[the_ad_group id=”107″]

ኅብረቱ የቲቢ ጆሽዋ ጉዳይ ከእንግዲህ የእኔ ነው አለ

March 24, 2016
ኅብረቱ የቲቢ ጆሽዋ ጉዳይ ከእንግዲህ የእኔ ነው አለ

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዚደንት መጋቢ ጻድቁ አብዶ፣ ትላንት መጋቢት 14 ቀን፣ 2008 ዓ.ም. በጽ/ቤታቸው ጋዜጠኞችን ጠርተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኅብረቱ የሥራ አመራር ቦርድ የ“ነቢይ” ቲቢ ጆሽዋ ወደ ኢትዮጵያ መምጣትና አገልግሎት መስጠትን በተመለከተ ሙሉ ኀላፊነቱን መልሶ እንደሚወስድ አስታወቁ፡፡

የግለ ሰቡ “ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ማገልገልን በተመለከተ የረጅም ጊዜ አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል” የሚለው የፕሬዚዳንቱ መግለጫ፣ “የነቢዩን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ማገልግል የማይደግፉ፣ ከመምጣቱ በፊት ሰፊ ጥናትና የጸሎት ቆይታ ይኑረን ያሉ፣ በሌላ በኩል መምጣቱ ለአገራችን ቤተ ክርስቲያን ጠቀሚ በመሆኑ የሚደረግለት ጥሪ ይቀጥል ዘንድ ይገባል የተሰኙ ሐሳቦች በቤተ እምነቶች በኩል” የቀረቡ መሆኑን አስታውሶ፣ ሥራ አስፈጻሚ ቦርዱ “ኅብረቱን ከመጠበቅ አንጻር የነቢይ ቲቢ ጆሽዋን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት እንደግፋለን ያሉ ቤተ እምነቶች ዝግጅቱን እንዲያካሂዱ ይሁንታውን የሰጠ መሆኑ ይታወሳል” ብሏል፡፡

ሆኖም ግን የታሰበው ፕሮግራም በተያዘለት ጊዜና ዕቅድ መሠረት መከናወን ባለመቻሉ “ለኅብረቱም ሆነ ለእርስ በእርስ ግንኙነታችን ክፍተት ሊፈጥር ይችላል ብሎ ስላመነ፣ ኀላፊነቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ጽ/ቤቱ መልሶ በጕዳዩ ላይ እየተነጋገርንና እየተመካከርን አንድነታችንን በማይጎዳ ሁኔታ መሥመርና አቅጣጫ እናስይዘዋለን” የሚል ውሳኔ የካቲት 4 ቀን፣ 2008 ዓ.ም. ባካሄደው 27ኛ ልዩ ስብሰባው ላይ ማሳለፉን ፕሬዚደንቱ ተናግረዋል፡፡ በተላለፈው ውሳኔ ላይ ሁሉም ቤተ እምነቶች ስምምነት እንዳላቸው ነው መጋቢው ያሳወቁት፡፡

በሌላ መግለጫው፣ በብሔራዊ ደረጃ የሚከበሩት ክርስቲያናዊ በዓላት ከጊዜ ወደ ጊዜ መልካቸውን እየቀየሩ መምጣታቸው ኅብረቱን እንዳሳሰበው መጋቢ ጻድቁ አብዶ ተናገሩ፡፡ “… ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንዶቻችን ዘንድ አከባበራቸው ልማዳዊ ወደ ሆነ ሥርዐት ወርዶ ዐቢይ የሆነው ጭብጡ በዘመን ብዛት እየደበዘዘ እንዳይሄድ ከወዲሁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወደ ሆነ መሥመር መመለስ ግድ ይላል” ያሉት ፕሬዚደንቱ፣ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግም ከዚህ በኋላ በዓላቱን ኅብረቱ የማስተባበር ኀላፊነቱን ወስዶ በብሔራዊ ደረጃ ለማክበር እንቅስቃሴ ጀምሯል ብለዋል፡፡ ይህንንም ዐሥር ይደርሳሉ ከተባሉት የኅብረቱ የክልል ቢሮዎች ጋር ተነጋግሮ ስምምነት ላይ መደረሱንም ገልጸዋል፡፡

ክርስቲያናዊ በዓላትን በተመለከተ እንደ ቀድሞው ዘመን መንፈሳዊ ይዘቱን አጉልቶ ከማክበር ይልቅ፣ መብል እና መጠጡ ላይ የማመዘን ልማድ እያደገ መምጣቱን የተናገሩት መጋቢ ጻድቁ፣ መጪውን የትንሣኤ በዓል መንፈሳዊ ድባቡን አጉልቶ በተመሳሳይ ሰዓትና የአከባበር ይዘት በመላ አገሪቱ ላይ እንዲከበር ውሳኔ ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም አገራችን በአሁነ ሰዓት ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ማሰብ እንደሚያስፈልግ፣ በተለይም የአየር ንብረት መዛባት ባስከተለው ድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ በማድረግ እና በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ መደፍረስን ተከትሎ ክርስቲያኖች ራሳቸውን በመመልከትና ወደ እግዚአብሔር ቃል በመመለስ ስለ አገራቸው የሚጸልዩበት ጊዜ መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት በአገሪቱ በአንዳንድ አካባቢዎች በተነሡት ግጭቶች የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገረም ሆነ፣ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሊያሰሙ በሚችሉት ነቢያዊ ድምፅ ረገድ ምን ጥረት አድርገዋል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት መጋቢ ጻድቁ፣ ለሚመለከታቸው የመንግሥት ከፍተኛ አመራር አካል ሥጋታቸውን በጊዜው ከመግለጽ ባለፈ መሆን አለበት ያሉትን መናገራቸውን፣ ወደ ፊትም ቢሆን ኅብረቱ ከመናገር ዝም እንደማይል ጠቁመው፣ “ይህንን አድርጌአለሁ፣ ይህንን አደርጋለሁ አይባልም፡፡ ʻቤተ ክርስቲያናት የነቢይነት ድምፅ የላቸውምʼ ለሚባለውም፣ ነቢይ መሆን ማለት እኮ ቀጥታ የሚመለከታቸው ሰዎች ጋር መሄድ ነው” ሲሉ መላሽ ሰጥተዋል፡፡

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Latest News

ስለ ቤተ መጻሕፍት አደረጃጀት ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ሥልጠና ተሰጠ

“የቤተ መጻሕፍት አደረጃጀት” የተሰኘ የግማሽ ቀን ሥልጠና ለተለያዩ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ተወካዮች ተሰጠ። በሕንጸት የመጽሐፍ ክበብ አዘጋጅነት የተዘጋጀው ሥልጠና፣ ቅዳሜ ሚያዚያ 14 ቀን፥ 2015 ዓ.ም. በላቭ ኤንድ ኬር ማዕከል የተካሄደ ነበር። 

Read More »
SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.