አሰሳ ፈውስ
ከዓመታት በፊት የኤች.አይ.ቪ-ኤድስ ቫይረስ በደሟ ውስጥ እንደሚገኝ ከምርመራ ውጤቷ ተረዳች። ይህንን በተገነዘበችበት ቅጽበት የመኖር፣ ሠርታ ሀብት ንብረት የማፍራትና የወደ ፊት ተስፋዋ ሁሉ ጨለመ። ግና በዚህ የጨለመ በሚመስል የሕይወት ጎዳና አንድ የመጨረሻ የምትለው “የብርሃን መንገድ” ታያት፤ ይሄውም “በመለኮት ጣልቃ ገብነት ፍጹም ፈውስ የሚገኝበት የእንጦጦ ማርያም ፀበል መንገድ”። የነበራትን ጥሪት ሁሉ ሸጣ ከዐግላይ ማኅበረ ሰብና ከወዳጅ ዘመዶቿ ተለይታ ፈውስ ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ አቀናች። የእንጦጦውን ኑሮ በእምነትና በተስፋ እንደ ዐቅሟ ብትገፋውም የጠበቀችው ፈውስ ግን በቶሎ አልጎበኛትም። “ያኖረኛል” ብላ በእጇ የያዘችው ገንዘብ ማለቅ ደግሞ ይበልጥ ያሳስባት ጀመር። የፈራችው ነገር ግን እንደ ተስፋዋ አልዘገየም፤ ማጣትና ብቸኝነት አብረዋት በደባልነት ሊኖሩ ከጎጆዋ ገቡ። ሕመሙ ያከሰመው የሥራ ተነሣሽነቷ ዳግም የሚያንሰራራ አልመስል ስላላት “ለእግዚሓር ያደሩ ̋ ሰዎችን ምጽዋት ጠባቂ ለመሆን ተገደደች። ይህ ታሪክ የወርቅአንጥፍ ጸጋዬ ታሪክ ብቻ ሳይሆን “የእንጦጦ ቤት ዕደ ጥበብ” ሴቶች ሁሉ የጋራ ታሪክ ነው።
እንጦጦ ቤት ዕደ ጥበብ?
የእንጦጦ ቤት ዕደ ጥበብ የተለያዩ ጌጣጌጦችን በማምረት ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ምርቱን የሚያቀርብ ለትርፍ የተቋቋመ ድርጅት ነው። የእንጦጦ ቤት ዕደ ጥበብ ምንም እንኳን አትራፊ ድርጅት ቢሆንም በውስጡ ያሉ ሠራተኞች ግን ድርጅቱ ከአትራፊነት ያለፈ ሚና እንዳለው የድርጅቱ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ወ/ሮ ቤተልሔም ብርሃኔ ለሕንጸት እንደገለጹት ከድጋፍ ሰጪና ከአስተዳደር ሠራተኞች ውጪ ያሉ 128 ሴቶች ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ናቸው። እነዚህ ሴቶች የጌጣጌጥ ሥራ ሥልጠና አግኝተው በእንጦጦ ቤት ዕደ ጥበብ ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ብዙዎቹ በልመና ተሰማርተው የሚኖሩ ሲሆኑ፣ ጥቂቶቹ ደግሞ ድጋፍ ከሚያደርጉላቸው ድርጅቶችና ግለ ሰቦች በሚያገኙት ድጎማ ሕይወታቸውን የሚመሩ ነበሩ። እንደ ወ/ሮ ቤተልሔም ገላጻ ዕደ ጥበብ ቤቱ በእሳቸው ባለቤትነት አንድ ድርጅት ሟሟላት ያለበትን ነገር አሟልቶ ሥራ የጀመረው በ2004 ዓ.ም. ቢሆንም ጅማሬው ግን ከዚያ በፊት እንደ ሆነ ይናገራሉ። በ2001 ዓ.ም. “ቤዛ አውትሪች” የተሰኘና በቤዛ ኢንተርናሽናል ቤተ ክርስትያን ሥር ያለ ግብረ ሠናይ ድርጅት በእንጦጦ የሚገኙና ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሴቶችን በማሰባሰብ የጌጣጌጥ ሥራ ሥልጠና ለስድስት ወራት እንደ ሰጣቸውና ሥልጠናውን ያገኙ ሴቶች ወደ ሥራ እንደ ተሰማሩ ወ/ሮ ቤተልሔም ያስረዳሉ። ነገር ግን በ2003 ዓ.ም.፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች ለትርፍ ያልተቋቋሙ እንደ መሆናቸው ትርፍ አስገኚ የሆኑ የድርጅቱ አጋር ተቋማት በራሳቸው ፈቃድ እንዲሠሩ በሕግ በመደንገጉ ዕደ ጥበብ ቤቱ ተዘጋና ሴቶቹ ተበታተኑ።
በወቅቱ የደከሙ እጆቻቸው በረትተውና ከጠባቂነት መንፈስ ተላቅቀው በደስታ ኑሯቸውን መምራት ጀምረው እንደ ነበር የሚስታውሱት በእንጦጦ ቤት ዕደ ጥበብ ሠራተኛ የሆኑት ወ/ሮ ተስፋነሽ ኢላላ ናቸው። “ቤተ ሰቤንና ሌሎች ሰዎችን ከማስቸገር ብዬ የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት ሞክሬ ነበር፤ ነገር ግን ሊሳካልኝ አልቻለም። ኋላ ወደዚህ ሥራ ገብቼ ከራሴ አልፌ ለቤተ ሰዎቼ ሁሉ መትርፍ ችዬ ነበር። ድርጅቱ ሲዘጋ ግን እንደ ገና ተስፋ ወደ መቁረጥ ተቃረቡኩኝ” በማለት ምን ያህል የድርጅቱ መዘጋት ለችግር እንዳጋለጣቸው በትውስታ ያወጋሉ።
ከወራት በኋላ በታኅሣሥ 2004 ዓ.ም ወ/ሮ ቤተልሔም ሴቶቹን እንደ ገና በማሰባሰብ ሥራውን እንደ ጀመሩ ይናገራሉ። የሁለተኛው ሥራ ጅማሬ ምንም እንኳን አበረታችና ተስፋ ሰጪ ባይሆንም በሂደት ነገሮች እየተስተካከሉ መምጣታቸውንና የሠራተኞቹም ተስፋ እንደ ገና እንደ ለመለመ አክለው ይገልጻሉ።
“አረጋዊያንን፣ ሕፃናትንና ሕሙማን የሚረዱ ሰዎችን አደንቃለሁ፤ የእኔ ምርጫ ግን ይህ አይደለም። የድርጅታችን ራእይም መሥራት የሚችሉ፣ ነገር ግን ተገቢውን ሥልጠና እና የሥራ ዕድል ላላገኙ ሰዎች ዕድሉን በመስጠት ሠራተኞችና ወደፊት ሥራ ፈጣሪዎች እንዲሆኑ ማስቻል ነው”
ሰለ ሴቶች
የሴቶችን ሰብዓዊ መብት ለማስከበር ጠንካራ ሕጎችን ከማርቀቅ ጀምሮ የተለያዩ አካላት እንቅስቃሴ ከማድረግ ባይቦዝኑም የሚደርስባቸው ጥቃት ግን እየተባባሰ መምጣቱን በመገናኛ ብዙኀን ከሚተላለፉ አሰከፊ ዘገባዎች መረዳት ይቻላል። ለኤች.አይ.ቪ-ኤድስ ለሌሎች መሰል ችግሮች ከወንዶቹ ቁጥር በላቀ ሁኔታ ተጋላጮቹ ሴቶቹ እንደ ሆኑ ጥናቶች ያመለክታሉ። “አንድ ነገር ኖሮኝ ለአገሬ በተለይም ለኢትዮጵያዊያን ሴቶች አንድ በጎ ነገር የማድረግ ራእይ ነበረኝ” የሚሉት ወ/ሮ ቤተልሔም ብርሃነ ለሴቶች የተለየ ሸክም እንዳላቸው አልሸሸጉም። “ሴቶች ዕድል ቢሰጣቸው ምን ያህል ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ እናቶቻችን ምሳሌ ናቸው፤ ሆኖም ካለንበት የከፋ ድኽነት የተነሳ ኤች.አይ.ቪን ጨምሮ ለብዙ ጥቃቶች የተጋለጡ መሆናቸው ለእነሱ ያለኝ ሸክም የተለየ እንዲሆን አድርጎታል” በማለት ለምን ትኩረታቸው ወደ ሴቶች እንዳዘነበለ ያስረዳሉ።
አቶ ፍቅረማርቆስ መርሶ “ሴቶች፣ ልጃገረዶች እና ኤች.አይ.ቪ-ኤድስ በኢትዮጵያ” በተሰኘው ጥናታቸው ሴቶች ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ ለምን እንደ ሆኑ ያስረዱሉ። በተለይም ዕድሜያቸው ከ15-29 የሆኑ ሴቶች በቀጥታ በቫይረሱ ተጠቂ የመሆን ዕድላቸው በተመሳሳይ ዕድሜ ካሉ ወንዶች ጋር ሲነጻጸር ልዩነቱ በጣም የጎላ መሆኑን ጥናታቸው ያሳያል። “ሴቶችን ለቫይረሱ የሚያጋልጡ ምክንያቶች ሥነ ተዋልዷዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የሕግ ማዕቀፎችን የሚያጠቃልል በመሆኑ ራሳቸውን የመከላከል አቅማቸው ለአደጋ የተጋለጠ” እንዳደረገው ነው አቶ ፍቅረማርቆስ በጥናታቸው ያሰፈሩት።
ሥራ፦ የበጎነት ቁንጮ
ለሌሎች ማከፈልና የተቸገሩትን በመከራቸው መረዳት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው በጎ ተግባር ነው። በተለይም ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትንና መበለቶችን በመከራቸው መጠየቅ “ነውር ዐልባ አምልኮ” እንደ ሆነም መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። በሌላ በኩል ደግሞ ከከንቱ ድጋፍ ባሻገር መሥራት የሚችሉ ሰዎችን ጠባቂ ብቻ እንዲሆኑ ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ ሙግታቸውን የሚያስቀምጡም አሉ።
ዊልበር ኦዶኖቫ “መጽሐፍ ቅዱሳዊ ክርስትና በዘመናዊቷ አፍሪካ” በተሰኘው መጽሐፋቸው የተቸገሩትን ለመረዳት በጎ የሆነ እና በጎ ያልሆነ መንገድ እንዳለ ጽፈዋል። “የተቸገሩትን መርዳት የሚቻልበት ጥሩም መጥፎም አቀራረብ አለ” የሚሉት ኦዶኖቫ፣“ጥሩው አቀራረብ የተቸገሩ ሰዎችን ትጋትና ኀላፊነት በማሳደግ ለእግዚአብሔር ዋጋ ያላቸው መሆናቸውን ያረጋግጣል። መጥፎው መንገድ ግን እነሱን በማዋረድ ጥገኝነት፣ ምስኪንነት፣ ተስፋ ቢስነትና ዋጋ የለሽነት እንዲሰማቸው ያደርጋል” ሲሉ አትተዋል።
ወ/ሮ ቤተልሔም ብርሃነ በበኩላቸው መሥራት እየቻሉ በተለያዩ ምክንያቶች ዕድል ያላገኙት ሰዎችን ማበረታት የተሻለው አማራጭ እንደ ሆነ ይሞግታሉ። “አረጋዊያንን፣ ሕፃናትንና ሕሙማን የሚረዱ ሰዎችን አደንቃለሁ፤ የእኔ ምርጫ ግን ይህ አይደለም። የድርጅታችን ራእይም መሥራት የሚችሉ ነገር ግን ተገቢውን ሥልጠና እና የሥራ ዕድል ላላገኙ ሰዎች ዕድሉን በመስጠት ሠራተኞችና ወደፊት ሥራ ፈጣሪዎች እንዲሆኑ ማስቻል ነው” ይላሉ።
ይህንን የወ/ሮ ቤተልሔምን ሙግት የሚያጠናክር ሐሳብ የምታስተጋባውና ከመረዳት ይልቅ ሠርቶ መኖር የበለጠ ምቾት እንሚሰጣት የምትናገረው ደግሞ በእንጦጦ ዕደ ጥበብ ሠራተኛ የሆነችው ሠናይት አዲፋ ናት። “ከቫይረሱ ጋር እንደምኖር ካወኩ ጊዜ ጀምሮ ድጋፍ የሚያስፈልገኝ ደካማ አድርጌ ራሴን ስለማስብ መሥራት አልችልም የሚል አስተሳሰብ ነበረኝ፤ አሁን ግን ሠርቼ መኖር በመቻሌ ተደስቼና ሕመሜን ረስቼ እኖራለሁ” ትላለች። የሠናይትን ሐሳብ የምትጋራው ወርቅአንጥፍ ጸጋዬ በበኩሏ፣ “መሥራት እንደምችል እስኪነገረኝ ድረስ የሥራ አቅም ቢኖረኝም ምንም ዐይነት የመሥራት ዕቅድ ግን አልነበረኝም” በማለት ያለፈውን ጊዜ ታስታውሳለች።
የሥራ ተነሣሽነት መቀዛቀዝ ከሕመሙ ባሻገር ሥነ ልቦናዊ አንድምታም እንዳለው የምታናገረው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በክሊኒካል ሳይኮሎጂ የድኅረ ምረቃ ትምህርቷን የምትከታተለው ዮዲት ዶዳ ናት። “ሁል ጊዜ ሕመም በራሱ የሥራ ሞራልን አያጠፋም፤ ነገር ግን ከእንግዲህ መሥራት አልችልም የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ በሰዎች ዘንድ በማደሩ ምክንያት የሥራ ተሣሽነታቸው ይጠፋል” ትላለች። ችግሩ ሥነ ልቦናዊ ብቻ ሳይሆን በማኅበራዊ ጫናዎችም ጭምር የታጀበ እንደ ሆነ የሚናገረው ደግሞ የአካባቢ ጤና ባለሙያና በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የሜዲካል ሳይንስ ተማሪው የሆነው ዮሴፍ ለማ ነው። ዮሴፍ “ማኅበረ ሰቡ በተለምዶ አንድ ሰው በማንኛውም ሕመም ከተጠቃ መሥራት እንደሌለበት ያምናል። ጉዳዩ ወደ ኤች.አይ.ቪ ሲመጣ ደግሞ ትንሽ ባስ ይላል። ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖሩ ሲያውቁ ወይም ሲታወቅባቸው፣ እንኳን ሠርቶ የመኖር ተስፋ ይቅርና የመኖር ተስፋቸው ወዲያው ይከስማል” ሲል አሰተያየቱን ይሰጣል።
ትግል እና ጽናት
“ተግዳሮት ከሌለ ሥራ የለም” የሚሉት ወ/ሮ ቤተልሔም የዕደ ጥበብ ቤቱን ሥራ ከጀመሩ ወዲህ ብዙ ተግዳሮቶች እንደገጠሟቸው ይናገራሉ። “ገና ከጅምሩ ብዙ ፈተኛዎች ገጥመውናል፤ ነገር ግን ይህ ራእይ የእኔና የቤተ ሰቤ ብቻ ሳይሆን የአገርና የትውልድ ነው። የራእዩ ባለቤት ደግሞ እግዚአብሔር ራሱ ነው የሚል እምነት ነበረኝ። ከብዛቱ የተናሣ አንድ ሁለት ብዬ መቁጠር ባልችልም ተግዳሮቶቹ ለበለጠ ሥራ እንድነሣሣ ረድተውኛል እንጂ ሥራ አላቆምኩም።
የእንጦጦ ቤት ዕደ ጥበብ ሠራተኞች በከፊል
ይልቅ አሁን አሁን የተግዳሮት አስፈላጊነት በጣም ጎልቶ ይታኛል፤ እንዳልተኛም አድርጎኛል። ይህን ስል ግን ጉዳት ወይም ሕመም የለውም ማለት አይደለም።” በማለት ለገጠማቸው ችግሮች እጅ እንዳልሰጡ ይናገራሉ።
ከሁሉ በላይ ግን ከባድ ፈተና የሆነባቸው በቂ የሆነ የመሥሪያ ቦታ ያለማግኘት ችግር እንደ ሆነ ነው ወ/ሮ ቤተልሔም የሚናገሩት። “አሁን እንኳን ባለንበት ሁኔታ ድርጅቱ ከመቶ ሰው በላይ የመቅጠር አቅም ኖሮት በዚሁ የመሥሪያ ቦታ ጥበት የተነሣ ለአምስት፣ ለስድስት ወራት ሰዎችን መቅጠር አልቻልንም።” በማለት ችግሩ አሳሳቢ እንደ ሆነ ይናገራሉ። ስድስት ኪሎ ከግብጽ ኤምባሲ፣ ወደ ኢየሱስ በሚወስደው መንገድ አንድ መለስተኛ የግለ ሰብ ግቢን በመከራየት የሚሠራው ዕደ ጥበብ ቤቱ ለሠራተኞቹ በቂ እንዳልሆነ ወ/ሮ ተስፋነሽ ኢላላ ይናገራሉ። ምክንያታቸውን ሲገልጹም፣ በሳምንት አምስት ቀን መሥራት እየቻሉ ሁሉንም ሠራተኞች በአንድ ጊዜ መያዝ የሚችል የመሥሪያ ቤታ ባለመኖሩ የተነሣ ሁለት ቀን ብቻ ለመሥራት ተገድደዋል።
የእንጦጦ ቤት ዕደ ጥበብ ሠራተኞች በከፊል
የፈውስ ቀውስ
የክርስትና እምነት ቀዳሚ አስተምህሮው የነፍስ ድነት ላይ የተመሠረተ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር በሰዎች ላይ ያለውን ሥጋዊ ደዌ እንደ ፈወሰ በመጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ተጽፎ እንመለከታለን። በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የእምነት ክፍሎች፣ በተለይም በአገራችን ባሉ ወንጌላውያን እና ኦርቶዶክስ ቤተ እምነቶች ብዙዎች ከነበረባቸው ሕመም እንደ ተፈወሱ በየምስባኩ ሲመሰክሩ መስማት እየተለመደ መጥቷል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ምስክርነቶቹ በተለያዩ የብዙኀን መገናኛ፣ በኤሌክትሮኒክስና በኅትመት ውጤቶች መሰራጨታቸው ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት እየተሰጠው እንዳለ አመላካች ነው።
በእንጦጦ ዕደ ጥበብ የሚገኙ ሴቶች ሁሉ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ፈውስን ፍለጋ ወደ መዲናዪቱ የመጡ ናቸው። ከሰባት ዓመታት በላይ ከቫይረሱ ጋር የቆዩት ወ/ሮ ተስፋነሽ ኢላላ አሁንም ያለ ተስፋ መቁረጥ ፀበል እየተጠመቁ እንዳሉ ይናገራሉ። ምንም እንኳን እስከ አሁን ድረስ ከእነሱ መካከል ተፈውሻለሁ ያለች ሴት ባትኖርም ብዙዎች ተፈወሰው ሲመሰክሩ መሰማታቸውን ግን እነ ወ/ሮ ተስፋነሽ ይናገራሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ ፈውሳቸውን እንደ ተቀበሉ በአደባባይ ከተመሰከረላቸው ወይም ራሳቸው ተቀባዮቹ ከመሰከሩ በኋላ ሕመማቸው ዳግም አገርሽቶባቸው ለስቃይ የሚዳረጉ ሰዎች እንዳሉ ይደመጣል። ምንም እንኳን ይሄኛው እንደ “የእምነት ማነስ” እና በተለያዩ ማመካኛዎች የታጀበና እንደ ፊተኛው በየመድረኩ ሥፍራ ባይሰጠውም ጥቂት በማይባሉ ሰዎች ግን የሚታወቅ የአደባባይ ምስጢር ነው። ፊሊፕ ያንሲ “ቅይማት” በተሰኘ መጽሐፋቸው የዚህ ዐይነት ምክንያት ለእምነቱ መሻከር መነሻ ስለሆነበት ሪቻርድ ስለተባለ ወጣት አገልጋይ ጽፈዋል። ወጣቱ በአንድ ወቅት በካትሪን ኩልማን አገልግሎት ተሳታፊ በሆነበት አንድ ጉባኤ የሕክምና ባለሙያ የሆነ አንድ ሰው በሸክም ገብቶ ለስድስት ወራት ካሰቃየው ሕመም መፈወሱን በራሱ አንደበትና በእግሮቹ እየተመላላሰ መመስከሩን እንዳየ፣ ከሳምንት በኋላ ግን ያን ሰው ሊያገኘውና የጠራ ምስክርነቱን ሊሰማ ሲደውል ሰውዬው ማረፉን እንደተረዳና ይህም በኋላ ለፈነዳው የቅይማት ቦንብ መንስኤ እንደ ሆነ ያንሲ ይናገራሉ። ለሪቻርድ እምነት መሸርሸር ምክንያት የሆነው “ፈውስ” ዛሬ የብዙዎችን ቀልብ እንደ ሳበ ሁሉ ለብዙዎች ደግሞ ጥያቄን ፈጥሯል።
ፈውስ በክርስቶስም ሆነ በሐዋርያት አገልግሎት የተገለጠና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው የእግዚአብሔር ስጦታ ነው የሚለው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአፕላይድ ሊንጉስትክስ ኤንድ ኮሚዩኒኬሽን የፒኤች.ዲ ተማሪ የሆነው ታሪኩ አነጋ፣ በዘመናችን ግን ይህ አገልግሎት የተለየ ትርጉም እያገኘ እንደ ሆነ ይናገራል። “የሰዉ ለፈውስ ያለው ከፍተኛ ጥማትና የእግዚአብሔርን ጊዜ ያለመጠበቅ ምእመኑን ለሐሰት ትንቢት ፈውስ አጋልጦታል” በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል።
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህርና በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በዲቁና አገልግሎት የሚሳተፈው ፍቅሩ ገ/እግዚአብሔር በበኩሉ የችግሩ መነሻ አንድም ከአገልጋዮቹ እንደገናም ምእመናን እግዚአብሔር ሁልጊዜም የመፈወስ ዐላማ እንዳለው አድርገው ከማሰባቸው የሚመነጭ እንደ ሆነ ይናገራል። “በቤተ ሰቤ ከደረሰው ነገር ተነሥቼ ብናገር እንኳን እግዚአብሔር ፈውሶ እንዳመሰገንን ሁሉ ባለመፈወስም ፈቃዱን ገልጦ ለጊዜው ብናዝንም ግን ተቀብልናል፤ የእኛን ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔርንም ፈቃድ ለመቀበል ዝግጁ መሆን አለብን” ይላል ዲያቆን ፍቅሩ።
ወ/ሮ ቤተልሔም በበኩላቸው “መድኃኒቱን እንዲወስዱና በርትተው እንዲሠሩ ምክር እንሰጣቸዋለን፤ ለሕመማቸው ፈውስም እንጸልይላቸዋለን። ነገር ግን ከሁሉም በላይ መዳናቸው የመቁረጥ ሕይወት መውጣቷ ብቻ ሳይሆን አሁን ራሷን ችላ ለቤተ ሰቧ መትረፏንም ትናገራለች። “አቅም ስለሚያንሰኝ ልጄን እንዲያሳድጉልኝ ለዘመድ ሰጥቼ ነበር፤ አሁን ግን ለራሴም ለልጄም በቂ የሆነ ገቢ ስለማገኝ አብረን እንኖራለን፤ እንደገናም ትምህርቷንም ቀጥላለች።” ስትል ለውጥ እንዳለ ትመሰክራለች።
ወ/ሮ ቤተልሔም የዕደ ጥበብ ቤቱን ሥራ ከጀመሩ ወዲህ የሠራተኞቹ ኑሮ ብቻ ድርጅቱም ሰፊ የሥራ ዕድል በማግኘቱ የእሳቸውና የቤተ ሰባቸውም ኑሮ መሻሻሉን አልሸሸጉም። “ሥራው ዘላቂ እንዲሆን ትርፍ መገኘት ስላለበት ጠንክረን እንሠራለን። በዚህ ምክንያት በምናገኘው ገቢና ትርፍ መጠን የደመወዝ ጭማሪ እናደርጋለን፤ የሠራተኞቻችን የእኛም ኑሮ ተለውጣል።” ብለዋል።
ለወደ ፊቱስ?
ወ/ሮ ቤተልሔም ብርሃነ እስካሁን ድርጅቱ ሠራተኞቹን ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ በየዓመቱ ደሞዛቸውን እየጨመረ አሁን በሰዓት 13 ብር እንደሚከፍላቸው ገልጸዋል። አክለውም ያለባቸው የመሥሪያ ቦታ ችግር መንግሥት ቃል በገባላቸው መሠረት በአጭር ጊዜ የሚቀረፍ ከሆነ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሌሎች ተጨማሪ ሁለት ሺህ በተመሳሳይ ሁኔታ ያሉ ሠራተኞች የመድረስ ዕቅድ እንዳላቸው ለሕንጸት ተናግረዋል። አያይዘውም፣ “ይህ የሥራ ዘርፍ ምንም እንኳን አድካሚ ቢሆንም ባለ ሀብቶችና ትልልቅ ድርጅቶች ወደ መስል ሥራዎች በመግባት ለብዙዎች የሚተርፍ በጎ ነገር እንዲሠሩ አበረታታለሁ” ሲሉም ጥሪ አድርገዋል።
ወርቅአንጥፍ ጸጋዬ በበኩሏ የእንጦጦ ቤት ዕደ ጥበብ አሠራር በተለያዩ ድርጅቶች እንደ ተሞክሮ ቢወሰድ ለትውልድ የሚተርፍ ቁም ነገር መሥራት እንደሚቻል ትገልጻለች። “መሥራት የሚችሉ ግን ዕድል ያላገኙ ለልመናና ለሌሎች አላስፈላጊ ተግባራት ራሳቸውን እያዘጋጁ ያሉ እኅቶቻችን አሉ። እነሱም እንዲህ ያሉ ዕድሎችን ቢያገኙ ሠርተው መለውጥ ይችላሉ። እነሱን ማገዝ ቤተ ሰባቸውንና ትውልድን ማገዝ ነው።”
Add comment