በተገኝ ሙሉጌታ የተጻፈውና “የእግዚአብሔር ክርስቶስ?” የተሰኘው መጽሐፍ ባለፈው ቅዳሜ ጥቅምት 15 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሥነ መለኮት ድኅረ ምረቃ ት/ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተመረቀ።
መጽሐፉ ነገረ ክርስቶስን ጭብጡ ያደረገ ሲሆን፣ በክርስቶስ ማንነት ላይ በተለያዩ ዘመናት የተነሡ ሐሳቦችን በስፋት ያስቃኛል። በስድስት ክፍሎች የተከፈለው ይህ መጽሐፍ መነሻ ሐሳብ፣ መግቢያና መንደርደሪያን ሳይጨምር 192 ገጾች ያሉት ነው። “የእግዚአብሔር ክርስቶስ?፦ የነገረ ክርስቶስ ምልከታ በቅድመ ዘመናዊነት፣ በተሃድሶ፣ በዘመናዊነት እና በአሁኑ ዘመን” የተሰኘው ይህ አዲስ መጽሐፍ፣አንባቢያን በርእሰ ጉዳዩ ላይ ያላቸውን ግንዛቤ በእጅጉ የሚያሳድጉበት እንደ ሆነ በቀዳሚ አንባቢያን ተነግሮለታል።
ተገኝ ሙሉጌታ ከዚህ ቀደም “የሕይወት ጸጋ እና ‘ቀጋ’ ” የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ ማቅረቡ የሚታወስ ነው። አዲሱ “የእግዚአብሔር ክርስቶስ?” የተሰኘው ሥራው በ150 ብር ለሽያጭ ቀርቧል።