ሕንጸት የመጽሐፍ ክበብ
የሕንጸት የመጽሐፍ ክበብ፣ በክርስቲያን ማኅበረ ሰቡ ዘንድ የንባብና የውይይት ባሕል እንዲዳበርና ብርቱ ጸሐፊያን እንዲጎለብቱ በሚል በወር አንድ ጊዜ የሚደረግ የመጽሐፍ ግምገማ/ውይይት ያካሄዳል፡፡
በዚህም የሚከተሉትን ዝርዝር ዓላማዎችን ለማሳካት ይሠራል፡-
- የንባብ ባሕል እንዲዳብር የበኩሉን ድርሻ መወጣት፤
- ክርስቲያን ጸሐፊያን እንዲበራከቱ ማበረታታት፤
- የሚታተሙ መጻሕፍት ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ሒሳዊ ምልከታዎችን በማቅረብ ማገዝ፤
- በክርስቲያን ማኅበረ ሰቡ መካከል የውይይት ባሕልን ማዳበር፤
ለግምገማ የሚቀርቡ መጻሕፍ ከሞላ ጎደል የሚከተሉት ይሆናሉ፡-
- በዋናነት የወንጌል አማኝ ማኅበረ ሰቡን የሚመለከቱ ሆነው ሲገኙ፤
- የመጻሕፍቱ ፋይዳ ጉልሕ ሆኖ ሲገኝና ይህም አሳማኝ በሆነ መልኩ መብራራት ሲችል፤
- በተቻለ መጠን ደረጃቸውን የጠበቁና ʻሊነበቡ ይገባቸዋልʼ ተብለው የሚታመነባቸው ሥራዎች ሊሆኑ ይገባል፤
- ጻሓፍቱ በአማኝ ማኅበረ ሰቡ ውስጥ ያላቸው ተደማጭነት ጉልሕ ሆኖ ሲገኝ ዕድል ሊሰጠው ይችላል፤
- የወንጌል አማኝ ማኅበረ ሰቡን በክፉም ሆነ በደግ የሚመለከቱና በማናቸውም አካላት የተጻፉ ሥራዎች ሲገኙ፤
- ወቅታዊና አንገብጋቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የተጻፉ መጻሕፍት ሲኖሩ፤
ከላይ የተዘረዘሩት መሥፈርቶች በየትኛውም የሥነ ጽሑፍ ዘውግ ውስጥ ያሉትን መጻሕፍት ይመለከታል፡፡