[the_ad_group id=”107″]

ዊክሊፍ

የታላቁ ለውጥ አጥቢያ ኮከብ

የከፍተኛ ትምህርቱን በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ቀጽሎ በነገረ መለኮት የዶክትሬት ዲግሪውን አገኘ፤ በዕውቀቱ የበረታ በመሆኑ በፕሮፌሰርነት ማዕረግ የፍልስፍናና የቲዎሎጂ አስተማሪ እንዲሆን የዩኒቨርስቲው ከፍተኛ የአመራር አካል አጨው። በዚህ ጊዜ ዝናው ከምድረ እንግሊዝ አልፎ በሌሎች የአውሮፓ አገራት ጎልቶ ተሰማ። ይህ አካዳሚያዊ ከበሬታው ምክንያት ሆኖም፣ የእንግሊዝ ነገሥታት በራቸውን ወለል አድርገው ከፈቱለት። በክህነት አገልግሎቱ ላይ ሰፊ የምርምር በር የተከፈተለት ይህ ምሁር፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን በጥልቀት መመርመርን፣ መፈተሽንና ማገናዘብን ጀመረ። የንባቡም ምጥቀት ክህነት ያደረላት ቤተ ክርስቲያን እየተጓዘችበት ያለው መንፈሳዊ ጎዳና አቅጣጫ መሳቱን እንዲያስተውል ረዳው። እንደ በርካታ ታሪክ ጸሓፊዎች አመለካከት፣ ካህኑ ያስተዋላቸው የአካሄድና የፍታቴ ስሕተቶች ከሁለት ምዕት በኋላ በተነሡት ተሓድሷውያን የጥንካሬና የዐሳብ መነሻ ምክንያት በመሆኑ ታሪክ “ከተሓድሷውያን አስቀድሞ ፈር ያመላከተ ዐዳሽ” ሲል ስሙን በከበሬታ ያነሣዋል።

በመልካም ሊቅነቱና በድንቅ ተሰጥኦው ዝናን ያተረፈው ይህ ማእምር የብርሃንን በር በከፈቱለት በነገረ መለኮት፣ በፍልስፍናና አገሪቱ ባወጣችው ሕግጋት፣ ይልቁንም “ፈሪሓ እግዚአብሔር” የእውቀት ሁሉ ሀብት ሲል በሚያሞካሸው ብኂሉ እየተመራ፣ የክርስቶስን ጸጋ ከሕዝቡ ያራቁትን ኀይላት በጽኑ ለመፋለም ቆርጦ ተነሣ። በዚህም የቅዱሳት መጻሕፍትን እውነት በቅንነት በማስረዳት ሥራውን ጀመረ። አስከትሎም ክህነት የገባላት ቤተ ክርስቲያን ስለ ሰው ወግና ስለ ክብሯ ስትል የቃለ እግዚአብሔርን እውነት እንደቀበረች ያለ ፍርሀት ያስተምር ገባ። በዚህ እውነትን በማዳፈን ክፉ ተግባር የተሰማሩትን ካህናትም ወነጀለ። ʻእውነት ወደ መንበሯ ልትመለስ ይገባታልʼ ሲልም ወተወተ።

ደፈር ብሎም የሕይወት መሥዋዕትነትን የሚጠይቀውንና “ጳጳሱ አይሳሳቱም” የተሰኘውን አንቀጽ በማሄስና ፍጹማዊ ሥልጣኑን በመኮነን ድምፁን ዐሰማ፤ አስከትሎም የቤተ ክርስቲያን ራስ ክርስቶስ ብቻ እንደ ሆነ፣ የድነት ምንጭም የአበው ብያኔዎችና የኀጢአት ማስተስሪያ ጽሑፎች ሳይሆኑ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠው መንገድ ብቻ እንደ ሆነ አስተማረ፤ ሰበከ፤ ዐሳወቀ።

ነባሯ ቤተ ክርስትያን እንደ አበው ሐዋርያት መንፈሳዊነትን ከቅይጥ አስተምህሮ አፋትታ በእውነት ጎዳና ላይ ትራመድ ዘንድ ብርቱ ትግል ያደረገበትን፣ “ቤተ ክርስትያን” የተሰኘውን መጽሐፉን ወደ ሕዝቡ ሰደደ። ይህም ድርጊት ከቤተ ክርስቲያኒቱ ካህናት ብርቱ ትግልና የከረረ ጠብ አስነሣበት።

ነገሮች በተካረሩበት በዚህ የግለት ሰዓት የጆን ዊክሊፍ ተማሪዎች የመምህራቸውን ትምህርት በየአቅጣጫው ይዘው ሮጡ። ይህ “ደፋር” ድርጊታቸውም ሮም ደርሶ ኖሮ፣ የመንበሩን ቁጣ ቀሰቀሰ። እናም ዊክሊፍ በሎንዶን መንበረ ጵጵስና ቀርቦ ምላሽ ይሰጥ ዘንድ መጥሪያ ደረሰው። ይሁን እንጂ፣ በምድረ እንግሊዝ ውስጥ ባለው ከበሬታ፣ በተለይም ከቤተ መንግሥቱ ባገኘው ድጋፍ ሳቢያ ክሱ ሳይሰማ ቀረ።

ዘግየት ብሎ ፖፕ ጎርጎርዮስ 11ኛ ዊክሊፍ ከበተነው መጽሐፍ ወደ ሃያ የሚጠጉ “ግድፈቶችን” ነቅሰው በማውጣት ለካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስ፣ ለንጉሥ ኤድዋርድ፣ ለሎንደኑ ጳጳስና ለኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ አመራሮች ሰድደው የክሱ ሂደት በአስቸኳይ እንዲታይ መመሪያና ትዕዛዝ ሰጡ። ይሁንና ጉዳዩ በውጥረት ላይ እያለ ፖፕ ጎርጎርዮስ በመሞታቸው ክሱ ዳግመኛ ሳይነሣ ቀረ።

የፖፑ ሞት ምክንያት ሁኖ ሁለት ጳጳሳት የʻወንበሩ ይገባኛልʼን ጥያቄ በማንሣታቸው በሮም ውስጥ ውጥረት ነገሠ። ጳጳሳቱም እርስ በርስ ከመወጋገዝ ባለፈ ደጋፊዎችን የማሰባሰብ ዘመቻቸውን ጀመሩ። በቅስቀሳቸውም፣ አብሯቸው የሚቆም ምእመን በመንግሥተ ሰማይ ውለታውን እንደሚያገኝ የተስፋ ቃል ገቡለት። ሁኔታው እየከፋ ሲመጣም የአንዱ ወገን በሌላው ላይ ጦር መዘዘ፤ የደጋፊውም የሕዝብ ስሜት ገደብ ጥሶም ደም ፈሰሰ።

የሥልጣን ሽኩቻው እንዲህ ንሮ ባለበት ሰዓት፣ ለእርሱ ፋታ የሆነለት ዊክሊፍ ዐሥራ ሁለት አናቅጽ የያዘውንና የጳጳሳቱን ግድፈቶች የሚነቀፈውን ጽሑፍ አወጣ። በይዘቱም የጳጳሳቱ የእርስ በርስ ሽኩቻና መወጋገዝ ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊና ኢ-ሥነ ምግባራዊ እንደ ሆነ አመላከተ፤ እርሱም በለውጡ ፍኖት ላይ ጠንክሮ እንደሚሠራ ገለጠ።

በዚህ “ድፍረቱ” የካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስ ጠላት ሁነው ተነሡበት፤ በኦክስፎርድ ካለው የማስተማር ሥራም አገዱት። እንዲያም ሆኖ እውነትን የማብሰሪያ አደባባዮችን ሊነፍጉት ግን አልተቻላቸውም። ይህም ዊክሊፍ ወንጌልን ይዞ ወደ መንደሮች ይዘልቅ ዘንድ ረዳው። ፈለጉን የተከተሉና የጸጋውን ቃል ለመስበክ በሕይወታቸው የተወራረዱ የወንጌል ሰባክያንም የክርስቶስን ወንጌል አንግበው በእንግሊዝ ግዛቶች ላይ ዘመቱ።

በአገልግሎቱም፣ ቃለ እግዚአብሔርን ማንበብና ማሰላሰል ለእምነት ጥንካሬና ለሕይወት ዕድገት መሠረታዊ ጉዳይ እንደ ሆነ ተገነዘበ። በዚህ አላበቃም፤ መጽሐፍ ቅዱስን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ለመተርጎም ልቡን አነሣሣ፤ እናም የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ከላቲኑ ቩልጌት ወደ እንግሊዝኛ መለሰ። በዚህም የእንግሊዝ ሕዝብ በገዛ ቋንቋው መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ በክርስቶስ የሆነለትን የማዳን ሥራ እያደነቀ ወደ ሕይወት ይፈልስ ዘንድ ተጋለት።

ወቅቱ የኅትመት መሣሪያ አውሮፓውያኑን ያልዘለቀ በመሆኑ፣ መጽሐፉን የማሠራጨት ሂደት አሰልቺና አባታይ ሆነ። በእጅ ይጻፋል፣ በእጅ ይገለበጣል፤ በእጅ ይዳጎሳል፣ በእጅ ይሰራጫል። በዚህ አድካሚና የተጓተተ ተግባር ሳቢያ ፍላጎትና አቅርቦት ኩታ ገጠም መሆን አልቻሉም። ይሁን እንጂ የዊክሊፍ ትርጉም የእያንዳንዱን እንግሊዛዊ ጥማት አንሮት ወደ አነስተኛ መንደሮች ሳይቀር መዝለቁን ተያያዘው።

የበርካቶች የማሰብ ኀይል መንቃት ጀመረ፤ የድነት መንገድም ወለል ብሎ ታየ። የመንበረ ጵጵስናው ጥላም በምድረ እንግሊዝ መግፈፍ ጀመረ። በቆራጦቹ ወንጌላውያን ተጋድሎም ከፊሉ የእንግሊዝ ግዛት የወንጌልን ምሥጢር ወደ ማወቅ ደረሰ።

የመጽሐፉ በሁሉም ሰዎች እጅ መግባት ከፍተኛ “የመሬት መንቀጥቀጥ” አስነሣ። ከላቲን ቋንቋ ውጪ ተራው ሕዝብ በሚግባባበት ቋንቋ የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጉም ይከናወናል የሚል ስጋት ባለመኖሩ፣ ትርጉሙን የሚመለከት የክልከላ ሕግ አልወጣምና ሮም የተቃውሞ ድምፅዋን ከማሰማቷና ሕግ ከመደንገጓ አስቀድሞ አንድም ሰው መጽሐፉ ወደ ሕዝብ እንዳይገባ የገታ አልነበረም።

ይሁንና በተከታዩ ጊዜያት ተደጋጋሚ ክስ የዊክሊፍን በር ማንኳኳት ጀመሩ። ይግባኝ ባለበት በምክር ቤቱ መንበርና በንጉሡ ችሎት ፊት የመከራከሪያ ነጥቡን በማቅረብ፣ የዘመኑ ጳጳሳት ከቅዱሳት መጻሕፍት ያፈነገጡ ትምህርቶችን በማሠራጨት ከድነት መንገድ እንደ ራቁ ያለ ፍርሃት ሞገተ።

ጉዳዩ እየገፋ ሲመጣ፣ በሊቀ ጳጳሱ ፊት ቆሞ ጉዳዩን እንዲገልጥና ምላሽ እንዲሰጥ ወደ ሮም ተጠራ። ይሁን እንጂ እምነትና ዐሳቡን በደብዳቤ ከመግለጥ በቀር ወደዚያ አላቀናም። በደብዳቤውም እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው ዐላማ ግልጽ በሆነ መንገድ በወንጌላት ውስጥ መጠቀሱ፣ ክርስቶስ በምድር ላይ የኖረው ሕይወትም እንደ ጳጳሳቱ ሳይሆን፣ ውዳሴን ዝናን ያራቀና ከፍ ለማለትም መውረድን ያመላከተ እንደ ሆነ ገለጠ፤ እንዲሁ ሊቀ ጳጳሳቱም ከክህነታዊ ተግባር ውጪ በምድራዊ ሥልጣን ሊተበተቡና ከክርስቶስ ፈለግ ውጪ ሊወጡ እንዳይገባ፣ በእርሱ በኩል ግን የመዳንን እውነት ያገኘበትን ወንጌል ፈጽሞ ከመስበክ እንደማይገታ አስታወቀ።

እንደ ጥንት የቤተ ክርስቲያን ጸሐፊዎች አመለካከት፣ ዊክሊፍ የቅዱስ ቃሉን የበላይነት አጉልቶ አመላክቷል፤ ከሺህ ዓመታት በላይ ያስቆጠረውን ሰብዓዊ ወግ አጥብቆ ተፋልሟል፤ ወደ ቃለ እግዚአብሔር እንመለስ ሲልም ተማጥኗል፤ አስተምሯል፤ ተጋድሏል። እውነቱን ለመናገር መንፈሳዊ ጽልመት ነግሦ በነበረበት በዚያን ዘመን የወንጌሉን እውነት በኑሮና በግብር ገልጦ አመላክቷል፤ በዚህ ተጋድሎ መካከል እያለ ነበር ምድራዊ ሩጫውን በ1376 አጠናቆ የተሰበሰበው።

ታሪክ እንዳሰፈረው፣ የወንጌል እውነት በእንግሊዝ ምድር ከመሰበኩ የተነሣ ማኅበራዊ ኑሮ ፈር ይዟል፤ ከነገሥታትና ከመሳፍንት ብዙዎች ለወንጌል ያደሩ ሆነዋል። የመሳፍንቱ መመለስ ክፉኛ ያስቆጣት ሮም የነበራትን ገደብ ዐልባ ሥልጣን በመጠቀም የእንግሊዝ መሪዎችን መጫን ጀመረች። በዚህም በእንግሊዝ መንደሮችና ቀዬዎች የተበተኑትን የምስራች ነጋሪዎችና ሕይወታቸው የተለወጠ አማኒያንን ማሳደድ፣ ማደንና ንብረታቸውንም መውረስ ጀመረች። በዚህም የአያሌ ሰባኪያንና ምእመናን ሕይወት ተሰውቷል፤ በመሥዋዕታቸውም ወንጌል እንዲሮጥ አድርገዋል።

ስደቱ ከመጽናቱ የተነሣ የመሳፍንት ዝርያ ያለባቸው ቤተ ሰቦች ወህኒ ተወረወሩ፤ ንፁሓን አሰቃቂ ፍርዶችን ተቀበሉ፤ በአማኞች ላይ የመከራ መዐት ተናደ። በኮንስታንስ የተሰበሰበው ሲኖዶስ የዊክሊፍን ትምህርቶች አወገዘ፤ የጻፋቸውም መጻሕፍትና የተረጎመው መጽሐፍ ቅዱስም እየተሰበሰበ ወደ እሳት እንዲጣል አዘዘ።

የእንግሊዝን ቤተ ክርስቲያን ታሪክ የጻፈው ፉለርና ታዋቂው የታሪክ ዘጋቢ ፊሊፕ ሼፍ እንደሚሉት፣ ከዊክሊፍ እረፍት በኋላ የተሰበሰበው ይህ ጉባዔ የዊክሊፍ ዐፅም ከተቀበረበት ወጥቶ በእሳት እንዲጋይ ብይን አስተላለፈ። ፍርዱ ከተከናወነ በኋላም በእሳቱ ኀይል ወደ ዐመድነት የተቀየረው አካሉ በታላቅ ወንዝ ላይ ተበተነ። በተለይ ፉለር ይህን ክዋኔ ሲገልጽ፣ እየተመመ የሚያልፈው ወንዝ ወደ ዐመድነት የተቀየረውን አካሉን ውጦ አላሰረገውም፤ ይልቁን እየተቀባበለ በማስገስገስ ከሰፊው ውቅያኖስ ቀላቅሎታል። በተምሳሌቱም ለሰፊው ዓለም አስተዋውቆታል። የዚህን እውነት ለማረጋገጥ ብዙ ምርምር አይጠይቅም። በአጭሩ የዊክሊፍ ተጋድሎ በምድረ አውሮፓ ገንኖ በነበረበት ዘመን ከቦሂምያ (ቺኮዝላቫኪያ) የተገኘው ዮሐንስ ኹስ የዊክሊፍን ትምህርቶች በፕራግ ዩኒቨርስቲ በማስረጽ ወንጌልን ሰብኳል። በዚህም በእንግሊዝ የተቀጣጠለው የወንጌል እሳት ይበልጥ እንዲግም ብርቱ ተጋድሎ አድርጓል። ከቡቃያው እንደታየውም ለዚህ ወንጌል ነፍሱን በመክፈል መሥዋዕትነትን ተቀብሏል።

እንደ ታዋቂው የታሪክ ባለሙያ ፊሊፕ ሼፍ ትንታኔ፣ የታላቁ ለውጥ “አጥቢያ ኮከብ” የተሰኘው ዊክሊፍ በ15ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ከተከሰተው የተሓድሶ እንቅስቃሴ ሁለት ምዕት ቀደም ብሎ ወደዚህች ምድር ገባ። ለተጠራበት ተግባርም ሕይወቱን ጭምር በመስጠት በ1376 ዓ.ም. ይህቺን ምድር ተሰናበተ።

Fikreyesus Hundessa

የቤተ ክርስቲያን የመድረክ አገልግሎት ከባድ ፈተና ላይ መውደቁ ተነገረ

የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የመድረክ አገልግሎቶች ከፍተኛ የሆነ ችግር እንደ ገጠማቸው ተገለጸ። ይህ የተገለጸው፣ በአዲሰ አበባ ያሉ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት መሪዎች በተገኙበት ሴሚናር ላይ ነው። ሴሚናሩ የተካሄደው ማክሰኞ ጥቅምት 27 ቀን፥ 2016 ዓ.ም.፣ በኢንተርናሽናል ኢቫንጀሊካል ቸርች (IEC) ነው። በውይይት መድረኩ ላይ ከሦስት መቶ በላይ የሚሆኑ የአጥቢያ መሪዎች ተገኝተዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ

እምነታችን ሲፈተሽ

የእምነትን አመለካከት በሁለት አቅጣጫ ዐጠር ባለ ሁኔታ እንመልከት። ይህም አንደኛ፤ እምነትን ለግል ኑሮ የምንጠቀምበት አግባብና፣ ሁለተኛ እምነትን ለመንግሥቱ የምንጠቀምበት አግባብ ነው።  እምነት ለግል ኑሮ በግል

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.