የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ተማሪዎችና ምሩቃን ማኅበር (ኢቫሱ) አምስተኛውን የክርስቶስ ልዕቀት ጉባኤ ላለፉት ሦስት ቀናት በቤዛ ኢንተርናሽናል ቤተ ክርስቲያን መሰብሰቢያ አዳራሽ ሲያካሂድ ቆይቷል።
ከመጋቢት 6 – 8፥ 2011 ዓ.ም. በተካሄደው በዚሁ ዓመታዊ ጉባኤው ላይ እስከ ሁለት ሺህ የሚደርሱ ተማሪዎች እንደተገኙ ከማኅበሩ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል። ተማሪዎቹ በአዲስ አበባ፣ አምቦ፣ ወልቂጤ፣ ፍቼ፣ ደብረ ብርሃን፣ አዳማ፣ አሰላ እና ወሊሶ ውስጥ ካሉ የመንግሥትና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመጡ ናቸው ተብሏል።
የዘንድሮው ጉባኤ መሪ ጥቅስ “ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” (የሐዋርያት ሥራ 1፥8) ሲሆን፣ በሦስቱ ቀናት ለተማሪዎቹ ይቀርቡ የነበሩ መልእክቶችና ትምህርቶችም በዚሁ ጭብጥ የተቃኙ ነበሩ። ኢቫሱ በመላ አገሪቱ እስከ አምሳ ሺህ የሚደርሱ የወንጌል አማኝ ተማሪዎችን የሚያስተባብር ማኅበር ሲሆን፣ በአፍሪካ ውስጥ ካሉ የተማሪ አገልግሎቶች ውስጥ ትልቁ እንደ ሆነም ይነገርለታል።