[the_ad_group id=”107″]

“የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል” በይፋ ተቋቋመ

March 14, 2020
5a61d31ed794cb758475f6c89477dfed_L

“የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል” ዛሬ ቅዳሜ መጋቢት 5 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. የመሥራች ጉባኤውን አካሂዷል፤ ዋና እና ምክትል ፕሬዚዳንቱንም መርጣል። በጉባኤው ላይ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ የሚያህሉ ከቤተ እምነት እና አብያተ ክርስቲያናት ኅብረቶች የተውጣጡ ተወካዮችና ሁለት መቶ ታዛቢዎች በተገኙበት ነው ምሥረታው ይፋ የሆነው።

ከሁለት ሳምንታት በፊት አራት መቶ የሚደርሱ መሪዎች ባደረጉት የምክክር መድረክ ተቋሙን ለመመሥረት በመርሕ ደረጃ መስማማታቸውንና ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ ለዛሬ መጋቢት 5 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ መያዛቸውን ሕንጸት መዘገቡ ይታወሳል። በዚሁ መሠረትም የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ፣ የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት፣ የኢትዮጵያ ቪዥነሪ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት፣ የጴንጤቆስጤ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት እና በየትኞቹም ኅብረቶች ያልታቀፉ ቤተ እምነቶች ናቸው መሥራች ጉባኤው ላይ የተገኙትና ውሳኔውን ያሳለፉት።

ጉባኤው፣ ለካውንስሉ ፕሬዚዳንትነት ዕጩ ሆነው ከቀረቡ አራት ግለ ሰቦች መካከል የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ፕሬዚዳንት የሆኑትን ዶ/ር ኢያሱ ኤልያስን በከፍተኛ ድምፅ መርጧል። ለምክትል ፕሬዚዳንት ዕጩ ሆነው ከቀረቡት ሦስት ግለ ሰቦች መካከል የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስን በፕሬዚዳንትነት የሚያገለግሉትን ቄስ ዮናስ ይገዙን መርጧል።

በዛሬው ዕለት የተካሄደውና ታሪካዊ እንደ ሆነ የተነገረለት ጉባኤ፣ ከመሥራች ቤተ እምነቶቹና ኅብረቶች የተወከሉትንና ከአጠቃላዩ 51 የቦርድ አባላት መካከል የ49ኙን ውክልና ተቀብሎ አጽድቋል። ቦርዱ የአንድ ዓመት የአገልግሎት ዘመን የሚኖረው ሲሆን፣ የካውንስሉን ረቂቅ የውስጥ መተዳደሪያ ደንብ ላይ ማሻሻያ የማድረግና የካውንስሉን ጽሕፈት ቤት የማደራጀት ኀላፊነት ይኖረዋል ተብሏል።

ካውንስሉ በዐዋጅ የሚቋቋምበትንና በሕግ ባለሙያዎች ተዘጋጅቶ የቀረበውን ረቂቅ ሕግ በሙሉ ድምፅ ያጸደቀው ሲሆን፣ ረቂቅ ሕጉም ለሚመለከተው የመንግሥት አካል እንደሚቀርብ ተነግሯል።

ወንጌላውያንን በአንድ ጥላ ሥር በማድረግ በውስጣዊና ውጫዊ ጉዳዮቻቸው ላይ የጋራ መድረክ እንዲኖራቸው ያደርጋል፣ በሕግ ፊትም የወካይነት ሚና ይጫወታል የተባለለት ይህ ካውንስል፣ የኢፌዲሪ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰኔ 13 ቀን፥ 2011 ዓ.ም. ቁጥራቸው አራት መቶ ለሚደርሱ የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ያቀረቡትን በአንድ ጥላ ሥር የመሰባሰብ ጥሪ ተከትሎ እውን የሆነ ነው።

የአስተምህሮና የልምምድ መቀየጥን፣ የቤተ እምነት ወይም ኅብረቶች መጨፍለቅን ሊያመጣ ይችላል በሚል ጥቂት በማይባሉ አማኞች ላይ ስጋት የፈጠረውና በአንዳንዶች ዘንድም የከረረ ተቃውሞ ሲገጥመው የቆየው የካውንስሉ ምሥረት ዛሬ እውን ለመሆን የበቃው ከብዙ እልህ አስጨራሽ ጥረት በኋላ እንደ ሆነ የምክረ ሐሳብ አቅራቢ ግብረ ኀይል ሰብሳቢ የሆኑት ቄስ ደረጀ ጀምበሩ ለጉባኤተኛው ተናግረዋል።

ዐሥራ አራት አባላት ያሉት ምክረ ሐሳብ አቅራቢ ግብረ ኀይሉ ያለፉትን ዘጠኝ ወራት አማራጭ ሐሳብ ለማቅረብ ሲሠራ መቆየቱንና ቤተ እምነቶችና ኅብረቶች ተቋማዊና አስተምህሯዊ መለያቸውን ሳይለቅቁ በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ በአብሮነት የሚሠሩበት መድረክ ሊሆን እንደሚችል በዛሬ ጉባኤ ላይ በአጽንኦት ሲነገር ነበር።

በመሥራች ጉባኤው ላይ ከተነሡ አንኳር ነጥቦች መካከል፦

  • የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ሕይወት ብርሃን ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ገነት ቤተ ክርስቲያን እና የመሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት መወከላቸውን ትተው፣ በቤተ እምነት ደረጃ መሥራች ለመሆን በመጨረሻ ላይ ጥያቄ ማቅረባቸውንና ምክረ ሐሳብ አቅራቢ ግብረ ኀይሉ ውሳኔውን ለካውንስሉ የቦርድ አመራር መተዉ ተነግሯል፤
  • የካውንስሉ ቦርድ ለመሆን ለመሥራች ቤተ እምነቶችና ኅብረቶች የተሰጠው የኮታ ድልድል፦ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ እና የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን እያንዳንዳቸው ዐሥር ዐሥር የቦርድ አባላት ያቀረቡ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ዐሥራ አራት፣ የኢትዮጵያ ቪዥነሪ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ሰባት፣ የጴንጤቆስጤ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት አምስት እንዲሁም በኅብረት ያልታቀፉ ቤተ እምነቶች አምስት አባላት ልከዋል፤
  • በዛሬው መመሥረቻ ጉባኤ ላይ ድምፅ የነበራቸው መሪዎችና ተወካዮች ቁጥር በአጠቃላይ 2300 ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ እና የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን እያንዳንዳቸው 440 (በድምሩ 880) ተወካዮችን፣ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት 550፣ የኢትዮጵያ ቪዥነሪ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት 330፣ የጴንጤቆስጤ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት 220 እንዲሁም በኅብረት ያልታቀፉት ቤተ እምነቶች 220 ተወካዮችን አሳትፈዋል፤
  • ምክረ ሐሳብ አቅራቢው ግብረ ኀይል ከኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት እና ከጴንጤቆስጤ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የተጠቆሙ ሁለት ዕጩ የቦርድ አባላትን ጥያቄ ሳይቀበል በመቅረቱ ነው ከአጠቃላዩ 51 የቦርድ አባላት የ49ኙን ውክልና እንዲጸድቅ ያደረገው፤ አዲስ የተቋቋመው ቦርድ ሁለቱን ግለ ሰቦች በሚመለከት ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፤
  • ለዋና እና ምክትል ፕሬዚዳንትነት ዕጩ ሆነው ከቀረቡት አራት ግለ ሰቦች መካከል ሁለቱ ዶ/ር ቤተ መንግሥቱ እና ሐዋርያው ዮሐንስ ግርማ ሲሆኑ፣ ዶ/ር ቤተ መንግሥቱ በኅብረት ካልታቀፉ ቤተ እምነቶች የተጠቆሙ ናቸው፤ ሐዋርያው ዮሐንስ ግርማ በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት መወከላቸውን ዐጭር የማንነት መግለጫ በተነበበት ጊዜ ተጠቅሷል፤
  • የዲያስፖራ አብያተ ክርስቲያናትን ወክለው እንደመጡ የተነገረላቸውና ከአውሮፓና ሰሜን አሜሪካ አብያተ ክርስቲያናት የተውጣጡ መሪዎች በጉባኤው ላይ ተገኝተዋል፤ በወካያቸው ቄስ ቶሎሳ ጉዲና አማካኝነትም የካውንስሉን መቋቋም የሚደግፉ መሆናቸውን አሳውቀዋል፤
  • ካለፈው ሁለት ሳምንታት ወዲህ ምክረ ሐሳብ አቅራቢው ኮሚቴ የመሥራች አባልነት ጥያቄ ከተለያዩ አካላት የቀረበለት መሆኑን ተናግሯል፤ አንዳንዶቹን ከዚህ ቀደም በስም እንደማያውቃቸውና ለአዲሱ ቦርድ ጥያቄያቸውን ያስተላለፈ መሆኑም ተገልጿል፤
  • በጉባኤው መክፈቻ ላይ በቅርቡ በሁለት የአገሪቱ ክፍሎች ጥቃት ለደረሰባቸው የሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን ምእመን፣ ለኮሮና ቫይረስና ከሕዳሴ ግድባ ጋር በተያያዘ ላለው ውጥረት ጸሎት ተደርጓል።

Hintset

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Latest News

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.