የሥላሴያውያን መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ያሳተመው “አዲስ ኪዳንና መጽሐፈ መዝሙር” የተሰኘ መጽሐፍ ቅዱስ ተመረቀ። መጽሐፉ የተመረቀው ዛሬ ታኅሣሥ 1 ቀን፥ 2015 ዓ.ም. አቧሬ በሚገኘው የወንጌል ብርሃን ቤተ ክርስቲያን ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ነው።
“ቀጥተኛ ትርጕም” የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ መጽሐፍ ቅዱስ፣ “ቀጥተኛ እኵያ” (Formal equivalence) የተሰኘውን የትርጕም መርሖ የተከተለ ነው ተብሏል። ማኅበሩ፣ ተቀባይነት አለው ያለው የኪንግ ጀምስ ትርጕም የተጠቀማቸውን የዕብራይስጡ “ማሶሬቲክ” እና የግሪኩ “ቴክስተስ ሪሴፕተስ” የተሰኙ ቅጆችን መጠቀሙ ተነግሯል። በተጨማሪም፣ በፕሮቴስታንት ተሓድሶ ጊዜ የተተረጐሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጕሞችን እንደ ምንጭ መውሰድ የትርጓሜው ሥልት አካል መሆኑ ተያይዞ ተገልጿል።
“የፕሮቴስታንት” ለሚላቸው አስተምህሮዎችና ለሥላሴ ትምህርት የጸና አቋምና ታማኝነት እንዳለው የሚናገረው ማኅበሩ፣ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ከአርባ በላይ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጕም ሥራዎች ወይም ክለሳ ፕሮጀክቶች አሉኝ ብሏል። እንደ አውሮፓውያን አቈጣጠር በ1831 በእንግሊዝ አገር ሎንዶን ከተማ፣ ከሁለት ሺሕ በላይ በሆኑ አባላቱ የተመሠረተው የሥላሴያውያን መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር (Trinitarian Bible Society)፣ በኢትዮጵያ ለመንቀሳቀስ የሚያስችለውን ሕጋዊ ሰውነት ማግኘቱ በመድረኩ ላይ ተገልጿል።
እስከ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ አሳታሚ ማኅበሮች ዐምስት ሲሆኑ፣ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፣ ቢብሊካ ኢትዮጵያ፣ ዎርድ ፎር ዘ ዎርልድ፣ ኤስ አይ ኤል እና ዋይክሊፍ ኢትዮጵያ ይሰኛሉ።
2 comments
ቋንቋ፣ አገባቡ፣ አረዳዱ፣ ያድጋል ይለወጣል ይሞታልና፣ ለየትውልዱ በሚገባ መንገድ የእግዚአብሔርን ቃል መተርጎም አስፈላጊ ነው። ከዕብራይስጥ/አረሜይክ፣ ግሪክ ምንጭ ወደ አማርኛ ማምጣት ሙሉ ለሙሉ አይሳካም፤ ከአንድ በላይ ትርጓሜ መኖሩ ስለዚህ አስፈላጊ ነው። ያም ሆኖ፣ አማርኛ/ትግረ ወደ ዕብራይስጥ ምንጭ ይቃረባልና፣ ወደ እንግሊዝኛ ከመተርጎም ይቀላል። የትርጓሜ ብዛት ግን እንደ ታሰበው በጎ ውጤት ያስከትላል ማለት አይደለም። በእንግሊዝኛ ብቻ ቢያንስ 50 ያህል ትርጓሜዎች አሉ። ከእነዚህ ብዙዎቹ የምዕራቡን ባህል ከማንፀባረቃቸው ብዛት የቃሉን መሠረት እንደሚገባ አይገነዘቡም። የገበያ ኃይላት ተጽእኖም አለ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ህትመትና ሥርጭት ትልቅ ንግድ ነው። የባፕቲስት መጽሐፍ ቅዱስ አለ፤ የሜተዲስት፣ የፔንቲኮስታልስ፣ የካቶሊክ፣ የኦርቶዶክስ፣ ወዘተ። በያመቱ ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያስገኛል። ንግድ ባለበት ደግሞ፣ ገበያተኛውን (ማህበረ ምእመኑን) አለማስቀየም የሚመረጥባቸው ጊዜአት ይኖራሉ። ለምሳሌ፣ ሪክ ዋረን “ዘ ፐርፐስ ድሪቭ ቸርች” ን ሲያሳትም፣ “አይሁድ” እንደ ማለት “የመካከለኛ ምሥራቅ ሰዎች” የሚለውን ጥቅስ ወስዷል! ፆታን በተመለከተ፣ የቆዳ ቀለምን በተመለከተ፣ ወዘተ፣ ለውጦች ታይተዋል።
“ይኸኛው ትርጉም የበለጠ ግልፅ ያደርገዋል” ሲባል ሰምተናል ወይም ብለናል። ይህን የምንለው ባብዛኛው ልንለው ያሰብነውን ሲልልን እንዲልልን ነው። ያሰብነውን የሚልልንን ፍለጋ ከትርጓሜው ወደ ትርጓሜ እንሯሯጣለን። አንዳንዶች እንግሊዝኛው እንዲህ ይላል የሚሉት አንድም ለዚህ ነው። ከሰባኪ ሰባኪ የምናማርጠው አንዳንዴም ለዚህ ነው። እከሌ እከሊት ግሩም አስተማሪ ነው እንላለን። ግሩም አስተማሪ ሊሆኑ ይችላሉ። ቃሉን በጥልቀት ካላወቅነው፣ ማመሳከር የሚጠይቀውን ኃላፊነት እና ትጋት ካልኖረን፣ በብዙ ፀሎት፣ በቅንነት፣ በማህበር በማጥናትና በመንፈስ ቅዱስ ላይ ካልተደገፍን ግን እድገታችን ይገታል።
ከአዳዲስ ትርጓሜዎች ጎን ለጎን፣ እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያኑ የቃሉ አስተማሪዎችን እንዲያስነሳ መፀለይ እጅግ አስፈላጊ ነው። በቀኃሥ ዘመን የታተመው መጽሐፍ ቅዱስ ቋንቋው አንዳንዴ ግር ይል ይሆናል፤ ለሚተጒ አስተማሪዎች ግን አሁንም ዋነኛ ምርጫ ሊሆን ይገባል።
የሥላሴአውያንን ትርጓሜ አላነበብኩም። ከዚህ ቀደም በሌላ ሥፍራ እንዳልኩት፣ ስንት ግድፈት ይገኝበት ይሆን? የሚል ስጋት አለብኝ።
Thanks