[the_ad_group id=”107″]

በወጣቱ ዙሪያ ባሉ ተግዳሮቶች ላይ ውይይት ተካሄደ

February 2, 2016

“ለአገርና ለቤተ ክርስቲያን ተረካቢ ትውልድ ማዘጋጀት” በሚል መሪ ቃል አልቃሽ ሴቶች የምልጃ አገልግሎት በኢትዮጵያ ጥር 22 ቀን፣ 2008 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሥነ መለኮት ድኅረ ምረቃ ት/ቤት (EGST) የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለክርስቲያን መምህራንና የትምህርት ባለ ሙያዎች የውይይትና የምክክር መድረክ አዘጋጀ፡፡ የመድረኩ ዋነኛ ትኩረት በወጣቶች ዙሪያ፣ በተለይም በትምህርቱ ዓለምና በተማሪዎች ዙሪያ ያሉ የተለያዩ ተግዳሮቶችን፣ ክፉ ልምምዶችንና ከጀርባቸው ያሉ አመለካከቶችን አስመልክቶ ለክርስቲያን መምህራንና ለትምህርት ባለ ሙያዎች ግንዛቤ ማስጨበጥ እንደ ሆነ በዕለቱ ተገልጿል፡፡

አገልግሎቱ ይህንን መድረክ ሲያዘጋጅ ዐላማው ትውልድን በመልካም ሞራል ለማነጽና የመፍትሔ ሐሳቦችን መምህራኑና የትምህርት ባለ ሙያዎች በቅረበት እንዲመካከሩና እርስ በእርስ የሚያያዙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እንደ ሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በምክክር መድረኩ ተናጋሪዎች የነበሩት መጋቢ አቢ እምሻው እና ዶ/ር ስዩም አንቶንዮስ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባቸዋል ባልዋቸው ጉዳዮች ላይ ሐሳባቸውን አካፍለዋል፡፡ መጋቢ አቢ በሠለጠኑ ዓለማት እኩይ የሆኑና ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጪ የሆኑ ፅንሰ ሐሳቦች በመደበኛውም ሆነ መደበኛ ባልሆነው የትምህርት ሥርዐት ውስጥ በመግባት ትውልዱን ከእውነት መንገድ በማሳት ጉዳት እያደረሱ እንደሆነና በእኛም አገር ሙከራዎች እንዳሉ በማስገንዘብ ተሳታፊዎች ትኩረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

ዶ/ር ስዩም አንቶንዮስ በበኩላቸው ትውልዱን ለማሳት “ሰይጣን የሚጠቀምባቸው ዘዴዎች” ያሉዋቸውን ነጥቦች አስቀምጠዋል፡፡ ቅድመ ጋብቻ ወሲብ፣ ወሲባዊ ርኩሰትን የሚያስፋፉ ቀስቃሽ ምሰሎች (Pornogarphy)፣ ሴጋ (masturbation)፣ ውርጃና ግብረ ሰዶማዊነት ትውልድን ለማታተል የተዘጋጁ ሰይጣናዊ ዘዴዎች ካሏቸው መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ አክለውም፣ “የሥራ ቦታዎቻችን ለእንጀራችን ብቻ የምንሠራባቸው ሳይሆን፣ የአገልግሎት መስኮቻችን (mission fields) ናቸው፤ ክርስቲያናዊ ኀላፊነትና ኑሮ በምንገኝበት ሁሉ ነው” በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በመጨረሻም፣ በቀረቡት የውይይት መነሻ ሐሳቦችም ላይ ውይይት ተካሄዷል፡፡

Latest News

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.