[the_ad_group id=”107″]

የወ/ዊ ያሬድ ጥላሁን መጽሐፍ ለንባብ በቃ

August 12, 2017
የወ/ዊ ያሬድ ጥላሁን መጽሐፍ ለንባብ በቃ

“እፎይ-ታ” የተሰኘው የወንጌላዊ ያሬድ ጥላሁን “የጥሞና ጽሑፎች” መድብል ቅዳሜ ነሐሴ፣ 7 ቀን 2009 ዓ.ም. በዘፀአት አፖስቶሊክ ሪፎርሜሽን ቤተ ክርስቲያን ቊጥራቸው ብዙ የሆኑ ታዳሚያን በተገኙበት ተመረቀ፡፡ መጽሐፉ፣ በየዕለቱ የሚነበቡ ስድሳ የጥሞና መልእክቶችን የያዘ ነው፡፡

የጎልደን ኦይል ሚኒስትሪስ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ጌቱ ግዛው ባደረጉት ንግግር፣ ወ/ዊ ያሬድ ጥላሁን ምእመናንን  ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ በሚፈለገው ደረጃ አለመተግበሩን በመረዳት፣ “ጎልደን ኦይል በመባል የሚታወቅ አገልግሎት በማቋቋም ባለፉት በርካታ ዓመታት በተለያዩ መንገዶች ደቀ መዛሙርትን በማፍራት ሥራ ላይ ተጠምዶ” እንደሚገኝ አውስተዋል፡፡ አያይዘውም፣  በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እየተጋፈጠቻቸው ላሉ ውስጣዊ ችግሮች መፍትሔ እንዲሆኑ “እግዚአብሔር በምድራችን ከፊት ለፊታችን ያሰልፋቸው ዘንድ ከጠራቸው የወንጌል አገልጋዮች አንዱ ወ/ዊ ያሬድ ጥላሁን ነው” ሲሉም ወንጌላዊው ባለፉት በርከታ ዓመታት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሰጠውን አገልግሎት ዘክረዋል፡፡

የዕለቱ የክብር እንግዳ በመሆኑ ንግግር ያደረጉት ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ሲሆኑ፣ እሳቸውም በበኩላቸው ለወንጌላዊ ያሬድ ጥላሁን ያላቸውን ፍቅርና ክብር ለመግለጥ በሚል በስፍራው እንደተገኙ ገልጸው፣ እውነተኛ የወንጌል ብርሃንን የማብራት አስፈላጊነት በተመለከተ የምክር ቃል አስተላልፈዋል፡፡ በማስከተልም ዶ/ር ማሙሻ ፈንታ የዕለቱን መልእክት አቅርበዋል፡፡ ዶ/ር ማሙሻ በመልእክታቸው ማጠቃለያ ላይም፣ ወ/ዊ ያሬድ ለስድሳ ቀናት ብቻ ሳይሆን፣ ለተቀሩትም ቀናት የሚሆኑትን የጥሞና ጽሑፎቹን መጻፍ እንዲቀጥል አበረታትዋል፡፡

ስለ መጽሐፉ ይዘትና ቅርፅ መጠነኛ ገለጻ ያደረጉት አቶ ንጉሤ ቡልቻ ነበሩ፡፡ እሳቸው እንዳሉትም፣ መጽሐፉ በይዘቱም ሆነ በቅርፁ የታለመለተን ዐላማ የሚያሳካ ሆኖ እንዳገኙት ለጉባኤው አብራርተዋል፡፡ በተለይም በዚህ ዘመን፣ ይህን መሰሉ የጥሞና መጻሕፍት እንደሚያስፈልጉ አጽንኦት በመስጠት ተናግረዋል፡፡ በማስከተል ተናጋሪ የነበረው ዶ/ር ምሕረት ደበበ ሲሆን፣ እርሱም እንደ ቀዳሚ አንባቢነቱ መጽሐፉ በይዘቱ እጅግ ጠቃሚ ሆኖ እንዳገኘው በመግለጽ፣ ወ/ዊ ያሬድ መጻፉን እንዲቀጥል አሳስቧል፡፡

በዝግጅቱ ማጠናቀቂያ ላይ፣ የ“እፎይ-ታ” መጽሐፍ ጸሐፊ የሆነው ወ/ዊ ያሬድ ጥላሁን ከሚኖርበት አሜሪካን አገር ሆኖ በቪዲዮ የላከው መልእክት ቀርቧል፡፡ “በአገልግሎት ምክንያት ከአገር በመራቄ በመካከላችሁ ልገኝ አልቻልኩም” ያለው ወ/ዊ ያሬድ፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት ያለመታከት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን በአገር ቤትና በመላው ዓለም በመዘዋወር ማገልገሉን አስታውሷል፡፡ አያይዞም፣ ጎልደን ኦይል ሚኒስትሪስ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በአሜሪካን አገር ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ሆኖ መመዝገቡን በመጠቆም፣ እርሱም ሆነ ሚኒስትሪው በመጪዎቹ ዘመናት ይህንኑ አገልግሎታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጿል፡፡ አሁን መኖሪያውን ባደረገበት ሰሜን አሜሪካ እርሱና ቤተ ሰቡ “የሃይማኖት ቪዛ” (R-1) የተሰኘውን የቪዛ ዐይነት አገኝተው በማገልገል ላይ እንደሚገኙ ተናግሯል፡፡

ጸሐፊው ከዚህ ቀደም፣ “አምልኮ”፣ “እግዚአብሔርን መምሰል” እና “ታላቅ ርስት” የተሰኙ ሦስት መጻሕፍት ለንባብ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ “እፎይ-ታ፡- የጥሞና ጽሑፎች” 127 ገጾች ያሉትና ሲሆን፣ በአገር ውስጥ በ50 ብር፣ በውጪ ደግሞ በ14፡99 የአሜሪካን ዶላር ለሽያጭ የቀረበ መጽሐፍ ነው፡፡

Hintset

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Latest News

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.