[the_ad_group id=”107″]

የቤተ ክርስቲያን የመድረክ አገልግሎት ከባድ ፈተና ላይ መውደቁ ተነገረ

November 8, 2023
photo_2023-11-08_02-25-25

የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የመድረክ አገልግሎቶች ከፍተኛ የሆነ ችግር እንደ ገጠማቸው ተገለጸ። ይህ የተገለጸው፣ በአዲሰ አበባ ያሉ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት መሪዎች በተገኙበት ሴሚናር ላይ ነው። ሴሚናሩ የተካሄደው ማክሰኞ ጥቅምት 27 ቀን፥ 2016 ዓ.ም.፣ በኢንተርናሽናል ኢቫንጀሊካል ቸርች (IEC) ነው። በውይይት መድረኩ ላይ ከሦስት መቶ በላይ የሚሆኑ የአጥቢያ መሪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላያውን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት፣ ኢክዩፕ ሚድያ እና ሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር በጋራ ያዘጋጁትና፣ “የምስባኮቻችንን ነቀፌታ የሚፈትሽና መፍትሔዎቻቸውን የሚያመላክት ውይይት” የሚል ርእስ በተሰጠው በዚህ ሴሚናር ላይ፣ ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ሦስት ወረቀቶች የቀረቡበት ነበር። በስብከት/ትምህርት፣ በዝማሬ አምልኮ እና በጸሎትና ነጻ የማውጣት አገልግሎት ላይ ትኵረት ያደረጉት ወረቀቶች፣ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መድረኮች የገጠማቸውን አሳሳቢ ችግር የሚያመላክቱ ናቸው ተብሏል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ በሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር የጥናትና ምርምር ክፍል የተዘጋጀው የዳሰሳ ጥናት ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ ጥናቱ በስብከት/ትምህርት፣ በዝማሬ አምልኮ እና በጸሎትና ነጻ የማውጣት አገልግሎት ላይ የምእመናንን ምልከታ የሚፈትሽ ነው። ጥናቱ የተካሄደው፣ በአዲስ አበባ ባሉ ዐሥራ ዘጠኝ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ላይ ሲሆን፣ አጥቢያዎቹ ከተለያዩ ቤተ እምነቶች የተውጣጡ ናቸው።

በቀረቡት ወረቆትችና በጥናት ውጤቱ ላይ የፓናል ውይይት ተካሄዷል። ውይይቱም የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ችግር ውስጥ የሚከትት አደገኛ ሁኔታ መፈጠሩን የሚያመላክት ነበር። በሴሚናሩ መጨረሻ ላይም፣ የጕባዔው ተሳታፊዎች ለቀጣይ ተግባራዊ ርምጃ ያግዘናል ያሉትን፣ ባለ ስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጠተዋል።

የአቋም መግለጫው እንደሚከተለው ይነበባል፦

“የምስባኮቻችንን ነቀፌታ የሚፈትሽና መፍትሔዎቻቸውን የሚያመላክት ውይይት” በሚል ርእስ፣ ጥቅምት 27 ቀን፥ 2016 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት፣ በኢክዩፕ ሚዲያ እና በሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አዘጋጅነት፣ በኢንተርናሽናል ኢቫንጀሊካል ቸርች በተካሄደው የአንድ ቀን ሴሚናር ላይ የተገኘን እኛ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፣ የሚከተለውን ባለ ስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል፦

1. የመድረክ አገልግሎቶች፣ በተለይ የቃለ እግዚአብሔር ስብከት/ትምህርት፣ የዝማሬ አምልኮ እና የጸሎትና ነጻ የማውጣት አገልግሎቶች የክርስቶስን አካል ለማነጽ ያላቸው አስተዋጽዖ እጅግ ከፍተኛ የመሆኑን ያህል፣ እየታዩ ያሉ ተደጋጋሚ ስሕተቶች፣ ለቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ስኬት ትልቅ ዕንቅፋት ከመሆናቸውም ባለፈ፣ የተልእኮው ቅቡልነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ማድረጋቸውን በቀረቡት ወረቀቶች፣ የዳሰሳ ጥናት እና የውይይት መድረክ መረዳት ችለናል።

2. ይህን አሳሳቢ የሆነ የቤተ ክርስቲያን ውስጣዊ ፈተና ለመመከት፣ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል የተቀናጀ ዝግጅትና ቁርጠኝነት የሚጠይቅ መሆኑን በመገንዘብ፣ እኛ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት መሪዎችና አገልጋዮች ተገቢውን ርምጃ ለመውሰድ ወስነናል።

3. በሴሚናሩ በቀረቡት ዝጅቶች ላይ ማስተዋል እንደ ተቻለው፣ የዕውቀትና የግንዛቤ ዕጦት በመድረክ አገልግሎቶች ላይ ላለው ችግር ትልቁን ድርሻ የሚወስድ በመሆኑ፣ ይህን ክፍተት ለመሙላት መሰል መድረኮች ላይ በመሳተፍ፣ በራሳችን አደረጃጀትም ተመሳሳይ ዝግጅቶችን በማድረግ፣ የመድረክ አገልጋዮቻችንን አቅም ለማሳደግ እንሠራለን።

4. ተጠያቂነትና ኀላፊነትን የመውሰድ ጠንካራ አሠራር አለመኖር፣ በመድረክ አግልግሎቶች ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለማረም የሚደረገውን ጥረት አታካች አድርገውታል። በመሆኑም፣ እኛ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና አገልጋዮች በራሳችን አደረጃጀትም ሆነ፣ በኅብረቶቻችን ለሚሠሩ ስሕተቶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተጠያቂነትን የምናሰፍንበትና ኀላፊነት የምንወስድበትን አሠራር ለመዘርጋት ቃል እንገባለን።

5. የነገረ መለኮት ተቋሞቻችን አገልጋዮችን ለማፍራት የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ እጅግ ከፍ ያለ መሆኑን የምንገንዘብ ስንሆን፣ የነገረ መለኮት ተቋሞቹ ለመድረክ አገልግሎቶች ዝግጁ የሚያደርግ ሥርዐተ ትምህርት በመቅረጽ፣ አሁን እያበረከቱት ካለው አስተዋጽዖ በላቀ መልኩ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ እናቀርባለን።

6. የክርስቲያን ሚዲያ ተቋማትም ሆኑ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተጽዕኖ መፍጠር የሚችሉ የሚዲያ ባለሙያዎች፣ ባለባቸው ታላቅ የአገልግሎት ኀላፊነት የሚያስተላልፏቸው የመድረክ አገልግሎቶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረቱን የጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥ፣ ለጊዜያዊ ጥቅም በሚል ከሚደረግ ኀላፊነት ከጎደለው የሚዲያ ስርጭት እንዲቆጠቡ እኛ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጥሪ እናቀርባለን።

Hintset

2 comments

Your email address will not be published. Required fields are marked *

  • እጅግ ልሰራበት የሚገባ ወቅታዊ እና አንገብጋቢ ጉዳይና ነው፣አለያ ግን ቤተክርስቲያን ልኖራት የምገባ ገፅታ ጠፍቶ መድረኩ የትወናና የከንቱ ፍልስፍና ቃላት መፍለቂያ መሆኗ አይቀርም ።

  • በጌታ በኢየሱስ ስም ሰላምታዬ ይድረሳችሁ፣በአምላካችን መድረክ የሚቀርቡ አካሉን ለማነፅና ለመገንባት የሚጠቅሙ እንዳሉ ቢታወቅም በተለይ የቃሉን ሥልጣን ወደታች ዝቅ አድርጎ ልምምድንና ፣የሰዎችን ዝናና ክብር፣ አልፎም ፡ ሰዎች ወደ መመለክ እስኪደርሱ (Cultic Personality) ድረስ የተኬደበት የመድረኮቻችን አካሄዶች እጅግ ያሳስቡናልና፣የነገረ-መለኮት መምህራንም ጭምር ምክክር ፥የሥልጠና ማኑዋሎች በጋራ ቢዘጋጁ፣በደምብ ቢሠራበት እላለሁ፣ተባሩኩ፡፡ትዕግሥት ታዴዎስ ከሐዋሳ ቃ/ሕይወት

Latest News

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.