ፈረስ ባይዋጋም፣ ከጦር ሜዳ ያደርሳል። በውድድር ይሳተፋል። ይታረስበታል። ብቻ አንዳች ፋይዳ አያጣም። ይህ ይሆን ዘንዳ ግን መገራት አለበት። ለዚህም አለንጋ እና ልጓም ያስፈልጋሉ። ሰውም ልክ እንደ ፈረስ ነው!
አለንጋ ሲታሰብ ወላጆች ቀድመው ይታወሳሉ። ሥዕሉ በደንብ እንዲታየን አባትን በማሳያነት እንጠቀም። አባትና አለንጋ አይተጣጡም። አባት አለንጋ ታጥቆ ነው የሚኖረው። ፈረሱ ሲደነብር ሾጥ ያደርገዋል። ፈረሱ እንዳይደነብርም ሾጥ ያደርገዋል። ፈረሱ ፈሩን ሲስት ሾጥ! ፈረሱ ፈሩን እንዳይስት ሾጥ! ፈረሱ ሲፋንን ሾጥ! ፈረሱ እንዳይፋንን ሾጥ! … ሾጥ! ሾጥ! ሾጥ! ሰውም ልክ እንደ ፈረስ ነው!
ሰው ያለ አለንጋ አይኖርም። አባቱ ከሌለ፣ “የሴት ልጅ” እንዳይባል የምትሠጋው እናቱ አትራራለትም። አባትየው ኖሮ አለንጋ ለመሰንዘር ከሳሳም፣ “ያለ ምቀኛ እንዳይኖር ለተፈጠረ፣ ምቀኛ ቢጠፋ እናቱ ምቀኛው ትሆናለች” የተባለው ይፈጸማል። አሊያ ታላቅ ወንድም ወይም እኅት የባለ አለንጋነት ተፈጥሯዊ ሚናቸውን ይጫወታሉ። ይህም ሲጐድል አጎትና አክስት ወይም ዘመድ ክፍተቱን ይደፍናሉ። ከዚህ የሚያመልጥ ከዕድል እና ከመንግሥት አያመልጥም። ያው እንደምናውቀው ዕድል (ሕይወት) አርጩሜ ወይም አለንጋ አጥታ አታውቅም፤ ግርፊያም ተክናለች። መንግሥትማ አለንጋ ያመርታል። አለንጋ ሁሉ ግን አንድ ዐይነት አይደለም። ከፍቅርና ከምክር ጋር አለንጋቸውን በጥበብ የሚጠቀሙ አባቶች የመኖራቸው ያህል፣ ከአለንጋ ጋር አንድ አካል አንድ አምሳል የሆኑም ሞልተዋል። ጨካኝና ክፉ አባቶች ዛሬም ነገም ይኖራሉ። እነኚህ ፈረሱን ከመግራት ይልቅ ይሰብሩታል። ሰውም እንደ ፈረስ ነው፤ ይሰበራል።
ሆኖም ሰው እንደ ፈረስ ነውና ያለ አለንጋ አይኖርም። በአባቱ ያልተቀጣ ሲያድግ የሚያማርረው ለዚህ ነው። ጨካኝ አባት የገጠመው አባቱን ቢረግምም፣ ብዙው ሰው ግን ከ“አባቱ” ቤት ሲወጣ አባቱን ያከብራል። ብስለትን ሲዛመድ፣ አለንጋውን ከነሙሉ ክብሩና ጥቅሙ ጋር የማጤን አቅም ያዳብርና የአባቱን አለንጋ ያመሰግናል። የእርሱ ተራ ሲደርስም የአባቱን ጕድለት ላለመድገም እየጣረ፣ በቤቱ ድንጉላ እና ባዝራ ላይ አለንጋ ያነሣል። እናም ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው አለንጋ በዚህ መልኩ ነገም ይቀጥላል።
ሰው እንደ ፈረስ ነው። አለንጋ ብቻ ሳይሆን፣ ልጓምም አያጣውም። ልጓሙ ትዳር ነው። አሁንም ሐሳቡን ለመግለጥ ሚስትን በምሳሌነት እንጠቀም። ሚስት እንደየሁኔታው ልጓም ታጠብቃለች፤ ልጓም ታላላለች። መቼም ግን ከፈረሱ ላይ ልጓሙን አትፈታም። ከጉያዋ ከትታ አሞሌ እያላሰች ትሸብበዋለች። እንዲያውም ሚስት ራሷ ልጓም ናት። ሰው እንደ ፈረስ ነው!
አለንጋን ከልጓም ማነጻጸር ግን አልተቻለም። የአባቱን ቤት ሲለቅቅ፣ ስለ አባቱ አለንጋ ሁሉም ይተርካል። ከሚስቱ ጉያ ግን መቼ ይወጣና ምስጢሯን ያወጣል!? አንዱን ልጓም ሲበጥስ ሌላ ይጠልቅለታል እንጂ፣ ሰው ያለ ልጓም አይኖርም። እናም ስለ ልጓሙ እንዳይናገር ልጓሙ ያቅበዋል። ሳንሱር በነገሠበት አገር ስለ ሳንሱር ይጻፋል? ብቅል፣ ዋዛና ፍልስፍና በሆዱ የታመቀውን ጥቂት ይቀንሱለት እንደሆን እንጂ፣ ሰው የቤቱን ልጓም ገመና ወደ ውጭ አይተነፍስም። ሲያስብ እንኳ ተቀይዶ ነው የሚያስበው። “ስለ ሴቶች እውነቱን የምናገረው ልክ አንድ እግሬ ከመቃብር ሲገባ ነው። ከዚያ በፍጥነት ሳጥኑን በላዬ እጠረቅመዋለሁ” ያለው ደራሲ ለሁላችንም ተናግሯል። ስለ ሁላችን ተናግሯል። ሰው እንደ ፈረስ ነው። አለንጋና ልጓም ይገሩታል።
በአግባቡ የተገራ ፈረስ ለባለቤቱ ክብር ያመጣል። ወደ ጦር ሜዳ ቢያደርስም፣ ዋንጫ ቢያሸንፍም፣ ታርሶበት ቢያመርትም፣ ግልቢያ ቢያሳምርም ትርፉና ክብሩ ለባለቤቱ ነው! የጥርኝ ዳንግላሳ ለፊታውራሪ መሸሻ ኩራት ከመጨመር በቀር ለራሱ ምን አስገኘለት? ምናልባት ጥቂት ገብስ ለራቱ ቢደርሰው ነው። በቃ ሕይወቱ ከዚህ አይዘልም! ስሙ እንኳ የጌታው መታወሻ ነው። በአባ ታጠቅ አጤ ቴዎድሮስ እንጂ ፈረስ ትዝ የሚለው አለ? “አባ መላ” ሲባል ሀብተ ጊዮርጊስ፣ “አባ ነጋ” ቢባል አሉላ፣ “አባ ዳኘው” ሲባል ምኒልክ እንጂ ፈረሶቻቸውን ማን ያስታውሳል? ጋላቢው ይገንናል እንጂ ፈረሱ አይዘከርም። ከጥቂት ልዩነት በቀር የፈረስ መልኩም አንድ ነው። ስለዚህ ከጌታው በቀር ፈረሱን የሚያውቀው የለም። ሰውም እንደ ፈረስ ነው!
በውኑ ነጻነት የታል? ከምናብ ዓለም በስተቀር ማን ነጻነትን አግኝቷል? ከሌለስ ለምን ያምረናል? ያልነበረና የሌለን ሁሉ እንዴት ይናፍቀዋል?
የሆነስ ሆነና ፈረሱ የማን ነው? ጋላቢውስ ማን መሆን ነው ያለበት? የፈረሱን መገራት የፈለገው ማነው? አለንጋን እና ልጓምን ማን ነው የመደበለት? ትዳር በማን ተመሠረተ? አባትነትስ የሚሰየመው በማን ነው? በእግዚአብሔር አይደለምን!? ሰው እንደ ፈረስ ከሆነ፣ የፈረሱ ጌታ ወይም ባለቤት እግዚአብሔር ነው። የፈረሱ ስም፣ የፈረሱ ዝና፣ የፈረሱ ክብር የተገባው እርሱ ብቻ ነው! ታዲያ አባት ባለ አለንጋው እና ሚስት ልጓሚቱ እርሱን ከማገልገል በቀር ምን ድርሻ አላቸው? ሚስት አላግባብ ልጓም ከሆነች፣ ወይም ፈረሱን ልጋልበው ካለች ራሷን ታጌተያለች። አባትም አላግባብ የሚጋረፈው ወይም ፈረሱን ልጋልብ የሚለው እግዚአብሔርነት ሲያምረው ነው! ባልደራስነት ትርጕሙ ባለቤትነት አይደለም! ለባለቤቱ ያልዋለ ፈረስ እንግዲህ ዋጋው ምንድን ነው?
ሰው እንደ ፈረስ ነው። አለንጋም ልጓምም ቢያጣ እፎይታን አይዛመድም። ከአለንጋ ሲያመልጥ፣ “አሳዳጊ በደለው” ይባላል። “አባቴ ቢቀጣኝ ኖሮ!” እያለ ራሱም ይቆጫል። ልጓም ካላጠለቀም ልቅነት አይቀርለትም። ደስታንም አያገኛትም። እናማ፣ “ትዳር አጣሁ” እያለ ሲተክዝ ስንቱን አይተናል!? ፍራሹን መሬት ጎትቶ ስንቱስ ልቅሶ ተቀምጧል!?
ሰው እንደ ፈረስ ነው። ያለ አለንጋና ያለ ልጓም አይኖርም። ልከኛው ባለአለንጋ ግን እግዚአብሔር ነው። ሲሻውም ልጓም ይሆናል። ከሚስት ልጓም ለከለላቸው ራሱ ልጓም ይሆናቸዋል። አሊያማ፣ “ጳውሎስ ልጓም የለውም፤ ተገርቶም ለጌታው ክብር አላመጣም” ሊባል ነው!? ይልቁኑ እርሱን መሳይ ቡሩካን እንዳስተማሩን ከሆነ፣ እግዚአብሔር አንዳንዶችን ልጓምም ራሱ፣ ጋላቢም ራሱ ሆኖ ይገራቸዋል።
ሰው እንደ ፈረስ ነው። ያለ አለንጋና ያለ ልጓም አይኖርም። ልከኛው ባለአለንጋ ግን እግዚአብሔር ነው። ሲሻውም ልጓም ይሆናል።
ሰው እንደ ፈረስ ነው። ግና አለንጋና ልጓም ለምን ሁልጊዜ አይመቹንም? ቍርቋሬአቸውንስ ለምን አንላመድም? ልጅ ሳለን ከ“ሁሉን ፈቃጅ” አባቶች በተወለዱ ብጤዎቻችን፣ ትዳር ስንይዝ ደግሞ በትዳር ባልታሰሩ ወዳጆቻችን ለምን እንቀናለን? ነጻነት የሚባል ነገር ከሌለ፣ ውስጣችንን ነጻነት ለምን ይርበዋል? ዙሪያ ገባውን ስናየው የሁሉም ናፍቆት ይኸው ነው። ሰው በነጻነት ስም ይገድላል። ለነጻነቱ ይሞታል። ስለ ነጻነት ያልማል። ነጻነትንም ያዜማል። ብዕሩ “ነጻነት፣ ነጻነት” ይላል፤ ወይ በስም አስታክኮ ልጁ ላይ ይህን ይጭናል። በውኑ ነጻነት የታል? ከምናብ ዓለም በስተቀር ማን ነጻነትን አግኝቷል? ከሌለስ ለምን ያምረናል? ያልነበረና የሌለን ሁሉ እንዴት ይናፍቀዋል?
ነጻነት አንድ ወቅት ነበረ። ግን እዚህ አይደለም አገሩ። እዚያ ነው፤ ከዚህ ዓለም ማዶ፣ የነጻነት ሰፈሩ። ምን ብንጥር ብንፍጨረጨር ቅምሻ እንጂ ምሳ አይሆነንም። ነገሩ የጠፋው ጥንት ነው። ዳፋው ግን ዛሬም እንደ መርግ ተጭኖናል። ከአጥሩ ወዲያ ወዳለው ብርሃንና ነጻነት እንዴት መሻገር ይቻላል? ነገሩ እንደዚህ ነው …
የሰው ሕላዌ የተመሠረተው፣ ሕይወቱ የተገነባው በነጻነት ላይ ነበር። በነጻነት ነጻ ሆነን እንድንኖር ነበር የተበጀነው። የእግዚአብሔር ወርጅናሌ ዐላማ፣ ሰው ያለ አለንጋ እና ያለ ልጓም ይኖር ዘንድ ነበር። በርግጥ ትዳር ከውድቀት በፊትም ነበረ፤ ልጓም ግን አልነበረውም። አዳምም ሕፃን ስላልነበረ፣ አለንጋ ሳይቀምስ ጎልምሷል። ሚስት ልጓም የማትሆንበት ትዳር፣ አባት አለንጋ የማይሆንበት ሕይወት ነበር የእግዜሩ ቀዳሚ ሐሳብ። ሕይወት ነጻነት፣ ነጻነት ሕይወት ነበረ ያኔ! ነበረ ነው እንግዲህ …
… እንዳለመታደል ሆነና ይህ ሕይወት አልበረከተም። የነጻነት ሕይወትነት፣ የሕይወት ነጻነትነት አልታየው ብሎ ሰው በነጻነት ላይ ዐመፀ። በሕይወት ላይ ሸመቀ። የነፍሱ ወዳጅ በሆነው በአንድዬ ላይ መከረ። እናም ሰዎች ከነጻነት ነጻ ወጡ። ባርነትን አመጡ። እግዚአብሔር ግን ጥሎ አይጥልምና አባትን አለንጋ አስታጥቆ፣ ሚስትን ልጓም አድርጎ ባልደራስነት ሾማቸው። ከዚያማ … ሰው ጠፍቶ እንዳይቀር በእጅ አዙር የመግራት ሥራን “ሀ” ብሎ እግዜር ጀመረ። ሰው እንደ ፈረስ ነው!
እናም … ሰው ነጻነትን ካላገኘ ግን እፎይታ እንደ ሌለው ያውቃል። ግና ቁጭ ብሎ የሰቀለውን ማውረጃ መላ ጨርሷል። ዓለም የአለንጋን ቅጣት በሕግ ከልክሎ፣ ፍችን በሕግ አጽድቆ ቢሞክረውም፣ እስካሁን ልቅነት እንጂ ነጻነት አልተገኘችም። ምክንያቱም ነጻነት አለመገራት አይደለም! የነጻነት ሕይወቷ፣ የሕይወት ነጻነቷ እግዚአብሔር ነውና ከእርሱ በቀር ነጻነት የለም። ለእግዚአብሔር ያልኖረ ነጻነትን አይኖርም። ይህም ሆኖ እንኳ፣ የነጻነትን ዋስትና ወይም ቅምሻ ካልሆነ በቀር፣ ሰው ነጻነትን በምድር አያጣጥምም። ስለዚህ ነጻነትን እየናፈቀ፣ በአለንጋና በልጓም ሕይወትን ይመነዝራል፤ ምክንያቱም ሰው እንደ ፈረስ ነው!
ዓለም የአለንጋን ቅጣት በሕግ ከልክሎ፣ ፍችን በሕግ አጽድቆ ቢሞክረውም፣ እስካሁን ልቅነት እንጂ ነጻነት አልተገኘችም። ምክንያቱም ነጻነት አለመገራት አይደለም!
… ይህ ግን በዚህ ምድር ብቻ ነው! ትንሣኤ ሁሉን ይለዋውጣል። ያኔ ሰዎች አያገቡም፤ አይጋቡም። የሁሉም ልጓም ይወልቃል! በትዳር ውስጥ “አሞሌ መላስ” ለሚያፈቅሩ ይህ መርዶ ቢመስልም፣ አዎን በዚያ ትዳር አይሆንም። አሞሌው የሰማያዊው ርካታ ናሙና ነውና አገልግሎቱ እዚህ ያከትማል። ፊት ለፊት ጌታን ስናየው ርካታን እንጨብጣለን! ያኔ ልጓማችን መውለቁ ሳያንስ፣ አለንጋም አይኖርብንም! ከውድቀት በፊት እንደ ታቀደው ሰው በነጻነት ይኖራል። የእግዚአብሔር ዐብሮ ኋኚነት የየቀን ሕይወት ይሆናል። ትንሣኤ ነጻ ያወጣናል። ግና እስከዚያው … ሰው እንደ ፈረስ ነው፤ አለንጋ ልጓሙን እንደ ታቀፈ ይኖራል!
የሆነስ ሆነና … በትንሣኤው አገር በነጻነት የሚኖር፣ ነጻነትን የሚመጥን ሰብእና የምናበጀው እንዴት ነው? የዛሬዎቹ አለንጋና ልጓም እዚያ የሚደርስ ውጤት ይኖራቸዋል? ወይስ ፋይዳቸው እዚህ እና አሁን ብቻ ነው? ይህን በርግጠኝነት አላውቅም። አንድ ነገር ግን ዐውቃለሁ። ይኸውም፣ ሰው እንደ ፈረስ ነው!
2 comments
Thank you
betam tru new ewedachewalehu