[the_ad_group id=”107″]

“ታሪካዊ” የተባለው የኅብረቱ ውሳኔ እና የተሰጠው ምላሽ

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ጠቅላላ ጉባኤ፣ ከመጋቢት 21-22፣ 2009 ዓ.ም. ድረስ ባካሄደው 32ኛ መደበኛ ስብሰባው፣ በአስተምህሮ ዝንፈት፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባልሆኑ ልምምዶች እና በሞራል ውድቀት ላይ እጅግ ጠንካራ ነው የተባለለት የአቋም መግለጫ አወጣ፡፡ መግለጫው የወጣው በተጠቀሱት ጕዳዮች ላይ ኅብረቱ ያዘጋጀው ጥናት ለጠቅላላ ጉባኤው ከቀረበና ውይይት ከተካሄደበት በኋላ እንደ ሆነም ተነግሯል፡፡ የኅብረቱ ፕሬዚዳንት መጋቢ ጻድቁ አብዶ ለጉባኤው ባደረጉት ንግግር፣ በአስተምህሮ ዝንፈት፣ ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆኑ ልምምዶች እና በሞራል ሕይወት ውድቀቶች ላይ የቀረበው ጥናት፣ ከአንድ ዓመት በፊት የኅብረቱ ጠቅላላ ጉባኤ ባደረገው ውሳኔ መሠረት የተዘጋጀ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግም ዘጠኝ አባላት ያሉት አጥኚ ቡድን ያለፈውን አንድ ዓመት ሥራውን ሲከውን መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ይህ ባለ ዐሥር ነጥቦችን የያዘው መግለጫ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትን አደጋ ውስጥ ጥለዋቸዋል ባላቸው ጕዳዮች ላይ አቋም የያዘ ነው፡፡ “ጕዳዩ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ከመገንዘባችን በላይ፣ አፋጣኝ መፍትሔ ካልተሰጠው የክርስትናን መሠረታዊ ይዘት የሚያፋልስ፣ የመንፈስ አንድነታችንን የሚያናጋ፣ የወንጌልን ግስጋሴ የሚገታ ትልቅ አደጋ እንደተጋረጠብን ይታየናል፡፡” ሲልም የአሳሳቢነቱን ደረጃ ያሳያል፡፡

ይህንን ተከትሎ የኅብቱ ፕሬዚዳንት እና የሥራ አመራር ቦርድ አባላት በኅብረቱ ጽ/ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ “ወንጌላውያን በታሪካቸው እንደዚህ ያለ አንገት የሚያስደፋ ችግር ገጥሟቸው አያውቅም” ያሉ ሲሆን፣ ጕዳዩ የአቋም መግለጫ ከማውጣት ያለፈ ተግባራዊ ርምጃ የሚያሻው እንደ ሆነ አጽንኦት ሰጥተው አስረድተዋል፡፡ ጋዜጠኞች ʻችግር አለባቸው የተባሉትን ለምን በስም አልጠቀሳችሁም፤ እነዚህን ግለ ሰቦችስ ቀድማችሁ አነጋግራችኋቸዋል ውይ?ʼ በሚል ላነሡት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት መሪዎቹ፣ ስም ጥቀሶ የማውገዙ ተግባር ወደ ፊት ሊደረግ የሚችል እንደ ሆነ፣ አሁን ግን በዋናነት በኢትዮጵያ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የሆኑትን የመጠበቅና ወንጌላውያን ያሰኛቸውን “መሥመር የማሥመሩ”ን ሥር እንዳስቀደሙ አብራርተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ በሂደት ከስሕተት መንገድ ሊመለሱ ለሚችሉት ዕድል ለመስጠት በማሰብ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የአቋም መግለጫው ከመውጣቱም በፊት፣ ከኅብረቱ ውጪ ካሉ ቤተ እምነት መሪዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ያስታወሱት መጋቢ ጻድቁ፣ “አንዳንዶቹ አሁን ባለው ነገር ደስተኞች እንዳልሆኑ ገልጸውልናል” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
በዚህም መሠረት የአቋም መግለጫው፣ “የእምነት ቃል እንቅስቃሴ” እና “የብልፅግና ወንጌል”፣ በመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች ስም የሚደረጉ ማጭበርበሮችን፣ ግለ ሰቦችን ያለ ቅጥ በማግነንና የሁሉም መንፈሳዊ አገልግሎቶች ማእከል በሚያደርጉ ልምምዶች ላይ ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡ በተጨማሪም፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ከሆነው የሞራል ሕይወት እጅግ ተጻራሪ በሆነ መልኩ ኀጢአትን መለማመድ እና በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ላይ ከተገነባው የወንጌለውያን የእምነት መሠረት እጅግ ያፈነገጡ ሌሎች ተግባራትን አውግዟል፤ እንዲህ ዐይነቶቹም የኢትዮጵያ ወንጌላውያንን ክርስትና አይወክሉም ብሏል፡፡

በዚህ ዐይነት አስተምህሯዊ አቋም፣ ልምምድና የሞራል ሕይወት ውስጥ ያሉ ሁሉ ከዚህ ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ አካሄድ እንዲመለሱ ጥሪ የሚያቀርበው መግለጫው፣ ይህንን ክርስቲያናዊ የፍቅር ጥሪ በማይቀበሉት ላይ ግን የኅብረቱ ጽ/ቤት ከኅብረቱ የሥራ አመራር ቦርድ ጋር በመሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያለውን ርምጃ እንዲወስድ ኀላፊነት መስጠቱን አመልክቷል፡፡ በተለይም፣ በክርስትና ስም የሚደረጉ ማናቸውም ዐይነት የማጭበርበር ድርጊቶችን ተከትሎ ለሚመጡ የሕግ ጥያቄዎችና ክሶች የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ምንም ዐይነት ሽፋንም ሆነ ከለላ እንደማይሰጡ ይገልጻል፡፡

“የእምነት ቃል እንቅስቃሴ” ሲል በጠራው የስሕተት ትምህርት ውስጥ መገለጫዎቹ ናቸው ብሎ ከዘረዘራቸው መካከል፣ “ሰው መንፈስ ነው፤ ነፍስ አለው፤ በሥጋ ውስጥ ይኖራል”፣ “እኛ እና አብ አንድ ነን”፣ “እኛ እና ክርስቶስ አንድ ነን”፣ “እኛ ትንንሽ አማልክት ነን”፣ “ክርስቶስ ሰይጥኗል”፣ “እኛ ካልፈቀድንለት በስተቀር እግዚአብሔር በምድር ላይ መሥራት አይችልም፤ ሕገ ወጥ ይሆናል”፣ “የእኛ እምነት እንደ እግዚአብሔር ያለ እምነት ነው”፣ “በሥጋ የሚሠራ ኃጢአት ችግር የለውም” ማለቱን እንዲሁም “የክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት ለኀጢአት ስርየት በቂ አይደለም” ማለቱን ይጠቅሳል፡፡

በተመሳሳይም፣ “የብልፅግና ወንጌል” በተሰኘውና ከወንጌላውያን ክርስትና አስተምህሮ ይለያል በተባለው የስሕተት ትምህርት ላይ በወጣው አንቀጽ፣ ትምህርቱ “አማኞች ፍጹም ሊታመሙ አይችሉም”፣ “አማኞች ፍጹም ሊደኸዩ አይችሉም”፣ “ሰዎች የሚታመሙትም ሆነ የሚደኸዩት ከእምነት ዕጦት የተነሣ ነው”፣ “ከአንደበታችን የሚወጣው ቃል ልክ እንደ እግዚአብሔር ቃል የመፍጠርና የማድረግ ጉልበት አለው” ማለቱን እና “የክርስቶስን መስቀል ምሳሌያዊ ጥሪ አንቀበልም” የተሰኙ ትምህርቶቹን አብያተ ክርስቲያናቱ አጥብቀው እንደሚቃወሙት በመግለጫው ተካትቷል፡፡

“መዘግየት ከመቅረት ይሻላል…”

የመግለጫው መውጣት በአማኝ ማኅበረ ሰቡ ዘንድ ትልቅ የመነጋገሪያ ርእስ ሆኖ እንዲሰነብት አድርጓል፡፡ ይኸው ዜና በሕንጸት የማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መነበቡን ተከትሎ ʻኅብረቱ የወሰደው ውሳኔ ተገቢና ጊዜውን የጠበቀ ነውʼ የሚሉ ወገኖች ቊጥር አብላጫውን የያዘ ነበር፡፡ ሕንጸት በአካል ያነጋገራቸውም ይህንኑ ስሜት የሚያንጸባርቁ ናቸው፡፡

ከኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት አባልነት በገዛ ፈቃዷ የለቀቀችው የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ምክትል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ዶ/ር ወይታ ወዛ፣ የኅብረቱ ጠቅላላ ጉባኤ ያወጣውን መግለጫ እሳቸውም ሆኑ ቤተ ክርስቲያናቸው በደስታ እንደሚቀበሉት ለሕንጸት ተናግረዋል፡፡ “አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ባወጣው የአቋም መግለጫ እንደ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን በጣም ደስተኞች ነን፡፡ ከአብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ስንወጣ እንደ አንድ ነጥብ አድርገን፣ ʻእነዚህ ነገሮች ይታረሙʼ ብለን ካስቀመጥናቸው አቅጣጫዎች አንዱ እሱ ነው፤ እንደ ዋና ምክንያት ባይሆንም፡፡” ሲሉ የአስተምህሮ ዝንፈት ቤተ እምነታቸው ከኅብረቱ ጋር እንዳትቀጥል ምክንያት መፍጠሩን ያስታውሳሉ፡፡

ቤተ ክርስቲያኒቱ ከአንድ ዓመት በፊት ተመሳሳይ ይዘት ያለው የአቋም መግለጫ በቤተ እምነት ደረጃ ማውጣቷን የሚናገሩት ዶ/ር ወይታ፣ “መጋቢት 9፣ 2008 ዓ.ም. በኩሪፍቱ ማዕከል በተደረገው 55ኛው ጠቅላላ ጉባኤያችን፣ ባለ 7 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተን ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ያወጣው መግለጫ እኛ ካወጣነው ጋር ተመሳሳይነት አለው” ይላሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያናቸው በወቅቱ መግለጫ ለማውጣት መነሻ የሆናትን ምክንያት ሰያስረዱም፣ “ለሕዝቡ መድረስ አለብን፤ ሕዝቡ ሲዘረፍ፣ በወንጌል ስም ገንዘቡን ሲሰበስቡ፣ ሲያራቁቱ ዝም ብለን ማየት የለብንም፤ ወደ ሕዝቡ መውረድ አለብን፤ ሕዝቡን ማስተማር አለብን” በሚል የእረኝነት ኀላፊነት አቋም እንደያዙ ያብራራሉ፡፡

በወርኀ ሰኔ፣ 2007 ዓ.ም. “የተሐድሶ ፎረም” በተሰኘና ስድስት በሚደርሱ አጋር የቤተ ክርስቲያን ተቋማት እንዲሁም የተለያዩ ግለ ሰቦችን በያዘ አካል አማካኝነት፣ “የተሐድሶ ንቅናቄ መፍጠር” በሚል አንድ አገር አቀፍ መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዚህ የሁለት ቀን ስብሰባ ላይ በመላው ኢትዮጵያ ካሉ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የተውጣጡ መሪዎችና አገልጋዮች ተሳትፈዋል፡፡ ይህ መድረክ “የአስተምህሮ ጥራት”፣ “የአመራር ጥራት” እና “የሕይወት ጥራት” በተሰኙ ሦስት ርእሰ ጕዳዮች ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚያስችሉ ጽሑፎችን አቅርቦ መሪዎችንና አገልጋዮችን አወያይቷል፡፡ አንዳንድ ቤተ እምነቶችም በዚሁ መድረክ የቀረቡትን የውይይት ሐሳቦች ወደ ቤተ ክርስቲያናቸው በመውሰድ ለአገልጋዮችና ለምእመና እንዲደርስ አድርገዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ተማሪዎችና ምሩቃን ማኅበር (ኢቫሱ) የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ፈቀደ ተፈራ የዚህ መድረክ አስተባባሪ ከሆኑት ግለ ሰቦች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ያወጣውን የአቋም መግለጫ በተመለከተ ከሕንጸት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አቶ ፈቀደ፣ “በመሠረቱ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ያወጣው የአቋም መግለጫ ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡” ይላሉ፤ ወሳኔውም ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረ መሆኑን ያስታውሳሉ፡፡ “ይሄ ጩኸት የቆየ ጩኸት ነው፤ ምናልባት ይህንን በተመለከተ የዛሬ 22 ዓመት በዚህ ጕዳይ ላይ ጥቂት ወንድሞችና እኅቶች ተሰባስበው፣ ʻየምንሄድበት መሥመር እየለቀቀ ነው፤ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ እየተፋለሰ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ አዳዲስ ትምህርቶችና ልምምዶች እየመጡ ናቸውʼ በሚል ትምህርቶች ተዘጋጅተው ነበር፡፡ በተለይ፣ በእምነት ቃል እንቅስቃሴና በብልፅግና ወንጌል ላይ ሰፊ ትምህርቶች ለአገልጋዮች በየቤተ ክርስቲያኑ ተሰጥቶ ነበር፡፡ እንግዲህ በወቅቱ ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና አገልጋዮች ተገቢውን ግንዛቤ የወሰዱ አልመሰለኝም፡፡” ሲሉ ዛሬ ተባብሶ የታየው ችግር ቀደም ሲል ለተደረገው ጥሪ በቂ ምላሽ ባለመሰጠቱ እንደ ሆነ ይጠቁማሉ፡፡ ይሁን እንጂ ከሁለት ዓመት በፊት የተደረገው “የተሐድሶ ፎረም” ተጨማሪ የማንቂያ ደውል እንደ ፈጠረና ኅብረቱ ወደዚህ አቋም እንዲመጣ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከቱን እንደሚያምኑ ነው አቶ ፈቀደ የሚገልጹት፡፡

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት አባል ባልሆነቸው “የመማጸኛ ከተማ ቤተ ክርስቲያን” መጋቢ የሆኑት ሞላልኝ አዱኛ እንደሚሉት ከሆነ፣ ኅብረቱ ያወጣው የአቋም መግለጫ አንድ ትልቅ ትርጕም አለው፤ ይኸውም አሁን ሥርዐት ባጣ መልኩ እየተጓዘ ላለው አካሄድ ʻያገባኛልʼ የሚል አካል መነሣቱ ነው፡፡ “እኔ ʻሀይʼ የሚል፣ ግድ የሚለው አካል በመነሣቱ በጣም ተደስቻለሁ፤ ከሚገባው በላይ ተደስቻለሁ፡፡ ምክንያቱም እንደዚህ ዐይነት አካል አስፈላጊ ነው፤ ደግሞም ጊዜውን ያማከለ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡” ይላሉ መጋቢ ሞላልኝ፡፡

“ብረትን … እንደ ጋለ ነው”

ምንም እንኳን ኅብረቱ ያወጣው መግለጫ በራሱ እንደ አንድ ትልቅ ርምጃ የሚቈጠር ቢሆንም፣ ዐቢዩ ሥራ ግን በቀጣይ የሚተገበረው ስለ መሆኑ ብዙ ክርክር የሚያስነሣ አይመስለም፡፡ በተለይም፣ በአቋም መግለጫው ተራ ቊጥር 8 ላይ፣ የኅብረቱ ጽ/ቤት እና የሥራ አስፈጻሚው ቦርድ በጋራ እንዲተገብሯቸው የተሰጡ ኀላፊነቶች፣ የአቋም መግለጫውን ከማውጣት ያለፈ ተግባር በኅብረቱ ላይ መውደቁን ያመለክታል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ኅብረቱ ቀጣይ ርምጃዎቹን የሚተገብርበት ጊዜና መንገድ ከሁሉም በላይ ትኩረት መሳቡ አልቀረም፡፡

“የተሐድሶ ፎረም” አስተባባሪ የሆኑት አቶ ፈቀደ ተፈራ ኅብረቱ ቀጣይ ርምጃዎቹን በሚመለከት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ይመክራሉ፡፡ “አንደኛ፣ እንደ መንፈሳዊ ሰው ነገሮችን ሁሉ በማስተዋልና በጥበብ ማድረግ ይጠይቃል፡፡ ጕዳዩ የኀይል ጕዳይ አይደለም፤ ኀይል የእግዚአብሔር ነውና፡፡ የቤቱም ሆነ የሕዝቡ ባለቤት እግዚአብሔር ስለ ሆነ ኀይል የምንጠቀምበት አይደለም፡፡ ስለዚህ የምንሄድበትን አቅጣጫ እግዚአብሔር እንዲያሳየን፣ የሰዎቹንም ልብ ወደ ፈቃዱ እንዲመልስ ጸሎት ማድረግ የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡” አቶ ፈቃደ በሁለተኛ ደረጃ መደረግ አለበት የሚሉት፣ ሕዝቡ የመግለጫውን ምንነት በበቂ መንገድ እንዲያውቀው በተለያየ አቅጣጫ ግንዛቤውን ሊያሳድግለት የሚችል ሥራ መሠራት አለበት፡፡ “ሚዲያውን በስፋት በመጠቀም፣ በራሪ ጽሑፎችን መበተን፣ በየቤተ ክርስቲያኑ ማብራሪያ መስጠት፣ ምእመኑ የውሳኔውን ትክክለኛ መንፈስ እንዲያውቅና እንዲረዳ ግልጽ የማድረግ ሥራ መሠራት አለበት፡፡” ይላሉ፡፡

“በሦስተኛ ደረጃ፣ እነዚህ ትምህርቶችና ልምምዶች ምንድን ናቸው? በምን ምክንያት ነው ከመጽሐፍ ቅዱስ የተለዩት? የትምህርቶቹ ጥንስስ እነማን ናቸው? የሚለውን በተመለከተ ለመሪዎች፣ ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው በወንጌል አገልግሎት ለተሰማሩት ሰዎች ዐውደ ጥናትና የመሳሰሉትን በማዘጋጀት ማስታጠቅ ይጠይቃል፡፡” ይላሉ አቶ ፈቀደ፡፡ አክለውም፣ “ለሕዝቡና ለአገልጋዮች በተሰጡ ትምህርቶች ላይ ክትትል ማድረግ” እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡ “ምን ላይ እንደ ተደረሰ? ምን ችግር ገጠመ? ለገጠሙ ችግሮችስ ምን ዐይነት መፍትሔ መስጠት ይቻላል?” በሚሉት ላይ ሰፊ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ የስሕተት ትምህርት የሚያስተምሩትንና በዚህ ልምምድ ውስጥ ካሉት ሰዎች ጋር ተቀራርቦ መነጋገር እንደሚያስፈልግ የሚያስታውሱት አቶ ፈቀደ፣ “በስሕተት ወይም ባለማወቅ የጠፋውንና የሄደውን ገንዘብ ለማድረግ ጥረት ማድረግ” ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

የቃለ ሕይወቱ ዶ/ር ወይታ በበኩላቸው፣ በስሕተት ትምህርቶችና ለምምዶች ላይ የውይይት መድረክ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ይግልጻሉ፡፡ በተለይም፣ “የተሳሳተው በስሕተቱ እንዲጠፋ አንጸልይም፤ ከስሕተቱ ተመልሶ፣ ታርሞ ወደ ትክክለኛው ጎዳና እንዲመጣ ነው የምንፈልገው” የሚሉት ዶ/ር ወይታ፣ “ስሕተት የሚያስተምሩ ሰዎች መለስ ብለው ራሳቸውን አይተው ʻወደ መጽሐፍ ቅዱሳዊው እውነታ እንመጣለንʼ ካሉ፣ በሥነ መለኮት ምሁራንና በተወሰኑ የሥነ መለኮት ት/ቤቶች ደረጃ ውይይቱ” ሊጀመር እንደሚገባ አጽንኦት ይሰጣሉ፡፡
አቶ ታምሩ ዘለቀ የጌጃ ቃለ ሕይወት መጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅ ፕሪንሲፓል ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ከሆነ፣ ኅብረቱ አሁን ባወጣ የአቋም መግለጫ ብቻ ተገድቦ እንዳይቀር ተገቢውን ስትራቴጂ ነድፎ መንቀሳቀስና ራሱን የበለጠ ማደራጀት ያስፈልገዋል፡፡ በተለይም፣ “የቲሎጂካል ኮሚሽኑ ሥራና ኀላፊነት ከዚህ በላይ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ኮሚሽኑ፣ አሉ የሚባሉ ችግሮችን በጥልቀት ማጥናት፣ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ሊኖራቸውን የሚችለውን አንድምታ መመርመርና ዘለቄታዊ መፍትሔ ያመጣል የሚለውን ምክር ለኅብረቱም ሆነ ለአባል አብያተ ክርስቲያናቱ ማቀበል ለነገ የማይባል ሥራው ሊሆን ይገባል” ይላሉ አቶ ታምሩ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኅብረቱ በራሱ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበትን አሠራር መዘርጋት፣ ʻለምን እዚህ ጋር ደረስን?ʼ ብሎ መጠየቅና መንስዔውንም ማወቅ እጅግ አስፈላጊ እንደ ሆነ ይጠቁማሉ፡፡
“ኅብረታችን በአስተምህሯችን ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት” የሚሉት ደግሞ መጋቢ ሞላልኝ ናቸው፡፡ “ባህላዊ የሆነው ግንኙነታችን አሁን መስተካከል አለበት፤ ባህላዊ ከሆነ ግንኙነት ወጥተን ዶክትሪናል የሆነ አንድነት መያዝ እንዳለብን አምናለሁ፡፡ ይሄ ከጊዜው ጋር መሠራት ያለበት ነገር ነው፤ ልዩነቱ ግን መምጣቱ አይቀርም፡፡” ሲሉ ኅብረቱ ለአስተምህሮ ቅድሚያ መስጠት እንዳለበትና ለኅብረት ብቻ ሲል አስተምህሯዊ ጕዳዮችን ችላ እንዳይላቸው ያሳስባሉ፡፡

“የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ኅብረቱ ካወጣው የአቋም መግለጫ ጋር ወደ ፊት አብሮ ለመሥራት ምን አስባለች?” በሚል ከሕንጸት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ዶ/ር ወይታ ወዛ፣ “ማንኛውም መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ካላቸው ጋር፣ ከአብያተ ክርስቲያናትም ሆነ ከሚኒስትሪዎች ጋር፣ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን እየሠራች ነው” ያሉት ምክትል ዋና ጸሐፊው፣ “አብያተ ክርስቲያናት ያወጣው መግለጫ መጽሐፍ ቅዱስን እስካልተቃረነ ድረስና ወቅታዊ ሁኔታዎችን በግልጽ እስከ አስቀመጠ ደረስ” አብረው የሚቆሙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደምም ቢሆን፣ የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ከወንጌላውያን አብያት ክርስቲያናት ጋር በጋራ የወንጌል ሥራ ሲትሠራ የቆየች መሆኗን አውስተው፣ አሁንም ያንኑ እንደሚቀጥሉበት የሚናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን፣ የሥነ ጽሑፍና ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኀላፊ የሆኑት አቶ ተመስገን ይህንኑ በሚመለከት ሲናገሩ፣ “ሁላችንም እየተጋፈጠን ያለነው ችግር አንድ ዐይነት ነው፤ የአቋም መግለጫዎቻችንም በጣም ተመሳሳይ ናቸው፡፡ የቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትን ያገለግላሉ፤ የወንጌላውያኑም የቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያንን ያገለግላሉ፤ ስለዚህ ወንድማማችነቱ አለ፡፡ ይሄን አቋም ይዞ መንቀሳቀሱ ደግሞ በመተማመንና በአንድነት የመሄዱን ነገር ያጠነክረዋል፡፡” ሲሉ ቤተ ክርስቲያናቸው ለኅብረቱ አጋርነቷን እንደማትነፍግ ያረጋግጣሉ፡፡

በዚሁ ሁሉ ሂደት ውስጥ መዘናጋት እንዳይመጣ፣ ብሎም የተጀመረውን ዳር ሳይደርስ እንዳይቀር፣ ʻለነገʼ ተብሎ የሚተው ሥራ እንዳይኖር ኅብረቱም ሆነ አባል ቤተ እምነቶቹ ኀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው በተለያዩ ወገኖች ተደጋግሞ የሚሰጥ አስተያየት ሆኗል፤ “ብረትን … እንደ ጋለ ነው” እንዲሉ፡፡

“የኢትዮጵያ ቪዥነሪ አብያተ ክርስቲያን ኅብረት” ምላሽስ?

በተመሳሳይ፣ “የኢትዮጵያ ቪዥነሪ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት”፣ ሰኞ ሚያዝያ 23 ቀን 2009 ዓ.ም. በ9 ሰዓት፣ በሳሮ ማርያ ሆቴል የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት በ32ተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤው ላይ ላወጣው የአቋም መግለጫ የብዙኀን መገናኛ ባለሙያዎችን ጠርቶ “ምላሽ” ያለውን ሰጥቷል፡፡

ይሄኛው ኅብረት ምላሽ ለመስጠት ተገደድኩባቸው ያላቸውን አምስት ምክንያቶች አቅርቧል፡፡ እነዚህም፡- “የወንድማማችነትን ኅብረት ለመጠበቅና እንደ ባለድርሻ አካላትም ዝምታ ስለማይጠበቅብን”፣ “የቅዱሳንን አንድነት ለመጠበቅ ሲባል”፣ “ወደ አለመግባባት ሊያመራ ለሚችለው ለዚህ አቋም መግለጫ ምላሽ መስጠት ግድ” ስለሆነ፣ “እንደ ጥንት የእምነት አባቶቻችንና እንደ መንግሥታችን ሁሉ ከጽንፈኝነት ይልቅ በእኩልነትና በመቻቻል፣ ማለትም በብሔር ብሔረሰብ እኩልነት፣ በጾታ እኩልነት፣ በሃይማኖት እኩልነት የምናምን በመሆኑና … የሌላውን መብትና ጥቅም በሚነካ መልኩ ለተዘጋጀው” ምላሽ መስጠቱ ስላስፈለገ እንዲሁም፣ ኅብረቱ “መግለጫው ከመውጣቱ ጥቂት ቀናት በፊት … የኢትዮጵያ ቪዥነሪ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት አባል ቤተ እምነት መሪዎችን ጠርቶ ማነጋገሩ አግባብ ስላልሆነ … ምእመኖቻችን[ም] ላይ ብዥታ” የፈጠረ በመሆኑ ምላሽ መስጠት እንዳስፈለገው ይገልጻል፡፡

ከዚህም የተነሣ፣ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅበረት ያወጣው የአቋም መግለጫ፣ “ለእግዚአብሔር የመንግሥቱ ሥራ ቅድሚያ ያልሰጠ በመሆኑ፣ ሰዎች ጥፋተኛ ሆነው ባልተገኙበት ሁኔታ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሰጠውን የመመለስና የንስሓ ዕድል የነፈገና ፍርድ ለመስጠት የተሞከረበት በመሆኑ፣ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሰጠውን ከሕግ አንጻር መሠረታዊ መብት ተብሎ የሚታወቀውን የሰው ልጆች ነጻነት የሚጻረር በመሆኑ፣ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶችንና የዲሞክራሲያዊ መብቶችን የሚቃረን በመሆኑ፣ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንጻርም ሆነ ከሌሎች ሀገራዊ ጕዳዮች አንጻር ሲታይ የዜጎች መብትና ጥቅም ያላማከለ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት 32ኛ ጠቅላላ ጉባኤው ላይ በቀን 22/08/2009 ወጣ የተባለውን የአቋም መገለጫ አካሄዱና አቀራረቡን መንፈሳዊነት ስለሚጎድለውና የሕግ ሕጸጾችም ስላሉት እንዲሁም ደግሞ ከመግለጫው አውጪው ክፍል አልፎ ሌሎችን የሚነካ በመሆኑ የመግለጫውን አካሄድና አቀራረብ መጽሐፍ ቅዱሳዊና ሕጋዊ አይደለም ስንል በጽኑ ይቃወማል፡፡” ይላል፡፡

ʻየኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የሚፈልገውን አካል ስብሰባ የመጥራት፣ አባላቶቻችሁም በተጠሩበት ስብሰባ ላይ እንዳይገኙ የሚከለክላቸው ሕግ አለ ማለት ነው?ʼ በሚል ከሕንጸት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት መሪዎቹ፣ “የእኛን አባላት በተናጥል መጥራት አይችልም፤ ምክንያቱም እኛ እንደ ኅብረት እንወያይ ብለን ጠይቀናል፡፡” ሲሉ ቅድሚያ ለጠየቁት የእንወያይ ጥሪ ምላሽ ሳይሰጥ አባላቶቻቸውን ማነጋገሩ ተገቢ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ እንደ መሪዎቹ እምነት ከሆነ፣ ኅብረቱ ይህን ያደረገው በመካከላቸው መከፋፈልን ለማምጣት ብሎ ነው፡፡ የአባላቶቻቸውን የስብሰባ ተሳትፎ በተመለከተ ግን፣ “የእኛ አባላት ከእኛ ፈቃድ ሳይጠይቁ የትም መሰብሰብ፣ ብሎም አባል መሆን” ይችላሉ ሲሉ ነጻነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ʻኅብረቱ የራሱን እምነት በአቋም መግለጥ አይችልም ወይ?ʼ በሚል ለተነሣው ጥያቄ፣ “የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የፈለገውን መግለጫ መስጠት ይችላል፤ ነገር ግን እኛን የሚመለከት ነገር ሳንወያይ በአንድ ወገን ጥናት ላይ ተመርኩዞ፣ ያውም አጥኚዎቹ ማንነታቸው ጥያቄ ውስጥ ባለበት ሁኔታ፣ ያወጣው መግለጫ” አግባብ እንዳልሆነ ነው የተናገሩት፡፡

አቶ ጂማ ዲልቦ የሕግ ባለሙያና አማካሪ ናቸው፡፡ “የኢትዮጵያ ቪዥነሪ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት” በሰጠው ምላሽ ላይ፣ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የአካሄድ ስሕተቶችን ስለ መሥራቱ ብቻ ሳይሆን፣ ዓለም አቀፍ የሆኑ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶችንና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ተቃርኗል ስለ መባሉ ሙያዊ አስተያየት እንዲሰጡ በሚል ሕንጸት አነጋግሯቸው ነበር፡፡ እንደ እርሳቸው እምነት ከሆነ፣ መግለጫው ምላሽ ሆኖ መቅረቡ በራሱ ጥያቄ እንደሚፈጥር ያስረዳሉ፡፡ “መግለጫው በምላሽ መልክ ሆኖ ለምን እንደ ቀረበ ግልጽ አይደለም፤ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት በሰጠው መግለጫ የተቋምንም ሆነ የግለ ሰቦችን ስም አልጠቀሰም፡፡ ኅብረቱ ʻየማይወክሉኝ እንቅስቃሴዎች አሉʼ ነው ያለው እንጂ፣ ʻእከሌʼ ለሚባል ተቋምም ሆነ ግለ ሰብ ይድረስልኝ” እንዳላለ ያስረዳሉ፡፡ አያይዘውም፣ መግለጫው ትኩረት የሚያደርገው፣ ʻወንጌላውያን ያሰኙንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮዎችን በለቀቀ መልኩ የሚደረጉ እንቅስቀሴዎች አሉʼ ብሎ እነዚያን እንቅስቃሴዎች በዝርዝር ከጠቀሰ በኋላ፣ “ቢያንስ እነዚህ እንቅስቃሴዎች የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረትን የማይወክሉ መሆናቸውን ነው የገለጸው እንጂ፣ የትኛውንም የእምነት ተቋም የሚያንቋሸሽ ነገር በኅብረቱ መግለጫ ላይ አላየሁም፡፡” ይላሉ አቶ ጂማ፡፡

“የቪዥነሪ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት” ያወጣው መግለጫ ያለበት ሌላኛው ችግር “እርስ በርሱ የሚምታታና የሚጋጭ” መሆኑ ነው፤ እንደ ሕግ ባለሙያው አቶ ጂማ ማብራሪያ ከሆነ፡፡ “ʻኅብረቱ ያወጣውን መግለጫ በመሠረተ ሐሳብ ደረጃ እንጋራለንʼ ይላል፡፡ ወደ ታች ከወረደ በኋላ ግን ʻበሕግም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱሱ አካሄድ ለመቀበል የሚያስቸግሩ ቃላትን ነው የተጠቀሙትʼ ይላል፡፡ እንደዚህ ዐይነት ቃላትን የአብያተ ክርስቲያናት ኅብረት መግለጫ ውስጥ አላየሁም፡፡” ይላሉ፡፡ “ʻመግለጫው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም፤ ዲሞክራሲያዊና ሰብኣዊ መብቶችን የጣሰ ነውʼ የሚለው በጣም የተለጠጠና የተጋነነ ነው፡፡ የቱ ጋ ሰብኣዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን እንደ ተቃረነ፣ የቱ ጋ የሰው ልጆችን መብት እንደ ተጻረረና የመመለስና የንስሓ ዕድል እንደ ነፈገ በግልጽ አያስረዳም፡፡ ሲጠቀልልም፣ ʻበጽኑ ይቃወማልʼ ነው የሚለው ይሄ ትክክለኛ አካሄድ አይመስለኝም፡፡” ይላሉ፡፡

በተለይ፣ “በገጽ 3፣ 4ኛ አንቀጽ ላይ፡- ʻየአንድ ወገን ፍላጎት በሌሎች ላይ በመጫን በ“ወንጌላውያን አማኞች ወይም ፕሮቴስታንቱ” ማኅብረ ሰብ መካከል ግጭት ለመቀስቀስና ሰላምን ለማናጋት ስውር ፍላጎት ባላቸው አካላት የተቀነባበረና ሌሎችንም ለማሳተፍ ጥረት የተደረገበት የሚመስልʼ ይላል፡፡ ይሄ በወንጀል ሁሉ የሚያስጠይቅ ነገር ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ማናቸው? ማነው ይህን ለማድረግ የሚሠራው? ይሄ መልስ ሊሰጥበት የሚገባው ነው፡፡ አብያተ ክርስቲያናት ይህንን መግለጫ ያወጣው ግጭትን ለመቀስቀስና ሰላምን ለማናጋት ነው ብሎ መናገር ትልቅ ድፍረት ነው፤ ከዚያም ሲያልፍ በሕግ የሚያስጠይቅ ነው፡፡” ይላሉ የሕግ ባለሙያው አቶ ጂማ፡፡

ዶ/ር ዓለም ባዘዘው በሙያቸው መካኒካል መሃንዲስ ቢሆኑም፣ በተለያዩ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉና ይህን አማኝ ማኅበረ ሰብ በቅርበት ያውቃሉ የሚባሉ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ያወጣው የአቋም መግለጫ፣ “አቋም የሌላቸውንና የእምነት ብዥታ ውስጥ የገቡትን ወንጌላውያን አማኞችን በመጣ ንፋስ ከመወሰድ የመጠበቅ” ፋይዳ እንዳለው ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ፣ “ራሱን ʻየኢትዮጵያ ቪዥነሪ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረትʼ ብሎ ያስተዋወቀው” ቡድን የሰጠው ምላሽ፣ “የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት መሪዎች ያወጡትን መግለጫ የሚቃወምና በምድራችን እየተንሰራፋ ያለውን የስሕተት ትምህርት የሚደግፍ” እንደ ሆነ አድርገው እንደተመለከቱት ተናግረዋል፡፡ “መግለጫውን ሳነብበው ʻቪዥነሪʼ ከምለው ʻኮንፍዩዥናልʼ ብለው የሚቀል መስሎኛል፡፡” የሚሉት ዶ/ር ዓለም፣ “የቆመለትን ዐላማ በቅጡ የማያስረዳ፣ ʻየተጻራሪነትʼ መንፈስ የተንጸባረቀበት፣ አባቶቻችን ʻምን ያለበት ምንን አይችልምʼ ብለው እንደተረቱት ራሱንና ባዶነቱን የገለጠ መግለጫ ነው፡፡” ሲሉ ይወቅሳሉ፡፡ እንዲህ ያለውም መግለጫ አማኝ ማኅበረ ሰቡ ያለበትን ደረጃና እየተፈጠረበት ላለው ብዥታ ጉልሕ ማሳያ አድርገው ይወስዱታል፡፡
መግለጫዎቹን ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያም ሆነ በመደበኛው የብዙኀን መገናኛዎች ጎራ የለዩ ሙግቶች መቅረባቸው እንደ ቀጠለ ነው፤ በቅርቡ ማቆሚያ የሚያገኙም አይመስልም፡፡ በኢትዮጵያ፣ “የፕሮቴስታንት ክርስትና እምነት ተከታይ” ተብሎ በወል የሚጠራው ማኅበረ ሰብ፣ ወደማይመለስበት አዲስ አቅጣጫ እየተጓጓ ይሆን?

Mikyas Belay

ሚክያስ በላይ የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር መሥራችና ዳይሬክተር ሲሆን፣ የሕንጸት ሚዲያ ዋና አዘጋጅ ነው። በኢቫንጄሊካል ቲዎሎጂካል ኮሌጅ በሥነ መለከት ጥናት የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአፍሪካ ጥናት የማስተርስ ዲግሪ ሠርቷል።

Share this article:

የመጽሐፍ ቅኝት:- “መጽሐፍ ቅዱስና የትርጓሜ ስልቱ”

ይህ ጽሑፍ፣ “መጽሐፍ ቅዱስና የትርጓሜ ስልቱ” በተሰኘው የምኒልክ አስፋው መጽሐፍ ላይ ዳሰሳ የሚያድረግ ነው። ዳሰሳውን የሚያቀርበው ነቢዩ ዓለሙ (ዶ/ር) ሲሆን፣ ምኒልክ በሥነ አፈታት ምንነትና ፋይዳ ላይ ፈር ቀዳጅ የሆነ ሥራ ማበርከቱን ያወሳል።

ተጨማሪ ያንብቡ

መልካም ጅምሩ እንዳይደናቀፍ

የሥነ መለኮት ጥናት በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያን አጭር ዕድሜ ያለው ነው፡፡ የዕድሜው ዕጥረት ከወንጌላውያን ክርስትና አጀማመር ጋር የራሱ ቁርኝት አለው፡፡ የአብያተ ክርስቲያናቱ የቆይታ ዘመን በአንጻራዊነት ከታየ አጭር የሚባል ነውና፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በርካታ ቤተ ክርስቲያናት፣ አጋር ቤተ ክርስቲያናትና ግለ ሰቦች የመጽሐፍ ቅዱስ ት/ቤቶችን መክፈት ጀምረዋል፡፡ በመሠረቱ ይህን መሰሉ ጥረት ሊበረታታ ይገባል እንላለን፡፡ ይሁን እንጂ ጥረቱን ማበረታታት እንዳለ ሆኖ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በዋናነት ከትምህርት ጥራት ጋር የተገናኙ ናቸው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.