[the_ad_group id=”107″]

የኢትዮጵያ ነገረ መለኮት ተቋማት ማኅበር በቲቢ ጆሽዋ ላይ ያደረገውን የዳሰሳ ጥናት አቀረበ

September 7, 2015
የኢትዮጵያ ነገረ መለኮት ተቋማት ማኅበር በቲቢ ጆሽዋ ላይ ያደረገውን የዳሰሳ ጥናት አቀረበ

በኅብረቱ ውስጥ ባሉ ቤተ እምነቶች መካከል ያለው ልዩነት መፍትሔ ያገኘ አይመስልም 

የኢትዮጵያ ነገረ መለኮት ተቋማት ማኅበር ቲቢ ጆሽዋ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ መባሉን ተከትሎ በግለ ሰቡ ሕይወት፣ አገልግሎት እና አስተምህሮ ላይ ትኩረት ያደረገ የዳሰሳ ጥናት ለአብያተ ክርስቲያናት መሪዎችና ለሚመለከታቸው ነሐሴ 19 ቀን፣ 2007 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሥነ መለኮት ድኅረ ምረቃ ት/ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ አቀረበ፡፡

ማኅበሩ ግለ ሰቡን በተመለከተ ያደረገው ዳሰሳዊ ጥናት በአነስተኛ መጽሐፍ መልክ ተዘጋጅቶ ለታዳሚያን የቀረበ ሲሆን፣ ሠነዱ እንደሚያትተው ከሆነ በቲቢ ጆሽዋ ሕይወትና አገልግሎት ጋር በተያያዘ የሚነሡ ጥያቄዎች መኖራቸው፣ በተለይም ግለ ሰቡ “ነቢይ፣ መሲሕ እና የእግዚአብሔር ሰው” ተብሎ ቢታወቅም በአገሩ ናይጄሪያም ሆነ በዓለም ዙሪያ ባሉ ክርስቲያኖች ዘንድ ነቀፌታ የሚቀርብበት መሆኑ፣ አገልግሎቱ በአገሩ ናይጄሪያ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረቶች ተቀባይነት የሌለው መሆኑ እንዲሁም ግለ ሰቡን በቅርበት እናውቀዋለን የሚሉ ሰዎች በተለያየ ጊዜ የሚያጋልጧቸው ምልክቶች መጨመራቸው ጥናቱን ለማዘጋጀት እንደ መነሻ ምክንያት ከተጠቀሱት መካከል ይገኙበታል፡፡

በአገራችንም ሆነ በተቀረው ዓለም ቲቢ ጆሽዋን በተመለከተ ያለው አመለካከት የተከፈለ በመሆኑ፣ “የሚቀርቡ መሟገቻዎች በሙሉ አሉታዊ ናቸው ብሎ መደምደም አስቸጋሪ ነው” የሚለው ሠነዱ፣ “ይህ ጥናት የመረጠው አካሄድ፣ ሰውየውንና አገልግሎቱን በሚመለከት የቱንም ያህል አሉ የሚባሉ አዎንታዊ ነገሮች ሊያስተባብሏቸው የማይችሏቸውን አሳሳቢ ነገሮች ብቻ ነቅሶ በማውጣትና በማሳየት ይህ ሰው ለአገልግሎት እንዲጋበዝ የማያበቁ በቂ ምክንያቶች መኖራቸውንና አለመኖራቸውን ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ማስገንዘብ ነው፡፡” ሲል፣ ግለ ሰቡ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት ይመለከተናል የሚሉ ወገኖች ሁሉ የግለ ሰቡን የሕይወትና የአገልግሎት ገጽታዎች በማጤን ለውሳኔ የሚያግዝ ግብአት ለማቅረብ እንደ ሆነ ይገልጻል፡፡

በሌላ መረጃ፣ ቲቢ ጆሽዋን ለማምጣት ይፋዊ ግብዣ አቅርቦ እንደ ነበረ የተነገረው የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የቦርድ አመራር መካከል የተነሣው ውጥረት እስካሁን መፍትሔ እንዳላገኘ ምንጮች ለሕንጸት ገለጹ፡፡ በኅብረቱ የሥራ አስፋጻሚ ቦርድ አመራር አካላት መካከል ልዩነት ፈጥሮ ሲያጨቃጭቅ የከረመው ይኸው ጉዳይ፣ ኅብረቱ ለቲቢ ጆሽዋ ያደረገው የግብዣ ጥሪ እንዲቋረጥ የሚፈልጉ በአንድ በኩል፣ ጥሪው እንዲዘገይ የሚፈልጉ በሌላ ወገን እንዲሁም አሁኑኑ እንደሚጣ የሚፈልጉት ደግሞ በሦስተኝነት አቋም እንደያዙ ሲነገር ነበር፡፡ በመጨረሻም፣ ኅብረቱ ቲቢ ጆሽዋን አሁን መጋበዝ እንደሌለበትና በግለ ሰቡ ላይ ለሚነሡት ጥያቄዎች ተገቢው ምላሽ በጥናት ታግዞ ሲቀርብ ውሳኔ የሚሰጥበት እንደሚሆን በአብላጫ ድምፅ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር ይላሉ ምንጮች፡፡

ይሁን እንጂ የግለ ሰቡን መምጣት በሚፈልጉ ቤተ እምነቶች ግፊት መርሓ ግብሩ ተጠናክሮ መቀጠሉን ማወቅ ተችሏል፡፡ ሕንጸት የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ዋና ጸሐፊ ከሆኑት ከቄስ ዓለሙ ሼጣ ጠይቆ እንደ ሰማው ከሆነ፣ ቲቢ ጆሽዋ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ የተያዘው ዕቅድ በትክክለኛ መንገድ ላይ እየሄደ እንዳለና ፕሮግራሙም መስከረም 8 እና 9 በአዲስ አበባ ስታዲዮም እንዲሁም መስከረም 10 እና 11 2008 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም፣ የኅብረቱ ጽ/ቤት የቤተ ክርስቲያን እና የውጪ ግንኙነት አስተባባሪ የሆኑት መጋቢ ዶ/ር ስለሺ ከበደ እንዳሉት በቲቢ ጆሽዋ የአገልግሎት ግብዣ ላይ ከአንድ ቤተ እምነት በስተቀር የኅብረቱ የቦርድ አባላት በሙሉ በጆሽዋ መምጣት እንደሚያምኑ፣ ይህንን በተመለከተም በኅብረቱ የቦርድ አመራር አባላት መካከልም ምንም ዐይነት ልዩነት እንደ ሌለ ለሕንጸት ገልጸዋል፡፡

“በቲቢ ጆሽዋ ላይ ጥያቄ ያላቸው ሰዎች እንዳሉ እናውቃለን፤ ነገር ግን ተጨባጭ የሆነ ነገር የለም” ያሉት መጋቢ ዶ/ር ስለሺ፣ አሉ የተባሉትም ከኢንተርኔት የተቀዱና አስተማማኝ የሆነ ማስረጃ የሌላቸው ናቸው ሲሉ “ከአሉባልታ በስተቀር” ይሄ ነው የሚባል ማስረጃ የሌለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም፣ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ይህንኑ ለማጣራት ወደ ናይጄሪያ ተልከው እንደ ነበረ፣ እነዚሁ ሰዎችም “ፕሮግራሙን አይተው፣ መጽሐፎቹን ቃኝተው” ከመጡ በኋላ “ቦርዱ ይሄ ነገር ይቀጥል” እንዳለ ያስረዳሉ፡፡ ውሳኔውም የአንድ ቦርድ ብቻ ሳይሆን፣ “ሁለት ነው ይህንን ነገር ያጸደቀው፡፡ እንደ ገናም የመጀመሪያው ጠቅላላ ጉባኤ ሪፖርት ተደርጎለት የተቀበለው ጉዳይ ነው፡፡” ሲሉ በቅርቡ ከተመረጠው ሥራ አስፈጻሚ በፊት የነበረው ቦርድ ግብዣውን እንዳረጋገጠው ጠቁመዋል፡፡

መጋቢ ዶ/ር ስለሺ ከበደ ይህን ይበሉ እንጂ፣ ሕንጸት የቦርዱ አባል የሆኑትን የቤተ እምነት መሪዎች አነጋግሮ እንደሰማው ከሆነ ሁሉም ቤተ እምነቶች በግለ ሰቡ መምጣት ላይ ሙሉ ስምምነት ላይ አልደረሱም፡፡ የኢትዮጵያ ጉባኤ እግዚአብሔር ቤተ ክርሰቲያን መጋቢና በኅብረቱ የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል የሆኑት መጋቢ ደረጀ ታፈሰ ለሕንጸት እንደተናገሩት በቲቢ ጆሽዋ መምጣት ላይ ቦርዱ ግማሽ ለግማሽ በሚባል የተከፈለ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ መጋቢ ስለሺ እንዳሉት ከአንድ ቤተ እምነት በስተቀር የተቃወመ የለም የሚለውም ከእውነታ የራቀ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው አስረድተዋል፡፡ በመጨረሻም ቦርዱ የደረሰበት ስምምነት፣ “ኅብረቱ ቲቢ ጆሽዋን ለመጥራት ጊዜው እንዳልሆነና በግለ ሰቡ ላይ አሉ የተባሉት ነቀፋዎች ምላሽ ሲያገኝ ምናልባት ወደፊት ሊሆን እንደሚችል” የቤተ እምነታቸውም ሆነ በቦርዱ ስምምነት ላይ የተደረሰበት አቋም መሆኑን ገልጸው፣ ግለ ሰቡን ኅብረቱ እንደጠራ ተደርጎ የሚቀርበው ትክክል አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይም አንድ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ በኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን በከፍተኛ አመራር ደረጃ ላይ ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ፣ ጉዳዩንም በቅርበት እንደሚያውቁ የሚናገሩ መጋቢ ለሕንጸት እንደገለጹት፣ የቤተ እምነታቸው አቋም ግለ ሰቡ “ይምጣም አይምጣም” እንዳልሆነ፣ ነገር ግን የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያን ኅብረት ቲቢ ጆሽዋን ለመጥራት አሁን ጊዜው እንዳልሆነ ስምምነት ላይ መደረሱን እንደሚያውቁ ተናግረዋል፡፡ “ከቶ ነገር በአንድ ግለ ሰብ ላይ ይህን ያህል ውዝግብ ውስጥ መግባት ከእኛ የማይጠበቅና የደረስንበትን ደረጃ የሚያሳይ ነው” የሚሉት መጋቢው፣ ጉዳዩን የጴንጤቆስጤ አስተምህሮ በሚቀበሉና በማይቀበሉ መካከል ያለ ልዩነት አድርገው ማቅረብ የሚፈልጉ ግለ ሰቦች “ኅብረቱን ለማፍረስ ስለሚፈልጉ ካልሆነ በቀር ጉዳዩ ከዚህ ፈጽሞ የራቀ” ነው ብለዋል፡፡

በግለ ሰቡ መምጣት ላይ ጽኑ ተቃውሞ ካላቸው ቤተ እምነቶች መካከል የኢትዮጵያ አማኑኤል ኅብረት ቤተ ክርስቲያን እና መሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ይገኙበታል፡፡ የመሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የቦርድ አመራር በቲቢ ጆሽዋ ላይ አራት መሠረታዊ ጥያቄ ያለው ሲሆን፣ ይህም የግለ ሰቡ አስተምህሮ፣ ልምምድ፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን አንድነት ከማስጠበቅ አንጻር የሚኖረው ሚና እንዲሁም ለቤተ ክርስቲያን ከሚያበረክተው ፋይዳ አንጻር ታይቶ በቤተ እምነት ደረጃ አቋም የተያዘበት መሆኑን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

እንደ ሕንጸት ምንጮች ከሆነ፣ የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ጉባኤ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፣ ፣ የኢትዮጵያ የሕይወት ብርሃን ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ አማኑኤል ኅብረት ቤተ ክርስቲያን፣ የምርጦቹ ሰባት ሺህ ቤተ ክርስቲያን እና ዘፀኣት አፖስቶሊክ ሪፎርሜሽን ቤተ ክርስቲያን የቲቢ ጆሽዋ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ላይ ጥያቄ ያላቸውና ጊዜው አይደለም የሚሉ ናቸው፡፡

ከኅብረቱ ውጪ ያሉና የቲቢ ጆሽዋን መምጣት ከማይቀበሉ ቤተ እምነቶች መካከል የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ፣ የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ብርሃነ ወንጌል መጥምቃውያን ቤተ ክርስቲያን እና ቤዛ ባብቲስት ቤተ ክርስቲያን እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል፡፡

Hintset

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Latest News

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.