እውነተኛ ገጠመኝ ነው። ከኹለት ዐሠርት ዓመታት በፊት ታቦተ ሥላሴ ደባል[1] በኾነበት በአንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሐምሌ ሥላሴ ክብረ በዓል የተገኙት ምእመናን በቍጥር ጥቂት ነበሩ። ይህን የታዘቡትና በሥልጣን በመናገር የሚታወቁት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በኹኔታው ዐዝነው እንዲህ ብለው ነበር፤ “ምእመናን ዛሬ የሥላሴ በዓል እኮ ነው? ምነው ታዲያ ምእመናኑ ጥቂት ኾኑ? ይህን ጊዜ የገብርኤል በዓል ቢኾን እንኳን ለዓመቱ ለወሩም ብዙ ሕዝብ ይገኝ ነበር፤ ምእመናን ከገብርኤል እኮ ሥላሴ ይበልጣሉ? ስለዚህ ማንን ማምለክ እንዳለብን ማስተዋል ይገባናል።” በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ሐምሌ ፯ ቀን በየዓመቱ የሥላሴ ዓመታዊ በዓል ይከበራል። በዓሉ የሚከበርበት ምክንያት ሥላሴ እንግዶች ኾነው ወደ አብርሃም ቤት መምጣታቸውንና የይሥሐቅን መወለድ ማብሣራቸውን ለመዘከር እንደ ኾነ የቤተ ክርስቲያኒቱ መጻሕፍት ይመሰክራሉ። መጽሐፈ ስንክሳር በሐምሌ ፯ ንባቡ እንዲህ ይላል፤ “ወበዛቲ ዕለት ቦኡ ሥሉስ ቅዱስ ውስተ ቤተ አብርሃም፥ ወተሴሰዩ ዘአቅረበ ሎሙ በከመ ጽሑፍ ውስተ ኦሪት ወአብሠርዎ ልደቶ ለይሥሐቅ። – በዚች ቀን ልዩ ሦስቱ አካላት (ሥላሴ) በኦሪት መጽሐፍ እንደ ተጻፈ ወደ አብርሃም ቤት ገቡ። ያቀረበላቸውንም ተመገቡ። የይሥሐቅንም ልደት አበሠሩት።” ይህም የበዓሉ ታሪክ የተመሠረተው በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 18 ላይ መኾኑን ያሳያል። ለክፍሉ የተሰጠው ትርጓሜም ‘ሦስቱ ሰዎች ሥላሴ ናቸው’ የሚል ነው።
መልክአ ሥላሴ የተባለውና ስለ ሥላሴ የተደረሰው ባለ ዐምስት ቤት የግእዝ ግጥምም የሚከተለውን አስፍሯል፥
“ሰላም ለኅሊናክሙ በከዊነ ኄር ዘተሐምየ፤
እም ከላውዴዎን አብርሃም ዘምድረ ካራን ኀረየ
ሥላሴክሙ ሥላሴ ሶበ ይኔጽር ዕሩየ
ሠለስተ እደወ ሊሉያነ ውስተ ርእሰ ሐይመት ርእየ
ወለአሐዱ ነገሮ ረሰየ።”
ትርጓሜ፥ ደግ በመኾን ለታወቀው ኅሊናችኹ ሰላምታ አቀርባለኹ፤
ከከላውዴዎን ካራንን የመረጠው አብርሃም
የሦስትነታችኹን ትክክለኛ ሦስትነት በተረዳ ጊዜ፥
ሦስት ልይዩ (የተለያዩ) ሰዎችን ከድንኳኑ በላይ ተመለከተ፤
ከሦስቱ አንደኛውም ነገሩን አከናወነለት (ይሥሐቅ እንደሚወለድ ነገረው)።
በዚህ ድርሰት ውስጥ ለአብርሃም የተገለጡት ሦስቱ ሰዎች እኩል፥ የተለያዩም መኾናቸው ተመልክቷል። ‘እኩል ናቸው’ ተብለው መገለጣቸው ሰዎቹ ሥላሴ ናቸው ለሚለው አመለካከት ማስረጃ እንደሚኾን ሲታሰብ፥ ወዲያውም ሰዎቹ የተለያዩ መኾናቸው መጠቀሱ ደግሞ ሦስትነታቸውን ሊያሳይ ይችላል። ይህም በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 18 ለአብርሃም የተገለጡት ሥላሴ ናቸው የሚለውን ፍቺ የተከተለ ኾኗል።
ከላይ ለማየት እንደ ሞከርነው፥ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ስለ ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 18 የሚነገረውና የሚታመነው ይህ ብቻ ነው ማለት ግን አይቻልም። ስለ ሦስቱ የአብርሃም እንግዶች የተለየ አመለካከትም አለ። ርግጥ ጐላ ብሎ የሚታየው አመለካከት ለአብርሃም የተገለጡት ሥላሴ ናቸው የሚለው መኾኑ ባይካድም፥ ከዚህ በተቃራኒ የምዕራፉን ሐሳብ የሚያብራራ ሌላ አመለካከትም በቤተ ክርስቲያኒቱ መጻሕፍት ውስጥ እንዳለ ማወቅ ተገቢ ነው። ቀጥሎ በቅደም ተከተል አመለካከቶቹን ለመመርመር እንሞክር።
ሦስቱ ሰዎች ሥላሴ ናቸው
በቅድሚያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሥላሴ (በአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ) ከሚያምኑ አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ መኾኗን መግለጥ ያስፈልጋል። ማመን ብቻም ሳይኾን ትምህርተ ሥላሴን በቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነትና በአበው ሐተታ ላይ ተመሥርታ አምልታና አስፍታ በማስተማርም ትታወቃለች። ትምህርተ ሥላሴን ለማስተማር በብዙዎች ዘንድ ከሚጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መካከልም አንዱ ዘፍጥረት 18 ነው። እንደ ብዙዎቹ አመለካከት ለአብርሃም የተገለጡት ሥላሴ ናቸው። ለዚህም ማስረጃ ተደርጎ የሚቀርበው በምዕራፉ ውስጥ ለአብርሃም እግዚአብሔር እንደ ተገለጠለት ከተነገረ በኋላ፥ ዐይኑን አንሥቶ ሦስት ሰዎችን እንዳየ፥ ነገር ግን አንድን ሰው እንደሚያናግር ኹሉ፥ “አቤቱ፥ በፊትኽስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ኾነ ባሪያኽን አትለፈኝ ብዬ እለምናለኹ” ማለቱ፥ የእግዚአብሔርን አንድነት ያሳያል ሲሉ፥ እንደ ገናም መልሶ፥ “ጥቂት ውሃ ይምጣላችኹ፥ እግራችኹን ታጠቡ፥ ከዚህችም ዛፍ በታች ዕረፉ፤ ቍራሽ እንጀራም ላምጣላችኹ፥ ልባችኹንም ደግፉ፥ ከዚያም በኋላ ትኼዳላችኹ፤ ስለዚህ ወደ ባሪያችኹ መጥታችኋልና።” ማለቱ ደግሞ ሦስትነቱን ሲያጠይቅ ነው ይላሉ።
ከቍጥር 9 – 10 “እነርሱም፦ ሚስትኽ ሣራ ወዴት ናት? አሉት። እርሱም፦ በድንኳኑ ውስጥ ናት አላቸው። እርሱም፦ የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለኹ፤ ሚስትኽ ሣራም ልጅን ታገኛለች አለ” በሚለው ጥያቄና መልስ ውስጥ፥ በመጀመሪያ ጠያቂዎቹ ሦስቱ ሰዎች “እነርሱ” በተባለው ተውላጠ ስም መጠቀሳቸው ሦስትነትን ያጠይቃል ሲሉ፥ አብርሃም ምላሽ ከሰጠ በኋላ ሣራ ልጅ የምታገኝ መኾኑን የተናገረው ግን “እርሱ” መባሉ አንድነትን ያሳያል ይላሉ። በእነዚህ ማብራሪያዎች ላይ በመመሥረት ዘፍጥረት 18 የሚናገረው፥ ሥላሴ የአብርሃም እንግዶች መኾናቸውን ነው በማለት ይደመድማሉ። በዚህ አተረጓጐም ላይ የተመሠረተ ኾኖ “የአብርሃሙ ሥላሴ” የሚል አጠራር በኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ዘንድም የተለመደ ኾኗል።
እግዚአብሔር እና ኹለት መላእክት ናቸው
ይህ ኹለተኛው አመለካከት ነው። በዘፍጥረት ምዕራፍ 18 ላይ የተገለጡት እግዚአብሔርና ኹለት መላእክት ናቸው የሚለው ይህ አመለካከት፥ የመጀመሪያውን አመለካከት በሚያራምዱት ዘንድ ብዙም የማይታመንበትና በአንዳንዶቹ ዘንድ ምናልባትም ትምህርተ ሥላሴን እንደ ማስተሐቀር (እንደ ማቃለል) የሚቈጠር አመለካከት ተደርጎ ሳይወሰድ አይቀርም። ይኹን እንጂ ይህ አመለካከት ከውጪ ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ የገባ ሳይኾን፥ በቤተ ክርስቲያኒቱ አንዳንድ መጻሕፍት ውስጥ ተገልጦ የሚገኝ ነው። የሚከተሉትን ማስረጃዎች ማቅረብ ይቻላል።
በመጽሐፈ ቅዳሴ ላይ፥ “ኦ ዘአፍቀርከ ትሕትናሁ ለእጓለ እመ ሕያው እም ዕበዮሙ ለመላእክት። ኦ ዘአፍቀርከ ንዴተ ዚኣሁ ለአዳም እመዛግብቲሆሙ ለነገደ አብርሃም። – ከመላእክት ታላቅነት ይልቅ የሰውን ልጅ ትሕትና የወደድኽ፥ ከነገደ አብርሃም መዝገቦች ይልቅ የአዳምን ንዴት (ድኽነት) የወደድኽ …” የሚል ንባብ አለ። ለንባቡ በተሰጠው የሊቃውንት አንድምታዊ ትርጓሜ ውስጥ፥ አብርሃም በእንግድነት የተቀበለው ሥላሴን ሳይኾን መላእክትን መኾኑ ተጠቍሟል፤ እንዲህ ተብሎ፥ “ከመላእክት ባሕርይ ይልቅ የአዳምን ሥጋ ለመወሐድ የመረጽ[ጥ]ኽ፥ አብርሃም እንግድነት ከተቀበላቸው ከመላእክት ከባሕርያቸው ይልቅ የአዳምን ባሕርይ የወደድኽ” (መጽሐፈ ቅዳሴ ንባቡና ትርጓሜው 1988፣ ገጽ 376)። ይህ ሐተታ አብርሃም በእንግድነት መላእክትን እንጂ እግዚአብሔርን በሥላሴነት (በሦስትነት) እንዳልተቀበለ ያስረዳል።
በተመሳሳይም ከአዋልድ መጻሕፍት መካከል አንዱ በኾነው በድርሳነ ሚካኤል ላይ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፤ “ዳግመኛም መላእክት ወደ አብርሃም ዘንድ መጥተው ይሥሐቅ እንዲወለድ ነገሩት።” (ድርሳነ ሚካኤል ዘሚያዝያ ቍጥር 11)። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው፥ ለአብርሃም ከእግዚአብሔር ጋር ኹለት መላእክት መገለጣቸው እውነት ቢኾንም፥ የይሥሐቅን መወለድ የተናገረው ግን እግዚአብሔር ነው እንጂ መላእክቱ አይደሉም። ቃሉም፥ “እርሱም፦ የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ፤ ሚስትኽ ሣራም ልጅን ታገኛለች አለ” ነው የሚለው (ቍጥር 10)። “እርሱ” የተባለው እግዚአብሔር እንደ ኾነ ይታመናል።
በገድለ አበው ወአኀው ላይ እንደ ተመዘገበውም፥ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ከደቂቀ እስጢፋኖስ ደቀ መዛሙርት መካከል መነኰሳይያትን (ሴቶች መነኰሳትን) በምን እንደሚያምኑ ወይም ስለ ሃይማኖታቸው በጠየቃቸው ጊዜ፥ “ሃይማኖታችን አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ነው አሉት። ንጉሡም ሐዲስና ብሉይ እየጠቀሳችኹ አስረዱኝ አላቸው።” እነርሱም እየጠቀሱ አስረዱት። በዚህ ውስጥ ዘፍጥረት 18ን አልጠቀሱለትም መሰል፥ “በአብርሃም ቤት የተስተናገዱት ሰዎች እነማናቸው ትላላችኹ?” የሚል ጥያቄ ሰነዘረላቸው። ቅዱሳኑም ሲመልሱ፥ “መጽሐፉ ሦስት ሰዎች ይላል አሉት” (ደቂቀ እስጢፋኖስ፥ በሕግ አምላክ ከጌታቸው ኀይሌ 1996፣ ገጽ 128)። ንጉሡ፥ ሥላሴ እንዲሉት ጠብቆ ይኾናል፤ እነርሱ ግን ሥላሴን ባይክዱም፥ በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ትምህርተ ሥላሴን ማስደገፍ አልፈለጉ ይኾናል፡፡ ይህም ምዕራፉን በተለየ መንገድ እንደሚተረጕሙት ሳያመለክት አይቀርም።
መጽሐፉ ምን ይላል?
ለአብርሃም ስለ ተገለጡለት እንግዶች መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይነግረናል? ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 18ን ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻውና የቀጣዩን ምዕራፍ የመጀመሪያ ቍጥር (19፥1) ስናነብ፥ ለአብርሃም የተገለጡት እግዚአብሔርና ኹለት መላእክት መኾናቸውን እንረዳለን። ከላይ እንደ ተመለከትነው፥ ሦስት ሰዎች መገለጣቸውንና አብርሃም አንድ ጊዜ ከአንድ በላይ ሰዎችን እንደሚያናግር ብዙዎች እያደረገ ሲያናግራቸው፥ የብዙ ቍጥር ተውላጠ ስምንም ሲጠቀም እንመለከታለን። እንደ ገናም አንድን ሰው እንደሚያናግር በነጠላ ቍጥር ሲጠቀም እናያለን። ኾኖም ሰዎቹ ሦስት መኾናቸው ብቻውን ሥላሴ ናቸው (አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ናቸው) ወደሚል ድምዳሜ አያደርሰንም።
በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ለአብርሃም ተገለጠለት የተባለው እግዚአብሔር መኾኑና አብርሃምን በዋናነት ሲያናግረው የነበረውም እርሱ መኾኑ በሚከተሉት ቍጥሮች ውስጥ ተጠቅሷል (ቍ. 1፣13፣17፣20፣26)። ይልቁንም “ሰዎቹም ከዚያ ፊታቸውን አቀኑ፥ ወደ ሰዶምም ኼዱ፤ አብርሃም ግን በእግዚአብሔር ፊት ገና ቆሞ ነበር” (ቍ. 22) የሚለው ለአብርሃም የተገለጠው እግዚአብሔርና ኹለት ሰዎች መኾናቸውን ያስረዳል። ምዕራፍ 18 ላይ “ሰዎች” እየተባሉ የተገለጡት ምዕራፍ ፲፱ ቍጥር ፩ ላይ “ኹለቱም መላእክት” ተብሎ ቍጥራቸው ኹለት፥ ማንነታቸው ደግሞ መላእክት መኾኑ ተጠቅሷል። ይህም አብርሃም በድንኳኑ የተቀበላቸው እንግዶች እግዚአብሔርና ኹለት መላእክት መኾናቸውን በግልጥ ያመለክታል።
በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ለአብርሃም እግዚአብሔር በሦስትነቱ ተገለጠለት የሚል ንባብ ስለማናገኝ ነው እንጂ፥ በዚህ መንገድ ሊገለጥለት ይችላል ብለን ማሰብ አንከለከልም። ብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር፥ አንድነቱንና ሦስትነቱን በምንገነዘብበት ስም ማለትም ብዙ ቍጥርን በሚያመለክት ስሙ በኤሎሂም ተገልጧል። ከዚህ በቀር በሐዲስ ኪዳን በግልጥ በተገለጠበት ኹኔታ ተገልጦ አናይም። ከጥንት የቤተ ክርስቲያን አባቶች አንዱ የኾነውና የቂሣርያ ኤጲስ ቆጶስ የነበረው ጎርጎርዮስ እንዲህ ብሏል፤ “ወባሕቱ ኢየአምሮሙ መኑሂ እም ሰብእ እንበለ ዳዕሙ እም ድኅረ ተሠገወ ወልደ እግዚአብሔር ወልድ ዋሕድ ወከሠተ ዘንተ እንዘ ይብል አባ ናሁ ከሠትኩ ስመከ ለሰብእ ሊተኒ ሰብሐኒ በስብሐቲከ። – ነገር ግን [ሥሉስ ቅዱስን/አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስን] ከሰው ወገን ማንም አያውቃቸውም ነበር፤ የእግዚአብሔር ልጅ ወልድ ዋሕድ ሰው ኾኖ፥ አባቴ! እነሆ ስምኽን ለሰው ኹሉ ገለጥኹ፤ እኔንም የባሕርይ ልጅኽ እንደ ኾንኹ ያውቁ ዘንድ ዓለም ሳይፈጠር በነበረ ጌትነትኽ ግለጠኝ ብሎ ካስረዳ በኋላ ነው እንጂ” ሲል አስተምሯል (ሃይማኖተ አበው 1982፣ ገጽ 21)። ከእዚህ ምስክርነት አንጻርም በዘፍጥረት 18 ውስጥ እግዚአብሔር በሦስትነቱ ተገለጠ ማለት ብዙ እንደማያስኬድ ግንዛቤ መውሰድ ይቻላል።
ብሉይ ኪዳን ትንቢት፥ ሐዲስ ኪዳን ደግሞ የትንቢቱ ፍጻሜ ነው። በብሉይ ኪዳን የተነገሩና የተከናወኑ አንዳንድ ትንቢቶችና ድርጊቶች በሐዲስ ኪዳን የተፈጸሙበትን መንገድና የተሰጣቸውን ትርጓሜ ከሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ማገናዘብ ይኖርብናል። የዕብራውያኑ ጸሓፊ፥ “እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ በዚህ አንዳንዶች ሳያውቁ መላእክትን እንግድነት ተቀብለዋልና” ሲል የጻፈው የሚያመለክተው አብርሃምና ሎጥ የተቀበሏቸውን እንግዶች እንደ ኾነ በብዙዎች ዘንድ ይታመናል። እነርሱ መላእክትን እንግድነት እንደ ተቀበሉ ተጽፏልና። የ1953ቱን ዕትም ጨምሮ ብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ዕትሞች በኅዳጋቸው ለዕብ. 1፥1-2 የሚያጣቅሱት ዋቢ ስለ አብርሃምና ሎጥ እንግዳ መቀበል የሚናገረውን ክፍል ነው። ይህም ክፍሉ አብርሃም በእንግድነት የተቀበለው እግዚአብሔርንና ኹለት መላእክትን እንጂ እግዚአብሔርን በሥላሴነት እንዳልተቀበለ ያስረዳል።
መደምደሚያ
መጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ክፍሎች ስለ እግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት ያስተምራልና በሥላሴ (በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ) ማመን የክርስትና ዋና መሠረት ነው። ይህን የሚያምኑና ስለ ትምህርተ ሥላሴ በሚጠቅሷቸው ጥቅሶች የማይስማሙ ቢኖሩ እንኳ፥ ልዩነቱ የአተረጓጐም እንጂ መሠረታዊ አይደለም። ስለዚህ አመለካከቶችን በአክብሮት ማስተናገድ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ጠቃሚ ነው። በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባሉ ወገኖች መካከል ብቻ ሳይኾን፥ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናትም በዋናው መሠረት በሥላሴ በማመናቸው ተመሳሳይ ከኾኑ፥ እንደ ንኡሳን በሚታዩ በሌሎች ጕዳዮች ላይ የተፈጠሩ ልዩነቶች ቢኖሩም እንኳ፥ በዋናው መሠረት በሥላሴ በማመናቸው ተመሳሳይ እስከ ኾኑ ድረስ አንድ ከመኾን አያግዷቸውም።
[1]ለታቦት “ደባል” የሚባለው፥ ለምሳሌ በሚካኤል ስም በተሠየመ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሌላ ስም የሚጠራ ሌላ ታቦት በይፋ ከገባና በዚያው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በዓሉ የሚከበርለት ከኾነ፥ ያ ታቦት ደባል ነው ይባላል።
1 comment
በጣም ተመችቶኛል