላት ስለ ዮሴፍ የጻፉት ጥቂት ቢሆንም የዚህ አናጢ ቤት ግን ከሔሮድስ ቤተ መንግሥት የበለጠ ኀያል ንጉሥ አስተናገደ። እግዜር ቤትህን ሲመርጠው በፌሪቴል በትር ቅጽበታዊ ቅያሬ አያደርገውም፤ በአንተ ልክ አንሶ ስለሚመጣ የኖርከውን ኑሮ እየኖረ እንግዳህ ይሆናል። እግሩን ልታጥበው ሳይሆን እግርህን ሊያጥብህ ነው። ያኔ ነው መጠንቀቅ፤ እንግዳው ተራ እንግዳ ይመስልህና እግር አጣቢ ብቻ ላድርገው እንዳትል።
የጽድቅ አጋፋሪው የዮሴፍ ታሪክ ማቴ 1፥18-25 ባለው የቤተ ሰብ ታሪክ ውስጥ ተዘግቦልናል።
ቁጥር 18፣ “እናቱ ማሪያም ለዮሴፍ ታጭታ” ይላል። ይህ በምስክሮች ፊት የሚጸና ቃል ኪዳን ነው፤ ቢተዋት ብትተወው ‘ፈታት፣ ፈታችው’ ነው የሚባለው። ሳታገባው፣ አብረው ከመተኛቷ በፊት ቢሞት ‘ባሏ ሞተ ነው’ የሚባለው። “ጸንሳ ተገኘች” ሲል በቃ ነፍሰ ጡር መሆኗ ታወቀ ማለት ነው፤ ዮሴፍ አወቀ ማለት ነው። ሁለት ነገር ነው የሚያውቀው፦ እንዳልደረሰባት እና እንደ ጸነሰች (ይሄ እውቀት እርሷ ዘንድም አለ)። በመካከላቸው ግን ሦስተኛ አካል ይህንን ሥራ እየሠራ ነው፤ መንፈስ ቅዱስ። ምድር የማትችለውን የማሪያም ማሕጸን ችሏል። ዝም ብላ ጸንሳ ተገኘች ሳይሆን ቁ18. እና 20 “ከመንፈስ ቅዱስ”፤ ይህንን ሊያደርግ የሚችለው መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው።
ሚስት አድርጎ ያላገባት ማሪያም በእጮኝነቷ ማርገዟ ለዮሴፍ እኮ ውርደት ነው። በዚህ ጊዜ አማራጩ ለዮሴፍ ከባድ ነው፤ እንዲህ ዐይነቱን ከዳተኛነት ችላ ብሎ ማለፍ ከክፉ ጋር መተባበር ነው፤ ይህንን መግለጥም ሌላ ክፉ ነገር ነው። ከዚህ ሁሉ ‘ሚስቴ አድርጌ ከመውሰድ ብቆጠብስ…’። እርሷ ላይ የተለየ የመለኮት መገኘት አስደንግጦት አልፈራም፣ ከዳተኛ አድርጎ ቆጥሯትም አልተበሳጨም፤ ነባሩ ትርጉም “በስውር”፣ “በሰው ፊት ሊያጋልጣት ስላልፈለገ በስውር ሊተዋት ወሰነ” (አመት)።
በየትኛውም መልኩ የዮሴፍ ውሳኔ በእርሱ ላይ ማኅበራዊ ሸክም ያመጣል። ሳያጋልጣት፣ ሊተዋት ሲወስን ሕጉ የሚጠይቀውን ማሟላት ሊኖርበት ነው። ምንም እንኳ እጮኛው ብትሆንም፣ የእርሱ በመሆኗ ለሌላ እንዳትሆን ተደርጋለችና ግንኙነታቸው የጋብቻ ያህል ጠንካራ ነው። ስለዚህ በሕጉ መሠረት ነጻነቷን ሊሰጣት ይገባል። ይህ ደግሞ በደሉ ያለው እርሱ ዘንድ እንዲሆን ያደርግበታል፤ ቢሆንም ይህንን መረጠ እንጂ ራሱን የማንጻት ሩጫ አልሮጠም።
ቁጥር 19. “ጻድቅ ሰው ስለነበረ”፤ ፍትሕና ርቱእነትን የያዘ ቃል ነው። “ጻድቅ” ማለት “ትክክለኛና ፍትሓዊ” ማለት ነው። “ፍትርት” ይሉታል አንዳንዶች፤ ለእግዚአብሔር ታማኝነት ነው፤ ለሕጉ ፍትሐዊ ነው። ዮሴፍ በሕጉ መሠረት ራሱን ነጻ የሚያወጣበትን ነገር ሳይሆን፣ በሕጉ መሠረት ማርያምን ነጻ የሚያወጣበትን አሰበ። ለምን? ጻድቅ ሰው ነበረ! ስለ ጸነሰች መፍታት አለበት፤ እርሱ የሌለበት ጕዳይ ነውና። ይሁን እንጂ ሊያዋርዳት፣ ሊያጋልጣት አልፈለገም፤ በስውር ፍቺ ማረግ ፈለገ። በአደባባይ አያድርገው እንጂ አሁንም በሕጉ መሠረት ቢያንስ ሁለት ምስክሮች ያስፈልጕታል።
እግዚአብሔር ራሱ ጣልቃ ገባ! ዮሴፍ ጻድቅ ሰው ሰለሆነ የጽድቅ ሐሳብ ነው ያሰበው፤ ይሁን እንጂ የእግዚአብሔርን ዕቅድ በትዳሩ የዓለም ጉዳይ እየተፈጸመ እንደ ሆነ አላወቀም። “ ‘ኀጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ’ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው።” (1ጢሞ1፥15) የሚለው ይህን እኮ ነው። የመጣው በእነ ማርያምና ዮሴፍ ቤት ነው።
በጥንት ጽሑፎች የግለ ሰብን የሕይወት ታሪክ የሚጽፉ ሰዎች የሚጻፍላቸው ግለ ሰቦች ከእንዴት ያለ የላቀ ምግባር ካለው ቤተ ሰብ እንደተወለዱም ይጻፋል። ዐይናችን ተከፍቶ ስናይ ማቴዎስ የሚተርክልን ስለ ኢየሱስ የውልደት ታሪክ ብቻ ሳይሆን፣ አስቀድሞ የትውልድ ሐረጉንና ቤተ ሰቡን ከእንዴት ያሉ የጽድቅ ባለጸጋ ቤተ ሰቦች እንደተወለደም ጭምር ነው። ንጉሥ የተወለደው ከባለጸጋ ቤት ነው የሚለን።
እግዜር እንግዳ ሆኖ በእያንዳንዳችን ቤት ቢመጣ እንዴት ነው የምናስተናግደው? በአገራችንስ? ቤተ ክርስቲያናችንስ? (‘ቤቱ አይደለም ወይ ምን እንግድነት ያስፈልገዋል?’ እንዳትሉኝ) በየግል ሕይወታችንስ? እግዜር ወደ ቤታችን ሲመጣ እንደ አሜሪካ እንግድነት የእኛን ፕራይቬሲ ለመጠበቅ ስልክ ደውሎ አይመጣም። እንግድነት እንደሚመጣ እንጂ በምን ዐይነት ሁኔታና መቼ እንደሚመጣ አይነግረንም። አመጣጡ እኛን ላያስከብረን ይችል ይሆናል፤ እርሱን በማስተናገድ ማኅበራዊ ውርደት ሊያጋጥመን ይችል ይሆናል። እስኪመቸን የምንጠብቅ ከሆነ አናስተናግደውም። በሰው ተዋርዶ በእግዜር መክበር ዕድል መሆኑ የገባቸው ያስተናግዱታል።
ጸሎት፦ ስንት ጊዜ በየቤታችን መጥተህ በር እንደዘጋንብህ የምታወቀው አንተ ነህ። እኛ መች አጣነው ራሳችንን? የእኛ የእንግድነት ፕሮቶኮል ብዙ ነው። ጌታ ሆይ፤ እባክህ በየቤታችን ደግመህ ና! የአንተ ጉብኝት የማያስፈልገው ቤት የለንም። እኔ ቤት ብቻ ሳልሆን የሚጠሉኝ ሰዎች ቤት ሁሉ እባክህ ግባ! እንደ ከተማ ነዋሪ የእግርህን ጫማ፣ እንደ ዘረኞች የማን ትውልድ እንደሆንክ፣ እንደ ባለጠጋ ስንት ካፒታል እንዳለህ፣ እንደ ፖለቲከኞች ምን አጀንዳ እንዳለህ ሳንጠይቅህ፣ ብቻ ድምፅህን እንድንለይ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ግባ’ እንድንልህ የቤታችንን በር እንድንከፍትልህ፣ ለድምፅህ ንቃት እንዲኖረው፣ የልባችንን ጆሮ ቀድመህ ክፈትልን!!! አሜን
Share this article:
“The fear of God is a form of xenophobia—a fear of the stranger, or, in this case, the One who is utterly strange and altogether different.” By Michael Horton, (the article is picked from TGL)
አገራችንን በዚህ ጊዜ እየተፈታተናት ያለው ጉልሕ ችግር፣ በማንነት ላይ ያሉ ጥያቄዎቻችን ምላሽ ስላላገኙ ነው፤ ይህንንም በተገቢው መንገድ እስካልፈታን ድረስ ውጥረቶች መቀጠላቸው አይቀርም ይላል በሰላም ግንባትና በእርቅ ላይ ተመራማሪ የሆነው ሰሎሞን ጥላሁን።
“ስንቶች ለስምህ ቆመው ዘምረዋል
ስንቶች በስምህ ስብከትን ሰብከዋል
አሁን ብትመለስ ጌታ ወደ ቤትህ
ከሕይወት ጎድለዋል ጠፍተዋል ልጆችህ”
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society
Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.
Add comment