[the_ad_group id=”107″]

የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ምክረ ሐሳብ አቅራቢ ኮሚቴ የሥራ ሂደት መግለጫ ሰጠ

September 10, 2019
የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ምክረ ሐሳብ አቅራቢ ኮሚቴ የሥራ ሂደት መግለጫ ሰጠ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ ሰኔ 13 ቀን፥ 2011 ዓ.ም. ቁጥራቸው አራት መቶ ለሚጠጋ የወንጌላውያን (ፕሮቴስታንት) አማኞች አብያተ ክርስቲያናት መሪዎችና አገልጋዮች በጽሕፈት ቤታቸው ጠርተው ያደረጉትን ስብሰባ ተከትሎ፣ አብያተ ክርስቲያናቱን በአንድ ጥላ ሥር ለማሰባሰብ የሚያስችል ምክረ ሐሳብ የሚያቀርብ ዐሥራ አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴ መዋቀሩ ይታወሳል። ይኸው ኮሚቴ ዛሬ ጷጉሜ 5 ቀን፥ 2011 ዓ.ም. ረፋዱ ላይ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫው ባለፉት ወራት ኮሚቴው ሠርቻቸዋለሁ ያላቸውን ሥራዎች ለአማኝ ማኅበረ ሰቡ ለማሳወቅ በሚል የተሰጠ እንደ ሆነ ተጠቁሟል።

ኮሚቴውን ወክለው መግለጫውን የሰጡትና ከጋዜጠኞች ለተነሡ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የኮሚቴው አባላት ቄስ ደረጀ ጀምበሩ፣ አቶ ንጉሤ ቡልቻ እና መጋቢ ስንሸት ተካ ናቸው። በጽሑፍ የተነበበው መግለጫ እንደሚያመለክተው፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት የተካሄደው ስብሰባ፣ “ስብጥሩ ብዙ፤ አጠራሩም ድንገት ከመሆኑ የተነሣ አብዛኛው የውይይት ጉዳይ ልዩ ልዩ መልክ ያለው ነበር” ሲል ያስታውሳል። የሦስት ወር ዕድሜ የተሰጠው የምክረ ሐሳብ አቅራቢ ኮሚቴ፣ ከሁለት ወራት በላይ በፈጀው ቆይታው፣ ኀላፊነቱን መለየትና የሥራ ስልት መቀየስ ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሠራ እንደቆየ ተነግሯል።

በቅድሚያ “በፆምና በጸሎት ጉዳዩን ወደ እግዚአብሔር” ማቅረቡን የገለጸው የኮሚቴው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊቷ ቤተ ክርስቲያን “በብዙ ረገድ በሞራል፣ በእምነት፣ በኅብረት በመሳሰሉት የሚጠበቅባትን እንዳልተወጣች ይልቁንም በብርቱ ሕመም ላይ እንዳለች” በመቀበል መድኃኒት እንደሚያስፈልጋት መተማመን ላይ ደርሻለሁ ብሏል።

ይህም ብቻ ሳይሆን፣ “የተበታተነ ገጽታ ያላቸው የወንጌላውያን አማኞች አብያተ ክርስቲያናትን … በአንድ የተባበረ ጥላ ሥር ሆነው … መብታቸውንና ግዴታቸውን በተገቢው መንገድ እንዲወጡ መንገድ መፈለግ” የኮሚቴው ኀላፊነት መሆኑን መገንዘቡን መግለጫው ያስረዳል። ይህንኑ ኀላፊነት ለመወጣትም ዐሥር ንዑስ ኮሚቴዎችን በማዋቀር ሥራውን እንደ ጀመረ ተጠቁሟል።

የጸሎት አስተባባሪ ቡድን፣ ልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናትንና ኅብረቶችን የሚያነጋግርና አስተያየት የሚሰበስብ ቡድን፣ መሠረታውያን የሆኑትን የወንጌላውያን አማኞች የእምነት አቋም አጥንቶ የሚያቀርብ የነገረ መለኮት ንዑስ ቡድን፣ ሕግንና ደንብን የሚመለከቱ ጉዳዮች ተወያይቶ በስምምነት ሊዋቀር የሚችል የኅብረት ወይም የጋራ መድረክ ምክረ ሐሳብ ንዑስ ቡድን፣ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን፣ የቤተ ክርስቲያን አጋዥ ድርጅቶችን አስተያየት ሰብሳቢ፣ የገንዘብ አሰባሳቢ፣ ዝግጅትና ፕሮግራሞች አቀናባሪ፣ ከኢትዮጵያ ውጭ ባሉ ወንጌል አማኞች ጋር ግንኙነት አስተባባሪና ምክረ ሐሳብ አጠናቃሪ ኮሚቴው አዋቅሬአቸዋለሁ ያላቸው ዐሥሩ ንዑሳን ቡድኖች ናቸው።

ምክረ ሐሳብ አቅራቢ ኮሚቴው እስከ አሁን ሠራኋቸው ያላቸው ተግባራት፣ የተለያዩ ቤተ እምነቶች እና ኅብረቶች መሪዎችን ማነጋገር፣ የነገረ መለኮት ምሁራን የተሳተፉበት የወንጌል አማኞች አዕማድ እምነቶች መግለጫ ማዘጋጀት፣ በሁሉም አካላት ስምምነት ሊያሰባስብ የሚችል አንድ አካል ለማዋቀር አማራጭ የአወቃቀር ሞዴሎችን የሚያሳይ ሕጋዊ ንድፍ ማዘጋጀት፣ የቤተ ክርስቲያን አጋዥ ድርጅቶች ከአብያተ ክርስቲያናትና ተባባሪዎቻቸው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት ማየትና ከእግዚአብሔር ምሪትን ለማግኘት የጸሎትና የምልጃ ቡድን ያልተቋረጠ ጸሎት ሲያደርግ እንደ ቆየ ተነግሯል።

የመግለጫው ሙሉ ቪዲዮ

Hintset

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Latest News

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.