[the_ad_group id=”107″]

ኅብረቱ አራት ነቢያትን “በአጋር አባልነት” ተቀበለ

September 19, 2018
ኅብረቱ አራት ነቢያትን “በአጋር አባልነት” ተቀበለ

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት፣ አራት አገልጋዮችንና የሚመሩትን ቤተ እምነቶች “አጋር አባል” (Affiliate members) ሲል በሰየመው አዲስ የአባልነት መስፈርት መሠረት፣ ዛሬ አባል ማድረጉን የኅብረቱ ፕሬዚዳንት መጋቢ ጻድቁ አብዶ ከአገልጋዮቹ ጋር በጽሕፈት ቤታቸው የመግባቢያ ሰነድ በተፈራረሙበት ወቅት ገልጿል።

አጋር አባል በመሆን ኅብረቱን የተቀላቀሉት፣ ነቢይ ኤርሚያስ ሁሴን፣ ነቢይ ሱራፌል ደምሴ፣ ነቢይ መስፍን በሹ እና አገልጋይ/ነቢይ ዮናታን አክሊሉ ናቸው። በመግባቢያ ሰነድ የፊርማ ሥነ ሥርዐት ላይ አገልጋይ/ነቢይ ዮናታን አክሊሉ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ሊገኝ አልቻለም ተብሏል።

በመግባቢያ ሰነድ ስምምነቱ ፊርማ ላይ ንግግር ያደረጉት መጋቢ ጻድቁ አብዶ፣ የኅብረቱ ጠቅላላ ጉባኤው ባዘዘው መሠረት ጉዳዩ ለአንድ ዓመት ያህል በቦርድ ደረጃ ተይዞ ሲመከርበት የቆየ መሆኑን አብራርተዋል። አገልጋዮቹ በበኩላቸው ይህንን ቀን በጉጉት ሲጠብቁ መቆየታቸውንና ለአገልግሎታቸው አጋዥ ማግኘታቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት በአስተምህሮ ዝንፈት፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባልሆኑ ልምምዶችና በሞራል ውድቀቶች ላይ መጋቢት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ባለ ዐሥር ነጥብ የአቋም መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ፣ ከስሕተታቸው ለመመለስ ፈቃደኞች ከሆኑት ጋር አብሮ ለመሥራት በተገባው ቃል መሠረት ከአራቱ አገልጋዮች ጋር በአስተምህሮ ይዘታቸው ላይ፣ በልምምዳቸውና በግል ሕይወት ዙሪያ ውይይት፣ ምክክርና ግሳጼ ሲያደርግ መቆየቱን መጋቢ ጻድቁ ተናግረዋል። ይሆንንም ተከትሎ አገልጋዮቹ፣ የኅብረቱን መሪዎች ምክርና ግሳጼ በመቀበል፣ በትክክለኛው መንገድ ለመሄድ ፈቃደኞች በመሆናቸው የመግባቢያ ሰነዱን ለመፈረም መቻሉ ነው የተገለጸው። የኅብረቱ ጽ/ቤት በየስድስት ወሩ ያሉበትን ደረጃ እየገመገመ ለቦርዱ ያቀርባልም ተብሏል።

የመግባቢያ ሰነዱ አዳዲስ ቤተ እምነቶችን በአባልነት ለመቀበል ኅብረቱ ያወጣውን መስፈርት ሊያሟሉ ያልቻሉ አብያተ ክርስቲያናትን በአጋር አባልነት ለመቀበል የተዘጋጀ ነው። በዚህም መሠረት አንድ ቤተ እምነት የኅብረቱ አጋር ሲሆን፣ ሊያሟላቸው ይገባል የተባሉ ዐሥራ ሦስት ግዴታና ኀላፊነቶች አሉ።

ከእነዚህም መካከል፣ በአስተምህሮ፣ በልምምድና በሞራል ጉዳዮች ከኅብረቱ ጋር ተመሳሳይ ወይም አንድ ዐይነት አቋም ያላቸው መሆኑ፣ የአመራር ዘይቤአቸው የአገልጋይ/ሎሌነት መርሕን የሚከተልና የሚተገብር መሆኑ፣ በአገልግሎታቸውም ሆነ በአመራራቸው ክርስቶስንና ወንጌሉን ማዕከላዊ አድርገው የሚንቀሳቀሱ መሆናቸው፣ ከኅብረቱ መሥራች ቤተ እምነቶች ጋር መልካም ግንኙነት የሚያደርጉ መሆኑ፣ ኅብረቱ ከሚቀበለው አስተምህሮም ሆነ ልምምድ እንዲሁም በተግባራው እንቅስቃሴአቸው ካፈነገጡ ተቋማት ጋር የተለየ ግንኙነት የሌላቸው መሆኑ ሲረጋገጥ፣ በጸጋ ስጦታዎች ስም የማይነግዱ ማለትም ‘የተጸለየባቸው ናቸው፤ ፈውስ ይሰጣሉ’ ብለው የተለያዩ ቁሳቁሶችን መሸጥና ሌሎች ባዕዳዊ ልምምዶችን የማይፈጽሙ መሆናቸው ሲረጋገጥ፣ ኑፋቄአዊ ተክለ ሰብእና (personality cult) የማይገነቡ ሲሆኑ፣ ያለ ኅብረቱ ዕውቅና በየትኛውም የአገሪቱ ክልሎች በኅብረቱ ስም የጀማ ስብከተ ወንጌል የማይሳተፉና ገንዘብ የማያሰባስቡ እንዲሁም በእስካሁኑ የአገልግሎት ጉዟቸው በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ላጠፉት ጥፋት በግልጽ ይቅርታ ለመጠየቅ የተዘጋጁ የሚሉት ይገኙበታል።

በአንጻሩ ኅብረቱ ለአጋር አባላቱ ከሚተገብራቸው ግዳታና ኀላፊነት መካከል፣ ለተባባሪ አባላቱ በደንቡ መሠረት የሚደረገውን ትብብርና ድጋፍ ያደርግላቸዋል፣ ሥልጠናዎችን፣ ዐውደ ጥናቶችንና ምክክሮችን ያዘጋጅላቸዋል፣ ለሕይወታቸውና ለአገልግሎታቸው ስምረት የሚችለውን በጎ አስተዋጽኦ ያደርግላቸዋል፣ እንዲሁም ግንኙነቱ በመግባቢያ ሰነዱ መሠረት በአግባቡ መፈጸሙን በየስድስት ወሩ ይገመግማል የሚሉት ተካትተውበታል።

Hintset

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Latest News

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.