[the_ad_group id=”107″]

እስራኤል ዳንሳ ሐሰተኛ ነቢይ ተባለ

October 9, 2017
እስራኤል ዳንሳ ሐሰተኛ ነቢይ ተባለ

ኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዚዳንት ዓርብ መስከረም 26 ቀን፣ 2010 ዓ.ም. በጽ/ቤታቸው ጋዜጠኞችን ጠርተው እስራኤል ዳንሳ ሐሰተኛ ነቢይ መሆኑን በይፋ ተናገሩ፡፡ ግለ ሰቡ በተለያዩ ጊዜያት የተናገራቸው ትንቢቶች አለመፈጸማቸው ብቻ ሳይሆን፣ ትንቢቶቹ በእግዚአብሔር ቃል ሲመዘኑም ስሕተት መሆናቸውን ጭምር ነው መጋቢ ጻድቁ አብዶ የተናገሩት፡፡

በዕለቱ ለጋዜጠኞች የተበተነው መግለጫ እንደሚለው ከሆነ፣ “እስራኤል ዳንሳ፣ 2009 ዓ.ም. ከመጠናቀቁ አስቀድሞ” ይፈጸማሉ ብሎ የተነበያቸው ትንቢቶች በተባለው ጊዜ አለመፈጸማቸውን ያወሳል፡፡ እነዚህም፡- “የኢትዮጵያ ሥርዐት ነቢይ በሚያወጣው ቃል ይቀጥላል፣ የፓርላማ አባላትና ነቢያት በጋራ ሕግ ያረቅቃሉ፣ የእነዚህ ተግባራት ክንውኖች በመንግሥት ቴሌቪዥን ለሕዝብ ይተላለፋል፣ የሚጠለፉ አውሮፕላኖች አሉ፣ በአገር ደረጃ የነቢያቶችና የሐዋሪያት ስብሰባ ይደረጋል፣ ከሕገ መንግሥቱ የሚሻር አንቀጽ መኖሩ፣ በ2009 ዓ.ም. ከመጠናቀቁ አስቀድሞ እነዚህ ትንቢቶች ፍጻሜ ያገኛሉ፣ ትንቢቶቹ ተፈጻሚነት ካላገኙ እስራኤል ዳንሳ (አገልግሎት/ነቢይነት) ይለቅቃል” ሲል የተናገራቸው እንደ ሆነ ጠቅሷል፡፡ አያይዞም፣ “በወርኀ ሚያዝያ 2009 ዓ.ም. በተነበየው ትንቢት 2009 ዓ.ም. ከመጠናቀቁ በፊት መጋቢ በቀለ ወ/ኪዳን 13 ታላላቅ ነቢያትን በሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ ውስጥ ይቀባል ሲል ተንብዮአል፤ ይሁን እንጂ ያ ትንቢት እንዳልተፈጸመ ይታወቃል” ሲል እነዚህ ሁሉ በእግዚአብሔር ስም በድፍረት የተነገሩ የሐሰት ትንቢቶች መሆናቸውን መግለጫው አስረድቷል፡፡

ግለ ሰቡ በአሁኑ ሰዓት በሰሜን አሜሪካ “በአገልግሎት” ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የአገልግሎት ጥሪ ያደረጉለትም በዚያ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት መሆናቸው ተነግሯል፡፡

ሙሉ መግለጫውን ከዚህ በታች ይመልከቱ፡-

ሐሰተኛ ነቢያትንና ሐዋሪያትን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት 32ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ፣ በአስተምህሮ ዝንፈቶች፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረትን በለቀቁ ልምምዶችና በሞራል ውድቀቶች ዙሪያ እየታዩ ያሉ ክፍተቶችን አጢኖና አገናዝቦ የወንጌላውያንን ማንነት የሚገልጸውን፣ እንዲሁም ወንጌላውያን አማኞችን ወንጌላውያን ያሰኛቸውንና በርቱዕ የክርስትና እምነት ውስጥ ተቀባይነት ያላቸውን ትምህርቶች በማስተንተን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አቋሙን በግልጽ ማስቀመጡ ይታወቃል፡፡

በዚህም አስተምህሮአዊ የሆኑ ዝንፈቶችን በተመለከተ እውነተኛውን አስተምህሮ ገልጦ በማሳየት፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ልምምዶችንና የሞራል ውድቀቶችንም በተመለከተ በየጊዜው እየተከታተለ የእርምት እርምጃ በመውሰድ የእግዚአብሔር ሕዝብ የበግ ለምድ ከለበሱ ተኩላዎች እንዲጠነቀቅ ማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

አሁንም ቢሆን በሰማይና በምድር ፈጣሪ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም በድፍረት የተተነበዩና ተፈጻሚነት ያጡ ሐሰተኛ ትንቢቶች በየቦታው እየተነገሩ እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ሰምተንማል፡፡ እነዚህ የሰዎችን ምድራዊ ምኞትና የልብ ሐሳብ ይዘው በአደባባይ በጌታ ስም የሚነገሩ ትንቢቶች በሌሎች አስተሳሰብ በወንጌላውያን አማኞች የሚፈጸሙ ተግባራት ተደርገው ቢቆጠሩም፣ ከእግዚአብሔር ሳይሆን ከሰዎች ልብ ፈልቀው የተነገሩ እነዚህ መልእክቶች በልምምድም ሆነ በተግባር የወንጌላውያን አማኞችን ማንነት የማያመለክቱ እንደ ሆነ ማሳወቅ ግድ ይሆናል፡፡

ያም ስለሆነ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት፣ በወንጌላውያን አማኞች ስም የሚካሄዱ ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶችን፣ የሐሰት ትንቢቶችን፣ በተግባር እየተፈጸሙ ያሉ ሃጢአቶችን እየተለማመዱ ያሉ አገልጋይ ነን ባዮችን ነቅሶ በማውጣት ለምዕመናን አስፈላጊውን መረጃ ሲሰጥ ቆይቷል፤ መስጠቱንም ይቀጥላል፡፡ ከዚሁ ጋርም በወንጌላውያን ምዕመናን ላይ በመንጠላጠል በስመ እግዚአብሔር የልባቸውን ምኞች የሚተነብዩ ሐሰተኛ ነቢያትና የክርስቶስ ወንጌልን በንዋይ የለወጡ አገልጋይ ተብዬ ምንደኞች ላይ ያለውን አቋም በተከታታይ ያሳውቃል፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ በኦሪት ዘዳግም 13÷1-5 “በመካከልህም ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ ቢነሳ፣ ምልክትም ተዓምራትም ቢሰጥህ፣ እንደነገረህም ምልክቱ ተዓምራቱ ቢፈጸም፣ እርሱም ሄደን የማታውቃቸውን ሌሎች አማልክት እንከተል እናምልካቸውም ቢልህ. . .የዚያን ነቢይ ቃል ወይም ያንን አላሚ አትስማ. . . ከአምላካችሁ ከእግዚአብሔር ሊያስታችሁ ተናግሯልና ያ ነቢይ ወይም ያ ህልም አላሚ ይገደል” በማለት ብርቱ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፡፡ እንደዚሁም፣ በኦሪት ዘዳግም 18÷20፣ “ነገር ግን ይናገር ዘንድ ያላዘዝኩትን በስሜ በድፍረት የሚናገር ወይም በሌላ አማልክት ስም የሚናገር ነቢይ እርሱ ይገደል፡፡ በልብህም፣ እግዚአብሔር ያልተናገረውን ቃል እናውቅ ዘንድ እንዴት ይቻለናል? ብትል ነቢዩም በእግዚአብሔር ስም በተናገረ ጊዜ የተናገረው ነገር ባይሆን፣ ባይመጣም፣ ያ ነገር እግዚአብሔር ያልተናገረው ነው፤ ነቢዩ በድፍረቱ ተናግሯልና እርሱን አትፍራው፡፡” ሲል በእግዚአብሔር ስም ተነግረው ባልተፈጸሙ ትንቢቶች ላይ የተነበዩትን ነቢያት የሚገስጽበትን መሥመር አመላክቷል፡፡ ነቢዩ ኤርምያስ፣ “የምታስደንቅና የምታስደነግጥ ነገር በምድር ላይ ሆናለች ነቢያት በሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፣ ካህናትም በእነዚህ እጅ ይገዛሉ፣ ሕዝቤም እንዲህ ያለውን ነገር ይወዳል” ብሎ በትንቢቱ ሲገልጥ፣ በሌላኛው ክፍልም፣ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ ትንቢት የሚናገሩላችሁን የነቢያትን ቃል አትስሙ ከንቱነትን ያስተምሯችኋል ከእግዚአብሔር አፍ ሳይሆን ከገዛ ልባቸው የወጣውን ራዕይ ይናገራሉ. . . በምክሬ ግን ቢቆሙ ኖሮ፣ ለሕዝቤ ቃሌን ባሰሙ ነበር” (ትንቢተ ኤርሚያስ 23÷16፡22) በማለት እንደዛሬው ጊዜ የልብ ሐሳብ የነገሠበትና ይህም የልብ መሻት በትንቢት መልክ ገሃድ የወጣበት ክፉ ጊዜ እንደ ነበር ያሳየናል፡፡

በሌሎችም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም መንፈሳቸውን ስለሚከተሉ፣ በንዋይ ማልለው ሕዝቡን ስለሚበዘብዙና የሰዎችን ቤት ባዶ ስለሚያስቀሩ ነቢያት በፍርድ ቃል የተነገሩ ክፍሎችም እንዲህ ተጽፈዋል፡፡

 • ምንም ሳያዩ የገዛ መንፈሳቸውን ለሚከተሉ ለሰነፎች ነቢያት ወዮላቸው፤ ት.ሕዝ. 13÷3፣4፣6-9
 • እስራኤል ሆይ ነቢያትህ በምድረበዳ እንደሚኖሩ ቀበሮዎች ናቸው፤ ት.ሕዝ. 13÷4
 • እጄም ከንቱ ራዕይን በሚያዩ፣ በውሸትም በሚያሟርቱ ነቢያት ላይ ትሆናለች÷
 • በውስጧ ያሉ ነቢያት እንደሚጮህና እንደሚናጠቅ አንበሳ አንድ ሆነው ተማማሉ፣ ነፍሶችን በልተዋል፣ ብልጥግናና ሐብትን ወስደዋል፣ በውስጧም መበለቶችን አብዝተዋል፤ ሕዝ. 22÷25
 • እግዚአብሔር ሕዝቡን ስለሚያስቱ ነቢያት እንዲህ ይላል፣ በጥርሳቸው ሲነክሱ በሰላም ይሰብካሉ፣ በአፋቸው ግን አንዳች በማይሰጥ ሰው ላይ ሰልፍን ያስቡበታል፤ ሚክ. 3÷5
 • ስለዚህ ሌሊት ይሆንባቸዋል እንጂ ራዕይ አይሆንላቸውም፤ ጨለማም ይሆንባችኋል እንጂ አታሟርቱም፤ ፀሐይም በነቢያት ላይ ትገባለች፣ ቀኑም ይጠቁርባቸዋል፡፡ ሚክ.3÷6

ስለሆነም በመካከላችን ተንሰራፍተው የልባቸውን ሽንገላ እና የግል ምኞታቸውን ፈቃድ በእግዚአብሔር ስም አስታከው የሚናገሩ ነቢይ ተብዬዎችን በቸልታና በግድ የለሽነት ማየት የእግዚአብሔር ሕዝብ በስሕተት ውስጥ እንዲዘፈቅና አቅጣጫ ስቶ መረን እንዲወጣ ማድረግ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት በወንጌላውያን ምዕመናን መካከል ተንሰራፍተው በሚገኙ ሐሰተኛ ነቢያትና ሐሰተኛ አስተማሪዎች ላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አቋሙን ይፋ ማደረጉ ተገቢም ግድም ሆኗል፡፡

ያም በመሆኑ ኅብረቱ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሁኔታዎችን በማጤን እስራኤል ዳንሳ፣ 2009 ዓ.ም. ከመጠናቀቁ አስቀድሞ በወንጌላውያን አማኞች ዘንድ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም ድፍረት በተሞላበት አካሄድ የተነበያቸውንና በትንቢቱ ስሌት መሠረትም ያልተፈጸሙ ትንቢቶችን አጠቃላይ መልክ እንዲህ ነቅሷቸዋል፡፡

 1. የኢትዮጵያ ሥርዐት ነቢይ በሚያወጣው ቃል ይቀጥላል፣
 2. የፓርላማ አባላትና ነቢያት በጋራ ሕግ ያረቃሉ፣
 3. የእነዚህ ተግባራት ክንውኖች በመንግሥት ቴሌቪዥን ለሕዝብ ይተላለፋል፣
 4. የሚጠለፉ አውሮፕላኖች አሉ፣
 5. በአገር ደረጃ የነቢያቶችና የሐዋሪያት ስብሰባ ይደረጋል፣
 6. ከሕገ መንግሥቱ (?) የሚሻር አንቀጽ መኖሩ፣
 7. በ2009 ዓ.ም. ከመጠናቀቁ አስቀድሞ እነዚህ ትንቢቶች ፍጻሜ ያገኛሉ፣
 8. ትንቢቶቹ ተፈጻሚነት ካላገኙ እስራኤል ዳንሳ (አገልግሎት? ነቢይነት?) ይለቃል፣
 9. ከነዚህ ትንቢቶች አስቀድሞ በወርኀ ሚያዝያ 2009 ዓ.ም. በተነበየው ትንቢት 2009 ዓ.ም. ከመጠናቀቁ በፊት መጋቢ በቀለ ወ/ኪዳን 13 ታላላቅ ነቢያትን በሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ ውስጥ ይቀባል ሲል ተንብዮአል፤ ይሁን እንጂ ያ ትንቢት እንዳልተፈጸመ ይታወቃል፣
 10. በቁጥር 4 የሆኑ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የተጭበረበሩበትን መረጃ በማኅበራዊ ሚዲያ ማጋለጣቸውና ሌሎችም መሰል ማጭበርበሮች እንዲሁም ዝርፊያዎች በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም በድፍረት ተፈጽመዋል፡፡

እነዚህ ትንቢቶች በሕዝቡ ዘንድ በሰፊው የታወቁ፣ በማኅበራዊ ሚዲያም ብዙ የተባለላቸው፣ እንደተባለላቸውም በዕለተ ቀኑ አለመፈጸማቸው በይፋ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ እስራኤል ዳንሳ ከዚያ ቀደም ሲልም ያልተፈጸሙ ትንቢቶችን በተለያየ ስፍራ መናገሩ ምስጢር አይደለም፡፡ እነዚህ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም በድፍረት የተነገሩ የስሕተት ትንቢቶች ተደጋግመው መሰማትና ሰውየው ያከናወናቸው የማስመሰያና የማታለያ ስልቶች ተደማምረው እስራኤል ዳንሳ ሐሰተኛ ነቢይ ለመሆኑ ተጨማሪ ዋቢ ሳይጠራ ብቻቸውን ምስክር ይሆናሉ፡፡

ከዚህ በመነሣሳት የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት፣ በወንጌላውያን አማኞች መካከል እየተዘዋወረ ሕዝቡን በማሳት ላይ የሚገኘውን እስራኤል ዳንሳን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ባስቀመጠው መስፈርት መሠረት ሐሰተኛ ነቢይ ሆኖ አግኝቶታል፤ ከዚህ የተነሳ እስራኤል ዳንሳ፣ በማናቸውም የወንጌላውያን አማኞች ጉባዔ ላይ ለአገልግሎት እንዳይጠራ ወስኗል፡፡ ይሁን እንጂ እስራኤል ዳንሳ በደሉንና ጥፋቱን አውቆ በይፋ በንሰሐ በመመለስ መንገዱን የሚያስተካክል ከሆነ ኅብረቱ ይህንኑ በግልጽ የሚያስታውቅ ይሆናል፡፡

በንሰሐ የመመለስ መንገድ ውስጥ መናዘዝ አንዱ ገጽታ እንጂ የንስሐው ሙሉ አካል ባለመሆኑ ከእውነተኛ ንስሐ ርቱዕ የሆነ የንሰሐ ፍሬ ይጠበቃል፡፡ ስለሆነም፣ ንሰሐ የሚያስፈልጋቸውና በስህተት ጎዳና ያሉ በደለኞች፣ በደሉን ለማድረስ ምክንያት ከሆኑአቸው ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮዎችና ልምምዶች፣ እንዲሁም የእግዚአብሔርን ሕዝብ ካስነወሩበትና ከበዘበዙበት ኢ-ሥነምግባራዊ ድርጊቶች ሊመለሱ ይህንንም በግብር ሊያሳዩና ሊገልጡ ይገባቸዋል፡፡

ያም ሆኖ አንዳንዶች ንሰሐ ገባን በሚል አስባብ፣ የንስሐ ፍሬ በሌለበት መንገድ መጓዝን ሥራዬ ብለው መያዛቸው ከበደሉ ጋር ተስማምተው መሄድን እንደመረጡ የሚያሳይ ስለሆነ ወንጌላውያን አማኞች ይህን የስህተት አካሄድ ልንቀበልም ሆነ በሕዝባችን ላይ እንዲሰለጥን ልንፈቅድ አይገባም፤ በመሆኑም በወንጌላውያን አማኞች ሽፋን ሕዝቡን ከጽድቅ መስመር ለማውጣት የሚሯሯጡ ነቢያትና ሐዋሪያት ተብዬዎችን ከደረሰን መረጃና ማስረጃ እየጠቀስን ለሕዝባችን በተከታታይ የምንገልጥ መሆኑን እናሳውቃለን፡፡

ጻድቁ አብዶ (ፓስተር)

የኢወአክኅ ፕሬዚዳንት

Hintset

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Latest News

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.