
መሪነት እና ጴንጤቆስጤያዊው እንቅስቃሴ
“ከታሪክ የምንማረው ነገር ከታሪክ አለመማራችን ነው።” ይህን አባባል የተናገሩት ከዓለማችን ቢሊየነሮች መካከል ከፊተኞቹ ተርታ የሚገኙቱ አሜሪካዊው ዋረን ባፌት ናቸው።
[the_ad_group id=”107″]
ከእናንተም የሚያርስ ወይም ከብትን የሚጠብቅ ባሪያ ያለው፥ ከእርሻ ሲመለስ ወዲያው ቅረብና በማዕድ ተቀመጥ የሚለው ማን ነው? የምበላውን እራቴን አሰናዳልኝ፥ እስክበላና እስክጠጣ ድረስ ታጥቀህ አገልግለኝ፥ በኋላም አንተ ብላና ጠጣ የሚለው አይደለምን? እንዲሁ እናንተ ደግሞ የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ፥ የማንጠቅም ባሪያዎች ነን፥ ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል በሉ። (ሉቃ. 17፥7-10)
የምንኖረው እጅግ በዘመነ ትውልድ ውስጥ ነው። በዘመኑ ውስጥ በዓይናችን የምናያቸውና በልቡናችን የምናስተውላቸው በርካታ ነገሮች አሉ። በተለይም በብዙ አቅጣጫ ውሸተኞች ሆነው ሳሉ ነገር ግን እውነተኛውን መስለው የሚገለጡ ነገሮችን እናስተውላለን። እነዚህ እውነተኛውን የሚመስሉ ነገሮችን በልዩ ልዩ የሥራ ዘርፎች ውስጥ ልናያቸው የምንችላቸው ናቸው። ነጋዴዎች “ኦሪጂናል” ናቸው ብለው የሚሸጧቸው ዕቃዎች ከቀናት በኋላ እንዳልሆኑ በተግባር ይታያሉ። ምክንያቱም ዕቃዎቹ ኦሪጂናሉን የሚመስሉ እንጂ እውነኞች ስላልሆኑ ነው። ይህንን የተመለከቱ ዕቃ ገዢዎች አንድ ነገር ለመግዛት ሲያስቡ ‘ምን ይሻላል?’ በማለት ይጨነቃሉ። ቁጥራቸው አያሌ የሆኑ ግለ ሰቦች ገንዘባቸውን እውነተኛ በሚመስል፣ ነገር ግን ባልሆነ ዕቃ ላይ ጨርሰው በኀዘን ቤታቸው ተቀምጠዋል። አንድ ነገር ለመግዛት ሲፈልጉ እንደቀድሞው እንዳይታለሉም በማሰብ ስለ ዕቃው በቂ እውቀት አለው ብለው የሚያስቡትን ሰው ይዘው ወደ ገበያ ቦታ ለመሄድ ይገደዳሉ።
በተመሳሳይም፣ በመንፈሳዊው ዓለም ላይ ያለውን አገልግሎት ስንመለከት እውነተኛ ያልሆነ፣ ነገር ግን እውነተኛውን የሚመስል አገልግሎት እናያለን። በዛሬ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ያለውን አገልግሎት ስንመለከት በእውነተኛ ልብና ከፈጣሪ በመጣላቸው መለኮታዊ ጥሪ ተነሣስተው የሚደክሙ እውነተኛ አገልጋዮች እንዳሉ ሁሉ፣ የግል ጥቅማቸውን ማእከል ያደረጉ በርካታ አስመሳይ “አገልጋዮችም” ደፋ ቀና ሲሉ ይታያሉ። ከዚህም የተነሣ በአሁኑ ጊዜ ጌታን ያመኑ ቅዱሳን በአስመሳይ “አገልጋዮች” ሲጉላሉና ንብረታቸውን ሲዘረፉ ማየታችን ‘እውነተኛ አገልጋይ ማነው?’ ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል።
የተባረከው ቅዱስ ቃሉ እውነተኛ አገልጋዮች ምን ዐይነት እንደሆኑና እንዴት ባለ ሕይወት መኖር እንዳለባቸው ይነግረናል። በጥንቷ የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን የነበሩና በብዙ ዋጋ መክፈል ወንጌልን ወደ እኛ ያስተላለፉልንን የእውነተኞቹን ሐዋርያት ሕይወትና አገልግሎት ብንመለከት መለኮታዊ ጥሪ አሁን እኛ እንዳለንበት ዘመን ተድበስብሶና ከግል ጥቅም ጋር ተቆራኝቶ እንዳልነበረ በቀላሉ መገንዘብ እንችላለን። በዛሬው መልእክት ላይ ሰፊ የሆነ የእውነተኛ አገልጋይ ባሕርያትን ለማየት አንችልም፣ ሆኖም ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ውስጥ ካስተማራቸው ትምህርቶች ውስጥ በመግቢያው ላይ ከተጠቀሰው ክፍል እንመለከታለን። በዚህም ‘እውነተኛ አገልጋይ ምን ዐይነት ባሕርይ ሊላበስ ይገባል?’ የሚለውን ለማየት እንሞክራለን።
በዚህ ክፍል ላይ እንደምናየው ጌታ የተናገረው ምሳሌ የአንድ አገልጋይን ባሕርይ በግልጽ የሚያሳይ ሲሆን፣ በጊዜው ለነበሩ ሰዎች ቀላልና ግልጽ ነበር። ምክንያቱም በባሪያና በጌታ ወይም (ባሪያ አሳዳሪ) መካከል የነበረው የሥራ ግንኙነት ለአድማጮቹ በቀላሉ ሊገባ የሚችል ነበር። በሥራ መስክ ላይ ተሰማርቶ ሲደክም የዋለ አገልጋይ ወደ ቤቱ በተመለሰ ጊዜ በቤቱ ከጌታው ጋር ያለውን ግንኙነት ያሳየናል። አገልጋዩ በውጭ ያለውን ሥራውን ጨርሶ የተመለሰ ቢሆንም እንኳን በቤት ውስጥ ጌታውን ማገልገል ይጠበቅበታል። ጌታው ባሪያውን ‘በማዕድ ተቀመጥና ብላ አይለውም’ ይላል። ይልቁንም እርሱ በማዕድ ከመቀመጡ አስቀድሞ ጌታው የሚበላውን ማዕድ በማዘጋጀት እንዲበላና እንዲጠጣ ያገለግለዋል። ጌታውን ካገለገለ (ካበላና ካጠጣ) በኋላ ደግሞ እርሱ ሊበላ በማዕድ ይቀመጣል። እዚህ ላይ ልናስተውል የሚያስፈልገው ዋናው ነገር ባሪያው ወይም አገልጋዩ ከራሱ ፍላጎት ይልቅ ቅድሚያ ሰጥቶ ሊያገለግል የሚገባው ጌታውን መሆኑን ነው። በዚህ ስፍራ ላይ ጌታው የሚለው ነገር ‘አንተ ከመብላትህ አስቀድመህ እኔን አገልግል ወይም አብላኝ’ ነው። በሌላ አነጋገር ‘ያንተ ነገር ከኔ መቅደም የለበትም’ ማለቱ ነው፤ እውነተኛ አገልጋይ ሁልጊዜ የሚያስቀድመው የጌታውን እንጂ የራሱን ነገር አይደለምና። የአገልጋይ ብድራት ከምድር ሳይሆን ከሰማይ ነው። ስለሆነም አገልጋይ በምንም ሁኔታ ውስጥ ለጌታው ቅድሚያን በመስጠት ማገልገል ይጠበቅበታል።
ዛሬ በዚህ ዘመን አገልጋዮች የሆንን የምናስቀድመው ማንን ይሆን? የጌታን ወይስ የራሳችንን ነገር? እንደው እውነት እንነጋገር ከተባለ ዛሬ አገልጋይ በብርቱ እየሮጠ ያለው ከጌታው ክብር ይልቅ ለራሱ ክብር ይመስላል። በአሁኑ ጊዜ በአብዛኛው የአገልጋዩ ዋነኛ ሩጫ ለክብርና ለሥልጣን እንዲሁም ለገንዘብ እንጂ ከራሱ አስቀድሞ ጌታውን ለማክበርና ለማገልገል አይደለም። ይህንን ስል ግን ጥቂት ቢሆኑም ከራሳቸው በፊት ጌታን ለማገልገልና ለማክበር፣ ለስማቸው ሳይሆን ለስሙ የሚተጉ እውነተኞች የሉም ማለቴ አይደለም። በአሁኑ ጊዜ ‘ቤተ ክርስቲያንን በኀላፊነት እመራለሁ፤ መለኮታዊ ጥሪም አለኝ’ የሚለው አገልጋይ ለጌታው ሳይሆን ለራሱ ስምና ክብር እንዲሁም ለንዋይ ካለው ጽኑ ፍቅር የተነሣ ከሌሎች ጋር የሚፈጥረው የይገባኛል አምባጓሮ ቤተ ክርስቲያን የሰላም ቀጠና ሳትሆን የጦርነት አውድማ እንድትሆን አድርጓታል። እንደውም በአሁኑ ጊዜ የአገልጋይ አጀንዳ የተቀየረ ይመስላል። በተለይ በአንዳንድ ቦታ ላይማ አገልጋይ አገላጋይ ሆኗል። የጥሪው ዋነኛ ማዕከል የሆነውን ወንጌሉን ትቶ ጦርነት አብራጅ፣ ኮሚቴ አዋቃሪና እሳት አጥፊ ሆኗል። ይገርማል አቤት ያለንበት ጉድ! ይልቅ ቶሎ ብለን እንንቃና ለራሳችን ጥቅም የምናደርገውን እሽቅድምድም ትተን ጌታን ለማገልገል እንነሣ። የራሳችንን ስም እንደ ባንዲራ ማውለብለቡን ትተን እንደ ቀደሙት እውነተኞች ሐዋርያት ራሳችንን እንደብቅና የጌታን ስም እናድምቀው።
በዚህ ክፍል ውስጥ ጌታ ስለ እውነተኛ አገልጋይ ከተናገረው ነገር የምናየው ሌላው ነገር አገልጋይ ስለፈጸመው አገልግሎቱ የሚኩራራና ራሱን እንደ ልዩ አድርጎ የሚቆጥር ሳይሆን ከጌታው ይሠራ ዘንድ የተሰጠውን የሥራ ኀላፊነት እንደፈጸመ ብቻ አድርጎ መቁጠር እንዳለበት ነው። ከዚህ በኋላ ጌታ ሲናገር “እንዲሁ እናንተ ደግሞ የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ” በማለት በአገልጋይ ስለሚሠራ አንድ የሥራ ክንውን ይናገራል። እውነተኛ የክርስቶስ አገልጋይ የሚያገለግለው በራሱ አቅምና ኀይል ሳይሆን ያገለግል ዘንድ ከአምላኩ በተሰጠው መለኮታዊ ጸጋና ብርታት ብቻ መሆኑን ጠንቅቆ የተረዳ ነው። አገልጋይ ይሠራ ዘንድ ከጌታው የተሰጠው ሥራ እንዳለው ይሄ ክፍል በግልጽ ያስረዳናል። “የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ” የሚለው ሐረግ የሚያሳን አገልጋይ ከጌታው ይሠራው ዘንድ ተሰጠው የሥራ ድርሻ እንዳለው ነው።
ጌታ በዚህ ስፍራ ላይ ለተከታዮቹ በዋናነት ያሳሰባቸው ነገር የተሰጣቸውን የሥራ ድርሻ መፈጸማቸውን ብቻ ሳይሆን ሥራውን ከፈጸሙ በኋላ ለራሳቸው ሊኖራቸው ስለሚገባው ምላሽ ነው። እነዚህ አገልጋዮች ከጌታቸው ተሰጣቸውን የሥራ ኀላፊነት በድል ከተወጡ በኋላ ስለ ራሳቸው በትክክል ማሰብ የሚገባቸው ነገር የማይጠቅሙ ባሪያዎች እንደሆኑ አድርገው መሆን ይኖርበታል። ጌታ ኢየሱስ በግልጽ እንዳስቀመጠው፣ “የማንጠቅም ባሪያዎች ነን፥ ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል በሉ” በማለት ነው። ጌታ ይሄንን ሲል አገልጋይ ካገለገለ በኋላ ስለ ራሱ ሊያስብ የሚገባው በዙሪያው የከበቡት ሰዎች ያሞካሹትን ቃል ወይም በልቡ የተሰማውን የድል አድራጊነት ስሜት ይዞ ‘ዘራፍ! ያለ እኔ ማን አለ?’ እያለ እንዲኩራራ ሳይሆን፣ አገልግሎቱን የተወጣው በጌታ ጸጋ ብቻ እንደ ሆነ በመረዳት ራሱን በትሕትና ዝቅ አድርጎ ‘እኔ የማልጠቅም ሰው ነበርኩ፤ ነገር ግን ጌታ ጸጋውን ሰጥቶኝ ሌሎችን እንድጠቅም አድርጎኛል’ እንዲል ነው።
ዛሬ በዘመናችን ጌታን ካገለገልን በኋላ ለራሳችን የሚሰማን ስሜት ምን ዐይነት ነው? በሕይወታችን ትናንትና ጌታ የሠራውን ድንቅ ሥራ ስናስብ ራሳችንን ዝቅ አድርገን ጌታን ማክበር ይኖርብናል። ምክንያቱም የአገልግሎታችን ሁሉ ስኬት በጌታ ጸጋ እና ኀይል እንጂ በራሳችን አቅም አይደለምና። የቀደመውን ስኬታችንን ስናስብ በፍጹም ትሕትና ራሳችንን ዝቅ አድርገን ‘እኛ የማንጠቅም ሰዎች ነበርን፤ ጌታ ግን ሌሎችን እንድንጠቅም ጸጋውን ሰጥቶ የእርሱ አገልጋዮች አደረገን’ ልንል ይገባል እንጂ፣ በትዕቢት ተወጥረን በራሳችን ሳይሆን በጌታ ኀይል በእኛ የተሠራውን ሥራ ሌሎች እንዲያውቁልን ነጋሪት እየጎሰምን ስማችንን ማነብነብ አይገባንም።
ዛሬ ግን በአንዳንድ ቦታዎች እንደምንመለከተው አንዳንድ አገልጋዮች ራሳቸውን በሌሎች ላይ ከመቆለላቸው የተነሣ የሚንቀሳቀሱት በልዩ ጠባቂዎች እስኪሆን ደርሰዋል። ከዚህ በተጨማሪም የሚያስፈራራ “የትንቢት ቃል” እየተናገሩ ሰዎች እጣን እንዲያጥኑላቸውና አጎንብሰው እንዲያደገድጉላቸው እያደረጉ ነው። እኛ ታዲያ ይሄንን አጉል ልማድ ከወዴት አመጣነው? ጌታችን ይህንን አላስተማረም፤ ሐዋርያትም አልነካካቸውም። እንደውም እነርሱ ከሰዎች የሚመጣን ክብር እየሸሹ ጌታቸውን ብቻ በማክበር የመሥዋዕትነትን አገልግሎት አገልግለው አልፈዋል። አገልጋይ ሆይ፤ ዛሬ ጠቃሚ እንድትሆን ያደረግህ የጌታ ጸጋ ብቻ በመሆኑ ራስህን አዋርደህ ጌታን አክብርና አገልግል። ይሄ ሲሆን ዛሬ በቤታቸው ሆነው የእውነተኛ አገልጋይ ያለህ እያሉ ለሚጮኹት ጻድቃን የጸሎት መልስ ትሆናለህ። አሜን!
Share this article:
“ከታሪክ የምንማረው ነገር ከታሪክ አለመማራችን ነው።” ይህን አባባል የተናገሩት ከዓለማችን ቢሊየነሮች መካከል ከፊተኞቹ ተርታ የሚገኙቱ አሜሪካዊው ዋረን ባፌት ናቸው።
የአብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ቁጥራቸው 150 የሚደርሱ “መንፈሳዊ” ተቋማትን በአጋር አባልነት የመቀበሉን መራር እውነታ አውቀናል። በኅብረቱ መግለጫ ሚዲያ ተጠርቶላቸው የካሜራ ክብር ያገኙት ግን አራቱ ብቻ ናቸው። ሌሎቹ ነገራቸው በድብስብስ የታለፈ ሊባል የሚችል ነው። ራሳቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ብቅ ብለው እኛም ነበርንበት ባይሉ መኖራቸውን ከቶውን ባላወቅን ነበር። አራቱ ትኩረት ያገኙበት ምክንያት፣ በተክለ ሰውነት “አውራዎች” ስለሆኑ ይሆናል።
The Oromo Liberation Front (OLF) has returned to Ethiopia saying it will continue its struggle peacefully after years of armed fighting from outside. The long-time leaders and icons of the movement have been welcomed by many on September 15, 2018 after many years of exile. Sadly, my father didn’t live long enough to see this day.
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society
Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.
Add comment