[the_ad_group id=”107″]

ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትን በአንድ ጥላ ሥር የሚያሰባስብ ተቋም ለማቋቋም ከስምምነት ላይ ተደረሰ

February 29, 2020
ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትን በአንድ ጥላ ሥር የሚያሰባስብ ተቋም ለማቋቋም ከስምምነት ላይ ተደረሰ

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትን በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ ያሰባስባቸዋል የተባለለት ተቋም እንዲመሠረት ከስምምነት ላይ ተደረሰ። ዛሬ የካቲት 21 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ቁጥራቸው አራት መቶ የሚደርሱ የቤተ እምነትና የአብያተ ክርስቲያናት ኅብረት መሪዎች በተገኙበት ነው ከስምምነት ላይ የተደረሰው። ተቋሙ ከሁለት ሳምንታት በኋላ በይፋ የመሥራች ጉባኤውን ሊያካሂድ እንደሚችል ይጠበቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ሰኔ 13 ቀን፥ 2011 ዓ.ም. ቁጥራቸው አራት መቶ ለሚደርሱ የወንጌላውያን ቤተ እምነቶችና አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት መሪዎች የአንድነት ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል። ይህንኑ ተከትሎ ምክረ ሐሳብ እንዲያቀርብ የተዋቀረና ዐሥራ አምስት አባላት የነበሩት ግብረ ኀይል ላለፉት ዘጠኝ ወራት ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል። ይኸው ግብረ ኀይል ሲዘጋጅበት የቆየበትን ምክረ ሐሳብ ካቀረበ በኋላ ነው መሪዎቹ በመርሕ ደረጃ ተቋሙን ለመመሥረት ከስምምነት ላይ የደረሱት።

ሊመሠረት የሚታሰበው ተቋም ለወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት በዐዋጅ የሕግ እውቅናን የሚያጎናጽፋቸው እንደሚሆን የሕግ ባለሙያዎች ለጉባኤተኛው ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፣ ይህም የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትን አሁን በሕግ ከሚታወቁበት ከተራ የማኅበርነት ምዝገባ በዐዋጅ ወደሚደነገግ የሃይማኖት ተቋምነት የሚያሸጋግራቸው ነው ተብሏል።

በ1952ቱ የፍትሓ ብሔር ሕግ በዐዋጅ የተቋቋመችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስትሆን፣ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትን በዐዋጅ ለማቋቋም የሚንስትሮች ምክር ቤት መወሰኑና ውሳኔው ለተወካዮች ምክር ቤት መላኩ ይታወሳል።

ይመሠረታል የተባለው ተቋም በአጠቃላይ አምስት መሥራቾች የሚኖሩት ሲሆን፣ ሁለት ቤተ እምነቶችና ሦስት የአብያተ ክርስቲያናት ኅብረቶች ሊያቋቁሙት እንደሚችሉ ግብረ ኀይሉ ባቀረበው ምክረ ሐሳብ ላይ ተገልጿል። በዚህም መሠረት፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ፣ የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት፣ የኢትዮጵያ ቪዥነሪ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት እንዲሁም የኢትዮጵያ ጴንጤቆስጤ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት መሥራች አባላት እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

ይኸው ተቋም በጊዜ ሂደት አዳዲስ የሚመሠረቱና በየትኞቹም ኅብረቶች ውስጥ የሌሉ አብያተ ክርስቲያናትን ሊቀበል የሚችል ሲሆን፣ የቤተ ክርስቲያን አጋር ተቋማትን (ሚኒስትሪዎችን) በተባባሪ አባልነት የሚቀበል እንደሚሆን ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ እና የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ፕሬዚዳንቶች በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር፣ በተቋሙ መመሥረት ላይ በመርሕ ደረጃ ስምምነት እንዳላቸው ገልጸው፣ ውሳኔ ለመስጠት የቤተ እምነቶቻቸው አሠራር በሚፈቅደው መሠረት ውሳኔ አሰጥተው በዐጭር ቀናት እንደሚያሳውቁ ገልጸዋል። የሚቋቋመው ተቋም የቤተ እምነት ማንነትን የማይደፈጥጥና የአስተምህሮ መበረዝን እንዳያመጣ በተቋሙ ውስጠ ደንብ ላይ ተገቢው ጥንቃቄ መወሰድ እንዳለበትም ነው መሪዎቹ ያሳሰቡት።

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዚዳንት መጋቢ ጻድቁ አብዶ በበኩላቸው፣ እሳቸው የሚመሩት ኅብረት ከአንድ ቀን በፊት ከአባል ቤተ እምነቶቹ ጋር በጉዳዩ ላይ ምክክርና ውይይት አድርጎ ተቋሙን በኅብረት ደረጃ ለመመሥረት መወሰኑን ተናግረዋል። በተቋሙ ምሥረታ አስፈላጊነት ላይ ስምምነት እንዳለ የተናገሩት መጋቢ ጻድቁ፣ ከአስተምህሮ አንጻር ሊወሰዱ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች ችላ ሊባሉ እንደማይገባ በአጽንኦት አሳስበዋል።

በጉባኤው ከተነሡ ጉዳዮች መካከል የሚከተሉት አንኳር ነጥቦች ይገኙበታል፦

  • ግብረ ኀይሉ ለተቋሙ “መማክርት/Council” የተሰኘ ስያሜን እንደ ሐሳብ አቅርቧል፤ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ፕሬዚዳንት “ፌዴሬሽን” የሚል ስያሜ በጥቆማ አቅርበዋል።
  • በወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት የትብብር ምክረ ሐሳብ አቅራቢ ግብረ ኀይል ቁጥር ዐሥራ አምስት የነበረ ሲሆን፣ አንድ ግለ ሰብ በፈቃዳቸው ከኀላፊነታቸው መልቀቃቸው ተገልጿል።
  • ግብረ ኀይሉ ከ25 ጊዜያት በላይ ለስብሰባ ተቀምጧል፤ ከተለያዩ ቤተ እምነት መሪዎችና ኅብረቶች ጋር ምክክር ሲያደርግ ቆይቷል።
  • የምሥረታ ረቂቅ ዐዋጁን ለማዘጋጀት የሕግ ባለሙያዎች ኀላፊነት ወስደዋል።
  • ግብረ ኀይሉ የሥነ መለኮት ምሁራን ያዘጋጁለትንና ሰባት አንቀጾች ያሉት የእምነት አንቀጾች በመመሥረቻ ማቋቋሚያ ደንብ ውስጥ አካትቶ አቅርቧል።
  • ተቋሙ በአስተምህሮና ልምምድ ላይ የሚታዩ መዛነፎችን ለማረቅ ትልቅ ዕድል ሊፈጥር እንደሚችል ተገልጿል።
  • የሞራልና የሥነ ምግባር መመሪያ ያወጣል፤ በሚያፈነግጡ ቤተ እምነቶች ላይ ከአባልነት እስከ ማሰናበት የሚደርስ ቅጣት ሊጥል ይችላል ተብሏል።
  • ቁጥራቸው እስከ 2500 የሚደርሱ መሥራቾች በሚገኙበት የምሥረታ ጉባኤው ከሁለት ሳምንታት በኋላ ሊካሄድ እንደሚችል ተገልጿል።
  • የተቋሙ መሪዎችን ለመምረጥ አብያተ ክርስቲያናት ለተከታታይ ቀናት በአንድነት የጾም ጸሎት ዐዋጅ ለማድረግ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
  • ምሥረታው በሚሊኒየም አዳራሽ አማኞች በተገኙበት ለሕዝብ ይፋ ይሆናል ተብሏል።

ምስል ከሕንጸት ማኅደር

Hintset

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Latest News

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.