[the_ad_group id=”107″]

የዘመነ ዜማ ለዘመናት ንጉሥ – ዜማ ለክርስቶስ

ከ1960ዎቹ የሙሉ ወንጌል ሀ መዘምራን እስከ ዜማ ለክርስቶስ ህብረት፣ በአንድ እጅ ጣት ከሚቆጠሩ ዝማሬዎች እስከ አለንበት ዘመን የዝማሬ ጎርፍ፣ ከለሆሳስ የጓዳ ዝማሬ እስከ አደባባይ ሆታ፣ ከአንጋፋ እስከ ወጣት ዘማሪያን እስከ ወጣት ዘማሪያን . . . ይህ የኢትዮጵያ ቤ/ክ የዝማሬ ታሪክ ነው፡፡ መዝሙር ተቀዛቅዟል የለም አድጓል የሚለውን ሙግት የሻረ አዲስ የዝማሬ መንፈስ፣ ሁሉንም የሚያስማማ አቀራረብ፣ የተዋጣለትና የተሟላ ዝማሬ እነሆ ከወጣት ዘማሪያን ለኢትዮጵያ ቤ/ክ ተብርክቷል፤ ከዜማ ለክርስቶስ፡፡ ወጣትነታቸውን፣ ጉብዝናቸውንና ችሎታቸውን ሁሉ ለጌታ የሰው ወጣቶች የሰጠኸንን አንሆ ብለው ለዘመናት ንጉስ ከልብ የሆነ ሕያው ዝማሬ ተቀኝተዋል፡፡

ዜማ ለክርስቶስ ዘማሪያን በዝማሬ ይዘት፣ በሙዚቃ ክህሎት፣ በድምጽ ተሰጥኦ የተዋጣላቸው መሆናውን ሁሉም ይስማማል፡፡ ‹‹ሕብረቱ ከመቋቋሙ አስቀድሞ እንኳ ወጣቶቹ ለሙዚቃ የተሰጡ›› እንደነበሩ የስታውቃል የሚለው በመዝሙር አርት ሚኒስትሪ የሙዚቃና ዝማሬ መምህር የሆነው ኦዮብ በረከት ነው፡፡ ኢዮብ ሐሳቡን ሲያጠናክር “ያሰባሰባቸው እራሱ ይህ የሙዚቃ ተሰጥኦአቸውና ፍላጎታቸው ነው” ይላል፡፡ በእርግጥ አገርኛ ዝማሬዎቹን ከውጪውጋ እያዛነቁ ማዜማቸው አድማጮቻቸውን አበርክቶታል፡፡ የቤዛ አለም አቀፍ ቤ/ክ ዘማሪ እና የስነመለኮት ተማሪዋ ጽዮንም አድናቆቷን ስትገልጽ “ቆየት ያሉ ዝማሬዎችን በአዲስ መልኩ ለአሁኑ ትውልድ ማቅረባቸው የትውልድ ክፍተት አንዳይፈጠር በማድረግ አስተዋጽኦ አለው” ትላለች፡፡

ጅማሬና እድገት

የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት አባል በሆኑ ወጣቶች ዜማ ለክርስቶስ በ1999 ዓ.ም እንደተመሰረተ አባላቱ እምነት ተጋፋው፣ሐና መኮንን፣ ምህረት ተጋፋው፣ ዳዊት ጌታቸውና ኬኔሳ ይናገራሉ፡፡ በመስረታው ወቅት የነበሩ አባላት የሙዚቃ ትምህርት ቤት ተማሪ በመሆናቸው ያላቸው የሙዚቃ እውቀትና የአገልግሎት ፍላጎት ለመሰባሰባቸው ምክንያት ነበር፡፡ ወጣቶቹ ከእድሜያቸው በላቀ የበሰሉና የሰከኑ ዝማሬዎችን ከአስደናቂ ሙዚቃ ክህሎትጋ አቅርበዋል፡፡ በግልም ዳዊት ጌታቸው ፣ሐና ተክሌ እና ሌሎችም የሰሯቸው የዝማሬ ካሴቶች፣ ቪሲዲዎችና ኮንሰርቶች ለቅዱሳን በረከት ሆነዋል፡፡ ለዚህ በሙዚቃ ችሎታውና በድንቅ የዝማሬ አቀራረቡ በርካታ ሽልማቶችን ያገኘው ዳዊት ጌታቸውን እንዲሁም ዘማሪ ሐናን እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡

ይዘት

ለነገሮች ትርጉም የሚሰጠው እንደሰሚው ነው ወይስ እንደተሰሚው ለሚለው ሃሳብ ሁለት ጎራ የለየ ክርክር እንዳለ አስተውያለሁ የሚለው የነገረ መለኮት ሁለተኛ ዲግሪውን በወንጌላውያን ነገረ መለኮት ኮሌጅ በማጥናት ላይ የሚገኘው እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ሁለተኛ ዲግሪ ተማሪው ዮናስ ዘውዴ ነው፡፡ ዮና “በዜማ ለክርስቶስ የዝማሬ ቡድን ዝማሬዎቻቸው ውስጥ ጎልቶ የሚታዩ ነገሮች አሉ” ይላል አስተያየቱንም በመቀጠል “ዝማሬዎቻቸው በሰው ላይ ሳይሆን በእግዚአብሔር ላይ ያተኮሩ” ሆነው እንዳገኛቸው ይናገራል፡፡ በርካታ መዝሙሮች ያተኮሩት ምድራዊ ኑሮና በረከት ላይ፣ በላሁ፣ ጠጣሁ፣ ተባረኩሁ፣ እጥላለሁ፣እጥሳለሁ፣ እጠረምሳለሁ፣ እራስ እሆናለሁ በሚሉና ትኩረታቸው በዘማሪው/ዋ/ ስኬት፣ ታላቅነት፣ ዝነኝነት በአጠቃላይ እኔነትን ማዕከል ያደረጉ ዝማሬዎች ናቸው የሚል አስተያየት ይደመጣል፡፡ “ነገር ግን የዜማ ለክርስቶስ የዝማሬ ቡድን ዝማሬዎች ስንመለከት የመዝሙራቸው ማዕከል ገናናው እና ወደር የለሹ ጌታችን መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቃይ፣ እንግልት፣ ድልና ዳግም ምጽአት፣ እግዚአብሔርን ማዕከል ያደረጉ (God – centered or Theo-centric) ሆኖ እነዳገኛቸው ወጣት ዮናስ ይገልጻል፡፡ የመዝሙር አቀራረባቸው እና ይዘትን በተመለከተ እንደ እነሱ ያለ ምሳሌ የስፈልገናል የምትለው ደግሞ ዘማሪት ጺዮን ናት፡፡ “ከቡድኑ አባላት ሶስቱ ያህል ተማሪዎቼ ነበሩ፡፡ የመጀመሪያ አልበማቸውንም የሰሩት በእኔ እስቱዲዮ ውስጥ ስለነበር በየግዜዉ እንገናኝ ነበር፡፡ ሁለት ኮንሰርታቸዉም ላይ አብሬ ተጫውቻለሁ” ያለው የሙዚቃ ባለሙያውና ዜማ ለክርስቶስ የዝማሬ ቡድኖችን በቅርበት የሚያውቀው ዮናስ ጎርፌ ነው፡፡ አክሎም “ዝማሬዎቻቸውና ኮንሰርታቸው የተዋጣለት ነበር፤ በጣም ጥሩ ተሰጥኦና ጥሩ አብሮ የመስራት ባህል” አላቸው ይላል፡፡

በዝማሬዎች ውስጥ ቃል በቃል የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን እየጠቀሱ መዘመር ምንም ክፋት ባይኖረውም ቃሉ የተጠቀሰበትን አውድ በተገቢው መንገድ ማጤን ተገቢ ነው፡፡ ይህም ከብዙ ነገረ መለኮታዊ ስህተት ያድናል፡፡ “መልዕክቱን የሚሸከሙትን ቃላቶች ትንሽ ዳጎስ ያሉና የተመረጡ ቢሆኑ ዝማሬውን ያገዝፈዋል፡፡” የሚለው ዮናስ ዘውዴ ነው፡፡ በሙዚቃቸው ውስጥ ሃገርኛ ዜማና ሙዚቃዊ ስልት እነዲሁም ባሕላዊ መሳሪያዎች ቢካተቱ ይበልጥ ውጤታማና ዘመን ተሻጋሪ ያደርጋቸዋል የሚለው አስተያየት የበርካቶች ነው፡፡ ዘማሪያን የዝማሬ ጥበብ (Muzic Art) ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ የዝማሬውን መንፈስ (መልእክቱን) እንዳይዘነጉ ያስፈልጋል፡፡ “እኛ ግን የዝማሬውን መንፈስም የሙዚቃውን ጥበብም ይዘን መሄድ አንፈልጋለን አንዲያውም ሁለቱን መለያየት ለእኛ ከባድ ነው” ትላለች ሐና መኮንን፡፡ ዜማ ለክርስቶስን የተመለከተ አስተያየት ሰጪዎች ጉራማይሌ ናቸው፡፡ ሙዚቃው በዛ፣ ቅላፄው በጣም መጠቀ፣ ግጥሙ አንዳንዱ አይሰማም፣ ከሀገርኛ ይልቅ የፈረንጁ ተጭኖታል፣ በጣም አሪፍ ናቸው ፐ- ሙዚቃ፣ ፐ-ቅላፄ፣ ፐ-ግጥም እንደ አሸን አንጎደጎዱት የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የነገረ መለኮት ተማሪው ቶማስ ገብረመስቀል ዜማ ለክርስቶስ ለበርካታ ወጣቶች አርአያ የሚሆኑ የአዘማመር ስልት የተከተሉ ክርስቶን ማዕከል ያደረጉ ዝማሬዎች እንደሚያቀርቡ ሲገልጽ ዮናስ ዘውዴም በበኩሉ ዜማ ለክርስቶሶች ለእኔ “እንደስማቸው ናቸው” ይላል፡፡

ስኬት

ዋናው ስኬታቸው እራሳቸው አምላኪ መሆናቸው ነው የምትለው የቤዛ ኢንተርናሽናል ቤ/ክ ዘማሪዋ ጽዮን ናት፡፡ ጽዮን አስተየቷን በመቀጠል የሙዚቃ ልእቀታቸው የዜማ እውቀታቸውና ስነመለኮታዊ ሚዛናዊነታቸው ዜማ ለክርስቶሶችን የተሟላ ዘማሪ ያደርጋቸዋል ትላለች፡፡ ስኬታውን በተመለከተ አባላቱም ሲናገሩ “ትልቁ ስኬታችን” ይላሉ “በአገልግሎቱ መጠቀማችን ነው” በማለት ከሕይወታቸው የተቆረሰ አገልግሎት በማቅረባቸው ደስተኞች እንደሆኑ ይገልጻሉ፡፡ “በሕብረቱ ውስጥ መጸለያችን፣ የእግዚአብሐየርን ቃል መማራችን፣ ማገልገላችን በመንፈሳዊ ሕይወታችን እንድናድግና እንድንተናነጽ አድርጎናል” ይላሉ፡፡ አገልግሎታቸው እስከመቼ እንደሚዘልቅ ለቀረበላቸው ጥያቄ እምነት መልስ ስትሰጥ “እንዲሁ እያገለገልን አብረን ማርጀት ነው የምንፈልገው፡፡ ልጆቻችንን እና የልጅ ልጆቻችንም ይዘን ማገልገል ነው የምንፈልገው” ብላለች፡፡ ይህን አሳብ ሌሎቹም ቢጋሩትም የግል አገልግሎት ሕብረቱን እየተጫነው ነው የሚለው አስተያየት ግን በርክቷል፡፡

አስተዋጽኦን በተመለከተ እስካሁን ካዘጋጇቸው ታላላቅ ኮንሰርቶችና የዝማሬ አልበሞች በተጨማሪ ወደፊትም በአዲስ አበባና በተለያዩ ክፍለ አገራት ኮንሰርቶን እና አልበሞችን ማዘጋጀት ፣ ዩኒቨርሰቲዎች ላይ ትኩረት ያደረገ አገልግሎት፣ የሕግ ታራሚዎችን ማገልገል፣ ወጣቶችንና ህጻናተን በዝማሬ ማሰልጠን ራዕያቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በቅርቡም የሰሩትን የዝማሬ አልበም “አባት ለሌላቸው ብሩህ ተስፋ” ለሚሰኝ ምግባረ ሰናይ ድርጅት መስጠታቸው በእርግጥም ቤተክርስቲያንን ለማገልገል ሁለንተናዊ ድጋፍ ማድረግ ሀሳብ አንዳላቸው ያሳያል፡፡ ኬኔሳ ይህንን ሲያብራራ “ሰርተን ያበረከትነው አልበም ተሽጦ ለዚህ አገልግሎት እንዲውልን ድጋፍ አድርገናል፡፡ ይህ መጽሐፈ ቅዱስ አንደሚለው እውነተኛ አምልኮ ነው” ይላል፡፡ መጀመሪያውን አገልግሎት በሮያል ፋሚሊ ቤ/ክ ካደረጉት እስከ ደብረዘይት፣ ምስራቅ መሰረተ ክርስቶስና ብሔራዊ ቴአትር መድረኮች ባሉ አገልግሎቶች ጌታ ከአነስተኛ ጉባኤ እስከ ሰፊ የአግልግሎት መስክ እንደረዳቸው ይናገራሉ፡፡ “ብህረታችን ወስጥ ያሉ አባላት የተለያየ ተሰጥኦ ያላቸው መሆናቸው ጠንካራ ጎናችን ነው” የሚለው ኬኔሳ “አንዳችን አንደዚህ ሌላችን እንደዚያ ባለ ተሰጥኦ ሕበረታችንን ሙሉ ለማድረግና ለማነጽ እንተጋለን” ይላል፡፡ አንዱ በጸሎት ሌላው ፕሮግራም በማስተባበር፣ ቃል በማካፈልና በማስተማር፣ በሙዚቃና በዜማ አንዱ የጎደለውን ሌላው በመሙላት ለማደግ እየተጉ አንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ ዝማሬን በተመለከተ ከሌሎች በተለየ ቆየት ያሉ ዝማሬዎችን ለወጣቱ ትውልድ ማቅረባቸው አዲሱ ትውልድ ከአባቶች ዝማሬ ጋ እንዳይፋታ ድልድይ በመሆን እያገለገሉ እንደሆነ ዘማሪት ጽዮን ትገልጻለች፡፡

ተግዳሮት

“የበርካታ ዘማሪዎች ተግዳሮት በጣም ብዙ ቢሆንም አንዱና ትልቅ ፈተናቸዉ ገና ምንም ሳይሰሩ እራሳቸዉን አተልቀው በትእቢት መወጠር ሲጀምሩ ቃሉ እንደሚል ትእቢት ውድቀትን ትቀድማለች” የሚለው ዮናስ ጎርፌ ነው፡፡ በተለይ የብዙዎቹ ‹‹የሶሎ ዘማሪ›› ተብዬዎች ለተጠሩበት አገልግሎት እራሳቸውን አለማግዛት፣ ለጸሎትና ለእግዚአብሔር ቃል ትኩረት አለመስጠት፣ ትሁት አለመሆን የበርካቶች ተግዳሮት ነው፡፡ ዜማ ለክርስቶሶችም ይህ መሰናክል አንዳይገጥማቸው ሊጠነቀቁ ይገባል የሚለው የዮናስ አስተያየት ነው፡፡ ወጣቶቹ እስከ አሁን ድረስም የሙዚቃ መሳሪያ ችግር፣ የመሰብሰቢያ ቦታ እጦት ቢገጥማቸውም ችግሩን ተቋቁመው እያገለገሉ ነው፡፡ የሙዚቃ ባለሙያው ዮናስ ጎርፌ ስቱዲዮ ፈቅዶላቸው እዚያ ፕሮግራሞቻቸውን ያደርጉ አንደነበር አሁንም የመካነ ኢየሱስ ሙዚቃ ት/ቤት በፈቀደላቸው ስፍራ እየተሰባሰቡ ፕሮግራማቸውን እንደሚያደርጉ ይናራሉ፡፡ ዜማ ለክርስቶስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየገጠሙት ነው ከሚባሉት ተግዳሮቶች ውስጥ “ከቡድን ይልቅ ለግል አገልግሎት ቅድሚያ መስጠት” ዋነኛው ነው ቢባልም፤የህብረቱ አባላት ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ ቡድኑ ወጥ የሆነ አሰራርና አመራር እንዲሁም መተዳደሪያ አለመኖሩ ምናልባት አንዳያዝረከርካቸው ያሰጋል፡፡ በዚህ አስተያየት ግን ዳዊት የሚስማማ አይመስልም “የግል አገልግሎትን ከህብረቱጋ ለማጣጣም ፕሮግራሞችን ማናበብ ያስፈልጋል ይህ ዘማሪውን ጫና ውስጥ ከመክተቱ በስተቀር የማገልገል ፍላጎቱ ካለ ሁለቱንም አብሮ ማስኬድ” እንደማያስቸግር ይናገራል፡፡ ሌላው የበርካታ ክርስቲያን ሙዚቀኖች ችግር የሆነው ወደ አለም ጎራ ብሎ ከባንዶች ጋ ዘፈኖችን መጫወት የወጣቶቹ ተግዳሮት እንዳይሆን ያሰጋል የሚለው የበርካቶች አስተያየት ነው፡፡ አስተያየቱ ወጣቶቹን ከመሰሰት እና እዳያጧቸው ከመስጋት የሚሰነዘር ነው፡፡ ዘማሪ ጽዮን ግን በዚህ አትስማማም አብዛኞቹ የዜማ ለክርስቶስ አባላት መንፈሳዊ ሕይወታቸው በጌታ ስር የሰደደ ስለሆነ ወደ አለም ይሄዳሉ ብላ አንደማትሰጋባቸው ትገልጻቸል፡፡

“ላለፉት 15 አመታት ቤተክርስቲያንን እና አምልኮን ለማዳከም ሰይጣን መጀመሪያ የተጠቀመው እስትራቴጂ ኳየሮችን መምታት ነበረ፡፡ ቀጥሎ ዝማሬ በወጣት ዘማሪያን ጫንቃ ላይ ወደቀ፡፡ ያውም ባልበሰሉ እና ሐላፊነት መሸከም በማይችሉ ወጣቶች ላይ፡፡ ይህ የዝማሬ መቀዛቀዝ ምክንያት ሆነ፡፡ ለዚያም ነው ዝማሬ ዛሬ ላለበት ዝቅጠት የበቃው” የሚለው እስተያየት ቢደመጥም በዚህ በሀሳብ የማይስማሙ በርካቶች ናቸው፡፡ ዜማ ለክርስቶሶች በዘማሪዎች ላይ የወደቀውን ነቀፋ የሻረ ሕይወትና አገልግሎት ታይቶባቸዋል፡፡ በመካከላቸው የነገረ መለኮት ተማሪዎች መኖራቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዝማሬዎችን እንዲያቀርቡ ያስችላቸዋል የሚለው ቶማስ ገብረ መስቀል ፤ “ነገር ግን አገልግሎቱ ቀጣይነት ላይ ጥያቄ አለኝ” በማለት ስጋቱን ይገልጻል፡፡ ይህም ለህረቱ ያላቸው ትጋት አንደቀድሞው መሆንና በአንዳንድ ሙዚቀኞች ላይ እንደሚታየው ወደ አለማዊ ሙዚቃ መሳብ ሕይወታቸውንም አገልግሎታቸውንም ሊጎዳው ይችል ይናሆል ብሎ እንደሚሰጋ ይገልጻል፡፡ የስነ ምግባር ችግርን በመተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ “ይህን ያክል የጎላ ችግር በመካከላችን የለም ቢኖርም እንወቃቀሳለን በተጨማሪም ማንኛውንም የሕብረቱን አባል ለመርዳት ዝግጁ ነን ይላሉ” ድጋፍን በተመለከተም “ትልቁ የሚየሥፈልገን ድጋፍ ጸሎት ነው” በማለት የፋይናንስ እጥረት አገልግሎታቸውን እንደገደበው በመግለጽ “ልዩ ልዩ ድጋፍ አንሻለን በገንዘብ፣ በቁሳቁስ የሚደግፉን ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡ ምንም አይነት የሙዚቃ መሳሪያ የለንም የምንጠቀመው በምንጋበዝበትን ቤ/ክ መሳሪያ ነው” ይላሉ፡፡

‹‹አታዋክቡን››

በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ዝማሬ አገልግሎት በተመለከተ አስተያየት የሰጡ ሰዎች ለዘማሪዎች ያስተላለፉት መልእክት “አታዋክቡን” የሚል ነው፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ ዝማሬዎች ወደ ፈጣን ምት እና እንቅስቃሴ ያጋደሉ በመሆናቸው ረጋ ያሉ በጥሞና ሊደመጡና ሊዘመሩ ከሚገባቸው ዝማሬዎች ጎድለናል ይላሉ፡፡ የሙዚቃ ባለሙያው ዮናስ ጎርፌ “በምናቤ ሳየው ለመሆኑ አሁን ያለው የፕሮቴስታንት አማኝ ትውልድ የጥሞና ጊዜ ምን እንደሆነ ያውቅ ሆን? ካላወቀስ የማነው ጥፋቱ?” ብሎ ይጠይቃል፡፡ ዘማሪዎች እና አምልኮ መሪዎች ለጉባኤ የሚሆንና የማይሆን ዝማሬ በማለት በመከፋፈል የጉባኤ ዝማሬዎች ላይ ትኩረት ሰጥተዋል፡፡ ምስጋናና አምልኮ ላይ ብቻ ያተኮሩና ሰውን የሚያንቀሳቅሱ ፈጣን ምት ያላቸው ዝማሬዎችን ብቻ መምረጣቸው ሕዝቡ ከዝማሬዎች ሊያገኝ የተገባውን ሁለንተናዊ ጥቅም አጥቷል፡፡ “ዘማሪ የኖረውን እና መኖር ያለበትን ካልዘመረ ዘፋኝ ነው” የሚለው ዳዊት ሕዝቡን ብቻ ማዘመር ከባድ አንደሆነ ያሰምርበታል አክሎም “ዘማሪዎች አንደ አርቲስት ሳይሆን አንደ መንፋሳዊ ሰው ሊኖሩ ይገባል” ይላል፡፡ “ዝማሬ አርት አንደመሆኑ የሰይጣን ትኩረት ያለበት አገልግሎት ነው” ካለ በኋላ “አለም ሰይጣንም ትኩረት ያደርጉበታል ለዚህም ነው በርካታ ሙዘቀኞችና ዘማሪዎችን ያጣነው ስለዚህ ዘማሪዎች ከመዘመር ያለፈ ሕይወት ሊኖርን ይገባል” ይላል፡፡ ኬኔሳም ይህንን ሃሳብ ሲያጠናክር “እግዚአብሔርን ለማክበር እስከተዘመረ ድረስ ከቃሉ መንፈስ የጎደለ መዝሙር ነው ለማለት ይከብደኛል” ይላል፡፡ በርካቶች በአንድ ነገር ይስማማሉ ዝማሬ እግዚብሔርን አንድናስብ፣ ክርስቶን አንድናከብር፣ ንሰሀ እንድንገባ፣ አንድንጽናና፣ እድንጸልይ፣ ከሀጢአት እንድንመለስ፣ እግዚአብሔርን አንድንፈራ፣ ይቅርታ እንድንጠይቅና እንድናደርግ. . . ካላደረጉንና መዝናናት ላይ ብቻ ካተኮሩ ስጋ ስጋ የሚሸቱ፣ ጉባኤ ከማሞቅና ስሜትን ከማነቃቃት እንዲሁም ዘማሪውን ከማስተዋወቅ ያለፈ ፋይዳ የላቸውም፡፡ በዚህ ሀሳብ ላይ ዳዊት አስተያየቱን ሲሰጥ “መለኪያው ያለው እግዚአብሔር እጅ ነው” ይላል፡፡ “ለሰው አእምሮ የተመቹ ዝግተኛ ዝማሬዎችን እግዚአብሔር ላይቀበላቸው ይችላል ፤ በአንጻሩ እንደዳዊት ክብር አስጥለው የሚዘመሩ ለአእምሮ የማይመቹ የታባሉ ዝማሬዎችን ደግሞ ሊቀበላቸው ይችላል፤ ዋናው ነገር ግን እግዚአብሔርን ማክበር ነው” ይላል፡፡ እግዚአብሔርን በመፍራትና በመውደድ፣ ከመታዘዝም የመነጨ ዜማና ግጥም በትክክል እግዚአብሔርን የሚያክብር ይሆናል፡፡ “በአሁን ጊዜ ያለው የቤተ ክርስቲያን ዝማሬ ወደ አንድ ጎን አዘንብሏል ብቻ ሳይሆን ከሚገባዉ በላይ ቅጥ አንባሩ ጠፍቶታል፡፡ ለእኔ በአሁኑ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚካሄደዉ ’አምልኮ’ ተብዬው ነገር ፈረንጆቹ ’ሂፕኖቲዚም’ ወይንም እንደ ድግምት ያለ አንድን ነገር ሳያቋርጡ በመደጋገም አእምሮን ባዶ በማድረግ ማስተዋልን የሚሰርቅ፤ በተረጋጋ መንፈስና በጥሞና ከአምላክ ጋር የሚደረግ ልብ ለልብ የንስሃና የጥሞናን ጊዜ አሽቀንጥሮ የሚጥል፤ ሁካታና ግርግር የበዛበት” በማለት የሚገልጸው ዮናስ ጎርፌ ነው፡፡

እንደ ማጠቃለያ

“ኳስ ብቻ አይደለም ልምምድ የሚያስፈልገው ማንበብም ልምምድ ያስፈልገዋል በተመሳሳይ መልኩ ሰባኪ ብቻ አይደለም ማንበብ የሚያስፈልገው ዘማሪም ጭምር እንጂ ስለዚህ እናንተ ዘማሪያን የማንበብ ልምድ አዳብሩ” የሚለው ዮናስ ዘውዴ ነው፡፡ አንድ ነገር ቤተሰባዊ ወይም (familier) ስለሆነ ትክክል ነው ማለት አይደለም፡፡ መዝሙር ስለ ተዘመረ የሚዘመረውን መዝሙር እና ዘማሪውን ስላወቅነው (ቤተሰባዊ) ስለሆንን መዝሙሩ ትክክል ነው ማለት አይደለም፡፡ ዜማ ለክርስቶስ የመጡበት መንገድ እና የሚጠብቃቸው ረዥም ጉዞ ቢሆንም ያለባቸውን ተግዳሮት ተቋቁመው ለመሄድ ብርቱ ትግል ይጠብቃቸዋል፡፡ በተለይ የግል አገልግሎትና የአልበም ስራ ሕብረቱን እየጎዳው ነው፣ ከአለማዊነትም ተጠበቁ የሚለው አስተያየት እየበረከተ ነው፡፡ ሕረቱን በተመለከለተም ወጣቶቹ ጥሩ ተሰጥኦ እንዳላቸው የሚናገረው ዮናስ ጎርፌ “የግሩፑ የሙዚቃ ስራ በአንድ ሰው (በዳዊት) ዙሪያ የሚያጠነጥን ይመስለኛል፡፡ ሙዚቃውን በተመለከተ የሌሎቹ ተሳትፎ በጣም የጎላ አይመስለኝም” ይላል፡፡

ለዜማ ለክርስቶስ ዝማሬ መፍለቅ ጀምሯል ምንጩን አጎልብተው ጥርት ብሎ ይበልጥ እየፈለቀ ጥም ያረካ ይሆን? ወይስ ምንጩ ይደርቅ ይሆን? በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ከፍታ ተምዘግዝጎ የወጣውና በስኬት ጎዳና መሄድ የጀመረው አገልግሎታቸው በስጋት የተከበበ ይመስላል፤ ዛሬ አገልግሎታቸው እዚህ ደርሷል ነገስ?

ቴክኖሎጂ እና ክርስትና

ስለ ቴክኖሎጂ ሲነሣ በአብዛኛው ወደ ሰው አእምሮ አስቀድሞ የሚከሰተው የቴክኖሎጂ ፈጠራ ኮምፒውተር፣ ገመድ አልባ (ተንቀሳቃሽ) ስልክ ወይም በይነ መረብ (Internet) ነው፡፡ ነገር ግን የቴክኖሎጂ ፈጠራ ዘርፍ ብዙ ሲሆን፣ ለምሳሌ አውቶሞቢል፣ ባቡር፣ አውሮፕላን፣ ራዲዮ፣ ቴሌቭዥን፣ መገናኛ አውታሮች፣ ኅትመት እና ሌሎችም… ናቸው፡፡ ዛሬ የምንነጋገርበት ጉዳይ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች በክርስትና ላይ ያሳረፉትን እና እያሳረፉ ያሉትን በጎ ተጽዕኖ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

መሪነት:- ወሳኙ ጉዳይ

ʻመሪዎች ለሁሉም ዐይነት ተቋማዊ ችግር ፍቱን መድኃኒቶች ናቸውን?ʼ በርግጥ በአመራር ላይ ጥናት ያደረጉ ጥቂት የማይባሉ ምሁራን መሪዎችን እንዲህ ባለ መልክ አያቀርቧቸውም። እጅግ የተደነቁቱ የአመራር ዘይቤዎችም ሳይቀሩ (ለምሳሌ፡- ሎሌያዊ አመራር – “Servant Leadership” እና ተሃድሷዊ አመራር – “Transformational Leadership”) ላለንበት ተቋማዊም ሆነ አገራዊ ችግር ብቸኛ መፍትሔ እንዳይደሉ እነዚሁ ምሁራን ይስማማሉ። ይህን አቋማቸውን “Leadership is not a panacea to all our problems” በማለት ነው የሚገልጡት – መሪነት ለችግሮቻችን ሁሉ ፍቱን መድኃኒት አይደለም እንደማለት ነው። ይህ ሲባል ግን የመሪዎች ሚና እንደዋዛ የሚታይ ጉዳይ እንዳልሆነ ሊታሰብበት ይገባል።

ተጨማሪ ያንብቡ

መስቀሉ፦ ሲሞን ቬይ

የክርስቶስ ስቃይ ያለ ጥርጥር ልዕለ ተፍጥሯዊ ፍትሕ ነው። ያሉትን የርኅራኄ ርዳታ ሁሉ ፍጹም የከለከል ፍትሕ ነው፤ የእግዚአብሔር አብ ፍቅር እንኳ እንዳይራራለት ያደረገ ፍትሕ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.