ሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር፣ ለዕይታ የሚያቀርባቸው የቪዲዮ ዝግጅቶቹ በኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን አዘጋጅነት በሚቀርበውና፣ በቅርቡ መደበኛ ሥርጭቱን በጀመረው የሕይወት ቲቪ ላይ እንዲተላለፍ የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጋር አደረገ።
የመግባቢያ ስምምነቱን የተፈራረሙት፣ የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ስምዖን ሙላት እና የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር ዳይሬክተር አቶ ሚክያስ በላይ ሲሆኑ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ የሚዲያ አገልግሎት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዳግማዊ ውቤ እና የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ዘላለም አበበ ተግኝተው የምስክርነት ፊርማቸውን አኑረዋል።
ስምምነቱ ሕይወት ቲቪ፣ የሕንጸትን የቪዲዮ ዝግጅቶችና በድረ ገጹ ላይ የወጡ ጽሑፎችን ለቴሌቪዥን ዝግጅቶቹ ግብዓት አድርጎ መጠቀም የሚያስችለው እንደ ሆነ በስምምነቱ ላይ ተገልጿል።
በቤተ ክርስቲያኒቱ ዋና ጽሕፈት ቤት በተደረገው የስምምነት ሥነ ሥርዐት ላይ የተገኙትና ቤተ ክርስቲያኒቱን ወክለው ስምምነቱን የፈረሙት ዶ/ር ስምዖን፣ ሕንጸት ለዕይታ የሚያቀርባቸው ዝግጅቶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ደርዛቸውንና የዝግጅት ደረጃቸውን የጠበቁ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ለቅዱሳን መታነጽ አስተዋጽዖ የሚያደርጉ መሆናቸውን አውስተዋል።
የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር ዳይሬክተር የሆነቱ አቶ ሚክያስ በላይ በበኩላቸው፣ ሕንጸት ከሕይወት ቲቪ ጋር በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ መደረሱ እንዳስደሰታቸው በመጠቀስ፣ በአጋርነት ለማገልገል ስለተገኘው ዕድል የቤተ ክርስቲያኒቱን አመራር አመስግነዋል።
ሕይወት ቲቪ፣ ከየካቲት 6 ቀን፥ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ መደበኛ ሥርጭቱን፣ በ11105 ፍሪኩዌንሲ፣ 45000 ሲምቦልሬት፣ ሆሪዞንታል ፖላራይዜሽን የጀመረ የ24 ሰዓት የቴሌቪዥን አገልግሎት ነው።
2 comments
እጅግ በጣም ደስ ይላል በቀጣይኘት እንከታተላለን
Good